የትንቢት መጻሕፍት አጠቃላይ ገጽታ

በብሉይ ኪዳን ጥናታችን እስካሁን ሦስት ዋና ክፍሎችን ተመልክተናል። በመጀመሪያ፥ ፔንታቱክ በመባል የሚታወቁትን አምስቱን የመጀመሪያ መጻሕፍት ተመልክተናል። እነዚህ አምስት መጻሕፍት በይበልጥ ስለተመረጠው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጅማሬ ማለትም ስለ አይሁድ የሚናገሩ ናቸው። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር በሲና ተራራ ስላደረገው ቃል ኪዳን ይናገራሉ። ይህ ቃል ኪዳን የቀሩትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሁሉ ለመረዳት መሠረት የሚጥል ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፥ የእስራኤል ሕዝብ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወስደው ከቆዩ በኋላ እስከተመለሱበት፥ እስከ ነህምያ ዘመን ድረስ ያለውን፥ ታሪካቸውን የሚናገሩትን አሥራ ሁለት መጻሕፍት ተመልክተናል፡፡ እነዚህ የታሪክ መጻሕፍት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ከእስራኤላውያን ጋር የገባውን ቃል ኪዳን በታዘዙበትና ባልታዘዙበት ወቅት ስላጋጠሙዋቸው ነገሮች የሚናገሩ ናቸው። ከእነዚህ የታሪክ መጻሕፍት በግልጽ እንደምንመለከተው፥ እስራኤላውያን በሲና ተራራ በተሰጣቸው ቃል ኪዳን ውስጥ የተዘረዘረው ፍርድ የደረሰባቸው በተቀበሉት ቃል ኪዳን መሠረት ለመኖር ባለመቻላቸው ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ የተመለከትነው፥ አምስቱን የግጥምና የቅኔ ወይም የጥበብ መጻሕፍት ነው። እነዚህ መጻሕፍት አምልኮ እንዴት መከናወን እንዳለበትና እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን በማክበር እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምሩናል።

የውይይት ጥያቄ፥ አሥራ ሰባቱን የትንቢት መጻሕፍት ዘርዝር። በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ክፍፍል ውስጥ፥ የመጨረሻውና እጅግ ሰፊ የሆነው ከኢሳይያስ እስከ ሚልክያስ ያለው አሥራ ሰባቱን የትንቢት መጻሕፍት የያዘው ክፍል ነው።

እነዚህን የትንቢት መጻሕፍት ለመከፋፈል ሦስት የተለያዩ መንገዶች አሉ፡-

1. በመጀመሪያ፥ እነዚህን መጻሕፍት በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ልንከፍላቸው እንችላለን። የመጀመሪያው ክፍል ታላላቅ ነቢያት በመባል ይታወቃል። ይህ ክፍል ከኢሳይያስ እስከ ዳንኤል ያሉትን የመጀመሪያዎቹን አምስት የትንቢት መጻሕፍት የያዘ ነው። ሰቆቃወ ኤርምያስ በዚህ ክፍል ውስጥ የተመደበው ከትንቢተ ኤርምያስ ጋር በቅርብ የተያያዘ ስለሆነ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉት ከቀሩት የነቢያት መጻሕፍት ይልቅ የበለጠ ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆኑ ሳይሆን፥ ረጃጅምና መልእክታቸው ከሌሉቹ መጻሕፍት የበለጠ በዝርዝር የቀረበ በመሆኑ ብቻ ነው።

ሁለተኛው ክፍል ታናናሽ ወይም የአሥራ ሁለቱ ነቢያት መጻሕፍት በመባል ይታወቃል። እነዚህም ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ የሚገኙትን አሥራ ሁለት የነቢያት መጻሕፍት የሚያጠቃልሉ ናቸው። 

2. በሁለተኛ ደረጃ፥ እነዚህን የነቢያት መጻሕፍት ነቢያቱ ባገለገሉባቸው ሦስት ዐበይት የታሪክ ወቅቶች ልንከፋፍላቸው እንችላለን። 

ሀ. የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ከተከፈለ በኋላና ከምርኮ በፊት ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ ነቢያት ቅድመ-ምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። አብዛኛዎቹ ነቢያት በሚከተለው ክፍል የሚመደቡ ናቸው፡- ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሰቆቃወ ኤርምያስ፥ ሆሴዕ፥ አሞጽ፥ ሚክያስ፥ ኢዩኤል፥ አብድዩ፥ ዮናስ፥ ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ።

ለ. እስራኤላውያን በምርኮ ምድር በነበሩበት ጊዜ ያገለገሉ ነቢያት፡ እነዚህ ነቢያት የምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። በዚህ ወቅት ያገለገሉት ሁለት ነቢያት ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው። 

ሐ. እስራኤላውያን 70 ዓመታት በባቢሎን ምርኮ ቆይተው ከተመለሱ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ ነቢያት ድኅረ ምርኮ ነቢያት በመባል ይታወቃሉ። በዚህ ወቅት ያገለገሉት የመጨረሻዎቹ ሦስት ነቢያት ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ናቸው። 

3. አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ነቢያት በተለያዩ ክፍሎች የሚመደቡበት ምስተኛው መንገድ ነቢያቱ ባገለገሉባቸው ወይም ትንቢት በተናገሩባቸው አገሮች ነው። 

ሀ. ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት፡- እነዚህ እስራኤልን ያገለገሉ ነቢያት ሆሴዕና አሞጽ ነበሩ። 

ለ. ለደቡቡ የይሁዳ መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት፡- አብዛኛዎቹ የቅደመ-ምርኮ ነቢያት የሚመደቡት በዚህ ክፍል ነው። እነዚህም ኢሳይያስ፥ ኤርምያስ ከሰቆቃወ ኤርምያስ ጋር፥ ኢዩኤል፥ ሚክያስ ዕንባቆምና ሶፎንያስ ናቸው። 

ሐ. ለአሕዛብ መንግሥታት ያገለገሉ ነቢያት፡- ዮናስና ነህምያ በአሦር፥ አብድዩ ደግሞ በኤዶም ላይ ትንቢት ተናግረዋል። እነዚህ ነቢያት አይሁድ ሲሆኑ፥ መልእክታቸው ግን በይበልጥ ያተኮረው በአሕዛብ ላይ ነበር። 

መ. በምርኮ ለነበሩ አይሁድ ያገለገሉ ነቢያት:- እነዚህ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ነበሩ። 

ሠ. ከምርኮ ለተመለሱ አይሁድ ያገለገሉ ነቢያት፡- የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ነቢያት ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ ከባቢሎን ተመልሰው በይሁዳ ምድር ከተቀመጡ አይሁድ ጋር የሠሩ ናቸው። 

ሁለተኛ፣ ከነቢያት አብዛኛዎቹ ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ መሆኑ፡፡ ዮናስ፣ አሞጽና ሆሴዕ በሰሜን እስራኤል ያገለገሉት ኢሳይያስና ሚኪያስ በይሁዳ ሳልገሉበት ዘመን ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ኤርምያስ፣ ዕንባቆምና ምናልባትም አብድዩ በይሁዳ ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ ነበር።

ሦስተኛ፣ እነዚህ ጊዜያት ግምታዊ ስለሆኑ አንዳንድ ማብራሪያዎች የተለዩ ጊዜያት ሊሰጡ ይችላሉ። የአንዳንድ የትንቢት መጻሕፍትን በሚመለከት የተጻፉበትን ጊዜ ለመወሰን የምናገኛቸው ታሪካዊ መረጃዎች በጣም አነስተኛ ናቸው። ምሁራን፣ በተለይ ከነቢያት መካከል ሁለቱ ኢዩኤልና አብድዩ ስላገለገሉባቸው ጊዜያት ይከራከራሉ። ስለዚህ ነው በነዚህ ጊዜያት ላይ የጥያቄ ምልክት የተደረገባቸው። 

ዳንኤልና ሕዝቅኤል ያገለገሉት በተመሳሳይ ጊዜ ሲሆን፥ ሐጌና ዘካርያስ ደግሞ በተመሳሳይ ጊዜ አገለገሉ። ዳንኤልና ሕዝቅኤል አገልግሎታቸውን የጀመሩት በይሁዳ ነገሥታት በነበሩበት ጊዜ ቢሆንም፥ እነዚህ ሁለት ነቢያት የኖሩትና ያገለገሉት በባቢሎን ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የትንቢት መጻሕፍት አጠቃላይ ገጽታ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: