የትንቢተ ኤርምያስ ዓላማ፣ ዋና ዋና ትምሕርቶች እና ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት

የትንቢተ ኤርምያስ ዓላማ

ትንቢተ ኤርምያስ የተጻፈው ስለ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበር፤ አንደኛ፡- የይሁዳ ሕዝብ ለምን እንደተማረኩ ለመግለጽ ነበር። ይህ ክፍል እግዚአብሔር ለሕዝቡ የነበረውን የመጨረሻ መልእክት የሚነግረን ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ራሱ ለመመለስ የሞከረበት፥ ሕዝቡ በእግዚአብሔርና በሕጉ ላይ በማመፃቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ነገር በማሳየት የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ሁሉ የምናይበት ነው። ሕዝቡ የነበረበትን መንፈሳዊ ሁኔታ፥ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ አሻፈረኝ ማለታቸውንና በዚህ ምክንያት የደረሰባቸውን የምርኮ ፍርድ ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሰዎች እግዚአብሔር ለምን እንደሚቀጣቸው ማወቅ ያለባቸው ለምንድን ነው? ለ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ የሚከናወነው እንዴት ነው?

የትንቢተ ኤርምያስ ሁለተኛ ዓላማ የነቢዩ ኤርምያስን ሕይወትና ያለፈበትን ትግል ማሳየት ነበር። የኤርምያስ ሕይወት ተቀባይነት በማይገኝበት መሃከል የታማኝነት አመራር ምሳሌ ይሆን ዘንድ ቀርቧል። ኤርምያስ ሥራው ምንም ለውጥ የሚያመጣ በማይመስልበት ሁኔታ እንኳ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ የሚኖር ሰው ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔርን እንከተላለን በሚሉ ሰዎች አማካይነት ስደትና ተቃውሞ ቢገጥመውም እንኳ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ቆረጠ። ይህም ማለት ኤርምያስ አልታገለም፤ አገልግሎቱን ለማቋረጥ አልፈለገም ማለት አይደለም። ኤርምያስ እግዚአብሔርን በፍጹም ተጠራጥሮ አያውቅም ማለትም አይደለም። በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ እነዚህን ትግሎች እናያለን፤ ነገር ግን ኤርምያስ ለራሱ የሚመቸውን ነገር በመምረጥ የተጠራበትን አገልግሉት አላቋረጠም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህንን ትምህርት በሕይወታችን መማር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ለ) በኢትዮጵያ ውስጥ የኤርምያስን ዓይነት ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን በምሳሌነት ጥቀስ።

ኤርምያስ ብዙ ሚስዮናውያንና ወንጌላውያን ከሙስሊሞችና ለማመን ፈቃደኞች ካልሆኑ ሰዎች ጋር በሚሠሩበት ጊዜ ለሚገጥሟቸው ችግሮች ጥሩ ምሳሌ ነው። ብዙ ሚሲዮናውያን በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ በአንድ አካባቢ ሠርተው አንድም ሰው እንኳ ወደ ክርስቶስ ሳያመጡ አልፈዋል። እነዚህ ሰዎች አልሠመረላቸውም ማለት ነውን? ለዚህ ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ለመስጠት እንፈተን ይሆናል። እግዚአብሔር ግን እንዲሠሩ ያዘዛቸውን ነገሮች በታማኝነት እስከሠሩ ድረስ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አሉታዊ ነው። በእግዚአብሔር አመለካከት ታላቅነት ማለት በአገልግሎታችን የተዋጣልን ለመሆን መቻል ነው በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ መጠመድ የለብንም።

በትንቢተ ኤርምያስ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ትምህርቶች

1. ኤርምያስ ስለ እግዚአብሔር ብዙ ያስተምረናል። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ እንደሚቆጣጠርና እርሱ የመጨረሻው ባለሥልጣን እንደሆነ ያስተምረናል። እግዚአብሔር የሕያዋን ነገሮች ሁሉ ፈጣሪ ነው (ኤርምያስ 32፡27፤ 48:15፤ 51፡57)። እግዚአብሔር የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ማድረግ ይችላል፤ (ኤርምያስ 32፡17)። እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ነው፤ ነገር ግን ኃጢአት የሚያደርጉትን ሁሉ የሚቀጣ አምላክም ነው (ኤርምያስ 32፡18)። እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ እንደየሥራቸው ይከፍላቸዋል። የዓለምን ሕዝቦች ሁሉ የሚቆጣጠርና በላያቸው ላይ ፍርድን የሚያመጣው እግዚአብሔር ነው (ኤርምያስ 5፡15፤ 46-5)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያኖች ስለ እግዚአብሔር ታላቅነትና ባሕርይ ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያሉት አባላት በሙሉ ስለ እግዚአብሔር እውነተኛውን ነገር እንዲያውቁ ስለ ባሕርዩ ልታስተምር የምትችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር።

2. ትንቢተ ኤርምያስ እግዚአብሔር ሕዝቦቹን በሚመለከት ስላለው መመሪያ ያስተምረናል (ኤርምያስ 18፡7-11)። የትንቢተ ኤርምያስ የመጨረሻ ክፍል (46-51) በይሁዳ ላይ ጥቃት በፈጸሙ መንግሥታት ላይ ስለሚመጣ ፍርድ የሚናገር ነው። እግዚአብሔር በራሱ ሕዝብ ላይ ስላደረሱት ነገር ፈረደባቸው። አንዳንዶቹ ትንቢቶች ወዲያውኑ ሲፈጸሙ እናያለን፤ ሌሎች ደግሞ ለመፈጸም ብዙ ዓመታት ወስደዋል። አሕዛብ የሚፈረድባቸው መቼ እንደሆነ የሚወስነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ በላይ ስለሆነ ደግሞ ሕዝቦች ያንን ፍርድ ሊቋቋሙት አይችሉም። አንድ ሕዝብ ክፉ ከሆነ እግዚአብሔር ይፈርድበታል። ነገር ግን አንድ ሕዝብ መልካም ከሆነ ወይም ከክፉ ሥራው ንስሐ ከገባ፥ እግዚአብሔር ያንን ሕዝብ ያድናል። እግዚአብሔር በአሕዛብ ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ስለሆነ ስለፈጸሙት ክፉ ተግባር ይፈርድባቸዋል። ብዙ ጊዜ መንግሥታትና ሕዝቦች ክፉ እየሠሩ ያልተቀጡ ቢመስልም፥ እግዚአብሔር ግን በራሱ ጊዜ ይቀጣቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዓለማችን ላይ ጨቋኝ በሆኑ መንግሥታት ሥር ለሚኖሩ በርካታ ክርስቲያኖች ይህ ጉዳይ ማበረታቻ የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) መንግሥት ክፉና ጨካኝ በሚሆንበት ወቅት ክርስቲያኖች ምን ማድረግ አለባቸው?

3. ትንቢተ ኤርምያስ ስለ ሐሰተኞች አስተማሪዎችና ነቢያት ብዙ ነገር ይናገራል (ኤርምያስ 14፡11-16፤ 23፡9-40፤ 28፡1-17)። የኤርምያስ ቀንደኛ ጠላቶች የዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች ነበሩ። ካህናቱ ኤርምያስን ብዙ ጊዜ ይቃወሙትና ንጉሡ እንዲገድለው ይጠይቁ ነበር፤ ዳሩ ግን ከእነዚህም የሚብሰው በእግዚአብሔር ስም እናስተምራለን እያሉ ሕዝቡን ወደ ክሕደት ይመሩ የነበሩ የሐሰተኞች ነቢያት ጉዳይ ነበር። ኤርምያስ ሊመጣ ስላለው ጥፋት ለሕዝቡ በመንገር ንስሐ እንዲገቡ በሚያስተምርበት ጊዜ ሐሰተኞች ነቢያት ግን ሕዝቡ በግማሽ ልቡ በሚፈጽመው አምልኮ እንዲቀጥል በማበረታታት እግዚአብሔር ብልጽግና፣ ሰላምና በጠላቶቻቸውም ላይ ድልን እንደሚሰጣቸው እንደተናገረ አድርገው ያቀርቡ ነበር። እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት ብዙ ከመሆናቸውም መልእክታቸውም ምንም ሕዝቡን እምብዛም የማያስጨንቅና በቀላሉ ተቀባይነት የነበረው በመሆኑ፥ ኤርምያስ ራሱ እንደ ሐሰተኛ ነቢይ ተቆጥሮ ነበር፤ መልእክቱንም የሚሰማው አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በዛሬይቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሐሰተኞች ነቢያት አሉን? መልስህን አብራራ። ለ) እነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት የሚሠሩት እንዴት ነው? ሐ) መልእክታቸው በብዙ ሰዎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት የሚያገኘው ለምንድን ነው? መ) የእነዚህ ሐሰተኞች ነቢያት መልእክት የሚያስከትለውን መዘዝ ለመገደብ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

4. ኤርምያስ የባቢሎን ምርኮ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በትክከል ተንብዮ ነበር፤ ይህም 70 ዓመታት ነበር (ኤርምያስ 29፡10)። (70ውን የምርኮ ዓመታት በሚመለከት ቀደም ሲል ያሰፈርነውን በሁለት የተለያዩ መንገዶች የተሰጠ ማስታወሻ ተመልከት።) ባለመታዘዛቸው ምክንያት እግዚአብሔር ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አልፈለገም። በከፍተኛ ደረጃ የቀጣቸው ቢሆንም እንኳ ከቅጣቱ ጊዜ በኋላ ግን የምሕረትና የይቅርታ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደገዛ ምድራቸው ለመመልስ ተስፋ ሰጠ።

ኤርምያስ እስራኤል የምትመለስበትንና አሕዛብ በእግዚአብሔር የሚሸነፉበትን፥ እንዲሁም አይሁድ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን በመፈጸም የሚኖሩበትን የመጨረሻ ዘመን አሻግሮ በመመልከት ተናግሯል። አይሁድ እስከ አሁን ድረስ በብዙ መንገድ በእግዚአብሔር ቅጣት ሥር ናቸው። ከአይሁድ ብዙዎች ወደ አገራቸው የተመለሱ ቢሆንም፥ ሌሉች እጅግ ብዙዎች ደግሞ በአሕዛብ መካከል ተበትነው ይገኛሉ። ይሁን እንጂ አንድ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ዳግም በማነጹ እዛው በአሕዛብና በአይሁድ ላይ ይነግሣል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ኤርምያስ 31፡31-34 አንብብ። በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የተካተቱ ተስፋዎች ምንድን ናቸው? ለ) አዲሱ ቃል ኪዳን ከቀድሞው ቃል ኪዳን የሚለየው እንዴት ነው? 

5. ኤርምያስ አዲስ ኪዳን የተመሠረተበትን አዲስ ቃል ኪዳን ያስተዋውቀናል። አዲሱንና የብሉይ ቃል ኪዳንን ብናወዳድር አንዳንድ ዐበይት ልዩነቶችን እንመለከታለን። ብሉይ ቃል ኪዳን የተመሠረተው በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ባለ የጋራ ስምምነት ላይ ነው። ቃል ኪዳኑ የተፈጸመው በስምምነት መልክ ሲሆን፥ እንዲታዘዙት እግዚአብሔር ያስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ነበር። ለሕጉ በሚሰጡት ምላሽ መሠረት በረከትና መርገም ይከተላቸው ነበር። ይሁን እንጂ አዲስ ኪዳን በስምምነት መልክ አልነበረም። ይልቁንም እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው ተስፋ ነበር። እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ ሕጉ በድንጋይ ጽላት ላይ ሳይሆን፥ በሰዎች ልብ ውስጥ መጻፍ ነበረበት። ይህም ሕጉን የበለጠ እንዲያውቁትና እንዲታዘዙት የሚያደርግ ነው።

ነገር ግን አዲሱ ቃል ኪዳን በብዙ መንገድ ሙሉ በሙሉ አዲስ አልነበረም። ሕግን (ኤርምያስ 31፡33) የፓልስጢናን ምድር (ኤርምያስ 32፡36-44) እንዲሁም የዳዊትን ሥርወ-መንግሥት (ኤርምያስ 33፡15-26) ይጨምር ነበር። ይህም ማለት አዲሱ ቃል ኪዳን በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር፥ ቀጥሉም ከዳዊት ጋር ያደረጋቸው የሁለት ቃል ኪዳኖች ቅጥያ ነው ማለት ነው። በቀድሞውና በአዲሱ ቃል ኪዳን መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት፡- በአሮጌው ቃል ኪዳን ውስጥ ከግብ ለማድረስ ፈጽሞ የማይቻለውን ጉዳይ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ ግን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምክንያት የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለመፈጸም መቻሉ ነው። ሁኔታዎቹ ከግቡ የሚደርሱት መንፈስ ቅዱስ ትክክለኞች የሆኑትን የእግዚአብሔር መመዘኛዎች ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ስለሚሰጥ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ክርስቲያን ከሆንክ ጀምሮ ሕይወትህ እንዴት ነው የተለወጠው? ለ) በሕይወትህ እንድትቀደስና የእግዚአብሔርን ሕግ ለመፈጸም እንድትችል መንፈስ ቅዱስ ሊረዳህ በመሥራት ላይ ያለው እንዴት ነው?

ትንቢተ ኤርምያስ ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት

ትንቢተ ኤርምያስ እንደ ትንቢተ ኢሳይያስ ከአዲስ ኪዳን ጋር በቅርብ የተያያዘ አይደለም። ትንቢተ ኤርምያስ ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው የቅርብ ግንኙነት ከቀድሞው ቃል ኪዳን የበለጠና የተሻለ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚመጣ ማመልከቱ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ያንን አዲስ ኪዳን አስተዋወቀ። ዛሬም እኛ ሁላችን በኢየሱስ ክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ በዚያ ቃል ኪዳን ውስጥ እንጠቃለላለን።

አንዳንድ ምሁራን በኤርምያስና በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል ብዙ ተመሳሳይነት መኖሩን ይናገራሉ። ሁለቱም አላገቡም፤ በወገናቸው ተንቀዋል፤ አገራቸውን አሳልፈው እንደሰጡ ተቈጥረው ተከሰዋል፤ በዘመናቸው ከነበሩት የሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፤ ስለ ኢየሩሳሌም ንስሐ አለመግባትና ጥፋት አልቅሰዋል፤ ደግሞም በዓለም አመለካከት ያልተሳካላቸውና ጥቂት ተከታዮች የነበሯቸው ነበሩ። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የትንቢተ ኤርምያስ ዓላማ፣ ዋና ዋና ትምሕርቶች እና ከአዲስ ኪዳን ጋር ያለው ግንኙነት”

Leave a Reply

%d bloggers like this: