የውይይት ጥያቄ፥ «ነቢይ» ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ በመመልከት ነቢይ ምን እንደሆነና ምን እንደሚሠራ የሚያመለክት አጭር መግለጫ ጻፍ።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነቢያት አሉን? ለ) ካሉ፥ የሚሠሩት ምንድን ነው? ነቢያት እንዳሉ የምናውቀውስ እንዴት ነው? ሐ) ከብሉይና ከአዲስ ኪዳን ነቢያት የሚለዩት ወይም የሚመሳሰሉት በምንድን ነው?
የትንቢት መጻሕፍት ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይተረጐማሉ። ለዚህ ዋናው ምክንያት በነቢዩ ማንነትና በሚሠራው ሥራ ረገድ የተምታታ ነገር ስላለ ነው። ስለ ነቢዩና ስለሚናገረው ትንቢት በምናስብበት ጊዜ በሁላችን አእምሮ የሚቀረጹ የተለያዩ ምስሎች አሉ። ብዙውን ጊዜ ነቢይ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር የማመልከት ችሎታ ያለው ሰው የሆነ ይመስለናል። የብሉይና የአዲስ ኪዳን ነቢያት ዋና ተግባር ይህ የሆነ ይመስለናል።
ይህም ነገር ሰዎችን ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነቢያት አሉን? የሚል ጥያቄ አሳድሮባቸዋል፤ ብዙዎችንም እንዲደነቁ አድርጓቸዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች የትንቢትን ስጦታ እንደሚሰጥ እናነባለን (1ኛ ቆሮ. 12፡28፤ ኤፌሶን 4፡11 ተመልከት)።
ይህ ስጦታ ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጡ እጅግ አስፈላጊ ስጦታዎች አንዱ ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችባቸው መሠረቶች አንዱ ክፍል ነው። በአሁኑ ዘመን ነቢይ የሚመስሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቢኖሩም፥ ነቢይ ማን እንደሆነና ምን እንደሚሠራ ስላለን ግንዛቤ ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። በተጨማሪ በዚህ ዘመን ያሉትን ነቢያት ሥልጣን በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ምንም ስሕተት ይናገሩ ከነበሩ ሰዎች ጋር እንዳናስተካክል ልንጠነቀቅ ይገባል። እንዲያውም አንዳንዶች የአዲስ ኪዳን ዘመን ነቢያት በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደነበሩ ነቢያት መለኮታዊ የመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደነበራቸው ተደርገው እንዳልታዩ ይናገራሉ።
ብዙ ጊዜ የነቢያት ሥራ ስለ ወደፊቱ ጉዳይ መናገር የሆነ ይመስለናል፤ ስለዚህ የትንቢት መጻሕፍት በምናጠናበት ጊዜ፥ ስለ ወደፊቱ የተነገረ ሰፊና ጥልቅ አሳብ እንፈልጋለን። በአመዛኙ ክርስቲያኖች የትንቢትን መጻሕፍት በሚመለከቱበት ጊዜ፥ የሚያነቡትን ነገር የኢየሱስን ምጽአት ወይም የዘመናት መጨረሻን በሚያመለክት መልኩ የሚተረጉሙባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። እነዚህን ጉዳዮች የሚያመለክቱ ትንቢቶች ቢኖሩም እንኳ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በአብዛኛው የሚናገሩት ስለ ኢየሱስ ወይም ስለ እኛ የወደፊት ሁኔታ አይደለም። አንዳንድ ምሁራን እንደሚገምቱት፥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገሩ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ከ2 በመቶ አይበልጡም። ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ስላሉት ጊዜያት የሚናገሩት ትንቢቶች ከ5 በመቶ በታች ናቸው። ከ1 በመቶ ያነሱት ደግሞ ዛሬ እኛም ብንሆን ገና ወደፊት ይፈጸማሉ የምንላቸው ናቸው።
የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ ወደፊቱ ሁኔታ አስታውቀዋል፤ ነገር ግን ይህ ብዙ ጊዜ ለእስራኤል ልጆችና በአካባቢያቸው ለነበሩት መንግሥታት የቅርብ ጊዜ አመልካች መልእክት ነበር፤ ስለዚህ ከእነዚህ የትንቢት መጻሕፍት የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ትንቢቶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበረችው እስራኤል ጋር የሚዛመዱ እንጂ ስለ እኛ ወደፊት ሁኔታ የሚናገሩ አይደሉም።
ነቢይ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ነቢይ የእግዚአብሔርን መልእክት ለሰዎች የሚያስተላልፍ ሰው ነው። አብዛኛውን ጊዜ መልእክቱ ያተኩረው በሕዝቡ ወቅታዊ ፍላጎት ላይ ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ሆነው እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን መታዘዝ እንዳለባቸው፥ ካልታዘዙ ግን ያለመታዘዛቸውን ውጤቶች የሚቀበሉ መሆናቸውን የሚያሳስቡ ነበሩ። ነቢያት ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ለቃል ኪዳኑ እንዲታዘዙ ለማድረግ የሚጥሩ የእግዚአብሔር አፈ-ቀላጤዎች ነበሩ። በቃል ኪዳኑ የተመለከተው ፍርድ እንደሚመጣባቸው የሚያስጠነቅቁ ነበሩ፤ ወይም ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ለቃል ኪዳኑ ታዛዥ ሆነው በሚኖሩበት ጊዜ ስለሚቀበሉት በረከት ይናገሩ ነበር። የነቢያት አገልግሎት ከእግዚአብሔር ርቆ የሄደው ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ማነቃቃትን አጥብቆ የሚሻ ነበር። ነቢያት ወደዚህ አገልግሎታቸው የመጡት በገዛ ፈቃዳቸው ሳይሆን፥ ጥሪውን ከእግዚአብሔር ተቀብለው ነበር (ለምሳሌ፡- ኢሳይያስ 6፤ ሕዝቅኤል 1-3)። ስለዚህ ነቢያት ብዙ ጊዜ የሚናገሩት እግዚአብሔር እንደሚናገር ሆነው የእግዚአብሔርን ድምፅ በመጠቀም ነበር። (እግዚአብሔር ራሱ እንደተናገራቸው እንጂ ነቢዩ እንዳልተናገራቸው የሚመስሉ ትንቢቶች ምን ያህሉ እንደሆኑ አስተውል።)
ነቢያት ስለ ወደፊት ሁኔታዎች የሚናገሩት አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። አብዛኛዎቹ ትንቢተቻቸው በእስራኤላውያን ላይ በቅርብ ጊዜ ስለሚሆኑ ነገሮች የሚያመለክቱ ነበሩ፤ ለምሳሌ አብዛኛዎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እስራኤል በአሦር፥ ይሁዳ ደግሞ በባቢሎን ስለ መደምሰሳቸው ወይም ደግሞ ስለ ሕዝቡ ከምርኮ መመለስ የተነገሩ ነበር። ስለ ኢየሱስ መምጣትና ስለ ዘመኑ ፍጻሜ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚናገሩ ጥቂት ትንቢቶች ነበሩ። እነዚህን በረዥም የጊዜ ሂደት ውስጥ የሚፈጸሙ ትንቢቶች በመስጠት ረገድ የእግዚአብሔርና የነቢያቱ መሠረታዊ ፍላጎት የእስራኤልን ሕዝብ ማስተማር ነበር። እግዚአብሔር በታሪክና በእነርሱ ሕይወት ውስጥ ያለውን የበላይ ተቈጣጣሪነት እንዲመለከቱ ይፈልግ ነበር። ስለሚመጣው ፍርድ ተረድተው እንዲጠነቀቁና በመጨረሻም ስለሚያገኙት በረከት በማሰብ እንዲነቃቁ ይፈልግ ነበር።
ትንቢቶች ወደፊት ስለሚሆኑ ነገሮች ዝርዝር መግለጫዎችን ይሰጣሉ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን አሁን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ስለ መኖር የሚያስተምሩን ናቸው። ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ለማወቅ ያለንን ጕጕት ለማርካት የተሰጡ አይደሉም። አንዳንድ ክርስቲያኖች በትንቢቶች አተረጓጐም ረገድ ግምታዊ አስተያየት በመስጠት፥ ኢየሱስ በዚህ ጊዜ መመለስ አለበት፤ ወይም ሐሰተኛው ክርስቶስ ይህ ወይም ያ ሰው ነው ማለታቸው ፍጹም ስሕተት ነው። ይህ ስለ ትንቢት የተዛባ ትርጕም መስጠት ነው።
እግዚአብሔር ለጥንት ነቢያት መልእክቱን ያስተላለፈው እንዴት ነበር? በአንድ የተወሰነ መንገድ ወይም ዘዴ አልተጠቀመም። ለአንዳንዶች መልእክቱን በሕልም ወይም በራእይ ተናግሯል። (ለምሳሌ፣ ለዳንኤል)። ለሌሎች ደግሞ በጥሞና በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር የተለያዩ ነገሮችን በማሳየት መልእክቱን አስተላልፏል (ለምሳሌ፣ ለሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት)። ዳሩ ግን እግዚአብሔር በአብዛኛው የተናገረበት መንገድ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት መልእክቱን በእርግጠኛነት እንዲያስተላልፉ ለነቢያቱ በቀጥታ በመናገር ነበር ( ለምሳሌ፣ 2ኛ ነገሥት 20፡4-6)።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናያቸው ያተኮሩት የወደፊቱን ሁኔታ በሚቈጣጠርና መልእክቱን ለነቢዩ በሚሰጠው በእግዚአብሔር ላይ እንጂ፥ በነቢዩ ላይ አይደለም። መልእክቱን የሚያዘጋጁት ነቢያት አልነበሩም፤ መልእክቱ የእግዚአብሔር ሲሆን፥ ነቢያት እግዚአብሔር መልእክቱን ለሕዝቡ የሚያስተላልፍባቸው መሣሪያዎች ብቻ ነበሩ። እነዚህ ነቢያት የእግዚአብሔርን አመለካከት፥ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚሰጣቸውን ምላሾች አሳቡንና ዕቅዱን ለእነርሱ በገለጠላቸው መንገድ ያቀርቡ ነበር፡፡ ስለዚህ የሚኮሩበትና የሚታበዩበት አንዳችም ምክንያት አልነበራቸውም።
የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ነቢያትን የሚመለከት ትምህርት ብዙ ሰዎች በዘመናችን ስለ ነቢያትና መልእክቶቻቸው ካላቸው አሳብ የሚለየው እንዴት ነው?
በብሉይ ኪዳን ውስጥ፥ የነቢያት ሥራ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ካደረገው ቃል ኪዳን ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነበር። አብዛኛው ትምህርታቸው (መልእክታቸው) በይዘት አዲስ አልነበረም። ይልቁንም እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ የሰጣቸውን የእርግማንና የበረከት አይቀሬነት በተለየ መንገድ አጠናክረው የሚያውጁ ነበሩ።
የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳግም 28-32 አንብብ። ሀ) በቃል ኪዳኑ ውስጥ የሚገኙት አንዳንድ በረከቶች ምን ነበሩ? ለ) ከእነዚህ አንዳንዶቹ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት እንዴት ነበር? ሐ) በቃል ኪዳኑ ውስጥ ይገኙ ከነበሩት መርገም አንዳንዶቹን ጥቀስ። መ) ከእነዚህ አንዳንዶቹ በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የተፈጸሙት እንዴት ነበር?
እነዚህ ነቢያት መልእክታቸውን የተቀበሉት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነበር። ሆኖም ከተናገሯቸው ነገሮች መካከል አብዛኛዎቹ በሙሴ ሕግ፥ በተለይም ባለመታዘዝ ስለሚመጣው መርገምና በመታዘዝ ስለሚገኝ በረከት በሚናገረው በቃል ኪዳኑ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ነበሩ። በሕግ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኘው ቃል ኪዳኑ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ በረከትን እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል። እነዚህ ሰረከቶች ሕይወት፥ ጤንነት፥ ብልጽግና፥ በእርሻ ፍሬያማ መሆን፥ የደኅንነት ዋስትናና በአሕዛብ መካከል የክብር ስፍራ ማግኘትን የሚጨምሩ ነበሩ። እስራኤል እግዚአብሔርን በታዘዘች ቍጥር ይህ ነገር ሲፈጸም እንመለከታለን (ለምሳሌ፣ የዳዊትና የሰሎሞን ዘመነ መንግሥት)። በፍርድ መልክ የተደነገጉት መርገሞች በሕዝቡ ሁሉ ላይ የሚደርሱ ነበሩ። ያለመታዘዝ ምትን፥ በሽታን፥ ድርቅን፥ አደጋን፥ ጥፋትን፥ በጠላቶች ድል መመታትን፥ በምርኮ መጋዝንና ውርደትን ያስከትል ነበር። የነቢያትን መልእክት በጥንቃቄ በምንመረምርበት ወቅት ከመልእክታቸው አብዛኛው ክፍል በእነዚህ በረከቶች ወይም መርገሞች ላይ የሚያተኩር እንደነበር ለማየት እንችላለን። የነቢያት መልእክቶች በሕግ ውስጥ የሚገኙት መርገሞች በእስራኤል ሕዝብ ላይ ሊደርሱ እንደተቃረቡ ያመለክቱ ነበር። በቃል ኪዳኑ ውስጥ የተሰጡት በረከቶች በሙላት የሚፈጸሙበትን የወደፊቱንም ጊዜ አመልክተዋል። በ586 ዓ.ዓ. የሆነው ምርኮ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ የአብዛኛዎቹ ነቢያት መልእክቶች ስለ ጥፋት የሚናገሩ ነበሩ። ከምርኮ በኋላ የነበሩት አብዛኛው የነቢያት መልእክቶች ደግሞ በወደፊት በረከቶች ላይ ያተኮሩ የማበረታቻ መልእክቶች ነበሩ።
ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ነቢያትን የሚጠራው ብሔራዊ ችግር በሚኖርበት ጊዜ ይመስላል። አንዳንድ ነቢያት ያገለገሉት የአንበጣ መቅሠፍት ከተፈጸመ በኋላ ነበር (ለምሳሌ፡- ኢዩኤል)። አብዛኛዎቹ ነቢያት ያገለግሉ የነበረው እንደ አሦርና ባቢሎን የመሳሰሉ የአሕዛብ መንግሥታት እስራኤልን ለመደምሰስ ጥቃት በፈጸሙበት ጊዜ ነበር። ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ ሕዝቡን ለማስተማር የተነሡትና ሕዝቡ በዚህ ፍርድ ሥር የወደቀው ለምን እንደሆነ ለማስገንዘብ ያገለገሉት በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ውስጥ የጨለማ ዘመን በመባል በሚታወቀውና መንግሥትዋ ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ነበር።
የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ በተለይ ከፍተኛ ችግር ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው?
በእስራኤል ሕዝብ ታሪክ በአጠቃላይ የተለያዩ ተግባራት ያሉአቸው የተለያዩ ነቢያት ነበሩ። እንዲያውም የነቢያት አገልግሉት በጊዜ ብዛት የተለወጠ ይመስላል።
1. ከነገሥታት ዘመን በፊት የነበሩ ነቢያት፡- ከሳኦልና ከዳዊት ዘመን በፊት የነበሩት አብዛኛዎቹ ነቢያት የእግዚአብሔርን መልእክት ለሕዝቡ የሚያደርሱ፥ ሕዝቡን በችግር ጊዜ የሚመሩና በእግዚአብሔር የተመረጡ መሪዎች ነበሩ። በዚህ ጊዜ ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ለተነገሩ መልእክቶች የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነበር። ይልቁንም ትኩረቱ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በመምራት ላይ ነበር። እንደ እነዚህ ያሉ ነቢያት ሙሴ (ዘዳግም 34፡10-11) እና ዲቦራ (መሳፍንት 4፡4) ነበሩ።
2. በመጀመሪያዎቹ የእስራኤል ነገሥታት ዘመን ማለት የሚጽፉ ነቢያት ከመነሣታቸው በፊት የነበሩ ነቢያት፡- በተባበረችው የእስራኤል ዘመነ መንግሥት ጊዜ ነቢያት የንጉሥ አማካሪዎች ነበሩ። ለነገሥታቱ የእግዚአብሔርን በረከት ወይም ተግሣጽ በመገለጥ የእግዚአብሔር አፍ ሆነው የሚያገለግሉ ነበሩ። አንዳንዶቹ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ በመመዝገብ ሥራ የተሳተፉ ቢሆንም የራሳቸውን የትንቢት መጽሐፍ አልጻፉም። በአመዛኙ ስለ እነዚህ ነቢያት የምናነብበው ለሕዝብ ከተናገሩት ይልቅ ያደረጉትን ነገር የሚገልጽ ነው። በዳዊት ዘመን የነበረው ነቢዩ ናታን (2ኛ ሳሙኤል 7፡2-5)፥ ኤልያስና ኤልሳዕ ለእንደነዚህ ዓይነት ነቢያት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው።
3. ለሁለት በተከፈለችው የእስራኤል መንግሥት ማብቂያ ላይ የነበሩ ነቢያት፡- በዚያን ጊዜ በርካታ የነበሩ ቢሆንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት መልእክቶቻቸውን በጻፉ 16 ነቢያት ላይ አትኩሯል። እነርሱንም በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ እናገኛቸዋለን (ከኢሳይያስ – ሚልክያስ)። እነዚህ ነቢያት አንዳንድ ጊዜ ከነገሥታት ጋር ይሠሩ ነበር። ይሁን እንጂ መልእክታቸው ብዙ ጊዜ ለእስራኤል ወይም ለይሁዳ ሕዝብ የተነገረ ነበር። መልእክታቸው ብዙ ጊዜ በኃጢአት በተበላሸ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕይወት ላይ የቀረበ ተግሣጽ፥ ለጽድቅና ለቅድስና ኑሮ የተደረገ ጥሪ፥ ሊመጣ ስላለው ምርኮ ማስጠንቀቂያና ስለ ወደፊቱ ተሐድሶ የሚናገር ነበር። ትኩረታቸው እግዚአብሔርን ወክለው ለሕዝቡ ባመጡት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስለነበር ስላደረጉት ነገር የምናነበው በጣም ጥቂት ነው።
በዚያን ዘመን ብዙ ነቢያት የነበሩ ቢሆንም፥ ልክ ዛሬ በዘመናችን እንደምናየው በርካታ ሐሰተኛ ነቢያትም ነበሩ። ብዙውን ጊዜ ሐሰተኞች ነቢያትን ከእውነተኞቹ መለየት አስቸጋሪ ነበር። ሁሉም የእግዚአብሔርን መልእክት በሕልምና የእግዚአብሔርን ድምፅ በመስማት እንደተቀበሉ ይናገሩ ነበር። ሁለቱም ወደፊት ስለሚከሠቱ ነገሮች ይናገሩ ነበር፤ ዳሩ ግን ሁሉም ከእግዚአብሔር አልነበሩም (ለምሳሌ፡- ኤርምያስ 14፡14፤ 23፡21)።
የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በብሉይ ኪዳን የነበሩ ነቢያት ተግባርና በአሁኑ ዘመን ያሉ ሰባኪዎች ሥራ የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) የሚለየውስ እንዴት ነው? ሐ) ሐሰተኛ ነቢያትን በተግባር ላይ የምናያቸው እንዴት ነው? መ) እንደ ነቢያት የሚያገለግሉ ሰዎች ዛሬ የሚያስፈልጉን በምን ዓይነት መንገድ ነው? ሠ) ለቤተ ክርስቲያንህም ሆነ ለአገራችን የሚሰጡት መልእክት ምን ዓይነት ይመስልሃል?
ነቢያት መልእክታቸውን የሚቀበሉት ከእግዚአብሔር ቢሆንም፥ በጽሑፍ በሚያሰፍሩት ጊዜ የራሳቸውን የአጻጻፍ ስልት እንዲጠቀሙ እግዚአብሔር ፈቅዶላቸዋል፤ ስለዚህ በእያንዳንዱ የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ የጸሐፊውን ችሎታና ጥበብ እንመለከታለን። አንዳንዶች እንደተማረ ሰው የሰዋስው አገባብ ጠብቀው ጽፈዋል። ሌሎቹ በሚገባ አለመማራቸውን በሚያሳይ አኳኋን ጥራት በሌለው ሰዋስው ጽፈዋል። እግዚአብሔር ግን መልእክቱን ለማስተላለፍ በሁለቱም ዓይነት ነቢያት ተጠቅሟል።
ትንቢትን ለመተርጐም አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ፣ አብዛኛው የተጻፈው በግጥም መልክ መሆኑ ነው፤ ስለዚህ መተርጐም የሚገባቸው በርካታ ተምሳሌቶችን እናገኛለን። እነዚህ ተምሳሌቶች ነቢያቱ በኖሩበት ዘመን ለነበሩ አንባብያን ግልጽ ቢሆኑም፥ ብዙ ጊዜ ለእኛ ግልጽ አይደሉም። ስለ ትንቢቶች የተለያየ ትርጕም ወደ መስጠት የሚያመራው ምክንያት ይህ ነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)