መሢሑ እንደ መድኅን 

በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ይጠባበቁ የነበሩት መጥቶ ንጉሥ የሚሆነውን መሢሕ ነበር። የተቀሩት ደግሞ ካህን ወይም ነቢይ የሚሆነውን መሢሕ ነበር። ሆኖም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሥቃይ የሚደርስበት መድኅን እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጉ ነበር። ብሉይ ኪዳን ግን እስራኤልን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው እንደሚመጣ በግልጽ ተንብዮአል። በመሆኑም ስለ ሌሎች ኃጢአት ሥቃይን የሚቀበል እገልጋይ መድኅን መምጣት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከተነገሩትና እጅግ በጣም ግልጽ ከሆኑ ትንቢቶች መካከል አንደኛው የሚገኘው በኢሳይያስ 52 እና 53 ሲሆን፥ ይህንንም ባለፈው ሳምንት ማጥናታችን የሚታወስ ነው። እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ብኢሳይያስ ውስጥ፥ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠበት፥ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነ መድኅን እንደሚመጣና ፍትሕን እንደሚሰጥ ደግሞም ሕይወታቸው የተሰበረውን መልሶ እንደሚጠግን ተመልክተናል (ኢሳይያስ 42፡1-4)። ይህ የእግዚአብሔር አገልጋይም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቀብሎ በመምጣት ወንጌልን እንደሚሰብክና ፈውስንም እንደሚሰጥ ልብ ብለናል (ኢሳይያስ 61፡1-2)። ከዚህም በስተቀር በኢሳይያስ በሌሎች ስፍራዎች የሚመጣው እርሱ መድኅን እንደሚሆን በግልጽ ይናገራል። 

1. የሚሠቃይ መድኅን እንደሚመጣ ብሉይ ኪዳን ተንብዮአል። 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 49፡7፥ 26፤ 60፡16 አንብቡ። በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የእስራኤል አዳኝ ማን ነው? 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 50፡4-10 አንብቡ። በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ በእግዚአብሔር አገልጋይ ላይ ምን ይደርስበታል? 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 55፡1-2 አንብቡ። ሀ) ለሕዝቡ ምን ጥሪ ደረሳቸው? ኢሳይያስ 55፡3-5 አንብቡ። ለ) እግዚአብሔር በማን አማካይነት ተስፋዎቹን ይፈጽማል? ኢሳይያስ 5፡6-7 አንብቡ። ሐ) እግዚአብሔርን ለሚጠሩትና ንስሐ ለሚገቡት ምን ተስፋ ተሰጣቸው? 

ጥያቄ፡- ኢሳይያስ 56፡1-8 አንብቡ። በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ እግዚአብሔር ደኅንነቱን ለእነማን እንደሚሰጥ ነው ተስፋ የገባው? 

ከኢሳይያስ ምዕራፍ 40-66 ድረስ ያለው መልእክት ፍሬ ነገር እግዚአብሔር ለሕዝቡ ደኅንነትን እንደሚያመጣ መናገሩ ነው። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ራሱ የሕዝቡ የእስራኤል አዳኝ እንደሆነ ተገልጾአል (ኢሳይያስ 43፡1-13፤ 49፡26፤ 60፡16)። እንዲሁም ካኢሳይያስ ምዕራፍ 44-66 ያለው ክፍል የእግዚአብሔር አገልጋይ ስለተባለው ሰው ብዙ የሚያስረዳው አለው። አንዳንድ ጊዜ ይህ አገልጋይ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር አንድ ሆኖ ይቀርባል (ኢሳይያስ 43፡10፤ 49፡3)። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከእስራኤል ሕዝብ የተለየ ሆኖ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል፥ በኢሳይያስ 49፡5 ላይ አገልጋዩ የእስራኤልን ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር መልሶ ያመጣቸዋል። በኢሳይያስ ውስጥ በሚገኙ በአብዛኞቹ ክፍሎች አገልጋዩ እንከን የሌለባትን ፍጹሚቱን፥ ለእግዚአብሔርም በመታዘዝ ብዙ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የምትመልሰውን እስራኤልን ይመስላል። በኢሳይያስ ምዕራፍ 40 እስከ 66 እንደተጻፈው አገልጋዩ በተለይ እስራኤልን ወደ እግዚአብሔር መልሶ ያመጣል፥ ደግሞም ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳኑን መልሶ ያጸናል (ኢሳይያስ 55፡3-4)። አገልጋዩ እስራኤልን በማዳኑ ረገድ የእግዚአብሔር ዋነኛው ወኪል ነው (ኢሳይያስ 42፡1-4)። ነገር ግን ይህ ደኅንነት በዋዛ የሚመጣ አይደለም። አገልጋዩ ለእስራኤል ደኅንነትን ለማምጣት ብዙ ሥቃይ ይደርስበታል (ኢሳይያስ 50፡4-9፤ 52፡13-53፡12)። በሚሠቃየው አገልጋይ አማካይነት የሚመጣውን ደኅንነት የሚያገኙት እስራኤላውያን ብቻ አይደሉም፤ አረማውያንና ለእስራኤል ከተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ውጭ የሆኑትም ጃንደረባዎችም ሳይቀሩ የደኅንነቱን በረከት ይቀበላሉ (ኢሳይያስ 49፡6፤ 56፡1-8)። በሚሠቃየው አገልጋይ አማካይነት የሚመጣውን ደኅንነት፥ ጥሪውን አድምጠው የሚቀበሉ፥ ንስሐ የሚገቡና በእርሱ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡት ሁሉ የማግኘት ዕድል አላቸው (ኢሳይያስ 55፡1-7)። 

በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች እግዚአብሔር በኢሳይያስ 42፡1-4 እና 49፡1-7 ውስጥ በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት መሢሑ ደኅንነትን ያመጣል ብለው ይጠባበቁ ነበር። አገልጋዩ የሚያመጣው ደኅንነት እግዚአብሔር ለዳዊት በሰጠው ቃል ኪዳን አማካይነት ይሆናል ብለውም ተስፋ ያደርጉ ነበር (ኢሳይያስ 55፡3-4)። እስራኤላውያን መሢሐቸው ከጠላት ሁሉ የሚያድናቸው ኃያል አዳኝ እንደሚሆን እንጂ ሥቃይን ተቀብሎ ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው መድኅን አድርገው በተስፋ አልተጠባበቁም። ይህም ሆኖ ኢሳይያስ ከምዕራፍ 40–66 ድረስ ባለው ክፍል ደኅነትን የሚያመጣው አገልጋይ ሕዝቡን ከኃጢአቱ ለማዳን እንደሚሠቃይ ደጋግሞ ይናገራል። ስለሆነም ደኅንነት ሊመጣ የሚችለው ስለ ሌሎች ኃጢአት በሚሠቃየው አገልጋይ አማካይነት ብቻ ነው። 

2. ኢየሱስ ለመሠቃየት፥ ለማገልገልና ለማዳን መጣ። 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 1፡21 አንብቡ። መልአኩ፥ ዮሴፍ የማርያምን ልጅ ስም «ኢየሱስ” ብሎ እንዲሰይመው በምን ምክንያት ነገረው? 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 1፡29 አንብቡ፡ ሀ) ዮሐንስ መጥመቁ ኢየሱስን ምን ብሎ ጠራው?። ማርቆስ 10፡45 አንቡ። ለ) ኢየሱስ ምን ሁለት ነገሮችን ሊፈጽም እንደ መጣ ተናገረ? 

መሢሐዊው መድኅን እንደሚወለድ፥ የመጀመሪያው ምልክት የመጣው መልአኩ ለዮሴፍ ተገልጦለት፥ እጮኛህን ማርያምን ውሰዳት ባለው ጊዜ ነበር። መልአኩም ለዮሴፍ ሕፃኑ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ መሆኑን አረጋግጦለት ነበር። ሕፃኑም በሚወለድበት ጊዜ ኢየሱስ ብለው መሰየም ነበረባቸው። «ኢየሱስ» የሚለውም ስም፥ «ያህዌ ያድናል» ማለት ነው። «ኢያሱ» ከሚለው የዕብራይስጥ ለያሜ የተወሰደ ሲሆን፥ የዚህም ትርጉም «ያህዌ ያድናል» ማለት ነው። ይህን ስም በምን ምክንያት አወጡለት? መልአኩ ለዮሴፍ፥ «ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል» ብሎ ነግሮት ስለነበረ ነው። ኢየሱስ ኃያል ንጉሥ ሆኖ የሚገዛና ሕዝብንም ከጠላቶቻቸው እጅ የሚያድናቸው መሢሕ ብቻ አልነበረም። ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድን መሢሕም እንደሚሆን ነበር፤ በኢሳይያስ ቱና 55 ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት ዓይነት መድኅንም ሆኖ መምጣት ነበረበት። 

በዮሐንስ 1፡29 ላይ እንደተጻፈው ዮሐንስ መጥመቁ ኢየሱስን ለተከማቸው ሕዝብ እያመለከተ እንዲህ አለ፥ «እነሆ፥ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።» ዮሐንስ ይህንን ሲል የሰሙት ሰዎች አባባሉ ለመመሥዋዕት የሚቀርቡ በጎችን ሥቃይ የሚያመለክት መስሎአቸው ይሆናል። ምናልባትም ስለ ኢሳይያስ 59፡7 ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት አስበው ይሆናል። በማርቆስ 10፡45 ውስጥ ኢየሱስ የመጣው ለማገልገልና ሕይወቱንም ለብዙዎች ቤዛ ለመስጠት መሆኑን ይናገራል። ይህንንም ሲል በኢሳይያስ ውስጥ ተስፋ የተሰጠበት አገልጋይ እርሱ መሆኑንና በሥቃዩ ብዙዎችን ከኃጢአታቸው እንደሚቤዣቸው መናገሩ ነበር። 

ነገር ገን ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ሲናገሩ ያደመጡዋቸው አገልጋዩ እንዴት በአንድ ጊዜ የሚሠቃይም የሚያድንም እንደሚሆን አልገባቸውም ነበር። ኢየሱስ ከተሰቀለና ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፥ የተሠቃየው መድኅን መሆኑ ግልጽ ሆነ። 

ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 3፡26፤ 4፡27፥ 30 አንብቡ። በእነዚህ በእያንዳንዳቸው ጥቅሶች ውስጥ ጴጥሮስ ኢየሱስን ማን ብሎ ይጠራዋል? 

ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 8፡26=5 አንብቡ። ከብሉይ ኪዳን ውስጥ የትኛው ክፍል ጃንደረባውን ወደ ክርስቶስ ሊያመጣው ቻለ? 

በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስቲያን አማኞቹ ኢየሱስ በኢሳይያስ የተነገረለት አገልጋይ መሆኑን ስለተገነዘቡ «የእግዚአብሔር አገልጋይ» ብለው ይጠሩት ጀመር። ሐዋርያው ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ውስጥ ለሕዝብ ሲሰብክ ከአማኞችም ጋር በሚጸልይበት ጊዜ ኢየሱስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው ይል ነበር። ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ በምድረ በዳ ውስጥ ባገኘው ጊዜ ጃንደረባው ኢሳይያስ 53ን ያነብ ነበር። ይህ ክፍል ደግሞ ስለሚሠቃየው አገልጋይ የሚናገር ክፍል ነው። ጃንደረባውም ይህ የሚሠቃይ ሰው ማን እንደሆነ ለማወቅ ይፈልግ ነበር። ፊልጶስም ወዲያውኑ የሚያነበው ክፍል የሚናገረው ስለ ኢየሱስ መሆኑን አስረዳው (የሐዋ. ሥራ 8፡35)። 

3. ተስፋ የተሰጠው አዳኝ ኢየሱስ እንደሆነ ሉቃስ ያመለክታል። 

3.1 ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መድኅን ነው። 

የሉቃስ ወንጌል ኢየሱስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተስፋ የ ተሰጠበት መሢሐዊው መድኅን መሆኑን ትኩረት ሰጥቶ ጽፎታል። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 168-69 አንብቡ። ዘካርያስ ሲናገር፥ እግዚአብሔር «እስነሥቶልናል» ብሎ ያለው ማንን ነበር? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 2፡11 አንብቡ። መልአኩ ማን ተወለደ ብሉ ተናገረ? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 2፡26፥ 30 አንብቡ። ስምዖን ማንን አየሁ አለ? 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 4፡16-21 እንብቡ። ሀ) ባለፈው ሳምንት በትምህርት አራት ላይ በኢሳይያስ ውስጥ የተማርነውን ትምህርት መለስ ብላችሁ ተመልከቱ። ኢየሱስ ያነበው የነበረው ጥቅስ ከየት ነበር? ለ) ኢየሱስ ይህን ትንቢት የሚፈጽመው ማን ነው አለ? 

ሉቃስ በወንጌሉ ውስጥ እንዳስተማረው ኢየሱስ ብሉይ ኪዳን መጥቶ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ሁሉ ያድናቸዋል ሲል ተስፋ የሰጠበት መሢሕ መሆኑን ይናገራል። 

በሉቃስ 1፡68-69 ውስጥ የመጥምቁ ዮሐንስ አባት ካህኑ ዘካርያስ የዮሐንስና የኢየሱስ መወለድ በዳዊት ቤት «የመዳን ቀንድን አስነሥቶልናል» ይላል። እንዲህ ማለቱም ከዳዊት ቤተሰብ የሚመጣው ወለደ ጊዜ መላእክቱና እንደሚያድናቸውም መመዘም የተነሣ መሢሕ እንደ እንስሳ ቀንድ ጠንካራ እንደሚሆን ነው። ከዚህም የተነሣ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው እጅ እንደሚያድናቸውም መጠቆሙ ነው። ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ መላእክቱ ለእረኞቹ፥ «እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል» አሏቸው። ይህንን ባበሠሩዋቸው ጊዜ ተስፋ የተሰጠበት መድኅን ከዳዊት ቤተሰብ ተወልዷል ማለታቸው ነበር። የኢየሱስ ቤተሰብ እርሱን ለማስገረዝ ይዘውት ወደ ቤተ መቅደስ በሄዱበት ጊዜ መሢሑን ሳያይ እንደማይሞት ተስፋ የተሰጠውን ስሞዖን የተባለ አረጋዊ ሰው አገኙት። እርሱም ኢየሱስን ባየ ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ ይህ ሕፃን መሢሕ ነው አለው። ይህን ጊዜ ሕፃኑን በእጁ ታቅፎ፥ «አሁን መሢሑን አይቻለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ማዳን ተመልክቼአለሁ» ሲል ባረከው። ኢየሱስ አገልግሎቱን እንደ ጀመረ በናዝሬት ወደነበረው ምኩራብ ሄዶ ከኢሳይያስ 61፡1-2 አነበበ። ይህ ክፍል ፍትሕ ያለበት ደኅንነት፥ ነጻነት፥ ፈውስና ለእግዚአብሔር ሕዝብ የሚበጀውን ሁሉ ስለሚያመጣው አገልጋይ የሚናገር ነበር። ከዚያም ኢያሱስ በዚህ ክፍል የተነገረው ሁሉ በዚያኑ ቀን መፈጸሙን ገለጸላቸው። በዚህም ኢየሱስ የተነገረውን ደኅንነት ለመዋጀት የመጣ መሆኑን አበሠራቸው። 3.2 ኢየሱስ በእርሱ የሚያምኑትን ከኃጢአት ሊያድን መጣ። 

ወንጌላዊው ሉቃስ ኢየሱስ መሢሐዊው አዳኝ መሆኑን ብቻ ትኩረት ሰጥቶ አልተናገረም። ነገር ግን ከሁሉ በፊት የመሢሑ ደኅንነት ከኃጢአት የሚፈውስ ደኅንነት መሆኑን ከማስተማሩም በላይ ሰዎች ይህን ደኅንነት ለማግኘት ከፈለጉ በእርሱ ማመን እንዳለባቸው አክሎ አሳስቦአቸዋል። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 1፡26=39፣ 48-50 አንብቡ። ሀ) የኢየሱስን እግር ሽቶ ልትቀሳ መጥታ የነበረችው ሴት በዚህ ክፍል እንዴት ሆና ተገለጸች? ለ) ኢየሱስ ለዚህች ሴት በቁጥር 48 ላይ ምን ዋስትና ሰጠ? ሐ) በቁጥር 50 ይህች ሴት በምን 

ምክንያት ልትድን ቻለች? 

በሉቃስ ምዕራፍ 7 ላይ ተጽፎ የሚገኘው ታሪክ ኃይልን የተሞላ የኃጢአት ይቅርታ ታሪክ ነው። ወደ ኢየሱስ ዘንድ መጥታ የነበረችው ሴት በኃጢአተኝነትዋ የታወቀች ነበረች። ነገር ግን ወደ ኢየሱስ ዘንድ እንደ መጣች እርሱ የእግዚአብሔርን የኃጢአት ይቅርታ ሰጥቶአት ከኃጢአትዋ እንደሚያድናት አመነች። ስለዚህ በፊቱ እንደ ቀረበች ራስዋን በትሕትና ዝቅ አድርጋ በመስገድ በእርሱ እንደምታምን ገለጸች። ኢየሱስም ይህን ተመልክቶ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘትዋን አረጋገጠላት። እርሱም አክሎ ይህን ደኅንነት ያስገኘላት እምነትዋ መሆኑን ገለጸ። በዚህ ታሪክ ውስጥ የምናስተውለው ዋናው ፍሬ ነገር ኢየሱስ ያመጣው ደኅንነት እጅግ ኃጢአተኞች ለሆኑት ሳይቀር የኃጢአት ይቅርታ መስጠት እንደ ነበር ነው። እንግዲህ ከዚህ የምንገነዘበው ማንኛውም የኃጢአት ይቅርታ ዋስትና ማግኘት የሚሻ ሰው የሚጠበቅበት ዋና ነገር በኢየሱስ ማመን ነው። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 19፡1-10 አንብቡ። ሀ) ዘኬዎስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ለ) [ በቁጥር 8 ላይ ዘኬዎስ ምን ዓይነት ቃል ይገባል? ሐ) ኢየሱስ በቁጥር 9 ላይ በምን ምክንያት ነው የከለ ድኖአል ያለው? መ) በቁጥር 10 ላይ ኢየሱስ በምን ምክንያት ወደ ምድር መጣሁ አለ? 

በሉቃስ ምዕራፍ 7 ላይ እንደተጠቀሰችው ኃጢአተኛ ሌት ሁሉ ዘኬዎስም በሕዝቡ ዘንድ ኃጢአተኛ መሆኑ የሚታወቅ ሰው ነበር። ዘኬዎስ ሀብታም ሰው ነበር፥ ግን ያንን ሁሉ ሀብት ያካበተው በማጭበርበር ስለነበረ ሰው ሁሉ ይጠላው ነበር። ሥራውም ግብር መሰብሰብ ነበር። በኢየሱስ ጊዜ በሕዝቡ ለተጠሉ ለሮማውያን አድረው ግብር የሚሰበስቡ አይሁዳውያን ከመደበኛው ግብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲሰጧቸው ሕዝቡን ማስገደድ ልማዳቸው ነበር። ዘኬዎስም ለተጠሉት ሮማውያን ሠራተኛ በመሆኑ፥ ከመደበኛው ግብር በላይ በሥልጣኑ ገንዘብ ይቀበላቸው ስለነበረ አይወዱትም ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ ዘኬዎስን አልጠላውም። እንዲያውም ወደ እርሱ ጠራውና ወደ ቤቱ ሄዶ አብሮት ምግብ በላ። ይህን ሰው ኢየሱስ ስላቀረበው በሠራው ኃጢአት ተጸጽቶ ንስሐ በመግባት ለውሳኔው ማረጋገጫ ይሆንለት ዘንድ አጭበርብሮ የሰበሰበውን ገንዘብ ለመመለስ ቃል ገባ። ወዲያው ኢየሱስ ዘኬዎስ ደኅንነትን ተቀብሏል ሲል ለሕዝቡ ገለጸ። «ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ዘር ነውና።» ኢየሱስ ይህንን ሲል የአማኞች ሁሉ አባት የሆነው አብርሃም እንዳመነው ሁሉ ዘኬዎስም አመነ ብሎ መናገሩ ነው። ዘኬዎስ ኢየሱስ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚሰጠው አምኖ እምነቱን በንስሐው ፍሬ አጸና። 

እንደዚሁም ሉቃስ ከደዌ ሁሉ የሚፈውስ መድኅን መሆኑን አበክሮ ተናግሮአል (ሉቃስ 17፡19)። እንዲሁም አንድ ቀን ፍትሕን፥ ሰላምና ብልጽግናን ለዓለም የሚያመጣ መሆኑንም ጽፎአል (ሉቃስ 4፡16-2)። ነገር ግን የሉቃስ ዋና ትኩረት ኢየሱስ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ባርነትና ከሰይጣን ሰንሰለት ነፃ ለማውጣት መምጣቱን በግልጽ ማስረዳት ነው (ሉቃስ 5፡20፤ 7፡48-50፤ 8፡12፤ 18፡25-26፤ 19፡10)። 

ጥያቄ፡- ሀ) በእናንተ አካባቢ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች እንዴት ያለ አዛኝ ይሻሉ? ለ) የኢየሱስ ደኅንነት አብዛኛዎቹ ሰዎች ከሚሹት ደኅንነት ጋር በምን ይመስላል? ሐ) የኢየሱስ ደኅንነት አብዛኛዎቹ ሰዎች ከሚፈልጉት ደኅንነት በምን ይለያል? መ) ለዎች ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው መድኅን እንደሚያስፈልጋቸው እንዴት አድርጋችሁ ልትገልጡላቸው ትችላላችሁ? 

ዛሬ ብዙ ሰዎች ደስታን፥ ሀብትን፥ ኃይልንና ጤናን የሚሰጣቸውን አዳኝ ይሻሉ። ውስብስብ ያልሆነ ሕይወት ይፈልጋሉ። ከጠላቶቻቸው መጠበቅ ይፈልጋሉ። ሰፊና የተሟላ ቤት፥ ሰፊ መሬት፥ ብዙም ሀብት ይሻሉ። ሁልጊዜ ጤነኞች መሆን ይፈልጋሉ። በሌሎቹ ላይ ሥልጣንን የሚያሰጣቸው የተደላደለ ሥራ ይሻሉ። እንዲህ ያሉ ሰዎች የሚፈልጉት አዳኝ እነዚህን ነገርች ሁሉ ሊሰጣቸው የሚችለውን ነው። 

ኢየሱስ እግዚአብሔር የላከው አዳኝ በመሆኑ ኃጢአትን ድል አድርጎአል። በሰይጣንና በሞት እንዲሁም በሰው ልጆች ጠላቶች ሁሉ ላይ ድልን ተቀዳጅቷል። እርሱ የዚህ ሁሉ ድል ባለቤት በመሆኑ አንድ ቀን ወደ ምድር ተመልሶ ፍጹም የሆነ ሰላምን፥ ብልጽግናንና ጤናን ለተከታዮቹ ሁሉ ይሰጣል። ከዚያም ዓለምን ክፉ ከሆነ ሁሉ የሚያድን መሢሐዊ ንጉሥ ሆኖ ይገዛል። ነገር ግን በዚህ ሳምንት የመጀመሪያው ቀን ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ ገና መንግሥቱን በምድር ላይ አልመሠረተም። ወደዚህ ምድር እስካልተመለሰ ጊዜ ድረስ ፍጹም የሆነ መንግሥቱም አይመጣም። ይህ እስኪሆን ድረስ፥ ከኃጢአታቸው ተመልሰው ንስሐ የሚገቡትንና እርሱ የኃጢአታቸው መድኃኒት መሆኑን የሚያምኑትን ይፈልጋል። ስለዚህ እርሱን የግል አዳኛቸው አድርገው የሚቀበሉት ብቻ ከጠላቶቻችን የሚታደገን ድል አድራጊ መድኅን ሆኖ በዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ የመንግሥቱና የደስታው ተካፋዮች ይሆናሉ። ኢየሱስ በእምነታችን ሳቢያ እኛን ከኃጢአታችን ለማዳን የመጣ ብቸኛው አዳኝ ነው። እኛ ኢየሱስን እንደ ግል መድኃኒታችን የተቀበልንና የኃጢአት ይቅርታን ያገኘን ሁሉ ኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር እንዴት እንደ ለያቸው ለሌሎች ልንመሰክርላቸው ይገባል። ኃጢአታቸው ወደሚመጣው የኢየሱስ የሰላም፥ የጤናና የብልጽግና መንግሥት እንዳይገቡ የሚከለክላቸው መሆኑን ልንነግራቸው ያስፈልጋል። እነርሱም አንድ ቀን የሚመጣው መንግሥት ተካፋዮች ይሆኑ ዘንድ ኢየሱስ ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው መድኅን መሆኑን አምነው ይቀበሉ ዘንድ ልናበረታታቸው ይገባል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

1 thought on “መሢሑ እንደ መድኅን ”

  1. thank so much

    On Wed, 16 Feb 2022 at 13:08, ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

    > tsegaewnet posted: ” በኢየሱስ ጊዜ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ይጠባበቁ የነበሩት መጥቶ ንጉሥ የሚሆነውን
    > መሢሕ ነበር። የተቀሩት ደግሞ ካህን ወይም ነቢይ የሚሆነውን መሢሕ ነበር። ሆኖም ጥቂት ሰዎች ብቻ ሥቃይ የሚደርስበት
    > መድኅን እንደሚመጣ ተስፋ ያደርጉ ነበር። ብሉይ ኪዳን ግን እስራኤልን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው እንደሚመጣ በግልጽ
    > ተንብዮአል። በመሆኑም ስለ ሌሎች ኃጢአት ሥቃይን የሚቀበል እገልጋይ መድኅን መምጣት በብሉ”
    >

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading