የፔንታቱክ ክለሣ

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) አምስቱን የፔንታቱክ መጻሕፍት ዘርዝር። ለ) በየመጻሕፍቱ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ገጸ ባሕርያት ዘርዝር። ሐ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ዋና ዓላማ ወይም ትምህርት ዘርዝር፡፡ መ) በእያንዳንዱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በአጭሩ ጻፉ።

የመጀመሪያዎቹ አምስቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ፔንታቱክ በመባል በአንድ መጽሐፍ ስም ይጠራሉ። ፔንታቱክ አምስት ንዑሳን-ክፍሎች ያሉት አንድ ትልቅ መጽሐፍ ነው። የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት የሚባለው ሲሆን፥ የሚያተኩረው በነገሮች ጅማሪ ላይ ነው። በመጀመሪያ በዓለም አጀማመር ላይ ያተኩራል። ዋናው ትኩረቱ ግን በእስራኤል ሕዝብ አጀማመር ላይ ነው፤ ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ አባቶች የሆኑትን የአብርሃም፣ የይስሐቅንና የያዕቆብን ታሪክ ይነግረናል። ቀጥሉም የእስራኤል ሕዝብ እንዴት ወደ ግብፅ ምድር እንደመጡ ለመናገር የዮሴፍን ታሪክ ይጠቀማል።

ኦሪት ዘጸአት፡- እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከነበሩበት የግብፅ ባርነት እንዴት በተአምር ነፃ እንዳወጣቸው የሚናገር ታሪክ ነው። የኦሪት ዘጸአት ዋና ትኩረት ግን እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን ወደገባበት ወደ ሲና ተራራ እንዴት እንደመራቸው ነው። ኦሪት ዘጸአት በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ስለተገባው ቃል ኪዳን ይነግረናል። በተጨማሪ እግዚአብሔር ያድርበት ዘንድና እነርሱም በዚያ ያመልኩት ዘንድ እስራኤላውያን የመገናኛውን ድንኳን እንዲሠሩ በሰጠው ትእዛዝ ላይ የተደረገ ትኩረት እንመለከታለን፡፡

ኦሪት ዘሌዋውያን፡- እግዚአብሔር በእርሱ ፊት የተቀደሱ ሕዝብ ሆነው ይኖሩ ዘንድ ለእስራኤል የሰጣቸው ሕግጋት የተመዘገበበት መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው እስራኤላውያን በሲና ተራራ ሰፍረው እያሉ ነው። ትኩረቱም እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉ አሕዛብ ተለይተው እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዴት መኖር እንደሚገባቸው በማሳየት ላይ ነው።

ኦሪት ዘኁልቁ፡- እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እስከተስፋይቱ ምድር ጫፍ ድረስ እንዴት እንደመራቸውና እነርሱ ግን ባለማመናቸው ወደ ምድሪቱ ለመግባት እንዴት እንዳልቻሉ የሚናገር መጽሐፍ ነው። በዚህም ሳቢያ ያ ትውልድ በሙሉ እስኪያልቅ ድረስ ለ 40 ዓመታት በምድረ በዳ ተንከራትተዋል። የመጽሐፉ ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ የተደረገ ዓመፅ ታሪክ ነው፤ ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በዮርዳኖስ ምሥራቃዊ አካባቢ ያለውን ስፍራ በጦርነት አሸንፈው እንደያዙም ይናገራል። እስራኤላውያን ከከነዓን ምድር ፊት ለፊት ሰፍረው ወደ ምድሪቱ ለመግባት እስከተዘጋጁ ድረስ ያለውን ታሪክ ይነግረናል። ከዚያም እግዚአብሔር ከ400 ዓመታት በፊት ለአብርሃም የገባለት ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ ወረራውና ድሉ ይከተላል።

ኦሪት ዘዳግም፡- የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት ተመዝግበው የሚገኙበት መጽሐፍ ነው። ሙሴ ለአዲሱ የእስራኤል ትውልድ እግዚአብሔር በሲና ተራራ የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ለማስታወስ ሦስት ዋና ዋና መልእክቶችን ይሰጣል። የእስራኤል ሕዝብም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል ኪዳን አደሱ። ሙሴ በተጨማሪ ለቃል ኪዳኑ አለመታዘዝ የሚያስከትለውን ውጤት በመናገር አስጠነቀቃቸው።

የኦሪት ዘዳግም መጨረሻ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የሚቀጥለው ደረጃ ወደሆነው ማለትም የከነዓንን ምድር ወደ መውረር ታሪክ ያመጣናል። ይህ ታሪክ የሚገኘው በመጽሐፈ ኢያሱ ውስጥ ሲሆን የሚቀጥለው ጥናታችን እርሱ ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፔንታቱክ ውስጥ በእምነት ምሳሌነታቸው የተጠቀሱትን ዋና ዋና ሰዎች ዘርዝር። ለ) በየትኛው መጽሐፍ እንደሚገኙና ቅደም ተከተላቸውንም ተናገር። ሐ) ከእያንዳንዳቸው ሕይወት የምናገኛቸውን መንፈሳዊ ትምህርቶች ጥቀስ። መ) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱን ምረጥና የዚያን ሰው ሕይወት የሚገልጥና ምሳሌነቱን እንዴት ልትከተለው እንደፈለግህ የሚያሳይ አንድ ገጽ ጻፍ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: