የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር መጽሐፈ ሩት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን ይመስልሃል?
መጽሐፈ ሩት ለምን እንደተጻፈና በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እንደተካተተ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ይከራከራሉ። ስለዚህ ጉዳይ ሦስት ዋና ዋና አመለካከቶች አሉ፡-
መጽሐፈ ሩት የተጻፈው የዳዊትን አያቶችና ቅድመ አያቶች በመናገር፥ እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ የዳዊትን የዘር ግንድ እንዴት እንደጠበቀ ለማሳየት ነው። አንዳንዶች የሩትና የቦዔዝ ታሪክ ዳዊት ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳየት የተጻፈ ነው ይላሉ። ኑኃሚን ከባዶነት ወደ ሙላት (1፡2)። ከከፍተኛ ራብና ችግር (1፡1-5)፥ ወደ ደኅንነትና ተስፋ (4፡13-17) እንደተመለሰች ሁሉ፥ ራስ ወዳድ ባልሆነው በዳዊት አመራር የእስራኤል ሕዝብ ከብሔራዊ አደጋ ወደ ሰላምና ብልጥግና ተመልሰዋል። በዚህ ዓይነት ዳዊት እውነተኛው የሩትና የቦዔዝ ልጅ መሆኑ ታየ። ይህ የመጽሐፉ ዓላማ ሊሆን የሚችል ነው ቢባልም ዋናው የመጽሐፉ ዓላማ ግን አይደለም።
- መጽሐፈ ሩት የተጻፈው አይሁድ አሕዛብን ወደ ይሁዲነት እምነት ለመለወጥ መሞከር እንዳለባቸው ለማስተማርና አሕዛብም እግዚአብሔርን በእውነተኛ እምነት ሊያመልኩ እንደሚችሉ ለማስተማር ነበር። ይህም ቢሆን የመጽሐፉ ዋና ዓላማ መሆን የሚያጠራጥር ነው።
- መጽሐፈ ሩት የሚያስተምረው፥ አጠቃላይ የሆነ ክሕደት ባለበት ዘንድ በእግዚአብሔር ላይ እውነተኛ እምነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማሳየት ነው። ብዙ ክፋት ባለበት ስፍራ እምነት ሊኖር ይችላል። እግዚአብሔር የእነዚህን ጥቂት ሰዎች እምነት ስለሚያከብር፥ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታም ውስጥ ጠበቃቸው። ከሦስቱ አመለካከቶች መካከል የመጽሐፈ ሩት ዋና ዓላማ ይህ ሳይሆን አይቀርም።
መጽሐፈ ሩትን ለመረዳት፥ ከመጽሐፈ መሳፍንት ቀጥሎ መምጣቱንና ዘመነ መሳፍንት ደግሞ ከፍተኛ ክፋትና የሥነ – ምግባር ብልሽት የታየበት ዘመን መሆኑን ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህ መጽሐፍ ንጉሥ ያልነበረበትን የዚህ ዘመን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳይ ነው።
መጽሐፈ ሩት፥ አብዛኛው የእግዚአብሔር ሕዝብ ከነበረበት አሳዛኝ ክሕደት ጋር በተነጻጻሪነት የቀረበ ታሪክ ነው። የመጽሐፈ ሩት ጸሐፊ በታላቅ ክፋት መካከል ጨርሶ ባልተጠበቀ ስፍራ፣ ባልታሰቡ ሰዎች ልብ ውስጥ እምነት ሊኖር እንደሚችል በብዙ ንጽጽር ያሳየናል። ጸሐፊው በርካታ የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም እውነተኛ እምነት በጥቂት ታማኝ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚያመጣውን ለውጥ ያሳያል። የሚከተሉትን ተመልከት፡
- የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆኑት አይሁድ የእግዚአብሐርን ንጉሥነት እምቢ ብለው ጣዖታትን አመለኩ። (ዘመነ መሳፍንት)
- የተናቀችው የአሕዛብ ወገን እውነተኛውን እግዚአብሔርን ለመከተል የጣዖት አምልኮን ተወች፡፡ (መጽሐፈ ሩት)
- ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በሕዝቡ ሕይወት በሚታየው ታላቅ ክፋት ላይ ነው።
- መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ እንደ ሩትና ቦዔዝ ባሉት ጥቂት ግለሰቦች እምነት ላይ ነው።
- ዘመነ መሳፍንት ትኩረቱ በወንዶችና በኃጢአተኛነታቸው ላይ ነው፡፡
- መጽሐፈ ሩት ትኩረቱ በሴቶችና በእግዚአብሔር ባላቸው እምነት ላይ ነው።
- ዘመነ መሳፍንት እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣ ያሳያል፡፡
- መጽሐፈ ሩት እግዚአብሔር፥ እምነታቸውን በእርሱ ላይ ለሚያደርጉ ሰዎች ታማኝ መሆኑን ያሳያል።
መጽሐፈ ሩት የሚመደበው «አጭር ታሪክ» ተብሎ ከሚጠራ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ነው። የታሪኩ ዓላማ ትልቅ የሃይማኖት መሠረታዊ ትምህርት ለማስተማር አይደለም፤ ነገር ግን በክፋት መካከል ሰዎች ሊኖራቸው የሚችለውን እምነትና በመታዘዝ ለሚከተሉት እግዚአብሔር ያለውን ታማኝነት ለማሳየት ነው። ታሪኩ፥ እውነተኛ እምነት ተራ በሆኑ በታማኝ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እንደሚመስል ይገልጣል።
የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 1፡18-31 አንብብ። ሀ) እነዚህ ጥቅሶች ተራ ሰዎችን በመጠቀም ውስጥ የእግዚአብሔር ዓላማ ምንድን ነው ይላሉ? ለ) እግዚአብሔር ይህንን የሚያደርገው ለምን ይመስልሃል? ሐ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ሲፈጸም የምታየው እንዴት ነው? መ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሀብታሞች ወይም በተማሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ስለማድረግ ይህ ምን ያስተምረናል? ሠ) ብዙ ጊዜ ተራ ሰዎች እውነተኛ እምነትና ታላቅ መንፈሳዊነት ለጥቂት የተማሩ ሰዎች ብቻ ነው ብለው የሚያስቡት በምን መንገድ ነው? ረ) እግዚአብሔር የተራ ሰዎችን እምነት እንደሚያከብር መጽሐፈ ሩት ምን ያስተምረናል?
የውይይት ጥያቄ፥ ሩት 1-4 አንብብ። ሀ) የአቤሜሌክ ቤተሰብ ወደ ሞዓብ የሄደው ለምን ነበር? ለ) የሩትን እምነት ከዖርፋ እምነት ጋር አወዳድር። የሩት እምነት ታላቅ የሆነው እንዴት ነው? ሐ) ሩት ለኑኃሚን ታማኝ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነበር? መ) እግዚአብሔር ሩት ለኑኃሚን ያሳየችውን ታማኝነት ያከበረውና ዋጋ የሰጠው እንዴት ነበር? ሠ) ከዚህ ታሪክ በእግዚአብሔር ላይ ሊኖረን ስለሚገባ ታማኝነትና እግዚአብሔር ለልጆቹ ስላለው ታማኝነት ልንማር የምንችለው ነገር ምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)