ሆሴዕ የኖረበት ዘመን እጅግ አስቸጋሪና ከባድ ነበር። ምንም እንኳ የተወለደው ከሰሎሞን ዘመን በኋላ እስራኤል አይታ የማታውቀው የተትረፈረፈ ብልጽግናና ሰላም በሞላበት ጊዜ ቢሆንም ሆሴዕ ግን የእስራኤልን ጥፋትና ውድቀት መስክሯል። ሆሴዕ ከአሦራውያን ጋር ውጊያ በተካሄደበትና የእስራኤል መንግሥት በተደመሰሰበት ዘመን ኖረ። ከእስራኤል ውድቀት በኋላ ምን እንዳደረገ የምናውቀው ነገር የለም። ከእስራኤል ውድቀት በኋላ የይሁዳ ንጉሥ እስከነበረው እስከ ሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት ድረስ እንደኖረ ተገልጾአል።
ሆሴዕ በእስራኤል ከተወለዱና መጻፍ ከሚችሉ ጥቂት ነቢያት አንዱ ነበር። በእስራኤል የተወለደና መጻፍ የሚችል ሌላው ነቢይ ዮናስ ነበር።
ሆሴዕ በተወለደ ጊዜ ንጉሡ ዳግማዊ ኢዮርብዓም ነበር። ኢዮርብዓም ከኢዩ ወገን የሆነ የነገሥታት ዘር ነበር። በፖለቲካ አንጻር ታላቅ ንጉሥ ነበር። አባቱ ዮአስ እስራኤልን ከሶርያ ጭቆና ነጻ ያወጣ ሰው ነበር። ዳግማዊ ኢዮርብዓም በዳዊትና በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት የእስራኤል የነበሩትን ግዛቶች ሁሉ ለማስመለስ ችሏል። እስራኤል በጳለስጢና ምድር ከነበሩ ነገሥታት ሁሉ እጅግ ኃያል ሆነች። ዳግማዊ ኢዮርብዓም ዋና ዋና የንግድ መተላለፊያዎችን ሁሉ ስለተቆጣጠረ እስራኤልን ባለጠጋ መንግሥት አድርጓት ነበር። ትልልቅ ሕንጻዎችን፥ ወታደራዊ መከላከያዎችን ገንብቶ ነበር። የዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት በሰው አመለካከት ለእስራኤል ሕዝብ እጅግ መልካም ጊዜ ነበር።
በመንፈሳዊ ረገድ ግን ነገሮች ሁሉ እጅግ ተበላሽተው ነበሩ። እግዚአብሔርን በማምለክ ረገድ በታማኝነት የጸኑ ጥቂት ሰዎች ነበሩ ሕዝቡ በአልን የመሳሰሉ ሐሰተኞች አማልክትን ያመልኩ ነበር። ሃይማኖታዊ መሪዎች በሥነ-ምግባር እጅግ የተበላሹ ነበሩ። ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ ውሸትን የሚያስተምሩ ሐሰተኞች ነቢያት ነበሩ፡፡ ነገሥታቱ ሰካራሞችና የገዛ ሕዝባቸውን የሚያስጨንቁ ነበሩ። የእስራኤል ሕዝብ ነገሮች ሁሉ መልካም የሆነለት ቢመስለውም፥ ሆሴዕ የእስራኤል ሕዝብ ፈጥኖ እንደሚደመሰስና የኢዩ ንጉሣዊ የዘር ሐረግም እንደሚያበቃ ተናገረ። ነቢዩ ትንቢቶቹ ምን ያህል ፈጥነው እንደሚፈጸሙ ምናልባት አልተገነዘበም ይሆናል።
ኢዮርብዓም በ753 ዓ.ዓ. ሲሞት፥ መንግሥቱ ፈጥኖ ተፍረከረከ። ስለ መጨረሻዎቹ የእስራኤል ነገሥታት የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል፡-
1. የኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ መንገሥ በጀመረ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በሰሎም ተገደለ። ይህም የኢዩ ሥርወ መንግሥት ፍጻሜ ነበር።
2. ሰሎም ለአንድ ወር ገዛና በምናሔም ተገደለ።
3. ምናሔም መንገሥ በጀመረ ጊዜ አገሪቱ ባለጠጋ ነበረች። በ745 ዓ.ዓ. ግን ቴልጌልቴልፌልሶር የአሦርን በትረ መንግሥት በመጨበጥ የአሦርን መንግሥት ወደ ምዕራብ አሰፋ። ይህ የአሦር መንግሥት ታላቁ የዓለም መንግሥት በመሆን ለ100 ዓመታት ገናና ሆኖ ቆየ።
አሦራውያን የንግድ መሥመሮችን ሁሉ እየተቈጣጠሩ በሄዱ ቍጥር እስራኤል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ያሠቃያት ጀመር። አሦራውያን ያሸነፏቸውን ሕዝቦች የሚቆጣጠሩበት አዲስ ዘዴ ማበጀት ጀመሩ። ካሸነፏቸው ሕዝቦች መካከል በከፍተኛ ቊጥር የሚገመቱትን ወደ ሌላ አገር በመውሰድ ያሰፍሯቸው ጀመር። ሌሎች ዝርያዎችን ደግሞ በጦርነት ወደ ያዙአቸው አገሮች ያመጡ ጀመር። በዚህ ዓይነት የተለያዩ ዝርያዎች እንዲቀላቀሉ በማድረግ በአሦር ላይ ማመፅን አስቸጋሪ አደረጉት። በ722 ዓ.ዓ. በእስራኤል ላይ የተፈጸመው ይህ ነበር።
ምናሒም የተባለው የእስራኤል ንጉሥ የአሦራውያን ጦር እንዳይወጋው ለአሦር መንግሥት በመገበር የዚህ መንግሥት አገልጋይ ሆነ።
4. ምናሴ ከሞተ በኋላ ልጁ ፋቂስያስ በፋቁሔ እስከተገደለ ድረስ ለሁለት ዓመታት ብቻ ነገሠ።
5. ፋቁሑ የአሦርን መንግሥት አገዛዝ ለማስወገድ ሞከረ። ከሶርያ ጋር በመተባበር አሦርን ለማጥቃት ያልተባበረችውን ይሁዳን ወጉ። ይህም ድርጊት አሦርን እጅግ ስላስቈጣት ሶርያን በማጥቃት በ732 ዓ.ዓ. ፈጽማ አጠፋቻት። ከዚያም ፋቁሑ ተገደለ።
6. የእስራኤል የመጨረሻ ንጉሥ የሆነው የኤላ ልጅ ሆሴዕ በአሶር ቊጥጥር ሥር የሚኖር የአሦር መንግሥት መሣሪያ ነበር። ይሁን እንጂ በ727 ዓ.ዓ. ቴልጌልቴልፌልሶር ሲምት ለማመፅ ወሰነ። አዲሱ የአሦር ንጉሥ ሰልምናሶር አምስተኛ እስራኤልን ወጋ። ከሦስት ዓመታት ጦርነት በኋላ የሰማርያ ከተማ ተያዘችና ተደመሰሰች። የእስራኤል መንግሥት በ722 ዓ.ዓ. ተደመሰሰ። አብዛኛው ሕዝብ በመካከለኛው ምሥራቅ ወደሚገኙ የአሕዛብ መንግሥታት በምርኮ ተወሰዱ። አሦራውያን ሌሎች ሕዝቦችን ይኖሩ ዘንድ ወደ እስራኤል አመጡ። እነዚህ አሕዛብ ከእስራኤላውያን ጋር በመጋባት በአዲስ ኪዳን ዘመን ሳምራውያን ተብለው የሚጠሩትን ሕዝቦች አስገኙ። ሆሴዕ የንጉሥ ሕዝቅያስን ስም ስለሚጠቅስ በምርኮ የተወሰደ አይመስልም ለመኖር ወደ ይሁዳ ሳይሄድ አልቀረም። የሚያውቃቸውና የሚወዳቸው በርካታ ሰዎች ግን በምርኮ ሳይወሰዱ አልቀሩም። እግዚአብሔር በእርሱ በኩል የተናገራቸው ትንቢቶች ሲፈጸሙ በማየት ልቡ በኃዘን ሳይሞላ አልቀረም። ሆሴዕን የሚያበረታታው ብቸኛው ነገር ሕዝቡ ከምርኮ እንደሚመለሱ እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል ብቻ ነበር።
ሆሴዕ የነበረበት ዘመን ብዙ አለመረጋጋትና ለውጥ የሚታይበት ነበር። እግዚአብሔር የሰጠውን መልእክት በቅድሚያ መንገር ሲጀምር ሕዝቡ በሰላምና በታላቅ ብልጽግና ውስጥ ስለነበሩ አይሰሙትም ነበር።
እውነት ጥያቄ፥ ብዙ ጊዜ ሀብታም የሆኑና ምንም ችግር የሌለባቸው ሰዎች ወንጌልን ለመቀበል የሚቸገሩት ወይም ከባድ የሚሆንባቸው ለምንድን ነው?
ሕዝቡ በአሦራውያን ምክንያት አለመረጋጋትና ጭቆና በነበረባቸው ጊዜ እንኳ ሰምተው ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች አልነበሩም። ሆሴዕ ግን ለእግዚአብሔር ባለው ታማኝነት በመጽናት እርሱ የሰጠውን መልእክት በግልጽ ያስተላልፍ ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡