ስለ ኢየሱስ ሰምተው የማያውቁ ሰዎች ምን ይሆናሉ?

ሰዎች ስለ ክርስቶስ “ሰሙም አልሰሙም” በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረቱ (ሮሜ 1፡20) እና በሰዎች ልብ ውስጥ (መክብብ 3፡11) እንደገለጠ ይናገራል፡፡ ችግሩ ያለው የሰው ዘር ኃጢአተኛ በመሆኑ ምክንያት ይህን መገለጥ ወደጎን በመግፋት በእግዚአብሔር ላይ ማመጹ ላይ ነው (ሮሜ 1፡21-23)፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፀጋ ባይሆን ኖሮ፣ ሁላችን ለልባችን ክፉ ምኞት ተላልፈን በመሰጠት ያለ እሱ ሕይወት ምንኛ እርባናቢስ እና አስከፊ መሆኗን እናውቅ ነበር፡፡ ያለማቋረጥ ጀርባቸውን በሚሰጡት ሁሉ ላይ ግን እግዚአብሔር ይህን ሕይወት እንዲጋፈጡ ይፈርዳባቸዋል (ሮሜ 1፡24-32)፡፡

የችግሩ እውነታ፣ እነዚህ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር አለመስማታቸው ሳይሆን የሰሙትን እና በፍጥረት ውስጥ ተገልጦ የሚታየውን እውነታ ለመቀበል አለመፍቀዳቸው ነው፡፡ ዘዳግም 4፡29፣ “…አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ” ይላል፡፡ ይህ ጥቅስ አንድ ጠቃሚ መርሕ ያስተምራል – እግዚአብሔርን በእውነት የሚፈልግ ሁሉ ያገኘዋል። አንድ ሰው እግዚአብሔርን በእውነት ለማወቅ ከፈለገ እግዚአብሔር ራሱን ይገልጥለታል።

ችግሩ፣ እግዚአብሔር አለመገለጡ ሳይሆን “…አስተዋይ” እና “እግዚአብሔርንም የሚፈልግ” ሰው አለመኖሩ ነው (ሮሜ 3፡11)፡፡ በርካታ ሰዎች በፍጥረት እና በልባቸው ውስጥ የሚገኘውን የእግዚአብሔርን እውቀት ወደጎን በማድረግ ራሳቸው የፈጠሩትን “አምላክ” ለማምለክ መርጠዋል፡፡ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር፣ የክርስቶስን ወንጌል ለመስማት እድሉን ባላገኘው ሰው ላይ ሳይቀር ይፈርዳል፤ በዚህ ፍርድ ፍትሐዊነት ላይ መከራከር አመክኗዊነት የለውም፡፡ ሰዎች እግዚአብሔር አስቀድሞ በገለጠላቸው ነገር አንጻር በእርሱ ፊት ተጠያቂዎች ይሆናሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሰዎች ለዚህ መገለጥ (እውቀት) ጀርባቸውን እንደሰጡ ይናገራል፤ ስለሆነም እግዚአብሔር በእነሱ ላይ የሚያስተላልፈው የገሃነም ፍርድ ፍትሃዊ ይሆናል፡፡

ወንጌል ባልሰሙት ሰዎች ዕጣ ፈንታ ላይ ከመከራከር ይልቅ እኛ ክርስቲያኖች እነዚህ ሰዎች ወንጌል መስማታቸውን ለማረጋገጥ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ወንጌልን ወደ አሕዛብ ሁሉ ለማዳረስ ተጠርተናል (ማቴዎስ 28፡19-20፤ ሐዋ 1፡8)፡፡ ሰዎች በፍጥረት ውስጥ ለተገለጠው የእግዚአብሔር እውቀት እንቢተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ ሃቅ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ የሚገኘውን የመዳንን የምሥራች እንድናበስር ሊያነሳሳን ይገባል። ሰዎች ከኃጢአታቸው የሚድኑትና ዘላለማቸውን ከእግዚአብሄር ተነጥለው ከማሳለፍ የሚተርፉት በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔርን ጸጋ በመቀበል ብቻ ነው፡፡

ወንጌልን በጭራሽ ሰምተው የማያቁ ሰዎች ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሳ እንዲሁ ይድናሉ ብለን የምናስብ ከሆነ ትልቅ ችግር ውስጥ ነን፡፡ ወንጌልን በጭራሽ ያልሰሙ ሰዎች ባለመስማታቸው ምክንያት እንዲያው የሚድኑ ከሆነ፣ እንግዳውስ ሰዎች ይድኑ ዘንድ ወንጌል እንዳይሰሙ ማድረግ ይኖርብናል የሚለው እሳቤ ምክንያታዊ ይሆናል፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት ወንጌል ሳንነግረው እንዲያው ይድን የነበረውን ሰው ወንጌል በመንገራችን እና እርሱም ይህን ወንጌል በመቃወሙ ምክንያት በፍርድ ስር እንዲወድቅ ማድረጋችን ትልቅ ጥፋት ይሆናል ማለት ነው፡፡ እውነታው፣ ወንጌልን ያልሰሙ ሰዎች በእግዚአብሔር ፍርድ ስር መሆናቸው ነው፡፡ አለበለዚያማ ወንጌል መስበካችን ምን ፋይዳ ይኖረዋል? ወንጌልን ባለመስማታቸው ምክንያት አስቀድሞዉኑ “ድነው” የነበሩትን ሰዎች ወንጌል ሰምተው እንዲቃወሙት በር በመክፈት እንዲጠፉስ ለምን እናደርጋለን? 

ምንጭ፡- https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፡- አዳነው ዲሮ ዳባ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.