የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በብሉይ ኪዳን

የመፍጠር ድርሻው 

አንዳንድ ጊዜ በብሉይ ኪዳን፥ መንፈስ የሚለው ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ ይናገር፥ ወይም ስለ እግዚአብሔር እስትንፋስ ግልጥ አይደለም (መዝ. 33፡6ን ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ በመፍጠር ውስጥ ድርሻ እንደነበረው የሚያሳዩ ጥቅሶች አሉ። አምላከ በመሆኑም፥ ሁልጊዜ በዓለም አለና መፍጠርን ጨምር በማናቸውም የአምላክ ሥራ ውስጥ ይሳተፋል። 

የመንፈስ ሥራ የሚዛመደው በተለይ ለፍጥረት ሕይወት ከመስጠት፥ (መዝ. 104፡30 ኢዮብ 33፡4)፣ ሥርዓት ከማስያዝ (ኢሳ. 40፡12-13፤ ኢዮብ 26፡13)፥ የእግዚአብሔርን ክብር ከማወጅ (መዝ. 33፥61 ኢዮብ 26፡13) እና የማያቋርጥ እደሳና ጥበቃ ከማድረግ (ይህ በመዝሙር 104፡29-30 መሠረት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ቢዛመድም፥ ባመዛኙ ከክርስቶስ ጋር ይያያዛል) ጋር ነው። 

በመለኮታዊ መገለጥ ውስጥ ያለው ድርሻ 

በምዕራፍ 2 ከመለኮታዊ መገለጥ እና ከእስትንፋሰ-እግዚአብሔር ጋር ስለተዛመዱ ነገሮች ማብራሪያ ተሰጥቷል። አሁን ደግሞ በዚህ ሥራ መንፈስ ቅዱስ በተለይ ያለውን ድርሻ እንመለከታለን። 

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን መልእክቱን ለሰዎች ለማስተላለፍ የተጠቀመው በነቢያት ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ከነቢያቱ ጋር በመሆን እግዚአብሔር ያላቸውን ብቻ እንዲያስተላልፉ ይመራቸው ነበር። ጴጥሮስ የብሉይ ኪዳንን ጸሐፊዎች በተመለከተ ሲገልጥ “በመንፈስ ተነድተው ተናገሩ” ብሏል (2ኛ ጴጥ. 1፡21)። ይህ አጠቃላይ ገለጣ በብዙ ዝርዝር ምሳሌዎች የተደገፈ ነው (2ኛ ሳሙ. 23፡2፤ ሚክ. 3፡8)። አዲስ ኪዳን፥ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት አያሌ ጥቅሶች የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ውጤቶች እንደሆኑ ያስረዳል (ማቴ. 22፡43፤ ሐዋ. 1፡16፤ 4፡25)። ጌታም በአዲስ ኪዳን ለሐዋርያቱ የገለጣቸውን ትምህርቶች መንፈስ ቅዱስ እንደሚያብራራላቸው ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር (ዮሐ. 14፡26)። ስለዚህ መለኮታዊ መገለጥን በባለቤትነት የመራና የጠበቀ መንፈስ ቅዱስ ሲሆን፥ ሰው መሳሪያ ወይም ወኪል እንደነበረና ምንጩ ደግሞ እግዚአብሔር እንደነበር እንረዳለን። 

መንፈስ ቅዱስ ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት 

በምርጫው (ቋሚ ባልሆነ ሁኔታ) በሰዎች ውስጥ መኖሩ። መንፈስ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ዘመን በአንዳንድ ሰዎች ያድር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጣል። ስለዚህ በዚያ ዘመን በሰዎች ውስጥ የመኖሩ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም (ዘፍጥ. 41፡38፤ ዘኁል. 27፡18፤ ዳን. 4፡8፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡11)። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በሰዎች ላይ ይወርድ ነበር (መሳ. 3፡10፤ 1ኛ ሳሙ. 10፡9-10)። ታዲያ በመንፈስ ቅዱስ በሰው ውስጥ መሆንና ከላይ መውረድ መካከል ልዩነት አለን? ምናልባት “ከላይ መውረድ” ተመልሶ የመሄድንም ሁኔታ ያመለክት ይሆናል (መሳ. 15፡14ን ከመሳ. 16፡20 ጋር ያነጻጽሩ)። ጌታ ኢየሱስ፥ መንፈስ ቅዱስ ከብሉይ ኪዳን ሰዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ከበዓላ አምሳ በኋላ ከሚኖረው ጋር ባነጻጸረበት ወቅት፥ መንፈስ ቅዱስ ሁሌ ከአማኞች ጋር እንደሚኖር ተናግሯል (ዮሐ. 14:17)። ይህ ከበዓለ አምሳ በፊትና በኋላ የነበረውን ልዩነት በግልጥ ሲያመለክት፥ የብሉይ ኪዳኑም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሉት ተገቢ እንደነበር “መኖር” በሚለው ቃል ተረጋግጧል። መንፈስ ቅዱስ ዛሬ በአማኞች ሁሉ ውስጥ ይኖራል። ይህ ሁለንተናዊና ነባራዊ እውነት በብሉይ ኪዳን ጊዜ ዋስትና አልነበረውም። 

ለልዩ አልግሎት ማብቃቱ። በአንዳንድ ሥራዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰጥቷል። ለምሳሌ፥ ከመገናኛው ድንኳን ጋር ለተያያዘ ልዩ ሥራ (ዘጻ. 31፡3) እና ለሌሎችም ታላላቅ ሥራዎች (መሳ. 14፡6፤ 1ኛ ሳሙ. 16፡13)። 

ኃጢአት ማገዱ። ኃጢአትን ማገድ ከጥንት ጀምሮ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ ሥራ ሲሆን (ዘፍጥ. 6፡3) ሰዎች ስሙንና ኃያልነቱን ባሰቡ ቁጥር ከኃጢአት ተግባር ይታቀባሉ (ነህ. 9፡20፤ መዝ. 51፣ 11)።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading