የመስጠት ጸጋ፣ ክፍል 1 (ቆሮንቶስ 8፡1-24)

 ከጳውሉስ ሦስተኛ የሚሲዮናዊነት ጉዞ አበይት አገልግሎቶች አንዱ በይሁዳ ለሚኖሩ ድሀ ክርስቲያኖች ልዩ «የርዳታ ስጦታ» ማድረግ ነበር። ጳውሎስ ከዚህ በፊት አንድ ጊዜ የዚህ ዓይነት አገልግሎት ያበረከተ ሲሆን (የሐዋ. 11፡27-30)፥ አሁንም ተመሳሳይ ግልጋሎት ለመስጠት ደስተኛ ነበር። የተዘነጋውንና «ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው» (የሐዋ. 20፡35) የሚለውን የጌታችን ብፅዕና ያስታወሰው ጳውሎስ እንደ ነበር መረዳት አስፈላጊ ነው። 

ይሁንና ድሆችን በገንዘብ ከመርዳትም በተጨማሪ በጳውሎስ አእምሮው ውስጥ የሚመላለሱ ሌሎችም በረከቶች ነበሩ። ከባሕር ማዶ ለሚገኙ የአይሁድ ማኅበራት የአሕዛብ አብያተ-ክርስቲያናት የሚያደርጉትን እርዳታ በማስታወስ፥ ይህ የቤተ ክርስቲያን አንድነት በበለጠ እንዲጠናከር ይፈልግ ነበር። ጳውሎስ አሕዛብ የአይሁድ «ባለ ዕዳዎች» እንደ ሆኑ አድርጎ ይመለከታል (ሮሜ 15፡25-28)፤ ልዩ የርዳታ አሰባሰቡም ያንኑ ዕዳ ለመክፈል አንድኛው መንገድ ነበር። 

እንዲሁም ይህ ስጦታ ለአይሁድ አማኞች (አሁንም አንዳንዶቹ ለሕጉ ይቀኑ ነበር) ጳውሎስ እንደሚወራበት የአይሁዶች ወይም የሙሴ ጠላት እንዳልነበር የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር (የሐዋ. 20 ከቁ 17 ጀምሮ)። ጳውሎስ በአገልግሎቱ መጀመሪያ አካባቢ ድሆችን ለማሰብ ተስፋ የሰጠ ሲሆን (ገላ 2፡6-10)፥ ያንኑ የተስፋ ቃል ለመጠበቅ በትጋት ይሠራ ነበር፤ ሆኖም ግን እግረ መንገዱንም የአይሁዶችን የቅናት መንፈስ ለመስበር በማሰብ ከአሕዛቦች የሚደረግላቸው እርዳታ እንዲጠናከር ያበረታታ ነበር። 

የሚያሳዝነው፥ የቆሮንቶስ ሰዎች የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ አልነበረም። እንደ ብዙዎቹ ሰዎች፥ የተስፋ ቃሎችን ቢሰጡም፥ ዳሩ ግን አልፈጸሙም ነበር። እንዲያውም፥ አንድ ዓመቱ በሙሉ በከንቱ ባክኗል (2ኛ ቆሮ.8፡10)። ለዚህ ምክንያቱ ምን ነበር? የቤተ ክርስቲያኗ በዝቅተኛ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ መገኘቷ ነበር። ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እስካልሆነች፥ በልግስና ልትሰጥ አትችልም። ሌላው ምክንያት ደግሞ የሚችሉትን ያህል ገንዘብ ከቤተ ክርስቲያን ሳይዘርፉ ያልቀሩት የአይሁድ ሃይማኖት አስፋፊዎች ወረራ ነበር (11፡7-12፥ 20፤ 12፡14)። 

ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ለዚህ የልግስና ስጦታ ተካፋይ ማድረጉ ቀላል እንደማይሆን ስለ ተረዳ፥ ልመናውን ወደ ከፍተኛ መንፈሳዊ ደረጃ ያሳድገዋል፡- መስጠት የጸጋ ተግባር እንደ ሆነ ያስተምራቸዋል። ጳውሎስ ስጦታውን ለማመልከት በዘጠኝ የተለያዩ ቃላት ቢጠቀምም ዳሩ ግን ከሁሉም በላይ የተገለገለበት «ጸጋ» በሚባለው ቃል ነበር። መስጠት በመሠረቱ ሌሉችን የሚረዳ አገልግሉትና ኅብረትን የሚያሳይ (8፡4) ቢሆንም፥ ዳሩ ግን የመመንጫው ምክንያት በልብ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ሊሆን ይገባል። ጳውሎስ ይህ የርዳታ አሰባሰብ የአሕዛቦች ዕዳ መቅረፊያና (ሮሜ 15፡27) የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው ፍሬ (ሮሜ 15፡27) ፍሬ እንደ ሆነ ቢያውቅም በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህም የላቀ ምክንያት እንደ ነበረው ተረድቶ ነበር፤ ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ልብ ውስጥ የመሥራቱ ውጤት መሆኑን ያምንበት ነበር። 

ስለዚህ ክርስቲያኖች ከልብ መስጠት ከመቀበል ይልቅ የተባረከ መሆኑን አምነው፥ ወደ መስጠት ጸጋ በሚገቡበት ጊዜ አስደናቂ ነገር ይሆናል። ጥያቄው ግን «በጸጋ መስጠትን» እየተለማመድን መሆኑን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? የሚለው ነው። ጳውሎስ ስጦታችን በጸጋ የተነቃቃ ለመሆኑ ማስረጃ የሚሆኑ ምልክቶች እንዳሉ አመልክቷል። 

በሁኔታዎች ሳንገደብ ስንሰጥ (2ኛ ቆሮ.8፡1-2) 

ጳውሎስ በምሳሌነት የጠቀሳቸው የመቄዶንያ አብያተ ክርስትያናት፥ የራሳቸው የሆኑ ከፍተኛ ችግሮች ቢኖሩባቸውም፥ ዳሩ ግን በልግስና ለመስጠት ወደ ኋላ አላሉም ነበር። «በብዙ መከራ ተፈትነው» (ቁ 2) ነበር እንጂ፥ እንዲሁ በ«መከራ» ውስጥ ብቻ ያለፉ አልነበሩም። በከፍተኛ ድህነት ማለትም «በመናጢነት» ደረጃ ላይ ነበሩ። በዚህ ሥፍራ የተጠቀሰው ቃል ምንም ነገር የሌለውንና ለወደፊትም ምንም ነገር የማግኘት ተስፋው የመነመነን ለማኝ የሚገልጽ ነው። ይህ አስቸጋሪ ሁኔታቸው የመነጨው ምናልባትም ክርስቲያን በመሆናቸው የተነሣ፥ ከሥራቸው በመፈናቀላቸው ወይም ከጣዖት አምልኮ ጋር ለመተባበር ባለመፈለጋቸውና ከንግድ ማኅበራት በመገለላቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል። 

ይሁንና የነበሩባቸው ሁኔታዎች ከመስጠት አላቀቡዋቸውም ነበር። እንዲያም፥ በደስታና በልግስና ሰጡ። ማንኛውም ኮምፒውተር ይህንን የሚከተለውን አስደናቂ ስሌት ሊገነዘብ አይችልም፡- ትልቅ መከራና ጥልቅ ድህነት ሲደመር ጸጋ ለ ብዙ ደስታና ብዙ ልግስና! ይህም በጳውሎስ አገልግሎት ውስጥ የነበረውን የተቃራኒ ነገሮች ዝርዝር ያስታውሰናል፡- «ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን። (6፡10)። በተጨማሪም የመገናኛው ድንኳን (ዘጸ. 35፡5-6) እና ቤተ መቅደሱ (1ኛ ዜና 29፡6-9) በተሠሩ ጊዜ የተሰጡትን የልግስና ስጦታዎች ያስታውሰናል። 

አንተም የእግዚአብሔርን ጸጋ በሕይወትህ ውስጥ እስከ ተለማመድህ ድረስ ለሌሎች ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማመካኛ አድርገህ አትጠቀምባቸውም። ለነገሩማ እንዲያውስ ሁኔታዎች የመስጠት አገልግሎታችንን ያበረታቱበት ወቅት ጨርሶ ይኖር ይሆን? በመጀመሪያው የመጋቢነት አገልግሎቴ ወቅት፥ አዲስ ቤተ ክርስቲያን 

ማነጽ በጣም ያስፈልገን ነበር፤ ዳሩ ግን አንዳንድ ሰዎች «ከኢኮኖሚው ሁኔታ» የተነሣ ተቃወሙት። በዚያን ወቅት የብረትና የሌሎችም ፋብሪካዎች ሥራቸውን በአድማ ለማቆም የተነሣሡበት ነበር። በተጨማሪም የባቡር ሐዲዶችና የነዳጅ ማደያዎችም ችግር ፈጥረው ነበር ..ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ የማይቻል ይመስል ነበር። ዳሩ ግን «በጸጋ መስጠት»ን የሚያምኑ በቂ ሰዎች ስለ ነበሩ፥ ቤተ ክርስቲያኗ አዲስ ሕንፃ ለማሠራት ቻለች ያንን ሁሉ የኢኮኖሚ ችግር በመወጣት! በጸጋ መስጠት ማለት በሁኔታዎች ሳይገደቡ መስጠት ማለት ነው። 

በፍላጎት ስንሰጥ (2ኛ ቆሮ.8፡3-4) 

በልግስና መስጠትና ደግሞም ያለ ፍላጎት መስጠት፥ ሁለቱም ይቻላሉ። አንድ ቆንቋና ምዕመን፥ «ሰባኪው እስኪጎዳኝ ድረስ መስጠት እንዳለብኝ ይናገራል፤ ለእኔ ግን፥ ስለ መስጠት ማሰቡ ራሱ ይጎዳኛል» እስከ ማለት መድረሱ ይነገራል። የመቂዶንያ አብያተ ክርስቲያናት፥ እንደ ቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መቀስቀስ ወይም ማስታወስ አላስፈለጋቸውም። እንዲያውም ከሚሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ለማዋጣት ፈቃደኞች ነበሩ። ይህም ዕድል እንዲሰጣቸው እስከ መማጸን ደርሰዋል። ለመሆኑ አንድ ክርስቲያን ስጦታውን ሌላው እንዲቀበለው እስከ መለመን የደረሰበት ሁኔታ ስንት ጊዜ አጋጥሞህ ይሆን? 

ስጦታቸው ፈቃደኝነትና ግብታዊነት የሚታይበት ነበር። የጸጋ እንጂ፥ ከመገደድ የተነሣ የተፈጸመ አልነበረም። ለልግስናው የተሽቀዳደሙት የእግዚአብሔርን ጸጋ ስለ ተለማመዱና ለመስጠት ስለፈለጉ ነበር። ጸጋ ከኃጢአት ማንጻት ብቻ ሳይሆን፥ ከራሳችንም ያነጻናል። የእግዚአብሔር ጸጋ ልብህንና እጅህን ይፈታዋል። የምትሰጠውም በቀዝቃዛ የሂሳብ ስሌት ተመርተህ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ከሙቅ ልብ በሚመነጭ ሐሤት ነው። 

እንደ ኢየሱስ ስንሰጥ (2ኛ ቆሮ.8፡5-9) 

በአገልግሎትም ይሁን በመከራ፥ ወይም ራስን በመሠዋት ሁሉ አማኙ ሊከተለው የሚገባው ከሁሉም የላቀውን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል የመቄዶንያ ክርስቲያኖችም ራሳቸውን ለእግዚአብሔርና ለሌሎች አሳልፈው ሰጥተዋል (ቁ 5)። ራሳችንን ለእግዚአብሔር ከሰጠን፥ ንብረታችንን ለእግዚአብሔር መስጠቱ ብዙም አይከብደንም። እንዲሁም ራሳችንን ለእግዚአብሔር ከሰጠን፥ ለሌሎችም ደግሞ ራሳችንን እንሰጣለን። እግዚአብሔርን እየወደዱ የባልንጀራችንን ችግር ችላ ማለት የማይቻል ነገር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለእኛ ሲል ሰጥቶአል (ገላ. 1፡4፤ 2፡20)። እኛስ ራሳችንን ለእርሱ መስጠት የለብንም? የሞተልን ለራሳችን ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ለእርሱና ለሌሉች እንኖር ዘንድ ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡15)። 

የመቄዶናውያን ስጦታ፥ ልክ እንደ ክርስቶስ በፍቅር አነሣሽነት የተከናወነ ነበር (8፡7-8)። ይህ በመንፈሳዊ በረከቶች ለበለጸጉት የቆሮንቶስ ሰዎች ምንኛ ተግሣጽ ነበር (1ኛ ቆሮ.8:4-5)። እነርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዙሪያቸውን ታጥረው ስለ ነበር፥ የመንፈስ ቅዱስን የጸጋ ስጦታዎችንም ሆነ በጸጋ ተነሣሥተው መለገስን ዘንግተው ነበር። የመቄዶንያ አብያተ – ክርስቲያናት «ጥልቅ ድህነት» (2ኛ ቆሮ. 8፡2) ደርሶባቸው ሳለ፥ ዳሩ ግን አብዝተው ሊሰጡችለዋል። የቆሮንቶስ ሰዎች ግን በርካታ መንፈሳዊ ስጦታዎች ቢኖሯቸውም፥ ዳሩ ግን ተስፋ የሰጡትን ቃል ለመጠበቅና በሚሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ግድ የለሾች ነበሩ። 

የመንፈሳዊ ስጦታዎችን አገልግሎት በልግስና ለማከናወን የመስጠት ተግባር ምትክ ሊሆን ይችላል ብለን ልንከራከር አይገባም። «በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ስለማስተምር፥ መስጠት አያስፈልገኝም» የሚለው ማመካኛ እንጂ፥ አጥጋቢ የማሳመኛ ነጥብ አይደለም። ስጦታዎቹ በእርግጥም ስጦታዎች እንደ ሆኑ የሚያስብ ክርስቲያን ምን ጊዜም የሚነሣው ለሌሉች ለመስጠት እንጂ በጌታ አገልግሎት ሽፋን «ልደበቅ» አይልም። እኔንም ቢሆን፥ አንዳንድ ሙሉ ጊዜያቸውን ለጌታ አገልግሎት በማዋላቸው፥ ለመስጠት እንደማይገደዱ በመግለጽ የተከራከሩኝ መጋቢዎችና ሚሲዮናውያን አጋጥመውኛል። ጳውሎስ ከዚህ የሚቃረን አሳብ ነበረው፡- ከእግዚአብሔር ዘንድ ግሩም ስጦታ ስለ ተሰጣችሁ፥ አብልጣችሁ ለመስጠት መሻት አለባችሁ። 

ከዚህም ሌላ ጳውሎስ እንዲሰጡ ያዘዛቸው ራሱ እንዳልሆነ በግልጽ እንዲያውቁት ይጠነቀቅ ነበር። እንዲያውም የቆሮንቶስን ሰዎች አመለካከትና ከመቄዶንያ ሰዎች ጋር እያነጻጸረ ነበር። የመቄዶንያ ክርስቲያኖች የጌታን ምሳሌ እየተከተሉ መሆናቸውን በግልጽ መሰከረ፡ ድሆች ሆነው ሳሉ ሰጡ። ከዚህም በመነሣት የቆሮንቶስ ሰዎች ጳውሎስን እንደሚወዱት ይናገሩ ስለ ነበር፥ በሚሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ተካፋይ በመሆን ፍቅራቸውን እንዲያረጋግጡለት ይጠይቃቸዋል። በጸጋ መስጠት የፍቅርን መኖር የሚያረጋግጥ ነው . ለክርስቶስ፥ ላገለገሉ የእግዚአብሔር ባሪያዎችና እኛ ልናቃልልላቸው የምንችለው ልዩ ችግር ላለባቸው ሰዎች ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ነው። 

በመጨረሻም፥ ስጦታቸው እንደ መሥዋዕትነት የሚቆጠር ነበር (ቁ 9)። ኢየሱስ ባለጸጋ የሆነው በምን መንገዶች ነበር? በመሠረቱ ዘላለማዊ አምላክ እንደ መሆኑ፥ በስብዕናው ባለጸጋ ነበር። የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ እንደ መሆኑ፥ ባሉት ነገሮችና ባለው ሥልጣን ባለጸጋ ነበር። ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ስለሚችል፥ በኃያሉ ባለጸጋ ነበር፡፡ ይሁንና እነዚህም ሆኑ ሌሉችም አያሌ ብልጽግናዎች እያሉት ድሀ ሆነ። 

የአንቀጹ የጊዘ አመልካች እንደሚያሳየው፥ በዚህ ሥፍራ ድህነት የተባለው ሥጋ መልበሱ፥ በቤተልሔም መወለዱ ነው። ራሱን ወደ ሰው ደረጃ ዝቅ አደረገና ሰብዓዊ ባሕርይ ተላበሰ። ባሪያ ለመሆን ዙፋኑን ለቆ መጣ። ያለውን ነገር ሁሉ ወደ ጎን ስለ ተወ፥ ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ እንኳ አልነበረውም። ከሁሉም በላቀው ጉስቁልና ውስጥ ያለፈው፥ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንደ ኃጢአተኛ በተቆጠረ ጊዜ ነበር። ገሃነመ እሳት ዘላለማዊ የድህነትና የጉስቁልና ስፍራ በመሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የድሆች ሁሉ ድሀ ሆነ። 

ለምን ይህን አደረገ? እኛ እንበለጽግ ዘንድ ነው! ይህም ኢየሱስ ክርስቶስን ከማግኘታችን በፊት ድሆችና ሙሉ ለሙሉ ጎስቋሎች እንደ ነበርን ያመለክታል። ይሁንና አሁን በእርሱ ስላመንን፥ የብልጽግናዎቹ ሁሉ ተካፋዮች ሆነናል! አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን፥ «የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን» (ሮሜ 8፡17)። ይህ እውነት ሆኖ ሳለ፥ እንዴት ለሌሉች ከመስጠት እንቆጠባለን? እኛን ለማበልጸግ እርሱ ድሀ ሆነ። ሲበዛ ድሀና ጎስቋላ ቢሆኑ፥ የመቄዶንያ አብያተ ክርስቲያናት የእርሱን ፈለግ በመከተል አብዝተው እንደ ሰጡ፥ እኛስ ምሳሌነቱን ልንከተል አንችልም ይሆን? 

በፈቃደኝነት ስንሰጥ (2ኛ ቆሮ. 8፡10-12) 

ቃል ኪዳን በመግባትና የተገባውን ቃል ከተግባር ላይ በማዋል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። የቆሮንቶስ ሰዎች ከአንድ ዓመት በፊት በልዩው የርዳታ አሰባሰብ ውስጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረከቱ ለቲቶ በትምክህት ተናግረው፤ ዳሩ ግን ቃላቸውን አላከበሩም ነበር (ቁ 6)። ጳውሎስ ከቁጥር 10-12 በፈቃደኛነት ላይ ትኩረት እንዳደረገ ልብ በል። በጸጋ የመስጠት ተግባር ከልብ መመንጨት አለበት እንጂ፥ ሰግድ ወይም በጉልበት የሚከናወን አይደለም። 

በአገልግሎት ላይ ባሳለፍኋቸው ዓመታት ውስጥ ብዙ ልመናዎች ታግሼአለሁ። ለማመን ስለሚያዳግቱ የድህነት ታሪኮች አሳዛኝ ገጽታም ሰምቻለሁ። ገንዘቤን እንዳካፍል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በቀረቡልኝ የተለመዱ የማታለያ ዘዴዎችም ለመሳቅ ተገድጃለሁ። ተግሣጽ፥ አሳፋሪ ሁኔታና ዛቻም ሳይቀር ተሰንዝሮብኛል፤ ዳሩ ግን ከእነዚህ ዘዴዎች አንዳቸውም ከዕቅዴ በላይ እንድሰጥ አላነሣሱኝም። እንዲያውም፥ የገንዘብ ፈላጊዎቹ ዓለማዊ አቀራረብ ስላሳዘነኝ፥ ከዕቅዴ በታች የሰጠሁባቸው ጊዜያትም ነበሩ። (ዳሩ ግን ከተንዛዛ የልመና ተግባር የተነሣ፥ በመበሳጨቱ፥ ለመስጠት ያቀደውን መከልከል ብቻ ሳይሆን፥ ከሙዳይ ምፅዋቱ ገንዘብ ቀምቶ መውሰዱን እንደ ተናገረው ማርክ ትዋይን ዓይነት የሚያስገርም አላደረግሁም!) 

መፍቀድና ማድረግ ጎን ለጎን የሚሄዱ ስለ ሆኑ፥ እዚህ ላይ መደናገር የለብንም። ለመስጠት ያለው ፈቃደኝነት እውነተኛና በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ፥ «በተግባር መገለጹ» የማይቀር ነው (ቁ 11፤ ፊልጵ 2፡12-13)። ጳውሎስ ፈቃደኛነት የማድረግ ምትክ ነው በማለት አልተናገረም፤ አይደለምም። ዳሩ ግን ስጦታችን በጸጋ የተነሣሣ ከሆነ፥ ስለ ተገደድን ሳይሆን፥ በፈቃዳችን እንሰጣለን። 

እግዚአብሔር የሚመለከተው «የልብን ስጦታ» እንጂ «የእጅን ስጦታ» አይደለም። ልብ ብዙ ለመስጠት ቢፈልግና ዳሩ ግን ይህንኑ ለማድረግ ባይችል፥ እግዚአብሔር ሁኔታውን ተመልክቶ በዚያው መሠረት ይመዘግባል። ዳሩ ግን እጅ ልብ ሊሰጥ ከሚፈልገው በላይ ቢሰጥ፥ እጅ የሰጠው ገንዘብ ምንም ያህል ቢበዛ፥ እግዚአብሔር የሚመዘግበው በልብ ውስጥ የተቀመጠውን ነው። 

አንድ ወዳጄ ለሥራ ወደ ሌላ አገር ሊሄድ ተነሥቶ ነበርና ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄዳቸው በፊት ባለቤቱ ለቤት ወጪ የተወሰነ ተጨማሪ ገንዘብ እንደምትፈልግ አስታወሰችው። እርሱም ልክ መባው ሊሰበሰብ ሲል፥ የተወሰነ ገንዘብ ከእጄ ላይ ጣል አደረገ፤ እርሷም የሰጣት ለሳምንታዊው የመባ አስተዋፅኦ ስለ መሰላት፥ በመባ መሰብሰቢያው ሙዳይ ውስጥ ጨመረችው። ዳሩ ግን ያ ገንዘብ ለሳምንቱ የሰጣት የቤት ወጪ ነበር። 

ወዳጄም «የሰጠነው ለጌታ ነውና እርሱም መዝግቦ ያቆየዋል» አለ። 

መጋቢያቸው ግን፥ «ምን ያህል ለመስጠት ወስናችሁ ነበር» ሲል ጠየቀ። ቁጥሩን ነገረው። 

መጋቢውም «እንግዲህ እግዚአብሔር የመዘገበው ይህንኑ ይሆናል፤ 

የልባችሁን መሻት አይቶአልና» በማለት መለሰ። 

እግዚአብሔር የሚመለከተው የምንሰጠውን ሳይሆን፥ የምንሰጠውን መጠን ነው። ከለገስነው በላይ ልንሰጥ የምንችል ብንሆንና ዳሩ ግን ባናደርገው፥ እግዚአብሔር ያንን ያያል። የበለጠ ለመስጠት ፈልገን ባይሞላልን ደግሞ ያንኑ ይመለከታል። ባለን አቅም በፈቃደኝነት ስንሰጥ፥ በጸጋ መስጠትን እየተለማመድን ነው ማለት ነው። 

በእምነት ስንሰጥ (2ኛ ቆሮ.8፡13-24) 

ጳውሎስ ድሀው ይበለጽግ ዘንድ ሀብታሙ እንዲደኸይ እየተናገረ አልነበረም። አንድ ክርስቲያን የሌላውን ሰው ዕዳ ለመክፈል ብሉ ለራሱ በዕዳ ውስጥ ቢዘፈቅ ይኼ አዋቂነት አይሆንም . የገባበትን ዕዳ መልሶ ለመክፈል እስካልቻለ ድረስ ስህተት ፈጽሟል። ጳውሎስ በሂደቱ ሁሉ ውስጥ «ሚዛናዊነትን» ይሻል፡- አሕዛብ በአይሁዶች አማካይነት በመንፈሳዊ ሀብት ስለ በለጸጉ፥ አይሁዶችም በተራቸው በቁሳዊ ነገሮች በአሕዛብ መበልጸግ ነበረባቸው (ሮሜ 15፡25-28 ተመልከት)። 

በተጨማሪም፥ በወቅቱ በይሁዳ የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በጭቆና ቀንበር ሥር ወድቀው ሳለ፥ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ግን በቁሳዊ ሀብት በልጽገው ነበር። ያ ሁኔታ አንድ ቀን ሊለወጥ ይችል ነበር። የአይሁድ አማኞች አሕዛብን የሚረዱበት አንድ ወቅት ወደ ፊት ሊከሰት ይችላል። 

ዳሩ ግን ይህን ሁኔታ የሚያስተካክለው ማነው? እግዚአብሔር ነው! ይህን ለማብራራት ጳውሎስ የመናን ተአምርና መመሪያ በመጥቀስ በምሳሌነቱ ተጠቅሞበታል (ዘጸ 16፡18)። አይሁዶች በየዕለቱ የቱንም ያህል መና ቢሰበስቡም፥ ዳሩ ግን ለሁሉም የሚያስፈልጋቸውን ያህል ያገኙ ነበር። መናውን ለማከማቸት የሚሞክሩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ይህን ለማድረግ እንደማይቻል ተረድተው ነበር። መናው አንድ ቀን ካደረ ይበሰብስና ይሸት ነበር (ዘጸ 16፡20)። ትምህርቱ ግልጽ ነው፡ የሚያስፈልግህን ያህል ሰብስብ፤ የሚችሉትን ያካፍሉ፤ የእግዚአብሔርን በረከቶች ለማከማቸት አይሞክሩ። እግዚአብሔር እርሱን ከተማመኑና ቃሉን ከጠበቅህ፥ በችግር ውስጥ እንዳትወድቅ ይጠነቀቅልሃል። 

ለመስጠት የሚያነሣሣን በሕይወታችን ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መንፈሳዊ በረከት ሲሆን፥ ዳሩ ግን ለመስጠት መለኪያ የሚሆነን የእግዚአብሔር ቁሳዊ በረከት ነው። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው በመጀመሪያ ደብዳቤው፥ «ከእናንተ እያንዳንዱ በየሳምንቱ በፊተኛው ቀን እንደ ቀናው መጠን እያስቀረ በቤቱ ያስቀምጥ» (1ኛ ቆሮ. 16፡2) በማለት አሳቡን በግልጽ አካፍሏቸዋል። በጸጋ የመስጠቱ ተግባር በአሥራት (ከ10 እጅ አንድ እጅ) ስለማይወሰን፥ ጳውሎስ ምንም የሒሳብ ስሌት መመሪያ ለማስቀመጥ አልሞከረም። በጸጋ መስጠት እንዴት እንደምንሰጥ የምንወስነው እንጂ በሕግ መልክ የሚደነገግ አይደለም። በጸጋ መስጠት እንችላለን ብለን በሕሊናችን በምናሰላው የገንዘብ መጠን ምን ጊዜም አይረካም። 

«የገቢያችንንና ወጪያችንን ሚዛናዊነት» የሚጠብቀው እግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ ጳውሎስን ከኮሚኒዝም ጋር የተመሳሰለ ትምህርት ስለ ማስተማሩ አንወቅሰውም። እንዲያውም፥ 2ኛ ቆሮንቶስ 8:13 ኮሚኒዝምን በቀጥታ የሚቃወም ክፍል ነው። «ኮሚኒዝም» የሚባለው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ (የሐዋ. 2፡44-47፤ 4፡32-37) ዛሬ ከሚታወቀው ኮሚኒስታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዘይቤ ጋር ምንም ዝምድና የለውም። የጥንቱ ክርስቲያኖች (እንደ ዛሬዎቹ በርካታ ክርስቲያኖች) የነበራቸውን ነገር በፈቃዳቸው ለሌሎች አካፈሉ እንጂ፥ ሰዎች በዚህ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ አላስገደዱዋቸውም። ዕቅዱም ራሱ ጊዜያዊ ነበር፤ ጳውሎስ በወቅቱ ችግር ላይ የነበሩትን ክርስቲያኖች ሁኔታ ለማሻሻል የተለየ የርዳታ ገንዘብ አሰባስቦ የመውሰዱ እውነታ፥ ዕቅዱ በኋለኞቹ የክርስቲያን ትውልዶች እንዲዘወተር ታስቦ እንዳልተደረገ የሚያረጋግጥ ነው። 

በጸጋ መስጠት የእምነት ጉዳይ ነው፡- የሌሉችን ጉድለት በምናሟላበት ጊዜ እግዚአብሔር የእኛንም ጉድለት እንደሚያሟላልን እናምናለን – እንታዘዘዋለንም። አይሁዶች በየቀኑ መና ይሰበስቡ እንደነበር እኛም «የዕለት እንጀራችንን» እንዲሰጠን በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን (ማቴ. 6፡11)። እግዚአብሔር የሚሰጠንን ነገር ማባከንም ሆነ ማከማቸት የለብንም። በእግዚአብሔር ፈቃድ መቆጠቡ ትክክል ነው። (አይሁዶች ዓርብ ዕለት የወረደውን መና ለሰንበት ዕለት (ቅዳሜ) ይቆጥቡ ነበር፤ መናውም አይበሰብስም ነበር (ዘጸ 16፡22-26]፡፡ ዳሩ ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ ሆነን የምናከማቸው ሀብት ይጎዳን እንደሆን እንጂ አይጠቅመንም (ያዕ. 5፡1-6 ተመልከት)። 

ጳውሎስ ከቁ. 16 ጀምሮ፥ ዋንኛውን መንፈሳዊ መመሪያ መስጠቱን በመግታት፥ ልዩ መዋጮው ስለሚሰበሰብበት ሁኔታ አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮችን ወደ መስጠቱ ይመለሳል። በጸጋ መስጠት በእምነት መስጠት መሆኑ እውነት ሆኖ ሳለ፥ በጸጋ መስጠት በዘፈቀደ መስጠት እንዳለሆነም እውነት ነው። ለሌሉች የሚያካፍለው ክርስቲያን፥ የሚሰጠው ነገር በታማኝነት መከናወኑን ማረጋገጥ አለበት። 

እኔም ለዓመታት ያህል ምዕመናን ታማኝ ለሆኑት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ሞክሬአለሁ። በዚያው መጠን ታማኝነት ለሚጎድላቸው ድርጅቶች ምዕመናን እርዳታ እንዳያደርጉ አስጠንቅቄአለሁ። ዳሩ ግን ማስጠንቀቂያዩን ችላ ብለው የሰጡት አንዳንዶቹ፥ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ እኔ መጥተው፥ «ለዚያ ድርጅት ቼክ ልኬ ነበርና አሁን ግን መታለሉን ተረድቻለሁ» ይሉኛል። እኔም ተከዝ ብዩ፥ «እንዳታደርጉት አስጠንቅቄአችሁ ነበር» እላለሁ። 

«እንግዲህ፥ ጌታ ልቤን ያውቀዋል፤ ገንዘቡ ቢባክንም ቅሉ፥ ትርፌን በመንግሥተ ሰማይ አገኘዋለሁ» ሲሉ ይከራከሩኛል። 

በጸጋ መስጠት ማለት በሞኝነት መስጠት ማለት አይደለም። በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንኳ፥ የመዋዕለ-ንዋይ ጉዳይ የሚያከናውኑ ሰዎች የተወሰኑ ብቃቶች ቢኖሯቸው መልካም ነው። ጳውሎስ የ«ሃይማኖታዊ ሌብነት»ን ዝና ስላልፈለገ፥ ከእጁ የገባውን የአደራ ገንዘብ በጥንቃቄ ስለሚይዝበት ሁኔታ በብርቱ ይጨነቅበት ነበር። በመሆኑም በሚሰበሰበው መዋጮ ውስጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ አብያተ ክርስቲያናት የተወሰኑ ወኪሉች ከእርሱ ጋር እንዲሄዱ ያስመርጥ ስለ ነበር፥ ሁሉም ነገር በታማኝነት፥ በአግባብና በሥርዓት ይፈጸም ነበር። 

በመጋቢነት ባገለገልሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ የሰንበት ትምህርት ክፍሎች በአንድኛው፥ አንድ ወጣት ምጽዋቱን ሲሰበስብ፥ ሲቆጥር፥ ብሉም አሁንም ራሱ ሲመዘግብና ከዚያም ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት ቢሮ ሲወስድ ታዝቤአለሁ። በመሆኑም ለማስፈራራት ብዩ ሳይሆን፥ አንድ ሰው የከሰሰው እንደ ሆነ አደገኛ ሁኔታ እንደሚደርስበት ገለጽሁለት፡- ገንዘቡን በታማኝነት ስለ ማስረከቡ ሊያረጋግጥ የሚችልበት መንገድ ወይም ምስክር የለውምና! እኔም «በበኩሌ አምንሃለሁ፤ ዳሩ ግን ሊከታተሉህና የትችት ቀዳዳ ሊያገኙብህ የሚሹትን ሰዎች አላምናቸውም» አልሁት። ሰውየው አሳቤን ተቀብሎ በመጠቀም ፈንታ፥ በጣም ተቆጣና ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሎ ሄደ። 

በየትኛውም መንፈሳዊ ዘርፍ . አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፥ የሚሲዮን ድርጅት፥ የወንጌላውያን ስብሰባ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች፥ የእግዚአብሔርን ገንዘብ የሚይዙ ከሆነ፥ የሚከተሉት ባሕርያት ሊኖሯቸው ይገባል። 

1. ከእግዚአብሔር የተሰጠ የማገልገል መሻት (2ኛ ቆሮ. 8፡16-17)። ጳውሎስ ቲቶን አላዘዘውም፤ ወጣቱ በልዩ መዋጮው ውስጥ የማገልገል መሻት በልቡ ውስጥ አድሮ ነበር። ሆኖም ግን ብዙውን ጊዜ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንደሚታየው፥ በዚህ መስመር ጌታን የማገልገል እውነተኛ መሻት የሌላቸው ሰዎች በመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴ ውስጥ ይሰየማሉ። ከሁሉም በላይ፥ የጌታን ገንዘብ የሚይዝ ሰው ከእግዚአብሔር አሳብ ጋር የሚስማማ ልብ ሊኖረው ይገባል። 

2. ለጠፉት ነፍሳት የሚሰማው ሸክም (2ኛ ቆሮ. 8፡18)። ይህ ወንድም ማን እንደ ነበር ባናውቅም፥ ዳሩ ግን ወንጌሉን የማጋራት ምስክርነት ስለ ነበረው እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ወንጌላዊ ሳይሆን ባለመቅረቱም፥ ቢያንስ በአብያተ ክርስቲያን አካባቢ፥ ነፍሳትን ለማዳን ሸክም የሚሰማው በመሆኑ የሚታወቅ ነው። ዳሩ ግን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዕጩዎችን የሚመርጡ ኮሚቴዎች «ነፍሳት በመማረኩ» ረገድ መልካም ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች፥ በወንጌል አገልግሎት ኮሚቴ ወይም በሚሲዮን ኮሚቴ ውስጥ ያስቀምጣሉ፤ እርግጥ ይህም ቢሆን ተገቢ ነው። ሆኖም ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴ ወይም በንብረት ተቆጣጣሪ ቦርድ ውስጥ መግባት አለባቸው። ለምን? ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች ለማቃናት! ነፍሳትን ለመማረክ አገልግሎት የሚውል ወጪ ለመመደብ በጅ የማይሉ ኮሚቴዎች፡ ለሕንፃዎች ግንባታና ለቁሳቁስ መግዣ ከፍተኛ አኀዝ ያዘለ ገንዘብ ሲመድቡ ተመልክቻለሁ። 

አንድ ዕለት አንድ ተስፋ የቆረጠ ወጣት መጋቢ ምክር ጠይቆኝ ነበር። «የመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴዎችን ለመወሰን ድፍረት በማጣቱ እያሳሰበኝ ነው። የኢኮኖሚ ሁኔታ ማናቸውንም ወጪ ለመመደብ እጃቸውን አሥሮታል። ጨርሶ ገንዘብ አይደማቸውም . በባንክ ቤት ደግሞ ብዙ ትርፍ ገንዘብ አለን» በማለት አጫወተኝ። ከዚህ ኮሚቴ ጋር ተገናኝቼ ባላውቅም፥ ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ሰዎች አንድ ነገር ለመረዳት ችያለሁ። የኃጢአተኞችን ሰዎች ሸክም የመጋፋት ስሜት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ 

3. እግዚአብሔርን ለማስከበር መሻት(2ኛ ቆሮ.8፡19)። ብዙውን ጊዜ የመዋዕለ-ንዋይ ዘገባዎች ቤተ ክርስቲያንን፥ ወይም የተለዩ የርዳታ ሰጪ ቡድኖችን እንጂ፥ እግዚአብሔርን አያስከብሩም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሥራ ዘርፍ ውስጥ «ለዓለማዊና ለተቀደሰ» ተግባር ወይም «ለንግድና ለአገልግሎት» የሚባል ክፍፍል የለም። የምናደርገው ነገር ሁሉ ለጌታ «የተቀደሰ ሥራ» እና አገልግሎት ብቻ ነው። አንድ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ፥ ዲያቆናት (ወይም ሽማግሌዎች) «መንፈሳዊ ጉዳዮችን እንደሚይዙ» እና ንብረት ክፍሎች ደግሞ «ቁሳዊና የመዋዕለ-ንዋይ ጉዳዮችን እንደሚያከናውኑ» በሚናገርበት ጊዜ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለውን ገደብ ማበጀቱ ነው። ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የምትችለው ከሁሉም የላቀው ነገር በጥበብ ገንዘቧን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ማዋል ነው። 

እግዚአብሔር የሚሰጠንን ነገር እርሱ በሚፈልገው መንገድ በመጠቀም እናከብረዋለን። የቤተ ክርስቲያንን መዋዕለ-ንዋይ የሚቆጣጠሩ ሰዎች እግዚአብሔርን የማስከበር ተጨማሪ ሸክም እስከሌላቸው፥ ብዙም ሳይቆይ ገንዘቡን የእግዚአብሔርን ስም በሚያሰድብ መንገድ መጠቀሚያ ሊያደርጉት ይጀምራሉ። 

4. በታማኝነት መልካምን ስም ማግኘት (2ኛ ቆሮ. 8፡20-22)። ጳውሎስ ከአብያተ-ክርስቲያናት የተወከሉትን ሰዎች በደስታ እንደ ተቀበለ ገልጾአል። ምንም ዓይነት ነቀፋ እንዲሰነዘርበት አልፈለገም ነበር። «ጌታ እኛ የምንሠራውን ይመለከታል!» ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም። ሰዎች የምንሠራውን ነገር ለማየት እንደሚችሉ መረዳት አለብን። ጄ. ቢ. ፊልጵስ ቁጥር 21ን በጥሩ ሁኔታ ተርጉመውታል፡ «በመዋጮው ክፍፍል ውስጥ ምንም ዓይነት ትችት እንዲነሣ አንፈልግም፤ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን፥ በሰዎች ፊት ጭምር ሙሉ ለሙሉ ከነቀፋ ነጻ ለመሆን እንሻለን።» 

በበኩሌ መልካም ስም ካለው ኮሚቴ ወይም ቦርድ፥ ወይም ድርጅት ጋር በሆነ መንገድ ኅብረት የማያደርገውን ክርስቲያን አገልጋይ ወይም ሚሲዮናዊ አልደግፍም። እንዲሁም የሒሳብ መዝገቡ ተመርምሮ ለረጂዎቹ ዘገባ የማይቀርብበትንም አገልግሎት አልደግፍም። ይህን ስል በግል የሚሠሩ ክርስቲያን አገልጋዮች ሁሉ ታማኞች አይደሉም ማለቴ ሳይሆን፥ ዳሩ ግን የመዋዕለ-ንዋይ ድጋፋቸውን ከሚቆጣጠር ቦርድ ወይም ድርጅት ጋር ኅብረት ቢያደርጉ የበለጠ በአገልግሎታቸው ላይ መተማመን ይኖረኛል ማለቴ ነው። 

በቁጥር 22 ላይ ትጋትን አስመልክቶ የተሰጠውን አጽንኦት አስተውል። መዋዕለ-ንዋይን ለመያዝ የሚያስፈልግ አንድ ነገር ቢኖር፥ ትጋት ነው። የገቢና ወጪን ወቅታዊ ዘገባዎች በትክክል ስለማያቀርቡትና «ምንም ጊዜ እንደ ሌላቸው» በማመካኘት፥ ዓመታዊ ዘገባዎችን በግድየለሽነት ስለሚያከናውኑ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ያዦች ብዙ ጊዜ ሰምቻለሁ። እንግዲህ በዚያ ክፍል ውስጥ ባይሠሩ ምንኛ መልካም ነበር! 

5. ተባባሪ መንፈስ (2ኛ ቆሮ. 8፡23-24)። ቲቶ ለዚህ አገልግሎት ልቡን መስጠት ብቻ ሳይሆን (ቁ 16) እንዴት መልካም «የቡድን አባል» መሆን እንደሚቻልም ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ቲቶን «አብሮኝ የሚሠራ» በማለት ይጠራዋል። ቲቶ፥ ገና በመጀመሪያው ስብሰባ ላይ፥ «በዚህ ኮሚቴ ውስጥ እስካለሁ ድረስ፥ በሙሉ ድምፅ ድጋፍ የሚተላለፍ ውሳኔ አይኖርም» ሲል እንደሰማሁት የኮሚቴ አባል አልነበረም። 

የመዋዕለ-ንዋይ ኮሚቴ አባላት የገንዘቡ ባለቤቶች አይደሉም፡ ገዝነቡ የጌታ ነው። ኮሚቴው ገንዘቡን በታማኝነትና በጥንቃቄ ለጌታ አገልግሎት ከማዋል የበለጠ ኃላፊነት የለውም። እንዲሁም ጳውሎስ ኮሚቴውን የአብያተ ክርስቲያናት ልዩ አገልጋዮች አድርጎ እንደ ተመለከተ ልብ በል። ይህ የተለየ «የርዳታ ገንዘብ» የአሕዛብ አብያት-ክርስቲያናት በመተሳሰር ለሚያከናውኑት ተግባር የሚውል እንጂ፥ ጳውሎስና ተወካዮቹ የአብያተ ክርስቲያናት «መልእክተኞች» ከመሆን ውጪ፥ ውሳኔ የሚሰጡ አልነበሩም። «ለተለየ ተልዕኮ የተላከ ሐዋርያ» የሚለውን ቃል የሚተካልን የግሪኩ ቃል «አፖስቶሉስ» የሚል ነው። እነዚህ ራሳቸውን የሰጡ ክርስቲያኖች፥ ለአብያተ ክርስቲያናት ሥራቸውን በታማኝነትና በስኬታማነት ማከናወንን ግዴታቸው መሆኑን አምነው ተቀብለውት ነበር። 

በጸጋ መስጠት ደስ የሚያሰኝ ልምምድ ነው። «በእምነት አማካኝነት በጸጋ» መስጠትን ስትለማመድ (ልክ በዳኑበት መንገድ – ኤፌ 2:8-9)፥ ከነገሮችና ከሁኔታዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ ነጻ መውጣት ትጀምራለህ። ለነባራዊ ሁኔታዎች ተገዢ በመሆን ፈንታ፥ አዳዲስ እሴቶችንና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ወዲያውኑ የመፈጸም ልምድ ታዳብራለህ። ከእንግዲህም ሕይወትን ወይም ሌሎች ሰዎችን በገንዘብ ወይም በንብረት ላይ ተመሥርተው አትለካም። ገንዘብ ከሁሉም የሚልቀው የስኬታማነት መለኪያ ቢሆን ኖሮ፥ ኢየሱስ ድሀ ስለ ነበር፥ ከውዳቂዎች በተቆጠረ ነበር! 

በጸጋ መስጠት ሌሉችን የማበልጸጉን ያህል አንተንም ያበለጽጋል። በጸጋ መስጠት ይበልጥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድትመስል ያደርግሃል። በጸጋ የመስጠትን ደስታ ተረድተኸው ይሆን?

Leave a Reply

%d bloggers like this: