ትንቢተ ዕንባቆም መግቢያ

የውይይት ጥያቄ፥ የምትመለከተው ክፉ ተግባር ከመብዛቱ የተነሣ እጅግ ታክተህ እግዚአብሔር ይህንን ተግባር የፈጸመውን ሰው ወይም ሰዎች የማይቀጣው ለምን እንደሆነ ተደንቀህ ታውቃለህን? ሁኔታውን አብራራ።

ምናልባት ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ወቅት በጣም ብዙ ክፋት ተመልክተን በመደነቅ እግዚአብሔር ይህንን ነገር ለምን እንደማይቀጣው ጠይቀን ይሆናል። ዙሪያችንን ስንቃኝና ሰዎች ኃጢአት ሲሠሩ፥ ድሆች መጠቀሚያ ሲደረጉ ትክክለኛ ፍርድን በጉቦ የሚያጣምሙ ሰዎች ያለምንም ቅጣት ተዝናንተው ሊኖሩ መመልከት፥ ልባችንን በኃዘን ይሞላል። ዓለም በቅን ፍርድና በጽድቅ የምትሞላበትን ጊዜ በልባችን እንናፍቃለን። ክፋት እስካልተቀጣ ድረስ ይህ ቀን ሊመጣ እንደማይችልም እንገነዘባለን። በዚህ አንጻር እግዚአብሔር ክፋትን ለምን እንደማይቀጣና ለእግዚአብሔር ለመኖር አጥብቀው የሚፈልጉትን ሰዎች ለምን እንደማይባርክ በማሰብ እንደነቃለን።

ነቢዩ ዕንባቆምም ከዚህ ጉዳይ ጋር ግብግብ ገጥሟል። የደም መፍሰስና ክፋት ያለ ቅጣት በዙሪያው ተንሰራፍቶ መመልከት ሰልችቶት ነበር። በመሆኑም ክፋትን በመቅጣት ጽድቁን እንዲገልጥ ወደ እግዚአብሔር ይጮህ ነበር፤ እግዚአብሔር የሚሰጠውን መልስ ግን አልጠበቀም ነበር። ትንቢተ ዕንባቆም የእግዚአብሔርን የጽድቅና የቅን ፍርድ ባሕርይ በሚመለከትበት ጊዜ ሊረዳ ያልቻላቸውን ነገሮች በሚመለከት ያቀረባቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች የምናገኝበት ነው።

ትንቢተ ዕንባቆም ከታናናሽ ነቢያት መጻሕፍት አንጻር ሲታይ ልዩ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፉ ውስጥ አንዳንድ ትንቢቶች በመኖራቸው ከነቢያት መጻሕፍት ቢመደብም የበለጠ የሚመሳሰለው ከጥበብ መጻሕፍት ጋር ነው። ከመጽሐፈ ኢዮብ ጋር የሚመሳሰለው የእግዚአብሔርን ቅንና ትክክለኛ ፍርድ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ክፉ ነገሮች አንጻር የሚመለከት ስለሆነ ነው።

የትንቢተ ዕንባቆም ጸሐፊ

የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዕንባቆም ነው። እንደ ናሆም ሁሉ ስለ ዕንባቆምም የምናውቀው ነገር የለም። መጽሐፉ በዚህ ዘመን የነበሩት ነገሥታት እነማን እንደነበሩ አይገልጽም። ዕንባቆም የት ይኖር እንደነበር አልተጻፈም። ከአዋልድ መጻሕፍት መካከል አንዱ በሆነው «ቤልና ድራጎን» በተባለው (በአልና ክንፍ ያለውና እሳት የሚተፋ ፍጡር) መጽሐፍ ውስጥ ዕንባቆም በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሉ ሳለ ዳንኤልን እንዴት እንደረዳው የሚናገር ታሪክ ብናገኝም፥ ታሪኩ እውነት አይመስልም።

መጽሐፉ መቼ እንደተጻፈ ለማወቅ፥ አሁንም መጠቀም የምንችለው በመጽሐፉ ውስጥ ባለው መረጃ ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈበትን ጊዜ በሚመለከት ሁለት ዐበይት አመለካከቶች አሉ፡-

1. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ባቢሎን ኢየሩሳሌምን በ605 ዓ.ዓ. ለመጀመሪያ ጊዜ ከማጥቃቷ በፊት ከ609-605 ዓ.ዓ. ነው። ይህም በንጉሥ ኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ገደማ ነበር። 

2. ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከ640-626 ዓ.ዓ. ነው። ትንቢተ ዕንባቆም የባቢሎን የዓለም ኃያል መንግሥት መሆን ጨርሶ ያልተጠበቀ ነገር እንደነበር የሚያሳይ ይመስላል። የባቢሎን መንግሥት ገናና መሆን የጀመረው ባቢሎን ከአሦር ተለይታ ነጻ በሆነችበት በ626 ዓ.ዓ. ነበር። ስለዚህ ትንቢተ ዕንባቆም የተጻፈው ከዚህ ጊዜ በፊት ይመስላል። ይህ መጽሐፍ የተጻፈበት ነው ሊባል የሚችለው የመጨረሻው ጊዜ 615 ዓ.ዓ. ነው። ምክንያቱም የአሦር መንግሥት በባቢሎን ሙሉ በሙሉ የተሸነፈው በ612 ዓ.ዓ. ነበርና ከዚህ በኋላ ይህ ትንቢት ለዕንባቆም ምንም ትርጉም የሌለው ይሆናል። 

ዕንባቆም ትንቢት የተናገረው ኢዮስያስ በይሁዳ ተሐድሶ ከመጀመሩ በፊት በነበረው የመጀመሪያው ዘመነ መንግሥቱ ገደማ እንደሆነ ዘመኑ ከሁሉም የሚሻል ይመስላል። ኢዮስያስ ገና በልጅነቱ ሆኖ የነገሠው በ640 ዓ.ዓ. ነበር። ያም በይሁዳ ፍትሕ ያልነበረበት ክፉ ጊዜ ነበር። የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ የይሁዳን ሕዝብ መለወጥ የጀመረው ቆይታ በ626 ዓ.ዓ. ገደማ ነበር። ስለዚህ ዕንባቆም የኖረውና በአካባቢው ከነበረው የፍትሕ መዛባት ጋር የታገለው በንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ገደማ ይመስላል። ምናልባት እርሱም የተሳተፈበት የንጉሥ ኢዮስያስ ተሐድሶ ሕዝቡን መለወጥ ሲጀምር እጅግ ሳይደሰት አልቀረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ይሁዳን በእርሱ ዘመነ መንግሥት እንደሚደመስስ መናገሩን ያውቅ ነበር። ስለዚህ ሸክም በተጫጫነው ልብ የባቢሎንን ምጥቀት ከመመልከቱም፥ ኢየሩሳሌምም ስትደመሰስ ምስክር እንድነበረ አይጠረጠርም።

ዕንባቆም ባገለገለበት ዘመን ሶፎንያስና ኤርምያስም አገልግለዋል። 

የትንቢተ ዕንባቆም ሥረ መሠረት 

የምናሴ ዘመነ መንግሥት (697-642 ዓ.ዓ.) የይሁዳ ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ወደ መጨረሻው ዓዘቅት የወረደበት ጊዜ ነበር።

ምናሴ ሕዝቅያስ ያካሄደውን ተሐድሶ ሁሉ ከመቅጽበት አበላሸ። የጣዖት አምልኮ እጅግ ተስፋፋ። ለጣዖት አምልኮ የሚሆን መሠዊያ አሠርቶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በማኖር የራሱን ልጅ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። በሃይማኖታዊ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፥ በሥነ-ምግባርና በማኅበራዊ ጉዳዮችም ሕዝቡ ፊታቸውን ከእግዚአብሔር በመመለሳቸው ማኅበራዊ ክፋት እጅግ የተለመደ ነገር ሆነ። ምናሴ ለመስበክና ሕዝቡን ስለ እግዚአብሔር ፍርድ ለማስጠንቀቅ የፈለጉትን ነቢያት ሁሉ አስገደለ። ይህም እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ፍርድ ለማምጣት እንዲወሰን አደረገው። ምናሴ በአሦር ላይ ለማመፅ በሞከረ ጊዜ፥ ተማርኮ ወደ አሦር ተወሰደ። በምርኮ ምድር ንስሐ ገባና ልቡ ተለወጠ፤ ከምርኮ ተለቆ ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜ ቀድሞ የፈጸማቸውን ክፉ ተግባራት ለማሻሻል ቢሞክርም አልቻለም።

ከምናሴ ሞት በኋላ ልጁ አሞን ነግሦ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ተገደለ። የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ግን ከአባቱ በተለየ መንገድ እግዚአብሔርን ተከተለ። ሥልጣን በያዘ ጊዜ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበር። በይሁዳ መንፈሳዊ ተሐድሶን ለማምጣት የወሰነውና ርምጃ የወሰደው ከነገሠ ከአሥራ ስምንት ዓመት በኋላ በሃያ ስድስት ዓመቱ ነበር። ዕንባቆም ትንቢቱን የተቀበለው ይህ መንፈሳዊ ተሐድሶ ከመካሄዱ በፊት ሳይሆን አይቀርም። ኢዮስያስ ያመጣው መንፈሳዊ ተሐድሶ በሕዝቡ መንፈሳዊ፥  ሥነ ምግባራዊና ማኅበረሰባዊ ሕይወት ላይ ለውጥ ከማምጣቱ በፊት በጦርነት ሞተ። ልጆቹም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእግዚአብሔር ዞር አሉ። ዕንባቆም ስለ ባቢሎን ምርኮ የተናገረው ትንቢት በ586 ዓ.ዓ. ተፈጸመ።

ራቅ ብሉ በስተሰሜን ምሥራቅ ይገኝ የነበረውና ለብዙ ምዕተ ዓመታት ኃያል የነበረው የአሦር መንግሥት በእርስ በርስ ጦርነት ይፈራርስ ጀመር። ባቢሎን በ627 ዓ.ዓ. በአሦር መንግሥት ላይ ያካሄደችው ዓመፅ ተሳካላት። በ612 ደግሞ የአሦርን ዋና ከተማ ነነዌን አሸነፈች። የአሦር ጦር እስከ 609 ዓ.ዓ. ድረስ ውጊያውን ሳያቋርጥ ቢታገልም፥ የቁጥጥሩ ኃይሉ ተንኮታኩቶ ነበር። ከለዳውያን በመባል የሚታወቁት ባቢሎናውያን ኃይላቸው እንደገና እየገነነ ሄደ፡፡ ይሁዳ በተከታታይ ለማመፅ የሞከረች ቢሆንም፥ ባቢሎን በ605 ዓ.ዓ. ኢየሩሳሌምን ደመሰሰቻት። በዚህም የዕንባቆም ትንቢት ይፈጸም ጀመር። የባቢሎን ኃያል መንግሥት ለ70 ዓመታት ብቻ ቆየና በ539 ዓ.ዓ. በሜዶንና በፋርስ መንግሥት ተደመሰሰ። እግዚአብሔር ከ100 ዓመታት በፊት በዕንባቆም በኩል እንደተናገረው ባቢሎንን ስለ ኃጢአትዋ ቀጣት።

የውይይት ጥያቄ፥ ስለ ዕንባቆም ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ያገኘሃቸውን ዋና ዋና እውነቶች ዘርዝር።

የትንቢተ ዕንባቆም አስተዋጽኦ 

1. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው የመጀመሪያ ጥያቄ፡- እግዚአብሔር በይሁዳ የሚታየውን ክፋት ለምን አይቀጣም? (ዕንባቆም 1፡1-4)

2. የእግዚአብሔር የመጀመሪያ መልስ፡- እግዚአብሔር ይሁዳን ለመቅጣት ባቢሎናውያንን ይልካል (ዕንባቆም 1፡5-11)።

3. ዕንባቆም ለእግዚአብሔር ያቀረበው ሁለተኛ ጥያቄ፡- ጻድቅና ትክክለኛ ፈራጅ የሆነው እግዚአብሔር ጥቂት ክፋት ያለባትን ይሁዳን እጅግ ክፉ በሆኑት ባቢሎናውያን እንዴት ይቀጣል? (ዕንባቆም 1፡12-2፡1)። 

4. የእግዚአብሔር ሁለተኛ መልስ፡- 

ሀ. ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል (ዕንባቆም 2፡2-5)፣

ለ. ባቢሎናውያንም ይቀጣሉ (ዕንባቆም 2፡6-20)። 

5. የዕንባቆም ጸሎት፡- ፍርድን በምታመጣበት ጊዜ ምሕረትህን አስብ (ዕንባቆም 3፡1-19)።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: