መጽሐፍ ቅዱስ፦ እስትንፋሰ- እግዚአብሔር

መጽሐፍ ቅዱስ፥ ጸሐፊዎቹ በእግዚአብሔር እየተመሩ የጻፉት ብቸኛ መጽሐፍ ነው። ይህ በእግዚአብሔር ምሪት መጽሐፍ ቅዱስን መጻፍ፥ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ይባላል። የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ትርጉም እግዚኣብሔር ሰብአውያን ጸሐፊዎችን ተጠቅሞ ለሰው ዘር ያለውን ሙሉና ተከታታይነት ያለውን አሳቡን ማስጻፉ ነው። ይህን ሲያደርግ ጸሐፊዎቹ እነሱነታቸውን፥ የአጻጻፍ ስልታቸውን እና የግል ሁኔታቸውን ሳይተዉ እንዲጽፉ ፈቅዷል። ጽሑፉን በማዘጋጀት ረገድ እግዚአብሔር በሰዎች መገልገሉ እውነት ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጽፉትን ሁሉ ባይረዱም፥ በእግዚአብሔር እየተመሩ መጽሐፉን መጽሐፍ ቅዱስ ያሰኙትን ስድሳ ስድስት መጻሕፍት ጽፈዋል። እነዚህ መጻሕፍት አስገራሚ አንድነት ወይም ተያያዥነት ያላቸው ከመሆናቸውም ሌላ፥ የተጻፈው ቃል ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ መጻፉ ቋሚ ማስረጃዎች አሏቸው። 

በዚህ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳን በሰው ብዕር ቢጻፍ፥ ሰው ለመሰሉ ሰው የጻፈው ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለሰው ያስተላለፈው መልእክት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እግዚአብሔር ቃል በቃል አጻፈውም አላጻፈው፥ የጥንት ዘገባዎች ግልባጭ ሆነም አልሆነ፥ የሰብአዊ ጻሐፊዎች የምርምር ውጤት፥ አሳብ፥ ምኞታቸው ወይም ፍርሃታቸው ሆነም አልሆነ፥ በማንኛውም መንገድ እግዚአብሔር እርሱ የሚፈልገውን ብቻ ይጽፉ ዘንድ ጸሐፊዎቹን መርቷቸዋል። ይህ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል የእግዚአብሔር ቃል ነው። ምንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች በአቀራረባቸው ምናልባት የሚለያዩ ቢሆኑ፥ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ነው። 

የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር አስተምህሮ፥ ልዕለ ተፈጥሮ (supernatural) በመሆኑ፥ ለሰዎች ግንዛቤ አንዳንድ ችግሮች ያስከትል ይሆናል። እንዴት ነው አንድ ሰብአዊ ጻሐፊ በራሱ አሳብና እውቀት እየጻፈ፥ እግዚአብሔር እንዲመዘግብ የሚያዘውን ብቻ በትክክል ሊጽፍ የሚችለው? ይህን ከመሳሰሉ ጥያቄዎች የተነሣ፥ ሰብአዊው ጸሐፊው ምን ያህል በመለኮት ቁጥጥር ሥር ነበር? በሚለው ጥያቄ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል። እነዚህ አስተያየቶች “እስትንፋሰ-እግዚአብሔርን አስመልክቶ የቀረቡ ንድፈ-አሳቦች” ተብለዋል። ስለሆነም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ፈቺዎች ሁሉ ከነዚህ ንድፈ-አሳቦች አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሆኑትን ንድፈ-አሳቦች ይከተላሉ። ተቀባይነት ያለው ንድፈ-አሳብ ለመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አፈታት ሁሉ መሠረት የሆነው ነው። ስለሆነም ስለ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ትክክለኛ የሆነውን ንድፈ-አሳብ በጥንቃቄ መለየት ይገባል። 

ሀ. የእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ንድፈ-አሳቦች 

1. “ቃል” እና “ምሉእ” እስትንፋሰ-እግዚአብሔር። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትክክለኛው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር የቃልና ምሉእ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ተብሎ ይገለጣል። “የቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ትርጉሙ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በተጻፉበት ጊዜ ጸሐፊዎቹን በቃላት አመራረጥ ሳይቀር እግዚአብሔር መርቷቸዋል ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰውን ጸሐፊነትም ያመለክታል። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊዎቹን የግል ባሕርይ ሰአጻጻፍ ስልታቸውና በቃላት አመራረጣቸው የሚገልጡ ሲሆን፥ ማንነታቸውም ብዙውን ጊዜ በአስተሳሰባቸው፥ በአመለካከታቸውና በጸሎታቸው ወይም በፍርሃታቸው ይታወቃል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰብኣዊነት ቢኖርም፥ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር፣ የተመዘገቡት ቃላት ሁሉ ከእግዚአብሔር እንዲሆን ያደርጋል። ይህ “ምሉእ” በመባል የሚታወቅ ሲሆን፥ ትርጉሙም (“ምሉእ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ማለት ነው። ይህ አሳብ፥ ለመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጠው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ግማሽ ነው የሚለውን አመለካከት ይቃወማል። 

ትክክለኛውና መሠረታዊው የእምነት ትምህርት ምን እንደሆነ ግልጥ ለማድረግ ብዙ ጊዜ ተጨማሪ ገላጭ ቃላት ታክለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት የለሽና ትክክል መሆኑን ለመግለጥ፥ የማይሳሳት፥ የእውነት ቃል መሆኑን ለመግለጥ ደግሞ፥ ስሕተት ኣልባ ተብሏል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ ኣንዳንድ ጊዜ እውነት ያልሆኑ ገለጣዎችን፥ ከዚያም አልፎ ዘፍጥረት 3፡4 ላይ እንደተመለከተው፥ የሰይጣንን የሐሰት ትምህርት ቢያቀርብም፥ እነዚህ ሁሉ ሰዎችን ወይም ሰይጣንን የሚያመለክቱ እንደሆኑ በግልጥ ተጠቅሷል። እግዚአብሔርም የእነዚህን ገለጣዎች እውነትነት አላረጋገጠም። መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በቃል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ነው ብሎ መግለጥ፥ እንዲሁም እውነትን በመግለጥ ረገድ ስሕተት አልባና ሐቅ ነው ማለት፥ መጽሐፉ እንደ መለኮታዊ ቃልነቱ ተዓማኒ ይሆን ዘንድ ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ልዕለ-ተፈጥሮና ፍጹም የሆነው የእግዚአብሔር ምሪት አለው ማለት ነው። 

እስትንፋሰ-እግዚአብሔር በእርግጥ የሚመለከተው የመጀመሪያዎቹን ወይም ዋነኞቹን ጽሑፎች እንጂ፥ ቅጂዎችንና ትርጉሞችን አይደለም። የመጀመሪያው ዋና ጽሑፍ በአሁኑ ጊዜ የሌለ ከመሆኑ የተነሣ፥ ምሁራን አሁን ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ለማረጋገጥና ለመወሰን ብዙ ጥረዋል። እውነትን ለመማማር ላለን ዓላማ ግን፥ አሁን በእጃችን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች፥ የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ትክክለኛ ብዢዎች መሆናቸውን ለመገመት ይቻላል። በይዘት ሳይሆን፥ በአገባብ ጥቃቅን፥ ልዩነቶች ቢኖሩም፥ የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮን እምብዛም የሚያዛንፉ አይደሉም። የተገኙት ተጨማሪ ጽሑፎችም ከላይ ከተጠቀሰው የግንዛቤ መደምደሚያ ጋር ይስማማሉ። 

ለተግባራዊ ዓላማዎች ሲባል፥ በዕብራይስጥ የተጻፈው ብሉይ ኪዳንና በግሪክኛ የተጻፈው አዲስ ኪዳን በአንድነት፥ የእግዚአብሔር የራሱ ቃል መሆናቸውንና እርሱ ለሰው ሊያስተላልፍ የፈለጋቸው እውነቶች መሆናቸውን አምኖ ለመቀበል ይቻላል። 

2. ሜካኒካዊ ወይም የቃል በቃል ንድፈ-አሳብ። ቀደም ሲል እንደተመለከተው፤ እውነተኛው እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ቃሉ በሚጻፍበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር አመራር ውስጥ የጸሐፊዎችን የመጻፍ ሰብእናና ነጻነት ይፈቅዳል የሚለው እውነተኛ አስተምህሮ ተገልጧል። የዚህ ተቃራኒ አመለካከት ግን ቅዱሳት መጻሕፍት በሚጻፉበት ጊዜ፥ ሰዎች የራሳቸውን የአጻጻፍ ዘዴ ምንም ሳይጠቀሙ እግዚአብሔር እንደ ጽሕፈት መኪና ተጠቅሞባቸዋል ይላል። እግዚአብሔር መጽሐፍ ቅዱስን ቃል በቃል አጽፎት ሲሆን ኖሮ፥ የአጻጻፉ ስልትና ቃላቱ በአጠቃላይ አንድ ዓይነት በሆኑ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የግል ፍርሃታቸውን፥ ስሜታቸውን፥ የእግዚአብሔርን ማዳን እና ጸሎታቸውን በብዙ ሁኔታዎች ገልጠዋል። በመሆኑም በተዘዋዋሪ መንገዶች የራሳቸውን ማንነት በዚሁ መለኮታዊ ጽሑፍ ውስጥ አስገብተዋል። ለምሳሌ ሮሜ 9፡1-3 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእስራኤል ያደረገው ጸሎት ቃል በቃል ከእግዚአብሔር የተሰጠ ቢሆን ኖሮ ትክክለኛ ትርጉሙን ያጣ ነበር። 

በመሆኑም እስትንፋሰ-እግዚአብሔር እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል የሚመለከት ቢሆንም፥ ማንነትን፥ የአጻጻፍ ስልትን ወይም የግል ፍላጎትን አያስቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ በአጻጻፍ ረገድ መለኮታዊውን ሥልጣን እንደሚቀበል ሁሉ፥ የጸሐፊውን ነጻነትም ያረጋግጣል። እግዚአብሔር ሰብአዊ ጸሐፊዎችን በመጠቀም ትክክለኛነትን አከናውኗል፤ ይህን ሲያደርግ ግን የቃል በቃል አጻጻፍን ተከትሎ አይደለም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር በቀጥታ እየተናገረ የተጻፉ መሆናቸው ተዘግቧል። አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግን፥ ቀጥታ ቃል በቃል ለመጻፋቸው ምንም ማስረጃ ስለሌለ በሰብአዊ ጸሐፊዎች ነው የተመዘገቡት ለማለት ይቻላል። 

3. ፅንሰ-ሐሳባዊ ንድፈ-አሳብ። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት በማቃለል፥ እግዚአብሔር እስትንፋሱን የሰጠው በትክክለኛዎቹ ቃላት ሳይሆን፥ ፅንሰ-አሳብን ብቻ ነው በማለት የመጽሐፉን ደራሲነት ለሰብአዊ ጸሐፊዎቹ ለመስጠት ሞክረዋል። ይህ አመለካከት ችግሮች አሉት። ምክንያቱም ሰዎች በሚጽፉበት ጊዜ እግዚአብሔር የገለጠላቸውን የተረዱት በከፊል ብቻ ቢሆንና ያን በራሳቸው ቃላት ቢያሰፍሩት ኑሮ በቀላሉ የማይገመት ችግር ያስከትሉ ነበር። 

ለጸሐፊዎች የተሰጧቸው ንድፈ-አሳቦች ብቻ ናቸው የሚለውን አስተያየት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ይቃወማል። የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በእግዚአብሔር መሪነት የተጻፈ መሆኑ ተደጋግሞ በአጽንኦት የተገለጠ እውነት ነው። የቃላት ጠቃሚነት በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ዘጸ. 20፡1፤ ዮሐ. 6፡63፤ 17፡8፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡13)። ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ ቃላቱ ከእግዚአብሔር መሆናቸው በተደጋጋሚ ተረጋግጧል (ዮሐ. 10፡17፤ ገላ. 3፡16)። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑ ኤፌሶን 6፡17፤ ያዕቆብ 1፡21-23፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡2 ውስጥ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። ከእግዚኣብሔር ቃል ላይ በሚቀንስ በማንኛውም ሰው ላይም ከባድ እርግማን ተላልፎበታል (ራእይ 22፡18-19)። ስለዚህም ይህ ንድፈ-አሳባዊ ትንታኔ፥ ቅዱሳት መጻሕፍት ራሳቸው በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፉ ስለመሆናቸው የሚያውጁትን እውነት በተመለከተ ከትክክለኛነት የራቀ ነው። 

4. ከፊል እስትንፋሰ-እግዚኣብሔር። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ናቸው በእግዚአብሔር መሪነት የተጻፉ የሚሉ የተለያዩ ንድፈ-ሐሳቦች ተከሥተው ነበር። ለምሳሌ አንዳንዶች፥ ስለ መለኮታዊ እውነት መገለጥ የሚናገሩት የቃሉ ክፍሎች ትክክለኛ ቢሆኑም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ታሪካዊ፥ መልከዓ-ምድራዊ ወይም ሳይንሳዊ አባባሎችን በዚህ መልኩ ኣንቀበላቸውም ብለዋል። ከዚህ ጋር ተጓዳኝ የሆነው አመለካከት ደግሞ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቂት ክፍሎች ይበልጥ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው ስለሆኑ፥ የእውነትና የስሕተታቸው ሁኔታ የደረጃ ጉዳይ ነው የሚለው ነው። ይህም መጽሐፍ ቅዱስ በሚጻፍበት ወቅት እግዚአብሔር ጻሐፊዎቹን በተለያዩ ደረጃዎች የረዳቸው ቢሆንም፥ ያለ ስሕተት ለመጻፍ የሚያስችላቸውን ክህሎት ግን አልሰጣቸውም የሚል ነው። በመሆኑም ከፊል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር በሁሉም አቀራረቡ የቃሉን የመጨረሻ ዳኝነት ለእያንዳንዱ አንባቢ ይተዋል። በመሆኑም በዚህ አካሄድ የቃሉ ሥልጣን፥ የአንባቢው ግለሰብ ሥልጣን ይሆንና፥ ሁለት አንባቢዎች በትክክል እውነት የሆነውና ያልሆነው የቱ ነው በሚለው እሳብ የማይስማሙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። 

5. አዲሱ ኦርቶዶክሲ (Neo-Orthodoxy) አስተሳሰብ ስለ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለው አመለካከት። በሀያኛው ምዕተ ዓመት ካርል ሳርት በሚባል ሰው አማካይነት አዲስ መለኮታዊ መገለጥ ማለት “እዲሱ ኦርቶዶክሲ” የተሰኘ አመለካከት ተከሠተ። ይህ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ በሚጻፍበት ጊዜ መለኮታዊ ድርሻ ያለበት መሆኑን ባይክድም፣ መጽሐፉ ስሕተቶች ስላሉበት እንደ ስሕተት አልባ ጽሑፍ ሊቆጠር አይገባም ይላል። ይህ አመለካከት እግዚአብሔር በቅዱሳን መጻሕፍት አማካይነት እንደሚናገርና እውነትን ወደ እኛ ለማስተላለፊያነት የሚጠቀምባቸው መሆኑንም ያምናል። 

በዚህ አመለካከት መሠረት እንግዲህ፥ መጽሐፍ ቅዱስ የመለኮታዊ መገለጥ መተላለፊያ የሚሆነው፥ የሚያምር አበባ ወይም ደስ የሚያሰኝ የፀሐይ መጥለቅ እግዚአብሔር ፈጣሪ መሆኑን የሚናገረውን ያህል ይሆናል ማለት ነው። በዚህ ንድፈ-አሳብ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚሆነው፥ እያንዳንዱ አንባቢ በተረዳው መጠን ሲሆን፤ እውነትም የሚረጋገጠው በዚያው ልክ ነው። የዚህ አመላካከት ታሪክ እንደሚያረጋግጠው፥ ሁለት የዚህ አመለካከት ደጋፊዎች በምንም አኳኋን መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው እውነት አይስማሙም። እንደ ከፊል እስትንፋሰ-እግዚአብሔር አመለካከት ሁሉ፥ እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትክክል ወይም ስሕተት የመሆኑን ውሳኔ ለግለሰብ አንባቢዎች ይተዋሉ። 

6. ተፈጥሮአዊ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የተሰኘው አስተሳሰብ ያለው አመለካክት። ይህ አመለካከት ከላይ ከጠቀሱት ሁሉ የባሰና ያለማመን አመለካከት ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማንኛውም ሌላ መጽሐፍ ነው የሚቆጥረው። በዚህ መሠረት ምንም እንኳን እግዚአብሔር ፅንሰ-አሳቦችን ይገልጡ ዘንድ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ልዩ ችሎታዎችን የሰጣቸው ቢሆንም፣ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ አመራር የሌለበት ፍጹም የሰው ሥራ ነው ይላል። ስለሆነም፥ ለዚህ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ የቀደሙ ሰዎችን መንፈሳዊ ልምምድ የሚገልጥ ተራ የሃይማኖት መጽሐፍ ነው። ይህ አመለካከት የመጽሐፍ ቅዱስን ልዩ መለኮታዊ ሥልጣን የሚሽር ከመሆኑም በላይ፥ መጽሐፉ በውስጡ የያዘውን አስደናቂ እውነት ትክክለኛነት አይገልጠውም። 

እንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ የሆነ ሰው ሰለዚህ መጽሐፍ ምንነት ምርጫ ማድረግ አለበት። ያለውም ምርጫ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን ስለሚናገር፥ ይህንኑ አምኖ መቀበልና እግዚአብሔር ራሱ ያለ ሰብአዊ ደራሲ እንደጻፈው ማመን ነው። ከዚህ ሌላ ያለው አማራጭ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውጀውን በማስረጃ ለማስደገፍ ኣይችልም፤ የእግዚአብሔር ቃል አይደለም፥ በማለት ይህን መጽሐፍ መካድ ይኖርበታል። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር መጻፍ አያሌ ማረጋገጫዎችን ማቅረብ ቢቻልም፥ ዋናው ማረጋገጫ ግን መጽሐፉ ስለ ራሱ የሚያቀርበው እውነት ነው። የመጽሐፉ ሕይወትን የመለወጥ ኃያል፥ እምነታቸውን በቃሉ እንዲሁም በሚሰጠው ተስፋ ላይ ባደረጉና በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ታይቷል። 

ለ. የክርስቶስ ምስክርነት 

መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል የመሆኑ እውነት በብዙ ውስጣዊ ማረጋገጫዎች ተደግፏል፤ በእግዚአብሔር ቃልነቱ የሰውን ሕይወት የመንካትና የመለወጥ ኃይሉም ተረጋግጧል። ከምስክርነቶቹ ሁሉ እጅግ ታላቁ የክርስቶስ ኢየሱስ የራሱ ምስክርነት ሲሆን፥ ያም መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን ያረጋግጣል። ክርስቶስ ከመጻሕፍት በሚጠቅስበት ጊዜ ሁሉ ቃሉ ሥልጣን እንዳላውና የመጣውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት መሆንን ሙሉ በሙሉ በመረዳት ነበር። በማቴዎስ 5፡18 መሠረት ከሕግ አንዲት ነጥብ ብትሆን እንኳን ሳትፈጻም እንደማትቀርም አረጋግጧል። ይህን ሲል አንዲት ነጥብ ከቃሉ ሳይፈጸም አይቀርም ማለቱ ነበር። እንግዲህ ትክክለኛነትና እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነት እስከ አንዲት ፊደል ድረስ በዝርዝር የሚሄድ ከሆነ፥ ክርስቶስ ያረጋግጥ የነበረው የብሉይ ኪዳንን እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነት ነበር። 

ክርስቶስ ዮሐንስ 10፡35 ውስጥ “መጽሐፉ ሊሻር አይችልምና” በማለት ያረጋግጣል። ማቴዎስ 1፡22-23 ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ የብሉይ ኪዳንን መፈጸም አዲስ ኪዳን በተደጋጋሚና በግልጥ አረጋግጧል (ከማቴዎስ 4፡14፤ 8፡ 17፤ 12፡17፤ 15፡7-8፤ 21፡4-5፥ 42፤ 22፡29፤ 26፡31፥ 56፤ 27፡9-10፥ 35 ጋር ያነጻጽሩ)። እነዚህ የማቴዎስ ወንጌል ጥቅሶች በመላው አዲስ ኪዳን የሚገኘው ማረጋገጫ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ናቸው። የስፍረ-ዘመን ለውጥ ወይም የሕይወት ሕግ ለውጥ በሚረጋገጥበት ጊዜ እንኳ፥ የመጀመሪያዎቹ (ዋናዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ገለጣዎች ሥልጣንና እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት የሚያጠያይቅ አይሆንም (ማቴ. 7-12)።

ከብሉይ ኪዳን የሚጠቀሱት ክፍሎች ወደ እያንዳንዱ ጠቃሚ ክፍል የሚደርሱ ሲሆኑ፥ እነርሱም ብዙ ጊዜ ሊብራልስት የሚባሉ ወገኖች የሚሟገቱባቸውና እንደ ኦሪት ዘዳግም፥ ትንቢተ ዮናስ እና ትንቢተ ዳንኤል (ዘዳ. 6፡16ን፤ ከማቴ. 12፡40፤ ዳን. 9፡27፥ 12፡11ን፤ ከማቴ. 24፡ 15 ጋር ያነጻጽሩ) ያሉት ናቸው። ስለዚህ የክርስቶስን ባሕርይና እውነትነት ካልተጠራጠሩ፥ የብሉይ ኪዳን እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነትን መጠራጠር ወይም አለመቀበል ከቶ ያዳግታል። ለዚህ ነው በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተገኘውን ቃል መካድ፥ ሥጋ የለበሰውን የእግዚአብሔር ቃል መካድ የሚሆነው። 

ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነትና ስሕተት አልባነት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፥ የአዲስ ኪዳንን መጻፍ አስቀድሞ ተናግሯል። በዮሐንስ 16፡ 12-13 መሠረት ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ከመንፈስ ቅዱስ እውነትን መቀበል ነበረባቸው። ደቀ መዛሙርቱ የእውነት ምስክሮች እንደሚሆኑ ክርስቶስ ተናግሮአል (ማቴ. 28፡19፤ ሉቃስ 10፡22-23፤ ዮሐ. 15፡27፤ ሐዋ. 1፡8)። ይህ ብቻም አይደል ደቀ መዛሙርቱ እውነትን እንዲናገሩ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል ሉቃስ 10፡16፤ ዮሐ. 13፡19፤ 17፡14-18፤ ዕብ. 2፡3-4)። 

አዲስ ኪዳን በሚጻፍበት ጊዜ ጸሐፊዎቹ በእግዚአብሔር መንፈስ መመራታቸውን ያውቁ ስለነበር፤ አዲስ ኪዳን እንደብሉይ ኪዳን እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን አውጀዋል። ልክ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደጻፈ (ማቴ. 22:43)፥ ዘማሪውም በእስትንፋሰ እግዚአብሔር እንደተቀኘ (ዕብ. 3፡7-11፤ መዝ. 95፡7-11)፥ አዲስ ኪዳንም በተመሳሳይ ሁኔታ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ነው። ዘዳግም 25፡4 እና ሉቃስ 10፡7 እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆናቸው 1ኛ ጢሞቴዎስ 5፡18 ውስጥ ተጠቅሷል። 2ኛ ጴጥሮስ 3፡15-16 ውስጥ የጳውሎስ መልእክቶች እንደ ሌላው የመጽሐፍ ክፍል መቆጠር ያለባቸው መሆኑ ተገልጧል። አዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ኪዳን እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን ራሱ ያረጋግጣል። 

ሐ. ስለእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ጠቃሚ ምንባቦች (ጥቅሶች) 

የመጽሐፍ ቅዱስን እስትንፋሰ-እግዚአብሔርነት ከሚናገሩት ማዕከላዊ ምንባቦች አንዱ፥ 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 ውስጥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት፥ በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል” የሚለው ነው። ሐዋርያው “መጽሐፍ” ሲል የሚያመላክተው በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡15 የተመለከቱትን “ቅዱሳን መጻሕፍት” ሲሆን፥ ሁለቱንም ማለት ብሉይንና አዲስ ኪዳንን ያጠቃልላል። “የእግዚአብሔር-እስትንፋስ” የሚለው አገላለጥ በአዲስ ኪዳን ግሪክኛ “ቲኦኒዮስቶስ” ማለት ሲሆን፥ ትርጉሙም “እግዚኣብሔር እፍ አለ” የሚል ይሆናል። ይህ አገላለጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር የወጣ መሆኑን ያመለክታል። በዚህ እውነት መሠረት ቃሉ የእግዚአብሔር ባሕርይ የሆነውን ፍጹምነት ይይዛል። የስሕተት ጸሐፊ መሆን ለእግዚአብሔር አይቻለውም። መጽሐፍ ቅዱስ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑ በሰው ጸሐፊዎች ላይ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር ቃልነት ላይ ያተኩራል። ጸሐፊዎቹ እንደ ሰብአዊነታቸው ስሕተትና የማይታመን ነገር ለመጻፍ የተጋለጡ መሆናቸውን በማወቅ ስሕተት አልባ የሆነ ቃሉን በነርሱ በኩል አስተላላፈ፥ በመለኮታዊ ኃይሉና ምሪቱ መራቸው። በመሆኑም እነሱ የጻፉት ቃል ስሕተት አልባ የእግዚአብሔር ቃል ነው። የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ ለትምህርተ እምነት፥ ለተግሣጽ፥ ልብን ለማቅናትና፥ በጽድቅ ላለው ትምህርት ይጠቅማል። 

ብዙ ጊዜ ከሚነሱ ጠቃሚ ጥያቄዎች አንዱ፥ እንዴት ነው እግዚአብሔር በአንድ በኩል ሰብኣዊ ደራሲነትንና ግለ ባሕርይን ፈቅዶ፥ በሌላ በኩል ደግሞ እስትንፋሱ የሆነውን ቃል ስሕተት አልባ የሚያደርገው? የሚለው ነው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ የሆነ አሠራሩን እንዴት እንደፈጸመ መመለስ ሁልጊዜ የማይቻል ቢሆንም ጥያቄውን በሚመለከት ግን 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21 ውስጥ “ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” ተብሎ ተገልጧል። ነቢያቱ በቃልም ተናገሩት ወይም ጻፉት፥ ማብራሪያው “በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው” ነው ይላል። “ተነድተው” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሸክምን ያመለክታል። በመሆኑም በዚህ አባባል መሠረት ጀልባ ተሳፋሪዎቹን ወደ አንድ መድረሻ እንደሚወስድ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችም እግዚኣብሔር ወዳሰበው መድረሻ ተወስደዋል። 

በጀልባ የሚጓዙ መንገደኞች (ተሳፋሪዎች) ጀልባው ውስጥ ለመመላለስ የሚያስችል ሰብአዊ ነጻነት ቢኖራቸውም፥ ወደጀልባው መድረሻ መወሰዳቸው እንደማይቀር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በውስጣቸው ይሠራ ነበር። እንደ ቧንቧ እንዲያስተላልፉም ቃሉን እፍ ይልባቸው ነበር። አንዳንድ የቃሉ ክፍሎች በትክክል ቃል በቃል በእግዚአብሔር እየተነገሩ የተጻፉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ዘጸአት 20፡1-17 ውስጥ የሕግ መሰጠትን እናገኛለን። ብሉይ ኪዳን በመደጋገም “እግዚአብሔር አለ” በማለት ያውጃል (ዘፍ. 1፡3)። ሌላው የተደጋገመ አገላለጥ፥ “የጌታ ቃል…መጣ” የሚለውና ከነቢያት አንዱ የመጣው ነው (ኤር. 1፡2፤ ሆሴዕ 1፡1፤ ዮናስ 1፡1፤ ሚክ. 1፡1፤ ሶፎ. 1፡ 1፤ ሐጌ 1፡1፤ ዘካ. 1፡ 1)። በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ እግዚአብሔር በሕልም ይናገራል (ዳን. 2፡1)፤ ወይም በሕልምና በራእይ ይገለጣል (ዳን. 7፡1)። የመለኮታዊ መገለጥ ዓይነቶችና ሁኔታዎች የተለያዩ ቢሆኑም፥ በነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር በሥልጣን፥ በትክክልና ያለ ስሕተት ይናገራል። በመሆኑም ቃሉ በእግዚአብሔር ያለውን ፍጹም የእውነት ባሕርይ ይናገራል። 

መ. ተጨማሪ ማብራሪያዎች 

መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር መሆኑን ስንናገር፥ እንዳንድ ጊዜ ውሸትን በውሸትነቱ የሚመዘግብ መሆኑን ማመን ይገባል። ይህ ዘፍጥረት 3፡4 ውስጥ የሰይጣንን ውሸት በመመዝገብ ተረጋግጧል። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ልምምድና አስተሳሰብ ለመመዝገብ ይችላል። ይህም በመጽሐፈ ኢዮብና በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን የምናገኘው ማስረጃ ነው። የሰዎቹን ማሰብ ወይም መናገር አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሰው ነገር፥ እዚያው መጽሐፉ ውስጥ ሌላ ስፍራ ባለው እውነት መፈተን (መመዘን) ይኖርበታል። በዚህ አኳኋን ስናየው፥ አንዳንዶቹ የኢዮብ ጓደኞች ንግግሮች ስሕተት ሲሆኑ፥ የመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን አንዳንድ ፍልስፍናና ምርምርም ከሰው ጥበብ ልቆ እንዳልሄደ እንረዳለን። መጽሐፍ ቅዱስ እውነትን እውነት ነው በማለት በሚመዘግብበት ጊዜ፥ ይህ ሁኔታ እውነት መሆን ያለበት በእግዚአብሔር ማንነት መገለጥ፥ በግብረገብ ደረጃዎቹ ወይም በትንቢት መርሐ ግብሩ ወይም ታሪክን፥ መልክዓ-ምድርን በማጠቃለሉ ወይም ከሳይንስ ጋር የሚዛመዱ እውነታዎችን ሲያገናዝብ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ትክከለኛነት የሚያስደንቅ ምስክርነት አለው። ይኸውም ጥንታውያን ጸሐፊዎች ምንም እንኳ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መገመት ሳይችሉ፥ እና ቴክኒካዊ ቋንቋ ባይጠቀሙ፥ ጽሑፋቸው የሰው ልጅ በምድር ከሚያገኘው እውነት ጋር አይቃረንም። 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥያቄ የሚያሥነሡ ችግሮችም አሉ። አንዳንድ ጊዜ በቂ መረጃ ካለማግኘት የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን የሚቃረን ሊመስል ይችላል። እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው፥ ኢያሪኮ ውስጥ የተፈወሱት ዓይነ ስውሮች አንድ ወይም ሁለት መሆናቸው (ማቴ. 20፡30፤ ማር. 10፡46፤ ሉቃስ 18፡35)፥ ደግሞም ድርጊቱ የተፈጸመው ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ሲገባ (ሉቃስ 18፡ 35)፥ ወይም ከኢያሪኮ ሲወጣ (ማር. 10፡ 46፤ ሉቃስ 19፡ 1) መሆን አለመሆኑ በግልጥ ያለመለየቱ ጉዳይ ነው። እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች የሚወገዱት፥ መጽሐፍ ቅዱስን በትዕግሥት በማጥናት ሲሆን፥ ችግሩ የሚቃለለውም እውነቱ በትክክል ሲታወቅ ነው። ለምሳሌ ሁለት የኢያሪኮ ከተሞች፥ ኣንድ ጥንታዊ እና ሌላ ዘመናዊ ነበሩ። ክርስቶስ ከላይ የተጠቀሰውን ድርጊት በፈጸመበት ጊዜ ከአንደኛው ኢያሪኮ ወደ ሌላኛው ኢያሪኮ በመግባት ላይ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የተባሉ ብዙ ስሕተቶች በከርሠ-ምድር ቁፋሮ ግኝት አማካይነት እውነትነታቸው ተረጋግጧል። 

ማንም ቢሆን የቅዱሳት መጻሕፍት አባባሎች የሚያመለክቱት፥ የዓለምን ወይም የሰውን አፈጣጠር ወይም ከዚያም አልፎ ሌላ ዝርዝር ትረካ መሆን አለመሆኑን ለመለየትና ለመቃረን የሚያስችል በቂ እውቀት የለውም። በሚገባ ከተገነዘቡት፥ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ትክክለኛነት እና እውነት እንደሚያረጋግጥ ሐውልት ነው። እግዚአብሔር ራሱ ለአንባቢው ግለሰብ የሚናገረው ተደርጎ ሊታመንም ይገባል። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስን ለማናናቅና ለማጥፋት በየዘመናቱ የተቻለው ሁሉ ሲሞከርም፥ መጽሐፉ የእግዚአብሔርን እውነት ለሚፈልጉ ሁሉ ብቸኛው ባለሥልጣንና የእውነተኛ መለኮታዊ መገለጥ ምንጭ እንደሆነ ይቀጥላል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.