የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች እና አስተዋጽኦ

የመጽሐፈ አስቴር ዓላማዎች

 1. መጽሐፈ አስቴር የእግዚአብሔርን ታላቅነትና በዓለም ሕዝብ ሁሉ ላይ ያለውን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለአይሁድ ለማስተማር የተጻፈ ታሪክ ነው። ጸሐፊው አይሁድን ለማስተማር የፈለገው ነገር፥ ሕዝቡ የሚኖሩት በተስፋይቱ ምድር ሳይሆን በምርኮ ምድር ቢሆንም እንኳ፥ እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ አሁንም ቢሆን ታማኝ መሆኑን ነው፤ ነገር ግን ይህንን እውነት ለማስተማር ጸሐፊው የተጠቀመው የመጽሐፍ ቅዱስን የተለመደ መንገድ አይደለም። በብሉይ ኪዳን ውስጥ በአጠቃላይ ግልጽ ተአምራትን በማድረግ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያስተማራቸውን እውነቶች እናያለን። እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን የተሻገሩበትንና ፈረዖን ከነሠራዊቱ የሰጠመበትን፥ ሕዝቅያስ ባደረገው ጦርነት እግዚአብሔር 180000 የአሦር ወታደሮችን የደመሰሰበትን ታሪክ እናነባለን። በመጽሐፈ አስቴር ውስጥ ግን የእግዚአብሔርን የበላይ ተቆጣጣሪነት ለማመልከት ጸሓፊው ልዩ የሆነ የአጻጻፍ ስልት ሲጠቀም እናያለን። ጸሐፊው ሆን ብሎ የእግዚአብሔርን ስም አልጠቀሰም። ይልቁንም እግዚአብሔር የአይሁድን ሕዝብ ከጥፋት ለማዳን በጣም ጥቃቅንና ኢምንት ናቸው የሚባሉ ድርጊቶችን እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው በተደጋጋሚ ትኩረት ሰጥቶት እናያለን።

ለምሳሌ፡- አስቴር ንግሥት ሆና ለመመረጥና ሕዝቧን ከጥፋት ለማዳን ቻለች። መርዶክዮስ እንደአጋጣሚ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ ለመስማትና ንጉሡን ለማስጠንቀቅ ከሚችልበት ሁኔታ ላይ ደረሰ። ንጉሡ አንድ ለሊት እንቅልፍ ርቆት ስለ መርዶክዮስ እንዲያነብብና የሚያሸልመው ድርጊት እንዲጋለጥ ሆኖ መርዶክዮስ ተሸለመ። አንድ የማያምን ሰው ይህንን ተመልክቶ አይሁድ ከጥፋት ለመዳን ዕድለኞች ሆኑ ቢልም፥ እንደ ጸሐፊው አስተሳሰብ ዕድል የሚባል ነገር የለም። ይልቁንም እግዚአብሔር ጥቃቅን ድርጊቶችን እንኳ በመቆጣጠር ለሕዝቡ ያለውን ዕቅድ ለመፈጸም ይጠቀምበታል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች የሆኑት በዕድል ነው ብለው የሚያስቧቸውን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙት በዕድል እንደሆነ የሚያስቡ ክርስቲያኖች አሉን? አብራራ። ሐ) ለዓለም ዕድል ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚመለከቱአቸው እንዴት ነው?

ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር አሠራር በማያምኑ ሰዎች ወይም በሥጋዊ ክርስቲያኖች ዘንድ የማይታዩና ለመረዳት የሚያስቸግሩ ቢሆኑም እንኳ በክርስቲያኖች ዘንድ ግን ግንዛቤ ውስጥ የሚገቡ ናቸው። ለእኛ በሚያደርገው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔርን እጅ በመሥራት ላይ መሆኑን ማየት መቻል አለብን። የብሉይ ኪዳን ተአምራት በማይፈጸሙበት ጊዜና አይሁድ በዓለም ሁሉ ተሠራጭተው በፋርስ መንግሥት ቁጥጥር ሥር በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር የጥንቱን ዓይነት ተአምራት ባይሠራም አይሁዳውያንን ግን አሁንም እንደደገፋቸው ነበር። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማድረግ ሕዝቡን ይጠብቅ ነበር (ለምሳሌ፡- ዘካ. 1፡2)። እግዚአብሔር የክፉዎችን ዕቅድ ፍሬ ቢስ ለማድረግ ይሠራ ነበር (መዝ. (140)፤ መጽሐፈ ምሳሌ 10፡24-25 አንብብ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአሁኑ ዘመን ክርስቲያኖችስ ይህንን እውነት መረዳት ያለባቸው ለምንድን ነው? 

 1. አይሁድ ፉሪም የሚባል ዓመታዊ በዓል ነበራቸው። ይህ ቀን ለአይሁድ እጅግ ከተወደዱ በዓላት አንዱ ሆነ። መጽሐፈ አስቴርን በማንበብ፥ በመብላትና በመጠጣት፥ ደግሞም ስጦታን በመለዋወጥ ያከብሩታል። የመጽሐፈ አስቴር ጸሐፊ ለአይሁድ የፉሪምን በዓል አጀማመር ለመግለጥ ፈልጓል። 
 2. እኛ በቀላሉ የምንገነዘበው ባይሆንም፥ ጸሐፊው በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል ስለሚደረገው የማያቋርጥ ጦርነት መናገሩ እንደሆነ አይሁድ ይገነዘቡት ነበር። ከብሉይ ኪዳን ታሪክ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ የመጀመሪያዎቹ ጠላቶቻቸው አማሌቃውያን ነበሩ (ዘጸ. 17፡8-16 ተመልከት)፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸው አይሁድን አዘዘ፤ (ዘዳ. 25፡17-19)። አይሁድ ግን ይህንን በማድረግ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዙ፥ በብሉይ ኪዳን ታሪክ በአጠቃላይ በአማሌቃውያንና በአይሁድ መካከል የተደረገውን የማያቋርጥ ጦርነት እንመለከታለን (ለምሳሌ. 1ኛ ሳሙ. 15፤ 1ኛ ዜና 4፡43)። በእስራኤላውያን አእምሮ አማሌቃውያን እነርሱንና እግዚአብሔርን ለሚቃወሙ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ሁሉ ተምሳሌት ናቸው። ሐማ ከአማሌቃውያን ወገን እንደመጣ ተገልጦአል (መጽሐፈ አስቴር 3፡1-6፤ 9፡5-10)። የሐማ ዕቅድ እንደ ከሸፈና እርሱም እንደተደመሰሰ በማሳየት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ሁሉ አንድ ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚጠፉ ጸሐፊው አስተምሮአል። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትምህርት ዛሬ እኛን የሚያበረታታን እንዴት ነው?

የመጽሐፈ አስቴር አስተዋጽኦ

 1. አስጢን ከንግሥትነትዋ ተሻረች (1) 
 2. አስቴር ንግሥት ሆነች (2፡1-18) 
 3. መርዶክዮስ በንጉሡ ላይ የተደረገውን ሴራ አጋለጠ (2፡19-23) 
 4. ሐማ አይሁድን ለማጥፋት ያወጣው ዕቅድ (3) 
 5. መርዶክዮስ የአይሁድን ሕዝብ እንድትረዳ አስቴርን አሳመናት (4) 
 6. የአስቴር የመጀመሪያ ግብዣ (5፡1-8)  
 7. መርዶክዮስ ተሸለመ (5፡9-6፡14)
 8. የአስቴር ሁለተኛ ግብዣና የሐማ መሰቀል (7) 
 9. የአይሁድ ሕዝብ ሕይወት መትረፍና የመርዶክዮስ መሾም (8-10) 

5ኛ ጥያቄ፥ ስለ አስቴር ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ፤ አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችንም ዘርዝር። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: