፩. በኦሪት ዘዳግም፣ በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል በሲና ተራራ ተደርጎ የነበረው የቃል ኪዳን ስምምነት እንደገና ተደገመና ሕጋዊ ሆነ። እንደምታስታውሰው በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ራሱን በገለጠበትና የሲና ተራራ ቃል ኪዳን በሰጠበት ጊዜ የነበሩ በዕድሜ ከ20 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በምድረ በዳ አልቀዋል። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ያወጣበትና በዓይናቸው ያዩትን የግል ምስክርነት መስጠት የሚችሉ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ ሦስት ሰዎች ብቻ ነበሩ። እነርሱም ሙሴ፥ ኢያሱና ካሌብ ነበሩ። አሁን የእነርሱን ስፍራ ለመረከብ አዲስ ትውልድ ተነሥቷል። እነዚህ በሲና ተራራ ቃል ኪዳን ለመስማት በቦታው አልነበሩም! ስለዚህ ወደ ከነዓን ከመግባታቸው በፊት ሙሴ የቃል ኪዳኑን ስምምነት ደገመላቸውና እግዚአብሔር በሲና ተራራ በሰጠው የቃል ኪዳን ስምምነት (ቅድመ ሁኔታዎች) ላይ ተመሥርተ አስፋፋው።
የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) እያንዳንዱ ትውልድ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ማንነት በሙሉ ሊረዳና ከግል ሕይወቱም ጋር ሊያዛምድ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው ክርስቲያኖች ስለሆኑ ብቻ እነርሱም ክርስቲያኖች እንደሆኑ የሚያስቡት ለምንድን ነው? ይህ አስተሳሰብ ስሕተተ የሆነው ለምንድን ነው? መ) እያንዳንዱ አዲስ ትውልድ ወንጌልን በሙላት እንዲረዳና እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነት እንዲኖረው ለመርዳት ቤተ ክርስቲያንህ ምን ማድረግ ትችላለች?
፪. ሙሴ አሪት ዘዳግምን የጻፈው፥ የእስራኤል አዲስ ትውልድና የሚቀጥለው ትውልድ ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ቅድመ-ሁኔታ እንዲያሟላ ከልብ ለማደፋፈር ነው፤ ነገር ግን ሳይታሰብ በቃል ኪዳኑ ላይ ውስጣዊ ያልሆነ መታዘዝ እንዲደረግ አልወደደም ነበር። ሙሴ በቃል ኪዳኑ መሠረት ላይ ሁለት ዋና ዋና ትእዛዛት እንደነበሩ አስተውሎ ነበር። የመጀመሪያው፥ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ የመውደድ፥ የማክበርና የመታዘዝ ነገር መኖሩ ነው (ዘዳግ. 6፡4-9፤ 10፡12-13)። ሁለተኛ ደገሞ፥ ባልንጀራን የማክበር፥ ተገቢውን ስፍራ የመስጠትና የመውደድ ትእዛዝ መሆኑ ነው፥(ዘሌ. 19፡18)። እስራኤላውያንና ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ እንደ መሆናቸው መጠን ተገቢውን ዝምድናን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው የሆነ የመታዘዝ፣ እርስ በርስ የመፈቃቀድ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግ።10፡12-13 በቃልህ አጥና። እግዚአብሔርን መፍራት፥ በመንገዱ መራመድና በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ እርሱን መውደድ ማለት ምን ማለት ነው?
የውይይት ጥያቄ፥ ባልንጀሮቻችንን በምንወድበት ጊዜ ከትእዛዛቱ አብዛኛውን የምንጠብቀው እንዴት ነው?
፫. ከዚህ ቀደም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያደረገው የቃል ኪዳን መሠረት እግዚአብሔር በሁለት ጽላቶች ላይ ጽፎ ለሙሴ የሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት እንደነበር ተመልክተናል። አሁንም ደግሞ በኦሪት ዘዳግም እነዚህን አሥር ትእዛዛት ከአይሁዶች አጠቃላይ ሕይወት ጋር ያላቸውን ዝምድና በግልጥ በሚያሳይ መንገድ አስፋፍቶ ያቀርባቸዋል። አንዳንዱ ምሁራን ሙሴ ይህንን መጽሐፍ ያዘጋጀው በአሥርቱ ትእዛዛት ዙሪያ ነው ይላሉ። በዚህ መሠረት ኦሪት ዘዳግምን የሚያብራሩት እንደሚከተለው ነው፡
- 1ኛ ትእዛዝ፡- ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ።
ሙሴ ይህንን ትእዛዝ ከኦሪት ዘዳግም 6-11 ባለው ክፍል ውስጥ አብራርቶታል። የእነዚህ ምዕራፎች ትኩረት እግዚአብሔር ፈጣሪ በመሆኑና እስራኤልን ከሌሎች አሕዛብ ለይቶ በመምረጡ ባለው መለኮታዊ ሥልጣን ላይ ነው፤ ስለዚህ እስራኤል ሌሎች አማልክትን ሳይሆን እግዚአብሔርን ልታከብርና እርሱን ብቻ ልታመልክ ይገባት ነበር። ትኩረቱ እግዚአብሔርን በመውደድና በመታዘዝ ላይ ነው። የእስራኤላውያን ተቀዳሚ ምርጫ እግዚአብሔርን ማምለክ ሲሆን እርሱ በሕይወታቸው ሁሉ ላይ የመጨረሻ ባለሥልጣን መሆን ነበረበት።
የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) እግዚአብሔር ከእያንዳንችን ስለሚፈልገው ነገር ከላይ የምናየው የመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ምንን ያመልክተናል? ለ) ይህ በሕይወትህ የታየው እንዴት ነው?
- 2ኛ ትእዛዝ፡- የተቀረፀ ምስል ለአንተ አታድርግ (ዘዳ. 12)።
ይህንን ትእዛዝ በጥሩ ሁኔታ ለመረዳት አማልክቶቻቸውን የሚወክሉ በርካታ የተቀረፀ ምስል ካሉአቸው ከከነዓናውያን ጋር በማነጻጸር ማየት የተሻለ ነው። እስራኤላውያን የከነዓናውያንን ልምድ ከመከተል ይልቅ ከፍተኛ ክብር እንዳለው በማወቅ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ነበረባቸው። እውነተኛውን የእግዚአብሔር ባሕርይ በማወቅ እርሱን ሊያከብሩ ይገባ ነበር። እግዚአብሔር መንፈስ ሰለሆነ በሥዕል ወይም በተቀረፀ ምስል ሊሳል አይገባውም፡፡ የዘለዓለማዊዉን አምላካዊ ታላቅነትን ስለማያንጸባር፥ እግዚአብሐርን ግኡዝ በሆነ መንገድ ለመግለጥ መሞከር እርሱን መስደብ ነው። እንደ ከነዓናውያን አማልክት ከእርሱ የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት በጥቃቅን መሥዋዕት የሚሸነገል አይደለም። የአምላኪውን ሰው የግል ፍላጎት ለማርካት የሚጠቅም ሊሆንም አይችልም። ይልቁንም እርሱ ሉዓላዊና ሁሉን የሚችል አምላክ ነው።
የውይይት ጥያቄ፣ ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር አንድን ነገር ለመስጠት ወይም አንድ ነገር እንደሚያደርጉለት ቃል በመግባት ወዘተ. ከእርሱ አንድ ነገር ለማግኘት የመሸንገል ሙከራ የሚያደርጉት እንዴት ነው? ) አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በፍቅር ከማገልገል ይልቅ፣ የግል ጥቅምን ከመፈለግ አንጻር ብቻ የሚያገለግሉት እንዴት ነው? ሐ) አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርn በፍቅር ከማገልገል ይልቅ የበለጠ እርሱ ስለሰጠህ ነገር ብቻ የምታገለግለው እንዴት እንደነበር ምሳሌ ስጥ። መ) ይህ ለሕተት የሆነው ለምንድን ነው?
- 3ኛ ትእዛዝ፡- የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ (ዘዳ. 13፡1-14፡21)።
ይህ ክፍል የሚገልጸው እግዚአብሔርን በሕይወታቸው ሙሉ በተለይ ደግሞ በከንፈሮቻቸው የማክበርና ራሳቸውን አሳልፈው ስለ መስጠት አስፈላጊነት ነው። እስራኤላውያን ስለ እነዚህ ነገሮች እርግጠኞች ለመሆን፡- ሀ) ለእግዚአብሔር ያላቸውን አምልኮ ንጽሕናን መጠበቅ፥ ለ) ኃጢአትን እንደመጥላታቸው፣ በመካከላቸው በሚከሰትበት ጊዜ መፍረድ፥ እንዲሁም ሐ) ንጽሕናቸውን ሊያጓድል የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ በማስወገድ የተቀደሰ ሕይወት መምራት ነበረባቸው።
- 4ኛ ትእዛዝ፡- የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ (ዘጻ. 14፡22-16፡17)።
ይህ ክፍል በእግዚአብሔር ማንነት ምክንያት ለእርሱ በሚገባው ክብር ላይ የሚያተኮር ነው። የእግዚአብሔርን የመፍጠር ሥራ የሚያስታውስ ስለሆነ እግዚአብሔር በሰንበት ቀን ሊመለክ ይገባዋል (ዘዳግ. 20፡11)። በተጨማሪ እርሱ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት እንዴት ነጻ እንዳወጣ ያሳስበናል (ዘዳግ. 5፡15)። እግዚአብሔር የመልካም ነገሮች ሁሉና የእስራኤላውያን ነጻነት ምንጭ ስለሆነ፥ ለእርሱና የእርሱም ቤተሰብ ለሆኑት ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ነገር በመስጠት ሊያከብሩት ይገባ ነበር።
- 5ኛ ትእዛዝ፡- አባትና እናትህን አክብር (ዘዳግ. 16፡18-18፡22)።
እንደምታስታውሰው፥ከ1-4 ያሉት ትእዛዛት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት የሚናገሩ ሲሆን፥ ከ5-10 ያሉት ደግሞ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ስላለው ኅብረት የሚናገሩ ናቸው። እግዚአብሔር ግድ የሚለው አንድ ዓይነት የሥልጣን ተዋረድ ስለሚከተለው ከወላጆቻችን ጋር ስላለን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፥ በተለያየ ሥልጣን ላይ ስላሉት ሁሉ ነው። በብሉይ ኪዳን ዋና ዋና የሆኑ አራት ዓይነት መሪዎች ነበሩ። ነቢያት የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የማድረስ ኃላፊነት ነበረባቸው። ካህናት የተጻፈውን የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች የማስተማር ኃላፊነት ነበረባቸው። ነገሥታት በእግዚአብሔር ትእዛዛት ላይ የተመሠረተ የጽድቅ መንግሥት የማዋቀር ኃላፊነት የነበረባቸው ሲሆን፥ መሳፍንት ደግሞ እግዚአብሔርና ነገሥታት ለመሠረቱት የአኗናር ስልት ሕዝቡ መታዘዛቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ነበረባቸው። እነዚህ ሁሉ መሪዎች መሠረታዊ ዓላማና ክብር ሊሰጣቸው የሚያስፈልበት ምክንያት፥ ከወላጆች ጭምር ሕዝቡ በሙሉ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲማሩና ለእግዚአብሔር እየታዘዙ በመኖር እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ለማደፋፈር ነበር።
- 6ኛ-8ኛ ትእዛዛት፡፡
6ኛ-8ኛ ትእዛዛት የሚያተኩሩት በሦስት የሕይወት ክፍሎች ላይ ነው፡- ሀ) ሰውን በመግደል ለ) በማመንዘርና ሐ) በመስረቅ። እነዚህ በ 19-24፡7ድረስ ተብራርተው ቀርበዋል።
ሀ) የእያንዳንዱ ግለሰብ ሕይወት በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ስለሆነ መከበርና ከአደጋ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ የአንድን ሰው ሕይወት በግድየለሽነት ማጥፋት ስሕተት ነው። በወንጀሉ ምክንያት መንግሥት በአንድ ሰው ላይ ሞት ቢፈርድ ወይም ጦርነት በማስነሣቱ ምክንያት ቢገደል የተከለከለ አይደለም።
ለ) ጋብቻ ሕይወትን በአንድነት የመካፈል መሠረት ስለሆነ፥ እስራኤላውያን የጋብቻን ቅድስና በጋብቻ ውስጥ በታማኝነት በመኖር መጠበቅ ይኖርባቸው ነበር። ነገር ግን ይህ አሳብ እርስ በርስ መጎዳዳትን፥ ሰላምን አንድነትን የሚያበላሹ ነገሮች ሁሉ መፈጸም የለባቸውም በሚለው አሳብ ተጠቃሎ እናየዋለን።
ሐ) ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ክብር ያላቸው ፍጥረቶች እንደመሆናቸው መጠን፣ የሰውን ክብር ወይም ዋጋ የሚነካ ማንኛውም ነገር መፈጸም የለበትም። ይህም መስረቅ ማለት ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ በባርነት መልክ ሰውን የመሰል ፍጡር ነጻነቱን መግፈፍ ተገቢ አይደለም።
- 9ኛ ትእዛዝ፡- በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር (ዘዳግ. 24፡8-16)።
መዋሸት ወይም በሐሰት መመስከር በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ላለው ግንኙነት ሁሉ መሠረት መሆን ያለበትን ነገር ማጥፋት ወይም ማበላሸት ነው። በእውነተኛነት ላይ የሚመሠረተውን መተማመን ያጠፋል። በሰዎች መካከል ያለውን እውነተኛነትና መተማመን የሚያጠፋ ነገር ሁሉ እንዳይደረግ ተከልክሏል።
- 10ኛ ትእዛዝ፡- አትመኝ (ዘዳግ. 24፡17-26፡15)።
መመኘት ማለት የሌላውን ሰው ንብረት የራስ ለማድረግ መፈለግ ማለት ነው። መመኘት የብዙ ኃጢአቶች መንስዔ ነው። የሌላውን ሰው መብት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወደ መጠቀም ይመራል። የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት እስራኤላውያን ግን እንደ እግዚአብሔር ሕዝብነታቸው፥ በኅብረታቸው ውስጥ ቅን ፍርድን በመፈለግ፥ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሠራተኞቻቸው፥ እንዲሁም ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ነበረባቸው።
የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔርን በሚያከብር መንገድ ከሌሎች ጋር ግንኙነት ስለ ማድረግ፥ ከእነዚህ አራት የመጨረሻ ነጥቦች ምን መማር እንችላለን?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)