ሕዝቅኤል 40-48

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከዚህ በፊት የቀመስከውን ወይም ያለፍህበትን አስቸጋሪና ከባድ ሁኔታን ጥቀስ። ለ) በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ስታልፍ በጽናት እንድትቆይ ያደረገህ «ተስፋ» ምን ነበር? ሐ) በከባድ መከራና ችግር ውስጥ እንኳ ክርስቲያን ደስተኛ ሆኖ እንዲጸና ሊያደርገው የሚገባ «ተስፋ» ምንድን ነው? መ) 1ኛ ተሰሎንቄ 14፡13-18፤ ቲቶ 2፡14፤ ዕብራውያን 6፡17-20፤ 1ኛ ዮሐንስ 3፡1-3 አንብብ። የሚያበረታቱንን የተለያዩ «ተስፋዎች» ዘርዝር።

ክርስቲያኖች በምንም ዓይነት አስቸጋሪና ከባድ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን፥ ምንም ያህል የጨለመና የከፋ ሁኔታ ቢያጋጥመን፥ ምንም ያህል ከፍተኛ ስደት ቢደርስብን፥ ልንበረታታና ልንጽናና የምንችልበት ብርሃን ወይም ተስፋ አለን። ይህ ተስፋ አሁን በመደረግ ላይ ካለው ባሻገር ወደፊት የሚሆነውን ያመለክታል። ይህ ተስፋ የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ፥ የዘላለም ሕይወት ተስፋ፥ አንድ ቀን ኢየሱስ ክርስቶስን የምንመስልበት ተስፋ፥ ከሞት እንደምንነሣና ከጌታ ጋር ለዘላለም በመንግሥተ ሰማያት መሆናችንን የሚመለከት ተስፋ ነው። ሌሎች በርካታ የተስፋ ቃሎችም አሉን። እነዚህ የተስፋ ቃሉች «የነፍስ መልሕቆች» ስለሆኑና በታላቅ የመከራ ማዕበል ውስጥ ብንሆንም እንኳ ለእግዚአብሔር በታማኝነት እንድንቆም ስለሚያደርጉን ክርስቲያኖች እነዚህን የተስፋ ቃሎች ሊረዷቸውና ሊያምኑባቸው ይገባል።

እግዚአብሔር ለአይሁድ «ተስፋ» ሰጥቷል። የኢየሩሳሌም መደምሰስ፥ በአሕዛብ መካከል መበተን፥ ለአሕዛብ ተገዥ መሆን፥ ሂትለር ፈጽም ሊያጠፋቸው የመቃረቡ ጉዳይና በዘመናት ሁሉ የገጠማቸው ስደት መዘተ. ለአይሁድ ከባድና አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም፥ የብርሃን ተስፋ ግን ነበራቸው። ይህም ተስፋ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያት አይሁድን አጽንተ የሚያቆማቸው መልሕቅ ነበር።

እነዚህ የተስፋ ቃሎች ምን ነበሩ? ባጭሩ አይሁድ አንድ ቀን ከተበተኑበት ስፍራ ወደገዛ ምድራቸው እንደሚሰበሰቡ ተስፋ ተሰጥቶአቸው ነበር። ሰላምና ብልጥግና ወደሞላባት ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ይመለሳሉ። ጠላቶቻቸውን ሁሉ ያሸንፋሉ። የዳዊት መንግሥት ክብርም ይመለስላቸዋል። የተከፋፈለው መንግሥት ፈውስ ያገኝና በአንድ ንጉሥ ጥላ ሥር አንድ መንግሥት ይሆናል። ይህ ንጉሥ መሢሑ ነው። መሢሑ በኢየሩሳሌም የሚነግሥ ሲሆን፥ የዓለም መንግሥታትና አሕዛብ ሁሉ ይታዘዙለታል። አይሁድ፥ ራሱ በደነገገላቸው መንገድ እግዚአብሔርን የማምለክ ነፃነት ይኖራቸዋል። አይሁድ እነዚህን የተስፋ ቃሎች በአእምሮአቸው በመያዝ፥ ለብዙ ዘመናት በፍትሕ አልበኝነት እነርሱን ለማጥፋት የተደረጉትን ሙከራዎች ሁሉ ተቋቊመዋል። የእስራኤል ሕዝብ ሕልውና እስከ ዛሬ ድረስ ሊቆይ የቻለው አይሁድ በእነዚህ የተስፋ ቃሎች ባለማቋረጥ በማመናቸው ነበር።

ሕዝቅኤል 40-48 እግዚአብሔር ለአይሁድ ያለውን ዕቅድ የሚያጠቃልልበት የመጨረሻው ዘመን መግለጫ ነው። ሕዝቅኤል በነበረበትና በሌሎችም ዘመናት ሁሉ በምርኮ ላይ ለነበሩ አይሁድ ተስፋ በመስጠት፥ እግዚአብሔር እንዳልረሳቸው ነገር ግን አንድ ቀን ከእነርሱ ጋር እንደሚሠራ የሚያረጋግጥ ነበር።

እነዚህን ምዕራፎች በሚመለከት በክርስቲያኖች በርካታ የአመለካከት ልዩነት አለ። አንዳንዶች አዲስ ኪዳን ኢየሱስ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል የነበረውን የልዩነት ግድግዳ እንዳፈረሰ ስለሚያስተምር እነዚህ ምዕራፎች ልክ እዚህ ስፍራ በተገለጸበት መልኩ የሚፈጽሙበት መንገድ የለም ብለው ያምናሉ (ኤፌሶን 2፡14)። ኢየሱስ በመስቀል ላይ የከፈለው መሥዋዕትነት የጥንቱን የመሥዋዕት ሥርዓት አስወግዶአል (ዕብራውያን 10፡11-18)። አሁን እግዚአብሔር በሰዎች ልብ ውስጥ ያደረ ስለሆነ ቊሳዊ የሆነ የሚታይ ቤተ መቅደስ አያስፈልግም (1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16)።

ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ እነዚህ የተስፋ ቃሎች በከፍተኛ ደረጃ በቀጥታ መፈጸም አለባቸው በማለት አጥብቀው ይከራከራሉ። አይሁድ የሚመለሱበት አገር ሊኖራቸው ይገባል። መሢሑ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ሊኖርና ሊገዛቸው ይገባል። የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት የሚከተል አንድ ዓይነት የአምልኮ አፈጻጸም ሊኖር ያስፈልጋል። እነዚህ መሥዋዕት ስለ ኃጢአት የሚቀርቡ ከመሆን ይልቅ የኢየሱስን ሞት የሚያስታውሱ ተምሳሌታዊ ተግባራት ይሆናሉ። እነዚህን ምዕራፎች በቀጥታ ካልተረዳናቸውና ካልተቀበልናቸው ትርጒማቸውን በምን እናውቃለን? የሚሉ ናቸው። እነዚህ ለአይሁድ የተሰጡ የተስፋ ቃሎች ወዲያውኑ ለእነርሱ ትርጒም የማይሰጡ ሆነው በመንፈሳዊ አንጻር በቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚውሉ ከሆነ አይሁድ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ የሚያምኑት እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን ከተሰጡት ሌሎች የተስፋ ቃሎች ጋር ይህ ክፍል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ሁሉም ተምሳሌታዊ ናቸውን? እነዚህን ምዕራፎች የሚመለከት ትርጕም ለማዘጋጀት መጀመር ማለት የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች የምንረዳበትና በመተማመን የምንናገርበት ጽኑ መሠረት የለንም ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሕዝቅኤል 40-48 አንብብ። ሀ) ስለ ወደፊቱ ቤተ መቅደስ የሰጡትን የተስፋ ቃላት ግለጽ? ለ) የእግዚአብሔር ክብር ምን ይሆናል? ሐ) በእዚህ ምዕራፎች የተጠቀሰው ልዑል ማን ነው? ) የከነዓን ምድር ምን ትሆናለች ሠ) በዚያን ጊዜ የሚቀርቡ መሥዕዋቶች ምን ዓይነት ይሆናሉ? 

1. አዲሱ ቤተ መቅደስ (ሕዝቅኤል 40-42)

በእነዚህ ሦስት ምዕራፎች ቤተ መቅደስ ምን እንደሚመስል ዝርዝር መግለጫዎች ተሰጥተዋል። ምሁራንና የሕንጻ ባለሙያዎች (አርክቴክቶች) ቤተ መቅደስ ምን እንደሚመስል ለማበጀት ቢሞክሩም፥ የተሰጠው የወርድና የስፋት መጠን ዝርዝር በቂ ስላይደለ አልተቻለም። ሆኖም ግን በተሰጠው መረጃ ብቻ ቤተ መቅደሱ ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ እንኳ እንደሚበልጥ እናውቃለን። የሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከጥንቱ ዘመን ሰባት ታላላቅ ሕንጻዎች አንዱ እንደነበር የሚታወስ ነው። እንደዚህ ዓይነት ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ስለማይታወቅ ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሱስ ክርስቶስ 1000 ዓመት መንግሥት ጊዜ የሚሠራው እንደሆነ ብዙ ምሁራን ያምናሉ።

ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ ገለጣ የሚሰጠው ከውጭው ግድግዳ ጀምሮ ነው። የምሥራቁ መግቢያ ወደ ቤተ መቅደሱ ውጫዊ ክፍልና ወደ ሌሎች የቤተ መቅደስ መውጫዎች የሚመራ ነው። ሕዝቅኤል በውጫዊው የቤተ መቅደስ ክፍል ስላሉትና ካህናት ስለሚጠቀሙባቸው ክፍሎች ይገልጣል። የቤተ መቅደሱን እውነተኛ ቅርጽም ጭምር ይገልጣል። 

2. የጌታ ክብር ወደ ቤተ መቅደሱ ይመለሳል (ሕዝቅኤል 43፡1-12) 

ሕዝቅኤል ቤተ መቅደሱን በሚመለከትበት ጊዜ አስደናቂ ነገር አየ። የጌታ የክብር ደመና ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመለስና በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደሱ እንደነበረው ዓይነት ሲሞላው ተመለከተ።

እንደሚታወሰው ከዚህ በፊት ሕዝቅኤል የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ ትቶ ሲሄድ ስለተመለከተ ይህ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው (ሕዝቅኤል 10-11)። እግዚአብሔር ወደ ሕዝቡ ወደ እስራኤልና ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደገና ይመለሳል። እግዚአብሔር እንደገና ከሕዝቡ ጋር ይኖራል። 

3. በቤተ መቅደሱ ውስጥ የነበረው መሠዊያ (ሕዝቅኤል 43፡13-27) 

4. የእስራኤል የወደፊት መሪዎች (ሕዝቅኤል 44)

ትዝ እንደሚልህ፥ ሕዝቅኤልና ሌሎች የትንቢት መጻሕፍት ለኢየሩሳሌም መደምሰስና ለእግዚአብሔር ሕዝብ መማረክ በዋናነት ጥፋተኞች ያደረጉት መሪዎችን እንደነበሩ የሚታወስ ነው። ነገሥታት፥ ካህናትና ነቢያት በሙሉ ብልሹዎች ስለነበሩ ሕዝቡን ከእግዚአብሔር አራቁአቸው (ለምሳሌ፡- ሕዝቅኤል 34)። ሕዝቅኤል ተገቢ የሆኑ የፖለቲካና መንፈሳዊ መሪዎች የሚነሡበትን ጊዜ አሻግሮ ተመለከተ። ትኲረቱ በሁለት ዓይነት መሪዎች ላይ ነበር። የመጀመሪያው፥ የፖለቲካ መሪ «አለቃ» ተብሏል። ሕዝቅኤል መሢሑን በሚመለከተው በዚህ ትንቢት ላይ ብዙም አላተኰረም። ሁለተኛ፥ የሃይማኖታዊ መሪዎች የሆኑት ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ። ሕዝቅኤል ራሱ ካህን ነበር። ስለዚህ ለሙሴና ለአሮን በተሰጡት ትንቢቶች ፍጻሜ መሠረት ትኵረቱን እውነተኛ መንፈሳዊ መሪዎች በሚኖሩባቸው ቀናት ላይ አድርጎአል። እነዚህ መሪዎች የሚኖሩት ሕግን በመጠበቅና በመፈጸም ስለሚሆን ሕዝቡን ወደ እውነተኛ አምልኮ ይመራሉ። 

5. የእስራኤል ምድር መከፋፈል (ሕዝቅኤል 45-48)

ሕዝቅኤል ወደፊት ምድሪቱ ስለምትከፋፈልበት ሁኔታ በዝርዝር ይገልጣል። የአለቃው ንብረት ባለበት በምድሪቱ ማዕከላዊ ስፍራ ቤተ መቅደሱ ይሠራል። በዚያ ሰፊ ምድር ለካህናትና ለሌዋውያን ስፍራ ይሰጣቸዋል። የቀረው የከነዓን ምድር ለአሥራ ሁለቱ ነገዶች በእኩልነት ይከፋፈላል። 

ሕዝቅኤል ስለሚቀርቡት የተለያዩ መሥዋዕቶችም ይገልጻል። የብሉይ ኪዳን ዋና ዋና መሥዋዕቶች በዚህ ክፍል አለመጠቀሳቸውን መገንዘብ ጠቃሚ ነው። አንዳንድ የተቀደሱ ቀናት በተለይ ከሁሉ የሚበልጠው ቤተ መቅደሱ የሚነጻበት የማስተስርያ ቀን እንኳ አልተጠቀሰም፡፡ የአይሁድ ምሁራን ይህ ለምን እንደሆነ አያውቁም። ብዙ ክርስቲያኖች እነዚህ ለውጦች በመሢሑ ዘመን ሰዎች ሁሉ በጌታ ስለሚዋጁ ለኃጢአት የሚቀርቡ መሥዋዕቶችና የቤተ መቅደሱ መንጻት የማያስፈለግ መሆኑን የሚያንጸባርቁ ናቸው ይላሉ።

እንዲሁም ሕዝቅኤል ከቤተ መቅደሱ ስለሚፈስስ ወንዝ ይገልጻል። ወደ ሙት ባሕር በመፍሰስ ሕይወትን ይሰጠዋል። በወንዙም ሳር ላይ ዓመቱን ሙሉ ፍሬ የሚያፈሩና ለሕዝብ ፈውስና መብል የሚሰጡ ዛፎች ይኖራሉ። (በራእይ 22 ያለውን ተመሳሳይ ወንዝ ተመልከት።) በኢየሩሳሌም ወንዝ ፈጽሞ አልነበረም። ውኃ የእግዚአብሔር በረከት ምልክት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። ምናልባት ይህ የእግዚአብሔር መንፈሳዊና ሥጋዊ በረከት ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ለሕዝቡ ሁሉ እንደሚደርስ የሚያሳይ ምልክት ይሆናል።

ሕዝቅኤል ትንቢቱን የሚደመድመው ለኢየሩሳሌም አዲስ ስም በመስጠት ነው። የከተማይቱ ስም «ያህዌ ማህ» ወይም «እግዚአብሔር በዚያ አለ» የሚል ይሆናል። ይህ ለረጅሙ የትንቢተ ሕዝቅኤል ክፍል ተስማሚ ማጠቃለያ ነው። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የምንመለከታቸው የዋና ነገሮች ስለ ቤተ መቅደሱ የተሰጡ ዝርዝሮች ወይም የምድሪቱ አከፋፈል አልነበሩም፤ የመሥዋዕት አቀራረብ ዝርዝርም አልነበረም። ይልቁንም ታላቁ «ተስፋ»፥ ከሁሉም ታላቁ ቃል ኪዳንና አይሁድ በዘመናት ሁሉ ገና ያልተፈጸሙላቸውን የተስፋ ቃሎች የሚያረጋግጥላቸው እግዚአብሔር አንድ ቀን በመካከላቸው እንደሚኖር የሚያሳየው ተስፋ ነበር። እርሱ በዚያ ይኖራል፤ ከቶም አይተዋቸውም።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ይህ ለክርስቲያኖችም ታላቅ የተስፋ ቃል የሚሆነው እንዴት ነው? ለ) ራእይ 21፡1-4 ተመልከት። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ተስፉ የተሰጠን ነገር ምንድን ነው? ሐ) ከፍተኛ ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ይህ የተስፋ ቃል እንዴት ሊያበረታታን ይችላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/hr6DEdHcDkzLrUjQ8

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading