በዘፍጥረት 6፡1-4 ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጆች” እና “የሰዎች ሴቶች ልጆች” የተባሉት እነማን ነበሩ?

ዘፍጥረት 6፡1-4 ስለ የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች እና ስለ ሰዎች ሴቶች ልጆች ጋብቻ (ፍትወት) መፈጸፍ ያወራል፡፡ የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የተባሉት እነማን እንደሆኑ እና ከሰው ሴቶች የወለዷቸው ልጆቻቸው ለምን ግዙፍ (ኔፊሊም የሚለው ቃል የሚያመለክተው ግዙፍ የሚለውን ቃል እንደሆነ ይታመናል) ሊሆኑ እንደቻሉ ለማብራራት በርካታ መላምቶች ይቀርባሉ፡፡ 

“የእግዚአብሔር ልጆች” ማንነትን በተመለከተ በቀዳሚነት የሚደመጡት ሦስቱ ዋና ዋና ዕይታዎች የሚከተሉት ናቸው፡- 1ኛ) የወደቁ መላእክቶች ናቸው፤ 2ኛ) ኃያል ሰብዓዊ ገዢዎች ናቸው፤ ወይም 3ኛ) ከክፉው የቃየል ዘሮች ጋር የተጋቡት መልካሞቹ የሴት ዘሮች ናቸው፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ “የእግዚአብሔር ልጆች” የሚለው ሐረግ ሁል ጊዜ መላእክትን (ኢዮብ 1፡6፣ 2፡1፣ 38፡7) የሚያመለክት መሆኑ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ሰፍሮ ለሚገኘው ዕይታ የበለጠ ክብደት እንድንሰጥ ያደርገናል፡፡ ሆኖም ግን፣ በማቴዎስ ምዕራፍ 22፡30 ውስጥ ሰፍሮ የምናገኘው፣ “መላእክት አያገቡም” የሚለው ሃሳብ ከዚህ ዕይታ አንጻር በተቃራኒ የቆመ ይመስላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መላእክት ጾታ ወይም የመራባት ችሎታ አላቸው ብለን እንድናምን የሚያደርገን ግልጽ ፍንጭ አይሰጠንም። በዚህም መሠረ፣ የተቀሩት ሁለቱ ዕይታዎች ይህንን ፈተና ያልፋሉ ማለት ነው፡፡

በ2ኛ እና 3ኛ ላይ የሰፈሩት ዕይታዎች ድክመት፣ ከተራ ሰዎች ፍትወት የተገኙ ልጆች እንዴት “ግዙፍ” ወይም “በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን” ሊሆኑ እንደቻሉ በቂ ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው ነው፡፡ በተጨማሪም፣ ሃያላኑ ወንዶች ወይም የሴት ዘሮች ተራ የሰው ልጅ ሴቶችን ወይም የቃየን ዘሮችን ማግባታቸው ሃጢአት እንደሆነ በግልጽ ባልተደነገገበት ሁኔታ እንዴት እግዚአብሔር የጥፋት ውኃ ፍርድን (ዘፍ 6፡5-7) በሰው ልጆች ላይ እንዳመጣ የሚያስረዱበት በቂ መከራከሪያ የላቸውም፡፡ የዘፍጥረት 6፡5-7 ፍርድ፣ በዘፍጥረት 6፡1-4 ውስጥ ከተከናወነው ጉዳይ ጋር መዛመዱን ልብ ይሉዋል፡፡ በምድር ላይ እንዲህ ዓይነቱን አስከፊ ፍርድ ሊያመጣ የሚችለው የወደቁ መላእክት ከሰው ሴት ልጆች ጋር ያደረጉት አስጸያፊ ጋብቻ ብቻ ይመስላል፡፡

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የመጀመሪው እይታ ድክመት፣ ማቴዎስ 22፡30 እንደሚገልፀው “ከትንሣኤ በኋላ ሰዎች እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም።” የሚለው ሃሳብ ነው፡፡ ሆኑም ግን ክፍሉ፣ “መላእክት እንደማያገቡ” እንጂ “ማግባት እንደማይችሉ” አይናገርም። በተጨማሪም፣ ማቴዎስ 22:30 የሚያወራው “በሰማይ ስላሉ ቅዱሳን መላእክት” እንጂ ስለ እግዚአብሔር የፍጠረት ሕግ ደንታቢስ ስለሆኑትና ይህንን ስርአት ዘወትር ስለሚቃወሙት የወደቁ መላእክት አይደለም። የእግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት አያገቡም ወይም ጾታዊ ግንኙነት አይፈጽሙም ማለት ሰይጣን እና አጋንንቱም እንደዛው ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል፡፡

ከዚህ በመነሳት 1ኛው ዕይታ ከተቀሩት የተሻለ ይመስላል። መላእክቶች ጾታ አልባ መሆናቸው እውን ሆኖ ሳለ “የእግዚአብሔር ወንዶች” ከሰው ሴት ልጆች ጋር በፍትወት ተጣምረው መውለዳቸውን ገራሚ “ተቃርኖ” እንደሚያደረገው እሙን ነው፡፡ ሆኖም፣ መላእክት መንፈሳዊ አካላት ቢሆኑም (ዕብ. 1፡14)፣ በሰው አካላዊ ሁኔታ ሊገለጡ እንደሚችሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ማርቆስ 16፡5)፡፡ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ከሎጥ ጋር ከነበሩት ሁለቱ መላእክት ጋር ፍትወት ለመፈፀም እንደፈለጉ ተጠቅሷል (ዘፍጥረት 19፡1-5)፡፡ መላእክት፣ የሰው ልጅ አካልን ከመምሰል አልፈው የሰውን ጾታዊነት መላበስና ብሎም ከሰው ጋር መራባት የሚያስችላቸው ብቃት ሊኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ፣ “እና ታዲያ የወደቁት መላእክት ለምን በዚህ ዘመንም ይህንን አጸያፊ ጋብቻ ከሰው ልጆች ጋር አያደርጉም?” የሚል ይሆናል፡፡ በይሁዳ 6 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ይህንን ክፉ ኃጢአት የሠሩትን የወደቁ መላእክት ያሰራቸው ይመስላል፡፡ የቀደሙት የዕብራይስጥ ተርጓሚዎች እና የአዋልድ መጻሕፍት ሁሉ በዘፍጥረት 6፡1-4 ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጆች” ተብለው የተጠቀሱት የወደቁ መላእክት ስለመሆናቸው በአንድነት ይስማማሉ፡፡ ሆኑም ይህ ክርክሩን ለማሸነፍ እንደዋና ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ዘፍጥረት 6፡1-4 ስለ ወደቁ መላእክት እና የሰው ልጅ ሴት ልጆች ጋብቻ የሚያወራ ስለመሆኑ ጠንካራ ዐውደ-ጽሑፋዊ ፣ ሰዋሰዋዊ እና ታሪካዊ መሠረት ያለ ይመስላል።

https://www.gotquestions.org ድረ-ገጽ ላይ የተተረጎመ፤ ትርጉም አዳነው ዲሮ፡፡

1 thought on “በዘፍጥረት 6፡1-4 ውስጥ “የእግዚአብሔር ልጆች” እና “የሰዎች ሴቶች ልጆች” የተባሉት እነማን ነበሩ?”

  1. ዘፍ6:1- የእግዚአብሔር ልጆች የሚለውን ከላይ ለማብራራት የተሞከረው መላእክት እንደሆኑ ነው ይህ አመለካከት ግን ብዙም አያስኬድም በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው ህዝቡን እንደሆነ እየታወቀ እንዴት መላዕክትን ሊሆን ይችላል ?መጽሐፈ ኢዮብ ላይ የተጠቀሰው ልጅነት ፈጽሞ ስለ መላዕክት አይደለም።በዕብ1:4–5 ላይ ከመላዕክትስ አንተ ልጄ ነህ ያለው ከቶ ለማን ነውይላል።ኢዮ2:1ከእለታት አንድ ቀን የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ ይላል።እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄና ዝርዝር ትንታኔ አለው ኢዮ38:-6-7 የለውም ከኤፌ1:-4 አንጻር የሚተነተን ነው ግን ብዙ መጻፍ ስለማልችል በድምጽ ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ ቢኖር ጥሩ ነበር ለማንኛውም የቃየን ወገንና የሴም ወገን መጋባታቸውን እንጂ የመላዕክትና የሰውጋብቻን አያወራም ።

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading