በዚህ ሳምንት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ቀናት ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንደ ያህዌ መልአክ ሆኖ ሲገለጥ ተመልክተናል። ይህ መገለጡም በአካል መልክ ነበር። አካሉም የሰውንም የመልአክንም የሚመስል ነበር። በብሉይ ኪዳን ሰውን ወይም መልአክን የሚመስል ሆኖም እግዚአብሔር ተብሎ የተጠራ አካል የተገለጠባቸው ሦስት ሌሎች ጊዜያት ነበሩ። በእነዚህ ክፍሎች ይህ አካል ያየህዌ መልአክ ተብሎ አልተጠቀሰም። ሆኖም እንደ ያህዌ መልእክ፥ ያዩት እርሱ ራሱ እግዚአብሔር መሆኑን ደርሰውበታል። እነዚህ መገለጦችም የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ የለበሰ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ ከመምጣቱ በፊት የሆኑ ናቸው።
ዘፍጥረት 18-19
ጥያቄ፡- ዘፍጥረት 18፡1-5 አንብቡ። ሀ) በቁጥር 1 ላይ የተጠቀሰው፥ ከአብርሃም እንግዶች መካከል አንዱ በመሆን የተገለጸው እንዴት ነበር? ለ) የአብርሃም ሦስቱ እንግዶች በቁጥር 2 ላይ የተገለጹት እንዴት ነበር? ሐ) አብርሃም ለሦስቱ እንግዶቹ ምን አደረገላቸው? መ) ከእንግዶቹ መካከል አንደኛው በቁጥር 10 እንደዚሁም ከቁጥር 13–14 ባለው ላይ ይናገራል። እነዚህ ቁጥሮች እንዴት ይገልጹታል? ሠ) ይህ እንግዳ በቁጥር 13 ላይ ያወቀው ምን ምሥጢር ነበር? ረ) በቁጥር 14 ላይስ ይህ እንግዳ ለአብርሃምና ለሣራ ምን ሊያደርግላቸው ተስፋ ሰጠ? 21ኛ ጥያቄ፡- ዘፍጥረት 18፡16–26 አንብቡ። ሀ) በቁጥር 17 እና 20 ላይ የተጠቀሰው ከአብርሃም ጋር የተነጋገረው እንግዳ የተገለጸው እንዴት ነበር? ለ) በቁጥር 22 ላይ ወደ ሰዶም የሄደው ማን ነበር? ደግሞስ ከአብርሃም ጋር የቀረው ማን ነበር? ሐ) ከአብርሃም ጋር የቀረው እንግዳ በቁጥር 25 እና 26 ላይ የተገለጸው እንዴት ነበር?
ጥያቄ፡- ዘፍጥረት 19፡1-17 አንብቡ። ሀ) አብርሃምን ተለይተው ወደ ሎጥ ዘንድ የሄዱት ሁለቱ እንግዶች በቁጥር 1 ላይ የተገለጹት እንዴት ነበር? ለ) ሁለቱ እንግዶች በቁጥር 5፥ 10፥ 12 እና 16 ላይ የተገለጹት እንዴት ነበር? ሐ) በቁጥር ላይለ ስለ ሁለቱ እንግዶች የተጻፈው እንዴት ነበር?
ዘፍጥረት ምዕራፍ 18-19 ያለው ታሪክ፥ እግዚአብሔር እንዴት አብርሃምን እንደ ጎበኘውና፥ ከዚያም የሰዶምን ከተማ በኀጢአቱ እንዴት እንደ ቀጣው ያብራራልናል። በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች አሉ። እነዚህም እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ ለገባው ቃል ኪዳን ታማኝ ስለ መሆኑ፥ እንደዚሁም እግዚአብሔር ተስፋውን ለመፈጸም ተአምራዊ በሆነ ኀይሉ እንደሚጠቀም፥ ቀጥሎም እግዚአብሔር በጽድቅ ኃጢአትን እንደሚቀጣ በተጨማሪም በኀጢአት የተከበበውን ሕዝብ ለማዳን እግዚአብሔር የሚሰጠው ምሕረትና ጸጋ ናቸው። ወደ እነዚህ ነጥቦች በዝርዝር ከመግባታችን በፊት አብርሃም ዘንድ የመጡት እንግዶች እነማን እንደ ነበሩ ለይተን ማወቅ አለብን።
አንዳንድ ሰዎች በ8ኛው ምዕራፍ ላይ አብርሃምን የጎበኙትን እንግዶች ሦስቱ የሥላሴ አካላት ናቸው ይላሉ። ከዚህ ሻል የሚለው ግንዛቤ ግን ከሦስቱ ሰዎች መካከል አንደኛው ራሱ እግዚአብሔር ነው፥ የተቀሩት ሁለቱ ግን ተራ መላእክት እንደ ነበሩ የሚገልጸው ነው። ዘፍጥረት 18፡1 እግዚአብሔር ራሱ ለአብርሃም እንደ ተገለጠለት ይናገራል። በዘፍጥረት 18፡2 ላይ አብርሃም በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ እያለ፥ አጠገቡ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ ይላል። ሦስቱም እንግዶች ሰዎችን ይመስሉ እንደ ነበር ግልጽ ነው። በወቅቱ አብርሃም ክብር የሚገባቸው እንግዶች መስለው ታዩት እንጂ መለኮታውያን እንግዶች መሆናቸውን ወዲያውኑ አላወቀም ነበር። ከሦስቱ እንግዶች መካከል አንደኛው እግዚአብሔር ለመሆኑ፥ ወይም ሦስቱም ሰዎች ሥላሴ ስለ መሆናቸው ቁጥር 1 እና 2 አይገልጽም።
አብርሃም ለዎ ስቱ እንግዶቹ ምግብ አቅርቦ አስተናገዳቸው። ከዚያም ያህዌ አነጋገረው። ይሁን እንጂ ከሦስቱ አንዱ አብርሃምን ያነጋግረው፥ ወይም ሦስቱም ያነጋግሩት የተብራራ ነገር የለም። ነገር ግን አብርሃምን ያነጋገረው እንግዳ መለኮታዊ እውቀትና ኃይል እንደ ነበረው ግልጽ ነው። በመጀመሪያ፥ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመልሶ ለአብርሃምና ለሣራ ልጅ እንደሚሰጣቸው ተስፋ ገባላቸው። ሁለተኛ፥ ምንም እንኳን ሣራ ለእንግዶቹ ባትታይም፥ ሣራ በድንኳኑ ውስጥ ምን እንደምታስብና ምን እንደምትሠራ ያውቅ ነበር። ያ የተናገረው እንግዳ በግልጽ የእግዚአብሔር የራሱ እውቀትና ኃይል ነበረው።
ሦስቱ እንግዶች ምግባቸውን ከበሉ በኋላ ለመሄድ ተነሡ። ዘፍጥረት ምዕራፍ 18፡16 ላይ እንግዶቹን ሰዎች ይላቸዋል። ስለዚህ የእነዚህ እንግዶች መልክ እንደ ማናቸውም ዓይነት ሰዎች መልክ ይመስል እንደ ነበረ ግልጽ ነው። ነገር ግን፥ በዚህ ሰዓት አብርሃም ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ አስተዋለ። ቁጥር 17፥ 20 እና 22 አብርሃምን በተለይ ያነጋገረው ያህዌ እንደ ነበረ ያስገነዝባሉ። በቁጥር 19 ላይ ደግሞ፥ እንግዳው አብርሃምን ራሱ እንደ መረጠው ይናገራል። እንግዳው በሰዶም ከተማ ላይ ሊወርድ ስላለው ቅጣት ሊናገር አብርሃም በቁጥር 5 ላይ «የዓለም ሁሉ ፈራጅ» ብሎ ጠርቶታል። ስለዚህ በአብርሃም ፊት የቆመውና ከእርሱም ጋር የተነጋገረው፥ እግዚአብሔር ራሱ ነበር።
እንደዚሁም፥ እግዚአብሔር አብርሃምን ለመነጋገር ከአብርሃም ጋር ሲቆይ፥ የተቀሩት ሁለቱ እንግዶች ቀድመው የሄዱ ይመስላል። ቁጥር 22 ላይ ሁለቱ ሰዎች ቀድመው ሲሄዱ፥ አብርሃም እግዚአብሔርን ሊያነጋግረው ከእርሱ ጋር ቆየ ይላል። ዘፍጥረት 19፡1 ደግሞ ሁለቱ መላእክት ሰዶም ደረሱ ይላል። እንደ ዘፍጥረት ምዕራፍ 18 እነዚህ በሰዶም ሎጥን የጎበኙት እንግዶች በተደጋጋሚ ሰዎች ተብለው ተገልጸዋል። ዘፍጥረት 195 ላይ እንግዶቹ፥ ሰዎች ስለመሰሏቸው የሰዶም ሰዎች ከእነርሱ ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሊፈጽሙ ፈልገው ነበር ይላል። ቀጥሎም ቁጥር 10 እና 12 ላይ «ሰዎች» ተብለው ተጠቅሰዋል። ግን ደግሞ ቁጥር 5 መላእክት ይላቸዋል። ማስታወስ ያለባችሁ በተጠቀሱት ስፍራዎች እንግዶቹ «የያህዌ መልአክ» ወይም «እግዚአብሔር» ተብለው አለመለጻቸውን ነው። የተጠቀሱት መላእክት ተብለው ብቻ ነው።
ስለዚህ ስዘፍጥረት ምዕራፍ 18 እና 19 ላይ የተጻፈው የሚሰጠን ግንዛቤ፥ እግዚአብሔር ራሱ አብርሃምን ከጎበኙት እንግዶች መካከል በሰው አምሳል መገለጡን ነው። እንደዚሁም በጉብኝቱ ወቅት የሰዎች አምሳል በነበራቸው ሁለት መላእክት ታጅቦ ነበር። እንግዶቹም ምግባቸውን በልተው እንዳበቁ እግዚአብሔር ራሱ ከአብርሃም ጋር ለመወያየት አብሮት ቆየ። ሁለቱ መላእክት ግን ተለይተው ሎጥን ከጥፋት ለማዳንና ሰዶምን ለመቅጣት ወደዚያ ሄዱ።
አንዳንድ ሰዎች በዘፍጥረት 18፡20-21 ውስጥ ያህዌ ወደ ሰዶም ሄዶ የከተማይቱ ሕዝብ እንደተባለው በጣም ኃጢአተኞች መሆን አለመሆናቸውን የሚመለከት መሆኑን ለአብርሃም ነግሮታል ይላሉ። ቢሆንም በምዕራፍ 18፡22 ላይ ሰዎቹ ወደ ሰዶም ከሄዱ በኋላ ያህዌ ከአብርሃም ጋር ሊወያይ አብሮት ቆይቷል።
አንዳንዶች ወደ ሰዶም የሄዱት ሁለቱም የሥላሴ አካል የሆኑ ያህዌ ነበሩ ሲሉ አሳብ ያቀርባሉ። ይህም የሚነቀፍ አስተያየት ባይሆንም፤ ለክፍሉ አጥጋቢ ማብራሪያ አይመስልም። እንደ ተመለከትነው ሁሉ፥ በምዕራፍ 19፡1 እና በ19፡15 ውስጥ ሁለቱ እንግዶች መላእክት ተብለው ተጠቅሰዋል። (የያህዌ መልአክ ግን አልተባሉም) እንዲያውም በምዕራፍ 18 ላይ አንዱ እንግዳ ያህዌ ተብሎ እንደተጠቀሰው በምዕራፍ 19 ላይ ተለይተው ያህዌ አልተባሉም። እንደዚሁም በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በሰው ቅርጽ የተገለጡበት ሌላ ቦታ የለም። በምዕራፍ 18፡22 የተጻፈው ቃል የሚለው የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች ለኃጢአታቸው አስቸኳይ ቅጣት መቀበል እንደሚገባቸው እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚያውቀውን ይህን ነገር ለማጽናት ከመላእክቱ ጋር በዚያ ተገኘ ብለን ብናጠቃልለው የተሻለ ነው።
ወደ ሰዶም የሄዱትን እንግዶች ማንነት ብዙም ሳንጨነቅበት ከአብርሃም እንግዶች መካከል በእግዚአብሔር መልክ የተገለጠው በተሠገዎ በኢየሱስ ክርስቶስ መልክ ከመገለጡ በፊት የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። በዚህ ሳምንት የመጀመሪያው ትምህርታችን ውስጥ እንደ ተመለከትነው ሁሉ፥ ለሰዎች ተገልጦ እግዚአብሔርን የሚያሳያቸው የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ከአብርሃም ጋር የተመገበ፥ ተስፋውን ጠብቆ ልጅ እንደሚሰጠው ቃል የገባለትን ቃል እንደሚጠብቅ ያረጋገጠ፥ ስሰዶም ላይ ፍርዱ የሰጠና አብርሃምን በምሕረቱ ያጽናናው ቅድመ-ተሠገዎ የተገለጠ የምድር ሁሉ ፈራጅ ክርስቶስ ለመሆኑ አያጠራጥርም።
ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ ምን ምን የክርስቶስ ባሕርያትን ታያላችሁ? ለ) እነዚህ ባሕርያት እንዴት ያጽናኗችኋል ደግሞስ ስለ ምን ያስጠነቅቋችኋል?
በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ ክርስቶስ ራሱን ለአብርሃም በብዙ መንገዶች መግለጡን እንረዳለን። በመጀመሪያ፥ ተስፋን የሚፈጽም አምላክ ሆኖ ራሱን ይገልጣል። በዘፍጥረት 17፡19 ላይ እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለሣራ ወንድ ልጅ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ስለነበረ፥ አሁን ያንን ተስፋ ከፍጻሜ እንደሚያደርስ ሊያረጋግጥላቸው ሊመለስ ይታያል። ሁለተኛ፥ የማይቻለውን ሊያደርግ የሚችል አምላክ አድርጎ ራሱን ይገልጣል። በዚህ ወቅት አብርሃምና ሣራ ልጆች ሊወልዱ የማይችሉ አረጋውያን ነበሩ። ቢሆንም እግዚአብሔር ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከዓመት በኋላ ለሣራ ልጅ ሊሰጣት ቃል ይገባላታል። ይህ የተስፋ ቃል የማይመስል ሆኖ ስለተሰማት ሣራ ለራሷ ሳቀች። በዚህም የሣራ እምነት ደካማ ሆኖ ቢታይና በሰብአዊ አስተሳሰብ ሊሆን የማይችል ቢመስልም፥ እግዚአብሔር ግን የሰጠውን ተስፋ ጠበቀ። ሦስተኛ፥ ከርስቶስ ኃጢአትን የሚቀጣ ፈራጅ አድርጎ ራሱን ይገልጣል። በመሆኑም የሰዶምና የገሞራ ኃጢአት ታላቅ ስለነበረ መቀጣት ነበረበት። ምንም እንኳን ክርስቶስ በፍቅር የተሞላ መድኅን መሆኑ ቢታወቅም ቅዱስና ጻድቅ ፈራጅም ነው። በጽድቅ ይፈርዳል እንጂ ፍርዱን ሳይፈጽም አይቀርም። በመጨረሻም፥ ክርስቶስ ራሱን መሐሪ አዳኝ አድርጎ ይገልጣል። ይህም በሰዶም እሥር ጻድቃን ብቻ እንኳን ቢገኙ፥ ከተማዋን ከጥፋት ሊታደጋት ተስፋ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም እሥር ጻድቃን በመታጣታቸው በኃጢአተኞች መካከል ይኖር የነበረውን ሉጥና ቤተሰቡን ከዚህ ጥፋት አድኖአቸዋል። እንግዲህ ክርስቶስ ምሕረቱን በይፋ ለማሳየትና የሚከተሉትንም ሁሉ ለማዳን ፈቃዱና ውዴታው ነው።
ጥያቄ፡- ክርስቶስ ታማኝና ተስፋውን የሚጠብቅ፥ ሁሉን ቻይ፥ ጻድቅ ፈራጅ እና መሐሪና አዳኝ ሆኖ በሕይወታችሁ ውስጥ አይታችሁታልን? እስቲ ከሁለት እስከ ሦስት የሚደርሱ ምሳሌዎችን ጻፉ፡፡
ዛሬም ቢሆን ክርስቶስ ለእኛ በታማኝነት ተስፋውን ይጠብቃል፤ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደ ተስፋው ቃል አሟልቶ ይሰጠናል። በሚያገኘን መከራ ከቶ አይተወን የገባልንን የተስፋ ቃል ይጠብቃል። ስንጸልይና አእምሮአችንን በቃሉ በምንሞላበት ጊዜ ሰላሙን እንደሚሰጠን ተስፋ ገብቷል። ስለሆነም ክርስቶስ አሁንም ቢሆን፥ ሁሉን ቻይና ጻድቅ ፈራጅ ነው። በቅድስና እንድናድግ ስለሚፈልግ፥ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ይገሥጸናል። ራሱ በመረጠው መንገድና ጊዜ፥ በአካባቢአችን ባሉ ሰዎች ኃጢአትም ላይ ፍርዱን ይሰጣል። ይህ ብቻ አይደለም አንድ ቀን በዓለም ላይ በሚፈርድበት ጊዜ ሁሉን ነገር ልክና ትክክል ያደርጋል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እርሱ በምሕረት የተሞላ አዳኝ ነው። ስለሆነም የዘላለም ደኅንነትን ሰጥቶናል። ኃጢአት ብንሠራና በኃጢአታችን አዝነን ንስሐ ብንገባ፥ ከእርሱ ጋር የነበረንን ኅብረት እንደገና ለማደስ ዝግጁ ነው።
ዘፍጥረት 32
ጥያቄ፡- ዘፍጥረት 32፡24-33 አንብቡ። ሀ) ያዕቆብ ስለታገለው ሰው በቁጥር 24፥25፥ 27 እና 28 ላይ የተገለጸው እንዴት ነው? ለ) ያዕቆብ በቁጥር 28 እና 30 ውስጥ የታገለውስ እንዴት ነው የተገለጸው? 26ኛ ጥያቄ፡- ሆሴዕ 12፡4-5 (በድሮው ትርጉም፥ ሆሴዕ 12፡3-4፥ በአዲሱ ትርጉም) በዚህ ክፍል ውስጥ ከያዕቆብ ጋር ስለታገለው፥ ለፋ ባለ ሁኔታ ምን ተባለ? ቢያንስ ሁለት መልሶችን ጻፉ።
በዘፍጥረት 32 ውስጥ እንደምናነበው፥ ያዕቆብ ከነቤተሰቡና ከመላ ንብረቱ ጋር ወንድሙን ዔሳውን ለመገናኘት ዝግጅት ያደርጋል። ምክንያቱም ያዕቆብ የወንድሙን የዔሳውን ብኩርናና በረከቱን አታልሎ ቀምቶት ስለነበር እርሱንና ቤተሰቡን እንዳይገድላቸው ሠግቶ ነበር። ከዚህ የተነሣ ያዕቆብ ቤተሰቡን ከወንዙ ባሻገር ላከና እርሱ ከወንዙ ወዲህ በአንዱ አካባቢ ቆየ። በዚያ ስፍራ ሌሊቱን አንድ ሰው ታገለው። ዘፍጥረት 32፡24፥ 25፥ 27ና 28 ከያዕቆብ ጋር የተጋለው ሰው እንደነበረ ያስረዳል። ይህ ሰው የተባለ ታጋይ ግን ከሰው በላይ እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህ ከያዕቆብ ጋር የተጋለው ከሰው በላይ ለመሆኑ በመጀመሪያ የተጠቆመው በዘፍጥረት 32፡28 ላይ ሰውየው ለያዕቆብ «ከእግዚአብሔር ጋር ታግለሃል» ብሎ በነገረው ጊዜ ነበር። ይህንም ማለቱ ሕይወቱን በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል እንደ ኖረና በዚያ ወቅትም ቢሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ይታገል እንደ ነበረ ለማሳየት ነው። እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ ወደ ያዕቆብ ዘንድ የመጣው ለሕይወቱ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት ሊሰጠው ነበር። ያዕቆብ በቀድሞ ሕይወቱ ሁሉን ነገር በራሱ መንገድ ለመፈጸም የሚጥር ሰው ሆኖ ቆይቷል። ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር በመግጠም (ዘፍጥረት 28፡20-20፥ የእግዚአብሔርን ዕቅድ በራሱ ፍላጎት አቅጣጫ ለመጠምዘዝ በተደጋጋሚ ሞክሯል (ዘፍጥረት 27፣ 30፡25-43)። በእግዚአብሔር ኃይል ቁጥጥር ውስጥ መሆኑንና ከእግዚአብሔር ጋር ተሟግቶ የእርሱን ዕቅድ ለግል ጥቅሙ የማዋል ዓቅም እንደሌለው ገና አላስተዋለም ነበር። ወደ እግዚአብሔር መጮኽና እርሱን መተማመን ብቻ እንደነበረበት አልገባውም። ስለዚህ እግዚአብሔር፥ እርሱ ሊረዳውና ትምህርት ሊያገኝ ወደሚችልበት ወደ እርሱ መንገድ መጣ። ያዕቆብ ሰዕድሜው ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል እንደ ቆየ ሊያሳየው በሰው ተመስሎ ወደ እርሱ በመምጣት ትግል ገጠመው። እግዚአብሔር ከያዕቆብ ጋር በታገለ ጊዜ፥ ያዕቆብን ለማሸነፍ ልዕለ ተፈጥሮአዊ በሆነ ኀይሉ አልተጠቀመም። ነገር ግን ያዕቆብም እንዲታገለው ለቀቅ ያደርግለት ነበር። የኋላ ኋላ ግን እውነተኛ ኃይሉን ለያዕቆብ አሳየው። የጭኑን ሹልዳ አንዴ በመንካት ብቻ ሽባ አደረገው። እግዚአብሔር የኀይሉን ብርታት ለያዕቆብ ለመግለጽና የእርሱንም ዓቅመ-ቢስነት ለማሳየት አንዴ ብቻ በመንካት አሽመደመደው። ከዚያም ያዕቆብ ሲታገለው የነበረው ሰው ማን እንደሆነ ተረዳ። እናም በሰው ተመስሎ ወደ እርሱ ዘንድ የመጣው እግዚአብሔር ራሱ ነበር። ያዕቆብም በዚያ ጊዜ ምን እንደሚያስፈልገው ላላወቀ ባርከኝ ሲል ጮኸ።
ሆሴዕ 12ትም ከያዕቆብ ጋር ይታገል የነበረው እግዚአብሔር ራሱ እንደ ነበረ የሚያስረዳ ሌላው ክፍል ነው። ምንም እንኳን አንድም በሰው ደግሞም በመልአክ ተመስሎ ቢገለጥም፥ ከዕቆብ ጋር የታገለው እግዚአብሔር ራሱ ነበር። በዘፍጥረት ምዕራፍ 18 ላይ እንደተገለጸው፥ ይህ የእግዚአብሔር በሰው መልክ የመገለጡ ሁኔታ የያህዌ መልአክ ተብሎ አልተጠቀሰም። ነገር ግን ይህ ቅድመ-ተሠገዎ፥ የእግዚአብሔር ልጅ መገለጥ ነበር ሊባል ይችላል። እግዚአብሔር በሰው መልክ ወደ ያዕቆብ የመጣበት ምክንያት ስለ ራሱ ማንነትና እንዲሁም እግዚአብሔር ለእርሱ አስፈላጊው ስለመሆኑ ጠቃሚ ትምህርትን ሊሰጠው ብሎ ነው። ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር በሕይወት ዘመኑ ሲታገል እንደ ቆየና በትግሉም እንዲበረታ የፈቀደለት እርሱ እንደነበረ አስተምሮታል። ነገር ግን በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ እግዚአብሔር የባርኮትን ኃይል በእጁ ውስጥ እንደ ያዘ ነበር። ታዲያ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር በመታገልና፥ እግዚአብሔር እንዲባርከው በማስገደድ ፈንታ፥ በእግዚአብሔር ኀይልና በቸርነቱ ታምኖ እንዲባርከው መማፀን ብቻ ነበረበት።
ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እንዲባርካችሁ ለማድረግ በምን አኳኋን ልታግባቡት፥ ወይም ልታስገድዱት (ልትደራደሩ) ሞክራችሁ ታውቃላችሁ? ለ) በእግዚአብሔር ታላቅ ኀይልና ቸርነት እንዴት አድርጋችሁ ማመን ይገባችኋል?
ብዙ ጊዜ አማኞች በራሳቸው ብቃት በመተማመን በብርታታቸው በረከት ለማግኘት ይጥራሉ። የባል ወይም የሚስት ወይም የልጆችን በረከት በኀይላችን ለማምጣት እንደክማለን። እንደዚሁም በራሳችን ኀይልና መንገድ በትምህርትም ሆነ በልዩ ልዩ ሥራ ስኬታማዎች ለመሆን እንፈልጋለን። በአገልግሎታችንም በራሳችን ጉልበት ስኬታማዎች ለመሆን እንፈልጋለን። አንዳንድ ጊዜም እነዚህን በረከቶች እንዲሰጠን ልናግባባው እንፈልጋለን። እግዚአብሔር የምንፈልገውን ቢሰጠን፥ እኛ ደግሞ በአጸፋው አንድ ነገር እንደምናደርግለት ቃል በመግባት እንለምነዋለን። አንዳንዴ ደግሞ ሁኔታዎችን በማቀናጀት የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት እንጥራለን። ስለዚህ የምንፈልገውን ትምህርት ወይም ባል ወይም ሚስት ለማግኘት ሁኔታዎችን እናመቻቻለን። ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወይም በማቀናጀት ለመጠቀም ስንጥር፥ በእግዚአብሔር በማመን ፈንታ በራሳችን ላይ እንተማመናለን። ክርስቶስ በሰው አምሳል ወደ ያዕቆብ ዘንድ መጥቶ ከእርሱ ጋር የመታገሉ ታሪክ የሚያሳስበን፥ ለሕይወታችን መባረክ በእርሱ ማመን ብቻ እንዳለብን ነው። ከእርሱ ጋር ለመደራደር መሞከር፥ ወይም ሁኔታዎችን አመቻችቶ በረከትን ለማግኘት መሞከር ተገቢ አይደለም።
ኢያሱ 5-6
28ኛ ጥያቄ፡- ኢያሱ 5፡13-5፤ 6፡1-5 አንብቡ። ሀ) ኢያሱ ኢያሪኮ አቅራቢያ ቆሞ ሳለ ማንን አየ? ለ) ቁጥር 5 ላይ ኢያሱ ዓማውን አወለቀ የተባለው ለምንድን ነው? ሐ) በኢያሱ 6፡1-5 ኢያሱን ያነጋገረው ማን ነበር? መ) ኢያሱና የእስራኤል
ሕዝብ ሲታዘዙት ምን እንደሚሰጣቸው ለኢያሱ ቃል ገባለት?
እግዚአብሔር በሰው መልክ የተገለጠበት ነገር ግን ራሱ እግዚአብሔር መሆኑም የተጠቀሰበት ሦስተኛው የብሉይ ኪዳን ክፍል ኢያሱ 5፡13-6፡5 ነው። የእስራኤል ልጆች የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ከነዓን እንደ ገቡ ኢያሱ ወዲያውኑ እስራኤላውያን ሊያጠቋት የተዘጋጁበትን የመጀመሪያ የሆነችውን የኢያሪኮ ከተማ መቃኘቱን ተያያዘው፥ እርሱም ኢያሪኮ ከተማ አጠገብ ቆሞ ሳለ፥ ሰው የሚመስል አንድ ጎልማሳ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በድንገት አጠገቡ ቆመ። ይህ እንደ ማንኛውም ሰው ሆኖ መታየቱ ግልጽ ነበር፥ ምክንያቱም ኢያሱ በመጀመሪያ የጠየቀው የእስራኤል ሠራዊት ወይም የጠላቶቻቸው ሠራዊት መሆኑን ነበር። ሰውየውም የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ነኝ ባለው ጊዜ ኢያሱ ወደ መሬት ወድቆ ሰገደለትና ጌታዬ ምን ልታዘዝ? ብሎ ጠየቀ። የኢያሱም ምላሽ የሚያመለክተው በፊቱ ሰይፍ ይዞ የቆመ ሰው፥ ከተራ ሰው በላይ መሆኑን መገንዘቡን ነው። ይህ የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥም ኢያሱ የቆመበት ስፍራ የተቀደሰ መሆኑን ነገረው። ይህም ሰው እግዚአብሔር ራሱ ለመሆኑ ይህ አባባል ሁለተኛው አመልካች ነጥብ ነው። በመጨረሻም፥ በኢያሱ 6፡2 ላይ ታሪኩ በመቀጠል ያህዌ ራሱ ኢያሱን እንዳነጋገረው ይገልጻል። ለኢያሱ በሰው አምሳል የተገለጠለት የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ እግዚአብሔር ራሱ መሆኑ ግልጽ ይመስላል። ዘፍጥረት ምዕራፍ 18 እና 32 ላይ እንደ ተጻፈውና ከዚያም በፊት በተለያዩ ክፍለ ምንባቦች ውስጥ ለለ ያህዌ መልአክ እንደ ተረዳነው ሁሉ፥ በሰው ተመስሎ የተገለጠው እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ልጅ ቅድመ= ተሠገዎ እውነተኛ መገለጥ ነው ብሎ መደምደሙ የተሻለ ይመስላል።
የእግዚአብሔር ሠራዊት አዛዥ ኢያሱ የኢያሪኮን ከተማ እንዴት ሊይዝ እንደሚችል ዝርዝር መመሪያ ሰጠው። የእስራኤል ልጆች ያልተለመደ ስልት በመከተል የኢያሪኮን ከተማ በሰልፍ መዞር ነበረባቸው፡፡ ይህን የእግዚአብሔርን መመሪያ በመታዘዝ፥ ከተማይቱ በእግዚአብሔር ኀይል ብቻ ልትያዝ እንደምትችል እምነታቸውን ማሳየት ነበረባቸው።
ጥያቄ፡- በራሳችሁ ኀይል በመታመን ፈንታ በእርሱ እንድትታመኑ – የሚያስገድዷችሁ ምን አስቸጋሪ ትእዛዛትን ክርስቶስ ሰጥቶአችኋል?
ኢየሱስ ክርስቶስ ኢያሱንና የእስራኤልን ሠራዊት ይመራ እንደ ነበረ ሁሉ፥ ዛሬም ቢሆን ክርስቶስ የእማኞችን ሕይወት ይመራል። በእርሱ ፍጹም እንዲታመኑ የሚጠይቁ ትእዛዛትን መስጠቱን ይቀጥላል። ሀብትና ንብረታችንን፥ ቤተሰቦቻችንን፥ አገልግሎቶቻችንን፥ ሥራዎቻችንንና ሕይወታችንን ለእርሱ ክብር እንድንሰጥ ያዘናል። እነዚህን ከሕይወታችን ጋር የተቆራኙ ነገሮች አሳልፈን ለክርስቶስ መስጠት ማለት ቀላል ነገር አይደለም። ምክንያቱም ለእርሱ አሳልፈን ሁሉንም መስጠት ማለት እኛ በእነርሱ ላይ የነበረንን ባለቤትነት ማጣት ማለት ነው። እነዚህን ነገሮች አሳልፈን ለእርሱ በምንሰጥበትም ጊዜ፥ በእርሱ ላይ ያለንን ጽኑ እምነት እናረጋግጥለታለን። እርሱም ፈቃዱንና በሕይወታችን ለማከናወን ያቀዳቸውን ታላላቅ ዓላማዎች በመፈጸም ለእምነታችን ምላሽ ይሰጠናል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ