የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ብዛት፥ ትርጉም እና ጥቅም በተመለከተ ብዙ ሲያከራክር ቆይቷል። በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሥርዓቶች ብቻ የነበሩ ሲሆን፥ እነሱም ጥምቀትና የጌታ እራት ናቸው። ከዚያ በኋላ ግን ሌሎች ሥርዓቶች ተጨምረዋል። ዛሬ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን “ሳክራምንት” [Sacrament] የሚባሉ ሰባት ሥርዓቶች አሏት። በ1545 ዓ.ም. የትሬንት ጉባኤ ሳክራመንት “በእግዚአብሔር የታቀደ፣ አንዳንድ መለኮታዊ እውነቶችን የሚያሳየን ብቻ ሳይሆን ጸጋንም የሚሰጠን” እንደሆነ ጠቅሷል። ይህን ትምህርት በአጠቃላይ የምሥራቃዊ ቤተ ክርስቲያናትም ጭምር ተከትለውታል። 

በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከተሃድሶ ጊዜ በኋላ አብዛኞቹ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያናት ሥርዓትን እንደሚከተለው ተርጉመውታል፡- “በክርስቶስ የታዘዘ፥ በቤተ ክርስቲያኑ በግልጥ የሚከናወን ሃይማኖታዊ ሥርዓት።” ይህ ጋብቻን ሊያጠፋ ይችላል፤ ምክንያቱም ጋብቻ ከክርስቶስ በፊት የተደነገገ በመሆኑ ነው። እንደ ፕሮቴስታንቶች አመለካከት፥ ሥርዓቶች፥ በሥርዓቱ የተካፈለ ሰው ጸጋን እንዲላበስ የሚያደርጉ ሳይሆኑ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ነገሮች የሚያስታውሱ ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ በማንኛውም ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው ሁለት ሥርዓቶች ላይ እንወያያለን።

የጌታ እራት። የተለያዩ ሰዎች ስለ ጌታ እራት የተለያየ ትርጉም አላቸው። የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች፥ ህብስቱና ወይኑ መልካቸውን ባይለውጡም፣ በትክክል የክርስቶስ አካልና ደም ይሆናሉ ብለው ያምናሉ። ይህ አመለካከት [“ትራንስብስታንሺዬሽን” /Transubstantiation] የሚባል ሲሆን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነም ነው። ምክንያቱም የክርስቶስ ደምና ሥጋ ይህ ሥርዓት በተፈጸመ ቁጥር መሥዋዕት ሆኖ በመቅረቡ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተቃራኒው የሚገልጠው የክርስቶስ ሞት ሙሉና በቂ፥ እንዲሁም ላንዴና ለሁልጊዜ የተፈጸመ መሆኑን ነው (ዕብ. 10፡101 9፡12)። ሉተራውያን ደግሞ ወይኑና ህብስቱ ለውጥ ባይኖራቸውም፥ ሰው ከቅዱስ ቁርባኑ በሚቋደስበት ጊዜ እውነተኛ የክርስቶስ ሥጋና ደም ይሆናሉ ይላሉ። ይህም “ካንሰብስታንቪዬሽን” [Consubstantiationa] ይባላል። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ ትክክል የሚመስል አመላካከት ያቀርባሉ፡- የጌታ እራት ሥርዓት የሚዘከረው ለመታሰቢያነት ብቻ ነው (1ኛ ቆር. 11፡24-25 “ለመታሰቢያዬ”) ህብስቱም ሆነ ወይኑ አይለወጡም፤ ክርስቶስ ግን በአገልግሉቱ ወቅት በመካከላችን ይገኛል፤ ያም ቢሆን ከህብስቱና ከወይኑ ውስጥ አይደለም ይላሉ። 

የጌታ እራት የተለያዩ ዓላማዎች አሉት፡-

1. የጌታችን ሕይወትና ሞት መታሰቢያ ነው። ህብስቱ ፍጹምና ቅዱስ ሕይወቱን ያመለክታል፤ ይህ ቅዱስ ሕይወት ለኃጢአት መሥዋዕትነት የበቃና ተቀባይነት ያለው ነው። ስለሆነም ህብስቱ ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ የተሸከመውን የክርስቶስ አካል ያመለክታል (1ኛ ጴጥ. 2፡24)። ወይኑም ለኃጢአታችን ስርየት የፈሰሰውን ደም ይወክላል። ያ አካል ዳግመኛ ሲሰቀል ለማየትም ሆነ ደሙ ሲፈስ ለመመስከር ስለማንችል፥ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ለመታሰቢያነት ሲባል ብቻ የሚደረግ መሆኑን ማወቅ አለብን። 

2. የጌታ እራት የወንጌልን እውነት የምናውጅበት ነው (1ኛ ቆሮ. 11፡26)። 

3. የጌታን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንድንጠባበቅ ያሳስበናል፡፡ ይህን ሥርዓት የምናከብረው እስከዚያ ዕለት (ጌታ እስኪመጣ ድረስ ብቻ ይሆናል (1ኛ ቆሮ. 12፡26)። 

4. እራቱ በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለንን አንድነትና በዚህ አካል ውስጥ ካሉት አባላት ጋር ያለንን ኅብረት ያስታውሰናል(1ኛ ቆሮ. 10፡17)። 

መቼ መቼ ነው የጌታ እራት መከበር ያለበት? አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየሦስት ወሩ ሲያደርጉ፥ በተለምዶ ሥርዓቱን ለመፈጸም ካሰቡበት እሁድ በፊት ዮዝግጅት አገልግሎቶችን ያከናውናሉ። አንዳንዶች በየወሩ ሲያደርጉ፥ በየእሁዱም መደረግ አለበት የሚሉ አሉ። እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የጌታን እራት መከበሪያ ጊዜ ለይቶ አይነግረንም። ከበዓለ አምሳ ሰኋላ የነበሩት የመጀመሪያ አማኞች በየቀኑ ያደርጉት የነበረ ይመስላል። ይህ ግን በየቀኑ በእያንዳንዱ ሰው ቤት ይከበር ነበር ማለት ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድ ማዕከል መፈጸሙን ለማመልከት ነው (ሐዋ. 2፡46)። በጢሮአዳ (ሐዋ. 20፡6) እሁድ ዕለት ተደርጎ ነበር። ታዲያ አንዳንዶች ከጥቅሱ በመነሳት በየእሁዱ ተደርጓል ቢሉም፥ በዚህ ሁኔታ ስለመዘከሩ በግልጥ የተጻፈ መረጃ አናገኝም። የቱንም ያህል ቢደጋገም፥ አንዳንድ ጊዜ በምሽት ቢከናወን ተመራጭ ሊሆን ይችላል። እራት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፥ ጠዋት ጠዋት መምጣት የማይችሉ ምእመናንም እንዲካፈሉ ለማድረግም ነው። ይህ ሥርዓት ቤተ ክርስቲያን ከምታደርጋቸው ሌሎች ሥርዓቶች ይበልጥ ጠቃሚ ስለሆነ ሰፊ ጊዜ የሚሰጠው እንጂ፥ በችኮላ የሚከናወን ጕዳይ አይደለም። 

ጥምቀት። የውኃ ጥምቀት ጉዳይ ሁለት ጥያቄዎች ያስነሳል። እነርሱም እንዴት ነው ጥምቀት መከናወን ያለበት? (አሠራሩ) እና በማን ላይ ነው መከናወን ያለበት? (አማኞች ብቻ ወይስ ሕፃናትም ጭምር) የሚሉ ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት ግን የጥምቀትን ትርጉምና ጥቅም መግለጥ አስፈላጊ ይሆናል። 

ማንኛውም የጥምቀት ትርጉም፥ ከክርስቲያን ጥምቀት ጋር ተያይዞ ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ይሁዲነት የሚለወጡ ሰዎች የሚወስዱትን ጥምቀት፥ የመንፈስ ቅዱስን ጥምቀትና በ1ኛ ቆሮንቶስ 10፡2 ላይ የተጠቀሰውን እንግዳ አሳብ ሳይቀር ማካተት አለበት። ብዙ ትርጉሞች የተመሠረቱት በውኃ ማጥለቅ በሚለው ቃል ላይ ነው። የጥምቀት ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም ግን ከአንድ ማኅበር፥ ወይም መልእክት ወይም ልምድ ጋር አንድ መሆንና ኅብረት መመሥረትን ነው የሚያስገነዝበው። 

የጥምቀት አፈጻጸም እስካሁን ያከራከረና ወደፊትም የሚያከራክር ጉዳይ ነው። በማጥለቅ ማጥመቅ አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ክፍሎች የሚከተሉትን መከራከሪያ ሃሳቦች ያቀርባሉ፡፡

1. “ባፕቲዞ” የሚለው የግሪክ ቃል ሁለተኛ ትርጉም አለው። ይኸውም “በአንድ ነገር፥ ወይም ተጽዕኖ ሥር መሆን” ማለት ነው። ስለዚህ ውኃውን በተጠማቂው ላይ ማፍሰስ፥ ወይም መርጨት፥ የሚሉት ቃላት ማጥለቅ ከሚለው በተሻለ ጥምቀት የሚለውን አሳብ ይገልጡታል። 

2. ጥምቀት የመንፈስ ቅዱስን በአንድ ሰው ላይ መውረድ የሚያስረዳ ከሆነ፥ የውኃ ጥምቀትን አስመልክቶም ማፍሰስ ወይም መርጨት የሚሉት ቃላት ይበልጥ ይገልጡታል። 

3. ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 2፡41 እንደተጠቀሰው በውኃ ውስጥ ማጥለቅ የማይቻልበት ሁኔታ ያጋጥም ይሆናል (በጣም ብዙ ሰዎችን በማጥለቅ ማጥመቅ ያዳግታል)። በሐዋርያት ሥራ 8፡38 (በረሃ ውስጥ ያለው ውኃ ትንሽ ስለሆነ) እና ሐዋ. 10፡47 እና 16፡33 (በየቤቱ ለማጥለቅ በቂ ውኃ አለመገኘቱ፣ በማጥለቅ የማጥመቁን ተግባር የማይችል ባያደርገውም፥ ተግባራዊነቱ ያጠራጥራል)። 

4. በዕብራውያን 9፡10 ጥምቀት የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ያሉትን ብዙ ወጎች ስለሚጠቅስና ከነዚህም አንዱ መርጨት ስለሆነ፥ ቃሉ ማጥለቅ ማለት ብቻ አይሆንም። 

5. ማጥለቅ ለሚለው ቃል ሌላ የማያጠራጥርና ግልጥ የሆነ የግሪክ ቃል አለ። ታዲያ ትክክለኛው የማጥመቅ አሠራር ማጥለቅ ከሆነ፥ ለምን ትክክለኛው የግሪክ ቃል አልተጠቀሰም? 

በውኃ በመጥለቅ መጠመቅን የሚደግፉ ወገኖች ከሚያቀርቡዋቸው ማስረጃዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡- 

1. “ባፕቲዞ የሚለው የግሪክ ቃል የመጀመሪያ ትርጉም ማጥለቅ ነው። 

2. “ወደ ውስጥ” እና “ወደ ውጭ” (ውኃ) የሚሉትን መስተዋድዶች በሚገባ ከተረዳን፥ ቃላቱ የሚያመለክቱት መጥለቅን ነው። 

3. ወደ ይሁዲነት የገባ ሰው የሚጠመቀው በማጥለቅ ነበር (ጥምቀቱን የሚፈጽመው ግን ሌሎች ሳይሆኑ ሰውየው ራሱ ነበር)። ክርስቲያናዊው አሠራርም ያን የተከተለ መሆኑን ከዚህ እንረዳለን (በሌላ ሰው የሚከናወን ቢሆንም። 

4. የማጥለቅ ጥምቀት፥ የጥምቀትን ጥቅም ማለትም የአሮጌውን ሕይወት ሞትና የአዲሱኝ ሕይወት ትንሣኤ በሚገባ የሚገልጥ አሠራር ነው (ሮሜ 6፡1-4)። 

5. የማጥለቅ ጥምቀት በጥንት ቤተ ክርስቲያናት ይፈጸም የነበረ አሠራር ሲሆን፥ አያሌ የአዲስ ኪዳን ምሳሌዎችም ይህን ያዛሉ፥ ወይም ይፈቅዳሉ (በኢየሩሳሌም አካባቢ ባሉ የውኃ ጉድጓዶች ውስጥ ሊጠመቁ ይችላሉ)። ሦስት ሺህ ሰዎች በበዓለ አምሳ ዕለት በመጥለቅ ሊጠመቁ ይችሉ እንደነበር መገመት አያዳግትም። 

6. የግሪኩ ቋንቋ ለማፍሰስና ለመርጨት የተለያዩ ቃላት አሉት፤ ይሁን እንጂ ጥምቀትን በማመልከት አገልግሎት ላይ አልዋሉም። 

አንድ ሰው ይህን ሲመለከት ማጥለቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሠራር ነው ለማለት ይገደድ ይሆናል። ማጥለቅ የየትኛዋም ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን አሠራር የነበረ ይመስላል። የቃሉ ተገቢ ትርጉምና በሥርዓቱ የሚተላለፈው መልእክት ማጥለቅን ያመለክታሉ። ከማጥለቅ ቀጥሉ በሥራ ላይ የሚውለው ማፍሰስ እንጂ መርጨት አልነበረም። ይህም በተግባር ይውል የነበረው፣ የታመሙና በመጥለቅ መጠመቅ የማይችሉ ሰዎችን ለማጥመቅ ነበር። ከዚህ በመነሳት ማፍስስ “የሕሙማን ጥምቀት” ይባላል። ሲፕርያን [Cyprian] የተባለ ሰው (200-257 ዓ.ም.) በመርጨት መጠመቅን በመደገፍ የመጀመሪያው ነበር። ይሁን እንጂ እሰከ አሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ይህ ዓይነቱ አሠራር በስፋት አልተለመደም። 

ሌላው ጥያቄ መጠመቅ ያለበት ማንነው? አማኞች ወይስ ሕጻናትም መጠመቅ ይችላሉ? የሚል ነው። የሕፃናትን ጥምቀት የሚደግፉ ወገኖች በእምነታቸው መሠረት የሚደረድሯቸው ነጥቦች፡- 

1. የግርዘት ሥርዓት (በሕፃናት ላይ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል) እና የጥምቀት ሥርዓት ተመሳሳይ ናቸው። ግርዘት የአሮጌው ኪዳን የመጀመሪያ ሥርዓት ሲሆን፣ ጥምቀት ደግሞ የአዲሱ መጀመሪያ ነው፡፡

2. የቤተሰቡ መጠመቅ ሕፃናትንም እንደሚጨምር አያጠራጥርም (ሐዋ. 16፡33)። 

3. በአዲስ ኪዳን ከቤተሰቡ አንድ ሰው አማኝ ከሆነ፥ ለቤተሰቡ ሁሉ የተስፋ ቃል የሚሰጥ ይመስላል። እንደዚህ ያለው ቤተሰብ ሕፃናትን ማጥመቁ አግባብ ይሆናል ይላሉ (1ኛ ቆሮ. 7፡14)። 

የሕጻናትን ጥምቀት የሚቃወሙና የአማኞችን ጥምቀት የሚደግፉ ደግሞ፥ የሚከተሉትን ማሳመኛ ነጥቦች ያቀርባሉ። 

1. ጥምቀት የመጀመሪያ ሥርዓት ከሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሰዎች የሚፈጽሙት ተግባር መሆን አለበት። የእስራኤል ወገን ለመሆን ከዚያ ዘር መወለድን ይጠይቃል። ዛሬ ደግሞ የእግዚአብሔር ቤተሰብ ለመሆን አዲስ ልደት ያሻል። ይህን የተረዱና ያመኑ ናቸው ሊጠመቁ የሚገባቸው። 

2. ስለ ቤተሰብ መጠመቅ በአዲስ ኪዳን በተጠቀሰው ክፍል፥ በቤተሰሱ ውስጥ ሕፃናት ስለመኖራቸው የተብራራ ነገር የለም። 

3. በሐዋርያት ዘመን፥ በአይሁዳውያንም ሆነ በክርስቲያኖች ዘንድ የሕፃናት ጥምቀት መኖሩን የሚያመለከት አንዳች ማረጋገጫ አይገኝም። ጥምቀት ከክርስቶስና ከክርስትና ጋር አንድ የመሆን ምልከት ከሆነ፣ ይህን ምልክት የሚጠቀሙበት አንድነት ያላቸው ብቻ ናቸው። ከከርስቶስና ከክርስትና ጋር ለመተባበር ደግሞ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው፡- ክርስቶስን በግል ማምን። ይህ እምነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው መጠመቅ ያለባቸው። ለምሳሌ የፊልጵስዩስ ወህኒ ጠባቂ ቤተሰቦች፥ ጳውሎስ የሰበከውን የጌታ ቃል ለመስማትና ለመረዳት በሚችሉበት የዕድሜ ክልል መሆናቸው ግልጥ ነው (ሐዋ. 16፡32)። ሰለዚህ አምነው የተጠመቁት፥ የተነገራቸውን ተረድተው ሊቀበሉ በሚችሉበት የዕድሜ ክልል ውስጥ የነበሩ ይሆናሉ። ይህ ልጆችን ይጨምራል ቢባል እንኳን፥ ሕፃናትን አይመለከትም። 

እንደገና መጠመቅስ (ዳግም ጥምቀት)? በአዲስ ኪዳን ለዚህ ማስረጃ የሚሆን አንድ ግልጥ ምሳሌ አለ። ይኸውም በዮሐንስ የተጠመቁ ሰዎች፥ ጳውሎስ ክርስትናን ከሰበከላቸው በኋላ የሰሙትን በማመን በክርስቲያን ጥምቀት መጠመቃቸው ነው (ሐዋ. 19፡1-7። ይህ ሁኔታ የዮሐንስ ጥምቀትና የክርስትና ጥምቀት የተለያዩ መሆናቸውን ሲያሳይ፣ አንድ ሰው ከዚህ በፊት ቢጠቅም፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሲያምን ከአዲሱ መልእክትና ውገን ጋር ያለውን አንድነት ለመግለጥ እንደገና ሊጠመቅ እንደሚገባው ያመለክታል። 

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading