የቤተ ክርስቲያን ንጥቀት ገለጣ (ዮሐ. 14፡1-3፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡51-57፣ 1ኛ ተሰ. 4፡13-18)

“መነጠቅ” [Rapture/ራፕቸር] የሚለው ቃል በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡17 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። እንዲሁም ፊልጶስ በሐዋርያት ሥራ 8፡39 እና ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 12፡2 4 ስለመነጠቃቸው ተገልጧል። በመሆኑም የቤተ ከርስቲያን መነጠቅ፥ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው። በዮሐንስ 14፡1-3 ላይ በተሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ መኖሪያ ስፍራ መምጠቅ ነው። ጳውሎስ በቆሮንቶስ መልዕክቱ ይህ ምስጢር ነው ይላል። “ምስጢር” የሚለው ቃል ትርጉም፣ ከዚህ በፊት ያልታወቀ፥ አሁን የተገለጠ ማለት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል። ትንሣኤ ምስጢር አልነበረም፤ ምክንያቱም ብሉይ ኪዳን ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደሚነሱ በግልጥ አስተምሯል (ኢዮብ 19፡25፤ ኢሳ. 26፡19 ዳን. 12፡2)። የተወሰኑ ሰዎች ሞትን ሳይቀምሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄዱ ግን በምንባቦቹ ውስጥ አልተገለጠም። ለዚህ ነው ሁላችን “አናንቀላፋም” የሚለው ቃል ምስጢር የሆነው (1ኛ ቆሮ. 15፡51)። በመነጠቅ ጊዜ በሕይወት ያሉ ሰዎች የማይሞት አካል ይለብሳሉ። በሞት የበሰበሱትም በትንሣኤ የማይብስብስ አካል ይሰጣቸዋል። በሁለቱም መንገድ ወደ ሰማይ የሚደረግ ጉዞ ለውጥ ይሻል፤ ሕያዋን መለወጥ፥ ሙታንም መነሳት አለባቸው፤ የመጨረሻው የክርስቲያን ትውልድ ሞትን አይቀምስም፡፡

ይህ ለውጥና መነጠቅ የዓይን ሽፋን መርገብገብን ያህል ቅጽበታዊ” እንጂ አዝጋሚ ክንውን አይደለም። እንዲሁም መነጠቅ ሳይከፋፈል በአንድ ጊዜ ይሆናል። ጳውሎስም ሁላችን እንለወጣለን አለ እንጂ ስለተወሰኑ አማኞች አልተናገረም። 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-58 ሦስት ነገሮች ያስተምራል። 

1. መነጠቅ የሞቱ አማኞችን ብቻ ሳይሆን፥ በጊዚው ሕያው የሆኑ አማኞችንም የአካል ለውጥ ያመለክታል። 2. በቅፅበት ይፈጸማል። 3. አማኞችን ሁሉ ያካትታል እንጂ፥ ለተወሰኑ ብቻ አይደለም። 

ከሌሎቹ ይልቅ በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 ያለው ጥቅስ ነው ጌታ ሲመጣ ምን እንደሚሆን የተብራራ አሳብ የሚሰጠን። በዚህ ክፍል አራት ነገሮች ተጠቅሰዋል። 

1. ክርስቶስ ራሱ ይመለሳል (ቁ. 16)፣ በአካል መገለጡ የሚያስከትላቸው በኃይል የተሞሉ ክስተቶችም ይኖራሉ፤ ታላቅ የትእዛዝ ድምጽ፥ የሊቀ መላእከት ድምጽ፥ የእግዚአብሔር መለከት ድምጽ ይሰማሉ። 

2. ትንሣኤ ይሆናል (ቁ. 16)። የሞቱት ይነሳሉ፥ ሕያዋንም ይለወጣሉ፥ ይህ ሁሉ በቅስበት የሚከናወን ይሆናል። የሰው ዘር በሙሉ ሳይሆን፥ የሞቱና ሕያዋን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው ይህን መነጠቅ የሚቀምሱት። ይህ አማኛችን ብቻ የሚመለከት ይሆናል፤ ምክንያቱም አንድ አጠቃላይ ትንሣኤ ሳይሆን የተለያዩ ትንሣኤዎች ናቸው ያሉት። 

3. መነጠቅ ይሆናል (ቁ. 17)። የቃሉ ትርጉም፣ አንድን ሰው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ መውሰድ ማለት ሲሆን ይህም ሕያዋን ሰዎችን ወደ መንግሥተ ሰማያት መውሰድ ማለትን በትክክል ያመለክታል (2ኛ ቆሮ. 12፡4)። 

4. ከዚያም እንደገና መገናኘት ይኖራል (ቁ. 17)፤ በጌታ ከሞቱና ከምንወዳቸው ሰዎች፥ እንዲሁም ከጌታም ጋር እንገናኛለን። ግንኙነቱም ዘላለማዊ ይሆናል። 

የመነጠቅ ጊዜ 

መነጠቅ ከጌታ ዳግም ምጽአት የተለየ ስለመሆኑ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። የመጀመሪያው መነጠቅ፥ ከርስቶስ የራሱ የሆኑትን ለመውሰድ የሚመጣበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከነርሱ ጋር በድል አድራጊነትና በክብር የሚመለስበት ወቅት ነው። አከራካሪው ጉዳይ በነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ምን ያህል የጊዜ ልዩነት አለ? የሚለው ጥያቄ ነው። አልቦ-ሺህ ዓመታውያን፥ ሁለቱም በፍዳው ዘመን መጨረሻ ላይ የሚከናወኑ ሲሆን፥ ንጥቀት ይቀድምና ወዲያውኑ ዳግም ምጽአት ይከተላል (ወዲያውኑ፥ ያለ ሺህ ዓመት አገዛዝ) ይላሉ። በቅድመ-ሺህ ዓመታውያን ዘንድ ስለመነጠቅ ጊዜያት አራት አመለካከቶች እንዳሉ ይታወቃል። 

የድህረፍዳ ዘመን አመለካከት። ይህ አመለካከት የመነጠቅንና የዳግም ምጽአትን የጊዜ ቅደም ተከተል አስመልክቶ የሚያሰራጨው ትምህርት ከአልቦ-ሺህ ዓመታውያን የተለየ አይደለም (የሺህ ዓመቱ አገዛዝ ከዳግም ምጽአት በኋላ ይከተላል በሚለው አመለካከቱ ግን ይለያል)። በዚህ አመለካከት መሠረት ቤተ ክርስቲያን በፍዳው ዘመን ሁሉ በምድር ላይ ትኖራለች። የክርስቶስ ለቅዱሳኑና ከነሱ ጋር መምጣት፥ በዚህ ዘመን ማብቂያ ላይ ወዲያውኑ የሚከሰቱ ድርጊቶች ናቸው። 

ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸው፡- 

1. መነጠቅና ዳግም ምጽአት በመጽሐፍ ቅዱስ በተመሳሳይ ቃላት ነው የተገለጡት። ይህ ሁለቱም በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ መሆናቸውን ያመለክታል (1ኛ ተሰ. 4፡15፤ ማቴ. 24፡27)። 

2. በፍዳው ዘመን ቅዱሳን እንደሚኖሩ ስለተገለጠ፥ ቤተ ክርስቲያንም በዚያን ጊዜ በምድር ትኖራለች (ማቴ. 24፡22)። 

3. ትንሣኤ በሺሁ ዓመት አገዛዝ መጀመሪያ ላይ የሚከሰት ነው ተብሎ ይታመናል። ይኽው ትንሣኤም በመነጠቅ ጊዜ የሚከናወነው ትንሣኤ መሆኑ ስለሚገመት፥ መነጠቅ ልክ ከሺሁ ዓመት አገዛዝ በፊት የሚፈጸም ይሆናል (ራእይ 20፡4)። 

4. ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ዘመን ቁጣ በመለኮታዊ ኃይል ትጠበቃለች። ጥበቃው የሚከናወንላት በዚያው ዘመን እየኖረች እንጂ፥ ከዚያ ወጥታ ወይም ተነጥቃ አይደለም እስራኤላውያን በግብፅ እየኖሩ ከመቅሰፍት እንደተጠበቁ)። 

5. መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት መፈጸም ያለባቸው ትንቢቶች እንዳሉ የሚያስተምር በመሆኑ፥ መነጠቅ ከታወቀው የፍዳ ዘመን ክንዋኔ በኋላ ይሆናል። 

6. ይህ ድህረ-ፍዳ ዘመን አመላካከት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነበር። 

ማዕከላዊ የፍዳ ዘመን። የዚህ አመለካከት አቀንቃኞች ክርስቶስ ለሕዝቡ የሚመጣው በፍዳው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው፤ ማለትም የፍዳ ዘመን ከጀመረ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላና ሊያልቅም ሦስት ዓመት ተኩል ሲቀረው ነው፤ ያኔ ነው ክርስቶስ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ከቅዱሳኑ ጋር የሚመጣው ይላሉ። 

የዚህ አመለካከት መከራከሪያ ነጥቦች፡- 

1. 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡52 ላይ የተጠቀሰው የመጨረሻ መለከት” በዮሐንስ ራእይ 11፡15 ላይ ከተጠቀሰው “ሰባተኛ መለከት” ጋር አንድ ነው፤ ይህም የተሰማው በፍጻሜው ዘመን መካከል ላይ ነው። 

2. እርግጥ ታላቁ የፍዳ ዘመን ከዳንኤል ሰባኛ ሳምንት ሱባኤ መጨረሻ የሳምንት አጋማሽ ሰለሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ከዚያ መከራ ነው የምትጠበቀው (ራእይ 11፡2፤ 12፡6)። 

3. የሁለቱ ምስክሮች ትንሣኤም የቤተ ክርስቲያን መነጠቅ ያመለክታል፤ የነሱም ትንሣኤ የሚከናወነው በመከራው ዘመን አጋማሽ ላይ ነው (ራእይ 11፡11)። 

ከፈል መነጠቅ። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች የሚያስተምሩት ደግሞ፥ ተገቢ የሆኑ አማኞች ብቻ የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ይነጠቃሉ፤ ሌሎች ግን ቁጣውን በትዕግሥት እንዲያልፉ ይተዋሉ ማለት ነው። በምድርም ለሚቀሩት ይህ ጊዜ የመጥራት ጊዜ ይሆንላቸዋል። አሳቡ የተወሰደው እንደ ዕብራውያን 9፡28 ካለው ጥቅስ ሲሆን፥ በዚህ ጥቅስ መሠረት ጌታን ለመገናኘት ቅድመ ዝግጅት ማስፈለጉ ግዴታ ይሆናል። ምንም እንኳን በዚህ አመለካከት መሠረት መልካም ሥራ አንድን ሰው ለመነጠቅ ያበቃዋል ሲባልም፥ ምን ያህል ጥሩ ሥራ ነው የሚያስፈልገው? ለሚለው ጥያቄ ግን የአሳቡ ደጋፊዎች መልስ አይሰጡም። እነዚህ ሰዎች በዚህ ሳይወሰኑ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51 ላይ “ሁላችንም እንለወጣለን” የሚለውን ግልጥ ቃል ወደ ጎን ይሉታል። 

ቅድመ-ፍዳ ዘመን። ይህ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያን ሰባቱ የፍዳ ዘመን ከመጀመሩ በፊት ትነጠቃለች በማለት ያስተምራሉ። ከሰባቱ ዓመት በኋላ ማለት፥ የፍዳው ዘመን እንዳለቀ፣ የሺህ ዓመቱን መንግሥት ለመመሥረት ጌታ ከሕዝቡ ጋር ይመጣል ብለው ሲያምኑ፥ አሳባቸውን ለማጠናከር የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳሉ። 

1. የፍዳው ዘመን “ታላቁ የቁጣ ቀን” (ራእይ 6፡17) ተብሎ ተጠርቷ፡፡ ከሚመጣው ቁጣ የሚታደጋቸው አዳኝ እንዳላቸው ያወቁ አማኞች (1ኛ ተሰ. 1፡10) እግዚአብሔር ለቁጣ እንዳልመረጣቸው እርግጠኞች ይሆናሉ (1ኛ ተሰ. 5፡9)። በዚህ ጥቅስ ምንባብ ጳውሎስ በጌታ ቀን ወይም በፍዳው ዘመን መጀመሪያ ስለሚኖረው ነገር ነው የሚናገረው (1ኛ ተሰ. 5፡2)፤ ከርስቲያኖች በዚያን ጊዜ እንደማይገኙና የቁጣው ዘመን ከመጀመሩ በፊት እንደሚወሰዱ ግልጥ አድርጓል። ይህ እውን የሚሆነው ግን መነጠቅ ከፍዳው በፊት የተፈጸመ እንደሆነ ብቻ መሆኑን በማስታወስ ነው። 

2. ከሞት የተነሣው ጌታ በፊላደልፊያ ላለችው ቤተ ክርስቲያን “በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ” (ራእይ 3፡10) በማለት ቃል ገብቷል። የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ተከታዮች ይሆን የተስፋ ቃል ለሌሎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከተጻፉት የተስፋ ደብዳቤዎች ጋር ያዛምዱታል (እርግጥ ይህን እውነት የሚያዩት ክርስቶስ ሲመጣ የሚኖሩት አማኞች ብቻ ቢሆኑም)። በመቀጠልም “የፈተና ሰዓት” የተባለው ጊዚ ዓለምን በሙሉ የሚያዳርስ ስለሆነ የፍዳን ዘመን ያመለክታል ይላሉ። የድህረ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ያላቸው ወገኖች ይህ ተስፋ (ከዳቶ ዘመን ጋርም ያዛምዱታል) ክርስቲያኖች ምንም እንኳን በፈተናው ዘመን ውስጥ መኖር ቢኖርባቸውም ከፍዳው ዘምን ፍርድ የሚጠበቁበት ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ተስፋው ከችግሩ ሳይሆን ከችግር ጊዚው እንደሚጠበቁ ነው የሚያረጋግጠው። ይህ ክርስቲያኖች በዚያን ጊዜ ፍጹም ይወገዳሉ ማለት ይመስላል። “ከ..እጠብቅሃለሁ” የሚል ቃል በአዲሰ ኪዳን ሁለት ጊዜ ብቻ የተጠቀሰ ሲሆን፥ እዚህ ቦታና ዮሐንስ 17፡15 ላይ ይገኛል። በሁለተኛው ጥቅስ፥ ጌታ አማኞች ከክፉ እንዲጠበቁ ጸልዮላቸዋል። ይህም ጸሎት ከጨለማው ሥልጣን ነጻ አውጥቶ ወደ ውድ ልጁ መንግሥት አስገብቶናል (ቈላ. 1፡13)። አንድ ነገር በሚከናወንበት አካባቢ ተገኝቶ ከዚያ ጊዜ ነጻ መሆን ይቻላል ተብሎ አይታሰብም። ስለሆነም በመጨረሻው ዘመን በዓለም ሁሉ ከሚደርሰው ዳ ለመዳን የግድ ከምድር መወሰድን ይጠይቃል። 

እንግዲህ ይህ የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ተከታዮች አሳብ ትክክል ከሆነ፥ የተስፋ ቃል ሌላ ትርጉም ያሻዋል ማለት ነው። ምክንያቱም በፍዳው ዘመን የሚኖሩ ቅዱሳን ከመከራና ስደቱ ተካፋዮች ከመሆናቸውም ባሻገር ብዙዎች ስለ እምነታቸው ይሞታሉ (ራእይ 6፡9-11፥ 7፡9-14፥ 14፡1-3፣ 15፡1-3)። 

3. 2ኛ ተሰሎንቄ 2፡1-12 ላይ ጠቃሚ የሆነ የቅደም ተከተሎች ዝርዝር ሰፍሯል። ጳውሎስ አንድ ነገር ሳይሆን የጌታ ቀን አይመጣም የፍዳው ዘመን አይጀመርም ይላል (ቁ. 3)። በመጀመሪያ የዓመፅ ሰው ይገለጣል (ቁ. 3)። ነገር ግን የዓመፅ ሰው አንድ ነገር (ቁ.6) እና አንድ ሰው (ቁ.7) ከመንገዱ እስኪወገዱ ድረስ ሊወገድ አይችልም። ከዚያ በኋላ ብቻ ነው የዓመፅ ሰው ለክፉ ሥራ የሚገለጠው። ከልካዩም ምንም ይሁን ማን፥ የዓመፃው ሰው ያን ጊዜ በሙላት እንዳይንቀሳቀስ ያግደዋል። ተሰሎንቄያውያን ግን ያ ከልካይ ማን፥ ወይም ምን እንደሆነ ያውቁ ነበር። ከዚህም በላይ የዓመጻው ሰው በሰይጣን ኃይል የተሞላ በመሆኑ፥ እርሱን የሚያግደው ከልካይ ከሰይጣን የበረታ መሆን አለበት። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህ ከልካይ በጳውሎስ ዘመን የገነነውና የተራቀቁ የሕግ ሥርዓቶች የነበሩት የሮም መንግሥት ነው ይላሉ። ነገር ግን ከሰይጣን በኃይል የበለጠ ወይም የሚበልጥ መንግሥት አለ? እግዚአብሔር ብቻ ነው ኃይለኛው፤ ስለሆነም ዓመጻን ከሚከላከለው ነገር ጀርባ፥ የኃይል ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር መኖር አለበት። እግዚአብሔር ክፋትን ለማስወገድ ያለጥርጥር በመልካም መንግሥታት፥ በተመረጡ መላእክት፣ በመጽሐፍ ቅዱስና በተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ የርሱ ኃይል ብቻ መኖር አለበት። ብዙ የቅድመ-ፍዳ ዘመን ደጋፊዎች ስለ ዓመጻ ከልካዩ ሲናገሩ፥ ያን የሚሠራው ከሥላሴዎች አንዱ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ነው ይላሉ (ዘፍጥ. 6፡3)። ይሁን እንጂ በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚያመለክተው በትክክል ስለ መንፈስ ቅዱስ ነው ማለት አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ሁኔታዎችን በትክክል ለመግለጥ መቻል አለመቻላችን የቅድመ-ፍዳ ዘመን አመለካከት ደጋፊዎችን የዚህ ምንባብ ክርክር አይለውጠውም። ክርክሩ እንዲህ ነው፡- 

የዓመጻው ከልካይ እግዚአብሔር፥ ዋና መሳሪያውም መኖሪያው የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ናት (ኤፌ. 4፡6፤ ገላ. 2፡20፤ 1ኛ ቆሮ. 6፡19 ይመልከቱ)። ይህችን ጌታ የሚኖርባትንና መለኮታዊ ኃይል የሚሰጣትን ቤት ክርስቲያን “የገሃነም ደጆች አይቋቋማትም” (ማቴ. 16፡18) ሲል ራሱ ተናግሮላታል። ከልካዩ ደግሞ የዓመፅ ሰው ከመገለጡ በፊትና፥ የጌታ ቀን ከመጀመሩ በፊት ሊወገድ ይገባል። ግን ከልካዩ እግዚአብሔር ስለሆነና እርሱም በአማኞች ውስጥ ስለሚኖር፣ ወይ አማኞቹ በፍዳ-ዘመን ውስጥ እንዲያልፉ በምድር በተተዉበት ጊዜ እርሱ ከልባቸው መውጣት አለበት፤ አለዚያም እርሱ ከምድር በሚመጣበት ጊዜ አማኞች ሁሉ ከእርሱ ጋር መነጠቅ አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድም ቦታ ላይ ክርስቲያኖችን እግዚአብሔር ይተዋቸዋል አይልም። ስለዚህ ያለው ብቸኛ አራጭ አማኞች የፍዳው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ከዓለም ይወሰዳሉ የሚል ይሆናል። ይህ ማለት መንፈስ ቅዱስ በዚያን ዘመን አይሠራም ማለት አይደለም። መኖሪያው የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ብትወሰድም ይሠራል። ዓመጻ ከልካይ ኃይል ይወገዳል ማለት፥ እግዚአብሔር ወይም ሥራው በምድር አይኖርም ማለት አይደለም። ብዙዎች በፍዳው ዘመን ይዋጃሉ፥ ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው (ራእይ 7፡14)። ስለዚህ ይህን ክፍል በአግባቡ ከተረጎምነው ቤተ ክርስቲያን ከፍዳው ለምን ቀድማ የምትነጠቅ መሆኗን ያረጋግጥልናል።

ምንጭ፡- “የመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓተ ትምህርት ጥናት”፣ በዶክተር ቻርልስ ሲ. ራይሪ ተጽፎ፣ በሲሳይ ደሳለኝ የተተረጎመ እና በየላፕስሊ/ብሩክስ ፋውንዴሽን የታተመ ነው፡፡ ለዚህ ድንቅ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡ ይህን ጽሁፍ ኮፒ እና ፕሪንት አድርጎ መጠቀም ይቻላል፤ ሆኖም ጽሁፉን መለወጥና ለሽያጭ ማዋል በሕግ የተከለከለ ነው፡፡

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.