መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ነውን?

በዚህ መጽሐፍ መግቢያ እንደተጠቀሰው ማንኛውም ሰው ለሚያስበውና ለሚያደርገው ሁሉ የሥልጣን መሠረት አለው። ለክርስቲያን የሥልጣን መሠረቱ ልዩ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እስቲ ይህን መብታችንን ረጋ ብለን እንመርምረው። 

“ባይበል” [Bible] (መጽሐፍ ቅዱስ) የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ጥቅልል” ወይም “መጽሐፍ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተገኘ ነው። እርግጥም “የፓፒረስ ጥቅል” [Papyrus] ነው (ሉቃስ 4፡17፤ ዳን. 9፡2)። በአዲስ ኪዳን “ቅዱሳት መጻሕፍት” የሚለውን ቃል በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትና (2ኛ ጢሞ 3፡16 እና ሮማ 3፡2) ሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎችን (2ኛ ጴጥ. 3፡16) ለማመልከት እንጠቀምበታለን። “የእግዚአብሔር ቃል” የሚለው ንኡስ ሐረግ ደግሞ የአዲስና የብሉይ ኪዳን ጽሑፎችን ይገልጣል (ማቴ. 15፡6፥ ዮሐ. 10፡35፥ ዕብ. 4፡12)። እነዚህ ቃላት ከሁሉ ወደሚበልጥ መጽሐፍ የሚመሩና የእግዚአብሔርን ልዩ መገለጥ ለሰው የሚያስገነዝቡ ናቸው። 

በብዙ መመዘኛዎች ሲታይ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ነው። ከ1500 ዓመታት በላይ በፈጀ ጊዜ ከ40 በሚበልጡ ልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተጻፈ ይሁን እንጂ፥ አንድ ወጥ የሆነና በውስጡ ያለው አሳብ የማይቃረን ነው። ስለሚታወቀውና ስለማይታወቀው፥ ስለ ደስታና ሃዘን፥ ስለ ሰው ልጅ አነሳስና ውድቀት፥ ስለአለፈውና ስለመጪው ጊዜ፤ ያለ አንዳች ማመንታት በቁርጥ ይናገራል። እንደዚህ በስፋትና በትክክል የሚናገር ሌላ መጽሐፍ የለም። 

የመገለጥ ትርጉምና መንገዶች 

መገለጥ ማለት “ሽፋንን ማስወገድ ወይም ገሀድ ማድረግ” ማለት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማዛመድ የተሰጠውን ትርጉም ስናይ ደግሞ፥ ሰው ጨርሶ ሊያውቀው የማይችለውን ነገር እግዚአብሔር ራሱ ያሳወቀ መሆኑን ያመለክታል። ይሁን እንጂ ይህ በቂ መግለጫ አይሆንም። ምክንያቱም ሰዎች በቦታው በመገኘት የዓይን ምስክር ለመሆን የበቁባቸው ብዙ ድርጊቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው ስለምናገኝ ነው። መለኮታዊ መገለጥ ባይጨመርበት ኖሮ ግን ልናውቃቸው የማንችላቸው አያሌ ነገሮች እንደተሰወሩ በቀሩ ነበር። በ1ኛ ቆሮንቶስ 2፡10 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ የተገለጠ ሥራ መሆኑ ተመልክቷል። ስለዚህ መገለጥ ስንል ተፈጥሯዊ ወይም መለኮታዊ በሆነ መንገድ ሊፈጸም የሚችል ሲሆን፥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ ክፍሎች ያስተምረናል (እግዚአብሔር ስለ ወደፊት ሁኔታዎች ለነቢያቱ ገለጠላቸው እንደሚለው ዓይነት፥ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ሙሉ በሙሉ በመጥቀስ ከየምዕራፉ ተስማሚ ስለሆነው ትርጉም መግለጥ ሲሆን ይችላል። 

የመገለጥ መንገዶች አጠቃላይና ልዩ በሚል ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ተመድበዋል። አጠቃላይ መገለጥ ከክርስቶስና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑትን መንገዶች ያካትታል። ለምሳሌ እግዚአብሔርን በፍጥረታቱ መገለጥ (ሮሜ 1፡18-21)፥ ለሰው ልጆች ባደረገው ልዩ ስጦታ (ሮሜ 8፡28)፥ ዓለማትን በማጽናት (ቁላ. 1፡17)፥ እንዲሁም የሰውን ሞራላዊ ተፈጥሮ በመገንባት (ዘፍጥ. 1፡26፤ ሐዋ. 17፡29) የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ልዩ መገለጥ ደግሞ በከርስቶስና (ዮሐ. 1፡18) እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል የተገለጠው (1ኛ ዮሐ. 5፡9-12) ነው። አጠቃላይ መገለጥ፥ ሰው በአንድ በኩል እግዚአብሔር እንደሚያስፈልገው እንዲያውቅ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የተለገሰውን ጸጋ ካልተቀበለ ለፍርድ እንደሚዳረግ ያስጠነቅቀዋል። ለመዳን ያለው ብቸኛ መንገድ ግን በክርስቶስ ማመን ይሆናል (ሐዋ. 4፡12)። ይህ ማብራሪያ አጥጋቢ ካልመሰለዎ እስቲ በሚከተለው መንገድ ለማየት ይሞክሩ። ለምሳሌ የትምህርት ቤቱን ዕዳ ለመክፈል 400 ብር የሚያስፈልገው ተማሪ ያውቃሉ እንበል። ተማሪው ዕዳውን እንዲያቃልል 3 ብር ይሰጡታል (ይህን ብቻ ነው ሊሰጡት የሚችሉት)። እርሱ ግን እያሾፈ “ይህ ትንሽ ገንዘብ የ400 ብር ዕዳዬን ለመክፈል ምን ያህል ይረዳኛል?” ብሉ ብሩን በንቀት ቢመልስልዎና እንደአጋጣሚ ደግሞ እርሰዎ በስጦታ ብዙ ብር ቢያገኙ፥ ለዚያ ተማሪ በሌላ ቀን ተጨማሪ 100 ብር ሊሰጡት ይነሳሱ ይሆን? አይመስለኝም! ለሰጡት 3 ብር አመስግኖት ቢሆን ኖሮ ግን ሌላ ተጨማሪ እርዳታ ሊያደርጉላት ይገፋፉ ነበር። ልክ እንደዚሁ የእግዚአብሔር አጠቃላይ መገለጥ ከተናቀ ፍርድን ሲያስከትል፥ ቢቀበሉት ግን ለመዳን አስፈላጊ የሆነውን የወንጌል የምስራች ያመጣል (ሐዋ. 10፡3-6)። 

“እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ማለት ምን ማለት ነው? 

መገለጥ እግዚአብሔር በተለይ ራሱን ለሰዎች ያሳወቀበትን ሁኔታ ሲያሳስብ፥ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር [Inspiration/ኢንስፕሬሽን] ግን የሚያመለክተው የተገለጡትን አሳቦች በጽሑፍ መዝግቦ ማስፈርን ነው። ይህም ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16 የአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ” ሲል የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ “በእግዚአብሔር የተተነፈሱ መጻሕፍት ሁሉ” ይላል። የአንድ ሰው ንግግር በቀጥታ ከእስትንፋስ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ለሰው ዘር መገለጥም ከእስትንፋሱ ጋር የተዛመደ ነው። ጥቅሱ መጽሐፍ ቅዱስ በምን መልኩ እንደተዘጋጀ ግልጥ ባያደርገውም በእግዚአብሔር መንፈስ ቀስቃሽነት የተጻፈ መሆኑን ግን ያስረዳል። 

“እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” የሚለው ቃል ፍቺ 

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ተዘጋጀ ለሚለው አሳብ በበኩሌ የምሰጠው ማብራሪያ፥ እግዚአብሔር ፍጡሩ የሆኑትን ሰዎች (ጸሐፊዎች) ማንነታቸውን ሳይሽር፥ በበላይነት ብቻ እየተቆጣጠረ ያለ አንዳች ስሕተት በመጀመሪያ ቋንቋቸው እንዲጽፉት አድርጓል የሚል ነው። ይህ አባባል አጥብቀን ልናተኩርባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉት። (1) እግዚአብሔር ሰዎቹን ቃል በቃል ባያጽፋቸውም፥ በበላይነት ተቆጣጥሯቸዋል፤ (2) ጸሐፊዎቹ ያለ ተጽዕኖ የየራሳቸውን የአጻጻፍ ስልት ተጠቅመዋል፤ (3) ያም ሆኖ የእጅ ጽሑፎቻቸው ስሕተት አልነበረባቸውም። 

ስለ እስትንፋሰ-እግዚአብሔር ያሉ እመለካከቶች 

ከላይ በተጠቀሰው ትርጉምና መልእክት፥ ሰዎች ሁሉ ይስማማሉ ማለት አይደለም። 

(1.) አንዳንዶች መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች በጣም ብልሆች እንደነበሩ ያምኑና፥ ቢሆንም በታሪክ እንደታዩት ሌሎች አሰተዋይ ሰዎች በግላቸው ተነሳስተው ጻፉት እንጂ፣ በመንፈስ አልተገፋፉም ይላሉ። ይህ አመለካከት ሰዎቹ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ እንደነበራቸው ይደግፍ እንጂ፥ ከተፈጥሮ ውጭ በሌላ ኃይል እንዳልተመሩ ያመለክታል። 

(2.) ከዚህ አስተሳሰብ አንድ ደረጃ ከፍ ያለው ሌላ አመለካከት ደግሞ፥ ምስጢራዊ ወይም ተመስጦአዊ ቅስቀሳ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፥ የዚህ እመለካከት አቀንቃኛች፥ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉ ሁሉ እንደማናቸውም የዘመናቸን አማኞች በመንፈስ የተሞሉና የተመሩ ናቸው የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። እንዲህ ከሆነ ዛሬ ማንኛውም በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን ሊጽፍ ይችላል ማለት ነው። ልክ ይህን የሚመስል ሌላ አሳብ ደግሞ፥ መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ከሌሎች ላቅ ባለ ሁኔታ መንፈስ ቅዱስ የመራቸው ሰዎች ናቸው ይላል። 

(3.) ሌላው የተለመደ ገላጣ ደግሞ፥ ጸሐፊዎች ምንም ድርሻ ሳይኖራቸው ሊጻፍ የተገባውን ሁሉ እግዚአብሔር ቃል በቃል እየነገረ አጽፏል የሚል ነው። እርግጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንዳንዶች እግዚአብሔር ቃል በቃል ያጻፋቸው መሆኑ የሚያጠራጥር እይደለም እንደ አሥርቱ ትእዛዛትና ሌሎችም ሕጐች)፡፡ ይሁንና ጸሐፊዎቹ በተለያየ ደረጃ የራሳቸውን የአጻጻፍ ስልት እንዲጠቀሙ እግዚአብሐር ነጻነት ሰጥቷቸዋል በሚል መንፈስ መረዳት ይኖርብናል። 

(4.) ክፊል እስትንፋሱ-እግዚአብሔር አለበት የሚሉ ወገኖች አመለካከት ደግሞ አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማለትም ሰው ሊያውቃቸው የማይችል (እንደ ፍጥረት ታሪክ፥ የነቢያት መጻሕፍት፥ ወዘተ.) ያሉት ብቻ በመለኮታዊ እስትንፋስ ተጽፈዋል ይላል። 

(5.) ብዙ ደጋፊዎች ያሉት ሌላ አስተሳሰብ ደግሞ የመጻሕፍቱ ፅንሰ አሳብ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት ይገኝ እንጂ ቃላቱ የእግዚአብሔር አይደሉም ይላል። ይህ አባል ቃላቶቹ ትክክል ባይሆንም ምንም አይደለም የሚል መብት የሚሰጥ ይመስላል። 

(6.) “የኒዮ-ኦርቶዶክስ” ወይም “የባርቲያን” ተከታዮች በዮሐንስ 1፡1 እንደተጠቀሰው መጽሐፍ ቅዱስ “ለእግዚአብሔር ቃል (በግሪክኛ “ሎጎስ) ምስከር ነው በማለት ያስተምራሉ። እንዲሁም የባርት ተከታይ የሆነ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እራሱ “የእግዚአብሔር ቃል” ነው ይል ይሆናል። ሆኖም ይህ እውነት የሚሆነው በሁለተኛ ደረጃ ሲሆን ምክንያቱም ክርስቶስ ዋተኛው “ቃል” በመሆኑ ነው። ክርቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ ብቃት በሌላቸው ጸሐፊዎች የተጻፈና በስሕተት የተሞላ በመሆኑ “የቃሉን” የተሟላና ትክክለኛ መግለጫ ሊሰጥ አይችልም ብለው ያምናሉ። በርቲያኖች የተቀበሉት ለዘብተኛ አመለካከት በስሕተት የተሞላ ቢሆንም፥ ስለ ክርስቶስ ለማስተማር እንደ መሣሪያ ይጠቀሙበታል። 

(7.) በአብዛኛዎቹ እምነት አጥቂዎች ዘንድ ዛሬ ያለው አመለካከት፥ “የመጽሐፍ ቅዱስ የማነሳሳት ዓላማ” ተብሎ ሊለይ ይችላል። ማለትም፥ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ሊታረቁ የማይችሉ እውነቶችን ቢይዝም “በትምህርቱ ሙሉነት” ግን የእግዚአብሔርን ዓላማ ያሟላል ይላሉ። ይህን አሳብ የሚደግፉ ወገኖች አመለካከታቸውን ሲያጠናክሩ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተትና ግድፈት አልባ ነው የሚለውን አባባል የሚጠቀሙት ለታሪካዊ እውነታው ወይም ለይዘቱ ሳይሆን፥ ለዓላማውና ለአጠቃላይ ትምህርቱ ግብ ነው። አንድ ጸሐፊ በቅርቡ “እኔ መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተትና ግድፈት የለውም የምለው፥ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ አማካይነት ለሰዎች ያለውን የማዳን ዓላማ ስለሚያከናውን ነው” ብሏል። ይህ ማለት የእግዚአብሔር መገለጥ የሆነው ደኅንነት ስሕተት በሌለው መንገድ ይተላለፍ እንጂ፥ ጸሐፊዎቹ ግን ስሕተት ሊኖራቸው ይችላል ማለት ነው። ይህን አቋም ከባርቲያኖች አስተሳሰብ ጋር ስናነጻጽረው፥ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች፥ ስለተጻፈበት ጊዜ በአጠቃላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተዓማኒነት ጥብቅ አቋም አላቸው። ነገር ግን በታሪክ አቅጣጫ ስሕተት አለው ካሉ፥ በትምህርቱስ አቅጣጫ ስሕተት እንደሌለው ማን በእርግጠኝነት መናገር ይችላል? ደግሞስ ትምህርቱንና ታሪክን የሚለይ ማን ነው? በክርስቶስ ኢየሱስ ሕይወት የተከናወኑትን ታላላቅ ድርጊቶች ስናስታውስ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በታሪክ ትክክል መሆናቸውን እናምናለን ። 

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነት 

ጊዜ ተለዋዋጭ መሆኑን ለማስረዳት ያህል ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሰው እምነቱን ለመግለጥ መጽሐፍ ቅዱስን “የእግዚአብሔር ቃል” እንደሆነ ማመኑ ብቻ በቂ ነበር። ከዚያም “በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ቃል” ማለት አስፈላጊ ሆነ። ቀጠለና ደግሞ “ቃል በቃል፥ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ቃል” ብሎ መጨመር አስፈለገ። ከዚያም ይህንኑ ለማለት “ሙሉ በሙሉ፥ ቃል በቃል በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ቃል” ተባለ። ቀጠለናም “ሙሉ በሙሉ፥ ስሕተት አልባ የሆነ፥ ቃል በቃል፥ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ቃል” ማለት አስፈላጊ ሆነ። ዛሬ ደግሞ “ሙሉ በሙሉ፥ ቃል በቃል፥ በመጀመሪያውም ጽሑፍ ስሕተት የሌለበት፥ በእግዚአብሔር እስትንፋስ የተጻፈ ቃል” ለመባል በቃ። ይህም ሁሉ ሆኖ ሰዎች የተፈለገውን አሳብ በግልጥ ማስተላለፍ አልቻሉም! 

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ ምን ይላል? 

(1.) ያቀፋቸው መጻሕፍት በሙሉ የእግዚአብሔር መንፈስ አለባቸው ይላል (2ኛ ጢሞ. 3፡16)፣ ይህም ማለት እውነተኛው አምላክ (ሮሜ 3፡4) እውነትን ተንፍሶባቸዋል ማለት ነው። 

(2.) ታዲያ ሰው ይሆን መጽሐፉን በሚጽፍበት ጊዜ እውነትን ለማጉደፍ የሞከረው? አይደለም! መጽሐፍ ቅዱስ ሲመሰክር የጻፉት ሰዎች “በመንፈስ ተነድተው ጻፉት” ይላል (2ኛ ጴጥ. 1፡21)። ስለዚህ ከእያንዳንዱ ሰብአዊ ጸሐፊ ጋር መንፈስ ቅዱስ አብር ይሠራ ነበር። በተለያዩ ሰዎች የተጻፉ የብሉይ ኪዳን ጽሑፎች በአዲስ ኪዳን ተጠቅሰው የምናገኝ ሲሆን፥ የሁሉም ጸሀፊ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ተነግሯል። እንግዲህ ሁለት ጸሃፊዎች እንዳሉ እንረዳለን ማለት ነው። (ማር. 12፡36 እና ዳዊት በመዝሙር 10 ላይ ያሰፈረውን መንፈስ እንደጻፈው ይገልጣል። በሐዋርያት 1፡16 እና 4፡24-25 ላይ እንደተገለጠው በመዝሙር 41 እንዲሁም በመዝመር 2 ላይ የተጻፉት አሳቦች በመንፈስ ቅዱስ የተጻፉ ናቸው፤ በተጨማሪ ዕብራውያን 3፡7፣ 10፡15-16ን ይመልከቱ) 

(3) ነገር ግን ጽሑፍ አልፎ አልፎ የጸሐፊዎችን ዘይቤና እገላለጥ የሚያንፀባርቅ መሆኑ ይታያል። ይህ ሁኔታ ሁለት ጻሐፊዎች ከሚያዘጋጁት ጽሑፍ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ጸሐፊዎቹ የራሳቸውን ስልት ተጠቅመዋል ማለት ስሕተት ፈጽመዋል ማለት እይህንም (እንደ ምሳሌ ሮሜ 9፡1-3ን ይመልከቱ)። 

(4.) መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት እንደሌለበት ራሱም ይመሰክራል። ጌታችን ስለ አንዲት ነጥብ የገለጠውም ለዚህ አሳማኝ ማስረጃ ይሆነናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም” (ማቴ. 5፡18)። የውጣ የተባለው በዕብራይስጥ ዮድ የተሰኘው ፊደል ሲሆን፥ ከፊደሎች ሁሉ ትንሹ ነው። በሌላም በኩል ነጥብ ፊደልን ከፊደል ለመለየት የሚጠቅም ነው። በሌላ አባባል ጌታ የሚናገረው እያንዳንዱ ፈደል ወይም እያንዳንዱ ቃል ጠቃሚ መሆኑ በብሉይ ኪዳን የተገለጠው ሁሉ ፊደል በፊደል፥ ቃል በቃል ተፈጻሚ ይሆናል። 

በማቴዎስ 22፡32 ላይ ጌታ በቋንቋ ሕግ የአሁን ጊዜን ግስ ጥቅም አሳይቷል። የትንሣኤን እውነት ለማጠናከር እግዚእብሔር የሕያዋን አምላክ መሆኑን ለሰዱቃውያን ሲያስረዳ፥ ከብዙ ዓመታት በፊት የሞቱ ቢሆንም የአብርሃም፥ የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ እኔ ነኝ” በማለት ለሙሴ የተናገረውን ቃል በመድገም አስረድቷቸዋል። ትንሣኤ እውነት ባይሆን ኖሮ እምላካቸው “እኔ ነበርኩ” ባለ ነበር። እንዲሁም ስለ ራሱ አምላክነት ሲከራክር በመዝሙር 110፡1 ላይ የተጠቀሰውን መሠረት በማድረግ “ጌታ” የሚለውን ቃል ተጠቅሞበታል (ማቴ. 22:41-46)። መጽሐፉ ስሕተት እንደሌለው ባያምን ኖሮ ክርክሩ ትርጉም ባልናረውም ነበር። በሌላ ወቅት እግዚአብሔርን ትሳደባለህ ለተባለው ክስ መዝሙር 82፡6ን በመጥቀሰ አሳማኝ መልስ ሰጥቶበታል (ዮሐ. 10፡34)። መጽሐፍ ያለው ቃል ሁሉ እንደማይሻር ለከሳሾቹ በማስገንዘብ በዚሁ ጥቅስ ክርክሩን አጠናክሯል። ጳውሎስም በገላትያ 3፡16 ላይ ሲያስረዳ፣ በቋንቋ ሕግ የነጠላ ቁጥር ከብዙ ቁጥር ይልቅ ጥቅም እንዳለው በማነጻጸር ያሳያል። ስለሆነም በቋንቋ አጠቃቀም የነጠላና የብዙ ቁጥር ልዩነት ባይታምንበት ኖሮ፣ የጳውሎስ ክርክር ዋጋ አይኖረውም ነበር። ይህን ሁሉ ምሳሌ ስንመለከት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ ትክክለኛነት የሚመሰክረውን ለመቀበል እንገደዳለን። 

(5.) መጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት እንደሌለበት የሚያምን ሁሉ፣ በመጽሐፉ የተጠቀሱ የንግግር ምሳሌዎች እንዳሉ አይክድም (እንደ የምድር ዳርቻ” ራእይ 1፡1)፥ እነዚህ አባባሎች እስካሁን ትክክለኛ መልእክት በማስተላለፍ ጥቅም ላይ ውለዋል። 

(6.) ጸሃፊዎቹ ጽሑፋቸውን ከማቅረባቸው በፊት የተለያዩ ምርምሮችን ማድረጋቸው የሚካድ አይደለም (ሉቃስ 1፡1-4)። የዚያኑ ያህል ጽሑፉ ከስሕተት ነጻ የሆነው በመንፈስ ቅዱስ ተቆጣጣሪነት መሆኑን እናምናለን። 

(7) ደግሞም ዛሬ እንደምናየው በመጽሐፉ አንዳንድ ክፍሎች ውስጥ ችግር አልነበረም ብለን ሙሉ በሙሉ አንክድም። ነገር ግን ችግርና ስሕተት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ መጻፉንና ከስሕተት ነጻ መሆኑን ራሱ ይመሰክራል። ሰው የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙትም፥ እምነቱን በሚሻረው የሰው አሳብ ላይ ከማድረግ ይልቅ፥ ተፈትኖ እውነትነቱ በተረጋገጠው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ቢያደርግ የጸና ዋስትና ይኖረዋል። ሰው የአንዳንድ ችግሮችን መንስዔ ለማወቅ እውቀቱ ውሱን ነው፤ ግምታዊ ግንዛቤውም ስሕተት ላይ እንደሚጥለው ተረጋግጧል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ የሚባሉት ችግሮች ግን የጊዜ ጉዳይ ሆኖ ዛሬ ምስጢር ቢሆኑብንም መፍትሔዎቻቸው ወደፊት እየተገለጠ እንደሚሄድ አያጠራጥርም። 

የትኞቹ ናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት? 

የ “ካኖን” [Canon] ትርጉም 

የትኞቹ መጻሕፍት ናቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መታቀፍ ያለባቸው? የሚለው ጥያቄ፥ የካኖን ጥያቄ ይባላል። ካኖን የሚለው ቃል የተገኘው ከግሪክ ሲሆን ትርጉሙም “መለኪያ” ወይም “መስፈሪያ” ማለት ነው። ቃሉን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስናዛምደው፣ በሥልጣንና በሀቀኝነታቸው መመዘኛውን ያለፉትን መጻሕፍት የሚያመለክት ይሆናል። ስለዚህም እነዚህ መጻሕፍት የሕይወታችን መለኪያ ወይም መመሪያ ናቸው ማለት ነው። የመጻሕፍቱ መሰብሰብ እንዴት ተከናወነ? 

የካኖን መመዘኛዎች 

ከሁሉ አስቀድሞ አንዳንድ መጻሕፍት ለመመዘኛ ከመቅረባቸው በፊት ገና ሲጻፉ ካኖናውያን እንደነበሩ ማስታወስ ጠቃሚ ነው። ይህ አባባል ፈተና ባይሰጣቸውም እጅግ ብልህ የሆኑ ተማሪዎች አሉ እንደማለት ነው። ፈተናው የሚያረጋግጠው ያለውን እውነት ነው። ልክ እንደዚሁ ሁሉ፥ እንድን መጽሐፍ ካኖናዊ የሚያደርገው ቤተ ክርስቲያን ወይም ጉባኤ አይደለም፤ መጽሐፉ ገና ሲጻፍ ሀቀኛ ወይም ሐሰተኛ መሆኑ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያናት ወይም ጉባኤዎች አንዳንድ መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ለመሆናቸው እውቅና በመስጠት እረጋግጠዋል። እነዚህ ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት ከጊዜ ብዛት ተጠርዘው ነው አሁን በምናየው መልክ መጽሐፍ ቅዱስ የሚል ስያሜ ለማግኘት የበቁት። 

ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍቱን የለካችባቸው መመዘኛዎች ምንድናቸው? 

(1.) በቅድሚያ የሚቀርበው ፈተና የጸሐፊውን ሥልጣን ማወቅ ነበር። ብሉይ ኪዳን ሥልጣኑ የሕግ ሰጪው፥ የነቢይ፥ ወይም በእስራኤል የነበረ መሪ እንደነበር ያመለክታል። በአዲስ ኪዳን ደግሞ መጽሐፉ ተቀባይነት ለማግኘት በሐዋርያ መጻፍ ወይም መደገፍ፥ ከዚህም አልፎ የሐዋርያው ፊርማ ወይም የውክልና ሥልጣን ማስረጃ እንዲኖረው ያስፈልግ ነበር። ለምሳሌ ጴጥሮስ፥ የማርቆስ፥ ጳውሎስም የሉቃስ ደጋፊዎች ነበሩ። 

(2.) መጻሕፍቱ ራሳቸው በይዘታቸው የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ነበረባቸው። ለሚያነበው ሰው ይዘቱ ከተራ መጽሐፍ የተለየ፥ የእግዚአብሔርን መገለጥ በመናገር ለማሳመን ብቃት ያለው መሆን ነበረበት። 

(3.) መጻሕፍትን በካኖናዊነት ለመመዝገብ የቤተ ክርስቲያንም ውሳኔ ጠቃሚ ነበር። የጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አባላት የእግዚአብሔር መንፈስ እለባቸው የሚሏቸውን መጻሕፍት ዝርዝር በተመለከተ በመካከላቸው አስገራሚ መስማማት ነበር። አንዳንድ ቤተ ክርስቲያናት ጥቂት መጻሕፍትን ለመቀበል ለጊዜው መጠራጠራቸው እርግጥ ነው። ብዙ ቤተ ክርስቲያናት የተጠራጠሯቸው መጻሕፍት ግን መቼም ተቀባይነት አላገኙም። 

የካኖን አመሠራረት 

የመጽሐፍ ቅዱስ ካኖን የተጀመረው እያንዳንዱ መጽሐፍ መጻፍ በተጀመረ ጊዜ ሲሆን፥ ያበቃውም የመጨረሻው መጽሐፍ ሲጠናቀቅ ነው ለማለት ይቻላል። ስለ ካኖን “አደረጃጀት” ስንናገር የመጻሕፍቱ ካኖናዊነት ታውቆ በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት ስላገኙበት ጊዜ መናገራችን ነው። ይህ ደግሞ ጊዜ ወስዷል። አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች፥ በካኖናዊነት የተመዘኑና ተቀባይነት ያገኙ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በ5ኛው መቶ ዓመተ ዓለም በእዝራ የተሰባሰቡና የተቀናበሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ። ጆሲፈስ [Josephus] በተባለ ጸሐፊ የተጠቀሱ ማስረጃዎች (95 ዓ.ም.) እንዲሁም መጽሐፈ ዕዝደረስ ካልዕ 14 (100 ዓ.ም.) እውቅና ያገኙት የብሉይ ኪዳን ካኖን መጻሕፍት የምናውቃቸው 39ኙ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ጃምኒያ [Jamnia] (70-100 ዓ.ም.) ይባል በነበረ ትምህርት ቤት የተካሄደው ውይይትም የካኖንን ውሳኔ ያረጋግጣል። ጌታችን፥ ከአቤል እስከ ዘካርያስ እግዚአብሔር ለእስራኤል የላካቸው ነቢያት ስለመግደላቸው አንስቶ (ሉቃስ 11፡51) የብሉይ ኪዳንን ካኖን ድንበር አመልክቷል። የአቤል ሞት በዘፍጥረት ሲሆን፥ የዘካርያስ ሞት ደግሞ በ2ኛ ዜና 24፡20-21 እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህ መጽሐፍ በዕብራውያን መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው ነበር (እንደ አማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሚልክያስ አልነበረም)። ስለዚህ ይህ የጌታ አነጋገር፥ “በደላችሁ ከዘፍጥረት እስከ ሚልኪያስ ባሉት መጻሕፍት ተጽፏል” እንደማለት ነው። ከዚህም ሌላ ምንም እንኳን ስለ ብዙ ሰማእታት የተመዘገበ ታሪክ ቢኖርባቸው፥ ጌታ በዚያን ጊዜ ከነበሩት አዋልድ መጻሕፍት አንዳቸውንም አልጨመረም። 

በአዲስ ኪዳን ያሉትን ሃያ ሰባቱንም መጻሕፍት ዝርዝር ያዘጋጀው በ397 ዓ.ም. በካርታጎ [Carthage] የተሰበሰበው የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ጕባኤ ነው። ከዚያ በፊት ግን አንዳንድ መጻሕፍት እንደ እግዚአብሔር ቃል ተቆጥረው ነበር (2ኛ ጴጥ. 3፡16፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡17)። ከሐዋርያት ዘመን በኋላም ብዙዎቹ ተቀባይነት አግኝተዋል (ዕብራውያን፥ ያዕቆብ፥ 2ኛ ጴጥሮስ፥ 2ኛ እና 3ኛ ዮሐንስና የይሁዳ መልእክቶች ለጥቂት ጊዜ አከራክረው ነበር)። የካኖናዊነት ምርጫ ጐዳይ እያንዳንዱ መጽሐፍ ተፈትኖ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የቀጠለ ነበር። 

አሥራ ሁለቱ አዋልድ መጻሕፍት ግን የተከበሩ ቢሆኑም፥ የእግዚአብሔር ቃል ተብለው እንደ ሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በአይሁዳውያንም ሆነ በጌታችን ተቀባይነት አላገኙም። “ሰፕቱዋጂንት” [Septuagint] (በ3ኛው መቶ ዓመተ ዓለም የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጓሜ የአዋልድን መጻሕፍት ከብሉይ ኪዳን ካኖናዊ መጻሕፍት ጋር ጨምሮአቸዋል። ጀሮም [Jerome] (340-420 ዓ.ም.) “የቨልይት” ን [Vulgate] መጽሐፍ (የመጽሐፍ ቅዱስ የላቲን ትርጉም) ሲተረጉም ካኖናዊ መጻሕፍትን ከአዋልድ ለይቷቸዋል። በዚህ ድርጊቱ አዋልድ [Apocrypha] መጻሕፍትን በሁለተኛ ደረጃ ነው የመደባቸው። የትሬንት Trent ጉባኤ (1548 ዓ..) በበኩሉ እነዚህ መጻሕፍት ካኖናዊ ናቸው ቢልም እንኳን በኋላ የተነሱት እምነት አዳሾች [Reformers] ይህን አሳብ አልተቀበሉትም። የእንግሊዝኛው መጽሐፍ ቅዱስ የከቨርዴል [Coverdale]፥ የጄኔቫና የኪንግ ጀምስ ትርጉሞች አዋልድ መጻሕፍትን ለይተዋቸዋል። አዋልድ መጻሕፍትን ለመጀመሪያ ሙሉ በሙሉ ያገለላቸው በ1640 አምስተርዳም የታተመው (የጀኔቫ መጽሐፍ ቅዱስ) ሲሆን፥ ይህን ተግባር የደገመው ደግሞ በአሜሪካ የታተመው የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ (አይትኬኝ መጽሐፍ ቅዱስ 1782 ዓ.ም.) ነው። 

የአሁኑስ ትርጉም ታማኝነት አለው? 

የመጀመሪያዎቹ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች ከሙሴ ጀምሮ (1450 ዓ.ዓ.) እስከ ሚልኪያስ (400 ዓ.ዓ.) የተጻፉት በብራና ወይም በመቃ ቅጠል (ፓፒረስ) ነበር። የሙት ባሕር ጥቅሎች የተባሉት እጅግ ድንቅ ቅጂዎች በ1947 ዓ.ም. እስከተገኙ ድረስ የነበረው ጥንታዊ ቅጂ ከ895 ዓ.ም. በኋላ የተጻፈው ብሉይ ኪዳን ነበር። ይህም የሆነው አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት ቅጂ ሲያረጅ ከልዩ አክብሮት የተነሳ የመቅበር ሃይማኖታዊ ልምድ ስለነበራቸው ነው። እርግጥ “ማሰሪትስ” [Masoretes] የተባሉት በ600-950 ዓ.ም. ብዙ የፊደል ሕጐችን በማውጣት ያዘጋጇቸው ቅጂዎች ስሕተት እንዳይኖርባቸው በጥብቅ ይጠነቀቁ በር። እያንዳንዱም ቅጂ በጥንቃቄ መገልበጡን ለማረጋገጥ በገጹ መካከል የሚገኙትን ፊደሎች ይቆጥሩ ነበር። ስለዚሁ አሠራር አንድ ሰው አድናቆቱን ሲገልጥ፥ “ሊቆጠር የሚቻለው ሁሉ ተቆጥሯል” ብሏል። ከሞት ባሕር ጥቅሎች በኋላ ከሁለተኛው እስከ እንደኛው መቶ ዓመተ ዓለም ድረስ በዕብራይስጥ ቋንቋ የተጻፉ ሌሎች ጽሑፎች ለማግኘት ተችሏል። ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከመጽሐፈ አስቴር በስተቀር ሁሉንም ለማግኘት ችለዋል። ይህ ግኝት እጅግ ጠቃሚ ነበር። ምክንያቱም ቀደም ሲል የነበረው የመሰሪትስ ቅጂ ትክክል መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። 

ሌሎች የዕብራይስጡን ቅጂ ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ትርጉሞች ደግሞ ሰፕቱዋጂንት የተባለው (የ3ኛው መቶ ዓ.ዓ. አጋማሽ ትርጉም፥ የአርማይክ “ታርገም” [Targum] (ስለ ብሉይ ኪዳን ጥቅሶች ማብራሪያ)፣ የጥንታውያን ክርስቲያን ጸሐፊዎች ጥቅሶች እና ከዕብራይስጥ በቀጥታ ወደ ላቲን በጀሮም የተተረጐመው መጽሐፍ ቅዱስ (በ400 ዓ.ም.) ናቸው። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው በአሁኑ ጊዜ ትክክለኛ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዳሉን ያረጋግጣሉ። 

አዲስ ኪዳን ከጥንታዊ ጽሑፎች ሁሉ በላይ የተፈተነ መሆኑን የሚያረጋግጡ ከ5,000 በላይ የሚሆኑ ጥንታዊ ቅጅዎች ዛሬም ይገኛሉ። ከሌሎቹ መጻሕፍት ጋር ሲነጻጸርም አስደናቂነቱን የሚያመላክቱን አያሌ ነጥቦች አሉ። ለዚህ ማስረጃነት የሚቀጥለውን ጥቅስ እንመልከት። 

“አዲስ ኪዳንን በጥንታዊ ቅጅዎች ብዛት ከሌሎች ተመሳሳይ ዕድሜ ካላቸው ሆኖም በቂ የታሪክ መረጃ ከሌላቸው መጻሕፍት ጋር ስናነጻጽር በምንመለከተው ሁኔታ መደነቅ አይበዛብንም። ቄሳር የተዋጋውን የጋሊክ ጦርነት በማስመልከት (በ58-50 ዓ.ዓ.) የተጻፉት የታሪክ መረጃዎች እምብዛም ከመሆናቸው ጋር ዘጠኝ ወይም እሥር ያህሉ ብቻ ናቸው በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ሁኔታ የሚኙት። ከዚህ በጣም ጥንታዊ ነው የሚባለው ከቄሳር ዘመን 900 ዓመታት በኋላ የተጻፈው ነው። በሮማዊው የታሪክ ጸሐፊ በሊቪ [Livy] (59 ዓ.ዓ.-17 ዓ.ም.) ስለ ሮም ከተጻፉት 142 የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ፥ ዛሬ የሚገኙት 35ቱ ብቻ ናቸው። ከነዚህም ቢሆን የታሪክን ቅደም ተከተል በከፊል በመመዝገብ የያዘው አንዱ ቅጂ ብቻ ሲሆን፥ ያም ከ400 ዓመታት በኋላ የተጻፈ ነው። በታሲተስ [Tacitus] (100 ዓ.ም.) ከተጻፉት 14 የታሪክ መጻሕፍት አራት ከግማሹ ብቻ፣ እንዲሁም ከአሥራ ስድስቱ የታሪክ መዘክሮቹ አሥሩ ሙሉ በሙሉ እና ሁለቱ ከፊል ይገኛሉ። እነዚህ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሁለት ታሪካዊ ሥራዎች በ9ኛውና በ11ኛው ክፍለ ዘመን ተቀድተው የተገኙ ናቸው። እንደዚሁም የቱሲዲዲስ [Thucydides] ታሪክ (460-400 ዓ.ዓ.) በ900 ዓ.ም. በተገኘ ቅጂ የተረጋገጠ ሲሆን የሄሮዶቶስ [Herodotus] ታሪክ ማስረጃም (480-425 ዓ.ዓ.) በተመሳሳይ ሁኔታ ዘግይቶ የተገኘ ነው። ይሁን እንጂ የትኛውም የታሪክ ተመራማሪ፥ ከመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች በ1300 ዓመታት ዘግይተው የተገኙትን እነዚህን ቅጂዎች ተመልክቶ የሁለቱን የታሪክ ሰዎች ሥራ ታማኝነት ሊጠራጠር አይችልም።

ዛሬ አያሌ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሲኖሩ ብዙዎቹ የጥንት ቅጂዎች ናቸው። እንደዚሁም በግምት 75 የሚሆኑና፥ ከአዲስ ኪዳን ሃያ ሰባት መጻሕፍት ውስጥ ሃያ አምስት ያህሉን የያዙ፥ ከጠቅላላው መጽሐፍም 40 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑ ጥንታዊ የፓፒረስ ቁርጥራጮች ተገኝተዋል። እነኝህ በ135 ዓ.ም. እና 8ኛው ምእተ ዓመት መካከል የተጻፉና በታሪክ መረጃነታቸው እጅግ ብርቅ የሆኑ ቅርሶች እንዲሁም ሌሎች ብዙ የብራና ጽሑፎች አሉ። በመቶ ከሚቆጠሩት የብራና ቅጅዎች መካክል ትልቁ “ኮዴክስ ሳይኒያትከስ” [Codex Sinaiticus] (4ኛው መቶ ዓመት)፥ “ኮዴክስ “ቫቲካነስ” [Codex Vaticanus] (4ኛው መቶ ዓመት) እና ኮዴክስ “አሌክሳንድሪነስ” [Codex Alexandrinus] (5ኛው መቶ ዓመት) ይገኙበታል። ከነዚህም በተጨማሪ 2,000 የሃይማኖት መጻሕፍት (ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን የያዙ)፥ በቤተ ክርስቲያን አባቶች የተዘጋጁ ከ86,000 በላይ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች፥ በ3ኛው ምእተ ዓመት በጥንታዊ ላቲን፣ በሶርያና ግብፅ ቋንቋዎች፥ እንዲሁም በአምስተኛው ምእተ ዓመት ጆሮም በላቲን የተረጎማቸው ሥራዎች አሉ። በእነዚህ ሁሉ መረጃዎች ላይ በየጊዜው የተካሄዱት የምሁራን ሥራዎች ሲታከሉባቸው፥ ዛሬ ያለንን አዲስ ኪዳን የሚታመን ያደርጉታል። 

መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግዕዝ ቋንቋ መተርጎም የተጀመረው በ4ኛው ምእተ ዓመት ሲሆን የተጠናቀቀውም በ7ኛው ምእተ ዓመት ነው። የዚህ ሥራ አብዛኛው ክፍል የተከናወነው፣ በስድስተኛው ምእተ ዓመት በተሰዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን አማካይነት ነው። የግዕዙ ትርጉም በሉሊየን [Lucian] የግሪክ-ሲሪያ ትርጉም (310 ዓ.ዓ.) ላይ የተመሠረተ ይመስላል። 

መጽሐፍ ቅዱስን በአማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጎመው አብርሃም (አባ ሮሜ) ሲሆን ይህም የሆነው በ19ኛው ምእተ ዓመት መጀመሪያ ላይ ነው። ለትርጉም ሥራውም ከጥንታዊ የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ ሰፕቱዋጀንት የተባለውን የዕብራይስጥ የመጀመሪያ ትርጉም እና የሶሪያን የአዲስ ኪዳን ትርጉም ተጠቅሟል። 

አዲስ ኪዳን በአማርኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ የወጣው በ1829 ዓ.ም. ላይ መሆኑ፥ ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስም በ1840 ዓ.ም. መታተሙ ይታወቃል። 

አዲስ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ በትግርኛ የተተረጎመው በ1890 ዓ.ም. ሲሆን፥ የታተመውም በ1902 ዓ.ም. ላይ ነው። በኦሮምኛ ተተርጉሞ የታተመው ደግም በ1893 ዓ.ም. ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት 

መጽሐፍ ቅዱስን በትክክለኛ ለመረdaት ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ፥ እነርሱም፡- 1ኛ. የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት illumination/ኢሉሚኔሽን ሥራ እና 2ኛ. የአንባቢው የትርጉም ሥራ ናቸው። 

አብርሆት 

የሚለው ቃል ለተለያዩ ትምህርቶች የሚጠቀስ ቢሆንም (ስለ ክርስቶስ መምጣት ለሰዎች እንደተሰጠው አጠቃላይ መረዳት ዓይነት ዮሐ. 1፡9)፥ በአጠቃላይ ግን በጽሑፍ የተገለጠውን እውነት በገሃድ የሚታየው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ይፋ እንደሚያደርገው ለማመልከት የምንጠቀምበት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስናዛምደው፥ “መለኮታዊ መገለጥ” ከመጽሐፉ ይዘት፥ “እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” መልእክቱ ከተጻፈበት ዘዴ፥ “አብርሆት” ደግሞ ከጽሑፉ ትርጉም ጋር መያያዛቸውን እንረዳለን። ያልዳነ (የጌታ ዳግም ያልተወለደ) ሰው የእግዚአብሔር እውነት የተሰወረበት ስለሆነ፥ የመንፈስን የአብርሆት አገልግሎት ሊለማመድ ወይም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሊማር አይችልም፤ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደ ሞኝነት ይቆጥረዋል (1ኛ ቆሮ. 2፡14)። 

በሌላ በኩል፥ ክርስቲያን የሚያነበው ሁሉ ይገለጥለት ዘንድ አብርሆት እንደሚያገኝ ተስፋ ተሰጥቶታል (ዮሐ. 16፡12-15፤ 1ኛ ቆሮ. 2፡9.3፡2)። 

እነዚህን ሁለት ጥቅሶች በመረዳት ሌሎች እውነቶች ላይ መድረስ ይቻላል። 

1. ከሁሉም በላይ መንፈስ እራሱ አስተማሪ መሆኑና፥ በአማኛች ሕይወት ውስጥ መገኘቱ የተልእኮውን ዓላማ ያሳካዋል፤ 

2. የትምህርቱ ይዘት “እውነትን ሁሉ” ያቅፋል። ትንቢትን (ወደፊት የሚሆነውን) መረዳትንም ይጨምራል፤ 

3. የአብርሆት ዓላማ ለክርስቶስ ክብር እንጂ፥ መንፈስ ቅዱስ ራሱን ለማክበር አይደለም፤ 

4. የአማኝ ሥጋዊነት ይህን የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ሊያግደው ብሉም ሊያስቀረው ይችላል(1ኛ ቆሮ. 3፡1-2)። 

ትርጉም 

አብርሆት እርግጠኛ ቢሆንም፥ ወዲያወኑ የምንረዳው ግን አይደለም። ከላይ እንደተገለጠው አማኝ የሆነ ሰው ይህን አገልግሎት ለመለማመድ ከጌታ ጋር ኅብረት ሊኖረው፥ ቃሉንም ሊያጠና ይገባል። እንዲሁም እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን በሰጣቸው መምህራን በመረዳት (ሮሜ 12፡7) ባለው ችሎታና በሚያጋጥመው ዕድል መጠቀም አለበት። 

መሠረታዊው የትርጉም መመሪያ ግልጥ በሆነ ቋንቋ ለመተርጎም ተጣጣር የሚል ነው። እዚህ ላይ ለቃል በቃል ትርጉም ቅድሚያ ያልተሰጠበት ምክንያት የአሳብ መዛባቶች እንዳይፈጠሩ በመስጋት ነው። ግልጥና ቀጥተኛ ትርጉም ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉትን ፍሬ አሳቦች ይይዛል፡- 

(1.) በግልጥ ለመተርጐም የሚሻ ሰው መጀመሪያ የእያንዳንዱን ቃል ፍቺ ከሰዋስዋዊ አገባቡና ከወቅቱ ታሪክ አኳያ መረዳት ይኖርበታል። 

(2.) ግልጥ ትርጉም ምሳሌአዊ አነጋገሮችን ይጠቀማል (አያስወግድም። በዘይቤአዊ አነጋገሮች ነው መልእክቱን በቀጥታ ሊያስተላልፍ የሚችለው። በሌላ አነጋገር ከእያንዳንዱ ዘይቤአዊ አነጋገር በስተጀርባ ቀላል የሆነ ትርጉም እንደሚኖር ተርጓሚው ሊረዳ ይገባል። 

(3.) ሁልጊዜ ሲያነቡ የጥቅሱን ወይም የአንቀጹን አገባብ በማጣጣም ይሁን። ምክንያቱም ከአውደ ምንባቡ በመነጠል ለጥቅሱ ሌላ ትርጉም ሰጥቶት ሊሆን ይችላል። ከሚያነቡት ክፍል ፊትና ኋላ ያለውን አንቀጽ ማንበብ ጥንቃቄ ብቻ ሳይሆን፥ ጥበብም ነው። መልእክቱንም በግልጥ እንዲገነዘቡ ይረዳዎታል። 

(4.) የምለኮታዊ መገለጥን እድገትና ሂደት ያስተውሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጊዜ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን ለመጻፍ 1600 ዓመታት ያህል የፈጀና በተለያዩ ጸሐፊዎች የተጻፈ መሆኑንም ያስታውሱ። ይህም ማለት እግዚአብሔር መልእክቱን ደረጃ በደረጃ ለሰው ሲገልጥ፥ በአንድ ዘመን የሰጠው መገለጥ በሌላ ዘመን ሊጨምርም ሊለውጥም እንደሚችል ከልብ ማጤን ያስፈልጋል። በብሉይ ኪዳን ያልተገለጠውን አዲስ ኪዳን በሰፊው አብራርቶ ይገልጠዋል። በአንዱ ዘመን ግዴታን ያዘለ ትእዛዝ በሌላ ዘመን ሊሻር ይችላል፡፡ (ለምሳሌ የአሳማ ሥጋ አለመብላት በአንድ ዘመን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ሕግ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ተሽሯል፥ 1ኛ ጢሞ. 4፡3)። ይህን የመሳሰሉ ነገሮችን ማጤን በጣም ጠቃሚ ነው፤ ያላዚያ መጽሐፍ ቅዱስ ሊታረቁ በማይችሉ ተቃራኒ አሳቦች የተሞላ ይመስላል (ማቴ. 10፡5-7ን ከ28፡18-20 ጋር ያነጻጽሩ)። 

(5.) መጽሐፍ ቅዱስ ክሱት በሆኑ ቋንቋዎች ጭምር እንደሚናገር ይረዱ። ይህ ማለት መጽሐፉ ነገሮችን እንደሚታዩ አድርጎ የሚገልጣቸው እንጂ በሳይንሳዊ ቋንቋ የሚጠቀም አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል ማለት ነው። ለምሳሌ ስለ ፀሐይ ሲነግረን፥ ፀሐይ ትወጣለች ወይም ትጠልቃለች (ይህም የዘልማድ አነጋገር ነው፥ አንዱንም አታደርግም? የሚለው አባባል ለዚህ ማስረጃ ሲሆን (ማቴ. 5፡45፤ ማር. 1፡32) ግልጥና የተለመደ አነጋገር ነው። 

(6.) ሲተረጉሙ የመጽሐፍ ቅዱስን ዋና ዋና ክፍሎች በጥንቃቄ ያስተውሉ። በጣም መሠረታዊ ልዩነት የሚገኘው በአዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል ነው። ደግሞም የተለያዩ የጽሑፍ ዓይነቶች አሉ። እነዚህም ታሪካዊ፥ ሥነ-ግጥም፥ ትንቢታዊ የመሳሰሉ ሲሆኑ፥ እነኚህን በትክክል ለመተርጎም ልዩነታቸው መታወቅ እለበት። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሲታስብ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ። ለምሳሌ ለአብርሃምም የተሰጠው ቃል ኪዳን (ዘፍጥ. 12፡1-3)፥ ከዳዊት ጋር የተገባው ቃል ኪዳን (2ኛ ሳሙ. 7)፥ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል የመሆኗ ምስጢርና (ኤፈ. 3፡6)፣ የሕግና የጸጋ ልዩነት የመሳሰሉትን በጥንቃቄ መረዳት ያሻል (ዮሐ. 1፡17፤ ሮሜ 6፡14)። 

እነዚህ ስለ ግልጥ ትርጉም የሚያስረዱ መሠረታዊ አሳቦች ናቸው። እግዚአብሔር የሚፈልገውም መንፈሱ ያለበትን መጽሐፍ ፍጥረታቱ ግልጥ በሆነ መንገድ በመተርጎም እንዲረዱት ነው።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: