ሕዝቅኤል 13-17

ለቤተ ክርስቲያን ከመንግሥትና ከሌሎች ሃይማኖቶች ከሚመጣባት ስደት ይልቅ እጅግ አደገኛው ነገር በውስጥዋ የሚነሱ የሐሰተኞች አስተማሪዎች ጉዳይ ነው። ራሳቸውን የእግዚአብሔር ልጆች አድርገው ስለሚያቀርቡ ወይም ስለሚያስመስሉ ሐሰተኞች አስተማሪዎችን እውነተኛ ፈሪሀ- እግዚአብሔር ከሞላባቸው መሪዎች መለየት ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል የሚለውጡት በጣም መጠነኛ በሆነ መንገድ ስለሆነና በእግዚአብሔርም ስም እንደሚናገሩ ስለሚያስመስሉ ብዙ ሕዝብን ወደ ክፋት ሊያስኮበልሉ የሚችሉ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ ወይም በሌላ ሰው ቤተ ክርስቲያን ሲፈጸም ያየኸው እንዴት ነው?

ሐሰተኞች ነቢያት የእውነተኞች ነቢያት ቀንደኛ ጠላቶች ነበሩ። ኤርምያስ ከእነርሱ ጋር እንዴት ግብግብ መግጠም እንደነበረበት ተመልክተናል። ሕዝቅኤልም እንደዚሁ ግብግብ መግጠም ነበረበት። ስለዚህ እግዚአብሔር በሐሰተኞች ነቢያት ላይ እንደሚፈርድ ተናገረ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 13-17 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ውስጥ ያሉትን ዐበይት ትንቢቶች ጥቀስ። ለ) ትንቢትን ለማስተላለፍ ያገለገሉትን የተለያዩ የአነጋገር ዘይቤዎች ዘርዝር።

1. በሐሰተኞች ነቢያት ላይ የተነገሩ ትንቢቶች (ሕዝቅኤል 13)፡- ሐሰተኞች ነቢያት መንፈሳዊ ቅጥሮቻቸውን ለመጠገን ከሰዎች ጋር ከመሥራት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ይሠሩ ነበር። የተሳሳተ መረጃ በመስጠት፥ ሰዎች ንስሐ ለመግባትና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ባላቸው ችሎታ ላይ እንቅፋት ያኖራሉ። መንፈሳዊ ለመምሰል በሚያደርጉት ሙከራ፥ በውጭ ሲታይ ያማረ ሆኖ ውስጡ ግን በቆሻሻ እንደተሞላ ኖራ እንደተቀባ ግድግዳ ነበሩ። የጦርነቱ ዝናብ በእነርሱ ላይ በመጣ ጊዜ፥ መልካም ይመስሉ የነበሩ የሐሰት መልእክቶቻቸው ታጥበው ይወሰዱና ክፋታቸው በሙሉ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሆን ነበር። እግዚአብሔር በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ሐሰተኞች ነቢያት በመጨረሻ እንደሚያጠፋቸው ሁሉ፥ የዚያ ዘመን ሐሰተኞች ነቢያትንም እንደሚያጠፉ ቃል ገብቶ ነበር። የሚያሳዝነው አብዛኛዎቹ እስራኤላውያን የሐሰተኞች ነቢያትን መልእክት መከተላቸው ሲሆን፥ ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች የሐሰት ትምህርት አስተማሪዎችን ይከተላሉ። 

2. በጣዖት አምላኪዎች ላይ የተነገረ ትንቢት (ሕዝቅኤል 14፡1-11)፡- የጣዖት አምልኮ በብዙ የተለያዩ መልኮች ይገለጻል። ዛፍን ወይም ድንጋይን ወይም አንድ ሌላ ጣዖትን ማምለክ ብቻ ሳይሆን፥ ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለ ሃይማኖት የሚቀርብ ማንኛውም የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ስለ እግዚአብሔር የተሳሳተ አስተሳሰብ ካለን ጣዖትን እያመለክን ነው ማለት ነው። አይሁድ ጣዖታትን በግልጽ ማምለክ ብቻ ሳይሆን፥ በልባቸው ውስጥ ጣዖታትን አኑረው ነበር (14፡3)። ሕዝቅኤል ጣዖት አምላኪዎችን ንስሐ እንዲገቡ ያስጠነቅቃቸዋል። ከጣዖት አምልኮ ፊታቸውን ከመለሱ፥ እግዚአብሔር ለጸሎታቸው መልስ እንደሚሰጥ ቃል ገባላቸው።

3. በይሁዳ ላይ የመጣው ፍርድ የሚያመልጡት ዓይነት አይደለም (ሕዝቅኤል 14፡12-23)፡- በይሁዳ ላይ የፍርድ ቀን መጥቶ ነበር፡፡ ይህም ፍርድ ለማምለጥ የሚቻል አልነበረም። ለሕዝቡ ጸሎት እንዳያደርግ እግዚአብሔር ኤርምያስን እንደከለከለው ተመልከተናል፡፡ አሁን በትንቢተ ሕዝቅኤል እግዚአብሔር ስለ ጽድቃቸው የታወቁ ሦስት ሰዎችን በመጥቀስ የጻድቅ ሰው ጸሎት እንኳ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ስለነበሩ አይሁዳውያን ነፃ መውጣትን ወይም ከጥፋት ማምለጥን እንደማያስገኝላቸው ያስረዳል። የኖኅ ጽድቅ በዚያ ክፉ ዘመን ከጥፋት ውኃ ያመልጥ ዘንድ ረድቶታል። ዳንኤልም በጽድቁ ምክንያት ከአንበሶች ጉድጓድ አምልጧል። ይህም በወቅቱ በባቢሎን ውስጥ ይኖር ስለነበረውና በአይሁድ መካከል በጽድቁ ስለታወቀው ነቢይ የሚናገር ይመስላል። ኢዮብ እጅግ ቢፈተንም እግዚአብሔርን አልሰደበም። እነዚህ ሦስት ሰዎች በወቅቱ በኢየሩሳሌም ውስጥ ቢኖሩ እንኳ ለአይሁድ ዕርዳታ ለማድረግ አይችሉም። የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን ቢችሉም፥ ከተማይቱንና የቀረውን ሕዝብ ለማዳን ስለማይችሉ፥ አይሁድን ባለማመናቸው ምክንያት እግዚአብሔር እንደሚያጠፋቸው ተናገረ። በዱር እንስሳ፥ በሰይፍ፥ በመቅሠፍት፥ በራብ አለቁ። የእግዚአብሔርን ታማኝነት ለማረጋገጥ ጥቂቶቹ ብቻ በሕይወት ቀሩ።

የውይይት ጥያቄ፥ የአንድ ሰው ጽድቅ ለሌላው ሰው ደኅንነትን ለማስገኘት ስላለው ብቃት ይህ ክፍል ምን ያስተምረናል?

4. ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር የማትጠቅም ወይን (ሕዝቅኤል 15)፡- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ስላሉ ግንኙነቶች ከሚገልጡ ዐበይት ምሳሌዎች አንዱ ስለ ወይን ተክል የቀረበ ምሳሌ ነው (ለምሳሌ፡- ዮሐንስ 15)። እግዚአብሔር ወይን የተከለው ፍሬ እንዲያፈራ ቢሆንም፥ በወይን የተመሰለችው ይሁዳ ግን ፍሬ አልሰጠችም ነበር። ከንቱና የማትጠቅም ሆና ነበር። የወይን ግንድ ለልብስ መስቀያ ወይም ለማገዶ እስከማያገለግል ድረስ ደካማ እንደሆነ ሁሉ፥ ይሁዳም ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የማትጠቅም ከንቱ ሆና ነበር። ስለዚህ ልትጠፋ ይገባት ነበር። ከባቢሎን ጋር ከሚደረግ አንድ የጦርነት እሳት ልታመልጥ ትችል ይሆናል (597 ዓ.ዓ.)፤ ነገር ግን ሌላ እሳት ፍጹም ያጠፋታል (586 ዓ.ዓ.)። 

5. የአመንዝራዪቱ የኢየሩሳሌም ምሳሌ (ሕዝቅኤል 16)፡- አይሁድ ከአባቶቻቸው በወረሱት ነገር ታብየው ነበር። የአብርሃም ልጆች ነበሩ፤ ከተማቸውም የዳዊት ከተማ ነበረች። እግዚአብሔር ግን እውነተኛውን ርስታቸውን በሥራቸው አሳያቸው። ኢየሩሳሌም ከከነዓናዊ አባትና ከኬጢያዊት እናት እንደተወለደችና እንዳልተፈለገች ልጅ ተደርጋ እንደተገለጸች እንመለከታለን። ከብዙ ጊዜ በፊት ኢየሩሳሌም የአሞራውያንና የኬጢያውያን ምድር ነበረች። ዳዊት በወረራ የያዛት ነበረች። ኢየሩሳሌም ልክ ተወልዶ ወደ ውጭ ከተጣለ ልጅ ጋር ተመስላ ቀርባለች። እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ወደዳት፤ መረጣት፤ አጠባት፤ ምግብና ልብስ ሰጥቶ እንድታድግ ተንከባከባት። ልክ እንደ ልዕልት እግዚአብሔር በረከቱን አትረፍርፎ ሰጣት። አንድ ባል ለሚስቱ ቃል ኪዳን እንደሚገባ፥ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ባይወልዳትም እንኳ ልጁ አድርጎ የወሰዳት ኢየሩሳሌም ግን ባደገች ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀች። ጣዖታትን በማምለክና ከአሕዛብ መንግሥት ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ አመንዝራ ሆነች። በዚህ ክፍል ውስጥ ሰዶም ተብላ እንደተጠራችው እንደ እኅቷ ሰማርያ ሆነች። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰማርያን (እስራኤል) እንደቀጣ ሁሉ፥ አመንዝራዋን ኢየሩሳሌምንም ይቀጣል። እግዚአብሔር የተናገረው ፍጹም እንደሚያጠፋት ሳይሆን፥ አንድ ቀን ከኢየሩሳሌም ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን በማድረግ ኃጢአቷን ፍጹም ይቅር እንደሚል ነው። በዚያን ጊዜ ኢየሩሳሌምና ይሁዳ ለእግዚአብሔር ታማኞች ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በእግዚአብሔር ፊት አመንዝራ ልትሆን የምትችለው እንዴት ነው? መግለጫዎችን ዘርዝር። ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ንጽሕት የክርስቶስ ሙሽሪት ትሆን ዘንድ እንዴት ማድረግ ትችላለህ?

6. የሁለቱ ንስሮችና የዝግባው ዛፍ ምሳሌ (ሕዝቅኤል 17)፡- በዚህ ምሳሌ ውስጥ ታላቁ ንስር ባቢሎን፥ ሁለተኛው ንስር ግብፅ፥ ሊባኖስ ኢየሩሳሌም ሲሆን፥ የዝግባው ዛፍ ደግሞ በዳዊት የዘር ግንድ ውስጥ የነበሩትን ነገሥታት የሚያመለክት ነበር። ባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ የዛፉን ቀንበጥ ቀንጥቦ ወደ ባቢሎን ወሰደው። ይህ በምርኮ የተወሰደውን ንጉሥ ኢዮአኪንን የሚያመለክት ነበር። ሁለተኛው ዛፍ ንጉሥ ሴዴቅያስ ነበር። እርሱ በሥልጣን ያደገ ንጉሥ ሲሆን ቅርንጫፎቹ ተስፋፍተው ሁለተኛው ንስር ወደሆነው ወደ ግብፅ ለእርዳታ እጆቹን ዘረጋ። ይህ ንጉሥ ሴዴቅያስ ከባቢሎን ጋር ያደረገውን ስምምነት በመጣስ የተደረገ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ንጉሥ ሴዴቅያስን የምሥራቅ ነፋስ በተባሉት በባቢሎን ኃይላት ሊያጠፋው ወሰነ። ዳሩ ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ከዳዊት ቤት የሆነ ሌላ ቅርንጫፍ ያስነሣል። ታላቅ ዛፍ ከመሆኑ የተነሣ ብዙ ሰዎች በቅርንጫፎቹ ሥር ያርፋሉ። ከማንኛቸውም ዛፎች ሁሉ የሚበልጥ ነው፤ ይህም ማለት ከአሕዛብ መንግሥታት ሁሉ በላይ ነው ማለት ነው። የመጨረሻው ዛፍ ስለ መሢሑ የተነገረ ትንቢት ነው። መሢሑ የዳዊት ልጅና የዓለም ሁሉ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተካተቱትን ጠቃሚ መንፈሳዊ እውነቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት የሚከተለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/73AKfyayVJt7BpKe7

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading