የትንቢተ ኢሳይያስ ዓላማ

የትንቢተ ኢሳይያስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ ጥልቅ የሥነ-መለኮት ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹን የያዘ ነው። መጽሐፉ የይሁዳ ሕዝብ በባቢሎን መንግሥት የሚማረክበትን ምክንያትና የይሁዳ ሕዝብ ቅሬታ ደግሞ በመጨረሻ ከምርኮ እንደሚመለስ ቢናገርም፥ የመጽሐፉ ተቀዳሚ ትኩረት ግን ይህ አይደለም። የኢሳይያስ ትኩረት በእግዚአብሔር ባሕርይ ላይ ነው። የቀሩት ትምህርቶች በሙሉ ኢሳይያስ ስለ እግዚአብሔር የነበረው ግንዛቤ ውጤቶች ናቸው። እግዚአብሔር በይሁዳ ሕዝብ ላይ እንደሚፈርድ ኢሳይያስ የሰጠው የማስጠንቀቂያ መልእክት የተመሠረተው በእግዚአብሔር ቅድስናና በሕዝቡ መካከል በሚከሠት ኃጢአት ላይ እንደሚፈርድ አስቀድሞ በሰጠው ቃል ኪዳን ላይ ነው። ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው የሚቆዩ ቅሬታዎች እንደሚኖሩ የተሰጠው ማረጋገጫ ወይም ዋስትና ደግሞ እግዚአብሔር ለገባው የተስፋ ቃል ያለውን ታማኝነት የሚያሳይ ነው። ስለ ሕዝቦች መሸነፍ የሚናገሩት ትንቢቶች ደግሞ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን ሁሉ በበላይነት እንደሚቆጣጠርና ሉዓላዊ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ናቸው። እግዚአብሔር ብቻውን በሚነግሥበት ጊዜ የሚኖረውን ወርቃማ ዘመንና ሰላም በምድር ላይ መስፈን የሚያሳየው፥ ንጉሥነቱንና በምድር ላይ ያለውን ዓላማ በመፈጸም መንግሥቱን እንደሚመሠርት ነው። በዚህ መንግሥት ጽድቅ ይኖራል፤ ደግሞም አይሁድም ሆኑ አሕዛብ እግዚአብሔርን ያመልኩታል።

የውይይት ጥያቄ፥ በኢትዮጵያ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ይህን ዓላማ በሚገባ መረዳት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ እግዚአብሔር በነቢይ በኩል ዛሬ ለኢትዮጵያ ቢናገር ኖሮ የሚሰጠው መልእክት ምን ዓይነት የሚሆን ይመስልሃል? ለምን?

ነቢይ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ወይም ቃል አቀባይ መሆኑን ተመልክተናል። በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች እንዲያደርስ እግዚአብሔር ግልጽ የሆነ መልእክት ይሰጠው ነበር። መልእክቱ ብዙ ጊዜ የሚያመለክተው ነቢዩ የነበረበትን ዘመን ነው። ይኸውም ሊመጣ ስላለው ፍርድ ማስጠንቀቂያ ወይም ተግሣጽ የሚሆን ወይም እግዚአብሔር ምን እንደሚያደርግላቸው የሚናገር የተስፋ መልእክት ነበር። አንዳንድ ጊዜ መልእክቱ ወደፊት የሚፈጸምን ነገር ያመለክት ነበር። በዚያን ዘመን ለነበሩ እስራኤላውያን በቅርቡ የተፈጸመ ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ገና ወደፊት በዘመናት መዉረሻ የሚፈጸም ትንቢት ሊሆን ይችላል።

ኢሳይያስ ከ740-680 ዓ.ዓ. ለይሁዳ ሕዝብ የእግዚአብሔር ቃል አቀባይ ነበር። ኢሳይያስ ታላቅ ነቢይ የነበረ ቢሆንም፥ መልእክቱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለመመለስ እስከዚህም ስኬታማ አልነበረም። ትንቢተ ኢሳይያስን ለመረዳት ከምዕራፍ 6 መጀመር አለብን። ይህ ክፍል ኢሳይያስ የእግዚአብሔር ነቢይ እንዲሆን እንዴት እንደተጠራ የሚያሳይ ነው። ይህ ጥሪ በ740 ዓ.ዓ. ለኢሳይያስ ደረሰውና ሕይወቱን ለወጠው። አብዛኛዎቹ የትንቢተ ኢሳይያስ ኋለኛ መልእክቶች የሚያንጸባርቁት እርሱ በተጠራ ጊዜ ምን እንደተማረ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ኢሳይያስ 6 አንብብ። ሀ) ኢሳይያስ ያየው ራእይ ምን ነበር? በዚህ ራእይ ውስጥ የታዩት የእግዚአብሔር ዐበይት ባሕርያት ምንድን ናቸው? ለ) ኢሳይያስ ስለ ራሱና ስለ እስራኤላውያን ሕይወት ከዚህ ራእይ የተነዘበው ምንድን ነው? ሐ) የኢሳይያስ መልእክት ምን መሆን ነበረበት? መ) ለኢሳይያስ ሥራ የተሰጠው ምላሽ ምን ነበር? ሠ) በሕዝቡ ላይ ምን ሊደርስ ነበር? (ቍጥር 11-13)።

ኢሳይያስ 6 የሚያንጸባርቀው የትንቢተ ኢሳይያስን ዋና ዋና ትምህርቶችን ነው። በኢሳይያስ 6 የሚከተሉትን ዋና ዋና ትምህርቶችን መመልከት እንችላለን፡-

1. የእግዚአብሔር ታላቅነትና ቅድስና (6፡1-4)፡- እነዚህን ሁለት የእግዚአብሔር ባሕርያት በመጽሐፉ በአጠቃላይ ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ የምናያቸው ናቸው። በመጀመሪያ፥ ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ታላቅነት «በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ» አየ። በዚህ ዓይነት ትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን የሰዎች ሁሉ ንጉሥ ወይም ገዥ አድርጎ ያለማቋረጥ ያቀርበዋል። እግዚአብሔር በሰማይ በዙፋኑ ላይ ሆኖ በምድር የሚፈጸሙ ድርጊቶችንና አካሄድን ይመራል። በሕዝቦች ላይ ይገዛል፤ ድርጊቶቻቸውንም ሁሉ ይቆጣጠራል። ኃይሉና ጥበቡ እጅግ ከፍተኛና የላቀ በመሆኑ፣ ሊቋቋመው የሚችል ማንም የለም።

ሁለተኛ፡ ኢሳይያስ እግዚአብሔርን ያየው በቅዱስነቱ ነው። ሱራፌልም ያለማቋረጥ ይህንን የእግዚአብሔርን ባሕርይ ያውጁ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ «ቅዱስ» ማለት ምን ማለት ነው? ይህንን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «ቅዱስ» የሚለው ቃል መሠረታዊ ትርጕም «መለየት» ማለት ነው። «መለየት» የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሁለት ነገሮችን ነው፤ በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር ከተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ የተለየ መሆኑን ያመለክታል። እርሱ ከተፈጠሩ ነገሮች ሁሉ የተለየና የላቀ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፥ «ቅዱስ» የሚለው ቃል የሚያመለክተው፥ እግዚአብሔር ከኃጢአት የተገለለ መሆኑን ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የሚፈርደው ቅዱስ ስለሆነ ነው።

በትንቢተ ኢሳይያስ፣ ነቢዩ እግዚአብሔርን የሚጠራበት የተለየ ስም አለው። ኢሳይያስ እግዚአብሔርን «የእስራኤል ቅዱስ» ብሎ ይጠራዋል፤ ይህም ስም 26 ጊዜ በመጽሐፉ ውስጥ ተጽፎ እናየዋለን። ስለሆነም፥ በትንቢተ ኢሳይያስ ውስጥ በአጠቃላይ በግልጽ እንደምናየው፥ የመጽሐፉ ትኩረት በእግዚአብሔር ቅድስና፥ በኃጢአት ላይ በሚገልጸው ቍጣና ኃጢአተኞችን ለመቅጣት ባለው ውሳኔ ላይ ነው። ይህም የራሱን ሕዝብ እስራኤልንና ይሁዳን፥ ደግሞም አሕዛብን በመቅጣቱ ታይቷል። 

2. የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢአተኝነት (6፡5-7)፡- ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ቅድስና በተመለከተ ጊዜ ወዲያውኑ የተገነዘበው ነገር እርሱና ሕዝቡ ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደሆኑ ነበር። የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያሳይ ራእይ ሁልጊዜ የሚያስገነዝበን የራሳችን ኃጢአት ከፍተኛነት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ የእግዚአብሔርን ቅድስና ይበልጥ በተረዳን ቍጥር የራሳችንን ኃጢአተኝነት በበለጠ በመገንዘብ ያዳነንንና የወደደንን እግዚአብሔርን እንዴት አብልጠን ልናደንቀውና ልናከብረው እንደሚገባን ግለጽ። 

የትንቢተ ኢሳይያስ አብዛኛው ክፍል የሚያተኩረው በፍርድ ላይ ነው። ይህ ፍርድ እግዚአብሔርን በካዱ ሕዝቦች ሁሉ ላይ ይመጣል። ነገር ግን ይህ ፍርድ በተለይ የሚመጣው የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ በሆኑት በአይሁድ ላይ ነው። ኢሳይያስ ይህ ፍርድ የሚመጣበትን ምክንያት ይናገራል። ይህ ፍርድ የሚመጣው በእግዚአብሔር ማንነት ምክንያት ነው። እርሱ ክፉዎችን የሚቀጣ ቅዱስና ጻድቅ ስለሆነ ነው። ፍርዱ የሚመጣው የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕግጋቱን በግልጽ በመቃወማቸው፥ ለሰዎች ቅን ፍርድን በመንፈጋቸው፥ በመታበያቸው፥ ወዘተ. ነው።

የውይይት ጥያቄ.፥ እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውና ሥራዎቻቸው ሁሉ እንደሚፈረዱና ፍርድ እንደሚሰጥ (እንደሚፈተኑ) በማወቅ መኖር ያለባቸው እንዴት ነው? (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡10-15 ተመልከት)።

3. የኢሳይያስ መልእክት ተገቢውን ምላሽ ማጣቱ (6፡9-10)፡- ኢሳይያስ መልእክቱን ለማስተላለፍ ከተዘጋጀበት ከመጀመሪያው አንሥቶ ማንም እንደማይሰማው እግዚአብሔር ነግሮት ነበር። ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡና ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ኢሳይያስ ያለማቋረጥ ቢለምንም፥ ሕዝቡ ግን አልተቀበሉትም። ኃጢአታቸው የእግዚአብሔርን ድምፅ መስማት የማይሹ ልበ-ደንዳናዎች አድርጎአቸው ነበር። ዓለማዊ በሆነ ምርጫቸው ረክተው ነበርና የያዙትን ለመለወጥ አይፈልጉም ነበር። አይሁዶች ሃይማኖታውያንና እግዚአብሔርን ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ቢሆኑም፥ እግዚአብሔርን ከልባቸው የሚያመልኩ ወይም ከእነርሱ ጋር በሲና ተራራ ላደረገው ቃል ኪዳን በመታዘዝ የሚኖሩ ሰዎች አልነበሩም።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ተመሳሳይ ነገር ዛሬም ቢሆን በክርስቲያኖች የሚፈጸመው እንዴት ነው? አንዳንድ መግለጫዎችን ስጥ።

4. የእግዚአብሔር ሕዝብ በንስሐ ስለማይመለስ እግዚአብሔር በሕዝቡና በከተማዋ ላይ ጥፋትን እንደሚያመጣ ተናግሯል (6፡11-13)። በትንቢተ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚቀጣ ተናግሯል። እስራኤል በሙሉ ተማርከው ወደ አሦር ተጋዙ። ኢሳይያስ፥ ይሁዳም ተማርካ ወደ ባቢሉን እንደምትሄድ ተናገረ። በኢሳይያስ የአገልግሎት ዘመን፥ ይህ የፍርድ ተስፋ ቃል አሦራውያን አብዛኛውን የይሁዳ ክፍል በመደምሰሳቸው ምክንያት በከፊል ተፈጽሟል። ሆኖም እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ታድጎአታል። 

5. እግዚአብሔር ይሁዳን የሚያጠፋው ሙሉ በሙሉ አልነበረም፤ ነገር ግን የቀረው ጉቶ «የተቀደሰ ዘር» ይሆናል (6፡13)። ይህ ሐረግ የሚገልጸው ኢሳይያስ ስለ ይሁዳ ቅሬታ የሚያስተምረውን ነገር ነው። አብዛኛው ሕዝብ ቢጠፋ ወይም በምርኮ ቢጓዝም፥ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ለእርሱ ታማኝ ሆነው የሚቀሩ «ቅሬታዎች» ይኖሩታል። እነዚህ ቅሬታዎች አንድ ቀን ወደ ይሁዳ ይመለሳሉ። እግዚአብሔር አንድ ቀን መንፈሱን የሚያፈስሰውና መንግሥቱንም የሚያመጣው በዚህ ቅሬታ ላይ ነው። በዚህ የኢሳይያስ ራእይ የተካተተው ሌላው ዐቢይ ትምህርት እግዚአብሔር በዘመናት መጨረሻ የሚያመጣው የዘላለም መንግሥት ነው። ትንቢተ ኢሳይያስ በብሉይ ኪዳን ከሚገኙ የትንቢት መጻሕፍት ሁሉ ይልቅ እግዚአብሔር ለዘላለም ስለሚነግሥበት ዘላለማዊ መንግሥት ይገልጻል። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: