መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት ያደረገው ለምን ይመስልሃል? ለ) የመጽሐፉን አተረጓጐም በሚመለከት ምን ሰምተሃል?

መጽሐፈ መክብብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመረዳት እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት መጻሕፍት አንዱ ነው። አስቸጋሪ ከሆኑት ውስጥ ሌላው ደግም መኃልየ መኃልይ ነው፤ ታዲያ ለምንድን ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተቱት? መኃልየ መኃልይ ላይ ላዩን ቢያዩት አስቸጋሪ አይመስለኝም። በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ስላለ ግንኙነት የቀረበ የፍቅር ግጥም ነው፤ ዳሩ ግን ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተካተተ? በመጽሐፉ ውስጥ ስለ እግዚአብሔር የተጠቀሰ ነገር የለም ማለት ይቻላል። መጽሐፉ ሊያስተምረን የሚሞክረው ነገር ምንድን ነው?

እነዚህ ጥያቄዎች በምሁራን መካከል ብዙ ክርክር አስነሥተዋል። ሰዎች ይህን መጽሐፍ በአጠቃላይ በታሪክ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች ተረድተውታል። መጽሐፉ የተተረጐመባቸው በርካታ የተለያዩ መንገዶች ቢኖሩም፥ በዘመናት ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የላቀ ስፍራ ከተሰጣቸው መጻሕፍት አንዱ ሆኖ ቆይቷል። አብዛኛዎቹ የጥንት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ አዘጋጆች ስለዚህ መጽሐፍ ታላላቅ ትርጓሜዎችን ጽፈዋል። ባለንበት ዘመን ግን ይህን መጽሐፍ የምንረዳበትን ሁኔታ በሚመለከት ጥያቄዎች ተነሥተዋል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተረሱትና ጥቂት ክርስቲያኖች ከሚያነቡት ወይም ከሚሰብኩት መጻሕፍት አንዱ ሆኗል። 

የመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ስያሜ 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በግዕዝ መኃልየ መኃልይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንድን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ጠይቅ። ለ) ለዚህ ስያሜ አቻ የሚሆን የአማርኛ ቃል ምንድን ነው?

በታሪክ ውስጥ ሁሉ ይህ መጽሐፍ የተለያዩ ስሞች ነበሩት። አንዳንድ ጊዜ «የሰሎሞን መዝሙራት» እየተባለ ይጠራል። ይህ የሚያንጸባርቀው መዝሙሩን የጻፈው ሰሎሞን እንደሆነ ሰዎች ያምኑ እንደነበር ወይም ስለ ሰሎሞን የተጻፈ መጽሐፍ እንደነበር ነው። አይሁድ ይህን መጽሐፍ «ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር» ብለው ይጠሩታል። ይህ ርእስ የተገኘው ከመኃልየ መኃልይ 1 ቁጥር 1 «ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር» ከሚለው ቃል ነው። በዕብራይስጥ «የመዝሙሮች መዝሙር» ማለት «ከሁሉ የላቀ ታላቅ መዝሙር» ማለት ሲሆን፥ ይህ የሚያሳየው በጥንት ጊዜ መዝሙሩ ምን ያህል ተወዳጅ እንደነበረ ነው። ይህ የዕብራይስጡ ርእስ፣ ጸሐፊው ሰሎሞን መሆኑን ወይም መዝሙሩ ለሰሎሞን የተበረከተ ይሁን ወይም መዝሙሩ የተጻፈው ስለ ሰሎሞን መሆኑን ግልጽ አያደርግም። 

የመኃልየ መኃልይ ጸሐፊ 

የዚህ መጽሐፍ ዋና ገጸ-ባሕርይ ሰሎሞን እንደሆነ የሚያጠራጥር አይደለም፤ ነገር ግን ይህ ማለት ሰሎሞን የዚህ ግጥም ጸሐፊ ነው ማለት አይደለም። ይህ መዝሙር ስለተጻፈበት ሁኔታ ሦስት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡- 

1. ሰሎሞን ያፈቀራትን ሴት አግኝቶ ስላገባበት ሁኔታ የጻፈው ግጥም ነው።

2. ሰሎሞን ከሚስቶቹ አንዷን ስላገባበት ሁኔታ አንድ ሌላ እስራኤላዊ የጻፈው ግጥም ነው።

3. ከሰሜን እስራኤል የሆነ አንድ ያልታወቀ እስራኤላዊ፥ በተከፋፈለው መንግሥት ዘመን መጀመሪያ ገደማ፥ ሰሎሞን ወደ ውድቀት የመሩትን ሴቶች እንዴት ባለማስተዋል እንደተከተላቸው ለማሳየት የጻፈው ግጥም ነው። 

ታሪካዊ ሥረ-መሠረት 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 4፡20-28፤ 10፡14-11፡4 አንብብ። ሀ) ሰሎሞን ከሴቶች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስል ነበር? ለ) ሰሉሞንን በኃጢአት እንዲወድቅ ያደረገው ምን ነበር?

በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ውስጥ በርካታ ታሪካዊ መረጃ ባይኖርም፥ ታሪኩ የሚያንጸባርቀው ከ971-931 ዓ.ዓ. በእስራኤል ላይ ነግሦ ስለነበረው ስለ ሰሎሞን እንደሆነ በቂ ማብራሪያ ይሰጣል። ሰሎሞን በዓለም ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ የላቀ ጥበበኛ ሰው የነበረ ቢሆንም የራሱ የሆነ ትልቅ ድክመት ነበረው። ልቡ በቀላሉ በሴቶች ይነሆልል ነበር። 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች እንደነበሩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። አብዛኛዎቹ ሴቶች ባዕዳን አማልክትን ያመልኩ የነበሩ የአሕዛብ ወገን የነበሩ ናቸው። እነዚህ ሴቶች የሰሎሞንን ልብ ወደ ጣዖት አምልኮ አሸፈቱት። እንዲሁም በርሱ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ አመጡበት፤ የእስራኤል መንግሥትም እንዲከፈል አደረጉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: