የመጽሐፈ አስቴር መግቢያ 

የውይይት ጥያቄ፥ ባለፉት 20 ዓመታት ስለ ተፈጸመው የኢትዮጵያ ታሪክ አስብ። መንግሥትን፥ ቤተ ክርስቲያንንና የግል ሕይወትህን በመቆጣጠር ረገድ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እንዴት አየህ? ምሳሌዎችን ስጥ።

መጽሐፈ አስቴር እግዚአብሔር በማይታይ መንገድ በሉዓላዊነቱ ሕዝቡን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች የእግዚአብሔር እጅ በሥራ ላይ ሆኖ ባያዩም እንኳ እግዚአብሔር በብዙ በማይታዩ መንገዶች ለራሳቸው ጥቅምና ለመንግሥቱ መስፋፋት በመሥራት ላይ ነው። ክርስቲያን ያልሆነ ሰው እንደ ዕድል የሚያየውን ነገር እኛ ክርስቲያኖች ዕድል እንዳይደለ እናውቃለን። ይልቁንም እግዚአብሔርን የማያምኑ ሰዎችንም ሆነ እጅግ ጥቃቅን የምንላቸውን ድርጊቶች ሁሉ ፈቃዱን ለማድረግ ይጠቀምባቸዋል።

መጽሐፈ አስቴር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልዩ መጻሕፍት ከምንላቸው አንዱ ነው። ምሁራን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ እጅግ በጣም ጥሩ ከሚባሉ ሥነ ጽሑፎች አንዱ ነው ይላሉ። ሆኖም ግን በቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ወይም በማንኛውም ጥንታዊ ጽሑፍ ተመሳሳይ የሆነ ሥነ-ጽሑፍ አለመገኘቱ በጣም ያልተለመደ ነገር ነው። መጽሐፈ አስቴር እጅግ አስደናቂ የሆነ ታሪክ ቢሆንም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለምን እንደተካተተ ምሁራን ብዙ ጊዜ በመደነቅ ይጠይቃሉ። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ የእግዚአብሔር ስምም ሆነ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ አምልኮ ወዘተ ጨርሶ አልተጠቀሰም፤ ስለዚህ መጽሐፉን ለማይረዱት ሰዎች ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ አይታያቸውም። ሌሎች ምሁራን ደግሞ መጽሐፉ ስለ ሌሉች ዓለማዊ ታሪኮች የሚጠቅሰው አንዳችም ነገር ስለሌለ የታሪኩን እውነተኛነት ይጠራጠራሉ። ስለሆነም ይህ ነገር አጭር ልብ ወለድ ወይም ሰዎችን ለማስተማር የተሰጠ ምሳሌ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን መጽሐፈ አስቴርን ከማንበብ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው ታሪኩን በእውነተኛነቱ እንደተመለከተው ነው (ለምሳሌ፣ አስቴር 10፡2)። 

የመጽሐፈ አስቴር ርእስ 

መጽሐፈ አስቴር ከዋና ዋናዎቹ ባሕርያት አንዷ በሆነችው በአስቴር ስም የተሰየመ ነው። አስቴር አባትና እናቷ የሞቱባት በኋላም የፋርስ ንግሥት የሆነችና የአይሁድን ሕዝብ ሁሉ ያዳነች ሴት ናት። ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሴቶች ስም ተሰይመዋል፤ አንደኛው መጽሐፈ ሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፈ አስቴር ነው። መጽሐፈ አስቴር ወደ ግሪክ ቋንቋ በተተረጎመበት ጊዜ ሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ያክሉበት ጀመር። እነዚህ ታሪኮች መርዶክዮስ ስላየው ሕልም፣ መርዶክዮስ ለአርጤክስስ ስለጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎችና አስቴርና መርዶክዮስ ስላደረጉዋቸው የተለያዩ ጸሎቶች የሚናገሩ ናቸው። እነዚህ ታሪኮች በካቶሊክና በኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የታከሉ ቢሆኑም፥ በመጀመሪያው መጽሐፈ አስቴር ውስጥ ያልነበሩ ታሪኮች ወይም ጥቅሶች ናቸው።

የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ 

መጽሐፈ አስቴርን ማን እንደጻፈው መጽሐፉ ራሱ የሚናገረው ነገር የለም። በአይሁድ አፈ ታሪክ መሠረት መጽሐፈ አስቴር የተጻፈው በመርዶክዮስ ነው ቢባልም ይህን በሚመለከት አንዳችም መረጃ የለንም፡፡ ሆኖም መጽሐፉን በምናጠናበት ጊዜ በግልጥ የምንረዳው ነገር ጸሐፊው አንድ አይሁዳዊ፥ የተማረና የሥነ-ጽሑፍ ችሎታ ያለው፥ የፋርስ ቤተ መንግሥትን መዛግብትና የቤተ መንግሥት ባህልንም ሊያገኝ የሚችል ሰው እንደ ነበረ ነው (አስቴር 10፡2)። እንዲሁም ጸሐፊው በአስቴርና በመርዶክዮስ መካከል የተደረጉትን ውይይቶች ያውቅ ነበር። መርዶክዮስ እነዚህን ሁሉ መመዘኛዎች ስለሚያሟላ መጽሐፉን እርሱ ጽፎት ሊሆን ይችላል። 

መጽሐፈ አስቴር የተጻፈበት ጊዜ 

ጸሐፊው ማን እንደሆነ ስለማይታወቅ፣ መቼ እንደተጻፈ አናውቅም። የምናውቀው ነገር ቢኖር ከ200 ዓ.ዓ. በፊት መጻፉን ነው። መጽሐፉ ከ400-350 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ሳይጻፍ አልቀረም። ከዚያ በኋላ የፉሪም በዓል የአይሁድ ብሔራዊ በዓል ሆነ። 

የመጽሐፉ ታሪካዊ ሥረ መሠረት 

ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፥ የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው በመጽሐፈ ዕዝራ አጋማሽ ላይ ነው። የተፈጸመውም በዕዝራ 6 ና በዕዝራ 7 መካከል ነው። እንደ መጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው በይሁዳ ሳይሆን በፋርስ ምድር ነው። እግዚአብሔር በሥራ ላይ የነበረው በይሁዳ ብቻ ሳይሆን፥ በምርኮ በነበሩ አይሁድ መካከልም ነበር።

የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ በተፈጸመበት ጊዜ ንጉሥ የነበረው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ አሕሻዊሮስ በመባል የሚታወቀው ቀዳማዊ አርጤክስስ ነበር። የዚህ ሰው አባት ታላቅ ጦረኛ የነበረውና የፋርስን መንግሥት ክልል በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ያስፋፋው ታላቁ ዳርዮስ ነበር። 

አርጤክስስ አዳዲስ ምድርን በወረራ ከመያዝ ይልቅ፥ ትኩረቱ ዋና ከተማ የነበረችውን ሱሳንና ሌሎች ዋና ዋና ከተሞችን በመሥራት ላይ ነበር። አማካሪዎቹ ግን ግዛቱን እስከ አውሮጳ ድረስ ለማስፋፋት ይችል ዘንድ ግሪክን እንዲወጋ መከሩት፤ ነገር ግን በዚህ ጦርነት አልተሳካለትም። ግሪኮች በጦርነቱ አሸነፉትና አብዛኛውን ጦሩንና የባሕር ኃይሉን ደመሰሱበት።

የዓለም ታሪክ ስለ አርጤክስስ የሚናገረው በርካታ ነገር ቢኖርም አስቴርን ግን የሚጠቅስ ታሪክ የለም። አስጢን የምትባል አንዲት ሚስት እንደ ነበረችውና በኋላም እርሷን በማስወገድ አስቴርን በንግሥትነት እንዳገባ የሚናገር ታሪክም የለም። የዓለም ታሪክ የሚናገረው አሚስቲሪስ ስለተባለች አንዲት ንግሥት ብቻ ነው። ይህ ስም የአስጢን ወይም የአስቴር ሌላ ስም እንደሆነም የምናውቀው ነገር የለም።

የአስቴር ታሪክ የተፈጸመው ንጉሡ አርጤክስስ ከግሪኮች ጋር ለመዋጋት ወደ ጦር ሜዳ ከመሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ምሁራን የግብዣው ዓላማ በግሪክ ላይ ስለሚደረገው ወረራ ለመነጋገር ነበር ብለው ያስባሉ። አስጢን እንደተወገደች አስቴር ወዲያውኑ ንግሥት ያልሆነችበት ምክንያትም ይህ ሊሆን ይችላል። አስጢን የተወገደችው አርጤክስስ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ሲሆን፥ አስቴር ንግሥት የሆነችው ደግሞ በ7ኛው ዓመት ነው። በመካከሉ የ4 ዓመታት ልዩነት አለ ማለት ነው። ይህም ማለት የመጽሐፈ አስቴር ታሪክ የተፈጸመው ከ483-471 ዓ.ዓ. ነበር ማለት ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የመጽሐፈ አስቴር መግቢያ ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: