መጽሐፍ ቅዱስ እንደ መለኮታዊ መገለጥ

ሀ. የመለኮታዊ መገለጥ ዓይነቶች 

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሕልውና፥ ሥራዎቹንና ዕቅዶቹን ለመግለጫነት ነው የተጻፈው። ፍጹም ልዑል የሆነው አምላክ ራሱን ለፍጥረታቱ መግለጡ ተገቢ ሲሆን፥ ፍጥረትን የፈጠረበት ዓላማም ይሞላ ዘንድ ይህ አስፈላጊ ነበር። አእምሮ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ ፈጣሪያቸውን ለማወቅ መሞከራቸው ትክክል ነው። የተፈጥሮ ከፍተኛ ደረጃ ሰው ከሆነ፥ ፈጣሪውን ለመገንዘብና ከርሱ ጋር አንድነት ለመፍጠር ከቻለ፥ ፈጣሪ ዓላማና ፍቃዱን እንዲህ ላለው ፍጡር በመግለጥ እንደሚገናኘው መገንዘብ ይቻላል። እግዚአብሔር በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ራሱን ገልጧል። 

1. የእግዚአብሔር መገለጥ በፍጥረት ውስጥ። የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ሥልጣንና ባሕርይ በፈጠራቸው ፍጥረታት አማካይነት ተገልጧል (ሮሜ. 1፡20)። ተፈጥሮአዊው ዓለም የእግዚአብሔር ሥራ እንደመሆኑ፥ እግዚአብሔር የማይወሰን ኃይልና ጥበብ ያለው መሆኑን፥ እንዲሁም ነባራዊውን ዓለም ጥበብ ለተሞላበት ዓላማ እንደፈጠረው ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በተፈጥሮ በኩል ያሳየው መገለጥ፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር፥ ወይም ቅድስና በተመለከተ ጥርት ያለ መግለጫ ስለማናገኝለት የራሱ ገደብ አለው። እግዚአብሔር በፍጥረት አማካይነት ያሳየው መገለጥ፥ የማያምነው ዓለም እርሱን እንደፈጣሪው ባለማምለኩ እንዲፈርድበት ቢያስችለውም፥ ይህ መገለጥ ኃጢአተኞች ቅዱስ ከሆነው እግዚአብሔር ጋር የሚታረቁበትን የድነት መንገድ አያመለክትም። 

2. በክርስቶስ የታየ የእግዚአብሔር መገለጥ። ታላቁ የእግዚአብሔር መገለጥ የተከናወነው ራሱ በወሰነው ጊዜ በተወለደው በክርስቶስ እና በክርስቶስ ሥራ ነው (ገላ. 4፡4)። የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ ወደ ዓለም የመጣው፥ ሰዎች ሊረዱት በሚቻላቸው አኳኋን እግዚአብሔርን ሊገልጥ ነው። ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ በመወለዱ እጅግ ከባድ የሆነ የእግዚአብሔር እውነት፥ ውስኑ የሰው አእምሮ በሚረዳው ደረጃ ተገልጧል። ስለዚህ በክርስቶስ የተገለጠው፥ የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ብቻ ሳይሆን፥ በጎነቱ፥ ቅድስናው፥ ጸጋውና ፍቅሩ ጭምር ናቸው። ይህንም ክርስቶስ ራሱ ሲመሰክር፥ “እኔን ያየ አብን አይቶአል” በማለት አረጋግጧል (ዮሐ. 14፡9)። ስለሆነም ክርስቶስ ኢየሱስን ያየውና ያወቀው ሁሉ፥ እግዚአብሔር አብንም አይቶታል፥ አውቆታልም። 

3. በተጻፈ ቃል አማካይነት የተሰጠ የእግዚአብሔር መገለጥ። በጽሑፍ የሰፈረው የእግዚአብሔር ቃል፥ በክርስቶስ በራሱና በሥራው ከታየው ይልቅ ግልጥ በሆነ ቃል እግዚአብሔርን ሊገልጠው ይችላል። ቀደም ብሎ የተጻፈ እንደመሆኑ መጠን፥ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ትንቢት ዓላማ ወይም ባለቤት እና እንደ ትንቢት ፍጻሜ የሚያስተዋውቀን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በዝርዝር ከመግለጥ አልፎም፥ እግዚአብሔር ለእስራኤል፥ ለመንግሥታትና ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፕሮግራም ያመለክታል። የሰው ዘር ታሪክንና የዓለማትን መታወቅ የመሳሰሉ ነገሮችንም ይመለከታል። 

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ዋና ጉዳዩ አድርጎ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን ዓላማም ይገልጣል። በጽሑፍ የሰፈረው መገለጥ አጠቃላይ ነው። እግዚአብሔርን በተመለከተ፥ በተፈጥሮ አማካይነት የተገለጡትን እውነቶች ሁሉ ለማስገንዘብ፥ የእግዚአብሔርን በክርስቶስ መገለጥ ብቸኛ ዘገባ ያቀርባል። እግዚአብሔር አብን፥ ወልድን፥ መንፈስ ቅዱስን መላእክትን፥ አጋንንትን፥ ሰውን፥ ኃጢአትን፥ ድነትን፥ ጸጋን፥ እና ክብርን በተመለከተ ያለውን መገለጥ በጥልቀት ይዘረዝራል። በዚህ መሠረት፥ መጽሐፍ ቅዱስ፥ በተፈጥሮ በከፊል የታየውን፥ ይበልጥ በሙላት በክርስቶስ የተገለጠውን እና በጽሑፍ በሰፈረው ቃል የተጠቃለለውን መለኮታዊ መገለጥ ከፍጻሜ እንዳደረሰ ሊቆጠር ይችል ይሆናል። 

ለ. ልዩ መገለጥ 

በመላው የሰው ልጅ ታሪክ እግዚአብሔር ልዩ ራእይ ወይም መገለጥን ሰጥቶአል። በኤደን ገነት ውስጥ ከሰው ጋር ፊት ለፊት ተነጋግሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከነቢያት ጋር በብሉይ ኪዳን ወይም ከሐዋርያት ጋር በአዲስ ኪዳን የተናገረባቸው ብዙ ሁኔታዎች ተመዝግበዋል። ከነዚህ ልዩ መገለጦች ጥቂቱና በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተሞላ ሥልጣን ያላቸው፥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ ስድሳ ስድስት መጻሕፍት ሌላ ኣዲስ መጻሕፍትን ሊያስጨምር የሚችል ልዩ መገለጥ አይኖርም። ስለዚህ አዋልድ መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔርነት ስለሌላቸው፥ ከስድሳ ስድስቱ መጻሕፍት እኩል የሚታዩ አይደሉም። 

ይሁን እንጂ፥ በአሁኑ ጊዜ በልዩ መገለጥ ፈንታ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጎልቶ ይታወቃል። የእግዚአብሔር መንፈስ ለቃሉ አብርሆት ወይም ብርሃን እንደሚሰጥ፥ የአሁኑ ጊዜ መገለጥም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ለግል ሕይወትና ሁኔታዎች ግልጥ የሚሆኑት በዚህ አኳኋን ነው። ከእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ጋር በተጓዳኝ የምናየው ነገር፥ መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሰው የሚያስፈልጉት አጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ የመምራቱ ሥራ ነው። ሁለቱም፥ ማለት ምሪትና አብርሆት ትክክለኛዎቹ የእግዚአብሔር ሥራዎች ቢሆኑም፥ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ ለመረዳቱ ወይም የእግዚአብሔርን ምሪት በትክክል ለመገንዘቡ ዋስትና አይሰጡም። ስለዚህ፥ አብርሆትና ምሪት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ቢሆኑም፥ ለስሕተት በሚጋለጥ ሰብአዊ ፍጡር በኩል የሚመጡና ለእርሱ የሚያስፈልገውን ነገር ለመግለጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ መልክ ስለሚሰጡ፥ “በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር” የተጻፈን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ስሕተት ኣልባ ሊሆኑ አይችሉም። 

1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10 ውስጥ እንደተመለከተው፥ ቃሉን በሚገልጥልን በእግዚአብሔር መንፈስ አማካይነት ካልሆነ በስተቀር፥ እውነትን በሚገባ የምንረዳበት መንገድ የለም። የእግዚአብሔር ቃል እውነት፥ በእግዚአብሔር መንፈስ ሊገለጥልን ይገባል። መማር ያለብንም በመንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡13)። 1ኛ ቆሮንቶስ 2፡14 ውስጥ እንደተጠቀሰው፦ “ለፍጥረታዊ ሰው የእግዚአብሔር መንፈስ ነገር ሞኝነት ነውና አይቀበለውም፥ በመንፈስም የሚመረመር ስለሆነ ሊያውቀው አይችልም”። ስለዚህ ትክክለኛ ፍቺውን መረዳትን በተመለከተ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያን ላልሆነና ከመንፈስ ቅዱስ ለማይማር ሰው ስውር ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን የሚማር ሰው፥ መንፈስ ቅዱስ እውነቱን ይገልጥለት ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። 

ሐ. ትርጉም ወይም ፍቺ 

አንድ በክርስቶስ አማኝ የሆነ ሰው፥ የእግዚአብሔርን ቃል መገለጥ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሚያጠናበት ጊዜ፥ ትርጉምን ወይም ፍቺን በሚመለከት አንዳንድ ችግሮች ይገጥሙታል። በመሆኑም አንድ ሰው “የመጽሐፍ ቅዱስ አፈታት ዘዴ” (“ኸርማኒዩቲክስ” /hermeneutics) ተብሎ በሚጠራው የእግዚአብሔር ቃልን የማጥኛ ስልት ለመጠቀም ከፈለገ፥ የአተረጓጎም መሠረታዊ ደንቦችን ሊከተል ይገባል። ፍቺን ወይም መረዳትን በተመለከተ በመንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍ አስፈላጊነቱ ሳይዘነጋ፥ አንዳንድ መሠረታዊ የማጥኛ ስልቶች ስለሚያስፈልጉ በዝርዝር ልናያቸው ይገባል። 

1. የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ዓላማ። መጽሐፍ ቅዱስ በሚተረጎምበት ወይም በሚፈታበት ጊዜ ራሱን በራሱ የማይቃረን መጽሐፍ ስለሆነ፥ እያንዳንዱ ጥቅስ ከአጠቃላዩ ይዘት ጋር መዛመድ አለበት። 

2. እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ የያዘው ልዩ መልእክት። የእግዚአብሔር ቃል ፍቺ ወይም ትርጉም ሥራ ሁልጊዜ የሚተረጎመውን መጽሐፍ ዓላማ ከግንዛቤ ማስገባት አለበት። በዚህ መሠረት፥ የመጽሐፈ መክብብ ጥናት ወይም አተረጓጎም፥ ከራእይ ወይም ከመዝሙረ ዳዊት ጥናት ይለያል። ለዚህ ነው አንድ ትርጉም ከሚተረጎመው መጽሐፍ ዓላማ መራቅ የለበትም የሚባለው። 

3. ለማን ተጻፈ? መጽሐፍ ቅዱስ በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተጻፈ ቢሆንም፥ ሁሉም በእኩልነት ሥራ ላይ የሚውል አይደለም። የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ አኳኋን ከመተርጎም የተነሣ ብዙ የሐሰት አስተምህሮዎች ተፈጥረዋል። ስለዚህ አንድ የንባብ ክፍል በሚጠናበት ጊዜ፥ ማን፥ ለማን፥ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሣት ተገቢ ነው። የተጻፈውን መልእክት ስንመለከት፥ የተጻፈላቸው የመጀመሪያዎቹ ተቀባዮች ሲሆኑ፥ ከዛ በኋላ የሚያነቡት ሁለተኛ ተጠቃሚዎች ወይም ከራሳቸው ጋር አዛማጆች ይሆናሉ። የመጀመሪያው ተግባር ጽሑፉ እስከተጻፈለት ግለሰብ ወይም ቡድን የሚደርስ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ለገላትያ ሰዎች የተላከው መልእክት ወይም በዳዊት የተጻፈው መዝሙር ሊሆን ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የንባብ ክፍል ውስጥ ያለ እውነት፥ በመጀመሪያ ጽሑፉ ለተጻፈላቸው ሰዎች የሚሆን ሲሆን፥ በሁለተኛ ደረጃ ሌሎችን የሚያጠቃልል እውነት ይኖረዋል። ስለዚህ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግ ለእስራኤል የተጻፈ ቢሆንም፥ በዚህ ስፍረ-ዘመን ያሉ ክርስቲያኖች ቃሉ የእግዚአብሔር ቅድስና መግለጫ እንደሆነ ተገንዝበው ያጠኑታል። በዚህ መሠረት አንዳንድ ልዩ ነገሮች ለኛ ሁኔታ የሚውሉና የሚጠቅሙ ሊሆኑ ይችላሉ። 

4. ዐውደ-ንባቡ ወይም አገባቡ (context)። ማንኛውም ምንባብ በሚብራራበት ጊዜ ልብ ሊባሉ ከሚገባቸው ጠቃሚ ነገሮች አንዱ፥ የምንባቡን የቅርብ ዐውድ ወይም አገባብ ማጤን ነው። ይህ አሠራር ብዙ ጊዜ በገላጣው ውስጥ ሊባል ስለተፈለገው ነገር ፍንጭ ይሰጣል። ማንኛውንም ጥቅስ የሚቀድም ወይም የሚከተል ቃል እንዲሁም ዓረፍተ ነገር፥ አንባቢው ጥቅሱን እንዲገነዘብ ይረዳዋል። 

5. በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በሌላ ስፍራ የሚኖሩ ተመሳሳይ ትምህርቶች። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ የሚቃረን ስላይደለ፥ ስለ አንድ ጥቅስ ትምህርተ-መለኮታዊ ገለጣ ሲሰጥ፥ በሌላ ስፍራ ካሉ ገለጣዎች ጋር መዋሐድ ወይም መጣጣም አለበት። ይህ ነው የቅንብራዊ ትምህርተ-መለኮት (Systematic Theology) ልዩ ተግባር። ይህ ቅንብራዊ ትምህርተ-መለኮት፥ መለኮታዊውን መገለጥ እንዳለ በመውሰድ፥ ከማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ጋር በማይቃረን ሁኔታ በትምህርትነት ሊያቀናብረው ይሞክራል። የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ብዙ ጊዜ ይደጋገፋሉ። ለምሳሌ፥ መጽሐፈ ራእይ ስለ መልእክቱ ፍቺ በዳንኤል ወይም በሌሎቹ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ላይ ይደገፋል። የእግዚአብሔር ደራሲ መንፈስ ቅዱስ ከሆነ፥ በመጽሐፉ አንድ ስፍራ የተጠቀሰ ነገር በሌላ ስፍራ የተባለውን ለመረዳት የሚያግዘን መሆን አለበት። 

6. የአንድ ጥቅስ ቃላት ትክክለኛ ትንታኔ። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች በመሆኑ፥ ብዙ ጊዜ በትክክለኛ ትርጉም አሰጣጥ ረገድ ችግር አለ። ስለሆነም የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበትን ቋንቋ ማወቁ፥ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ምን መልእክት እንዳለው በውል ለመረዳትና ለመወሰን በጣም ይጠቅማል። እነዚህ ቴክኒካዊ እውቀቶች የሌሏቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፥ አንድን የተለየ ጽሑፍ ከመጽሐፍ ቅዱስ መፍቻዎችና ማብራሪያዎች ይረዳሉ። ለአብዛኛው ጉዳይ ወይም ዓላማ ጥሩ ትርጉም በቂ ቢሆንም፥ ጥንቁቅ ተማሪዎች ልዩ ለሆኑ ጥቅሶች ማብራሪያ ሊሰጡ የሚችሉ ምሁራንን ያማክራሉ። 

የአንድን ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ከመወሰን ጋር፥ ቃሉን ፈሊጣዊ ነው ለማለት የሚያበቃ ነገር ከሌለ፥ እያንዳንዱ ቃል የራሱ ተገቢና ቀጥተኛ ትርጉም አለው። ትክክለኛው አተረጓጎም ይህን ይቀበላል። ለምሳሌ፥ ለእስራኤል ተስፋ የተገባለት ምድር መንግሥተ ሰማያትን የሚያመለክት ሆኖ ሊቆጠር አይገባም። ከዚያ ይልቅ፥ ቅድስቲቱን ምድር (አገር) የሚያመለክት መሆን አለበት። በተመሳሳይ ሁኔታ ለእስራኤል የተሰጡ ተስፋዎች በክርስቶስ ላመኑ አሕዛብም እንደሚሆኑ ለማድረግ ሲባል መንፈሳዊ ትርጉም ሊሰጣቸው አይገባም። የትርጉም ሕግ የሚለው፥ ፈሊጣዊ አነጋገር ከሌለ እና አገባቡም ይህን የሚመለከት ካልሆነ በቀር፥ ቃላት ትክክለኛ ወይም ቀጥተኛ ትርጉም ነው ሊሰጣቸው የሚገባ። 

7. ከመጥፎ አመለካከት መጠበቅ። አንድ የእግዚአብሔር ቃል ፈቺ ወይም ተርጓሚ፥ አንድን የንባብ ክፍል፥ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናትና ከትምህርተ-መለኮት እምነቱ አንጻር መመልከቱ ተገቢ ሲሆን፥ አንድን ጥቅስ ቀደም ተብሎ ከተፀነሰ አሳቡ ጋር ለማዋሐድ ሲል ሊያዛባው ግን አይገባም። ከሌሎች የመጽሐፉ ክፍሎች ጋር ያለውን ተዛምዶ በተመለከተ ያልተፈታ ችግር ቢኖርም እንኳን፥ እያንዳንዱ ቃል ራሱን በራሱ መፍታት አለበት። ከሌላ ቃል ጋር ያለውን መዋሐድ በተመለከተ ችግር ቢኖርበትም፥ እያንዳንዱ ጥቅስ በራሱ ቃል በቃል የሚሰጠውን ትርጉም መያዝ ይገባዋል። 

መጽሐፍ ቅዱስ በሚፈታ ወይም በሚተረጎምበት ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ቃል በመንፈስ ቅዱስ ለሚመሩ ሁሉ ይረዱት ዘንድ የተሰጠ መጽሐፍ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ እውነትን ማስተላለፍ ነው። በትክክል ሲፈታ፥ የተዋሐደ፥ እርስ በርሱ የማይቃረንና የተትረፈረፈ የትምህርት ፍሬ አለው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.