የመንፈስ ቅዱስ ሥራ፥ በክርስቲያኑ ሕይወት

ስጦታን ይለግሳል 

የመንፈሳዊ ስጦታዎች ምንጭ። መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ይሰጡናል(1ኛ ቆሮ. 12፡8-11)። 

የመንፈሳዊ ስጦታዎች ትርጉም። መንፈሳዊ ስጦታ፥ ለአገልግሎት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነው፡፡ በመጀመሪያ፥ ስጦታው ችሎታ መሆኑን ካወቅን፥ ዛሬ በሰዎች አእምሮ መንፈሳዊ ስጦታን በማስመልከት ካለው ግራ መጋባት እንድናለን። ብዙ ሰዎች፥ መንፈሳዊ ስጦታ ጥቂት የታደሉ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያገኙት ሹመት ነው ይላሉ። ይህ ትክክለኛ አባባል አይደለም። ለምሳሌ የመጋቢነትን ስጦታ ብንመለከት፥ መጋቢው ካለው ልምድና ሥልጣን ጋር የተያያዘ ይሆናል። በትከከለኛ ትርጉሙ ካየነው ስጦታ በየትኛውም ቦታ የእረኝነት አገልግሎት የመስጠት ችሎታ ነው። ስጦታ በጂኦግራፊ ክልል ወይም በድርጅታዊ መዋቅር የሚወሰን አይደለም። ለምሳሌ ማስተማር በየትኛውም ክፍለ ዓለም፥ በክፍል ውስጥና ውጭ ሊደረግ ይችላል። ማስተማር የእግዚአብሔርን እውነት የማስተላለፍ ችሎታ ነው። እንደዚሁም ስጦታ የተለየ መስፈርት ወይም የተለየ የዕድሜ ክልል አገልግሎትን የሚጠይቅ አይደለም። የወጣቶች ሥራ ወይም የጽሑፍ ችሎታ የሚባል ሰጦታ የለም። እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ስጦታን ጥቅም ላይ ለማዋያ ከትምህርት ወይም ከልምድ የተገኙ ሙያዎች ወይም ተልእኮን በሥራ መተርጐሚያዎች ሲሆኑ፥ ስጦታዎች ግን ከእግዚአብሔር የተለገሱ ችሎታዎች ናቸው። 

መንፈሳዊ ስጦታዎችን ማከፋፈል። መንፈሳዊ ስጦታዎች መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደ የሚለግሱ መሆናቸውን ከዚህ በፊት ተመልከተናል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ይብዛም ይነስ ስጦታዎች አሉት፥ ወይም ይኖሩታል (1ኛ ጴጥ. 4፡10)፤ ይህ ማለት ግን አንድ አማኝ ወይም ማኅበረ ምእመናን፥ ስጦታዎች ሁሉ አሉት ማለት አይደለም። 

የስጦታዎች ዝርዝር። የልዩ ስጦታዎች ዝርዝር በሮሜ 12፡6-8፥ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡8-10፥ 28-30 እና ከኤፈሶን 4፡11 ይገኛል። በዝርዝሩም ውስጥ ሐዋርያነት፥ ትንቢት፥ ተአምራት፥ ፈውስ ልሳን፥ ወንጌልን መስበክ፥ እረኝነት፥ መርዳት፥ ማስተማር፥ እምነት፥ ምክር፥ መናፍስትን መለየት፥ እውቀት፥ ምሕረት፥ ቸርነት፥ ማስተዳደር፥ ተጠቅሰዋል። ይህ ዝርዝር ሙሉ ነው ብንልም፥ ምናልባት የተሟላ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጠቀሰ ስጦታ ቢሆን እንኳን፥ በምንጩና በዓላማው የክርስቶስን አካል ለማነጽ የተሰጠ መሆን አለበት። ተፈጥሯዊ ችሎታን ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መለየት ይገባናል። እነዚህ ስጦታዎች፥ እንደ ሙዚቃ ሞያ መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለማከናወኛ ያገለግላሉ። 

መንፈሳዊ ስጦታን ማዳበር፡፡ መንፈስ ቅዱስ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ምንጭ ቢሆንም ስጦታውን በማዳበር ረገድ አማኙ ድርሻ አለው። “መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ ተመኙ” (1ኛ ቆሮ. 12፡3) የሚለው ጥቅስ የተባለውን ስጦታ ለማግኘት የመጣጣር ድርሻ እንዳለብን ያሳያል። ለምሳሌ የመርዳት ስጦታ ራስን በመግዛት ሊዳብር እንደሚችል ይታወቃል። 

የሌሎችን አገልግሎት በመጠቀምም ስጦታዎችን ማዳበር እንችላለን (ሮሜ 1፡11 ጳውሎስ ስጦታን እለግሳለሁ ሳይል፥ በአገልግሎቱ አማካይነት መንፈሳዊ ስጦታዎቹን ለሌሎች እንደሚያካፍል ይናገራል)። ስጦታ ያላቸው ሌሎችን ሲያገለግሉ፥ ሰዎች ይታነጻሉ፥ የታነጹትም በተራቸው ያገለግላሉ እነዚህም ሊያነጿቸው የሚችሉትን ያገለግላሉ፥ ወዘተ። ይህ የማያቋርጥ ኡደት ይሆናል። በዚህ መንገድ ነው የክርስቶስ አካል በብዛትም በዓይነትም ሊያድግ የሚችለው። 

ስጦታን መወቅ። እንድ ሰው ስጦታውን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? ይህን በተመለከተ ሦስት አሳቦች አሉ፡- አንደኛው፥ ያሉትን መንፈሳዊ ስጦታዎች ማወቅ ነው ለምሳሌ፥ ምሕረትን ማድረግ መንፈሳዊ ስጦታ መሆኑን የማያውቅ ሰው ይኖር ይሆናል። ይህ ግን ብዙዎች ሊጠቀሙበት የሚቻላቸው ስጦታ ነው። ስለዚህ በሕይወትዎ ያለውን ስጦታ ወደ ብርሃንና ወደ ጥቅም ሊያመጣው ይችላልና የእግዚአብሔርን ችሎታና እቅድ አይወስኑት። ሁለተኛ ማንኛውንም ነገር ለጌታ ለማድረግ ፈቃደኛ ይሁኑ። ብዙ ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን የዘወትር ሥራ ችላ ስለሚሉ ስጦታቸውን ሁሉ ለመጠቀም አይችሉም። ሦስተኛ፥ በአንድ ስጦታ መጠቀም ሌላውን ለማግኘት ይረዳልና ንቁ ይሁኑ! በአዲስ ኪዳን ፊልጶስን በመጀመሪያ ስናየው የመርዳት ስጦታ ነበረው (ሐዋ. 6፡5)፤ በዚህ ታማኝ ስለነበር እግዚአብሔር ወንጌልን የመስበክ ስጦታ ጨመረለት (ሐዋ. 8፡5)። ያለንን በታማኝነት ከተጠቀምንበት፥ ሰፈ ዕድልና አብሮት የሚሄድ ሰጦታ ይጨመርልናል። 

መንፈስ ቅዱስ ይሞላል 

ከየዕለቱ ጠቃሚ ክርስቲያናዊ ልምምዳችን በመነሳት፥ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ያለጥርጥር የዚህ ትምህርት ዋና ክፍል ነው እንላለን። ይህ ለእውነተኛ መንፈሳዊነት፥ ለእድገትና ብስለት መነሻ ነው። 

የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ምንድነው? የመንፈስ ሙላት ትክክለኛ ትርጉም በኤፈሶን 5፡18 “መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትሰክሩ ይህ ማባከን ነውና” በሚለው ጥቅስ ውስጥ ይገኛል። በስካርና በመንፈስ ቅዱስ ሙላት መካከል ያለው ንጽጽር መሠረታዊ ፍንጭ ይሰጣል። ይሄውም ቁጥጥር የሚለው ነው። ሰካራምና መንፈሳዊ ሰው ሁለቱም በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆኑ ይህም በመጠጥ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ናቸው ማለት ነው። ሁለቱም ከባሕርያቸው ውጭ የሆኑ ተግባራት ይፈጽማሉ። ጉዳዩን በሌላ አቅጣጫ ስንመለከተው ሁለቱም ራሳቸውን መቆጣጠር ባለመቻል ለመጠጥ ወይም ለመንፈስ ቅዱስ ተገዢ ሆነዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በመንፈሰ የተሞላ ሰው እንደ ሰካራሙ ግልፍተኛ ወይም ወፈፌ ሳይሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚገዛና የሚመራ ይሆናል። 

ደግሞም “ተሞሉ” የሚለው ቃል ትእዛዝ እንጂ የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ያስተውሉ። አማኞች ሁሉ ያለአንዳች ልዩነት መሞላት አለባቸው። በመንፈስ መሞላት ለጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለጤናማ የክርስቲያናዊ ሕይወት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ ነው። 

እንድ ሰው በምን ያህል ጊዜ ልዩነት ነው በመንፈስ መሞላት ያለበት? በኤፈሶን 5፡18 ላይ ያለውና “ተሞሉ” የሚለው ግስ ጥያቄውን ይመልስልናል። ግሱ የአሁን ጊዜ መሆኑ የሚያመለክተው መሞላት በተደጋጋሚ ሊለማመዱት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው። ስለዚህም “ሳታቋርጡ ተሞሉ” በማለት ቢተረጎም የሚሻል ይሆናል። በሌላ አነጋገር አንድ ክርስቲያን ይምላ፥ አሁንም ይሞላ፥ ደግሞም ይሞላ ይሆናል። ይህ ልምምድ በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ ወራት በሐዋርያት ዘንድ ታይቷል። በበዓለ እምሳ ዕለት ተሞልተው ነበር (ሐዋ. 2፡4)፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ እነዚሁ ሰዎች ሲጸልዩ አሁንም ተሞሉ (ሐዋ. 4፡31)። ሐዋርያት ለሁለተኛ ጊዜ የተሞሉት በሕይወታቸው ኃጢአት ስለተገኘ ሳይሆን፥ ያኔ ለገጠማቸው አዲስ ሁኔታ (ለመመስከር ድፍረት እንዲያገኙ) አዲስም ችግር ስለገጠማቸው (እንዳይናገሩ በሽማግሌዎች ስለተከለከሉ) መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። በአጭሩ በተደጋጋሚ መሞላት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በመንፈስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚገባቸው ያልታሰቡ የሕይወት ገጠመኞች ይኖራሉና። አንድ ክርስቲያን በሚሠራው ኃጢአት መጠን (ከራስ ወዳድነት የተነሳ) የመንፈስ መቆጣጠር እየከዳው እንዳይሄድ በተደጋጋሚ መሞላት የግድ ያስፈልገዋል። 

ለመምላት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ብዙ ክርስቲያኖች መሞላት በጸሎት ወይም በመናዘዝ ብዛት የሚገኝ ይመስላቸዋል። ነገር ግን አዲስ ኪዳን ውስጥ አማኞች ከበዓለ አምሳ ዕለት በኋላ ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት ጸልየዋል የሚል ምሳሌ አናገኝም። ለዚህ ትንሽ ቀረብ የሚለው ጳውሎስ ለኤፈሶን አማኞች መጸለዩ ሲሆን (ኤፌ. 1፡17) ይህም ቢሆን ለመሞላት የተደረገ ጸሎት አልነበረም። ምንም እንኳን ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት በጸሎት ጊዜ ማሳለፍ ወይም መቃተት አያሻም ብንልም መፈጸም ያለባቸው ሁኔታዎች ግን አሉ። 

በመንፈስ መሞላት በቁጥጥር ሥር መዋል ማለት ከሆነ፥ ራስን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠትንና ለእርሱ መገዛትን ይጠይቃል። ስለዚህ ቅድመ ሁኔታው ራስን ለመሥዋዕትነት ማዘጋጀት ነው። ይህም አንድ ሰው ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ለመስጠትና ለፈቃዱ ለመገዛት ፈቃደኛ መሆን አለበት። ይህ አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ከሚወሰድ ውሳኔ የተለየ ነው። ራስን መስጠት፥ ሕይወቱን የሚመራት ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ ፍጹም የሆነ መልስ ማግኘት ነው። 

ያም ሆኖ፣ ሁሌ ራስን ለእግዚአብሔር መስጠትና ፈቃዱን መፈጸምን ይጠይቃል። ጥያቄዎች ሲነሱም ትክክለኛውን ውሳኔ እንድናደርግ መንፈስ ቅዱስ ይመራናል (ሮሜ 8፡14)፤ ይህን የሚፈጽምልን ከእርሱ ጋር ካላን ቅርበት የተነሳ በመሆኑ ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን አያመነታም። ራሱን የሰጠ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ወይም አለመፈጸም የሚል ክርክር አይገጥምም። ከዚያ ይልቅ አደርገው ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምንድን ነው? በማለት ራሱን ይጠይቃል። 

ሁለተኛ፣ በመንፈስ መሞላት መንፈስን አለማሳዘንን ይጨምራል (ኤፈ. 4፡30)። መንፈስን የሚያሳዝነው ምንድነው? መልሱ ኃጢአት፥ በተለይ የአንደበት ኃጢአት ነው። በጥቅሱ ውስጥ ከአፋችሁ ከፉ ነገር አይውጣ ሲል ደጋግሞ ተናግሯል። 

ሦስተኛ፡- በመንፈስ የተሞላ ሕይወት፥ የመታመን ሕይወት ነው (ገላ. 5፡16)። ለምሳሌ መራመድን ብንመለከት የማያቋርጥ የመታመን ድርጊት ነው። አንድ እግራችንን አንስተን ከሌላኛው ፊት በማስቀደም ነው ጉዞ የምንጀምረው፤ ሌላው እግር ሙሉ ክብደታችንን እንደሚሸከምልን በመተማመን። እያንዳንዱም እግር ሌላው በሚንቀሳቀስበት ጊዜ በየተራ ድጋፍ ይሆናል። እግሮቻችንን እስካልተማመንባቸው ድረስ ባለንበት ቆመን እንቀራለን። ወደፊት መራመድ የሚቻለው በእምነት ብቻ ነው። የክርስትና ሕይወትም እንደዚሁ ነው። እድገት የሚኖረን በመንፈስ ቅዱስ ስንታመንና ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠረን ስንፈቅድለት ነው። 

በመንፈስ መሞላት በመንፈስ ቁጥጥር ሥር መሆን ማለት ሲሆን፥ ይህም ሕይወትን ለእርሱ ማስገዛት፥ ኃጢአትን ማስወገድና በእርሱ ኃይል ያለማቋረጥ መታመን ነው። ጸሎትና ቁርጥ ውሳኔ እነዚህን ሁኔታዎች ለማሟላት ያግዙ ይሆናል። ሁለቱ እንደተሟሉ የመንፈስ ቁጥጥር ወዲያው ስለሚተካ መሞላትን መለማመድ ይቻላል። 

የመሞላት ውጤቶች ምንድናቸው? በመንፈስ የተሞላ ሕይወት ቢያንስ አራት ውጤቶች፥ ወይም በመንፈስ የመሞላት ማስረጃዎች ይታዩበታል። የመጀመሪያው፡- ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ ሲሆን፥ ይሄውም ክርስቶስን መምሰል ነው (ይህ ጉዳይ ከመንፈስ ሙላት ጋር ተያይዞ በገላትያ 5 ላይ ይገኛል)። 

ሁለተኛው፡- አምልኮና ውዳሴ ሲሆን፥ ስለ ሙላት ዋና ከሆነው ጥቅስ በኋላ (ኤፌ. 5፡18) የመሞላት ውጤት የሆኑት ዝማሬና ምስጋና ይከተላሉ። 

ሦስተኛው፡- ታዛዥነት ነው (ኤፌ. 5፡21)። በመንፈስ ቁጥጥር ሥር መሆን ባልና ሚስት፥ በወላጅና በልጆች፥ በአሠሪና ሠራተኛ፣ መካከል ያለውን ግንኙነት ሁሉ ሰላማዊ ያደርገዋል። ይህን ጤናማ ግንኙነት የሚያናጋ ነገር ቢኖር በራስ መገዛት ነው። 

አራተኛው፡- የመሞላት ውጤት ለጌታ አገልግሎት መስጠት ነው። ምን ዓይነት አገልግሎት? አጠቃላይ መልሱ በመንፈስ ኃይል የመንፈስ ስጦታዎችን በመጠቀም የሚታይ አገልግሎት የሚል ይሆናል። በተለይ ግን በመንፈስ የመሞላት ውጤቱ ብዙዎችን ለደኅንነት ወደ ጌታ ማቅረብ ይሆናል። በሐዋርያት ሥራ እንዳየነው ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ሲሞሉ የተረጋገጠው ጉዳይም ይህ ነው (ሐዋ. 2፡4ን ከ2፡41 ጋር፤ 4፡8ንና 31ን ከ5፡14 ጋር፤ 6፡3ን ከ6፡7 እና 11፡24 ጋር እያነጻጸሩ ይመልከቱ)። 

ለመሆኑ በመንፈስ ተሞልቻለው ማለት ይቻላል? የጉባኤው መሪ በመንፈስ ተሞላን የምትሉ እስቲ እጃችሁን አንሱ የሚልበት ስብስባ ተካፍለው ከሆነ ምናልባት ብዙዎች እጃቸውን ለማንሳት ሲያመነቱ ተመልክተው ይሆናል፡፡ እንዳንዴ ተናጋሪው ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት ፈቃደኛ እንዲሆኑ፥ ከዚያም ተነስተው በመንፈስ ቅዱስ መምላታቸውን እንዲያሳውቁ ግፊት ያደርጋል። የትኛው ነው ትክክል? የብዙዎች ወደ ኋላ ማለት፥ ወይስ የአንዳንዶች ድፍረት? ሁለቱም እንደ ሁኔታው ልክ ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ በኩል አንድ ሰው ራሱን ለመንፈስ ቁጥጥር አሳልፎ ሲሰጥ፥ መንፈስ ይሞላዋል። በሌላ በኩል ማንም ሙሉ በሙሉ በመንፈስ ቁጥጥር ሥር ያልዋለ መሆኑንና ሁልጊዜም በሕይወቱ ውስጥ በመንፈስ ቁጥጥር ሥር ሊውሉ የሚገባቸው ተጨማሪ ነገሮች መኖራቸውን መገንዘቡ አንድን ሰው ጥርጣሬ ላይ ይጥለዋል። ስለዚህ እንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንደተሞላ ቢያውቅም፥ ነገ ደግሞ ተጨማሪ መሞላት እንደሚያሻው ይገነዘባል። 

መንፈስ ቅዱስ ያስተምራል 

ጌታ ከመሰቀሉ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጣቸው የመጨረሻ ተስፋዎች አንዱ፥ ያኔ ሊገነዘቧቸው የማይቻላቸውን ብዙ ነገሮች በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስተምራቸው የሚያረጋግጥ ነበር (ዮሐ. 16፡12-15)። ይህ “እውነትን ሁሉ” የሚያቅፍ የመንፈስ አገልግሉት ስለ ክርስቶስ መገለጥ ያስተምራል (እንደ ግሪኩ ጥቅስ ከሆን)። ጴጥሮስ በዓለ አምላ ዕለት የኢየሱስን ጌትነትና መሢህነት መረዳቱ፥ መንፈስ ቅዱስ ይህን እውነት እንዳስተማረው ያመለክታል (ሐዋ.2፡36)። በአሁኑ ጊዜ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለን መረጃ ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ፥ በቃሉ ውስጥ ያለውን ምስጢር መንፈስ ቅዱስ ለአማኙ ይገልጥለታል። ይህ ትንቢትንም (ወደፊት የሚሆነውን ነገር) የሚያጠቃልል ነው። 

እንዴት ነው መንፈስ አማኞችን የሚያስተምራቸው? ብዙውን ጊዜ የማስተማር ስጦታ ባላቸው አማኞች ይጠቀማል። ይህም በተለያዩ የማስተማር ዘዴዎች በመገልገል የሚከናወን ሊሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስ ሰውን ለማስተማር በቃል፥ ወይም በየትኛውም የቤተ ክርስቲያን ዘመን በተጻፈ ጽሑፍ ይጠቀማል። ዮሐንስ በ1ኛ ዮሐንስ 2፡27 የገለጠው የሰው አስተማሪነት አሰፈላጊ አለመሆኑን ሳይሆን፥ ያን ጊዜ በመካከላቸው ስለነበሩት ፀረ-ክርስቶሶች ቀደም ሲል ካስተማራቸው እውነት ሌላ ማንም እንደማይነግራቸውና መንፈስ ቅዱስ ብቻ እውነቱን በቀጥታ እንደሚያረጋግጥላቸው ነበር። 

መንፈስ ቅዱስ ይመራል 

በሮማ 8፡14 የተገለጠውና የመንፈስ ቅዱስ አንዱ ተግባር አማኞችን መምራት ሲሆን፥ ይህም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በሚገባ ተብራርቷል (ሐዋ. 8፡29፥ 10፡19-20፥ 13፡24፥ 16፡6-7፥ 20፡22-23)። መንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ በሆነ ሁኔታ በፍጹም አይመራም። ቃሉ ነው መሠረቱ። እግዚአብሔር እንዴት እንደሚመራን የሚነግረንም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ ሁኔታዎች ይጠቀም ወይም አይጠቀም ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ፥ መንፈስ ቅዱስ የምናደርገውን ይመራን ዘንድ ከጌታ ጋር በቅርብ በመሆን መጓዝ ማለት ነው። 

መንፈስ ቅዱስ መተማመኛ ይሰጣል 

መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያረጋግጥልናል (ሮሜ 8፡16)። ይህም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የእግዚአብሔር ወራሾች ያደርገናል። የክርስቲያን እምነት ማጠናከሪያ፥ ያለጥርጥር እግዚአብሔር አንድን ሰው ለማዳን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚፈጽማቸውን ነገሮች ከማስተዋል ነው። ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ማስተማመኛ ማስተማርንም ይጨምራል። ለምሳሌ በመንፈስ ስለመታተም እና መንፈስ የደኅንነታችን ፍጻሜ መያዣ እንደሆነ እየተረዳን ስንሄድ፣ እምነታችን የጸና ይሆናል። እንዲሁም ሕያው ከሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አካል ጋር አንድ መሆናችንን ያለጥርጥር እንረዳለን። 

ይጸልያል 

መንፈስ ቅዱስ በጸሎታችን ውስጥ በሁለት መንገድ ይሳተፋል። በመጀመሪያ ወደ እግዚአብሔር የምናቀርባቸው ልመናዎች እንደ ፈቃዱ መጠን ይሆኑ ዘንድ ይመራናል፥ ያሳየናል (ኤፌ. 6፡19)። ሁለተኛ “በማይነገር መቃተት” (ሮሜ 8፡26) ስለ እኛ ይጸልያል። ውጤቱ ግልጥ ባይሆንም፥ የጸሎቱ እውነተኛነት ግን የታመነ ነው። መንፈስ ይረዳናል ይላል ጥቅሱ፥ ይህም መንፈስ ቅዱስ በምናደርገው ጸሎት ከኛ ጋር ይለምናል ማለት ነው። መቃተት አለመናገርን ስለሚያመለክት ለመግለጥ ያስቸግራል። ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ጸሎት የሚቀርብበት አንዱ መንገድ ነው። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading