አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ ሆኖ ሊወለድ ይችላል?

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ ዳባ

በ 1996 “አድቮኬት” የተሰኘ የግብረ-ሰዶማዊያን መጽሔት፣ ግብረ-ሰዶማዊነት ሥነ-ሕይወታዊ (biological) መሠረት እንዳለው የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤት ይፋ ቢሆን የግብረ-ሰዶማዊያንን አመለካከት በማራመድ ረግድ ውጤቱ ስለሚኖረው ፋይዳ አንባቢዎቹን ጠይቆ ነበር፡፡ ከመጽሔቱ አንባቢዎች ውስጥ ወደ 61 ከመቶ የሚሆኑት እንደዚህ ያለው ሳይንሳዊ የምርምር ውጤት ይፋ ቢሆን፣ ሰዎች ለግብረ-ሰዶማውያን እና ግብረ-ሰዶማዊነት ያላቸው አመለካከት ይበልጥ አወንታዊ ይሆን ነበር ሲሉ መልሰዋል፡፡ ለአብነት፣ አንድ ሰው በዘረመል አስገዳጅነት ምክንት ቡናማ ወይም ሌላ አይነት የአይን ቀለም ይዞ ሊወለድ እንደሚችል ሁሉ በዚሁ መንገድ ግብረ ሰዶማዊ ሆኖ የሚወለድ ከሆነ፣ ፍትሃዊው ማህበረሰብ ይህን ግብረ ሰዶማዊ ግለሰብ ኢ-ተፈጥሮአዊ ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ብሎ ሊወቅሰው ባልቻለ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን፣ የግብረ ሰዶማውያን ተሟጋቾች እና የሊበራል ሚዲያዎች ግብረ-ሰዶማዊነት በተፈጥሮ የሚወረስ እና ልንለውጠው የማንችለው ሥነ-ሕይወታዊ (biological) ክስተት ነው የሚለው ሀሳብ መሬት እንዲይዝ በንቃት እየሰሩ ይገኛሉ፤ ተመራማሪዎችም ይህንን ሃሳብ የሚደግፍ ሳይንሳዊ ማስረጃ ለማግኘት በትጋት ሲፈልጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ የግብረ ሰዶማዊያኑ ተሟጋቾች ከሚፈልጉት በተቃራኒ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ምርምር ሁሉ ግብረ ሰዶማዊነት በዘረ-መል (ጅን) አማካኝነት የሚወረስ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ሳይንሳዊ ማስረጃ አልተገኘም፡፡

ክርክሩ እ.ኤ.አ. በ 1991 የሜዲካል ዶክተር በሆነው በሲሞን ሊቬይ አማካኝነት በተደረገው የምርምር ውጤት ይጀምራል፡፡ ሲሞን ሊቬይ የ 41 ሬሳዎችን አእምሮ በመመርመር በግብረ-ሰዶማውያን እና ግብረ-ሰዶማውያን ባልሆኑ ወንዶች መካከል ልዩነቶች እንዳሉ ይመለከታል፡፡ ይህ ተመራማሪ፣ የግብረ-ሥጋ ግንኙነትን ይቆጣጠራ ተብሎ የሚታመነው እና ሃይፖታለምስ (hypothalamus) የሚሰኘው የአንጎል ክፍል ግብረ ሰዶማዊ ካልሆኑት ወንዶች አንጻር በግብረ-ሰዶማውያኑ ወንዶች ላይ በመጠኑ አነስተኛ ሆኖ ያገኛል፡፡ ከዚህ በመነሳትም፣ ዶክተሩ ግብረ ሰዶማዊነት ሥነ-ሕይወታዊ (biological) መሠረት አለው ሲል ይደመድማል፡፡ ከሥነ-ሕይወታዊ ምክንያት ውጪ ይህን የአንጎል መጠን ልዩነት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶችን ለማየት ሲሞን ሊቬይ አልሞከረም፡፡ ለአብነት፣ 19 የሚሆኑት ግብረ ሰዶማዊያኑ የሞቱት የነርቭ ሥርዓትን ሊያውክ በሚችል በኤች አይ ቪ ኤድስ አማካኝነት ነበር፡፡ ምናልባትም ሃይፖታለምስ (hypothalamus) የተሰኘውን የአንጎል ክፍል በመጠን እንዲያንስ ያደረገው ይህ በሽታ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪ፣ የአንጎል ባዮኬሚስትሪ ጥናት የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች፣ አንድን ሃሳብ የምናስብበት መንገድ (አኳሃን) በአንጎላችን ትገበራ (በሚሠራበት መንገድ ላይ) ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይገነዘባሉ፤ በተለይም አስተሳሰባችን በአንጎላችን ውስጥ በሚለቀቁ የነርቭ ኬሚካሎች እና በተወሰኑ የነርቭ መንገዶች እድገትና ለውጥ ላይ ጉልህ ተጽእኖ እንዳለው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት፣ “በግብረ-ሰዶማውያኑ እና ግብረ-ሰዶማውያን ባልሆኑት ወንዶች መካከል የታየው መዋቅራዊ የአንጎል ልዩነት ከዘረ-መል ሁናቴአቸው የመነጨ ሳይሆን ካላቸው የአስተሳሰብ ልይነት የመነጨ ይሆን?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ፣ የሃይፖታላመስ መጠን እና ግብረ ሰዶማዊነት አንዱ የሌላው መንስኤ ወይም ውጤት ከመሆን አንጻር ሁለቱን የሚያገናኝ ምንም አይነት ማረጋገጫ የለም፡፡

እ.ኤ.አ. በ 1993 ዶክተር ዲን ሀመር የተሰኙ የግብረ-ሰዶማውያን አክቲቪስት በምርምራቸው፣ ግብረ-ሰዶማዊ የሚያደርግ ዘረ-መል ሊኖር ይችላል የሚል ሃሳብ አሰራጭተው ነበር፡፡ ይህ የምርምር ቡድን፣ በርካታ ግብረ ሰዶማውያን የሚገኙበት ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን በማጥናት በመካከላቸው የክሮሞዞም ልዩነት መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ እና ከኖረም ይህ ልዩነት ግብረሰዶማዊ ከሆኑት የቤተሰቡ አባላት ጋር ያለውን ዝምድና ለማወቅ ተከታታይ የሆነ የጂን ትስስር ጥናት አድርገው ነበር፡፡ ምንም እንኳን የሃመር የጥናት ናሙና በጣም ትንሽ ቢሆንም፣ በግብረሰዶማዊያኑ እና በማተርናል X ክሮሞዞሞች፣ (Xq28) መካከል ጉልህ የሆነ ትስስር ለማግኘት ችለው ነበር፡፡ በአንጻሩ፣ በርካታ ናሙናውችን በመውሰድ የተደረጉ ሌሎች ተጨማሪ ጥናቶች ግን ከዚህ ውጤት ጋር የሚጋጩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ የሃመር ምርምር ውጤት ማረጋገጫ ያልተገኘለት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ እንዳውም፣ ሌሎች የተመራማሪዎች ቡድን የሃመር ስራን በሌላ ተጨማሪ ምርምር ሊረጋገጥ የማይችል እና አልፎ ተርፎም ማጭበርበር የታየበት እንደነበር ጠቅሰዋል።

በግብረ-ሰዶማውያኑ መካከል የጋራ የሆነ ዘረ-መል ተገኝቶም ቢሆን እንኳ ያ ተዛምዶ የመንስኤ እና ውጤት ግንኙነት መኖር አለመኖሩን አያረጋግጥም፡፡ ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በፕሮፌሽናል አትሌቶች ላይ የሚደረግ የዘረ መል ምርምር በቀላል ቁጥር በማይገመቱት በእነዚህ ድንቅዬ አትሌቶች መካከል የጄኔቲክ ቅደም ተከተል ተማስሎ ሊታይ እንደሚቻል ይገመታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም፣ የአንድ ሰው ስፖርታዊ ውጤታማነቱ ከዘረመል ቅደም ተከተል የመጣ ነው የሚል ፈጣን መደምደሚያ ላይ ሊደረስ ይችላል፡፡  ሆኖም ግን፣ የሰውን የግል ምርጫ እና አካባቢያዊ ተፅእኖ የሚወስን ምንም አይነት ዘረመላዊ ምንስኤ ሊኖር አይችልም፡፡ የአትሌቲክስ ዘረመል ባህሪ ያላቸው ሰዎች በተፈጥሯቸው ወደ ሙያው ሊሳቡ ወይም በሙያው ውስጥ ለመሳተፍ ሊበረታቱ ይችላሉ፡፡ ምንም እንኳን አትሌቶች አንዳንድ የተለመዱ ባሕርያትን የሚጋሩ ቢሆንም ሙያዊ አትሌት መሆን በዘር የሚወረስ አይደለም፡፡ ግለሰቡ የሚያድግበት ባህል እና የሚያደርጋቸው ምርጫዎች የሚሄድበትን መንገድ ይወስናሉ፡፡

አካባቢያዊ ተጽእኖ ለግብረ-ሰዶማዊነት ክፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚያረጋግጡ በርካታ የጥናት ውጤቶች አሉ፡፡ ፍቅር በሌለው ወይም ድጋፍ በማይሰጥ ቤተሰብ ውስጥ አሉታዊ በሆነ አስተዳደግ ማለፍ ለግብረ ሰዶማዊነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በርካታ ተመራማሪዎች ያምናሉ። በቤቱ የሌለ አባት ወይም ቢኖርም ለልጁ ስሜት አልባ የሆነ አባት፣ ወይም ከልክ በላይ ተከላካይ ወይም አሞካሽ ወይም ጨቋኝ እናት ያለበት ቤተሰብ፣ ልጆች አሉታዊ በሆነ መንገድ የሚያድጉበት ቤተሰብ ባሕሪይ ዋና መገለጫዎች ናቸው፡፡ አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ወሲባዊ በደሎችም ከዚህ ጉዳይ ጋር በእጅጉ ተያያዥ ናቸው። የሥርዓተ-ጾታ ቀውስም ለግብረ ሰዶማዊነት አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ ሂደት የሚጀምረው ከሁለት እስከ አራት አመታት ባሉት ጊዚያት መካከል ነው፡፡ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ልጆች ከእናታቸው ጋር ካላቸውን የመጀመሪያ ግንኙነት ወጣ በማለት ተመሳሳይ ጾታ ካለው ወላጅ ጋር ጥልቅ ቁርኝት ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለወንዶች፣ የሰከነ ጾታዊ ማንነትን በማሳደግ ረገድ ዋነኛው መንገድ በእነርሱ እና በአባታቸው መካከል ያለው ግንኙነት ነው፡፡ አባትና ልጅ አብረው ጊዜ ባሳለፉ ቁጥር አባት ለልጁ ያለውን ዋጋ እና ፍላጎት በመግለጽ ለልጁ የወንድነትን ጾታዊ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ልጁም ከአባቱ አንጻር ራሱን በማየት ስለ ራሱ ወንድነት ግንዛቤ ያገኛል፡፡ በተቃራኒው፣ ከልጇ ጋር የቅርብ ግንኙነት የሌላት አበሻቃጭ እናት ወይም በአካል ከልጇ ጋር የሌለች ወይም በልጇ ደካማ ተደርጋ የምትታይ (ለአብነት በባሏ በደል የሚደርስባት) እናት የልጇን ጤናማ ሥርአተ ጾታዊ እድገት ልታስተጓጉል ትችላለች፡፡

ተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ጓደኞች ጋር ያለ ጉድኝትም በጤናማ ሥርአተ ጾታዊ እድገት ውስጥ የራሱን ሚና ይጫወታ፡፡ ከተመሳሳይ ጾታ እኩዮች ጋር ለዓመታት ከተደረገ ግንኙነት በኋላ ልጆች ወደ ጉርምስና ዕድሜ ይገቡና ለተቃራኒ ጾታ ትኩረት መስጠት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት በሚስተጓጎልበት ጊዜ ልጁ ወይም ልጅቷ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸውን ሰዎች ፍቅር እና ትኩረት መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ልጆች ከተመሳሳይ ጾታ ወላጅ ጋር ሊያደርጉት የፈለጉት ግንኙነት ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲገነዘቡ ከተቃራኒ ጾታ ወላጅ ጋር ግንኙነታቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ከዛም የተቃራኒ ጾታ ወላጃቸውን ዘይቤዎች እና ባህሪዎች መኮረጅ ይጀምራሉ፡፡ ሆኖም፣ ተመሳሳይ ጾታ ካለው ወላጅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ ፍቅር እና ማረጋገጫ ሁሌም ሊያገኙት የሚመኙት ሆኖ በውጣቸው ይቀራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያደጉ ልጆች ለተመሳሳይ ጾታ ካላቸው ጥልቅ ፍላጎት ጋር እንደተወለዱ አድርገው ራሳቸውን ያያሉ፡፡ በውጤቱም፣ ግብረ ሰዶማዊነት ወሲባዊ ፍላጎት ሳይሆን ስሜታዊ ረሃብ (emotional craving) በመሆን ማደግ ይጀምራል፡፡ ሕጋዊ የሆነው ይህ ወሲባዊ-ያልሆነ የተመሳሳይ ጾታ የፍቅር ዝንባሌ ውሎ ሲያድር በጉርምስና ዕድሜ ላይ ወሲባዊ ወደሆነ ግንኙነት ይቀየራል።

ምንም እንኳን ለአንድ ግብረሰዶም፣ ግብረ-ሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ ነው የሚለውን ሃሳብ ለመቀበል ቀላል ቢሆንም በበርካታ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች አንጻር ሃሳቡ ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ግብረ ሰዶማዊያን የዘርመል ቅድመ-ዝንባሌ (genetic predisposition) ሊኖራቸው ቢችልም ይህ እውነት የሰው ልጅ ምርጫ ለግብረ ሰዶማዊነት ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ ላይ ጥላውን ሊያጠላ አይገባም፤ ቅድመ-ዝንባሌ አስገዳጅ ሁኔታ ሊሆን አይችልምና። ከዚህ በመነሳት፣ ሥርአተ ጾታ የሚወሰነው በማሕጸን ውስጥ ሳይሆን ከማህፀን ውጭ ነው የሚለው ሃቅ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ እናገኘዋለን። በግብረ-ሰዶማዊነት አኗኗር ደስተኛ ላልሆኑ፣ ይህ እውነት የለውጥ ተስፋን ይሰጣል፡፡ በተደረገላቸው በቂ ክሊኒካው እርዳታ የተነሳ አንዳንድ ግብረ-ሰዶማውያን ከአሉታዊ አስተዳደጋቸው የተነሳ ያዳበሩትን ራስን የመከላከል ባሕሪይ መቀየር መቻላቸው ከላይ የተገለጸውን እውነት የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ 

በ 1ኛ ቆሮንቶስ 6፡9-10 ላይ በተጠቀሱት የሃጢአቶች ዝርዝር ስር ግብረ ሰዶማዊነት ከስርቆት ቀጥሎ ተቀምጧል፡፡ ለመስረቅ ምንም የዘረ መል ሰበብ እንደሌለ ሁሉ ለግብረ ሰዶማዊነትም ምንም አይነት የዘረ መል ሰበብ ሊኖር አይችልም፡፡ አካባቢ፣ ባህል እና የግል ምርጫ አንድን ሰው ሌባ እንደሚያደርጉት ሁሉ እነዚሁ ነገሮች አንድን ሰው ግብረ ሰዶማዊ ያደርጉታል፡፡

ክርስቶስ ለግብረ-ሰዶማዊው ሞቷል፡፡ ሁሉንም ኃጢአተኞች እንደሚያፈቅር ሁሉ እግዚአብሔር በማንኛውም ሥርአተ ጾታ ባሕርዪ ውስጥ ያሉትንም ያፈቅራል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳው “ገና ኃጢአተኞች ሳለን” እንደሆነ ይናገራል (ሮሜ 5፡8)። “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐ. 2፡2)። የክርስቶስ ወንጌል፣ “ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና” (ሮሜ 1፡16)። የፈውስ፣ የተሃድሶ፣ የይቅርታ እና የመፅናናት ምንጭ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ የሰማይ አባታችንን ይሁንታ፣ ድጋፍ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር የምናገኝበት ብቸኛ መንገድ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው።

1 thought on “አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ ሆኖ ሊወለድ ይችላል?”

  1. እግዚአብሔር ይባርካችሁ ታባረኩልኝ በጣም እየተማርኩ እየተባረኩበት ነው እወዳችኋለሁ❤❤❤

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading