እግዚአብሔር ሁልጊዜ በስራ ላይ ነው፤ እርስዎስ?

ትንሽ የማይባሉ አማኞች፣ የክርስቶስን አዳኝነት በተቀበሉ ሰአት ከእግዚአብሔር ጋር የጀመሩት ጉዞ እዛው ላይ እንደሚያበቃ ያስባሉ፡፡ ይህ ከእውነታው እጅግ የራቀ ነው። እርግጥ ነው ጌታን የመቀበል ውሳኔ የዘላለም አድራሻችንን እስከወዲያኛው ይለውጣል! ይህ ውሳኔ በሕይወታችን ከወሰነው ውሳኔ ሁሉ ታላቁና ወሳኙ ነው። በዚህ ውሳኔያችን አማካኝነት እንዲያው በጸጋው ከመንፈሳዊው ዘር ተወልደናልና (1ኛ ጴጥ 1፣23፤ ሮሜ 3፣24፤ ኤፌ 2፣8)፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ ስልጣንን አግኝተናል (ዮሐ 1፣12፤ ሮሜ 8፣16)። እናም የዘላለም ሕይወት አለን (ሮሜ 6፣23፤ 1ኛ ዮሐ 5፣11)! ነገር ግን፣ በምድር በሚኖረን ቀሪ የሕይወት ዘመን እግዚአብሔር ከእያንዳንዳችን ጋር ሊያደርገው የሚወዳቸው በርካታ መንፈሳዊ ጉዳዮች አሉ፡፡

እግዚአብሔር በአስተሳሰብህ፣ በቅደመ ሁኔታዎችህ (priorities)፣ በትምህርትህ፣ በመዝናኛዎችህ፣ በፍቅር ሕይወትህ፣ በወደፊት ሕይወትህ፣ በገንዘብህ፣ በጊዜ አጠቃቀምህ፣ በእቅዶችህ፣ እንዲሁም በማናቸውም የሕይወት ጉዳዮችህ ውስጥ እጁን ማስገባትና ዋነኛ ተዋናይ መሆን ይፈልጋል (ሮሜ 12፣2)፡፡ እግዚአብሔር በሕይወትህ ጉዳዮች ሁሉ ከአንተ ጋር ‹‹አንድ›› በመሆን እርሱ የሚያፈቅራቸውንና የሚሻቸውን ነገሮች ሁሉ አንተም በሙሉ ልብህ እንድታፈቅራቸውና እንድትሻቸው ይፈልጋል፡፡ ለአንተና የአንተ የሆነውን ሁሉ ማላቅና ማሳደግ ይሻል፣ ደግሞም ፈጣሪህ እንደመሆኑ ይህንን እንዴት መከወን እንዳለበትም ጠንቅቆ ያውቃል!
ከመፀነስህ ዘመን አንስቶ፣ ኧረ እንዳውም ከዚያም በፊት፤ እግዚአብሔር ሁለት ፈረጅ ያለው አላማ ለሕይወትህ ሰንቆልሃል፡- አንደኛው፣ ለዘላለም ከእርሱ ተለይተህ እናዳትኖር አንተን ከሲኦል መታደግ ሲሆን (የዘላለም ሕይወት/ድነት መስጠት)። ሁለተኛው ደግሞ፣ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትመስል ማድረግ ነው (የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ማድረግ)።

የመጀመሪያው አላማ፣ ጌታን በተቀበልክበት ቅፅበት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ሁለተኛው አላማ ግን የሕይወት ዘመን ጉዞህን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ጉዞ በመንፈሳዊ ልደትህ ወቅት ተጀምሮ የሚቀጥል ሂደት ሲሆን ሂደቱም ኢየሱስ በሰው አካል በምድር ላይ ሲመላለስ በነበረበት ወቅት ወደ ነበረበት ፍፁምነት እስክትደርስ ወይም ከዚህ አለም በሞት ተለይተህ በሰማይ እርሱን ለመገናኘት እስከምትሄድበት ጊዜ ድረስ የሚቀጥል ነው፡፡

እስካሁን በዚህች ምድር ላይ ወደዚህ ፍፅምና የደረሰ ፍጡር የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ነገር ግን ይህ ጉዳይ ተስፋ ሊያስቆርጥህ አይገባም! በመንፈሳዊ የብስለት ጎዳና ባደግህ መጠን፣ እግዚአብሔር ለአንተ ያሰበውን ‹‹የተትረፈረፈ›› ሕይወት ለመለማመድ ትችላለህ (ዮሐንስ 10፣10)፡፡ በመንፈስ በጎለመስክ ቁጥር፣ መገኘቱን፣ የባርኮት እጆቹን፣ በውሳኔዎችህ ውስጥ ደግሞ የእርሱን ምሪት ይበልጥ እየተለማመድክ ትሄዳለህ፡፡ ለእርሱ ያለህ ጠቀሜታ ባደገ ቁጥር ደግሞ፣ ደስታህና የመኖር አላማህ ጥልቅ እየሆነ ይመጣል፡፡ መኖርህንም ትወደዋልህ። መልካሙን ለማድረግና ክፉውንም ለመጸየፍ ያለህ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ለእርሱና ለሌሎች ያለህ ፍቅር ንጹህ እየሆነም ይሄዳል፡፡ በሕይወትህ ለነገሮች የምትሰጠው የቅደም ተከተል ተርታዎች ከእርሱ ቅደም ተከተሎች አንጻር የሰመሩና ግቡብ ይሆናሉ፡፡ ስለ እግዚአብሔር መንግስት እውነታ ያለህ ምልከታ ይጠራል፡፡ የእግዚአብሔር የእድገት መለኪያ እንደሆነው እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ማየት፣ ማድረግና ለነገሮች ምላሽ መስጠት ትጀምራለህ፡፡

ይህንን ለውጥ እውን ለማድረግ እግዚአብሔር በሉአላዊነቱ የሚወስደው ሃላፊነት እንዳለ ሆኖ፣ ቀሪው ድርሻ ግን ያንተው የራስህ ይሆናል፡፡ ድርሻህን ለመወጣት የምትንቀሳቀስበት የልብ ዝንባሌ፣ በመንፈሳዊ ጉዞህ ብስለት፣ ፍጥነት፣ ጥልቀት እና ውጤት ላይ ጠንካራ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ አዎንታዊ የልብ ዝንባሌ ሲኖርህ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለህ ሕብረት እየጠበቀ ይመጣል፣ እድገትህም አስተማማኝ ይሆናል፡፡ ዝንባሌህ አሉታዊ ሲሆን ደግሞ እድገትህ ይገታል፡፡ ይህ አይነቱ የልብ ዝንባሌ ምንኛ እግዚአብሔርን ያሳዝን ይሆን? እርሱ ሊሰጠህ፣ ሊያደርግልህ እና ከአንተ ጋር ሕብረት ሊያደርግ የሚሻባቸው በርካታ ነገሮች አሉ! እነዚህን  ነገሮች ወደጎን በመተው በአንተ ሕይወት ላይ ያለውን ድርሻ ብትቃወም፣ አያስገድድህም፡፡ ወደ እርሱ ሃሳብ በመምጣት ልብህን ከፍተህ በፍቅርና በመታዘዝ ምላሽ እስክትሰጠው ድረስ በሕይወትህ ደጃፍ ላይ ሆኖ ደጅህን በማንኳኳት በትዕግስት ይጠብቅሃል እንጂ (ዮሐንስ ራዕይ 3፣20)።

2 thoughts on “እግዚአብሔር ሁልጊዜ በስራ ላይ ነው፤ እርስዎስ?”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading