የድነት (የደኅንነት) ቃላት

ድነት (ደኅንነት) በእምነት ብቻ የሚገኝ መሆኑ በአዲስ ኪዳን ከ200 ጊዜ በላይ ተገልጧል። ይህም እምነት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ፋንታ ስለ ኃጢአታችን እንደሞተ መገንዘብና መቀበል ነው (ዮሐ. 3፡16፤ ሐዋ. 16፡31)። ድነት (ደኅንነት) ነጻ ስጦታ ነው። ስለዚህ በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን ድነትን እኛ ለእግዚአብሔር አንዳች ስጦታ አበርክተን እንዳገኘነው ከማስመሰል መጠንቀቅ ይኖርብናል። እርሱ ሁሉንም ስለሰጠን፥ በእምነት እንቀበላለን (ዮሐ. 1፡12)። 

ድነት በእምነት አማካይነት በጸጋ እንደሚገኝ የማይገልጥ ልዩ ወንጌል መስበከ፥ በገላትያ 1፡8-9 ያለውን መርገም [Anathema/አናቴማ] ያስከትላል። እንዲህ ዓይነት የሐሰት ወንጌል ዋጋ ቢስ (ውጉዝ) ነው። ይህ ከባድና ብርቱ ማስጠንቀቂያ ቢሆንም፥ ባለንበትም ሆነ ባለፉት ዘመናት ብዙዎች የሐሰት ወንጌል ሰብከዋል። 

ማመንና ራስን መስጠት 

እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ፡- ለመዳን ክርስቶስን እንደ ሕይወት ጌታ መቀበል ያስፈልጋልን? የሚል ነው። በአሁኑ ጊዜ ብዙዎች አዎን ያስፈልጋል ይላሉ። ለምሳሌ በጣም የታወቀ አንድ ጸሃፊ ወንጌልን በተሳሳተ ሁኔታ ሰለሚያቀርቡ ሰዎች ሲጽፍ፥ “ከሰዎች የሚፈለገው፥ ጌታን የኃጢአት ተሸካሚ አድርገው እንዲያምነት ብቻ ነውን? ራሳቸውን በመካድ የሕይወታቸው ገዥ ሊያደርጉትስ አይገባም?” ብሏል። በሌላ አባባል አንድ ሰው ለመዳን በጌታ ማመንና ራሱን ለርሱ ቁጥጥር አሳልፎ መስጠት አለበት። ሕይወት መስጠትን ባያጠቃልልም እንኳን፥ አንዳንድ ጊዜ ራስን የመስጠት ፈቃደኝነት ሊኖር ይገባል ይባላል። ይህ ቢያንስ ለሥጋዊ ክርስቲያኖች መኖር (ዛሬ በጣም ብዙ ናቸው) በር ይከፍታል። ታዲያ ፈቃደኝነትና እምነት በድነት ወቅት የሚያስፈልግ ከሆነ ምን ያህል ፈቃደኝነት ነው የሚያሻው? ለመዳን ራስን አሳልፎ መስጠት ካስፈለገ፥ ለምንድን ነው ታዲያ አዲስ ኪዳን የዳኑ አማኞች ጭምር ራሳቸውን እንዲሰጡ የሚጠይቅ (ሮሜ 12፡1)? 

ይህን ትምህርት በተመለከተ አራት ነገሮችን ለመጥቀስ ይቻላል፡- 1. የሰዎች እምነት ጥልቀት እንዲኖረው ከመጓጓት የመነጨ ቅን ሙከራ ነው፣ 2. “ጌታ” የሚለው ቃል፥ ያሉትን የተለያዩ ትርጉሞች ካለመረዳት ነው፤ 3. አማኙ ሕይወቱን በእግዚአብሔር ዓላማ መምራትን በመማሩ ረገድ እያደገ የሚሄድበት መንገድ ግልጥ አይደለም፤ 4. በቀላሉ “ማመን ብቻ” የሚለውን አሳብ ለመቃወም ነው፤ እርግጥ የነገሩ መጨረሻ የሚወሰነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለማመን፥ ስለመታዘዝና ራስን ስለመሰጠት የሚገልጠው እውነት ላይ በመመሥረት ብቻ ይሆናል። 

ጥልቀት የሌለው እምነት ቃሉ በሚሰበክበት ጊዜ የምንጠብቀው ጉዳይ መሆኑን ጌታ ራሱ ገልጧል (ሉቃስ 8፡12-15)። ራሳቸውን ያልሰጡ ብዙ አማኞች እንደነበሩ ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በራእይ 2-3 በተጻፈው ደብዳቤ ተገልጧል (በተለይ ራእይ 2፡13-14፥ 2፡19-20ን በጥንቃቄ ይመልከቱ)። ሥጋዊ ክርስቲያኖች ለሽልማት ባይበቁም፣ ሕይወታቸው እንደሚድን ተጽፏል (1ኛ ቆሮ. 3፡15)። አንድ ሰው የውሽት አማኞችና ሐሰተኛ ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያን እንዳይኖሩ ቢመኝም፥ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባል ይህ የማይቻል ነገር ነው። 

“ጌታ” የሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። አንዳንዴ የማዕረግ፥ ወይም የአክብሮት ቃል ይሆናል፣ “ጌቶች” እንደምንለው ዓይነት ( ዮሐ. 4፡11)። አንዳንድ ጊዜም የበላይ አለቃ እንደማለት ነው (ሉቃስ 6፡46)። በአዲስ ኪዳን ያለው አብዛኛው ትርጉም ግን፥ በብሉይ ኪዳን “ያህዌ” ከሚለው የእግዚአብሔር ስም ጋር የሚስተካከል ነው። የናዝሬቱ ኢየሱስ አምላክነቱን በገለጠና ተከታዮቹም ጌታ (ጌታ ኢየሱስ) ባሉት ጊዜ እሱ (የናዝሬቱ ኢየሱስ) ሥጋ የለበሰ የብሉይ ኪዳኑ ያህዌ ለመሆኑ ግልጥ ማስረጃ ነበር። አምላክ ሰው ለሆነበትም መግለጫ ነበር። “ክቡር ኢየሱስ” ቢባል፥ ወይም ሌላ የማዕረግ ስም ቢሰጠው ኖሮ፣ በጊዜው የነበሩ ሰዎች ሊወግሩት ወይም ሊሰቅሉት ባልተነሱ ነበር፤ “ያህዌ ኢየሱስ” መባሉ ነው ለሞት የዳረገው። እርግጥ በመለኮታዊነቱ ትርጉም መሠረት፡- ጌትነቱ ለአዳኝነት ተግባሩ ፍጹም አስፈላጊ ነበር። አዳኝ የማዳን ከህሎት ይኖረው ዘንድ፥ ሥጋ የለበሰ አምላክ መሆን ነበረበት፤ ለመሞት ሰው፥ ሞቱ ዋጋ ያለው የኃጢአት ከፍያ ይሆን ዘንድ ደግሞ፥ እግዚአብሔር መሆን አለበት። ይህ ነው የሮሜ 10፡9 እና የሐዋርያት ሥራ 2፡36 ትርጉም። 

ደቀ መዝሙር ተማሪ ነው። ልክ እንደ ይሁዳ ያልዳኑ የጌታ ደቀ መዛሙርት ሊኖሩ ይችላሉ። ደቀ መዛሙርት የማፍራት ተግባር ያመኑትን በማጥመቅና ያለማቋረጥ በማስተማር ይከናወናል (ማቴ. 28፡19)። ግራ መጋባት የሚፈጠረው ለመንፈሳዊ እድገት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንደሚያስፈልጉ ግዳጆች አድርገን ስንወስድ፥ ወይም የደቀ መዛሙርትነት ባሕርያትን ለደቀ መዝሙርነት መመልመያ መመዘኛ ስናደርግ ነው። እነዚህን ሁለት የደቀ መዝሙርነት ፅንስ አሳቦች ጌታ እንዴት ጎን ለጎን እንዳስቀመጣቸው በጥንቃቄ ያስተውሉ። በሉቃስ 14፡16-24 ላይ በተጠቀሰው ታላቅ የእራት ግብዣ ምሳሌ ወደ ግብዣው ማንም ሊገባ እንደሚችልና ጥሪው ለሁሉ ነጻ መሆኑን ሲጠቅስ፥ በሉቃስ 14፡25-33 ላይ እንዲሁ ደቀ መዝሙርነት ሳያቋርጡ እርሱን መከተል መሆኑንና ዕድሉም ለጥቂቶች የተወሰነ መሆኑን እስተምሯል። እነዚህን የአገልግሎት መመዘኛዎች የሕይወት ማግኛ ግዴታዎች ማድረግ ግን ወንጌልን ማምታታትና እንደ ንጹሕ ውኃ የጠራውን የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ሥራ ማደፍረስ ነው። በተጨማሪም ደቀ መዝሙርነት ድርጊትን እንጂ፥ ፈቃደኝነትን ብቻ እንደማይሻ ማስተዋል ይጠቅማል። 

ለመሆኑ ራሳቸውን ያልሰጡና ያልታዘዙ፥ ግን የእውነተኛ አማኞች ምሳሌ የሆኑ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አሉን? አዎ አሉ። በአዲስ ኪዳን “ጻድቅ” ተብሎ የተጠራው ሎጥ (2ኛ ጴጥ. 2፡7) በዘመኑ ሁሉ የእግዚአብሔርን ጌትነት ችላ ያለ ደካማ ሰው ምሳሌ ነበር። ጴጥርስ ለምሳሌ “ጌታ ሆይ አይሆንም” በማለት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የጌታን ጌትነት አልቀበልም ብሎ ነበር (ሐዋ. 10፡14)። ምናልባት በጣም ግልጥ የሆነው ምሳሌ፥ በኤፌሶን አማኞች ዘንድ የታየው ይሆናል (ሐዋ. 19፡8-19)። አንዳንዶች የአስማትና የጥንቆላ መጻሕፍታቸውን ከማቃጠላቸውና በእነዚህ መጻሕፍት መጠቀም ኃጢአት መሆኑን ከመናዘዛቸው በፊት ለሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የዳኑ ነበሩ። በሌላ ቃል በአስማት መጻሕፍት መጠቀም እንደሌላባቸው ያወቁ፥ ግን ያላስወግዱ፤ ክርስቲያን ከሆኑ ሁለት ዓመት የሞላቸውና ከርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉ ነበሩ። ያ ድርጊታቸው አማኝ ተብሎ ለመጠራት አልከለከላቸውም፡፡ ድነታቸው በእምነትና የአስማትን ዕቃ ለማስወገድ ፈቃደኛ በመሆናቸው ላይ የተመሠረተ አልነበረም። 

ማመን ቀላል ነገር ነውን? በእምነት ውስጥ የሚካተቱት ነገሮች እስከታወቁ ድረስ መልሱ አይደለም ይሆናል። ምክንያቱም እምነታችን የማይታመንን ነገር እንዲታመን ሰለሚጠይቅ ነው። ይሄውም ሰዎች ባላዩት፥ ወይም ዛሬ በሕይወት ከሚኖሩ ሰዎች መካከል አይቼዋለሁ ብሎ የሚናገርለት ምስክር በማይገኝለት ሰው፥ በጓደኞቹ የተጻፈን ታሪክ ብቻ በመመልከት እንዲያምኑ ስለምንጠይቅ ነው። በእውነት በማይታየው ክርስቶስ ማመን ቀላል ነውን? እንዲሁም ሰዎችን በዚህ ባልታየው ሰው እንዲያምኑ፥ በርሱም ሞት ምክንያት የኃጢአት ይቅርታና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ፥ የኃጢአታቸውም ዋጋ የተከፈለ መሆኑን አሜን ብለው እንዲቀበሉ እንጠይቃዋለን። ታዲያ ይህ ቀላል ጥያቄ ነው? 

በዚህ ባልተቀየጠ የእግዚአብሔር ጸጋ ላይ አንዳች ነገር ሳይጨምሩ (ከበጎ አሳብ ቢመነጭም እንኳ) በመጀመሪያ የእምነትዎን መሠረት ለሰዎች በጣም ግልጥ ያደርጉላቸው፤ ደግሞም ስለ እርሱ ምን ማመን እንደሚገባቸው ያስረዷቸው። ከዚያም ወደ ጌታ ኢየሱስ፣ ሰው ወደሆነው አዳኝ፥ ላመኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና የኃጢአት ይቅርታ ወደሚሰጠው አምላክ ያመልክቷቸው። ይህን ነው ጌታ ራሱ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ከኃጢአተኞች ጋር በመገናኘት ያከናወነው። ለሰማሪያይቱም ሴት “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኝው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት (ዮሐ. 4፡10)። የጠየቃት ነገር ቢኖር ክርስቶስ (መሲህ) መሆኑን (ቁ. 26) እንድታውቅና የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ከእርሱ እንድትቀበል ነበር። ለመዳን ይቻላት ዘንድ ውስብስብ የነበረውን የኃጢአት ሕይወቷን እንድታስተካክል አልነበረም የነገራት። 

ማመንና መጠመቅ 

ጥምቀት ከእግዚአብሔር የተሰጠና በጣም ጠቃሚ የሆነ የእምነት መመስከሪያ መንገድ እንጂ የድነት መመዘኛ አይደለም። ሳይጠመቁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ሊሄዱ ይችላሉ (በመስቀል ላይ እንደነበረው ወንበዴ)። ጥምቀት ለድነት ያስፈልጋል የሚሉ ሰዎች (ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ ጥቅሶችን ወደ ጎን በመተው) አንዳንድ ጥቅሶችን ለመደርደር ይሞክራሉ። በሐዋርያት ሥራ 2፡38 ላይ ያለው ቃል “ኃጢአት ስለተሠረየ ተጠመቁ” ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። እዚህ ላይ “አይስ” የሚለው የግሪክ መስተዋድድ የአማኙን የጥምቀት መሠረት ያመለክታል። መጠመቅ ያለበት ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለት ሳይሆን ኃጢአቱ ይቅር ስለተባለለት ነው። ይህ የመስተዋድዱ የተለመደ ትርጉም ባይሆንም፥ በማቴዎስ 12፡41 ላይ ይህን የመሰለ ትርጉም መቅረቡ እንደ ምሳሌ ሊቆጠር ይችላል። ስለዚህ የኃጢአት ሥርየት የመጠመቅ መሠረት እንጂ፥ የጥምቀት ዓላማ ሊሆን አይችልም። 

የሐዋርያት ሥራ 22፡16 ጥምቀት የጳውሎስን ኃጢአት እንዳነጻ የሚናገር ይማሰላል። በትክክል ሲታይ ግን የጥቅሱ አሳብ ይህ አይደለም። በዚህ ቁጥር ሁለት ትእዛዞች አሉ (ተጠመቅ እና ታጠብ)፥ ሌሎች ሁለት ነገሮች ተጠቅሰዋል (ተነስተህ እና እየጠራህ)። እነዚህም ሲጣመሩ፡- ተጠምቀህ ተነሳ፤ የጌታን ስም እየጠራህ ኃጢአትህን ታጠብ የሚሉ ሊሆን ይችላሉ። በሌላ አባባል የኃጢአት መታጠብና ጥምቀት እንደ ምክንያትና ውጤት ሊገናኙ አይችሉም። መነሳቱ ጥምቀት ስለወሰደ ነው፥ የኃጢአቱ መታጠብ ደግም የጌታን ስም ስለጠራ ነው፡፡

ማርቆስ 16፡16 በጥንታዊው የግሪክ ጽሑፍ ስለማይገኝ፥ በመጀመሪያው የማርቆስ ጽሑፍ ቅጂ ውስጥ መሆኑ በደንብ አልተረጋገጠም። ስለዚህ ለድነት አስፈላጊ የሆንውን የጥምቀት ትምህርት በዚህ ክርክርን ባስነሳ ጥቅስ ላይ መመሥረት አግባብ አይሆንም። ነገር ግን ቃሉ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለበት ከሆነ፥ በጥምቀት ዳግም ልደት ይገኛል ብለው የሚያስቡ ሁሉ፥ በጥቅሱ መጨረሻ ጥምቀት የሚለው ቃል መዘለሉን ልብ ሊሉ ይገባል። ለመዳን ጥምቀት አስፈላጊ ነው የሚሉ ወገኖች፥ በትምህርታቸው የሚያቀርቧቸው ጥቅሶች በሙሉ አከራካሪ ትርጉም ያላቸው ናቸው። የጌታና የሐዋርያት ትምህርት በግልጥ የሚያሳየን ግን በክርስቶስ ማመን ለድነት በቂ መሆኑን ነው (ዮሐ. 6፡29፤ ሐዋ. 13፡39)። 

ንስሐ መግባትና ማመን 

በግሪክ ቋንቋ “ንስሐ መግባት” በቀጥታ ሲተረጎም “አሳብን መለወጥ” ማለት ነው። ይህ ሲባል “ምንን በሚመለከት ነው አሳቤን የምለውጠው”? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። አንድ ሰው ኃጢአቱን በተመለከተ አሳቡን ቢለውጥ፥ ማለትም ኃጢአት በመሥራቱ ቢጸጸት ይህ ድርጊቱ ሊያድነው አይችልም። በዚህ አመለካከት እሥር ቤትም ሆነ ውጭ ሆነው ስለፈጸሙት ግፍ የሚያዝኑ ብዙ ወንጀለኞች አሉ። ለሰሩት ጥፋት ያዝናሉ፤ ይህ ግን ወንጀለኝነታቸውን ይተዋሉ ማለት አይደለም። እንዲሁም ሰዎች ከአዳኛቸው ይቅርታን ሳይሹ ስለ በደላቸው ሊያዝኑ ይችላሉ። 

ነገር ግን ንስሐ ማለት፥ ክርስቶስን ስለአለመቀበል ኃጢአት አሳብን መቀየር ማለት ከሆነ፥ ይህ ዓይነቱ ንስሐ ያድናል፤ በክርስቶስ ማመን ሆኖም ይቆጠራል። ይህን እንዲፈጽሙ ነበር ጴጥሮስ በበዓለ አምሳ ዕለት ሰዎችን ያሳሰባቸው። ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ የነበራቸውን አስተሳሰብ እንዲለውጡ ያስፈልግ ነበር። ቀደም ሲል ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነኝ በማለቱ፥ አምላክን እንደተሳደበ ቆጥረውት ነበር። አሁን ግን ለድነታቸው (ለደኅንነታቸው) ሊያምኑት የሚገባ አምላክና ሰው የሆነ አዳኝ እንደሆነ በማመን፥ ስለ እርሱ የነበራቸውን አሳብ መቀየር ነበረባቸው። ይህ ዓይነቱ ንስሐ ያድናል፤ የዳነ ሰው ሁሉ የዚህ ዓይነቱን ንስሐ የፈጸመ ነው፡፡

ሌላው የንስሐ ዓይነት ደግሞ የክርስቲያንን ሕይወት ይመለከታል። ክርስቲያን ንስሐ መግባት አለበት። ስለሰራቸው ልዩ ልዩ ኃጢአቶች አስተሳሰቡን መለወጥ ይኖርበታል። ንስሐ ሲገባ እነዚህን ኃጢአቶች ይናዘዝና ይቅርታን ይለማመዳል። በአጠቃላይ በዚህ ላይ የሚጨመር ሌላ ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ የሚታከል ሥራ ይሆናል። እምነት ብቸኛው መስፈርት ነው፥ መዳን የሚቻለውም ማዳን በሚችለው ክርስቶስ በማመን ብቻ ነው። ይህ ነው የእግዚአብሔር ጸጋ።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.