1ኛ ነገሥት 17-22

እጅግ የከፋ ነገር ባለበት ዘመን ሁሉ፥ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ ታማኝ ሰዎች አሉት። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ «ቅሬታዎች» የምንላቸው፥ ለሐሰት ትምህርት አንንበረከክም የሚሉ፥ ወይም ከፍተኛ ስደት ባለበት ጊዜ እምነታቸውን በጽናት ይዘው የሚቆዩ ሰዎች ናቸው።

ብዙውን ጊዜ በእዚህ የጨለማ ወቅቶች፥ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ ሰዎች ተስፋ ሊቆርጡና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን እምነታቸውን ለመተው ሊፈተኑ ይችላሉ። ለብቻ ከመቆም ይልቅ፥ የዓለምን የአኗኗር ስልት በመከተል ከብዙኃኑ ጋር መተባበር እጅግ ቀላል ነው።

ኤልያስ ብቸኛው የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር። እጅግ ክፉ በነበረው በአክዓብ ዘመን ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ነቢያት በአክዓብ ሲገደሉ፥ ኤልያስ በእምነቱ ጸንቶ ቆመ። አንድ ጊዜ ኤልያስ እጅግ ተስፋ ቆርጦ ሞቱን ሲለምን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት አጽናናው፡- «እኔም ከእስራኤል ጉልበታቸውን ለበአል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።» (1ኛ ነገሥት 19፡18)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሁሉም የተዉት በሚመስልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር መቆም አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ተስፋ መቁረጥ ቀላል የሚሆነውስ ለምንድን ነው? ሐ) ጨለማው እጅግ ድቅድቅ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታምነው የሚቆሙ ቅሬታዎች አሁንም ስላሉት በእግዚአብሔር ላይ የምንጽናናው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 17-22 አንብብ። ሀ) ኤልያስ ያደረጋቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝር። ለ) ኤልያስ የጣዖታትን ከንቱነት ያሳየው እንዴት ነው? ሐ) በእዚህ ክፍል የተጠቀሱት ሦስት ነገሥታት እነማን ናቸው? መ) ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሥዕላዊ መግለጫ ስጥ። 

ከ1ኛ ነገ. 17-2ኛ ነገ. 8 ያሉት እነዚህ ምዕራፎች፥ ከነገሥታቱ ይልቅ በኤልያስና ኤልሳዕ ላይ ያተኩራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ኤልያስና ኤልሳዕ የሚለውን ክፍል ተመልከት። ስለ ሕይወታቸው ጠቃሚ የሆኑ እውነቶችን ዘርዝር።

የ1ኛ ነገሥት የመጨረሻ ክፍል (ምዕ. 17-22) የሚያተኩረው ኤልያስ ከእስራኤል ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ነው። ኤልያስና ኤልሳዕ ያገለገሉት በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ነው። የበአል አምልኮ በእስራኤል እንዳይስፋፉ ለመከላከልና ሕዝቡን ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ ለመመለስ የተጠሩ የእግዚአብሔር ነቢያት ነበሩ።

በኤልያስና በኤልሳዕ ታሪክ ውስጥ ልናስታውሳቸው የሚገባን በርካታ እውነቶች አሉ፡-

 1. በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ነቢያት ተግባር የግድ የወደፊቱን ነገር መተንበይ አልነበረም፤ ነገር ግን ነቢዩ እግዚአብሔር በቀጥታ የሚናገረውና በእርሱም በኩል ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት ሰው ነበር። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለነቢያቱ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ይነግራቸው ነበር። ብዙ ጊዜ ግን ነቢዩ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያመጣው ለዚያን ጊዜ ነበር። 
 2. በዘመኑ የነበሩት የፖለቲካ መሪዎች (ነገሥታት) እግዚአብሔርን በሚተዉበት ጊዜ፥ የእርሱን መልእክት ለሕዝቡ ያደርሱ ዘንድ የተለዩ ሰዎችን ይመርጥ ነበር። ነቢያቱም ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ እንዳይያዙ ያስጠነቅቁ ዘንድ እግዚአብሔር ይጠቀምባቸው ነበር። 
 3. የነቢያት ዘመን ተብሎ በሚጠራው ጊዜ የተነሣ የመጀመሪያው ነቢይ ኤልያስ ነበር። ከኤልያስ ዘመን ጀምሮ፥ በሕዝቡ ላይ ስለሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ የሚያስጠነቅቅ የነቢያትን ተከታታይ አገልግሎት እናያለን። ኤልያስና ኤልሳዕ «የነቢያት ጉባኤ» በመባል የሚታወቀውን የነቢያትን የቡድን አገልግሎት መርተዋል። ይህ የነቢያት ቡድን ለብዙ ዓመታት በእስራኤል ውስጥ አገልግሏል። 

ለአይሁድ ኤልያስ የእውነተኛ ነቢያት ምሳሌ ለመሆን በቅቷል። አለባበሱና አኗኗሩን በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ የተከተሉት ነበር። በተለይ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን አድርጎአል። ብሉይ ኪዳን የሚጠናቀቀው ወደ እስራኤል በመጣ እንደ ኤልያስ ባለ ነቢይ እንደሚሆን ተነግሮ ነበር (ሚል. 4፡5)። ኢየሱስ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ ተናግሯል (ማቴ. 11፡1)። ኢየሱስ በተራራው ላይ በተለወጠ ጊዜ የሕግ መሪ ከነበረው ከሙሴና የነቢያት መሪ ከነበረው ከኤልያስ ጋር እንደተገናኘ መመልከት የሚያስደንቅ ነው። 

 1. ኤልያስና ኤልሳዕ መልእክታቸውን በጽሑፍ ያላስተላለፉ ነቢያት ናቸው። ይህንን ስንል በእስራኤል የተነበዩ ቢሆንም እንኳ፥ መልእክታቸውን ለሕዝቡ በጽሑፍ አላስቀሩም ማለታችን ነው። ከእነርሱ በኋላ የተነሡት ሆሴዕ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ ወዘተ. መልእክታቸውን በጽሑፍ ያስተላለፉ ነቢያት ናቸው። 
 2. የኤልያስና የኤልሳዕ አገልግሎት በበአል አምልኮ ላይ የቀረበ ቀጥተኛ ተቃውሞ እንደሆነ መመልከት አስፈላጊ ነው። የሚከተለውን የበአል አምልኮና የኤልያስና የኤልሳዕ አገልግሎት ንጽጽር ልብ በል፡- 

በአልና የእግዚአብሔር ነቢያት የሆኑት- ኤልያስና ኤልሳዕ 

– በአል ዝናምን የሚቆጣጠር አምላክ ተደርጎ ይታመን ነበር 

– ኤልያስ በምድሪቱ ላይ ድርቅ እንዲመጣ አዘዘ

– በአል የተትረፈረፈ ምርትን እንደሚሰጥ ተደርጎ ይታመን ነበር 

– እስራኤል ከፍተኛ ራብና ድርቅ ገጠማት ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር እርዳታ ኤልያስና ኤልሳዕ ግን እህልና ዘይት ሰጡ

– በአል መብረቅንና እሳትን እንደሚቆጣጠር ተደርጎ ይታመን ነበር

– ኤልያስ በእግዚአብሔር ስም በማዘዝ እሳትን ከሰማይ አወረደ

– በአል ሕይወትና ሞትን እንደሚቆጣጠር ተደርጎ ይታመን ነበር 

– ኤልያስና ኤልሳዕ በእግዚአብሔር ስም በሽተኛን ፈወሱ ሙታንን አስነሡ 

ኤልያስና ኤልሳዕ የሠሩአቸው ተአምራት እውነተኛ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና በአልም ኃይል የሌለው ውሸተኛ አምላክ (ጣዖት) እንደነበረ በግልጥ የሚያሳይ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች የዚህ ዓይነት ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ የማወቃቸው አስፈላጊነት ምንድን ነው? 

በ1ኛ ነገሥት 17:22 ዋናው ነቢይ ኤልያስ ነበር። ስለ ኤልያስ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. እግዚአብሔር ድርቅና ራብ እንደሚመጣ፥ የድርቁና የራቡ ዘመን እንደሚያበቃም ለመናገር የተጠቀመበት ሰው ነበር። 
 2. እግዚአብሔር በቁራዎች የመገበው ሰው ነበር። 
 3. መበለቲቱን ለመመገብና ልጄን ከሞት በማስነሣት ወደ ሕይወት ለመመለስ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር። 
 4. ለእስራኤል በሙሉ እውነተኛው አምላክ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆና የጣዖት አምልኮ አንዳችም ዋጋ የሌለው ከንቱ ነገር እንደሆነ አሳየ። በቀርሜሎስ ተራራ የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወርዳ መሥዋዕቱን እንድትበላ አደረገ። ከዚያ በኋላ 400 የበአል ነቢያትንም አስገደለ። 
 5. ኤልዛቤል የተባለችውን ሴት ፈርቶ ወደ ምድረ በዳ ሸሽና ሞትን ለመነ። እግዚአብሔርም ተገናኘውና ሠጸው። ለበአል ያልሰገዱ ሌሎች ሰዎች እንዳሉትም ነገረው። 
 6. እግዚአብሔር ኤልሳዕን የሚቀጥለው ታላቁ የእስራኤል ነቢይ አድርጎ ለመጥራት ኤልያስን ተጠቀመበት። 
 7. ኤልያስ የአክዓብን ቤት ፍጻሜና የኤልዛቤልን መሞት ተነበየ። በኤልያስ ዘመን የነበሩ ሌሎች ሁለት ነገሥታትም ተጠቅሰዋል፡-

ሀ. ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ (872-848 ዓ.ዓ.)

ከይሁዳ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ኢዮሣፍጥ ነበር። በአሳ የተጀመረውን መንፈሳዊ መነቃቃት ቀጠለ። የጣዖት አምልኮን አጠፋ። በተለይ ደግሞ አሻራ የተባለችውን የከነዓናውያንን የልምላሜ ሴት አምላክ አጠፋ። በይሁዳ ሁሉ እንዲሰማሩና ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያስተምሩ ሌዋውያንና መኳንንትን አደራጀ። በእርሱ የአመራር ዘመን በይሁዳ ምድር ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት አስነሣ። ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለሆ፥ እርሱ አከበረው። ፍልስጥኤማውያንና ዓረቦችን በበላይነት ሊቆጣጠርና ምድሪቱንም ጠንካራ ሊያደርጋት ቻለ።

የኢዮሣፍጥ ትልቁ ችግር ከእስራኤል ጋር መስማማቱና ልጁን ለአክዓብ ቤት መዳሩ ነበር። ይህ ድርጊቱ እርሱንና ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ነገር ሊጎዳ እንደሚችል አላሰበም ነበር። ከሞተ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ባለማስተዋል የተፈጸመ ድርጊት ቤተሰቡን ሊያጠፋ ደረሰ። ይህ ያለማስተዋል ተግባር በመላው ይሁዳ የጀመረውን ሃይማኖታዊ ተሐድሶ አደናቀፈው።

ኢዮሣፍጥ ከአክዓብ ጋር የነበረው የጓደኝነት ግንኙነት ሊያስገድለው ምንም ያህል አልቀረውም ነበር። ኢዮሳፍጥ የእስራኤልን ሽንፈት የተናገረውን የእግዚአብሔርን ነቢይ ሚክያስን ስላልሰማ ከአክዓብ ጎን ቆሞ በመዋጋት ላይ ሳለ ሊገደል ነበር። ነቢዩ ሚክያስ እንደተናገረው፥ አክዓብ በጦርነቱ ተገደለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ ከዓለም ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የኢዮሣፍጥ ሕይወት እንዴት ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናል ለ) ከማያምኑ ጋር ስለሚደረግ ጋብቻ አደገኛነትና ይህም በአማኝ ልጆች ላይ ስላለው ተጽዕኖ ምን ያስተምረናል?

እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ሲሰምርላቸውና እግዚአብሔር በኃይል ሲጠቀምባቸው፥ ሰይጣን ከዓለም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ሊያጠፋቸው ይሞክራል። የተከበረ ክርስቲያናዊ መሪ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ጋር ግንባር እንዲፈጥር ወይም የፖለቲካ መሪ እንዲሆን ይመረጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነትና በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ንጹሕ አቋም ከዓለም ጋር በዚህ ዓይነት ኅብረት ውስጥ ሆነው መጠበቅ የሚችሉ ጥቂት ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ናቸው። ይህ ነገር ብዙ ጊዜ የመሪውን ሕይወት ወደ ማጥፋትና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ወደማምጣት የሚያዘነብል ነው። ክርስቲያኖች በሚመሠርቱት ኅብረትና ከዓለም ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊኖሩ ይገባል። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ እርሱን የሚፈሩ መሪዎችን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸው ቢሆንም፥ እርምጃቸውንና እምነታቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊይዙ ይገባል።

ለ. የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ (853-852 ዓ.ዓ.)

እንደ አባቱ እንደ አክዓብ፥ አካዝያስም ክፉና የበአልን አምልኮ የተከተለ ሰው ነበር። ሁለት ዓመታት ብቻ ከነገሠ በኋላ ወደቀና ሞተ። የቀረው የአካዝያስ ታሪክ በ2ኛ ነገሥት ውስጥ ይገኛል።

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ክፍል ከተጠቀሱት ነገሥታትና ከኤልያስ ሕይወት ስለ መንፈሳዊ መሪነት የተጠቀሱትን አንዳንድ ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: