ከርስትናን ልዩ የሚያደርገው የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሲሆን፥ ክርስቶስ ልዩ ነው የምንለው፥ ሰውም አምላክም በመሆኑ ነው። በሌላ አባባል ክርስቶስ መለኮታዊ ሰው ሲሆን፥ ይህ እስከዛሬ ያልታየ ለዘላለምም የማይታይ ልዩ ክስተት ነው። አምላክ የሆነ ሰው በታሪክ ስለሌለና ከልምድም ሆነ ከምርምር እርዳታ ስለማናገኝ አሳቡን ለማነጻጸርም ሆነ ለመረዳት ያስቸግራል። ያም ቢሆን እምነቱ ያለአንዳች ጥያቄ በግዳጅ የምንቀበለው አይደለም፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት በመረዳት ከድምዳሜ የምንደርስበት እንጂ። ብዙ መረጃዎች ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ከሚለው መደምደሚያ ላይ ሲደርሱ፥ ሌሎቹ ደግሞ እውነተኛ ሰው መሆኑን ይጠቁማሉ። እንዲሁም በሁሉም የወንጌል ገጾች ላይ ሥራውን ሲያከናውን የምናየው አንድ ሰው ብቻ ነው። ይህ በእንድ እካል የተገለጠ ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰውነት በሥነ-መለኮት ትምህርት “ሃይፖስታቲክ ዩኒዮን” [Hypostatic Union] (የሁለት ባሕርያት አንድነት ማለት ነው) ሲባል ይህም የኢየሱስ ክርስቶስን ልዩ መሆን ያመለክታል።
ቅድመ-ሕልውና
ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም ከመወለዱ በፊት ይኖር ነበርን? መልሱ አዎን ነው። ይህ መልስ በራሱ አምላክነቱን ባያረጋግጥም (ምናልባት ከመወለዱ በፊት እንደ መልአክ ኖሮስ እንደሆነ ሊባል ይችላል ክርስቶስ እግዚአብሔርንና አብን ለመግለጥ ስለመምጣቱ ያመለክት ዘንድ ቅድመ-ሕልውና ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል። ከመወለዱ በፊት እርግጥ ይኖር ነበርን? ለሚለው ጥያቄ በብሉይ ኪዳን ከተሰጡት ስሞች የማረጋገጫ መልስ እናገኛለን። ሚክያስ 5፡2፥ የወልድን ዘላለማዊነት ያስተምራል። ይህ ቃል በዕንባቆም 1፡12፥ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ለማስረዳት ከዘላለም ጀምሮ አልነበርህምን?” ካለው ጋር ይመሳሰላል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ወልድም ሆኗል (በተጨማሪ ኢሳ. 9፡6ን ይመልከቱ)። ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱም ቅድመ-ሕልውና እንደነበረው “ከአብርሃም በፊት እኔ ነኝ” (ዮሐ. 8፡58) በማለት ገልጧል። “እኔ አለሁ” የሚለው ቃል ከአብርሃም በፊት ኗሪ መሆኑን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን፥ “ያህዌ” የተሰኘውን የእግዚአብሔር የተቀደሰ ስም የሚጠቅስ፥ በዚህም አምላክነቱን የሚገልጥ ነው (ዘጸ. 3፡14-15)። በክርስቶስ ተከናወኑ የሚባሉትን ሥራዎች ስንመለከትም፥ ቅድመ-ሕልውና ባይኖረው ኖሮ ሊከናወኑ እንደማይችሉ እንረዳለን (ለምሳሌ፥ ስለ ፍጥረት ቆላ. 1፡16)። ቀጥሎ የምንመለከተው ትምህርት አምላክነቱን የሚያሳየን ሲሆን ቅድመ ሕልውናውንም ያረጋግጥልናል።
አምላክነቱ
አያሌ የዘመናችን ሰዎች፥ የክርስቶስን አምላክነት ይክዳሉ። ይህን በማድረግም ክርስትናን የእምነት ምሶሶው ከሆነው መለኮታዊ አዳኝ ይለዩታል። ይህ ዓይነቱ ከህደት አዲስ አይደለም። በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያንም ነበር። “ኢቦናይት” [Ebionite]፥ “ሞናርኪያን” Monarchian እና የአርዮስ ተከታዮች ሁሉ የወልድን መለኮታዊነት ክደዋል። በተሀድሶያውያንም ጊዜ (በ16ኛው ክፍለ ዘመን ሱስንዮሳውያን [Socinians/ሶሲኒያንስ] የተባሉትም የነሱን አርአያነት በመከተል ኢየሱስን ሰው ብቻ ነው ብለውታል። በቅርቡም ሽለይርማከር [Schleiermacher]፣ ሪችል [Ritschl]፥ ዩኒተሪያኖች እና ለዘብተኞች ይህንኑ አሳብ አስተጋብተዋል። በዘመናችን ደግሞ የኢየሱስን አምላክነት የሚክዱ ሰዎች፥ አንድም እንደ ትልቅ ሰው (ሊያመልኩት ሳይሆን ሊከተሉት የሚገባ)፥ ወይም ጥሩ ሰው (ለዓላማው ጽኑነት የሞተ)፥ ወይም በጊዜው ከነበሩት ሰዎች ላቅ ያለ አስተሳሰብ የነበረው ብቻ አድርገው ይገምቱታል። ከዚህ አስተሳሰባቸው በመነሳት የክርስቶስን ተአምራታዊ ልደት፥ ሞትና ትንሣኤ ጭምር ይክዳሉ።
መለኮታዊነቱን ከሚክዱት ሰዎች አብዛኛዎቹ የናዝሬቱ ኢየሱስ አምላክ ነኝ አላለም፤ አምላከ ነው ያሉት ተከታዮቹ ናቸው፥ እነርሱም ቢሆኑ ተሳስተዋል ይላሉ። ይህ ከእውነት የራቀ አባባል ነው። እርሱ ራሱ አምላክነቱን እንዳረጋገጠ ቀጥሎ እንመለከታለን። በግልጽ እንደሚታወቀው የከርስቶስን አምላክነት የሚቃወሙ ክፍሎች መጽሐፍ ቅዱስን ካለመቀበላቸው የተነሳ፥ በውስጡ የተገለጠውን ታሪክ እውነተኛነት ለጥያቄ ያቀርቡታል። ምንም እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስ ስሕተት አልባ መሆኑን መካድ በአጠቃላይ የክርስቶስን አምላክነት መካድ ነው ባይባልም፥ የክርስቶስን አምላክነት መካድ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ አለማመን ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን አምላክነት የሚያረጋግጡ አያሌ ማስረጃዎች አሉትና።
(1.) ኢየሱስ ስለ ራሱ የተናገረው። የናዝሬቱ ኢየሱስ ከአብ ጋር እኩልነቱን ለማሳየት “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት ገልጧል (ዮሐ. 5፡18፥ 10፡30)። ይህን ሲል የሰሙት ራሱን ከአብ ጋር እንዳስተካከለ ተረድተው እግዚአብሐርን ሰድቧል ሲሉ ከሰሱት። እራሱን የገለጠው እንደ ልዩ ፍጡር አድርጎ ቢሆን ኖሮ በስድብ ክስ ባልወነጀሉትም ነበር፡፡ ከሊቀ ካህናቱ ፊት በቆመም ጊዜ ክርስቶስ ስለመሆኑ ለተጠየቀው ጥያቄ እውነት ነው በማለት አረጋግጧል (ማቴ. 26፡63-64)። በመሃላ ነበር የመለሰው።
በዮሐንስ 10፡36 እና በማቴዎስ 26፡63 “የእግዚአብሔር ልጅ” የሚል ሐረግ ተጠቅሷል። አንዳንዶች የኢየሱስን አምላክነት ላለመቀበል ሲሉ አባባሉ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር በታች እንደሆነ ነው የሚገልጠው ይላሉ፤ ተሳስተናል። ስሕተታቸውን ለማጋለጥ የሚከተለውን ጥቅስ እንመልከት።
“በአይሁዳውያን አጠቃቀም “የ…ልጅ” የሚለው ቃል ታናሽነትን ሳይሆን፣ እኩልነትንና የባሕርይ አንድነትን ነው የሚያሳየው፡፡ ስለዚህም በሐድሪያን Hadrian] ዘመነ ግዛት የአይሁድን ዓመጽ በ132-135 ዓ.ም የመራው ባር ኮክባ [Bar Kochba] “የኮከብ ልጅ” በሚል ስም ነበር የሚጠራው። ይህም የሆነው ራሱን በኍልቍ 24፡17 ላይ ከተወሰኑ ትንቢት ጋር ለማመሳሰል በማሰብ እንደሆነ ይገመታል፡፡“የመጽናናት ልጅ” የሚለው ሌላ ስም (ሐዋ. 4፡36) ያለጥርጥር “አጽናኝ” ማለት ነው። “የነጎድጓድ ልጆች” (ማር. 3፡17) ማለት “ነጎድጓዳዊ” ሰዎች ማለት ይሆናል። ለክርስቶስ የተሰጠውና በዳንኤል 7፡13 ላይ “የሰው ልጅ” የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥም በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡“ተወካዩ ሰው” ማለት ነው ትርጒሙ። ስለዚህ ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ልጅ” ሲል (ዮሐ. 10፡36)፣ በጊዜው የነበሩ ሰዎች እንደተረዱት ከእግዚአብሔር ጋር አንድነቱን ከአብ ጋር እኩልነቱን ማሳየቱ ነበር።”
ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆኑን ኢየሱስ ራሱ ካረጋገጠው በተጨማሪ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችም ደጋግመውታል (ዮሐ. 1፡1፤ 20፡28፤ ሮሜ 9፡5፤ ፊልጵ. 2፡6፤ ቲቶ 2፡13ን ይመልከቱ)።
(2.) ሥራዎቹ። የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር ብቻ ማድረግ የሚችለውን ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል በተጨማሪ ገልጧል። ጌታ ከጻፎች ወገን ቅራኔ ስለገጠመው፥ በአንድ በማይረሳ ወቅት አንድ ሽባ በመፈወስ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው አሳይቶ ነበር። ጻፎቹ ግን ኃጢአትን ይቅር ሊል የሚችል እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ስለሚያውቁ ይህን የጌታ አነጋገር እንደ ስድብ ቆጠሩት። የፈውሱ ተአምር የተከናወነው ክርስቶስ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ እንደሚችል ለማረጋገጥ ነው (ማር. 2፡1-12)።
ሌላ ጊዜ ደግሞ ፍርድ ሁሉ በእርሱ እጅ እንደሆነ (ዮሐ. 5፡27)፥ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክ (ዮሐ. 15፡26)፥ ሙታንን እንደሚያስነሳ (ዮሐ. 5፡25) ተናግሯል። እነዚህ ሁሉ የመለኮት ሥራዎች ስለሆኑ አምላክነቱን ያጸናሉ። ካልሆነ ግን ሐሰተኛ ያደርጉታል።
በአዲስ ኪዳን ሌሎች ከፍሎች ውስጥም ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል መሆኑን የሚያረጋግጡና፥ አምላክ ብቻ ሊሠራቸው የሚቻለውን ሥራዎች ሲሠራ ታይቷል። በፍጥረት ስለሠራው ሥራ ዮሐንስ 1፡3 እና ቆላ. 1፡16፥ ሁሉን በቃሉ ሥልጣን እንደሚደግፍ ቆላ. 1፡17 እና ዕብ. 1፡3 እንዲሁም በሰዎች ሁሉ ላይ ፈራጅ ስለመሆኑ የሐዋርያት ሥራ 17፡31ን ይመልከቱ።
(3) ባሕርያቱ። የናዝሬቱ ኢየሱስ አምላክ ብቻ ሊኖረው የሚገባ ባሕርይ ነበረው፡፡ ሁሉን አድራጊ መሆኑን ተናግሯል (ማቴ. 28፡18ን ከራእይ 1፡8 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ ሁሉን አዋቂ ከሆነ አካል ብቻ የሚገኝ እውቀት እንዳለውም አሳይቷል (ማር. 2፡8፤ ዮሐ. 1፡48)። በሁሉ ስፍራ እንደሚገኝም ቃል ኪዳን ገብቷል (ማቴ. 18፡20፤ 28፡20፤ ኤፌ. 1፡23)። እነዚህ ሁሉ ጉልህ ማስረጃዎች አምላክ መሆኑን ያረጋግጣሉ፥ ያለዚያ ታላቅ አታላይ ያደርጉታል።
(4.) የማዕረግ ስምቹ። ጌታ ራሱ የተናገረውን የሚያጠናክሩና አምላክነቱን የሚገልጡ ሌሎች ስሞች አሉት። በመላእክትና በሰዎች ተመልኳል (ማቴ. 14፡33፤ ፊልጵ. 2፡10፤ ዕብ. 1፡6)፤ ስሙ ከሥላሴ አባላት ጋር በእኩልነት ተጠቅሷል (ማቴ. 28፡19፣ 2ኛ ቆሮ. 13፡14)። የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ መሆኑን የባሕሪው አምሳያ (ዕብ. 1፡3) በማለት ገልጦታል። ይህ ቃል ጳውሎስ “በእርሱ አካል ውስጥ የመለኰት ሙላት ይኖራል” (ቆላ. 2፡9 ነጻ ትርጉም) ካለው ተጨማሪ ምስክርነት ጋር ተዳምሮ አምላክነቱን፥ እንደዚሁም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን እኩልነት በማጠናከር ይገልጠዋል። ደግሞም በአዲስ ኪዳን ያህዌህ ተብሎ የተጠራ ሲሆን፥ ይህም እውነት ሊሆን የቻለው ምሉእ የሆነ እግዚአብሔር በመሆኑ ብቻ ነው። ለዚህም ሉቃስ 1፡76ን ከሚልክያስ 3፡1 ጋር፤ እንዲሁም ሮሜ 10፡13ን ከኢዮኤል 2፡32 ጋር ያነጻጽሩ። በእነዚህ ላይ ሌሎች በአዲስ ኪዳን ስለ እርሱ የተሰጡት መለኮታዊ ስሞችን በመጨመር (አምላክ፥ ዕብ. 1፡8፤ ጌታ፥ ማቴ. 22፡43-45፤ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ፥ ራእይ 19፡16)፥ የክርስቶስን አምላከነት በግልጥ ያሳያሉ።
ከላይ ያቀረብናቸው አራት ማረጋገጫዎች የተገኙት ከሁለት አቅጣጫ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። ይህም ጌታ ስለ ራሱ ከተናገረው ቃል፥ እንዲሁም ከወንጌላት ውጭ በሌሎቹ የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ስለ እርሱ የተነገሩትን በመጥቀስ ነው። ሁለቱም እኩል እውነትነት አላቸው። አንዳንድ ሰዎች ግን ክርስቶስ የተናገረውን ቃል እንጂ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የጻፉትን መቀበል ያዳግታቸዋል። ከዚህ የምንገነዘበው የክርስቶስን አምላክነት ለሰዎች ስናስረዳ፣ በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች የተጠቀሱትን ማስረጃዎች ከማቅረባችን በፊት ክርስቶስ ስለ ራሱ የተናገረውን ማስቀደሙ የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው።
ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡