ሰይጣን፡- ማንነቱና ኃይሉ

ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ብልጫ ያለው ሆኖ ቢፈጠርም፥ በርሱና በሕያው፥ ዘላለማዊ እና ባልተፈጠረው አምላክ መካከል ሰው ሊረዳ ከሚችለው በላይ የሆነ ልዩነት አለ። በሚቀጥለው ምዕራፍ እንደሚቀርበው ሰይጣን ቀድሞ ቅዱስ መልአክ የነበረ ቢሆንም፥ ካሰበት ቅድስና በመውደቅ የእግዚአብሔር ተፃራሪና የወደቁ መላእክት መሪ ሆነ ። 

ሀ. የሰይጣን ማንነት 

ልክ እንደ እግዚአብሔር እና እንደ ሌሎቹ መላእክት ሁሉ ሰይጣንም በአካለ ሥጋ እይታይም። ማንነቱን ለማወቅ የሚቻለው በቅዱሳት መጻሕፍት በሚቀርበው ማስረጃ መሠረት ነው። ማስረጃዎቹም በሚቀጥለው አኳኋን ቀርበዋል። 

1. ሰይጣን አካል ሆኖ ነው የተፈጠረው። በሰማይና በምድር ያሉ ፍጥረታት ሁሉ “የሚታዩትና የማይታዩት፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት” በክርስቶስ ለክርስቶስ እንደተፈጠሩ በቁሳስይስ 1፡16 ውስጥ ተገልጧል። የሠራዊተ መላእክት አፈጣጠር ምናልባት ከሌሎች ቁሳዊ ፍጥረታት ይቀድም ይሆናል። ነገር ግን ዮሐንስ 1፡1-2 ውስጥ እንደተገለጠው፥ ሕልውናው ዘላለማዊ የሆነው መለኮት ግን ከሁሉ በፊት ነበር። 

ከሰማይ ሠራዊት ሁሉ የሰይጣን አፈጣጠር ነው በተለይ የተጠቀሰው። ይህ እውነት ከማይታዩ ሌሎች የእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ጋር ሲነጻጸር ሰይጣን ታላቅ የክብር ስፍራ የነበረው መሆኑን ያመለክታል። 

ሕዝቅኤል 28፡11-19 ውስጥ “ለጢሮስ ንጉሥ” የሙሾ መልእክት እንደመጣለት እንመለከታለን። የመልእክቱ ሙሾ በቀጥታ፥ ለጢሮስ ንጉሥ የተነገረ ነው። ነገሩን ወለቅና ሰፋ አድርገን በመንፈሳዊ ዓይን ስንመረምረው፥ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ ቁንጮና ታላቅ የሆነውን ፍጡር፥ ማለት ሰይጣንን እንመለከታለን። ይህ ፍጡር “ጥበብ የተሞላ፥ የውበትም መጨረሻ” ተብሏል።“በእግዚአብሔር ገነት በኤደን የነበርህ ተብሎም ተነግሮለታል። (ቁጥር 13 ላይ የተጠቀሰው ስፍራ ምናልባት ዘፍጥረት 3 ውስጥ የተገለጠው ሳይሆን፥ የመጀመሪያው የእግዚአብሔር ፍጥረት ወይም ቀዳሚው ኤደን ሊሆን ይችላል።) ሰይጣን በመለኮታዊ ዕቅድ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ተራራ እንዲሸፍን የተፈጠረና የተቀባ ኪሩብም ነበር (ቁጥር 14)። የእግዚአብሔር ተራራ በቅዱሳት መጻሕፍት አገላለጥ የሚያመለክተው፥ ዙፋንን ወይም የእግዚአብሔን የአጎዛዝ ኃይል ማዕከልን ነው። እዚህ ላይ የተገለጠውን ያህል ብቃት ያለው የጢሮስ ንጉሥ ኖሮ አያውቅም። ይህ አገላላጥ የሚያመለክተው ሌላ ማንንም ሳይሆን ከውድቀቱ በፊት የነበረውን የሰይጣንን ሁኔታ ብቻ ነው። 

2. ሕልው የሆነ አካል የሚፈጽማቸውን ድርጊቶች ሁሉ ሰይጣን ይፈጽማል። የሰይጣንን ማንነት ከሚገልጡ አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መካከል ለአብነት ያህል የሚከተሉትን መመልከት ይቻላል። 

(ሀ) ኢሳይያስ 14፡12-17። ነቢዩ በዚህ ስፍራ ሰይጣን ዘመኑ እንዳሰፈበትና በዘመኑም መጨረሻ እንደተፈረደበት፥ እንዲሁም ከታላቅ ቦታውና ክብሩ እንደወደቀ አስተውሎ ከተመለከተና ከተረዳ በኋላ በመለኮታዊ አጠራር የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ” በማለት ይጠራዋል። “መንገሥታትን ያናወጠው። እርሱ ቁጥር 12) በአምስት ሁኔታዎች በእግዚአብሔር ፈቃድ ላይ ዓምፆአል። ሕዝቅኤል 28፡15 ውስጥ እንደተገለጠው ሁሉ በዚህም ክፍል በልቡ የተሰወረውን ኃጢአት እግዚአብሔር አውቆ እንዳጋለጠው እንማራለን (1ኛ ጢሞ. 3፡6ን ይመልከቱ)። 

(ለ) ዘፍጥረት 3፡1-15። በዚህ ስፍራ በተመዘገቡት ድርጊቶቹ ሳቢያ ሰይጣን “እባብ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ምክንያቱም ለአዳምና ለሔዋን የተገለጠው በእባብ ተመስሎ ነበር። በዚያ የንባብ ክፍል የተጻፈው እያንዳንዱ ቃልና የተገለጠው የሰይጣን ዕቅድ ሁሉ ስለ እርሱ ማንነት ግልጥ ማስረጃ ነው (2ኛ ቆሮ. 11፡3፥ 13-15፤ ራእይ 12፡9! 20፡2)። 

(ሐ) ኢዮብ 1፡6-12፤ 2፡1-13። በእነዚህ ስፍራዎች የተገለጠው ልዩ ሁኔታ የሚያስረዳን፥ ሰይጣን እግዚአብሔር ዘንድ (ሉቃስ 22፡31፤ ራእይ 12፡10)፥ እንዲሁም ወደ ሰው (ኤፌ. 6፡10-12፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡8) መቅረብ እንደሚችልና የማናቸውንም እውነተኛ አካል ባሕርይ የሚያሳይ መሆኑን ነው። 

(መ) ሉቃስ 4፡1-13። በዚህም ስፍራ እንደተገለጠው ሰይጣን የመጨረሻው አዳም የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅ በምድረ በዳ በፈተነው ጊዜ ማንነቱ ተገልጧል። በልዑል እመሰላለሁ ብሎ ያሰበው (ኢሳ. 14፡14)፥ ይህን አሳቡንም ለመጀመሪያው ሰውና ለመጀመሪያይቱ ሴት ያስተላለፈው (ዘፍጥ. 3፡5)። አሁን ደግሞ ክርስቶስ ወድቆ ቢሰግድላት በምድር ያለ ሀብትና ንብረት እንደሚሰጠው ቃል ሲገባ ይታያል። ይህ ክርስቶስ አሻፈረኝ ያለው የሰይጣን ስጦታ የሆነ ሥልጣንና ኃይል ወደፊት በሚነሣው የጥፋት ልጅ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ ይከናወናል (2ኛ ተሰ. 2፡8-10፤ 1ኛ ዮሐ. 4፡3)። 

(ሠ) ኤፌሶን 6፡10-12። በዚህ ስፍራ የተመለከቱትና ሰይጣን የእግዚአብሔርን ልጆች የሚዋጋቸው እንዲሁም የሚቃወምባቸው መንገዶች ማንነቱን በሚገባ ያስረዳሉ። መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ሰይጣን የራሱ የሆኑትን፥ ማለት ያልዳኑና ዳግም በመንፈስ በመወለድ የእግዚአብሔር ልጆች ያልሆኑትን እንደሚዋጋቸውና እንደሚቃወማቸው ተጽፎ አናገኝም። እንዲያ ያሉ ሰዎች የራሱ ስለሆኑ በሥልጣኑ ሥር ናቸው (ዮሐ. 8፡44፤ ኤፌ. 2፡2፤ 1ኛ ዮሐ. 5፡19)። 

ለ. የሰይጣን ኃይል 

ሰይጣን የወደቀና በክርስቶስ የመስቀል ሥራ ላይ የተፈረደበት ቢሆንም (ዮሐ. 12፡31፤ 16፡11፤ ቈላ. 2፡15)፥ በዓለም ያለው ሥፍራ አልተወሰደበትም፥ ከኃይሉ ያጣውም ጥቂቱን ብቻ ነው። አካላዊና ሥልጣናዊ ብርታቱ በሁለት መንገዶች ይገለጣል። 

1. ጥንካሬው ፈገመት አይቻልም። ሰይጣን ራሱ እንደገለጠው እና ክርስቶስም እንዳልካደው፥ በዚህ ዓለም ማለት ተሰጥተውኛል በሚላቸው መንግሥታት ላይ ሙሉ ሥልጣን አለው። ይህን ሥልጣን ለሚፈቅደው ሊሰጥ ይችላል (ሉቃስ 4፡6)። በሞት ላይ ሥልጣን የነበረው መሆኑ ተነግሮለታል (ዕብ. 2፡14)። ይሁን እንጂ ይህ ሥልጣኑ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሽሮአል (ራእይ 1፡18)። ሰይጣን ኢዮብን በተመለከተ በሕመም ላይ ሥልጣን ነበረው (ኢዮብ 2፡7)፤ ሐዋርያው ጴጥሮስን እንደ ስንዴ ሊያበጥረው ይችል ነበር (ሉቃስ 22፡31፤ 1ኛ ቆሮ. 5፡5)። በተመሳሳይ ሁኔታ ሰይጣን “ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትን ያናወጠ፥ ዓለሙን ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችን ያፈራረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደቤታቸው ያልሰደደ” (ኢሳ. 14፡12-17) መሆኑ ተገልጧል። በሰይጣን ሥልጣን ላይ የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳ የስድብ ቃል ሊናገር አልደፈረም (ይሁዳ 9)። ይህ ሁሉ ቢሆንም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ ሰው ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በክርስቶስ ደም አማካይነት በሰይጣን ሳይ ድል አለው (ኤፌ. 6፡10-12፤ 1ኛ ዮሐ. 4: 4፤ ራእይ 12፡11)። ሰይጣን ኃይሉንና ሥልጣኑን ለመጠቀም የሚችለው፥ ከእግዚአብሔር በተፈቀደለት መጠን ብቻ ነው። 

2. ሰይጣን በአጋንንት ይታገዛል። የሰይጣን ኃይል የሚበረታው ፈቃዱን በሚፈጽሙና በሚያገለግሉት አጋንንት አማካይነት ነው። እንደ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ የሚገኝ፥ ሁሉን የሚችል ወይም ሁሉንም የሚያውቅ ባይሆንም፥ በሚያገለግሉት ርኩሳን መናፍስት አማካይነት መላውን ዓለም ያዳርሳል። 

ሰይጣን ዓለምን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ማናቸውም እንቅስቃሴ አጋንንት እጅግ ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ (ማር. 5፡9)። በሰዎችና በእንስሳት ውስጥ የማደርና እነርሱንም የመቆጣጠር ችሎታ እሳቸው (ማር. 5፡2-5፤ 11-13)። አካል ባለው ነገር ሁሉ ውስጥ የማደር ፍላጎት አላቸው (ማቴ. 12፡43-44፤ ማር. 5፡10-12)። 

እንዳንዴ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በሌላ ሁኔታ ደግሞ በሰዎች በማደር አካላቸውንና ንግግራቸውን ይቆጣጠራሉ (ማቴ. 4፡24፤ 8፡16፥ 28፥ 33፤ 9፡32፤ 12፡22፤ ማር. 1፡32፤ 5 ፡15-16፥ 18፤ ሉቃስ 8፡36፤ ሐዋ. 8፡7፤ 16፡16)። አጋንንት እንደ ሰይጣን ሁሉ ርኩሳንና ተንኮለኞች ናቸው። በመሆኑም የያዟቸውን ሰዎች ይጎዷቸዋል (ማቴ. 8፡28፤ 10፡1፤ ማር. 1፡23፤ 5፡3-5፤ 9፡17-26፤ ሉቃስ 6፡18፤ 9፡39-42)። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መሆኑን እንደሚያውቁ በብዙ ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ (ማቴ. 8፡28-32፤ ማር. 1፡23-24፤ ሐዋ. 19፡15፤ ያዕ. 2፡19)። 

እንደ ሰይጣን ሁሉ አጋንንትም ለዘላለም ቅጣት የተወሰኑ መሆናቸውን ያውቃሉ (ማቴ. 8፡29፤ ሉቃስ 8፡31)። አጋንንት የአካላት መናወጥ (ማቴ. 12፡22፤ 17፡15-18፤ ሉቃስ 13፡16) እና የአእምሮ መታወክን ሊያስከትሉ ይችላሉ (ማር. 5፡2-13)። የአእምሮ መታወክ በአካላዊ ችግሮች ሊከሰት ቢችልም፥ አንዳንድ የአእምሮ መታወክ ዓይነቶች ያለ ጥርጥር ከአጋንንት ናቸው። የአጋንንት ተጽዕኖ ወደተሳሳተ ሃይማኖት፥ ከሰው ተለይቶ ወደመኖርና ወደአለማመን ሊመራ ይችላል (1ኛ ጢሞ. 4፡1-3)። 

እጋንንት በክርስቲያን ላይ የሚያደርጉት ተጽዕኖ ግልጥ ነው (ኤፌ. 6፡12፤ 1ኛ ጢሞ. 4፡1-3)። የሥልጣናቸው ተጽዕኖ መጠንም ዳግም በተወለዱትና ባልዳኑት ነፍሳት ላይ ተመሳሳይ አይደለም። ምክንያቱም ክርስቲያን ከዳነበት (ዳግም ከተወለደበት ጀምሮ የሚያድርበት የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ አለ። እጋንንት ያልዳኑትን ሊይዙና ሊያድሩባቸው ሲችሉ፥ በዳኑት ላይ ግን ተጽእኖ ብቻ ሊያደርጉ ነው የችሉት። በዳኑት ላይ የሚያሳድሩት የተጽዕኖ ጊዜም ውስን ነው። ቁጥራቸው እጅግ የበዛ እነዚህ አጋንንት፥ የሰይጣንን ፈቃድ ባያከናውኑ፥ ትእዛዙንም ባያፈጽሙለት ኖሮ ሥራው ባልተከናወነለት ነበር። አጋንንት ስለሚያግዙት የማያቋርጥና በዓይን የማይታይ ጦርነት ከቅዱሳን መላእክት ጋር ሁሌ ያካሂዳል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: