ንጹሕ ሕሊና (2ኛ ቆሮ. 1፡12-24)

«ፕሮፋይልስ እን ከሬጅ» በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ፥ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፥ «ታላላቅ ፈተናዎች ታላላቅ ሰዎችንና ታላላቅ የጀግንነት ሥራዎችን ያስገኛሉ» በማለት ጽፈዋል። 

በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የሚደርሰው ፈተና ሰውየውን እንደሚያንጸው እውነት ቢሆንም፥ በሌላም በኩል ፈተናው የሰውየውን የመንፈስ ጥንካሬ እንደሚያመለክት የታወቀ ነው። ጲላጦስ ታላቅ ፈተና ተጋርጦበት ነበር፤ ዳሩ ግን ፈተናውን ያስተናገደበት መንገድ ጀግንነት ወይም ታላቅነት አላጎናጸፈውም። የሕይወታችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች የምናስተናግድበት መንገድ የሚወሰነው ባመዛኙ በባሕርያችን የጥንካሬ ደረጃ ሲሆን፥ ይህም የሚያሳየን ሕይወት በእኛነታችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንደ ግል ጥንካሬአችን መጠን መሆኑን ነው። 

ጳውሎስ በዚህ እጅግ የግላዊነት ባሕርይ ጎልቶ በሚታይበት ደብዳቤ ውስጥ፥ ልቡን ለቆሮንቶስ ሰዎች (እና ለእኛ) በመክፈት ያለፈባቸውን መከራዎች ገልጿል። በመጀመሪያ ደረጃ፥ ዕቅዶቹን በመቀየሩ ብቻ የገባውን የተስፋ ቃል ያልጠበቀ የመሰለባቸው አንዳንድ በቆሮንቶስ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አጥብቀው ይተቹት ነበር። ክርስቲያኖች በአሳብ ሳይገናኙ ሲቀሩ፥ ቅሬታቸው ሥር እየሰደደ ሊሄድ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ፥ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን የሚፈታተን የተቃውሞ ችግር ገጥሞት ነበር። ከምዕመኖቹ ውስጥ አንድ ሰው . ምናልባትም መሪ ሳይሆን አይቀርም – ለዚህ ጥፋቱ መቀጣት ይገባው ስለ ነበረ ጳውሎስ በዚህ የተነሣ በጣም አዝኖ ነበር። በመጨረሻም ፥ ጳውሎስ በእስያ ውስጥ በትዕግሥት ሊያሳልፋቸው የሚገባ ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡8-11)፤ መከራዎቹም የገዘፉ በመሆናቸው፥ በሕይወቱ ተስፋ ቆርጦ ነበር። 

ጳውሎስን ከውድቀት የታደገው ምን ይሆን? ከነዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች የደረሱባቸው ሌሎች ሰዎች ለውድቀት ተዳርገው ይሆናል! ይሁንና ጳውሎስ ሁኔታዎቹን ድል-መንሣት ብቻ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ከዚያው አስቸጋሪ ልምምዱ ካገኘው ትምህርት፥ ዛሬም የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ድል እንዲሻገር የሚረዳ ታላቅ ደብዳቤ አዘጋጅቷል። ጳውሎስ ጉዞውን እንዲቀጥል ያበረታቱት መንፈሳዊ ሀብቶች ምን ምን ነበሩ? 

ንጹሕ ሕሊና (2ኛ ቆሮ. 1፡12-24) 

ሕሊና የሚለው ቃል ኮም እና እስኪሬ ከሚሉ ሁለት የላቲን ቃላት የተገኘ ሲሆን፥ ትርጉማቸውም ኮምለ«ኪጋር»፥ እስኪሬለ«ማወቅ» ማለት ነው። ሕሊና ከመንፈሳችን ጋር በመተባበር ነገሮችን የሚያውቅና ትክክል ስንሠራ ትክክለኛነቱን የሚያረጋግጥ ፥ ስናጠፋ ደግሞ የሚወቅሰን ውስጣዊ ብቃት ነው። ሕሊና የእግዚአብሔር ሕግ አይደለም፤ ጻሩ ግን ለዚያው ሕግ ምስክርነቱን ይሰጣል። ሕሊና ብርሃንን ወደ ቤት የሚያስገባ መስኮት ነው፤ በመሆኑም ባለመታዘዛችን ምክንያት መስኮቱ ቢቆሽስ፥ ብርሃኑ እየደበዘዘ ይሄዳል (ማቴ. 6፡22-23፤ ሮሜ 2፡14-16 ተመልከት)። 

ጳውሎስ ሕሊና የሚለውን ቃል በመልእክቶቹ ውስጥና በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደ ተገለጸውም በአገልግሉቱም ውስጥ ጭምር በአጠቃላይ 23 ጊዜ ያህል ተጠቅሞበታል። «ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ» (የሐዋ. 24፡16)። አንድ ሰው ንጹሕ ሕሊና ካለው፥ ሌሎችን ለማጥላላት የሚጥር አታላይ ሳይሆን፥ ሐቀኛ በመሆኑ ሊታመን ይችላል። 

የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስ እንዳታለላቸውና ግድ የለሽ እንደ ሆንባቸው አድርገው የወቀሱት ለምን ነበር? ዕቅዶቹን ለመቀየር ስለ ተገደደ ነው። በመጀመሪያ «ጌታ ቢፈቅድ» (1ኛ ቆሮ. 16፡2-8) በጋውን በቆሮንቶስ እንደሚያሳልፍ ተስፋ ሰጥቶ ነበር። ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ለአይሁዳውያን ድሆች አማኞች ያዋጡትን ገንዘብ ለመሰብሰብና ቤተ ክርስቲያኒቱ እርሱንና የሥራ ተባባሪዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ የመሸኘት ዕድል እንድታገኝ ፈልጎ ነበር። 

ሆኖም ግን ጳውሎስ ከፍተኛ ጸጸትና እፍረት ቢያድርበትም ቅሉ፥ እነዚያን ዕቅዶች ለመቀየር ተገድዶ ነበር። እኔም በራሴ ውስን አገልግሎት ውስጥ እንኳን አንዳንዴ ዕቅዶችን ለመቀየርና የጉባዔዎችን ቀናት እስከ መሰረዝ ጭምር ስለምገደድ (ሐዋርያዊ ሥልጣን ሳይኖረኝ፥ ለገጠመው ነገር አዝንላታለሁ። ዊል ሮጀርስ እንደሚሉት፥ «ዕቅዶች ወደ ነገሮች ያደርሱዎታል፤ ዳሩ ግን መንገድዎን ማስተካከል አለብዎት።» ጳውሎስ ወደ መቄዶንያ ሲሄድና ሲመለስ፥ ሁለት ጊዜ ቆሮንቶስን ሊጎበኝ አቅዶ ነበር። ሐሳቡም ከቆሮንቶስ የተሰበሰበውን ገንዘብ ከመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት በተሰበሰበው ላይ በመጨመር ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ ነበር። 

የሚያሳዝነው ግን ሁለተኛውም ዕቅድ ሳይቀር አልተሳካለትም ነበር። ለምን? ምክንያቱም በፍቅር የተሞላው ልቡ ተጨማሪ «አሳዛኝ ጉብኝት» የማድረግ ጽናት ሊኖረው አይችልም ነበር (1፡23፤ 2፡1-3)። ጳውሎስ ዕቅዶቹን እንደ ቀየረ ቀደም ሲል ያሳወቃቸው ቢሆንም፥ ተቃውሟቸው ግን ሊበርድ አልቻለም ነበር። «ሥጋዊ ጥበብ» (1፡12) እንደ ተከተለ፥ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ግድ እንዳልነበረው (1፡17) እንዲሁም ዕቅዶቹን የሚወጥነው ራሱን ለማስደሰት ብቻ እንደ ሆነ በመግለጽ ወቀሱት። «ጳውሎስ አንድ ነገር ቢናገር ወይም ቢጽፍ፥ በርግጥ የሚያስበው ሌላ ነገር ነው። እርሱ አዎን የሚለው አይደለም ለማለት ሲሆን፥ አይደለም የሚለው ደግሞ አዎን ለማለት ነው» ይሉ ነበር። 

አንድኛው አለመግባባት ወደ ሌላው ስለሚያመራ፥ ብዙውን ጊዜ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የሚፈጠሩትን አሳብ አለመግባባቶች ለማስተካከል በጣም አስቸጋሪ ነው። አንድ ጊዜ የሌሎችን ታማኝነት ወይም ቃላቸውን መጠራጠር ከጀመርን፥ ለሁሉም ዓይነት ችግሮች መከተል በሩ ወለል ብሉ ይከፈታል። ዳሩ ግን ወቃሾቹ ምንም ቢናገሩ ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊና ስለ ነበረው፥ ጸንቶ ይቆማል። የጻፈው የተናገረውና የኖረው ሕይወት በሙሉ እርስ-በርሱ የሚቃረን ሳይሆን የሚደጋገፍ ነበር። በተጨማሪም፥ በመጀመሪያው ዕቅዱ ላይ «ጌታ ቢፈቅድ» የሚለውን ሐረግ ማከሉ ሊታወስ ይገባል (1ኛ ቆሮ. 16፡7፤ ያዕ. 4፡13-17 ተመልከት)። 

ንጹሕ ሕሊና እስካለህ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን መመለስ በመጠባበቅ ትኖራለህ (2ኛ ቆሮ. 1፡14)። «በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን» የሚለው ክርስቶስ ወደሚገለጽበትና ቤተ ክርስቲያኑን ወደ ሰማይ ወደምትወሰድበት ሁኔታ ያመለክታል። ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት በቆሮንቶስ አማኞች ደስ እንደሚሰኝና እነርሱም በእርሱ ሐሤት እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነበር። ዛሬ ምንም ዓይነት የአሳብ ልዩነት (ያለመግባባት) ቢኖርም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በምንቆምበት ጊዜ፥ ሁሉም ይቅር ተብሉና ተዘንግቶ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ወደ ክብር ይለወጣል። 

ንጹሕ ሕሊና ሲኖርህ፥ ከፍተኛውን ሥፍራ የምትሰጠው ለእግዚአብሔር ፈቃድ ይሆናል (ቁ 15-18)። ጳውሎስ ዕቅዶቹን በግድየለሽነት ወይም ሳያስብበት አልወጠነም፤ የጌታን ምሪት ሽቷል። ዳሩ ግን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ምን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ አልነበረም (የሐዋ. 16፡6-10)፤ ይህም ሆኖ ግን እንዴት ጌታን መጠበቅ እንዳለበት ያውቅ ነበር። አነሳሽ ምክንያቶቹ (ዓላማዎቹ) ታማኝነትን የተንተራሱ ነበሩ፡- እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ለማስደሰት አይጥርም ነበር። እንዲያውም በዚያ የመገናኛና የመጓጓዣ አገልግሎት አስቸጋሪ በነበረበት ወቅት ጳውሎስ ከሌላው ውጥረት ጎን ለጎን ስለዚህ ጉዳይ ጭምር ማሰቡን ስናሰላስል መገረማችን አይቀርም። 

ኢየሱስ የምንለውን ነገር በትክከል እንድንናገር አስተምሮናል። «ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው» (ማቴ. 5፡37)። አዎንታዊ ወይም አሉታዊ አባባሉን ለማጠናከር ተጨማሪ ቃላት የሚጠቀመው የመሠሪነት ባሕርይ ያለው ሰው ብቻ ነው። ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊና ስለ ነበረው፥ የቆሮንቶስ ሰዎች እውነተኛ ባሕርይ እንዳለው ያውቁ ነበር። ለ18 ወራት በመካከላቸው ተገኝቶ ሲያገለግል፥ ጳውሎስ ታማኝነቱን አረጋግጦላቸዋል፤ ባሕርዩም አንድም ቀን ተለውጦ አያውቅም ነበር። 

ንጹሕ ሕሊና ሲኖርህ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ታስከብራለህ (2ኛ ቆሮ. 1፡19-20)። በተመሳሳይ ጊዜ ክርስቶስን ማስከበርና የአታላይነትን ተግባር መወጣት አይቻልም። ይህን ለማድረግ ከሞከርህ ግን፥ ሕሊናህን ከማበላሸትህም ባሕርይህም በአደገኛ ሁኔታ ይቦረቦራል፤ ዞሮ ዞሮ ግን በመጨረሻ እውነት አሸንፋ ትወጣለች። የቆሮንቶስ ሰዎች ደኅንነትን ያገኙት ጳውሎስና ጓደኞቹ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ሰበኩላቸው ነበር። ታዲያ እግዚአብሔር እንዴት እውነትን በሐሰተኛ መምህራን አማካኝነት ሊገልጽ ይችላል? የምንሠራው ሥራ ከምንኖረው ሕይወት ስለሚፈልቅ፥ ምስክርነቱና የአገልጋዩ እርምጃ የግድ ጎን ለጎን ሊሄዱ ይገባል። 

ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ አዎንታ ወይም አሉታ ሊኖር አይችልም። ለሚተማመኑበት እርሱ የእግዚአብሔር «ዘላለማዊ አዎንታ» ነው። «እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ ለእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው» (ቁ20)። ኢየሱስ ክርስቶስ የተስፋ ቃሎቹን ይገልጻል፤ ይፈጽማል፤ የተስፋ ቃሎቹ የእኛ እንደ ሆኑ አድርገን እንድንቀበልም ያስችለናል። ከንጹሕ ሕሊና በረከቶች አንዱ ወደ እግዚአብሔርም ሆነ ወደ ሰው ፊት ለመቅረብ ወይም እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ የሚሰጠንን የተስፋ ቃሎች የራሳችን አድርገን ለመቁጠር አለመፍራታችን ነው። ጳውሎስ የራሱን የኃጢአት ልምምዶች መዝገብ ለማጥራት በእግዚአብሔር ቃል «ያለ አግባብ የመጠቀም» ጥፋት አልፈጸመም ነበር (4፡2 ተመልከት)። 

በመጨረሻም ልትረዳው የሚገባው ንጹሕ ሕሊና ሲኖርህ፥ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር መልካም ግንኙነት እንደሚኖርህ ነው (1፡21-24)። ማጽናት የሚለው ቃል የንግድ ቃል ሲሆን፥ ለውለታው በትክክል መፈጸም የሚሰጥ መተማመኛ ነው። ሻጩ ለገዢው የሚሸጠው ዕቃ አስቀድሞ በማስታወቂያ እንደ ተነገረለት አስተማማኝ ለመሆኑ ወይም የሚሰጠው አገልግሎት በተገባው ቃል ኪዳን መሠረት የሚፈጸም ለመሆኑ የሚሰጠው ማረጋገጫ ነው። 

መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ሊደገፉበት የሚቻልና ተስፋ የሰጠውን ሁሉ እንደሚፈጽም የሚያመለክት ማረጋገጫው ነው። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስን ላለማሳዘን ይጠነቀቅ ነበር፤ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ስለማይወቅሰው፥ አነሳሽ ምክንያቶቹ ትክክል እንደ ሆኑና ሕሊናውም ንጹሕ እንደ ነበር ያውቅ ነበር። 

ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል (ቁ 21)። በብሉይ ኪዳን ዘመን በእግዚአብሔር የሚቀቡት ነቢያት፥ ካህናትና ነገሥታት ብቻ ነበሩ። ቅብዓታቸውም ለአገልግሎት ያስታጥቃቸው ነበር። ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ሰምንሰጥበት ጊዜ፥ እግዚአብሔርን እንድናገለግልና ፈሪሃ-እግዚአብሔር ያለበትን ሕይወት እንድንኖር ያስችለናል። እግዚአብሔርን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንድናገለግል ልዩ መንፈሳዊ የመለየት ስጦታ ይሰጠናል (1 ዮሐ. 2፡20፥ 27)። 

በተጨማሪም የክርስቶስ ንብረት መሆናችንን ለማመልከትና በእርሱ እንደ ተጠራን ለማረጋገጥ መንፈስ ቅዱስ አትሞናል (ኤፌ. 1፡13፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡22)። ከውስጣችን ያለው የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንጂ ለማስመሰል እየጣርን እንዳለሆነ ዋስትና ይሰጠናል (ሮሜ 5፡5፤ 8፡9)። እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የእርሱ ንብረት ስለ ሆንን፥ እንደሚጠብቀን ያረጋግጥልናል። 

በመጨረሻም፥ መንፈስ ቅዱስ ሌሎች ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ትዕዛዝ የምንሰጥ «መንፈሳዊ አምባዎች» ሳንሆን፥ ዳሩ ግን ሌሎች እንዲያድጉ ለመርዳት እንደሚሹ አገልጋዮች እናገለግል ዘንድ ያስችለናል (2ኛ ቆሮ 1፡23-24)። የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን ያጨናነቁት የሐሰት አስተማሪዎች የአምባገነንነት ጥፋት ይፈጽሙ ስለ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11 ተመልከት)። የሕዝቡ ልብ ብዙ መሥዋዕትነት ከከፈለላቸው ከጳውሎስ ሸፈተ። 

መንፈስ ቅዱስ አንድ ቀን ከእርሱ ጋር በመንግሥተ-ሰማይ እንደምንሆንና የከበረውን አካል እንደምንለብስ የሚያረጋግጥልን የእግዚአብሔር «መያዣ» (ቀብድ፥ ዋስትና፥ ማስተማመኛ) ነው (ኤፌ 1፡14 ተመልከት)። ዛሬም ቢሆን በልባችን በመንግሥተ ሰማይ በረከቶች ሐሤት እንድናደርግ ያስችለናል! በልቡ ውስጥ ካደረው መንፈስ ቅዱስ የተነሣ፥ ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊና ስለ ነበረው በአሳብ አለመግባባት የተነሣ የሚፈጠሩ ችግሮችን በፍቅርና በትዕግሥት ለማስተናገድ ይችል ነበር። አንተም ብትሆን የሕይወት መመሪያህ ሰዎችን ለማስደሰት እስከ ሆነ፥ የአስተሳሰብ ግጭቶች ያስጨንቁሃል፤ ዳሩ ግን የምትኖረው እግዚአብሔርን ለማስደሰት ከሆነ፥ የአሳብ ልዩነቶችን ለማስወገድ በፍቅርና በብርታት ለመጋፈጥ ትችላለህ። 

የሚራራ ልብ (2ኛ ቆሮ. 2፡1-1) የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ መሆናችን መጠን፥ በተደጋጋሚ ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ይገልል የሚለውን አንድ ባልታወቀ ደራሲ የተቋረጠ ስንኝ ብዙ ጊዜ እጠቅስ ነበር። 

ከምንናፍቃቸው ቅዱሳን ጋራ 

ለዘለዓለምም በላይ መኖር 

አቤት ያለው ታላቅ ክብር! 

ግን – ካወቅናቸው ቅዱሳን ጋር 

ዕለት ዕለት በምድር ስንኖር 

መቼም አንርቅ ከማማረር! 

ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን አንዱ ጳውሎስን በእጅጉ አሳዝኖት ነበር። ይህ ሰው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 ውስጥ የጠቀሰውና በግልጽ በዘማዊነት ኃጢአት የተጠመደው ሰው ይሁን፥ ወይም የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን በይፋ የተፈታተነው ሌላው ሰው፥ በርግጠኛነት ልንናገር አንችልም። ጳውሎስ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ዘፍጥነት ወደ ቆሮንቶስ የገሰገሰ ሲሆን (2ኛ ቆሮ. 2:14፤ 13፡1)፥ በተጨማሪም ስለ ሁኔታው የሚያሳዝን ደብዳቤ ጽፎላቸዋል። በዚህም ሁሉ፥ የርኅራኄ ልብ አሳይቷል። የጳውሎስን ፍቅር የሚያመለክቱትን የሚከተሉትን መረጃዎች ልብ በል። 

በመጀመሪያ፥ ለሌሉች ቅድሚያ ሰጥቷል (2ኛ ቆሮ. 2፡1-4)። ስለ ራሱ ስሜቶች ሳይሆን፥ በመጀመሪያ ለሌሎች ሰዎች ስሜቶች ያስብ ነበር። በክርስትና አገልግሎታችን፥ ትልቅ ደስታ የሚያመጡልን ሰዎች ትልቅ ሐዘንም ሊፈጥሩብን ይችላሉ፤ ጳውሎስም እያለፈበት የነበረው ይህንኑ ዓይነት ልምምድ ነበር። ከልቡ ከተሰማው ጭንቀት የፈለቀና በክርስቲያን ፍቅር የታጀበ ጠንካራ ደብዳቤ ይጽፋል። ዓቢይ መሻቱም ቤተ ክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ቃሉን እንድታከብር፥ አጥፊውን እንድትቀጣና ለማኅበረ-ምዕመናኑም ንጽሕናና ሰላም እንድታመጣ ነበር። 

«የወዳጅ ማቁሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው» (ምሳሌ 27፡6)። ጳውሎስ የተጠቀማቸው ቃላት የሚወዳቸውን ወገኖች ሊያሳዝኑ እንደሚችሉ ያውቅ ስለነበር፥ ልቡ በሐዘን ተነክቶ ነበር። ዳሩ ግን (ማንኛውም አፍቃሪ አባት እንደሚያውቀው) ሰውን ስለ ፍቅር ብሎ በመጉዳትና በጠላትነት በማጥቃት መካከል ያለውንም ትልቅ ልዩነት ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የሚወዱን ሰዎች ራሳችንን እንዳንጎዳ ሲሉ ሊቀጡን ይገባል። 

ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን በመጠቀም ሰዎች እንዲያከብሩትና እንዲታዘዙት ለማድረግ ይችል ነበር፤ ይሁንና በፍቅርና በትዕግሥት ማገልገሉን መረጠ። እግዚአብሔር የጳውሎስ ዕቅዶች መለወጥ ቤተ ክርስቲያንን ከተጨማሪ ሕመም የመጠበቅ ዓላማ እንደ ነበረው ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 1፡23-24)። ፍቅር ሁልጊዜም የሌሎችን ስሜቶች በማጤን ከማንኛውም ነገር በፊት ለእነርሱ የሚበጀውን ያስቀምጣል። 

እንዲሁም ፍቅር ለሌሎች ይሻሻሉና ያድጉ ዘንድ ለመርዳት ይሻል (2ኛ ቆሮ 2፡5-6)። እዚህ ላይ ጳውሎስ የተቃወመውንና የቤተ ክርስትያንን ቤተሰብ የከፋፈለውን ሰው ስም እንዳልጠቀሰ ማስተዋል ጠቃሚ ነው። ይሁንና ጳውሎስ ለራሱ ለሰውየው ጥቅም ሲል ቤተ ክርስቲያኗ ይህንኑ ሰው እንድትቀጣ አሳስቧል። ይህ በ1ኛ ቆሮንቶስ 5 ውስጥ የተጠቀሰው ዘማዊው ሰው ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ተቀምጣ እንደ ቀጣችውና እርሱም ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ እንደ ተመለሰ እነዚሁ ቁጥሮች ያመለክታሉ። 

እውነተኛ ቅጣት የፍቅርን መኖር ያመለክታል (ዕብ 12 ተመልከት)። ልጆችን በማሳደጉ ረገድ «ዘመናዊ እይታ» ያላቸው አንዳንድ ወጣት ወላጆች ከመጠን በላይ እንደሚወዷቸው በመናገር፥ የማይታዘዙላቸውን ለመቅጣት አይፈልጉም። ዳሩ ግን በርግጥ ልጆቻቸውን ቢወዱ ኖሮ፥ ጥፋታቸውን በማሳየት እንዲታረሙ በረዷቸው ነበር። 

የቤተ ክርስቲያን የሥነ-ሥርዓት እርምጃ ተወዳጅነት ያለው ወይም በስፋት የሚሠራበት ዓይነት አይደለም። እጅግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ይህን ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን በመታዘዝ፥ «እውነትን በፍቅር በመናገር» (ኤፌ 4፡15) ምትክ፥ ብሉም ሁኔታውን በድፍረት ከመጋፈጥ የሚመርጡት፥ ነገሩ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው መተውን ነው። ንጽሕና ሳይኖር፥ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰላም ሊኖር ስለማይችል፥ «የሆነውን ሁሉ ዋጋ ከፍሎ በሰላም መኖር» የሚለው መርሆ ጨርሶ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም (ያዕ.3፡15-18)። ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገው የተተዉት ችግሮች በኋላ የመባዛትና ከቀድሞውም የከፉ ችግሮችን የመፍጠር ዕድል አላቸው። 

ጳውሎስ ያጋለጠውና ቤተ ክርስቲያን የቀጣችው ወንድም ፍቅር ያለበት አትኩሮት ተሰጥቶት ርዳታ አግኝቷል። ልጅ ሳለሁ፥ ምንም እንኳ ከተቀበልሁት የሚልቅ ቅጣት እንደሚገባኝ መናዘዝ ቢኖርብኝም፥ ቤተሰቦቼ የሚሰጡኝን ቅጣት ሁልጊዜም አልወድም ነበር። ዳሩ ግን አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስብ፥ ራሴን ለባሰ ጥቃት እንዳላጋልጥ ለመከላከል ሲሉ ቤተሰቦቼ ከፍቅራቸው የተነሣ እስኪጎዱኝ ድረስ ጨክነው ሊቀጡኝ በመውደዳቸው እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። «ይህን ማድረጋችን አንተን ከሚጎዳው በላይ እኛንም ይጎዳናል» ሲሉ ይናገሩኝ የነበረው ምን ማለት እንደ ሆነ፥ አሁን በግልፅ ተረድቼዋለሁ። 

በመጨረሻም፥ ፍቅር ይቅር ይላል፤ ያበረታታልም (2ኛ ቆሮ. 2፡7-11)። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያኗ ቤተሰብ ያንን ሰው ይቅር እንዲል ያበረታታ ሲሆን፥ ይህንኑ ምክር ከሥራ ላይ እንዲያውሉት ጠንካራ ምክንያቶችን ያቀርባል። በመጀመሪያ ደረጃ፥ ለሰውየው ይቅርታ መደረጉ «ከልክ ባለፈ ኃዘን እንዳይዋጥ» (ቁ 7-8)፥ ለራሱ ጥቅም ሲባል ነበር። ይቅርታ የተሰበረውን ልብ ለመጠገን የሚረዳ መድኃኒት ነው። ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ ንስሓ የገባ ሰው የፍቅሯ ተካፋይ የማድረጓን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነበር። 

በራሴ የመጋቢነት አገልግሎት ውስጥ፥ የሥነ-ሥርዓት እርምጃ የተወሰደባቸው አባላት ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ኅብረቱ በተቀላቀሉባቸው ጉባዔዎች ላይ መልእክት አካፍያለሁ፤ እነዚህም በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛና የተቀደሱ ሰዓታት ነበሩ። የቤተ ክርስቲያኗ ቤተሰቦች ይቅርታ ለተደረገለት ወንድም ወይም እህት ኃጢአታቸው እንደ ተዘነጋና ወደ ኅብረቱ እንደ ተመለሱ ሲያረጋግጡላቸው አካባቢው ድንቅ በሆነ በጌታ ሕልውና ይሞላል። ልጁን የሚቀጣ ወላጅ ሁሉ ከቅጣቱ አስከትሉ ፍቅርና ይቅርታው ከልብ የመነጨ ለመሆኑ ዋስትና መስጠት አለበት፤ ይህ ካልሆነ ግን ቅጣቱ ከማቃናት ይልቅ የባሰ ጠማማነትን ያስከትላል። 

ክርስቲያኖች ለጌታ ሲሉ ይቅር ለተባለው ወንድም ፍቅራቸውን ያለማጓደል መለገስ አለባቸው (ቁ 9-10)። እንዲሁም ቅጣት ለወንድም መሰጠት ያለበት ግዴታ የመሆኑን ያህል፥ ለጌታም የመታዘዝ ኃላፊነትን ያቀፈ ጉዳይ ነው። ይህን የመሰለው ችግር የሚንፀባረቀው ባዘነው ሐዋርያና ኃጢአትን በፈጸመው ወንድም መካከል ብቻ ሳይሆን፥ ኃጢአትን በፈጸመው ወንድምና በሚያዝነው አዳኝ መካከልም ጭምር ነው። ያ ወንድም በእርግጥም በቤተ ክርስቲያን እና በጳውሎስ ላይ በደል ቢፈጽምም፥ ዳሩ ግን ከሁሉም በላይ በጌታ ላይ ኃጢአትን ሠርቷል። ፍርሃት የሚያጠቃቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን የመሳሰለውን ሁኔታ በታማኝነት በመጋፈጥ ምትክ «አለባብሰው» ሲያልፉት፥ የጌታን ልብ ያሳዝናሉ። 

ጳውሎስ ሦስተኛ ምክንያትም ሰጥቷል፡- ጥፋት የፈጸመውን ወንድም ለቤተ ክርስቲያኗ ደኅንነት ሲሉ ይቅር ማለት ነበረባቸው (ቁ 11)። ለኃጢአት ተገቢ የሆነ መጽሐፈ ቅዱሳዊ መፍትሔ እንዳይገኝለት ከምዕመናኑ አንዱ እንቅፋት ሲሆንና ይቅርታ ለማድረግ ሳይፈቅድ ሲቀር፥ ሰይጣን በማኅበረ-ምዕመናን ውስጥ ተልዕኮውን የሚፈጽምበት ቀላል «መነሻ» ያገኛል። ይቅርታን የማያደርግ መንፈስ ካለን፥ መንፈስ ቅዱስን በማሳዘን «ለዲያብሎስ ፈንታ» (ኤፌ 4፡27-32) እንሰጣለን። 

ከሰይጣን «ማታለያ ዘዴዎች» አንዱ ኃጢአት የሠሩ አማኞች ፍጹም ተስፋ እንዲቆርጡ መክሰስ ነው። በእኔም በኩል፥ ከሰይጣን ጭቆናና ክስ በታች በመውደቃቸው ምክንያት እርዳታ ሽተው ደብዳቤ የጻፉልኝ ወይም ስልክ የደወሉልኝ ሰዎች በብዛት አጋጥመውኛል። መንፈስ ቅዱስ የሚወቅሰን፥ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ለመንጻት ወደ ክርስቶስ እንድንመለስ ሲሆን፥ ዳሩ ግን ሰይጣን ተስፋ ቆርጠን የእምነት ጉዞአችንን እንድንተው ይከሰናል። 

ያጠፋው ወንድም ወይም እህት ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ አኳያ ከተቀጡና ንስሐ ከገቡ በኋላ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰብ ይቅርታ በማድረግ እንደ ቀድሞው ሊያቅፏቸው ይገባል፤ ነገሩም ዳግመኛ ላይታወስ መደምደም አለበት። (ዳግም ላይወሳ)። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተሰብ ወይም ከቤተሰቡ ውስጥ ማንኛውም ሰው ይቅርታን የማያደርግ መንፈስ ካለው፥ ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ላይ አዳዲስ ጥቃቶችን ለማስከተል በዚሁ ቀዳዳ ይጠቀማል። 

ጳውሎስ ንጹሕ ሕሊናና የሚራራ ልብ ስለ ነበረው፥ ከፊቱ የተጋረጡትን ችግሮች ለማሸነፍ ችሏል። ዳሩ ግን ለድል ያበቃው ሦስተኛው መንፈሳዊ ሀብት ቀጥሎ የተጠቀሰው ነበር፡፡

1 thought on “ንጹሕ ሕሊና (2ኛ ቆሮ. 1፡12-24)”

  1. ስለ ሕሊና ዓይነቶች ለማወቅ ስፈልግ ይህን ጽሑፍ አንቤዋለሁ በጣም ጠቃሚና የሚያንጽ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ። ጌታ ጸጋና ሰላም ያብዛላችሁ

Leave a Reply to Pastor Ermias BehailuCancel reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading