የትንቢተ ዘካርያስ መግቢያ

ትንቢተ ሐጌ ያተኮረው እግዚአብሔር የሚመለክበትን ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ ነበር። ዳሩ ግን አንድን ሕንጻ ለቤተ መቅደስነት መሥራት ትክክለኛ የሆነ አምልኮ ለመካሄዱ ዋስትና አይደለም። ብሉይ ኪዳን ለእውነተኛ አምልኮ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል (ለምሳሌ፡- 1ኛ ሳሙኤል 15፡22-24፤ መዝሙር (51)፡16-17)። ከነቢዩ ሐጌ በኋላ ሁለት ወር ዘግይቶ አገልግሎቱን የጀመረው ነቢዩ ዘካርያስ ተገቢና ትክክለኛ በሆነ አምልኮ አስፈላጊነት ላይ ያተኩራል። ዘካርያስ ንስሐ እንዲገቡና መንፈሳዊ ተሐድሶ እንዲኖራቸው ለሕዝቡ ጥሪ አደረገ፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝብ በንጹሕ ልብና እግዚአብሔርን ለማምለክ በሚፈልግ ዝንባሌ ወደ እግዚአብሔር በሚቀርብበት ጊዜ ከሁሉም የበለጠ ለአምልኮ የሚያስፈልገውን ነገር አሟልተዋል ማለት ነው። አምልኮ የሚፈልገው ሕንጻን ሳይሆን በሚገባ የተዘጋ ልብን ነው፡፡ ስለዚህ ዘካርያስ የቤተ መቅደሱ ሥራ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በሚገባ እንዲያመልኩ በቅድሚያ የሕዝቡን ልብ ለማዘጋጀት ጥሯል።

የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ለአምልኮ የሚሆን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ሳይኖራቸው፥ የአምልኮ ሥርዓትን ብቻ በመፈጸም እግዚአብሔር የማይቀበለውን አምልኮ የሚያቀርቡት እንዴት ነው? ለ) ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለትክክለኛና ለእውነተኛ አምልኮ ማዘጋጀት እንዴት ይችላሉ? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አባሎቻቸው በየእሑዱ ለሚያካሄዱት የአምልኮ ፕሮግራም ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

የትንቢተ ዘካርያስ ጸሐፊ

ዘካርያስ 1፡1 «የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዘካርያስ እንዲህ ሲል መጣ» በሚል ዓረፍተ ነገር ስለሚጀምር ቃሉ የመጣው ወደ ዘካርያስ እንደሆነ እንመለከታለን። ስለዚህ የትንቢተ ዘካርያስ ጸሐፊ ዘካርያስ እንደሆነ ለመገመት እንችላለን።

ዘካርያስ ልክ እንደ ኤርምያስና ሕዝቅኤል ነቢይ ብቻ ሳይሆን፥ ካህንም ነበር፡፡ ዘካርያስ የተወለደው ከሌዊ ነገድ ከአሮን የዘር ግንድ ነበር። የተወለደውም በባቢሎን አገር በምርኮ ዘመን ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም በ538 ዓ.ዓ. አይሁድ ወደ አገራቸው በተመለሱ ጊዜ ከአያቱ ከዒዶ ጋር አብሮ የተመለሰ ይመስላል። የዘካርያስ አያት ዒዶ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱት ዐበይት ካህናት ኣንዱ ነበር (ነህ. 12፡4 ተመልከት)። በኋላ ኢያሱ ሊቀ ካህን በነበረ ጊዜ ስለ ዘካርያስ አባት ምንም ነገር ስለማንሰማ እርሱ ሞቶ ዘካርያስ የቤተሰቡን የክህነት ሥራ ተክቶ ሳይሠራ አልቀረም (ነህምያ 12፡16)። የዘካርያስ አባት በራክዩ በመጽሐፈ ዕዝራና ነህምያ ውስጥ ስላልተጠቀሰ ብዙ ሰዎች ዘካርያስ ገና ወጣት ሳለ አባቱ በመሞቱ፥ ያደገው በአያቱ በዒዶ እጅ እንደሆነ ይስማማሉ።

ዘካርያስ የነቢይነት አገልግሎቱን የጀመረው ሐጌ ማገልገል ከጀመረ ከሁለት ወራት በኋላ ስለነበር፥ ሁለቱም በኣንድነት አገልግለዋል (ዕዝራ 5፡1፤ 6፡14 ተመልከት)። ይህ ማለት ዘካርያስ አገልግሎቱን የጀመረው በ520 ዓ.ዓ. ነበር ማለት ነው። ይሁን እንጂ የዘካርያስ አገልግሎት ከሐጌ ኣገልግሎት ለበለጠ ጊዜ ቆይቷል። የመጨረሻው ትንቢቱ በ518 የተናገረው ነበር። ዳሩ ግን ዘካርያስ 9-12 የተጻፈው በዘካርያስ ሕይወት መጨረሻ ገደማ ነበር።

መጽሐፉ በአጠቃላይ በዘካርያስ ብቻ ወይም በሌሎች ሁለትና ሦስት ሰዎች ስለ መጻፉ ምሁራን ክርክር ይገጥማሉ። ብዙዎቹ ሊቃውንት ዘካርያስ 1-8 የተጻፈው ቤተ መቅደሱ ከመጠናቀቁ በፊት ከ520-518 ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ውስጥ በዘካርያስ እንደሆነ ይስማማሉ። ክርክሩ የሚካሄደው ከዘካርያስ 9-14 ባለው ክፍል ላይ ነው። አንዳንድ ምሁራን ዘካርያስ 9-11 የተጻፈው ባልታወቀ ሁለተኛ ሰው ሲሆን፥ ዘካርያስ 12-14 ደግሞ በሌላ ሦስተኛ ሰው እንደ ተጻፈ ያምናሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ዘካርያስ 9-14 የተጻፈው በሌላ ሁለተኛ ሰው ነው ይላሉ። እነዚህ ምሁራን የዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል የተጻፈው ከ300-100 ዓ.ዓ. ነው ይላሉ።

አንዳንድ ምሁራን ትንቢተ ዘካርያስን ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደጻፉትና የመጨረሻው ክፍል ዘግይቶ እንደተጻፈ የሚያምኑት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የትንቢተ ዘካርያስ የመጨረሻ ክፍል ከመጀመሪያዎቹ ስምንት ምዕራፎች ጋር ሲወዳደር በአጻጻፍ ስልቱና በሥነ-መለኮት ትምህርቱ ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱ በሌላ ጸሐፊ መጻፉን የሚያመለክት ነው ይላሉ። ሁለተኛ፥ ዘካርያስ “አፖሊፕቲክ” ተብሎ የሚጠራ የሥነ-ጽሑፍ ዓይነት ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። አፖካሊፕቲክ ሥነ-ጽሑፍ በአብዛኛው ስለ መላእክት፥ ስለ ሕልሞችና ራዕዮች ስለፍርዶችና የእግዚአብሔር ልጆች ባልተለመዱ መንገዶች ስለዳኑበት ሁኔታ የሚተርክ ነው። እነዚህ ምሁራን የዚህ ዓይነቱ የአጻጻፍ ስልት የተጀመረው ከ300 ዓ.ዓ. በኋላ ነው ይላሉ። ስለዚህ ዘካርያስ ይኖር ከነበረበት ከብዙ ዓመታት በኋላ በአንድ ሌላ ሰው ተጽፎ በትንቢተ ዘካርያስ ላይ እንደተጨመረ ያስባሉ።

ወግ አጥባቂ ከሆኑ ምሁራን ግን ይህንን መጽሐፍ በአጠቃላይ የጻፈው ዘካርያስ ነው ብለው ያምናሉ። የአጻጻፍ ስልት ልዩነት የመኖሩ ምክንያት ዘካርያስ የተለያዩ ዓይነት የአጻጻፍ ስልቶችና ጽሑፎችን መጠቀሙ ነው። ዘካርያስ ቀዳሚዎቹን ስምንት ምዕራፎች የነቢይነት አገልግሎቱን በጀመረበት የመጀመሪያው የወጣትነት ዘመኑ የጻፋቸው ሲሆን፥ የመጨረሻዎቹን አራት ምዕራፎች ደግሞ በሕይወቱ ዘመኑ መጨረሻ ገደማ እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ከሰጠው ራእይ በኋላ የጻፋቸው ናቸው ብለው ያስባሉ። መጽሐፉ የተጠቃለለው ከ500-470 ዓ.ዓ. ነው ብለው ያስባሉ። ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ጸሐፊዎች እንደ ጻፉት የሚጠቁም ምንም መረጃ ስለሌለ መጽሐፉን በሙሉ የጻፈው ዘካርያስ እንደሆነ መቀበል የተሻለ አማራጭ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የመመዘኛ ጥያቄዎችን ለማግኘት ከታች ያለውን ሊንክ (መስፈንጠሪያ) ይጫኑ፡፡

https://forms.gle/7xn3Ao2p4TTv6jMk7

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading