የወደፊት ተስፋ አለን (2ኛ ቆሮ. 5፡1-8)

«ይህ አገልግሎት አለን … ይህ መዝገብ … አለን .. ያው አንዱ የእምነት መንፈስ አለን … ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ (አለን)» (4፡1፥ 7፥ 13፤ 5፡1)። ይህ ጳውሎስ ስለ ክርስትና እምነት እውነታ የሰጠው ምስክርነት ምንኛ ድንቅ ነው! 

በጥቅሱ ውስጥ «የእግዚአብሔር ሕንፃ» ተብሎ የተገለጸው በዮሐንስ 14፡1-6 ውስጥ የምናገኘው ቃል የተገባለት የአማኙ ሰማያዊ ቤት ሳይሆን፥ የሚለብሰው የከበረ አካል ነው። ጳውሎስ ድንኳን ሠሪ ሲሆን (የሐዋ. 18፡1-3)፥ በዚህ ስፍራ ድንኳንን የአሁኑ ምድራዊ ሕይወታችን መግለጫ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ድንኳን ደካማ፥ መሠረቱ ጊዜያዊ የሆነና ብዙም ውበት የሌለው ሲሆን፥ ዳሩ ግን ወደፊት የምናገኘው የከበረው አካል፥ ዘላለማዊ፥ ውብና የድካም ወይም የመበስበስ ምልክት የማይታይበት ነው(ፊልጵ. 3፡20-21 ተመልከት)። ጳውሎስ የሰውን ሰውነት እንደ ምድራዊ ዕቃ (2ኛ ቆሮ 4፡70 እና ጊዜያዊ ድንኳን አድርጎ ይመለከታል፤ ዳሩ ግን አማኞች አንድ ቀን ከድንቅኛው የመንግሥተ ሰማይ ድባብ ጋር የሚስማማ ውብና የከበረ አካል እንደሚለብሱ ያውቅ ነበር። 

በዚህ አንቀጽ ውስጥ የጳውሎስን ምስክርነት መመልከት አስደሳች ነው። 

እናውቃለን (2ኛ ቆሮ. 5:10)። እንዴት እናውቃለን? በእግዚአብሔር ቃል ስለምንተማመን። ማንኛውም ክርስቲያን ወደፊት ምን እንደሚሆን ወይም ከሞት በኋላ ስለሚሆነው ነገር ለማወቅ፥ ዕድል-ተንባይ፥ ጨሌጣይ፥ መናፍስት ጠሪ፥ ወይም ሞራ ገላጭ ማማከር አያሻውም። እግዚአብሔር ማወቅ የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ በሰፈረባቸው ገጾች ላይ አስቀምጧል። ጳውሎስ «እናውቃለን» የሚለው በ4፡14 ላይ ከሚገኘው «እውቀት» ጋር የተያያዘ ሲሆን፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ይዛመዳል። እርሱ ሕያው ስለ ሆነ፥ ሞት በእኛ ላይ እንደማይሰለጥን እናውቃለን። «እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ» (ዮሐ 14፡19)። 

ድንኳናችን «ቢወድቅ» መሥጋት የለብንም። ሰውነት የምንኖርበት ቤት ብቻ ነው። አንድ አማኝ በሚሞትበት ጊዜ፥ ሰውነቱ ወደ መቃብር ይገባል፤ ዳሩ ግን መንፈሱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመኖር ወደ ሰማይ ይሄዳል (ፊልጵ. 1፡20-25)። ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲመለስ፥ የሞተውን ሰውነት በክብር ያስነሣውና፥ ሰውነትና መንፈስ በመንግሥተ ሰማይ ለዘላለም በክብር ለመኖር ይዋሃዳሉ (1ኛ ተሰ. 4፡13-18፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡35-58)። 

እንቃትታለን (2ኛ ቆሮ. 5፡2-5):: ጳውሎስ ለመሞት ያለውን ከፍተኛ መሻት እየገለጸ አልነበረም። እንዲያውም ዓረፍተ ነገሩ የዚህ ተገላቢጦሽ ነው። የከበረውን አካል «ይለብስ ዘንድ» ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመለስ ያለውን ጉጉት የሚያሳይ ነበር። ጳውሎስ ሰውነትን በድንኳን በመመሰል ሦስት አስተያየቶችን አቅርቦአል፡- 1) ሕያው – በድንኳን ውስጥ የሚኖር፤ 2) ምውት – እርቃኑን ያለ፥ ከድንኳን ውጭ የወጣ፥ 3) ልብስ የደረበ – ክርስቶስ ሲመለስ የሚፈጸመው የሰውነት መለወጥ። ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ሕያው ሆኖ በምድር ላይ እንደሚኖርና በሞት ልምምድ ውስጥ እንደማያልፍ ተስፋ ያደርግ ነበር። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15:51-58 ውስጥ በተመሳሳይ መግለጫ የተጠቀመ ሲሆን፥ በሮሜ 8፡22-26 ውስጥ ደግሞ የ«መቃተት»ን አሳብ አቅርቧል። 

የከበረው አካል በ2ኛ ቆሮንቶስ 5፡1 ላይ «በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ … ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ» ተብሎ ሲጠራ፥ በቁጥር 2 ላይ ደግሞ «ከሰማይ የሚሆነው መኖሪያችን» ተብሏል። ይህ ከምድር አፈር ከተሠራው ሟች ሥጋችን ጋር የሚቃረን ነው። «የዚያን የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን» (1ኛ ቆሮ. 15፡49)። ጳውሎስ የሚቃትተው ሰብዓዊ ሰውነት ለብሶ ስለሚኖር ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማየትና የከበረ አካል ለማግኘት ስለ ናፈቀ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። ለክብር እየቃተተ ነበር! 

ይህም አባባሉ ሞት ክርስቲያኖችን ለምን እደማያሸብር ግልጽ ያደርግልናል። ጳውሎስ ምድራዊ ሞቱን «መለየት» ብሎታል (2ኛ ጢሞ. 4፡6)። የዚሁ የግሪክ ቃል አንድኛው ትርጉም፥ «ድንኳን ነቅሉ ወደ ሌላ ስፍራ መጓዝ» የሚል ነው። ሆኖም ግን እኛ አንድ ቀን የጌታችንን የከበረ አካል የሚመስል አዲስ አካል እንደሚኖረን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? እርግጠኞች መሆን የምንችለው መንፈስ ቅዱስ ከውስጣችን ስለሚኖር ነው። ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 1፡22 ላይ የመንፈስ ቅዱስን ማተምና መያዣነት ጠቅሶአል (በተጨማሪም ኤፌ. 1፡13-14 ተመልከት)። በአማኙ ውስጥ የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ፥ የከበረውን አካል ጨምሮ፥ የወደፊቱን ውርስ የሚያረጋግጥ «መያዣ» ነው። በዘመናዊ የግሪክ ቋንቋ፥ መያዣ ተብሎ የተተረጎመው ቃል «የእጮኛ ቀለበት» ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ለኢየሱስ ክርስቶስ የታጨች ስትሆን ፥ ሙሽራው መጥቶ ወደ ሠርጉ ሥነ-ሥርዓት እንዲወስዳት እየተጠባበቀች ነው። 

ሁልጊዜም ተማምነን እንኖራለን (2ኛ ቆሮ. 5፡6-8):: የእግዚአብሔር ሕዝብ ሊገኝ የሚችለው ከሁለቱ በአንድኛው ስፍራ ነው በሰማይ ወይም በምድር (ኤፌ 3፡15)። ከእግዚአብሔር ሕዝብ ውስጥ አንድም ሰው ቢሆን በመቃብር፥ በሲዖል፥ ወይም በሰማይና በምድር መካከል በሚገኝ በማንኛውም «መካከለኛ ስፍራ» ሊኖር አይችልም። በምድር ላይ የሚኖሩት አማኞች «ሰሥጋ ያድራሉ»፥ የሞቱት አማኞች ደግሞ «ከሥጋ ተለይተዋል»። በምድር ላይ የሚኖሩ አማኞች «ከጌታ ተለይተው በስደት የሚኖሩ» ሲሆኑ፥ በሰማይ ላይ ያሉት አማኞች ግን «በጌታ ዘንድ የሚያድሩ» ናቸው። 

ጳውሎስ የዚህ ዓይነት መተማመኛ ስለ ነበረው፥ ለመከራና ለሥቃይ፥ ወይም ደግሞ ለአደጋዎች አይሠጋም ነበር። ይህ ማለት ደግሞ አጓጉል የድፍረት እርምጃዎች በመውሰድ ጌታን ተፈታተነ ማለት ሳይሆን፥ ዳሩ ግን ለክርስቶስና ለወንጌሉ አገልግሎት «ሕይወቱን ለማጣት» ፈቃደኛ ነበር ማለት ነው። በእምነት እንጂ በማየት አልተመላለሰም። ለዘላለም የሚኖረውን የማይታይ ነገር እንጂ፥ ለጊዘው የሚታየውን አልመረጠም (2ኛ ቆሮ. 4፡18)። ለጳውሎስ፥ መንግሥተ ሰማይ የመድረሻው ግብ ብቻ ሳይሆን የሚያነቃቃውም ተስፋ ጭምር ነበር። በዕብራውያን 11 ውስጥ እንደምናገኛቸው የእምነት ጀግኖች ሁሉ፥ ሰማያዊቷን ከተማ በመመልከት ሕይወቱን ከዘላለማዊ እሴቶች አንጻር መርቷል። 

ይህንን የ2ኛ ቆሮንቶስ ክፍል በምንከልስበት ጊዜ፥ ጳውሎስ የገጠሙትን ችግሮች ለመቋቋም እንዴት ብርታት እንደ ነበረውና ተስፋ እንዳልቆረጠ ልንመለከት እንችላለን። ሕይወትን የለወጠ ክቡር አገልግሎት ነበረው። በሰውነቱ ምድራዊ ዕቃ ውስጥ ውድ መዝገብ ነበረውና ያንኑ መዝገብ ለሚጠፋው ዓለም ለማጋራት ፈለገ። ፍርሃትን ድል የሚነግ አስተማማኝእምነትና መድረሻና ማነቃቂያ ሆኖ ያገለገለው ብሩህ የወደፊት ተስፋ ነበረው። 

ስለዚህ ጳውሎስ «ከአሸናፊዎች የሚበልጥ» መሆኑ (ሮሜ 8፡37) ያን ያህል የሚያስደንቅ አይሆንም! 

በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው እያንዳንዱም አማኝ ከጳውሎስ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ድንቅ በረከቶች ስላሉት፥ ማንኛውንም የሚያጋጥመውን ችግር በእነርሱ አማካኝነት በብርታት ሊወጣ ይችላል። 

Leave a Reply

%d bloggers like this: