የትንቢተ ሕዝቅኤል ዓላማ እና የሥነ መለኮት ትምሕርት

የትንቢተ ሕዝቅኤል ዓላማ

ሕዝቅኤል ይህን መጽሐፍ ለምን እንደ ጻፈው ለመረዳት፥ ሕዝቅኤል ያገለገለው ከኢየሩሳሌም ውድቀት ጥቂት ቀደም ብሎና ከውድቀቷ በኋላም ለጥቂት ጊዜያት መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ሕዝቅኤል ይህን መጽሐፍ የጻፈባቸው ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ነበሩ፡-

1. ሕዝቅኤል ጠባቂና የእግዚአብሔር ቃለ አቀባይ ስለነበር፥ ልባቸው ለደነደነባቸው አይሁድ የእግዚአብሔርን የማይለወጥ ፍርድ በመናገር የንስሐ ጥሪ ያቀርብ ነበር። ሕዝቅኤል የፍርዱን መልእክት በማስተላለፍ ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ ጥሪ ከማድረግ ይልቅ ዝም ቢል ይቀለው እንደነበር እግዚአብሔር ያውቃል። ዳሩ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ባያስጠነቅቅና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ጥሪ ባያደርግላቸው፥ ለሕዝቡ መሞት ተጠያቂ እንደሚያደርገው በመግለጽ ሕዝቅኤልን አስጠነቀቀው። የትንቢተ ሕዝቅኤል የመጀመሪያ ክፍል (ከምዕራፍ 1-14) የሚያተኩረው በዚህ ዓላማ ላይ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 3፡16-21 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል የሰጠው ማስጠንቀቂያ ምን ነበር? ለ) ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ለሆንን ለእኛም ይህ ማስጠንቀቂያ እውነት የሚሆነው እንዴት ነው? ) የበለጠ እንመሰክር ዘንድ ይህ እውነት ሊያበረታታን የሚገባው እንዴት ነው? መ) ብዙ ክርስቲያኖች የማይመሰክሩት ለምንድን ነው? እነዚህ ቍጥሮችስ ወንጌልን ለሌሎች በማካፈል የበለጠ ግልጽ ለመሆን የሚረዷቸው እንዴት ነው?

2. ሕዝቅኤል በኢየሩሳሌም ውድቀት ደስተኞች በነበሩና ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት በተባበሩ አሕዛብ ላይ የእግዚአብሔርን የፍርድ መልእክት ተናግሮ ነበር (ሕዝ. 25-32)። እግዚአብሔር በገዛ ሕዝቡ ላይ ቢፈርድም፥ አሕዛብ እውነተኛና ቅን ከሆነው ከእግዚአብሔር ፍርድ ተምረው ንስሐ መግባት ነበረባቸው። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሕዝብ በማጥፋት ተባበሩ ደስም አላቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር እንደሚቀጣቸው ተናገረ። እነዚህ ትንቢቶች ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ አሕዛብ በውድቀቷ በሚደሰቱበት ጊዜ ወዲያውኑ የተፈጸሙ ናቸው።

3. ሕዝቅኤል ከኢየሩሳሌም ውድቀት በኋላ የእግዚአብሔርን የማበረታቻ መልእክት የሚናገር ሰው ነበር (ሕዝቅኤል 33-48)። እግዚአብሔር ምርኮውን የተጠቀመበት ሕዝቡን ለማጥፋት ሳይሆን ለማጥራት ነበር። የእግዚአብሔር ፍላጎት የአይሁድ ሕዝብ ከእንግዲህ የእርሱን በረከት አንቀበልም ብለው ተስፋ እንዲቆርጡ አልነበረም። ስለዚህ ሕዝቅኤል ስለ አይሁድ እንደገና መመለስ፥ ከዳዊት ዘር ስለሆነው እውነተኛ እረኛ (ኢየሱስ) አይሁድ እንደገና አንድ ስለሚሆኑበት ሁኔታና ምድራቸው ከኃጢአት ሁሉ ነጽታ በእውነት እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩ ይነግራቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ወንጌልስ እንደዚሁ ፍርድ እንደሚመጣና በረከት እንዳለ የሚያበረታቱ የተስፋ ቃሎች ጥምረት የሆነው እንዴት ነው? ለ) ባለፈው ወር በቤተ ክርስቲያንህ ስለ ሰማሃቸው መልእክቶች አስብ። ከእነዚህ መልእክቶች መካከል የፍርድ መልእክት የነበሩት ምን ያህሉ ናቸው? የማበረታቻ መልእክት የነበሩትስ? ሐ) የፍርድን መልእክት ማወጅ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማበረታታትም የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ የሚገኝ የሥነ መለኮት ትምህርት 

ትንቢተ ሕዝቅኤል ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ባያጠኑትም ጠቃሚ በሆኑ የሥነ መለኮት ትምህርት እውነቶች የተሞላ ነው። ከዚህ በመቀጠል በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶችን እንመለከታለን፡-

1. ሕዝቅኤል እግዚአብሔር የሕዝቡንና የቀሩትን አሕዛብ ታሪክ በሙሉ የሚቆጣጠር መሆኑን በማሳየት፥ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ሉዓላዊነት ያስተምራል። በትንቢተ ሕዝቅኤል ውስጥ ከምናገኛቸው እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ሐረጎች አንዱ፡- «እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ» የሚለው ነው (ለምሳሌ፡- ሕዝ. 35፡15)። ይህ ሐረግ በመጽሐፉ ውስጥ 70 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል። ይህ ሐረግ በአይሁድ ላይ ስለመጣው የእግዚአብሔር ፍርድና የእርሱን ማንነት ተገንዝበው በንስሐ ወደርሱ ስለ መመለሳቸው አስፈላጊነት ለማሳየትና እንዲሁም እግዚአብሔር የሚቀጣቸውን አሕዛብ በሚመለከት አገልግሎአል። እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ያለው የበላይ ተቆጣጣሪነትና እነርሱን መቅጣቱ ሉዓላዊ አምላክ መሆኑን ለእነርሱ በተለይም ለራሱ ሕዝብ ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር ወደፊት እስራኤልን እንደሚባርክ የተናገራቸው ትንቢቶች መፈጸማቸው እንደማይቀርና እርሱም ታላቁ የእስራኤል አምላክ ያህዌ መሆንን ለሁሉም ለማሳወቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፣ ሕዝቅኤል 1ን አንብብ። ይህ ራእይ የእግዚአብሔርን ታላቅነት እንዴት ያሳያል?

ትንቢተ ሕዝቅኤል የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ኃይል የሚያሳይበት ሌላ መንገድ አለ፤ ይህም፡- ሕዝቅኤል በሚያያቸው ራእዮች አማካይነት ነው። እነዚህ ራእዮች በምልክቶች የተሞሉ ናቸው። ብዙዎቹ ዓይኖች እግዚአብሔር በሰዎች ልብ ውስጥ የተሰወሩትን ነገሮች ሳይቀር፥ የሚፈጸሙትን ነገሮች በሙሉ የማየት ችሎታ እንዳለው የሚያመለክቱ ናቸው። መንኰራኵሮቹ እግዚአብሔር በሁሉም ስፍራ የሚገኝ መሆኑን ያመለክታሉ። እርሱ በተስፋይቱ ምድር በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፤ ነገር ግን በምርኮ ምድር ከሚኖሩ አይሁድ ጋር ሳይቀር፥ በሁሉም ቦታ ይገኛል። እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል በሰጣቸው ራእዮች ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት የሚገልጹ ናቸው። እነዚህ ራእዮች እግዚአብሔር ሕያውና ኃያል መሆኑን ለማሳየት ለሕዝቅኤልና ለእስራኤል በሙሉ የተሰጡ ናቸው። እርሱ ሰው እንደሚያውቀው እንደማንኛውም ነገር አይደለም። በሰማይ የሚነግሥ ታላቅ ግርማ ያለው አምላክ ነው። እርሱ ነገሮችን ሁሉ ማለት ሕዝቡን፥ የቀሩትን አሕዛብ ሁሉና፥ የአሁኑን ዘመን ፍርድና እንዲሁም የወደፊቱን የአይሁድ መመለስና በረከት ይቈጣጠራል። ስለ ሕዝቡ ሆኖ ያለ ማቋረጥ ይሠራል።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች ይህን እውነት ሊረዱትና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱት የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ይህ እውነት እንዴት እንዳበረታታህ ለማስረዳት አንዳንድ መግለጫዎችን ስጥ።

2. የእግዚአብሔር ክብርና ቅድስና፡- ሕዝቅኤል በራእዩ የእግዚአብሔርን ቅድስና አየ። የእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕልውና ምልክት የክብር ደመና ነበር። እንደሚታወሰው፥ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ሁሉ ይህ የክብር ደመና እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የመኖሩ ምልክት ነበር። አይሁድ ይህን የክብር ደመና «የሺክናህ ክብር» በማለት ይጠሩታል።

ይህ የክብር ደመና እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው ሲወጡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጠ ሲሆን፥ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መርቶአቸዋል (ዘጸአት 40፡34-38)። ይህ የክብር ደመና በመጀመሪያ የመገናኛውን ድንኳን፥ በኋላ ደግሞ ቤተ መቅደሱ በተሠራ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ሞልቶታል (1ኛ ነገሥት 8፡10-10። በትንቢተ ሕዝቅኤል ይህ የክብር ደመና ከቤተ መቅደሱ ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ በር በመንቀሳቀስ፥ በመጨረሻ ከተማውን ለቅቆ ሲሄድ እንመለከታለን (ሕዝቅኤል 3ና 10)። ይህ ክብር በመጨረሻ ዘመን መሢሑ እንደገና እስኪመጣ ድረስ ወደ ኢየሩሳሌም አይመለስም (ሕዝቅኤል 43፡1-12)።

እግዚአብሔር እስራኤልን ቅዱስ ሕዝቡ እንዲሆኑ አድርጎ ሲመርጣቸው በመካከላቸው ለማደር ፈልጎ ነበር። ቤተ መቅደሱ የእግዚአብሔር ዙፋን በእስራኤላውያን መካከል የመኖሩ ምልክት ሲሆን፥ ደመናው ደግሞ የሕልውናው ምልክት ነበር። በመጨረሻ ግን የሕዝቡ ኃጢአት እግዚአብሔርን ከዚህ ቤተመቅደስ አስወጣው። እግዚአብሔር ሕዝቡ እንደገና እንዲቀደሱና እርሱም በመካከላቸው ያድር ዘንድ በምርኮ ሊቀጣቸው ወሰነ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) በአዲስ ኪዳንና በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕልውና የሚገለጽበት መንገድ የሚለያየውና የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ለ) በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ክብር ምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ዛሬም በመካከላችን ሊያድር የሚፈልገው እንዴት ነው? መ) ንጹሐንና እርሱ ሊያድርብን የምንችል ሰዎች እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ የሚቀጣን እንዴት ነው?

እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን በውጭ የሚታይ የቤተ መቅደስ ሕንጻን በማደሪያነት መጠቀመን አቁሟል። ሕልውናውንም በክብር ደመና ውስጥ አያሳይም። ይልቁንም የእግዚአብሔር ማደሪያ የእያንዳንዱ አማኝ ልብ ሆኖአል። አማኞች የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሆነዋል (1ኛ ቆሮ. 6፡19)። በተጨማሪ የአማኞች ማኅበረሰብ ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ናቸው (1ኛ ቆር. 3፡16)። እግዚአብሔር ሕዝቡ ቅዱስ እንዲሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ልጆቹ ቅድስናቸውን ይጠብቁ ዘንድ ብዙ ጊዜ ይቀጣቸዋል።

4. ሕዝቅኤል ዘጠና ጊዜ «የሰው ልጅ» ተብሎ ተጠርቷል። እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን የጠራበት ተወዳጅ ስም ይህ ነበር። ይህ ማዕረግ በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ ያተኮረው በመሢሑ ታላቅነት ላይ ሲሆን (ዳንኤል 7፡13)። በትንቢተ ሕዝቅኤል ግን ከእግዚአብሔርና ከመልእክቱ ታላቅነት በተቃራኒ በሕዝቅኤል ድካም ወይም ሰብአዊነት ላይ ያተኩራል። ኢየሱስ ራሱን «የሰው ልጅ» ብሎ ሲጠራ ምን ማለቱ እንደሆነ ምሁራን ዘወትር ይደነቃሉ። በሰብአዊነቱ ላይ አተኩሮ ነበር ወይስ እርሱ በትንቢተ ዳንኤል ውስጥ የተጠቀሰው የሰው ልጅ ፍጻሜ መሆኑ ነው? ምናልባት መልሱ ሁለቱም ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር። ልክ እንደ እኛ ሥጋና ደም የነበረው ሲሆን፥ ኃጢአት ግን አልነበረበትም። እንዲሁም ከወንጌላት በግልጽ እንደምንመለከተው፥ ኢየሱስ በትንቢተ ዳንኤል የተጠቀሰው መሢሕ መሆኑን ያውቅ ነበር (ለምሳሌ፡- ማቴዎስ 24፡29-31)። ይህ ሐረግ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያስታውሱትና በሕይወታቸው ሊጠቀሙበት የሚያስፈልግ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብዙ ጊዜ ልዩና ታላቅ እንደሆኑና ከፍተኛ ሥልጣን አለን ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እኛ የሰው ልጆች ሰብአዊ ፍጡራን ብቻ እንደሆንን ልናስታውስ ያስፈልገናል። አገልግሎታችን ወይም ስብከታችን ስኬታማ ቢሆንም በእኛ ምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም በእኛ ውስጥና በእኛም አማካይነት ሊሠራ በመረጠን በታላቁ አምላክ በእግዚአብሔር ምክንያት ነው። ስለዚህ የምንመካበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ጳውሎስ እንዳለው፡- አንዳንዶቻችን መትከል፥ ሌሎቻችን ደግሞ ማጠጣት እንችላለን፤ የሚያሳድግ ግን ሁልጊዜ እግዚአብሔር ነው (1ኛ ቆሮ. 3፡5-7)።

የውይይት ጥያቄ፥ ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብዙ ጊዜ ሊታበዩና ሊኮሩ የሚችሉባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ሲታበዩና ሊኮሩ ስለ ራሳቸው የሚረሱት ነገር ምንድን ነው? ሐ) ሊታበዩና ሲኮሩ ስለ እግዚአብሔር የሚረሱት ነገር ምንድን ነው? መ) «የሰው ልጅ» የሚለው ሐረግ የሚያስተምረው እውነት ለእነርሱ ማስጠንቀቂያ መሆን ያለበት እንዴት ነው?

5. ሕዝቅኤል የሰውን ሕይወት በሚመለከት ግላዊ ኃላፊነት ላይ ትልቅ ትኩረት አድርጎአል። አይሁድ ለሚደርስባቸው ችግር ብዙ ጊዜ ወላጆቻቸውን የመውቀስ ዝንባሌ ነበራቸው። ወላጆች ስለሚሠሩት አንዳንድ ኃጢአት እግዚአብሔር በልጆቻቸው ላይ ቅጣት እንደሚያመጣ ብሉይ ኪዳን የሚያስተምረውን ትምህርት በተሳሳተ መንገድ ተረድተውት ነበር (ለምሳሌ፡- ዘጸአት 20፡5-6)። ስለዚህ አይሁዶች በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርተው ራሳቸውን አይመረምሩም ነበር። እግዚአብሔር ሰውን የሚቀጣውም ሆነ የሚሸልመው ግለሰቡ ከእርሱ ጋር ባለው ግንኙነትና ክፋትን ለመተው በሚያሳየው ፈቃደኝነት መሠረት መሆኑን ለሕዝቅኤል ነገረው። «ኃጢአትን የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች» (ሕዝ. 18፡4)። ወላጆች የሚሠሩት ኃጢአት በልጆቻቸው ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ቢኖርም፥ እግዚአብሔር አንድን ሰው በወላጆቹ ኃጢአት ምክንያት ገሃነም አያገባውም። ጻድቃን ወላጆች ያሏቸው ልጆችም በወላጆቻቸው ጽድቅ ምክንያት ብቻ ወደ ዘላለም ሕይወት አይሄዱም። ስለዚህ (በእያንዳንዱ ትውልድ ያለ) እያንዳንዱ ሰው ኢየሱስን አምኖ በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ሕይወት ለመኖር መወሰን ወይም ኢየሱስን ክዶ ለመኖር መወሰን አለበት።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች የችግራቸው ምክንያት ወላጆቻቸው ወይም የትምህርት እጦት እንጂ የራሳቸው ኃጢአት እንዳይደለ የሚያስቡበትን መንገዶች ግለጽ። ለ) ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች በወላጆቻቸው እምነት ምክንያት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዳላቸው አድርገው የሚያስቡባቸውን መንገዶች ግለጽ። ሐ) ሕዝቅኤል 18ን አንብብ። ይህ ምዕራፍ ለእነዚህ ሁለት ችግሮች መልስ የሚሰጠው እንዴት ነው?

6. ስለ መጨረሻው ዘመን የተሰጡ ትምህርቶች፡- ከሕዝቅኤል 33-48 ያለው የመጨረሻው የትንቢተ ሕዝቅኤል ክፍል ስለ መጨረሻው ዘመን የሚናገር ነው። ሕዝቅኤል በዚህ ክፍል የሚተነብየው የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ እንደገና ስለሚዋሐዱበትና በከነዓን ምድር ስለሚኖሩበት ዘመን ነው። አንድ እረኛም ይኖራቸዋል። እርሱም ጻድቁ መሢሕ ነው። ቤተ መቅደሱ እንደገና ይሠራል። መሥዋዕት በቤተ መቅደሱ ይቀርባል። ምድሪቱም እኩል ትከፋፈላለች። አይሁድ በሙሉ እግዚአብሔርን ያመልካሉ። መሢሑም በመካከላቸው ይኖራል። እነዚህ ምዕራፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ዘንድ ሰፊ ውይይት ያስነሡ ናቸው። እግዚአብሔር በመጨረሻ ዘመን በሚያደርገው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ክርስቲያኖች የተለያየ ግንዛቤ እንዳላቸው የሚታወስ ነው። አንዳንዶች እግዚአብሔር በምድር ላይ የራሱ የሆነ መንግሥት የሚመሠርት ይመስላቸዋል። ኢየሱስ በምድር ላይ ለ1000 ዓመት እንደሚነግሥ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ እነዚህ ትንቢቶች ሁሉ እግዚአብሔር በረከቱን ለሕዝቡ እንደሚመልስ የሚያሳዩ ተምሳሌታዊ መግለጫዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። እነዚህ የተለያዩ አመለካከቶች፥ ሰዎች እነዚህን ምዕራፎች የሚተረጕሙባቸውን ሁኔታዎች የሚወስኑ ናቸው። ሕዝቅኤል 33-48 የሚተረጐምባቸው ሁለት ዐበይት መንገዶች አሉ፡-

1. የሕዝቅኤል ቃሉች እግዚአብሔር ከሁሉም ዘር በተውጣጡና የራሱ መንፈሳዊ ልጆች በሆኑት ሰዎች መካከል እንደገና እንደሚኖር፥ ኢየሱስ እረኛቸው እንደሚሆንና እውነተኛ አምልኮ እንደሚኖር የሚያሳዩ ተምሳሌታዊ መግለጫዎች ናቸው። የዚህ አመለካከት አራማጆች በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ እንደምናየው፥ እግዚአብሔር በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ያለውን የመለያየት ግድግዳ አፍርሶአል ይላሉ (ኤፌሶን 2፡13-16)። ስለዚህ ሕዝቅኤል አይሁድ ወደ ከነዓን ምድር ስለመመለሳቸው፥ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ስላለው ልዩነት መናገሩን ስናይ በተምሳሌታዊ መግለጫነቱ ብቻ ነው ልንረዳው የሚገባን። አሁን እውነተኛው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሕንጻው ሳይሆን ሰዎች መሆናቸውን አዲስ ኪዳን ያስተምራል ይላሉ። በመጨረሻም እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በእውነት የሚኖርበት መንግሥተ ሰማያት ይሆናል። ስለዚህ ግዙፍ የሆነ ቤተ መቅደስ አያስፈልግም። እንዲሁም ኢየሱስ የመጨረሻው ፍጹም መሥዋዕት ስለሆነ ሌላ የእንስሳ መሥዋዕት አያስፈልግም። ወደፊት በመሥዋዕትነት የሚቀርቡ የእንስሳ መሥዋዕቶች እንደሚኖሩ መናገር የኢየሱስ ሞት ለሕዝቡ ኃጢአት በቂ አይደለም እንደ ማለት ነው ይላሉ። 

2. ሌሎች ደግሞ የሕዝቅኤልን ቃሎች በቀጥታ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። እነዚህ ቃሎች ተምሳሌታዊ ብቻ ናቸው የምንልበት ምንም መሠረት የለንም። ይህን ማድረግ ማለት ቀጥተኛውንና ተምሳሌታዊውን ነገር በመወሰን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ፈራጆች ሆንን ማለት ነው። በዚህ ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስን መተርጐም ግምታዊ ሥራ ይሆናል። እግዚአብሔር በቃሉ የሚለው ምን እንደሆነ መገመት ማለት ነው። ስለዚህ እነዚህ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ የተለየ የወደፊት ዕቅድ እንዳለው ይናገራሉ። መሢሑም ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም ላይ ይነግሣል ይላሉ። አይሁድ ቤተ መቅደሳቸውን የአምልኮ ስፍራ አድርገው እንደገና ይገነባሉ። መሥዋዕቶች የሚቀርቡት ለተለየ ዓላማ በመሆኑ ነው። የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት የሚቀርቡ ሳይሆኑ፥ በመስቀል ላይ የቀረበውን የኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት የሚያስታውሱ መታሰቢያዎች ይሆናሉ።

ክርስቲያኖች በእነዚህ ዝርዝር ጉዳዮችና በአፈጻጸማቸው ላይ ልዩነት ቢያሳዩም፡ ሁሉም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመለስ ያምናሉ። እግዚአብሔር እነዚህን ትንቢቶች እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት አለን። ክርስቶስ በጽድቅ የሚነግሥበትን ዘመን አሻግረን ልንመለከትና ተስፋ ልናደርግ እንችላለን። ክርስቲያኖች በዚህ ፍትሕ በጐደለው ከፉ ዓለም ውስጥ በምንኖርበት ጊዜ ተስፋ የሚሰጠን ይህ ነው። ይህ ዓይኖቻችንን በዚህ ዓለም ሳይሆን በዘለዓለማዊነት ነገሮች ላይ እንድናሳርፍ ይረዳናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ፊልጵስዩስ 3፡20፤ ቈላስይስ 3፡1-6፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 4፡16-5፡10 አንብብ። ሀ) ክርስቲያን የየትኛው አገር ዜጋ ነው? ለ) የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምፅአት ማሰላሰል በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚገባው እንዴት ነው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽአት እንደሚጠባበቁ ቢናገሩም ይህ አኗኗራቸው የማይለወጠው ለምንድን ነው? መ) ኢየሱስ አንድ ቀን እንደሚመለስ እያሰብን ብንኖር የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/m6RzJUwU5QJ4XGWs9

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading