የትንቢተ ናሆም ዓላማ እና ዋና ዋና ትምርቶች

የትንቢተ ናሆም ዓላማ

ናሆም ብቸኛ ዓላማው የነነዌን ውድቀት ማመልከት ነበር። እንደ ዮናስ ወደ ነነዌ በመሄድ መልእክቱን አላቀረበም። መልእክቱን ያቀረበው በይሁዳ ሆኖ ነበር። የናሆም መልእክት አሦርን ስለሚመጣባት ሽንፈት ለማስጠንቀቅ የተሰጠ አልነበረም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ለነበሩት ለአይሁድ የተሰጠ የማበረታቻ መልእክት ነበር። ለብዙ ዓመታት በአሦር መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበሩ። አሁን ግን ነነዌ የምትደመሰስበት ጊዜ እንደደረሰ እግዚአብሔር ይነግራቸዋል። እግዚአብሔር የአሦርን የአገዛዝ ዘመን ወደ ፍጻሜ ያመጣዋል። ከመቶ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ በአሕዛብ ላይ ገዥ የነበሩትን አሦራውያንን ይቀጣል። እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሉዓላዊ ሥልጣን አለው። እርሱ ጻድቅና ትክክለኛ ፈራጅ ስለሆነ ነነዌ ፍርድ የምትቀበልበት ዘመን ደረሰ። 

የትንቢተ ናሆም ዋና ዋና ትምህርቶች 

1. የእግዚአብሔር ባሕርይ

ሀ. የእግዚአብሔር ትዕግሥትና ምሕረት፡- የትንቢተ ናሆም አብዛኛው ክፍል በእግዚአብሔርና በባሕርዩ ላይ የሚያተኩር ነው። በአንድ በኩል እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየና በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መሸሽጊያ እንደሆነ ተገልጿል (ናሆም 1፡3፡ 7)። እግዚአብሔር በነነዌ ላይ፥ በተለይም ደግሞ የዮናስን መልእክት ሰምተው ንስሐ ከገቡ በኋላ፥ ሳይፈርድ የዘገየው በዚህ ባሕርዩ ምክንያት ነበር።

ለ. የእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ፡- እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ብቻ አይደለም። ነገር ግን የቁጣ አምላክም ነው። እንደሚቀጣው በተናገረው ኃጢአት ላይ ቁጣውን ይገልጻል (ሮሜ 11፡22 ተመልከት)። እግዚአብሔር በትንቢተ ናሆም የተገለጸው ታላቅና ኃያል ሆኖ ነው። እግዚአብሔር ፍርዱ ቢዘገይም እንኳ፥ «… በደለኛውን ንጹሕ ነህ አይልም» (ናሆም 1፡3)። የእግዚአብሔር የቅጣት ኃይል በዚህ ስፍራ ከወጀብና ከዐውሎ ነፋስ፥ ከምድር መንቀጥቀጥም ጋር ተዛምዷል። ኃይሉ እጅግ ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ታላላቅ ወንዞችን ማድረቅ ይችላል። እኛ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር የፍቅር፥ ምህረትና በጎነት ባሕርይ ላይ ከሚገባ በላይ በማተኮር፥ እርሱ የቁጣ፥ የመዓት፥ የፍርድና የበቀል አምላክ መሆኑን እንዳንዘነጋ መጠንቀቅ ይገባናል።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ፥ የፍቅርና የምሕረት አምላክ መሆኑ የሚያበረታታን እንዴት ነው? ለ) የእግዚአብሔርን የቁጣና የፍርድ ባሕርይ ስንዘነጋ ምን ይሆናል? ሐ) እግዚአብሔር ጥፋተኛውን ለመቅጣት ያለውን ውሳኔ፥ ቁጣውንና ትክክለኛ ፍርዱን ብናስታውስ ድርጊታችን እንዴት ሊለወጥ ይችላል?

ሐ. እግዚአብሔር በመንግሥታትና በሕዝቦች ላይ ያለው የበላይ ተቆጣጣሪነት፡- ምንም እንኳ ዓለም የነነዌን ውድቀት በመመልከት፥ ይህ የሆነው በባቢሎን ገናናነትና በአሦር መሪዎች ደካማነት ነው ቢልም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እግዚአብሔር በነነዌ ላይ ለመፍረድና እርሷን ለማጥፋት በመወሰኑ እንደሆነ ያስተምራል። እግዚአብሔር አሦርን የእስራኤል መቅጫ በትር አድርጎ ተጠቀመባት። አሁን ፍርድን መቀበል የአሦር ተራ ነበርና እግዚአብሔር በእርሷ ላይ ለመፍረድ ባቢሎንን ተጠቀመ። 

2. የእግዚአብሔር ፍርድ በአሕዛብና በመንግሥታት ሁሉ ላይ፡- እግዚአብሔር የሚፈርደው በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን፥ በመንግሥታትም ላይ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ተመልክተናል። እግዚአብሔር መንግሥታትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጻፉ ሕግጋት ብቻ ሳይሆን፥ በልባቸው በጻፈውም ሕግ መሠረት መኖር አለመኖራቸውን በሚመለከት ተጠያቂዎች ያደርጋቸዋል (ሮሜ 1፡18-29)። መንግሥታትና የመንግሥታት መሪዎች የእግዚአብሔርን ሕግ በግልጽ እየተቃወሙና እየጣሱ ሲኖሩ ለጊዜው ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጡ ይችሉ ይሆናል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡና ተመልሰው የእርሱን በረከት እንዲያገኙ ይፈልጋል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡8-9)። ነገር ግን የእግዚአብሔርን በረከት እንዲያገኙ ትክክለኛና ቅን ፍርድ ማለት፥ የአሕዛብን ኃጢአት ሳይቀጣ አያልፍም ማለት ነው። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ በአሕዛብ ላይ ቅጣትን ያመጣል። በአጠቃላይ ታሪክን ያየን እንደሆነ የመንግሥታትና የሕዝቦች መውደቅና መነሣት ምክንያት ተፈጥሮአዊ ክስተት ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በእያንዳንዳቸው ላይ ፍርድን ለማምጣት የሚሠራው ሥራ ጭምር ነው። 

በክፋትና በጭቆና ላይ የሚመሠረት ማንኛውም መንግሥት በመጨረሻ መውደቁ አይቀርም። እግዚአብሔር በሌሎች ላይ ባሳየችው የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር አሦርን ተጠያቂ አድርጎ እርምጃ ሊወስድባት ተቃርቦ ነበር። በጥንት ታሪክ፥ በጭካኔያቸው ከሚጠቀሱ መንግሥታት ዋናዋ የአሦር መንግሥት ነበረች። ሰዎች እጅግ ይፈሩአት ነበር። አሦራውያን ማንኛውም ሕዝብ እንዳያምፅባቸው ለማድረግ ይህንን ጭካኔ ይጠቀሙበት ነበር። ማንኛውም የዓመፅ ተግባር ምልክት ወዲያውኑ ይቀጣ ነበር። ጠላቶቻቸውን በሕይወት እያሉ ያቃጥሏቸው፥ በአሰቃቂ ሁኔታ ይገርፏቸውና አካለ ጐደሉ ለማድረግ የሰውነት ክፍሎቻቸውን ይቀራርጡ፥ ወዘተ። ነበር። ሌሎች ሕዝቦችና መንግሥታትም የዚህ ዓይነቱን እጅግ አሠቃቂ ቅጣት ከመቀበል ይልቅ መገዛትን ይመርጡ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ይህንን ክፋት ይቆጥር ስለነበር፥ የፍርዱ ቀን ደርሶ ነነዌ በሌሎች ላይ የፈጸመችውን ክፋት በሙሉ ተቀበለች።

ዛሬ የነነዌ ከተማ በዓለም ላይ የለችም። እግዚአብሔር እንደወሰነና በናሆም አስቀድሞ እንደተናገረ፥ ነነዌ እንደገና በማታንሰራራበት ሁኔታ ጠፋች።

የውይይት ጥያቄ፥ ) ይህ እውነት በታሪክ ውስጥ የቀረበው እንዴት ነው? ወይም አንተ ለዓለም ታሪክ ባለህ ግንዛቤ መሠረት የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ ናሆም 1-3 አንብብ። ሀ) ነነዌ የፈጸመቻቸውን የተለያዩ ኃጢአተች ዘርዝር። ) ናሆም በነነዌ ላይ የተነበያቸውን የተለያዩ የቅጣት ትንቢቶች ዘርዝር።

1. ፈራጅ ስለሆነው እግዚአብሔር የቀረበ መግለጫ (ናሆም 1፡1-8)

ትንቢተ ናሆም ስለ እግዚአብሔር የተለያዩ መግለጫዎችን ይሰጣል። በክፉ ሕዝብ፥ በተለይም በነነዌ ላይ ሊፈርድ የተነሣውን የእግዚአብሔርን ሥዕላዊ መግለጫ እንመለከታለን። ጽድቅን የተሞላው የእግዚአብሔር ቁጣና ኃጢአትን ለመቅጣት የነበረው ውሳኔ ኃይሉን ለማሳየት በዚህ መልኩ ተገልጾአል። እግዚአብሔር ለቁጣ የዘገየ ቢሆንም እንኳ ቁጣው ገንፍሎ የሚመጣበት ጊዜ አለ። በዚያን ጊዜ «በቁጣው ፊት የሚቆም ማን ነው?»

ዳሩ ግን ዓለምን መምሰል ለማይፈልጉና ለእግዚአብሔር በጽድቅና በመታዘዝ ለመኖር ለወሰኑ ሰዎች እግዚአብሔር መልካም ነው። በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው። 

2. ስለ ነነዌ መደምሰስ የተነገረ ትንቢት (ናሆም 1፡9-14)

ምንም እንኳ ነነዌ በእግዚአብሔር ላይ በማሤር በክፉ መንገዷ መጓዝ ብትቀጥልም እግዚአብሔር የእርስዎን መደምሰስ ወስኖ ነበር፡፡ የነነዌ ተባባሪዎች ሁሉ ሊያድኗት አይችሉም ነበር። ነነዌና የአሦር ሕዝብ ተማርከው ይሄዳሉ። ከዝርያቸው ማንም አይቀርም፤ አማልክቶቻቸው ይደመሰሳሉ፤ ልክ እንደሞተ ሰው አሦር ልትቀበር ተዘጋጅታ ነበር። 

3. የይሁዳ ነፃ መውጣት (ናሆም 1፡15)

የነነዌ ውድቀት ለአሦር ሕዝብ ክፉ ወሬ ቢሆንም፥ ረዘም ላለ ጊዜ በከባድ ሁኔታ በአሦራውያን ሲሠቃዩ ለነበሩት የይሁዳ ሰዎች ግን መልካም ወሬ ነበር። ስለዚህ የአሦርን ውድቀት የሚያመለክተውን የምሥራች ይዞ የመጣው መልእክተኛ የተባረከ ነበር። አሁን ይሁዳ አሦርን ሳትፈራ እግዚአብሔርን ማምለክ ትችላለች።

4. ስለ ነነዌ ውድቀት የቀረበ ገለጻ (ናሆም 2-3)

የትንቢተ ናሆም የመጨረሻ ሁለት ምዕራፎች በተለያዩ መንገዶች የነነዌን ውድቀት ይገልጻሉ። የነነዌ መወረርና መበዝበዝ ተገልጿል። ነነዌ ኀፍረተ ሥጋዋ በሰው ሁሉ ፊት ከተገለጠ ጋለሞታ ጋር ተወዳድራ ቀርባለች። የነነዌ ኃጢአት በዝርዝር ተገልጿል። ነነዌ እጅግ ታላቅ ከተማ ብትሆንም፥ በመጨረሻ አንድም ሰው በነነዌ አይቀርም።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ከትንቢተ ናሆም የተማርሃቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ግለጽ። ለ) አንተ ባለህበት ቤተ ክርስቲያን ለሚገኙ ክርስቲያኖች እነዚህን ትምህርቶች ማስተማር ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: