እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- የማጥመቅ ተግባሩ

ሀ. የመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ ትርጉም 

የመንፈስ ቅዱስ ማጥመቅ አስተምህሮ ከሌሎቹ አስተምህሮዎች ይልቅ ግራ የሚያጋባ ይመስላል። ይህ ችግር በአብዛኛው የሚከሰተው፥ የመንፈስ ቅዱስ የማጥመቅ ተግባር የሚጀምረው ከሌሎቹ ታሳሳቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች፥ ማለት ከዳግም ልደት፥ መንፈስ ቅዱስ በአማኙ ውስጥ ከማደሩ እና ከማተሙ ተግባር ጋር በአንድ ላይ በመሆኑ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎችም የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና መሞላት ተግባር በአንድ ጊዜ ሆኖ ያውቃል። ይህ ሁኔታ አንዳንድ ተንታኞች ሁለቱም ክንውኖች ተመሳሳይ ናቸው እንዲሉ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጋር የተዛመዱ የመጽሐፍ ክፍሎችን በጥንቃቄ ሲመረምር፥ በአተረጓጎም የሚፈጠረው አለመግባባት ይፈታል። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን በሚመለከት አዲስ ኪዳን ውስጥ በአጠቃላይ አሥራ አንድ ግልጥ ጥቅሶች አሉ (ማቴ. 3፡11፤ ማር. 1፡8፤ ሉቃስ 3፡16፤ ዮሐ. 1፡33፤ ሐዋ. 1፡5፤ 11፡16፤ ሮሜ 6፡3-4፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡13፤ ገላ. 3፡27፤ ኤፌ. 4፡5፤ ቆላ. 2፡12)። 

ለ. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከጰንጠቆስጤ ዕለት በፊት 

አራቱ ወንጌላትና በሐዋርያት ሥራ 1፡5 ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ሲመረመሩ፥ በእያንዳንዱ ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከዚያ በቀደሙ ጊዜያት ያልሆነና የወደፊት ከንውን መሆኑ ግልጥ ይሆናል። ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ብሉይ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሰ ነገር የለም። አራቱ ወንጌላት ናቸው ከሐዋርያት ሥራ 1፡5 ጋር በአንድ ላይ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ጎና ሊሆን የሚገባው ነገር እንደነበር የገለጡት። ወንጌላት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ በኩል የሚያከናውነው ተግባር ሆኖ ነው የቀረበው። ለምሳሌ ማቴዎስ 3፡11 ውስጥ መጥምቁ ዮሐንስ “እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል” በማለት ስለ ክርስቶስ ተንብዮአል። በእሳት የማጥመቁ ጉዳይ በኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት ስለሚኖረው ፍርድ የሚያመለክት ይመስላል። ይህ ጉዳይ ሉቃስ 3፡16 ውስጥ እንጂ ማርቆስ 1፡8 ወይም ዮሐንስ 1፡33 ውስጥ አልተጠቀሰም። አንዳንድ ተንታኞች ይህን ሁኔታ በሐዋርያት ሥራና በመልእክቶች ከተጠቀሰው የመንፈስ ጥምቀት የተለየ አድርገው ነው የተገነዘቡት። የተሻለው አመለካከት ግን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በመላው አዲስ ኪዳን ተመሣሣይ መሆኑን መገንዘቡ ነው። በየትኛውም ሁኔታ ይሁን ጥምቀቱ የሚከናወነው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ነው። ይህም ክርስቶስ ራሱ የርሱን በዮሐንስ እጅ መጠመቅ ከአማኞች ወደፊት በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ጋር ባነጻጸረበት ሥፍራ ተገልጧል። ይህም ከእርገቱ በኋላ የሚፈጸም ነበር። ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፡- ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” (ሐዋ. 1፡5)። 

ሐ. በዚህ ዘመን ያሉ ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀዋል 

የመንፈስ ቅዱስን የማጥመቅ ሁኔታና ጊዜ በተመለከተ ከሚፈጠረው ግራ መጋበት የተነሣ ማንኛውም ክርስቲያን ድነትን ባገኘ ወቅት በመንፈስ ቅዱስ መጠመቁን ብዙዎች አይገነዘቡትም። ይህ እውነት በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ጉዳይ ማዕከላዊ ጥቅስ በሆነው በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ውስጥ “አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል” ተብሏል። ጥቅሱ የሚያመለክተው በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ከዚሁ መንፈስ ጋር ወደ እዲስ ግንኙነት የመግባታችንን እውነት ነው። 

“እኛ ሁላችን” የሚለው አገላሰጥ የሚያመለክተው ሁሉንም ሰዎች ሳይሆን፥ ክርስቲያኖችን መሆኑን በሚገባ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ይህም ክርስቲያኖች ለሆኑ ሁሉ የሚሆን እንጂ ከመካከላቸው ለተወሰኑ ቡድኖች ብቻ አለመሆኑ መታወቅ አለበት። እውነቱ ክርስቲያን ሁሉ ከዳነበት ቅጽበት ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ክርስቶስ አካል መጠመቁ ነው። በዚሁ መሠረት ኤፌሶን 4፡5 ላይ “አንድ ጌታ፥ አንድ ሃይማኖት፥ አንዲት ጥምቀት” ይላል። የውኃ ጥምቀት ሥርዓት የተለያየ ቢሆንም፥ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አንድ ብቻ ነው። የዚህ አገልግሎት ሁለንተናዊነት እንደሚያመለክተው ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ለመጠመቅ ጥረት እንዲያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድም ጊዜ አልተጠየቀም፤ ከመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላ ነው የተመከረው (ኤፌ. 5፡18)። 

መ. በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ ወደ ክርስቶስ አካል መጨመር 

በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ሁለት ዋና ዋና ውጤቶች ይገኛሉ። የመጀመሪያው አማኙ መጠመቁ ወይም ወደ ክርስቶስ አካል መጨመሩ ሲሆን፥ ከዚሁ ጋር የተያያዘውና ሁለተኛው ደግሞ አማኙ ወደ ክርስቶስ ውስጥ መጠመቁ ነው። እነዚህ በአንድ ላይ የሚፈጸሙ ሁለት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀቶች እጅግ ዋናዎቹ ናቸው። 

በዚህ ዘመን አንድ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት የእውነተኛ እማኞች ሕያው ሕብረት ወደሆነው የክርስቶስ አካል ይጨመራል። በዚህ ደረጃ የጥምቀት መሠረታዊ ትርጉም መጨመር፥ መገናኘት፥ እንዲሁም አዲስና ዘላለማዊ ግንኙነት መስጠት የሚለውን ይይዛል። በዚህ መሠረት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በተለያዩ ዘመናት ከተለያዩ ሕዝቦች የመጡ አማኞችኝ ሁሉ ወደ አንድ የክርስቶስ አካል እንዲጨመሩና አዲስና ዘላለማዊ ኅብረትን የሚካፈሉ ያደርጋቸዋል። 

በዚህ ሁኔታ በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት የሚፈጠረውና አዳዲስ አባላት በተጨመሩ ቁጥር የሚያድገው የእማኞች አካል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ሐዋ. 2፡47፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡15፤ 12፡12-14፤ ኤፌ. 2፡16፤ 4:4-5፥ 16፤ 5፡30-32፤ ቆላ. 1፡24፤ 2፡19)። የዚህ አካል ራስና ክንውኖቹን ሁሉ የሚመራ ክርስቶስ ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡3፤ ኤፌ. 1፡22-23፤ 5፡23-24፤ ቆላ. 1፡18)። በዚህ ሁኔታ በክርስቶስ የተፈጠረውንና የሚመራውን አካል ክርስቶስ ራሱ ያሳድገዋል፥ ይጠነቀቅለታል (ኤፌ. 5፡29፤ ፊልጵ. 4፡13፤ ቆላ. 2፡19)። ከከርስቶስ ተግባራት አንዱ ይህን አካል በክብር ለመገለጡ ዕለት ለማቅረብ መቀደስ ነው (ኤፌ. 5፡25-27)። 

እማኝም እንደ ክርስቶስ አካል አባልነቱ በዚህ አካል ውስጥ የሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ስጦታዎች ወይም ሥራዎች አሉ (ሮሜ 12፡3-8፤ 1ኛ ቆሮ. 12፡27-28፤ ኤፌ. 4፡7-16)። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ወደ ክርስቶስ አካል መጨመር፥ ዘር፥ ባሕል ወይም ማንነት የሌለበትን አካል ሕብረት ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፥ አማኙ የራሱ የተለየ ሥራና ሥፍራ ያለው የመሆን ዋስትና ይሰጠዋል። በአቅሙና በስጦታው መሠረት በአካሉ ውስጥ እግዚአብሔርን እንዲያገለግልም ዕድል ያስገኝለታል። አካሉ በአጠቃላይ “የተጋጠመና የተያያዘ” (ኤፌ. 4፡16) ነው። እባላቱ የተለያዩ ቢሆኑም፥ እካሉ ግን በሚገባ የተያያዘና የተደራጀ ነው። 

ሠ. መንፈስ ቅዱስ ወደ ክርስቶስ ውስጥ ማጥመቁ 

በመንፈስ የተጠመቀ አማኝ፡የክርስቶስ አካል ከሆኑት አማኞች ጋር ካለው አንድነት ተጨማሪ፥ በክርስቶስ ያለ በመባሉ አዲስ ሥፍራ አለው። ይህ ሁኔታ ዮሐንስ 14፡20 ውስጥ ክርስቶስ በመሰቀሉ ዋዜማ ምሽት “እኔ በአባቴ እንዳለሁ፥ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ፥ እኔም በእናንተ እንዳለሁ፥ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ” በማላት በተናገረው ቃል ተተንብዮ ነበር። “እናንተም በእኔ” የሚለው አነጋገር ሊመጣ ያለውን የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ነበር የተነበየው። 

አማኝ በክርስቶስ ውስጥ በመሆኑ ክርስቶስ በሞቱ፥ በትንሣኤውና በክብሩ ከፈጸመው ክንውን ጋር ይዛመዳል። ይህ ሮሜ 6፡1-4 ውስጥ አማኝ ወደ ክርስቶስ እካልነትና ወደ ሞቱ የተጠመቀ መሆኑን በሚያስገነዝበው ቃል ተረጋግጧል። በሞቱ ከተዛመደ ከክርስቶስ ጋር ተቀብሮ አብሮት ተነሥቷል። ብዙ ጊዜ ይህ ድርጊት የውኃ ጥምቀት ሥርዓትን የሚወክል ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ነገር በማንኛውም እኳኋን የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሚጨምር መሆኑና ያለ እርሱ የጥምቀቱ ሥርዓት ትርጉም የለሽ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ቆላስይስ 2፡12 ውስጥ ተመሣሣይ ምንባብ አለ። በመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አማካይነት ከክርስቶስ ጋር መመሳሰላችን፥ እግዚአብሔር ሰጊዜ ውስጥና ሰዘላለም ለአማኙ ለሚያደርገው ሁሉ ዋና መሠረት ነው። 

አንድ እማኝ ክርስቶስ ውስጥ ከመሆኑ የተነሣ፥ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራሷ ከሆነው ክርስቶስ የምትጋራው ሕይወት ተካፋይ ነው። ክርስቶስ ራሷ ከሆነው ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት፥ ልክ ሰብአዊ አእምሮ አካልን እንደሚመራ፥ እርሱም ልዑላዊ በሆነ መንገድ መምራቱ ነው። 

ረ. የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከመንፈሳዊ ልምምድ ጋር ሲዛመድ 

ማንኛውም ክርስቲያን ድነትን ባገኘ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቋል ከሚለው እውነት የምንረዳው ነገር፥ ጥምቀት በእምነት ልንቀበለው የሚገሳ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ነው። ምንም እንኳን የኋላ መንፈሳዊ ልምምድ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን የሚያረጋግጥ ቢሆን፥ ጥምቀት በራሱ ልምምድ አይደለም። ጥምቀት ለሁሉም አማኝ የሚሆንና በክርስቶስ ካለን ሥፍራ ጋር የሚዛመድ ስለሆነ፥ በቅጽበት የሚከናወን የእግዚአብሔር ሥራ እንጂ፥ ከዳግም ልደት በኋላ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ አይደለም። 

ብዙ ስሕተት የሚፈጠረው፥ ክርስቲያኖች በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን የልሳን በመናገር የተገለጠውን ዓይነት የመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ ሊፈልጉ ይገባል ከሚለው አመለካከት ነው። ሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሦስት ሁኔታዎች (ምዕራፎች 2፥ 10 እና 19) ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ሲጠመቁ በልሣን መናገራቸው ተገልጧል። ቢሆንም ያ ሁኔታ ያልተላመደና ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሽግግራዊ መሆን ጋር የተያያዘ መሆኑ ግልጥ ነው። የድነት ሥራ በተከናወነባቸው ሌሎች ሁኔታዎች፥ በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ ጊዜ በልሣን የመናገር አጋጣሚ አልተጠቀሰም። 

የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖች ሁሉ በመንፈስ መጠመቃቸው ግልጥ ቢሆንም፥ ሁሉም በልሳን ተናግረዋል ማለት ግን አይደለም። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ልዩ ለሆነ የእግዚአብሔር አሠራር ምክንያት አስፈላጊ አድርጎ መውሰድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። የመንፈስ ቅዱስ ሙላትን በልሳን ከመናገር ጋር በማያያዝ እንደ ብቸኛ ምልክት ከመውሰድ ይልቅ፥ ገላትያ 5፡22-23 ውስጥ እንደተጠቀሰው፥ በመንፈስ ፍሬ ነው የአንድን ሰው በመንፈስ ቅዱስ መሞላት መመዘን የሚቻለው። የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ሳይሞሉ በልሳን ተናግረዋል። 

ሁላት ዓይነት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አለ የሚል ሌላ ስሕተተም እንዳንዴ ይነገራል። አንደኛው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፥ ሌላው በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13 ላይ የተመሠረተ ነው። ሐዋርያት ሥራ 10-11 ውስጥ ያለውን የቆርነሌዎስ መለወጥ፥ ከሐዋርያት ሥራ 2 ጋር በማነጻጸር እሕዛብ በሆነው ቆርነሌዎስ ላይ የተፈጸመው ሁኔታ በጰንጠቆስጤ ዕለት ሰሐዋርያት ሳይ ከደረሰው ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ለመረዳት ይቻላል። ሐዋርያት ሥራ 11፡15-17 ውሰጥ ጴጥሮስ “ለመናገርም በጀመርኩ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ፥ ለእኔ ደግሞ በመጀመሪያ እንደወረደ፥ ለእነርሱ ወረደላቸው። ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ትጠመቃላችሁ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላመንነው ለእኛ ደግሞ እንደሰጠን፥ ያን ሰጦታ ለእነርሱ ካሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እኔ ማን ነበርሁ?” ብሏል። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት አንድን አማኝ ወደ ክርስቶስ አካል የሚጨምረው እንደመሆኑ፥ ከሐዋርያት ሥራ 

ምዕራፍ ሁለት ጀምሮ እስከዚህ ዘመን ድረስ ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው። 

ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ከክርስቶስ እና ከእማኞች ጋር በአዲስ ሕብረት የሚያገናኝ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ስለሆነ ታላቅ ነገር ነው። በክርስቶስ እዲስ ሥፍራ ያስገኛል፥ ከክርስቶስ አካል ጋርም በቅርብ ያስተሣሥራል። አማኙን ፍጹም አድርጎ በመጨረሻ በክብር የሚያቀርብ የጽድቅና የእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ መሠረት ነው። 

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.