መንፈስ ቅዱስ አካል ነውን?

ከሥላሴዎች ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለን ግንዛቤ ያለጥርጥር በጣም ትንሽ ነው። ለማረጋገጥ ያህል የሚከተሉትን አስቸጋሪ ቃላት እንመልከት። “አካል” ሦስት አካላት አንድ አምላክ ስንል ምን ማለታችን ነው? እንዲሁም “መንፈስ”ን እንደ አካል መግለጥ እንግዳ ነገር ይመስላል። ቢሆንም ይህን ፅንሰ አሳብ መረዳት ለብዙ ትምህርቶች፥ ለምሳሌ ለመጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃልነት፥ የደኅንነትን የተለያዩ ገጽታዎች ለማወቅና ክርስቲያናዊ አኗኗርን ለመረዳት መሠረት ነው። ስለሆነም ይህን ተገቢ ጥያቄ በማቅረብ እንጀምር። 

አካል የሚለውን ቃል ስናነሳ በመጀመሪያ የሚታወሰን የሰው አካል ነው። ስለዚህም አካል እንደ ሰው ሁሉ ቁሳዊ አካል፥ ነፍስና መንፈስ ያለው ነው ብለን እናስባለን። ሰውየው ሞተ ብለን እንናገራለን። እንደ እውነቱ ግን አካሉ ሞተ ማለት ነበረብን። በሌላ አነጋገር አካልን ከሰውነት ለይተን ለማየት ልምዱ ስለሌለን ግንዛቤው ያስቸግረናል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሲሞት መኖር አለማቋረጡን እንዲሁም ነፍሱና መንፈሱ በመንግሥተ ሰማያት፥ ወይም በገሃነም እንደሚኖር እንናገራለን። ሰውዬው ቢሞትም ኗሪነት አለው። ለምሳሌ አባትዎ ወይም እናትዎ በጌታ ድነው ቢሞቱ ከእግዚአብሔር ጋር እንዳሉ ያውቃሉ። ስለዚህ ስለ አካል ስንናገር ከሰብአዊው ሰውነት ባሻገር ለማሰብ መቻል አለብን። መላእክት እውነተኛ ፍጥረታት ሲሆኑ፥ ሰው መሰል አካል የሌላቸው መናፍስት መሆናቸውን ግን አለመዘንጋት ነው። ሆኖም መንፈሳዊ አካል አላቸው። እንደዚሁም እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ ደግሞም አካል አለው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስም አንድ አካል ስለሆነ፥ አካል የምንላቸው ባሕርያት ሁሉ አሉት ማለት ነው። ከዚህ በመነሳት መንፈስ ቅዱስም አካል ነው ከሚለው መደምደሚያ እንደርሳለን። 

አዎን፥ አካላዊ ባሕርይ ስላለው በእውነት አካል ነው 

አካልን አካል የሚያሰኙት ዋና ዋና ነገሮች ምንድናቸው? ሦስት ነገሮች አሉ፡- አካል እውቀትና ስሜት እንዲሁም ፈቃድ ሊኖረው ይገባል። ግዑዝ ነገር ግን እነዚህ ባሕርያት አይኖሩትም። መንፈስ ቅዱስ ግዑዝ አይደለም፤ እውቀት፥ ስሜት፥ ፈቃድ አለው። 

(1) መንፈስ የእግዚአብሔርን ነገር ያውቃል፥ ይህ ጥበብ ነው (1ኛ ቆሮ. 2፡10-11)። በተጨማሪ “የመንፈስ አሳብ” የሚል ቃል እናነባለን (ሮሜ 8፡27)። 

(2.) መንፈስን ማሳዘን ይቻላል (ኤፌ. 4፡30)፤ ግዑዝ ነገርን ማሳዘን ግን የማይታሰብ ነው። 

(3.) “እንደፈቀደ” መንፈሳዊ ዕጦታዎችን የሚለግስ መንፈስ ቅዱስ ነው (1ኛ ቆሮ. 12፡11)። ይህን ቃል “እንደ እርሱ ዓላማ” ብሎ መተርጎም ይቻላል። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ አካላዊ ባሕርያት አሉት። 

አዎን፥ እንደ አካል መሥራት ይችላል 

ምንም እንኳን መንፈስ ቅዱስ በሰዎች የሚሠሩ አያሉ ተግባራት ቢፈጽምም፥ ሥራዎቹ ሰዎች የሚያከናውኗቸው ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ መንፈስ ያስተምራል፣ የአካባቢ ሁኔታዎችም ያስተምራሉ። ከልምምዶች ብንማርም፥ ልምምዶች አካል አላቸው ማለት አይደለም። አካልና እስትንፋስ ባላቸው ነገሮች ብቻ የሚከናወኑ ነገሮች እንደመኖራቸው መንፈስ ቅዱስም የሚያከናውናቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ ይጸልይልናል (ሮሜ 8፡26)፥ ነገሮችና ሁኔታዎች ግን ይህን አያደርጉም። ተአምራት ያደርጋል (ሐዋ. 8፡39)፥ ይህም ግዑዛን ነገሮች የሚችሉት ተግባር አይደለም። 

አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ አካል መሰየሙ እውነት ነው 

መንፈስ የሚለው ቃል በግሪክ “ኑማ” ነው። (ይህም ከነፋስ ጋር ግንኙነት ላላቸው ቃላት መሠረት ሆኖ፥ እንደ “ኑማቲክ” ወይም “ኒዩሞንያ” (የሳምባ ምች) ያሉትን ጉዳዮች ለመግለጥ ያገለግላል።) ይህ ቃል ግዑዝ ጾታ ነው። ቋሚ የሰዋስው ሕግ እንደሚያስተምረን ተውላጠ ስም በስም ምትክ የሚገባው የስምን ጾታ እንደያዘ ነው። “መንፈስ” የሚለው ቃል ተውላጠ ስም ሲተካ ግን ይህ ሕግ ሁሌ እውነት አይሆንም። ለምሳሌ በዮሐንስ 16፡13-14 ላይ “እርሱ” የሚለው ቃል በተባዕታይ ጾታ ነው የተመለከተው። እንዲሁም በኤፌሶን 1፡14 ላይ “እርሱም” ተብሎ በተባዕታይ ተውላጠ ስም ተገልጿል። እነዚህ ሁሉ ለተሳሳተ ሰዋሰዋዊ አጠቃቀም ምሳሌ ቢሆኑም፥ ለጥሩ ሥነ-መለኮት ትምህርት እጅግ ጠቃሚ ናቸው። ምክንያቱም መንፈስ ግዑዝ ነገር ሳይሆን፥ አካል መሆኑን በግልጥ ያሳያሉ። 

አዎን፥ መንፈስ ቅዱስ እንደ አካልነቱ ከሌሎች አካላት ጋር ግንኙነት አለውና 

ለምሳሌ እርስዎ የጥምቀትን ሥርዓት እንዴት በትክክል ሊገልጡት ይችላሉ? (“በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም” ማቴ. 28፡19)፥ ሲሉ ሁለቱን አካላት (አብንና ወልድን) እና አንድ ነገር (መንፈስ ቅዱስ) ማለትዎ ይሆን? ይሆን ካሉ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከጌታ ጋር ባለው ግንኙነት ሳቢያ ሁለቱም አካል መሆናቸው ተገልጧል (ዮሐ. 16፡14)። እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ አካልነት ከሰዎች ጋር ባደረገው ግንኙነት ተገልጧል(ሐዋ. 15፡28)። 

መንፈስ ቅዱስ አካል አይደለም የሚሉ ወገኖች አመለካከት 

የመንፈስ ቅዱስን አካልነት ወይም መለኮትነት የሚክዱት ሰዎች ብዙውን ጊዜ በአንደኛው የሞዳሊዝም ዓይነት ይመደባሉ። ይህ ስሕተት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። “ሰቤሊያኒዝም” [Sabellianism] የተባለ ሌላ እምነት ደግሞ (215 ዓ.ም.) “እግዚአብሔር በሦስት የተለያዩ መልኮች ራሱን ቢገልጥም አንድ አምላክ ነው” የሚል ትምህርት ነበር የሚያስተምረው። ይህ የእምነት ክፍል እግዚአብሔር ራሱ ሦስት ሚና ይጫወታል በሚል ስሕተት የተነሳ የመንፈስን የተለየ አካልነት ይክዳል። እንደዚሁም ሶሲኒየስ (1539-1604 ዓ.ም.) መንፈስን “ከእግዚአብሔር ወደ ሰው የፈሰሰ ጸጋ ወይም ኃይል ነው” ብሎ ተርጉሟል። ብዙ ለዘብተኞች ከዚህ አሳብ ጋር ይስማማሉ፤ በነሱ አመለካከት መንፈስ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ቢጠቀስም አካል ሳይሆን ኃይል ወይም ተጽዕኖ ብቻ ነው። የባርቲያኒዝም” [Barthianism] ተከታዮች የሞዳሊዝምን አመለካከት በመጋራታቸው ብዙ ጊዜ ይወቀሳሉ፤ ምንም ቢሆን ስለ ሥላሴዎች ያላቸው ግንዛቤ ተመሳሳይ ነው።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.