መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ መፍረድ የለብንም ሲል ምን ማለቱ ነው?

ምንጭ፣ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፣ አዳነው ዲሮ ዳባ

የአውደ ንባቡን ሃሳብ ወደጎን በመተውና ተገቢ ባልሆነ መንገድ በመተርጎም በስፋት ከሚጠቀሱ የኢየሱስ ንግግሮች መካከል አንዱና ዋናው “አትፍረድ” የሚለው ቃል ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ” (ማቴዎስ 7፡1)፡፡ ብዙ ሰዎች ይህን ጥቅስ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም፣ ተቺዎቻቸውን “ተሳስተሃል ልትለኝ መብት የለህም” ለማለት እና ዝም ለማሰኘት ይጠቀሙበታል፡፡ ቃሉን በተናጥል ወስደን ካየነው “አትፍረዱ” የሚለው ይህ ትእዛዝ በእርግጥም ሁሉንም አሉታዊ ምዘናዎች እንዳናደርግ የሚያግድ ይመስላል። ሆኖም፣ የሃሳቡን ሙሉ ትርጉም ለማግኘት ከአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ አውድ አንጻር መፈተሽ ይኖርብናል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ሲያዘን፣ ምንም አይነት የመለየት (የመፈተሽ) ሥራ አትሥሩ እያለ አይደለም፡፡ ኢየሱስ “አትፍረዱ” ባለበት በዚያው ምዕራፍ ውስጥ “…የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።”(ማቴዎስ 7፡6) ሲል አዟል፡፡ በዚው ስብከት ውስጥ ትንሽ ቁጥሮች ወረድ ብሎ፣ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ …”(ማቴዎስ 7፡15-16) ይላል። በትምህርቶች እና በምግባሮች ላይ መፍረድ ካልቻልን እንዴት “ውሾች”፣ “እሪያዎች” እና “ሐሰተኛ ነቢያት” እነማን እንደሆኑ መለየት እንችላለን? በሌላ አነጋገር፣ ኢየሱስ እዚህ ቦታ ላይ ትክክል የሆነውን ካልሆነው እንድንለይ ፈቃድ እንደሰጠን መገንዘብ ይገባል።

መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ሲያዘን፣ ሁሉም ተግባራት እኩል ሥነ ምግባራዊ ፋይዳ አላቸው ወይም እውነት አንጻራዊ ነው እያለ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የጸና፣ ዘላለማዊ እና ከእግዚአብሔር ባሕርይ ተነጥሎ የማይታይ መሆኑን በግልጽ ያስተምራል። ከእውነት ጋር የሚቃረን ማንኛውም ነገር ውሸት ነው፡፡ ይህን ነገር “ውሸት” ብሎ መጥራት ደግሞ ፍርድን ማስተለለፍ ነው፡፡ ዝሙትን ወይም ነፍስ ማጥፋትን ኃጢአት ብሎ መጥራት ከእግዚአብሔር እውነት ጋር መስማማት ብቻ ሳይሆን ፍርድን ማስተላለፍም ጭምር ነው፡፡ ኢየሱስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ሲናገር፣ ማንም ሰው  የእግዚአብሔርን የኃጢአት ትርጉም መሠረት በማድረግ ኃጢያትን ኃጢያት አይበል ማለቱ አይደለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ሲያዘን፣ ኃጢአትን በተመለከተ አቋም የለሽ እና መሃል ሰፋሪ እንድንሆን እየመከረ አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መሳፍንት (ፈራጆች) የሚል ርእስ ያለው መጽሐፍ ይገኛል፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ እነዚህ መሳፍንት (ፈራጆች) በራሱ በእግዚአብሄር የተመረጡ (የተነሱ) ነበሩ (መሳፍንት 2፡18)፡፡ ዳኞችን ጨምሮ ዘመናዊው የፍትህ ስርዓት የአንድ ሕብረተሰብ ጠቃሚ አካሎች መሆናቸውን የሚክድ ግለሰብ አይኖርም፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ያለዳኝነት እና ፍርድ እውን ሊሆኑ አለመቻላቸው ግር የሚያሰኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ራሱ ከሰራው (ሮሜ 13፡1-4) ከዚህ ሥረአት በመነሳት የምንረዳው ነገር፣ ኢየሱስ “አትፍረዱ” ሲል “ማንኛውም ሰው በአይኑ ፊት ደስ ያሰኘውን እያደረገ ይኑር” ሊል አለመፈለጉን ነው፡፡

በሌላ ቦታ፣ ኢየሱስ “ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ።” (ዮሐ. 7፡24) ሲል እንድንፈርድ ቀጥተኛ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ሁለት ነገሮች እንረዳለን፡፡ አንደኛው፣ የመፍረድ ሃላፊነት እንዳለብን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትክክለኛ ፍርድ የመስጠትን አስፈላጊነት ነው፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማየት የተሳሳተ ፍርድ ምንነትን እንመልከት፡-

በውጫዊ ጉዳዮች ላይ በመመስረት መፍረድ፡፡ የሰውን ፊት በማየት ፍርድ መስጠት ኃጢአት ነው (ዮሐንስ 7፡24)፡፡ እውነታዎችን በአንክሮ ከመመርመር በፊት በጥድፊያ መደምደሚያ ላይ መድረስ የሞኝነት ተግባር ነው (ምሳሌ 18፡13)፡፡ ፈሪሳዊው ስምዖን በአንዲት ሴት ላይ በመልኳና በነበራት አዳፋ ዝና ላይ በመመስረት ፈጣን የፍርድ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር፤ ያላስተዋለው አንድ ነገር ቢኖር ይህች ሴት ይቅርታን የተቀበለች መሆኗን ነበር፡፡ ስምዖን፣ ስለ ኢ-ፍትሐዊ ፍርዱ በኢየሱስ ሲወቀስ እናነባለን (ሉቃስ 7:36–50)።

ግብዝ (አስመሳይ) ፍርድ መፍረድ፡፡ በማቴዎስ 7:1 ላይ የምናየው እና ኢየሱስ በሌሎች ላይ እንዳንፈርድ ካስጠነቀቀበት ክፍል ቀደም ብሎ ስለግብዞች (በማቴዎስ 6:2፣ 5፣ 16) እና ግብዝነት (ማቴዎስ 7:3-5) ማስጠንቀቅያ የሚሰጥበት ክፍል አለ፡፡ ሌሎችን በምንወቅስበት ሃጢአት ራሳችን ተወቃሾች ሆነን ከተገኘን መልሰን ራሳችንን እንኮንናለን (ሮሜ 2፡1)፡፡

ምህረት የለሽ ፍርድ መፍረድ፡፡ አንዳችን ሌላውን፣ “በየውሃት መንፈስ” እንድናቀና ይጠበቅብናል (ገላቲያ 6፡2)፡፡ ምሕረትን የሚቀበሉት ራሳቸው ምሕረትን የሚያሳዩ ናቸው (ማቴዎስ 5፡7)፡፡ ኢየሱስ እንዳስጠነቀቀው “…በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል” (ማቴዎስ 7:2)፡፡

ተመጻዳቂ ፍርድ መፍረድ፡፡ ትሁታን እንድንሆን ተጠርተናል፤ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል” (ያዕቆብ 4፡6)፡፡ በሉቃስ 18:9–14 ውስጥ በምናነበው የፈሪሳዊው እና ቀራጩ ምሳሌ ውስጥ ፈሪሳዊው በራሱ ጽድቅ ላይ በመኩራራት በቀራጩ ላይ ሲፈርድ እንመለከታለን፤ እግዚአብሔር ግን ልባቸውን በመፈተሽ ቀራጩን አጽድቆ ፈሪሳዊውን ይኮንናል።

ፍርደ-ገምድል ፍርድ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት ምስክርን በግልጽ ይከለክላል (ምሳሌ 19፡5)፡፡ 

ክርስቲያኖች ኃጢያትን በሚቃወሙበት ጊዜ ብዙውን ጊዜ “በፈራጅነት” ወይም “ባለመቻቻል” ይከሰሳሉ፡፡ ኃጢአትን መቃወም ስህተት አይደለም፡፡ የጽድቅን መስፈርት ከፍ ማድረግ በራሱ ክፋትን ይገልጻል፤ ይህ ተግባር ደግሞ እግዚአብሔርን ከመፍራት ይልቅ ኃጢአትን ለመረጡት ሰዎች ምቾት አይሰጥም፡፡ መጥምቁ ዮሐንስ የሄሮድያዳን ምንዝርና በተቃወመ ጊዜ የሄሮድስ ቆጣ አጋጥሞት ነበር (ማርቆስ 6፡18–19)። በመጨረሻ ሄሮድያዳ የመጥምቁን አንገት በማስቀንጠስ ዮሐንስን ዝም ማሰኘት ችላ ነበር፤ ሆኖም ግን እውነትን ዝም ማሰኘት አትችልም (ኢሳ 40፡8)፡፡

አማኞች በሌሎች ላይ ኢፍትሃዊ እና ቅንነት የጎደለው ፍርድ እንዳያስተላልፉ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፤ ሆኖም ግን ቅን ፍርድን እንዲያደርጉ ኢየሱስ ማዘዙን መዘንጋት የለብንም (ዮሐንስ 7፡24)፡፡ ሁሉን ነገር ፈትነን መልካሙን እንድንይዝ ታዘናል (1 ተሰሎንቄ 5፡21)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን አስመልክቶ የሚሰጠውን ትምህርት ጨምሮ አጠቃላይ የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ይኖርብናል (ሐዋርያት ሥራ 20፡27፣ 2 ጢሞቴዎስ 4፡2)፡፡ ደካማ ወንድሞችን ወይም እህቶችን በመልካም መንፈስ ልናቀና ይገባል (ገላትያ 6፡1)፡፡ ጥፋተኞችን ለማረቅ ቤተክርስቲያን ልትገስጽ ይገባታል (ማቴዎስ 18:15-17)፡፡ በአጠቃላይ፣ እውነትን በፍቅር መናገር ከሁላችን ይጠበቃል (ኤፌ 4፡15)፡፡

1 thought on “መጽሐፍ ቅዱስ በሌሎች ላይ መፍረድ የለብንም ሲል ምን ማለቱ ነው?”

  1. Tariku Kassahun

    Really l have edified by your writing concerning this topic “Don’t judge”. God bless you, l get something in your page which increasing my understanding.

Leave a Reply

%d bloggers like this: