የትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የብሉይ ኪዳን የትንቢት መጻሕፍትን ሁለት ዐበይት ክፍሎችን ጥቀስ። ለ) በእነዚህ ሁለት ዐበይት ክፍሎች ሥር የሚገኙትን መጻሕፍት ዘርዝር።

በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የመጨረሻ ክፍል አሥራ ሰባት የነቢያት መጻሕፍት የሚገኙ መሆናቸውን ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥናታችን የሚታወስ ነው። እነዚህ የትንቢት መጻሕፍት በሁለት ዋና ክፍሎች የሚከፈሉ ሲሆን፥ የመጀመሪያዎቹ አራት መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት ይባላሉ፤ እነርሱም ኢሳያይስ፥ ኤርምያስ (ሰቆቃወ ኤርምያስን ጨምሮ)፥ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት የታላላቅ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉት በመጠናቸውና በያዙዋቸው ትንቢቶች ጥልቀት ምክንያት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የምናገኘው አሥራ ሁለቱን የብሉይ ኪዳን የመጨረሻ መጻሕፍት ነው። እነዚህ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት በመባል ይታወቃሉ። የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት የተባሉበት ምክንያት በመጠን አነስተኛና የትንቢተቹ ዝርዝርና ጥልቀት ከሌሎቹ መጻሕፍት ያነሰ በመሆኑ ነው። አይሁድ እነዚህን አሥራ ሁለት መጻሕፍት «አሥራ ሁለቱ ነቢያት» የሚል መጠሪያ በመስጠት እንደ አንድ መጽሐፍ ጠርዘዋቸዋል። የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት በአራት ሊከፈሉ ይችላሉ።

ሀ. ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት (ሆሴዕ፥ አሞጽ ምናልባትም ኢዩኡል)፥

ለ. ከምርኮ በፊት ለደቡብ የይሁዳ መንግሥት ያገለገሉ ነቢያት (ሚክያስ፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስና ምናልባት ኢዩኤል)፥ 

ሐ. በአሕዛብ መንግሥታት ላይ ፍርድን ያወጁ ነቢያት (ዮናስ፥ አብድዩ፥ ናሆም)፥ 

መ. ከምርኮ መልስ በኋላ ያገለገሉ ነቢያት (ሐጌ፥ ዘካርያስና ሚልክያስ) ናቸው።

በእንግሊዝኛውና በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ መካከል የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት የአቀማመጥ ቅደም ተከተልን በሚመለከት ልዩነቶች አሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የአቀማመጥ ቅደም ተከተሉን የወሰደው ከዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፥ አማርኛው ደግሞ ከዕብራይስጥ ወደግሪክ ከተተረጐመው መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ በመሆኑ ነው። በዚህ ጥናታችን ውስጥ በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ቀደም ተከተል መሠረት እነዚህን መጻሕፍት እንመለከታለን።

አብዛኛዎቹ የታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አቀማመጥ በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት አይደለም። መጻሕፍቱ የተጻፉበትን ጊዜ ስለማይገልጹ አንዳንዶቹ መጻሕፍት መቼ እንደተጻፉ ለመናገር ምሁራን በአሳብ ይለያያሉ። በተለይ ትንቢተ አብድዩና ኢዩኤል መቼ እንደተጻፉ መወሰን በጣም አስቸጋሪ ነው። አንዳንዶቹ እነዚህ ሁለት መጻሕፍት ቀደምት የትንቢት መጻሕፍት (ከ840-835 ዓ.ዓ. የተጻፉ) እንደሆኑ ሲናገሩ፥ ሌሎች ግን ትንቢተ አብድዩና ኢዩኤል በ600 ዓ.ዓ. እንደተጻፉ ይገምታሉ። አሁን ባሉበት ቅደም ተከተል መሠረት የሚገኙት ለምን እንደሆነ አናውቅም። አሥራ ሁለቱ የነቢያት መጻሕፍት በጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት የሚገኙ ቢሆኑ ኖሮ፥ ቅደም ተከተላቸው የሚከተለው ሊሆን ይችል ነበር፡- ዮናስ፥ አሞጽ፥ ሆሴዕ ሚክያስ (ከ750-700 ዓ.ዓ.) ናሆም፥ ዕንባቆም፥ ሶፎንያስ፥ አብድዩ፥ ኢዩኤል (ከ650-586 ዓ.ዓ.) ሐጌ፥ ዘካርያስ፥ ሚልክያስ (ከ520-420 ዓ.ዓ.)

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ብዙ ጊዜ ከማይነበቡና ካልታወቁ መጻሕፍት መካከል ዋናዎቹ አሥራ ሁለቱ የነቢያት መጻሕፍት ናቸው። የእግዚአብሔር ቃል ቢሆኑም እንኳ የሚያነብቡአቸው ጥቂት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። በእግዚአብሔር ሙሉ ፈቃድ ውስጥ እንድንኖር የሚረዱንና ከሕይወታችን ጋር ልናዛምዳቸው የምንችል በርካታ መንፈሳዊ እውነቶችን ከእነዚህ መጻሕፍት እናገኛለን። የእነዚህን መጻሕፍት መልእክት አንድ ጊዜ ከተረዳን መልእክቱን በማድነቅ፥ የቤተ ክርስቲያናችንን ምእመናን ለማስተማር እንጠቀምበታለን።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ከአንድ ሰው ጋር ኅብረት በማድረግ ሊያድነውና ቢወደውም ከጊዜ በኋላ ሊተወውና በዘላለም ሞት ሊቀጣው ይችላልን? መልስህን አብራራ። ለ) ስለዚህ ጉዳይ ያለህን አመለካከት የሚደግፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ዘርዝር።

ትንቢተ ሆሴዕ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላለው ፍቅር የሚናገር መጽሐፍ ነው። ይህም ከሰው ፍቅር የተለየ አስደናቂ ነው። እግዚአብሔር ከኃጢአታቸው ተመልሰው እርሱን ለመታዘዝ ጨርሶ ፈቃደኞች ያልሆኑትን ሕዝቡን እስራኤልን ለመቅጣት የወሰነው በፍቅር ነበር። እግዚአብሔር ይህንን ያደረገው ከኃጢአታቸው ሊያነጻቸው እንጂ ሊያጠፋቸው አልነበረም። እግዚአብሔር ሕዝቡን ሙሉ ለሙሉ እንደማያጠፋቸውና እነርሱን መውደዱን እንደማያቋርጥ ነገር ግን በዘመናት ሁሉ ለእነርሱ ያለውን ፍቅር እንደሚጠብቅ በፍቅር ቃል ገባላቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመመለስና ለመባረክ ቃል ገብቶ ነበር። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ያለውን ፍቅር ማቋረጥ የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም።

ይህ እውነት ዛሬ እኛንም የሚመለከት ነው። በፍቅር እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ይቀጣናል። ይህ እርሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያመለክት በመሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያሳየናል (ዕብራውያን 12፡5-11)። ከእግዚአብሔር ወይም ከፍቅሩ ሊለየን የሚችል አንዳችም ነገር እንደሌለ እግዚአብሔር ቃል ገብቶልናል። (ሮሜ 8፡38-39)። ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ እግዚአብሔር ፍቅሩን ከእኛ አይወስድም። ከእግዚአብሔር ጋር ወዳለ እውነተኛ ኅብረት አንድ ጊዜ ከገባን፥ የእርሱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከሆንን፥ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ስጦታውን ከተቀበልን የእግዚአብሔር ፍቅር ለዘላለም ከእኛ አይወሰድም። ይህ እውነት አንድ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ልጅ እንዳልሆነ በሚሰማው ወይም ትልቅ ኃጢአት በሠራ ጊዜ ከፍተኛ ዋስትናና መጽናናት ሊሰጠው ይገባል። 

የትንቢተ ሆሴዕ ጸሐፊ 

ትንቢተ ሆሴዕ የተጻፈው ሆሴዕ በተባለ ሰው ነው። ሆሴዕ የሚለው የዕብራይስጥ ስም ኢየሱስ የሚለውን ስም (ማቴዎስ 1፡21) ካስገኘው ኢያሱ ከሚለው የዕብራይስጥ ስም (ዘኁልቁ. 13፡16) ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፥ ትርጕሙም ረዲኤት፥ ነፃነት መውጣት ወይም ደኅንነት ማለት ነው። መጽሐፉ ስያሜውን ያገኘው ከጸሐፊው ስም ነው።

ስለ ሆሴዕ የምናውቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው። በእስራኤል ተወልዶ ከዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የእስራኤል መንግሥት እስከወደቀበት እስከ 722 ዓ.ዓ. እና እስከ ይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ድረስ ለእስራኤል ሕዝብ አገልግሏል። የሆሴዕ የነቢይነት አገልግሎት ከ760-715 ዓ.ዓ. ድረስ ሳይዘልቅ አልቀረም።

ሆሴዕ ጎሜር የምትባል ሴት አግብቶ፥ ኢይዝራኤል፥ ስሩሃማና ሉዓሚ የተባሉ ሦስት ልጆችን ወልዷል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ የነቢዩን ሕይወት ለእስራኤል ልጆች ሕያው መልእክት አድርጎ ተጠቅሞበታል። እግዚአብሔር በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ቢፈርድም እንኳ የማያልቅ ፍቅር ለእነርሱ እንዳለው ለማስተማር የሆሴዕን ቤተሰብ ታሪክ ተጠቅሞበታል።

ትንቢተ ሆሴዕ የተጻፈው ከ760-722 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ነበር። ትንቢተ ሆሴዕ የይሁዳን ነገሥታትና ሕዝቅያስን ስለሚጠቅስ (ሆሴዕ 1፡1) ተጽፎ ያለቀው ከእስራኤል ውድቀት በኋላ በይሁዳ ሳይሆን አይቀርም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d