አሕዛብ በታሪክና በትንቢት

ሀ. አሕዛብ በእግዚአብሔር ዕቅድ 

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በታሪክና በትንቢት መሠረት ሦስት ዓበይት የሰው ልጆች ከፍሉችን ለማጤን ይቻላል። 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡32 ውስጥ በተመለከተው መሠረት የእግዚአብሔር ዓላማ ከአይሁዶች፥ ከአሕዛብና ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚገናኝ መሆኑ ተመልክቷል። ከዚህ ጋር የሰብአዊ ታሪክ ወይም ትንቢት ዓቢይ እካል ሆኖ የማይቆጠረው ለመላእክትና በነሱ በኩል የሚደረገው የእግዚአብሔር አገልግሎት ሊታከል ይችላል። 

እግዚአብሔር እስራኤልን የመለኮት መገለጫ፥ የክርስቶስ መምጫ ልዩ መንገድ ከማድረጉና የጸጋው መግለጫ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ካለው ዓላማ ጋር ሲነጻጸር፥ ለአሕዛብ ያለው ዓላማ ክብሩንና ሁሉን ቻይነቱን ካመግለጥ ጋር የተዛመደ ነው። 

ለ. አሕዛብን የሚመለከቱ ቀደምት ትንቢቶች 

በአንድ በኩል፥ ለአሕዛብ ትንቢት የተጀመረው ኤደን ገነት ውስጥ ነው። የዚህ ምክንያቱ በተወሰነ ደረጃ አሕዛብ የእግዚአብሔር የድነት ዓላማ ተካፋዮች በመሆናቸው ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ በኖኅ ዘመን ከርሱና ከቤተሰቡ በስተቀር የሰውን ዘር ጠራርጎ ስላጠፋው የጥፋት ውኃ ትንቢት ተነግሯል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ሰባቢሎን ግንብ ጊዜ እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ያወረደው ፍርድ ታሪክም ተመዝግቧል (ዘፍጥ. 11፡1-9)። ከዘፍጥረት ምዕራፍ 12 ጀምሮ ግን የሰው ዘር በሁለት ምድቦች ተከፍሏል። ይኽውም ከአብርሃም፥ ከይስሐቅና ከያዕቆብ የሚመጣውን የተስፋ ቃል ዘር እግዚአብሔር መግለጥ መጀመሩ ነው። ሌሎቹ ሁሉ በአሕዛብነታቸው ቀጠሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ጋር ያደረጋቸው መሠረታዊ ነገሮች ሁሉ ከእስራኤል ጋር በተያያዘ መልኩ ነው። 

የመጀመሪያዋ ታላቅ የአሕዛብ መንግሥት ሆና የምትታወቀው ግብፅ ናት። በመጀመሪያዎቹ አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ እንደተመዘገበው፥ እስራኤላውያን ከትንሽ ቤተሰብነት ወደ ትልቅ ሕዝብነት ያደጉት ግብፅ ውስጥ ነበር። በዳዊትና ሰለሞን ዘመን እስራኤላውያን ታላቅ ሕዝብ ለመሆን ቢበቁም፥ በ721 ዓ.ዓ. አሥሩ ነገዶች ሁለተኛይቱ ኃያል የአሕዛብ መንግሥት በነበረችው በአሦር ተማርከዋል። በአሦራውያን አማካይነት በእስራኤል ላይ የደረሰው የእግዚእብሔር ፍርድ ቀደም ብሎ የተተነበየ ሲሆን፥ እንደተሳለው በትክክል ተፈጽሟል። 

ይህም ሆኖ፥ ከእስራኤል ጋር በተያያዘ ሁኔታ የአሕዛብ ዓቢይ ሚና የተጀመረው በባቢሎን መንግሥት ነበር። ባቢሎን ሦስተኛዋ ኃያል የአሕዛብ መንግሥት ስትሆን፥ በዳንኤል ትንቢቶች ውስጥ ከሚገኙት አራት መንግሥታት ግን የመጀመሪያዋ ናት። 

ሐ. የአሕዛብ ዘመናት 

ከሦስቱ የእግዚእብሔር ዕቅዶች ሁለቱ ለነብዩ ዳንኤል ተገልጠውለታል። እነሱም እግዚአብሔር ለእስራኤልና ለአሕዛብ ያሉት ዕቅዶች ናቸው። ዳንኤል ምዕራፍ 2 ውስጥ እንደተገለጠው ናቡከደነፆር በተመለከተው ሕልም ተጀምሮ ለዳንኤል በታዩት ራእዮች በቀጠለው ተከታታይ መልኮታዊ መገለጥ፥ ከባቢሎን ጀምሮ እራት ኃያላን የአሕዛብ መንግሥታት እስራኤልን እንደሚገዙ እግዚአብሔር ገልጧል። ይህም ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ውስጥ በታየው ታላቅ ምስል ውስጥ ተገልጧል፤ የወርቁ ራስ ባቢሎንን፥ ከላይ ብር የሆነው ሜዶንና ፋርስን፥ የታችኛው የነሐስ ገጽታ ግሪከን፥ እና ብረት የሆኑት እግሮች ሮምን ያመስክቱ ነበር። ይህ እውነት ዳንኤል ምዕራፍ 7 ውስጥ ተጠናክሯል። በዚህ ምዕራፍ አራቱ አራዊት አራቱን መንግሥታት አመልክተዋል። 

ዳንኤል በትንቢት መጽሐፉ አምስተኛ ምዕራፍ እንደተጠቀሰው፥ ሁለተኛው መንግሥት (ሜዶንና ፋርስ) በ539 ዓ.ዓ. ባቢሎንን ሲያሸንፍ በሕይወት ኖሮ ለመታዘብ በቅቷል። ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ የግሪክ መንግሥት በታላቁ እስክንድር እየተመራ የፋርስና ሜዶንን መንግሥት ቅሬታዎች አሸነፈ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለት መቶ ዓመት ደግሞ የሮም መንግሥት ወደ ኃያልነቱ እየተሸጋገረ መጥቶ ከሁሉም ዘመን መንግሥታት ወደላቀ ደረጃ ደረሰ። 

ከባቢሎን ጀምሮ የነበሩት የአራት መንግሥታት ዘመን በክርስቶስ (የአሕዛብ ዘመን” ተብሎ የተጠራ ሲሆን (ሉቃስ 21፡24)፥ መለያ ባሕርዩም የኢየሩሳሌም በአሕዛብ አገዛዝ ሥር መውደቅ ነው። ምንም እንኳ በኢየሩሳሌም ላይ የነበረው የአሕዛብ አገዛዝ ለአጭር ጊዜ የተነሣ ቢሆን፥ ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስ ድረስ የኢየሩሳሌም ከአሕዛብ መንግሥታት አገዛዝ መሳቀቅ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚሆን ጉዳይ አይደለም። 

በባቢሎን፥ ሜዶን-ፋርስ፥ ግሪክና ሮም መነሣትና መውደቅ እንደታየው፥ አብዛኛው የአሕዛብ ዘመን ቀደም ብሎ ተፈጽሟል። ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ውስጥ እንደተመለከተው በምስሉ እግርና በዳንኤል 7 እሥር ቀንዶች ባሉት አውሬ የተመሰለው የመጨረሻው ደረጃ የሮም መንግሥት ግን በቀጥተኛ ትርጉሙ አልተከናወነም። እንደ 

መጽሐፍ ቅዱስ አገላለጥ፥ እራተኛው አውሬ ከሰማይ በሚመጣው የሰው ልጅ (ክርስቶስ) ይደመሰሳል። ይህም ዳንኤል ምዕራፍ ሰባት ውስጥ እንደተመለከተው ወይም ምዕራፍ ሁለት የናቡከደናፆርን ምስል እንደሚያወድም በተጠቀሰው ድንጋይ ተመስሏል። 

በነዚህ ትንቢቶች ላይ በመመሥረት፥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የሮም መንግሥት ወደፊት ዳግም እንደሚነሣ ያምናሉ። መንግሥቱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ክተነጠቀች በኋላና ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት ዳግም ከመመለሱ በፊት እንደሚነሣ ያስረዳሉ። ይህ ክስተት መጽሐፍ ቅዱስ የፍጻሜው ዘመን (ዳን. 11፡35) እያለ በሚጠራው ጊዜ የሚከናወን ሲሆን፥ ወደ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከሚያመራው ጊዜ ጋር ስለሚዛመድ፥ በዓለም ታሪከና ትንቢት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ይኖረዋል። 

ክርስቶስ ዳግም ወደ ምድር ሲመለስ፥ የአሕዛብ ዘመን ፍጻሜ ይሆናል። በዚህም ጊዜ የዳኑና በሺህ ዓመቱ ዘመን በምድር ላይ የሚገኙ እሕዛብ ከእግዚአብሔር ዘንድ ልዩ በረከትን ይቀበላሉ። ይህን ጉዳይ ወደ ኋላ ስለ ሺህ ዓመቱ መንግሥት በምንነጋገርበት ክፍል እንደገና እናየዋለን። 

በአጠቃሳይ መልኩ፥ አሕዛብን አስመልክቶ የቀረሰው መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንቢት አስተዋጽኦ የዓለም ታሪክ አስተዋጽኦ ነው። ይህም የቀደሙትን አያሌ ክሥተቶች የሚያብራራና በወደፊቱም ላይ ጥላውን የሚጥል ነው። አሁን በዓለም ላይ የሚታዩት ሁኔታዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ፥ የመጨረሻውን ዘመን ፈጣን ፍጻሜ የሚጠቁሙ ይመስላሉ። ከመጨረሻው ዘመን መከሠት ቀደም ብሎ ቤተ ክርስቲያን ትነጠቃለች። በማጠቃለያው ከዘመኑ ጋር የሚዛመዱ ነገሮች ሁሉ ተግባራዊ ከመሆናቸውም በላይ፥ ክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥቱን ለመመሥረት ይመጣል። 

አሁን ያለንበት ዘመን ስለ አሕዛብ የተነገረው ወይም በብሉይ ኪዳን የተመለከተው ዕቅድና ትንቢት መፈጸሙን አያመለክትም። ትንቢቱ በበዓለ ኀምሳ የተቋረጠና ከመነጠቅ በኋላ የሚቀጥል ይመስላል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም እድገት ውስጥ የሚገኙ ነገሮችም የዘመኑን ፍጻሜ የሚጠቁሙ ይመስላሉ። በዚሁ መሠረት የዘመኑን ወደ ፍጻሜው መቃረብና ስስ አሕዛብ የተነገረው ትንቢት ክንውን እንደገና መጀመር ምልክት ይታያል። ስለሆነም፥ ስለ አሕዛብ የተነገረውን ትንቢት ማጥናቱ፥ የጠቅላሳው ትንቢታዊ ዕቅድ አስፈላጊ ገጽታ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ዛሬ ምን በማድረግ ላይ እንዳለና ወደፊትም ምን ለማድረግ እንደሚፈልግ ለመረዳትም ያስችላል።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: