እግዚአብሔር አብ

ሀ. አብ የመጀመሪያው አካል 

አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስን በሚገልጠው የሥላሴ ትምህርት፥ የመጀመሪያው አብ ይባላል። አብ፥ ወልድም ሆነ መንፈስ ቅዱስ በተናጠል ሥሉስ አይደሉም። ሥላሴ ሦስቱንም አካላት ይይዛል። ምንም እንኳ የአብ፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን ሲሰጥና ይህ ቃል ለሥላሴ መጠሪያነት ያገለገለ ቢሆን፥ አዲስ ኪዳን ነው ሙሉውን አስተምህሮ የሚገልጠውና የሚያብራራው። አብ እንደ መራጭ፥ አፍቃሪና ለጋስ ተገልጧል። ወልድ እንደ ሕማም ሰው ፥ ተቤዥ እና ዓለማትን እንደሚይዝ ተገልጿል። መንፈስ ቅዱስ ዳግም ልደት የሚሰጥ፥ በሰው የሚያድር፥ የሚያጠምቅ፥ ኃያል የሚሰጥ እና የሚቀድስ ሆኖ ነው የተገለጠው። የአዲስ ኪዳን መገለጥ ዋና ጉዳይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስን መግለጥ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሲገለጥ፥ የእግዚአብሔር አብ እውነትም አብሮ ይገለጣል። አብ ልጁን የላከበትና የሾመበት፥ ወልድ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የላከበትና የሾመበት ቅደም ተከተል የማይዛባ ሲሆን፤ ይህ የሥነ-መለኮት ትምህርት ሊገለጥ የማይቻለውን የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን መለኮትነት በምንም ሳያሳንስ አብን የመጀመሪያው አካል አድርጎ የሚሰይም ነው። 

የእግዚአብሔርን አባትነት በሚመለከተው መገለጥ ውስጥ አራት የተለያዩ ሁኔታዎች ይታያሉ። (1) እግዚአብሔር አብ እንደ ፍጥረት ሁሉ አባት፥ (2) እግዚአብሔር አብ በቅርብ ግንኙነት፥(3) እግዚአብሔር አብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት፥(4) እግዚአብሔር አብ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነትና ጌትነት ለሚያምኑ ሁሉ አባት ነው። 

ለ. ለፍጥረት ሁሉ አባትነት 

ምንም እንኳን በመፍጠር ተግባር፥ እንዲሁም ቁሳዊዎቹን ዓለማትና በውስጣቸው ያሉትን በመደገፉ ረገድ፥ ሦስቱም አካላት ቢሣተፉ፥ የመጀመሪያው አካል፥ እግዚአብሔር አብ፥ በልዩ ሁኔታ የፍጥረታት ሁሉ አባት ነው። ኤፌሶን 3፡14-15 ውስጥ ጳውሎስ “ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ” ብሏል። እዚህ ላይ የተገለጠው የሥነ-ምግባራዊ ምርጫ ማድረግ ከሚችሉ ፍጡራን (መላእክትና ሰው) መካከል እግዚአብሔር አባት የሆነበት ቤተሰብን የሚያመለክት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ የመጀመሪያው አካል ዕብራውያን 12፡9 ውስጥ “የመናፍስት አባት” ተብሏል። ይህ እንደገና ሥነ-ምግባራዊ ፍጡራንን ሁሉ ማለት፥ ሰውንና መላእክትን ይጨምራል። 

ያዕቆብ 1፡17 ውስጥ በተገለጠው መሠረት የመጀመሪያው አካል፥“የብርሃናት አባት” ነው። ይህ ልዩ አገላለጥ፥ አካሉ የመንፈሳዊ ብርሃን ሁሉ ምንጭ መሆኑን የሚያመለክት ይመስላል። ኢዮብ 1፡6፤ 2፡1፤ 38፡7 ውስጥ መላእክት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል። ሉቃስ 3፡38 ውስጥ አዳም በፍጥረቱ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሏል። ነቢዩ ሚልክያስ በመጽሐፉ ምዕራፍ 2:10 ውስጥ “ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?” በማለት ይጠይቃል። ሐዋርያው ጳውሎስም አርዮስ ፋጎስ በተባለው ስፍራ ለአቴናውያን ባደረገው ንግግሩ፥ “እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች* ከሆንን” በማለት ጠቅሷል (ሐዋ. 17፡29)። (በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው “ጌኖስ” የሚለው ቃል “ዘር” ወይም “ልጅ” የሚለው ትርጉም አለው። የ1980ውና የ2001 ዓ.ም. የአማርኛ ትርጉሞች ሁለቱም “ልጆች” ብለው ተርጉመውታል። ይህም “ዘመዶች” ከሚለው ትርጉም ይልቅ ትክክለኛ ነው)። 1ኛ ቆሮንቶስ 8፡6 ውስጥ “ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ፥ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን” ተብሎ ተጽፏል። 

በነዚህ ጽሑፎች መሠረት፥ የሥላሴ ቀዳሚ አካል እንደፈጣሪነቱ የፍጥረታት ሁሉ አባት መሆኑን እና አካል ያላቸው ፍጡራን ሁሉ መነሻ እርሱ መሆኑን ለማመን የሚያበቃ ማረጋገጫ አለ። በዚህ መንገድ ብቻ ነው የእግዚአብሔርን ሁለንተናዊ አባትነት ለማመልከት የሚቻለው። በዚህ ሁኔታ ፍጥረታት ሁሉ ሁለንተናዊና ተፈጥሯዊ ወንድማማችነትን (ዝምድና) ይጋራሉ። ይሁን እንጂ ይህ አባባል ለዘብተኛ ትምህርተ መለኮታውያን (liberal theologians)፥ ሁለንተናዊ ድነት ወይም እግዚአብሔር ለማንኛውም ሰው በመንፈስ አባት ይሆነዋል፥ የሚሉትን የተሳሳተ አስተምህሮ አይደግፈውም። 

ሐ. በቅርብ ግንኙነት የሚመሠረት አባትነት 

ብሉይ ኪዳን ውስጥ የአባትነትና የልጅነት ፅንሰ-አሳብ እግዚአብሔርን ከእስራኤል ጋር ለማዛመድ በብዙ አጋጣሚ ተጠቅሷል። ዘጸአት 4፡22 ውስጥ ሙሴ ፈርዖንን እንዲህ ብሎታል “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡- እስራኤል የበኩር ልጄ ነው”። ይህ እግዚአብሔር ለእስራኤል ፈጣሪ ከመሆን በተጨማሪ ያለውን ግንኙነት ሲገልጥ፥ እስራኤላውያን ዳግመኛ ተወልደዋል ከማለት ደግሞ ጥቂት የሚያንስ ነው። ምክንያቱም፥ መንፈሳዊ ሕይወት የነበራቸው ሁሉም እስራኤላውያን አልነበሩም። ይህ ሁኔታ አባት ለልጁ እንደሚያደርገው፥ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ያለውን መለኮታዊ ግንኙነት፥ ክብካቤና ርኅራኄ ያመለክታል። 

እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ያለውን ፍቅር ለራሱ ለዳዊት ሲገልጥለት፥ በርሱና በዳዊት ልጅ በሰሎሞን መካከል የሚኖረው ግንኙነት የአባትና የልጅን ያህል እንደሚሆን እንዲህ በማለት አስታውቆታል፡- “እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል” (2ኛ ሳሙ. 7፡14)። በአጠቃላይ እንደ አምላካቸው ለሚተማመኑበት ሁሉ እንደ አባት እንደሚጠነቀቅላቸው እግዚአብሔር ገልጧል። ይህ አባባል መዝሙረ ዳዊት 103፡13 ውስጥ “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል” ተብሏል። 

መ. የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት 

የእግዚአብሔርን አባትነት በተመለከተ እጅግ ጠቃሚውና ሰፊው መገለጥ፥ የመጀመሪያው አካል ከሁለተኛው አካል (አብ ከወልድ) ጋር ያለውን ግንኙነት ያጠቃልላል። የመጀመሪያው አካል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት፥ ተብሏል (ኤፌሶን 1፡3)። የአዲስ ኪዳን ትምህርተ-መለኮታዊ አጠቃላይ መገለጥ እግዚአብሔር አብ ወይም የመጀመሪያው አካል፥ የሁለተኛው አካል የኢየሱስ ክርስቶስ አባት መሆኑን የሚያመለክተው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ እንደ እግዚአብሔር ልጅ መገለጡ፥ እንዲሁም የእግዚአብሔር ባሕርያትና ሥራዎች በተከታታይ ለርሱ መሰጠታቸው የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮትነት ያረጋግጣሉ። የሥላሴ ትምህርት ባጠቃላይ፥ ክርስቶስን እንደ ሁለተኛ አካልና ከአብ ጋር ደግሞ እንደ ልጁ ባለ ግንኙነት ይገልጠዋል። 

የሥነ-መለኮት ምሁራን አብ እንዴት የሁለተኛው አካል፥ ማለት የወልድ አባት ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት፥ ከአንደኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የበረታ ጥረት እድርገዋል። “አብ” እና “ወልድ” የሚሉት ቃላት የሚያመለክቱት፥ በአብና በወልድ መካከል ያለውን ልዩ የሆነ ግንኙነትን ሲሆን፥ ይህ፥ ግንኙነቱ በሰብአዊ አባትነትና ልጅነት መካከል እንዳለው የግንኙነት ዓይነት ነው ማለት እይደለም። ይህ ሁኔታ በተለይ የሚረጋገጥበት አሳብ አብና ወልድ ሁለቱም ዘላለማዊ መሆናቸውን በሚያሳየው እውነት ነው። በአራተኛው መቶ ክፍለ-ዘመን የተነሣው መናፍቅ፥ የአርዮስ የመጀመሪያ ስሕተት፥ ወልድ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው የሚለው ነበር። ጥንታዊቱ ቤተ ክርስቲያን ወልድ እንደ አብ ዘላለማዊ ነው ከሚለው መሠረተ አሳብ በመነሣት ይህን አስተምህሮ በኑፋቄነት አወገዘችው። 

አንዳንድ የሥነ-መለኮት ምሁራን የወልድን ዘላለማዊነት ተቀብለው፥ ነገር ግን ሁለተኛው አካል እንደ ወልድ ተግባሩን የጀመረበትን ሁኔታ በጊዜ ውስጥ አንድ ነጥብ ላይ ማለት፥ በፍጥረት መጀመሪያ፥ ሥጋ በለበሰበት ወቅት ወይም የኋላ ኋላ ሁለተኛው አካል ልዩ ግንዛቤ ባገኘ ጊዜ፥ ማለትም በተጠመቀበት ወቅት በትንሣኤው ወይም በዕርገቱ ጊዜ ነው ለማለት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ አማራጭ አመለካከቶች ሁሉ ስሕተት ናቸው። ምክንያቱም ወልድ ከዘመናት በፊት ጀምሮ ከአብ ጋር አንድነት ያለው መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያመለክታል። በዚህ መሠረት ወልድ፥ “አንድያ ልጅ (ዮሐ. 3፡16) ሲሆን፥ ሥጋ በለበሰ ጊዜ እግዚአብሔር ለዓለም የሰጠው” ልጁ ነው። ወልድ ለዓለም የተሰጠው እንደ እግዚአብሔር ልጅነቱ እንጂ፥ ከመሰጠቱ በኋላ ልጅ ይሆን ዘንድ አይደለም። ኢሳይያስ 9፡6 ውስጥ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል” ተብሏል። ይህ አሳብ ቆላስያዕ 1፡15-16 ውስጥ ይበልጥ ግልጥ ተደርጓል። በዚህ ስፍራ ክርስቶስ፥ «የማይታይ አምላክ ምሳሌ፥ … ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር” እንደሆነ ተነግሯል። ክርስቶስ የፍጥረታት ሁሉ በኩር ከሆነ፥ ማለት ከማንኛውም ፍጥረት ሁሉ በፊት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፥ የርሱ ልጅነት ከዘላለም በፊት መሆኑ ግልጥ ነው። 

ስለዚህ የአብና የወልድ አንድነት ከዘላለማዊነት አንጻር ከቅድስት ሥላሴ ዘላለማዊ መለኮትነት ጋር የሚያያዝ ገጽታ ሲኖረው፤ በሌላ በኩል ወልድ ሥጋን ከለበሰበት ዘመን እንጻር ደግሞ የሚታይ ለየት ያለ የጊዜ ገጽታ አለው። የኒቅያው ጉባኤ (325 ዓ.ም.) በአራተኛው ክፍለ-ዘመን ለተነሣው የአርዮስ ኑፋቄያዊ አስተምህሮ በሰጠው የመልስ ድንጋጌ፥ ለወልድ፥ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ፥ ከዓለማት መፈጠር በፊት የአብ የሆነ፥ ከእግዚአብሔር የወጣ እግዚአብሔር፥ ከብርሃን የሆነ ብርሃን፥ ከእውነተኛው አምላክ የወጣ እውነተኛ አምላክ፥ የተወለደ፥ ያልተፈጠረ፥ ከአብ ጋር አንድ የሆነ” ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ አትናቴዎስ በተባለው ጳጳስ አማካይነት የተቀናበረው ድንጋጌ እንዲህ ይላል፡- “ወልድ ከአብ ብቻ የሆነ፥ የተወለደ እንጂ ያልተሠራ ወይም ያልተፈጠረ፥ ከዘላለም በፊት ከአብ የወጣ። 

“አብ” እና “ወልድ” የሚሉት ቃላት ቀዳማዩንና ደህራዩን አካል ለመግለጥ በሚያገለግሉበት ጊዜ የሕይወትን፥ የባሕርይንና የልዩ መለያን አድነት ሊያስገነዝቡ በሚቻላቸው ከፍተኛ ሁኔታ ይገልጣሉ። ምንም እንኳን የጠበቀ የአባትና ልጅነት አንድነት ቢኖር፥ አብ ልጁን የመስጠቱና የመላኩ ሁኔታ፥ የወልድን እስከ መስቀል ሞት ድረስ መታዘዝን የሚጠይቅ ነበር። በዚህም የክርስቶስ በልጅነቱ መታዘዙ በሥላሴ የሥነ-መለኮት ትምህርት እኩልነታቸውን እና አንድነታቸውን የሚያሳይን ሐቅ በማፋለስ፥ የወልድን ከአብ ማነስ የሚያመለክት አይደለም። 

በቀዳማዩና ደሀራዩ የሥላሴ አካላት መካከል ያለው አንድነት፥ በአባትና በልጅ፥ እንዲሁም በልጅና በአባት መካከል እንዳለው ነው (2ኛ ቆሮ.1፡3፤ ገላ.4፡4፤ ዕብ. 1፡2)። ይህ አንድነት ፍጹም ከሆነው አእምሮ ዕቅድ ወይም አሳብ ጋር ራሱን የሚያስማማና እጅግ አስፈላጊ የሆነው እውነት መግለጫ ነው። አብ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የመሆኑ እውነት፥ ብሉይ ኪዳን ውስጥ አልፎ አልፎ ቢጠቀስም፥ (መዝ. 2፡7፤ ኢሳ. 7፡14፤ 9፡6-7)፥ አንዱ የአዲስ ኪዳን ዋናና አጠቃላይ አስተምህሮ ነው። 

1. የእግዚአብሔር ልጅ የአብ አንድያ ልጅ ተብሏል (መዝ. 2፡7፤ ዮሐ. 1፡14፥ 18፤ 3፡16፥18፤ 1ኛ ዮሐ. 4፡9)። 

2. አብ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልጄ ነው ብሎታል (ማቴ. 3፡17፤ 17፡5፤ ሉቃስ 9፡35)። 

3. ወልድ አብን አባቴ ብሎታል (ማቴ. 11፡27፤ 26፡63-64፤ ሉቃስ 22፡29፤ ዮሐ. 8፡16-29፥33-44፤ 17፡1)። 

4. አብ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት መሆንን ሰዎች አምነዋል(ማቴ. 16፡16፤ ማር. 15:39፤ ዮሐ. 1፡34፥ 49፤ ሐዋ. 3፡13)። 

5. ወልድ በመታዘዝ የአብን አባትነት አረጋግጧል (ዮሐ. 8፡29፥ 49)* 

6. ይህን በአብና ወልድ መካከል ያለ አንድነት አጋንንት እንኳን ያረጋግጣሉ (ማቴ. 8፡29)። 

ሠ. በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ አባት 

እግዚአብሔር አብ እንደ ፈጣሪነቱ ለፍጡራን ሁሉ አባት ከመሆኑ ግንዛቤ በተነጻጻሪ፥ በክርስቶስ ኢየሱስ ላመኑትና የዘላለም ሕይወት ላገኙት ልዩ በሆነ መልኩ አባት ነው። እግዚአብሔር የፍጥረታት አባት መሆኑ፥ ለሰዎች ሁሉ የድነት ወይም የዘላለም ሕይወት ዋስትና አይደለም። ድነት ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው በእምነት ለተቀበሉት ብቻ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ያስገነዝባል። እግዚአብሔር የሰው ዘር ሁሉ አባት ነው፥ በሰዎች መካከልም ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት አለ፥ የሚለው አሳብ ሁሉም ድነው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባሉ ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን፥ ለድነት በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑት ብቻ በመንፈሳዊ ትርጉሙ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ነው። ይህ የሚሆነው፥ ሰው ሆነው በመፈጠራቸውና የፈጠራቸው እግዚአብሔር በመሆኑ ሳይሆን፥ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ቤተሰብነት ከመንፈስ ዳግም በመወለዳቸው ነው ( ዮሐ. 1፡12፤ ገላ. 3፡26፤ ኤፌ. 2፡19፤ 3፡15፤ 5፡1)። 

መንፈስ ቅዱስ በሚያከናውነው ዳግም ልደት አማካይነት አማኝ የእግዚአብሔር የጸጋ ልጅ ይሆናል። አማኝ እግዚአብሔር አባቱ ስለሆነለት “አባ አባት ብሎ እንዲጠራው በመንፈስ ቅዱስ ይገፋፋል። ከእግዚአብሔር የተወለደ ነውና፥ የመለኮታዊው ባሕርይ ተካፋይ ነው። ከዚህ የልጅነት ሥልጣን የተነሣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሽ ነው (ዮሐ. 1፡12-13፤ 3፡3-6፤ ሮሜ 8፡16-17፣ ቲቶ 3፡4-7፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡4)። አማኝ በእምነት የሚጋራው መለኮታዊ ባሕርይ፥ በምንም ምክንያት ከርሱ በማይወሰድበት ሁኔታ ጸንቷል። 

የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ አሁን ካለው የሰይጣን ኃይልና ሥልጣን አኳያ ሲታይ፤ ሰዎች ሁሉ በሥጋዊ ትውልዳቸው የእግዚአብሔር ልጆች አለመሆናቸውን የሚያሳይ ተጨማሪ ማስገንዘቢያ ተሰጥቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የኢየሱስ ክርስቶስ ቀጥተኛና ታማኝ አባባሎች ማረጋገጫዎች ናቸው። ስለማያምኑ ሰዎች ሲናገር፡- “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ” (ዮሐ. 8፡4) ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ዳግም ስላልተወለዱት ሲናገር፥ “እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው”(ማቴ. 13: 38) በማለት ገልጧል። ሐዋርያው ጳውሎስ ድነት ስላሳገኙ ሰዎች ሲጽፍ፥ “የአለመታዘዝ ልጆች” እና “የቁጣ ልጆች” (ኤፌ. 2፡2-3) ብሏቸዋል። 

ሊተኮርበት የሚገባ እውነት፥ ማንም ቢሆን ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ሊያደርግ አለመቻሉ ነው። እግዚአብሔር ራሱ ነው ይህን ለውጥ ሊያከናውን የሚችል። ይህን የሚያደርገውም እርሱ ራሱ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ፥ ማለት ክርስቶስ ሊታመንበትና እንደ አዳኝ ሊቀበሉት የሚገባ በሆነው አሠራር አማካይነት ነው (ዮሐ. 1፡12)። 

የእግዚአብሔር አባትነት፥ የአዲስ ኪዳን ዋና አስተምህሮ ነው (ዮሐ. 20፡17፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡24፤ ኤፌ. 1፡3፤ 2፡18፤ 4፡6፤ ቆላ. 1፡12-13፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡3፤ 1ኛ ዮሐ. 1፡3፤ 2፡1፥ 22፤ 3፡1)። የሰማያዊው አባታችን ፍቅርና ጥበቃ ዋስትና ያለን መሆኑ፥ ለክርስቲያኖች ታላቅ መጽናናት፥ እንዲሁም ለእምነትና ለጸሎት የሚያበረታታን ነው።

ምንጭ፡- “ዋና ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጦች” መጽሐፍ በዶክተር ሉዊስ ስፔሪ ቼፈር የተጻፈ እና በተክሉ መንገሻ የተተረጎመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ስለ እነዚህ ቅዱሳን ድንቅ ስራ የተመሰገነ ይሁን፡፡ ማሳሰቢያ፡- ይህን ጽሁፍ መቀየርም ሆነ ለሽያጭ ማዋል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: