መሢሑ ኢየሱስ

ለኢየሱስ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆነው የማዕረግ ስም «መሢሕ» ወይም «ክርስቶስ» የሚለው ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለአይሁድ ሕዝብ በተስፋነት የተሰጠው ይህ መሢሕ ነበር። በብዙ መንገድ ሌሎቹ የኢየሱስ የማዕረግ ስሞች መሢሕ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የበለጠ የሚያብራሩ ናቸው። ሆኖም መሢሕ የሚለው ቃል ትርጉም ምን ማለት ነው? 

1ኛ ጥያቄ፡– ዘፀአት 28፡41 አንብቡ። አሮንና ልጆቹ በተቀቡ ጊዜ ምን ሹመት ተቀበሉ? 2ኛ ጥያቄ፡- 1ኛ ነገሥት 1፡39፥ 45 አንብቡ። ሰሎሞን በተቀባ ጊዜ ምን ሹመት እገኘ? 

3ኛ ጥያቄ፡- 1ኛ ነገሥት 19፡16 አንብቡ። ኤልሳዕ በኤልያስ በተቀባ ጊዜ ምን ሹመት ተቀበለ? 

4ኛ ጥያቄ፡- 1ኛ ሳሙኤል 16፡13 አንብቡ። ዳዊት በሳሙኤል እጅ በተቀባ ጊዜ ምን ሆነ? 

«መሢሑ» የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ «የተቀባው» ማለት ነው። በግሪክ ቋንቋም «ክርስቶስ» ማለት «የተቀባ» ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ሦስት ዓይነት ሰዎች ገና አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው በፊት በዘይት ይቀቡ ነበር። እነርሱም ነቢያት (1ኛ ነገሥት 19፡16፤ መዝሙር 105፡5)፥ ካህናት (ዘፀአት 28፡41፤ 29፡7፤ 30፡30፤ 40፡13-15፤ ዘሌዋውያን 4፡3፤ 8፡12፤ 16፡32፤ 21፡10)፥ እና ነገሥታት (1ኛ ሳሙኤል 10፡1፤ 1ኛ ነገሥት 1፡39፥ 45፣ 19፡16፤ 2ኛ ነገሥት 9፡6፤ 11፡12) ናቸው። የእነዚህ ሰዎች የመቀባት ዓላማ ስእግዚአብሔር ለልዩ እገልግሎት ተመርጠው የተለዩ መሆናቸውን ሁሉም እንዲያውቀው ለማድረግ ነው። ይህ መቀባት፥ እግዚአብሔር ሰወን መርጦ ለመሾሙ ምልክት ነው። እንደዚሁም ሳሙኤል ዳዊትን ስቀባው ጊዜ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን እንዳፈሰሰበት ሁሉ ለአገልግሎቱ በመረጠው ሰው ላይ መንፈሱን በማውረድ ለአገልግሎት የማስታጠቁ ምልክትም ነው 

(1ኛ ሳሙኤል 10፡1፥9፤ 16፡13፤ ኢሳይያስ 61፡1፤ ዘካርያስ 4፡1-14)። በተለይም ነገሥታት በእግዚአብሔር የተቀቡ በመሆናቸው ይታወቃሉ (1ኛ ሳሙኤል 24፡6፥ 10፤ መዝሙር 20፡6)። እንደዚሁም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የመረጣቸው ሰዎች ሁሉ የተቀቡ ተብለውም ይጠራሉ (መዝሙር 28፡8፤ 84፡9)። 

ብዙዎቹ የብሉይ ኪዳን የተለያዩ ክፍሎች ወደፊት መጥቶ በእግዚአብሔር በተለየ መንገድ ስለሚቀባው ሰው ይነግሯቸውና ያመለከቷቸው ስለነበር፥ ሕዝቡ ልዩ ትኩረት ይሰጧቸው ነበር። ከእነዚህ ክፍለ ምንባቦች ውስጥም ባለፈው ሳምንት ያጠናነው መዝሙር 2 አንዱ ነው። ምንም እንኳን ይህ መዝሙር በተወሰነ ሁኔታ የሚመለከተው እግዚአብሔርን ይፈሩ የነበሩትን የብሉይ ኪዳን የይሁዳ ነገሥታትን ቢሆንም፥ አንዳቸውም በመዝሙር 2 ውስጥ የተጠቀሰውን የትንቢት ቃል ሙሉ በሙሉ አልፈጸሙም። ከዚህ የተነሣ የተጻፈውን ትንቢት የሚፈጽም ንጉሥ ይነሣል የሚል ተስፋ በአይሁድ ሕዝብ መካከል እያደገ መጣ። እንግዲህ ይህ ንጉሥ የሚቀባው በመዝሙር 2 ውስጥ እንደተገለጸው ልዩ በሆነ መንገድ በእግዚአብሔር ነበር። እርሱም እስራኤልን ከጠላቶችዋ የሚያድናትና እንዲያውም የዓለም አረማውያን ሕዝቦችንም አጠቃልሎ ከአመራሩ ሥር የሚያደርግ ንጉሥ ነው። 

ሌላው ክፍል ደግሞ ነዳጅ በመስጠት የእስራኤልን ሕዝብ የተስፋ እሳት ያጋጋለው ነው። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲታደግና እንዲያስተዳድር የተቀባ ንጉሥ ይሰጣል። ይህ ክፍልም ዳንኤል 9 ነበር። 

ጥያቄ፡ ዳንኤል 9፡25-26 አንብቡ። ሀ) የሚመጣው ማን የሚመጣውስ መቼ ነው? ሐ) በሚመጣበት ጊዜስ ምን ይደርስበታል? 

ትንቢተ ዳንኤል 9፡25-26 የተቀባው እንደሚመጣ ይገልጻል። የአማርኛው ጥቅስ «መሢሑ» ይመጣል ይላል። ነገር ግን በዚህ ምዕራፍ ውስጥ «መሢሕ» የሚለው የዕብራይስጡ ቃል «የተቀባው» ማለት ነው። እርሱም ከሰባት ሱባዔና ከስድሣ ሦስት ሱባዔ በኋላ ይመጣል። «ሱባዔ» የተባለው የተወሰነ ጊዜን የሚያመለክት ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ክፍል ላይ እንደሚስማሙበት ከሆነ፥ ጊዜው በሰባት ዓመታት የሚተመን ዘመን ነው። ስለሆነም የመጀመሪያው ሱባዔ ሰባት ጊዜ ሰባት ወይም አርባ ዘጠኝ ዓመት ይሆናል። ከአርባ ዘጠኝ ዓመት በኋላ በዕዝራና በነህምያ የተጀመረው ኢየሩሳሌምን መልሶ የመገንባት ሥራ ይፈጸማል። ከሌላ ስድሳ ሁለት ሱባዔ ወይም 434 ዓመታት በኋላ ያ የተቀባው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጣል። ግን ከመጣ በኋላ ይገደላል። አብዛኛዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ትንቢት የሚገነዘቡት መሢሑ እንደሚገደል ቢሆንም፥ በሰባተኛውና በመጨረሻው የሰባት ዓመታት ሱባዔ ትርጉም ላይ ግን አይስማሙም። አንዳንዶቹ ይህ ጊዜ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ወዲያው ተፈጽሞአል ይላሉ። ወይም ሮማውያን እ.ኤ.አ በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ካጠፉ በኋላ ከፍጻሜ ደርሷል ባይ ናቸው። እንዲያውም ሰባተኛው ሱባዔ፥ የመጨረሻው ሰባት ዓመት ገና ወደፊት የሚፈጸም ነው የሚሉ ወገኖች ደግሞ አሉ። እዚህ ላይ ይህን በተመለከተ ምንም ጥያቄ አንሥተን አንነጋገርም (ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሆን የሚችለውን ነጥብ በሌሎች ትምህርተ መለኮት ተከታታይ መጻሕፍት ውስጥ ታጠኑታላችሁ)። እዚህ ላይ የሚገባን፥ የአይሁድ ሕዝብ የሚመጣውን ማለትም ያን የተቀባውን እንዲጠባበቁ በዳንኤል 9፡25-26 እንደ ተነገራቸው ነው። እግዚአብሔር የቀባውን ንጉሥ ልኮ ሕዝቡን እንደሚቤዥ ይህ የትንቢት ቃል፥ እውነትም የአይሁድን ሕዝብ ተስፋ አለመለመው። 

መዝሙር 2 እና ዳንኤል 9 በእግዚአብሔር የተቀባው እንደሚመጣ አመልክተዋል። ኢየሱስ በተወለደበት ዘመን የነበሩ የአይሁድ ሕዝቦች አብዛኞቹን የብሉይ ኪዳን ክፍሎችና በተለይ ስለ ታላቅ ገናና ንጉሥ መምጣት የሚናገረውን ትንቢት ከተቀባው መምጣት ጋር እያዛመዱ ይመለከቱት ነበር። ባለፈው ሳምንት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለዚህ መሢሕ ከሚገልጹ ክፍሎች መካከል በጣም ጠቃሚ የሆኑትን አጥንተን ነበር (ዘፍጥረት 49፡10፥ 2ኛ ሳሙኤል 2፡10-16፤ መዝሙር 2፤ ኢሳይያስ 7፡1-16፤ 9፡1-7፤ 11፡1-5፤ ኤርምያስ 23፡5-6፤ 33፡14-16፤ ሕዝቅኤል 34፡23፤ 37፡24 ሚክያስ 5፡1-4 ዘካርያስ 9፡9)። ይሁንና አይሁዶች ስለሚመጣውና ስለዚያ ስለተቀባው የሚናገሩ ናቸው ብለው የሚያምኑአቸው በርካታ ጥቅሶችም ነበሩአቸው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ንጉሣቸው ሆኖ ሕዝቡን የሚገዛ የዳዊት ልጅ እንደሚመጣ የሚናገሩ ናቸው (መዝሙር 45፡1-7፥ 17፤72} ኢሳይያስ 4፡2፤ 49፡3-11፤ 55፡3፥ 12-13፤ ሆሴዕ 3፡4-5፤ አሞጽ 9፡11-15)። የአይሁድ ሕዝብ እነዚህን ክፍሎች በማጥናት የሚመጣው መሢሕ በጠላቶቻቸው ላይ ድልን እንደሚቀዳጅ፥ እንዲሁም ሰላምን፥ ፍትሕንና ብልጽግናን እንደሚሰጣቸው ይጠባበቁ ነበር። እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለሚመጣው ስለዚያ ስለተቀባው የተነገረውን ትንቢት፥ ነቢይ እንደሚመጣ አድርገው በተስፋ ይጠብቁት ነበር (ዘዳግም 18፡15፣ 34፡10)። እንዲሁም ካህን ሆኖ መምጣቱን ይጠባበቁ ነበር (መዝሙር 110)። በተጨማሪም፥ ይህ የተቀባው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚመጣ ለመግለጽ «የእግዚአብሔር ልጅ» በሚል የማዕረግ መጠሪያም ይጠቀስ ነበር። በሚመጡት ሁለት ሳምንታት ጥናታችን በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ መሢሑ መምጣት የተነገረውን ተስፋ ኢየሱስ እንዴት እንደ ፈጸመ የሚያመለክቱትን የተለያዩ ስሞችና የኢየሱስ የማዕረግ መጠሪያዎች አዲስ ኪዳን እንዴት እንደተጠቀመባቸው እናያለን።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading