ኢየሱስ የራሱ ሰዎች እንድንሆን ከኃጢአት ዋጀን

ትናንትና በተከታተልነው ትምህርት ክርስቶስ በመስቀል ላይ በፈጸመው ተግባር እግዚአብሔር መልሶ ከራሱ ጋር እንዳስታረቀን አስተውለናል። እኛ ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር ራሱ በእኛና በእርሱ መካከል ሰላምን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ሁሉ አደረገ። ነገር ግን እግዚአብሔር በራሱና በእኛ መካከል በክርስቶስ ሞት ሰላምን ብቻ አላመጣም። እኛን ነፃ አውጥቶ ደግሞም ወደ ራሱ ዋጅቶ መልሶ አመጣን። ይህ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ነፃ አውጥቶ የመቤዥትና መልሶ ወደ ራሱ የማምጣት ሁኔታ «መዋጀት» ይባላል። 

ጥያቄ፡- ሮሜ 3፡24 አንብቡ። ኃጢአተኞች ሰማን አማካይነት እንደሚጸድቁ ተነገረ? 

በሮሜ 3፡24 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሱስ ክርስቶስ በተገኘው ቤዛነት በኩል ኃጢአተኞች እንደሚጸድቁ መረጋገጡን ተናግሮአል። «ቤዛነት» ማለት ዋጋ ከፍሎ አንድን ሰው ነፃ ማውጣት ማለት ነው። ይህ ቃል የሚጠቅመውም ባሪያን በገበያ ሊሸጡና ነፃ ሲለቅቁ ካለው ሁኔታ ነው። እንደዚሁም በጦርነት ጊዜ ተይዘው ምርኮኛ የሆኑ እስረኞችን ዋጋ ከፍሎ ቤዛ ሰጥቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረገውን ተግባር ለመግለጽ በጥቅም ላይ ይውላል። 

ብሉይ ኪዳን የመቤዠትን አሳብ እንድንረዳው ጠቃሚ የግንዛቤ መሠረተ አሳብን ይሰጣል። 

ጥያቄ፡- ዘፀአት 21፡28–30 አንብብ። አንድ በሬ ሰውን ወግቶ ቢገድል፥ የበሬው ባለቤት እንዴት ከሞት ይተርፋል? 

ጥያቄ፡- ዘዳግም 7፡8 አንብብ። እግዚአብሔር እስራኤልን ከምን ዋጀው? 

ጥያቄ፡– ሩት 4፡1-10 አንብቡ። ሀ) ቦዔዝ የሩትን የመጀመሪያ ባል የመሐሎንን የቤተሰብ ስም ለማስጠበቅ ብሎ የኑኃሚን ንብረት ለመቤዠትና ሩትን ለማግባት ምን አደረገ? ለ) ሩት 2፡20 እንብቡ። ኑኃሚን ቦዔዝን ምን ብላ ጠራችው? 

ስለ መዋጀት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ያለው አሳብ ቢያንስ ሦስት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው በዘፀአት 21፡28–30 ተገልጾአል። እግዚአብሔር ሕጉን በሰጠ ጊዜ አንድ በሬ ሰውን ወግቶ ቢገድል፤ በሬውና የበሬው ባለቤት፣ እንደሚገደሉ አዝዟል። ነገር ግን የበሬው ባለቤት ሕይወቱን ለመዋጀት ጉማ (ዋጋ ከፍሎ) ከሞት ሊያተርፍ ይችላል። ስለዚህ የበሬው ባለቤት ጉማ ቢከፍል ወይም የገንዘብ ቤዛ ቢከፍል ከሞት ይድናል። እንግዲህ በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው፥ መዋጀት ማለት ዋጋ ከፍሎ ሕይወትን ማትረፍ ወይም መግዛት ማለት ነው። 

ሁለተኛው «ስለ መዋጀት» የተሰጠው አሳብ በዘዳግም 7፡8 ውስጥ ይገኛል። እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ በኃይሉ ነፃ እንዳወጣቸው ማለትም እንደ ተቤዣቸው ይነግራቸዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ከጠላት ኃይል ነፃ አወጣ፥ አዳነ። ነጻነቱ ስዋጋ ሲተመን እጅግ ውድ ነበር። ነገር ግን ዋጋው ለጠላቱ አልተከፈለም። እግዚአብሔር እስራኤልን ከፈርዖን አልገዛም። የተከፈለው እጅግ ውድ የነበረው ዋጋ የእስራኤልን በኩራት ለማትረፍ በእነርሱ ፈንታ በፋሲካ ዕለት የተሠዉት የበጎች ሕይወት ነበር። ሆኖም ዋጋው ለእስራኤል ጠላት ለፈርዖን አልተከፈለም። በዚህ ክፍል መዋጀት ማለት ዋጋ በመክፈል ከጠላት እጅ ነፃ ማውጣት ማለት ነው። ነገር ግን ዋጋው የተከፈለው ለጠላት አይደለም። 

ሦስተኛው «የመዋጀት» አሳብ የሚገኘው በሩት 4፡1-10 ውስጥ ነው። ሩት ምዕራፍ 4 የሩት፥ የቦዔዝና የኑኃሚን ታሪክ ማሳረጊያ ምዕራፍ ነው። የሩት የመጀመሪያው ባል መሐሎን ሩት ልጅ ሳትወልድ ሞተ። ይህም የሚያሳየው ሩትና ኑኃሚን ለቤተሰባቸው ንብረት ወራሽ አልነበራቸውም ማለት ነው። የቤተሰቡን መሥመር ጠብቆ የሚወርስ አልነበረም። ሆኖም ቦዔዝ የኑኃሚን የመጀመሪያው ባልዋ የነበረው የአቤሜሌክ የሥጋ ዘመድ ነበር። በሩት 2፡20 ውስጥ ኑኃሚን ቦዔዝን «ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው እርሱም ሊቤዠን ከሚችሉት አንዱ ነው» አለች። ምክንያቱም ቦዔዝ የቅርብ ዘመድ በመሆኑ ሊቤዥ ስለሚችል የአቤሜሌክንና የመሐሎንን ንብረት በስማቸው ሊገዛ የተገባ ሰው ነበር። በዚህ ጊዜ ደግሞ ሩትን ያገባታል። እንግዲህ ከቦዔዝና ከሩት ጋብቻ የሚወለዱ ልጆች በሕግ ከአቤሜሌክና ከመሐሎን ዘር እንደ ተገኙ ተደርገው ይቆጠራሉ። እነርሱም የአቤሜሌክንና የመሐሎንን ስም ይዘው፥ የአቤሜሌክንና የመሐሎንን ንብረት ይወርሳሉ፡ ስለዚህ ንብረቱ ከቤተሰብ ውጭ ተሽጦ እንዳይተላለፍ ቦዔዝ ንብረቱን ገዛ፡ ንብረቱን በቤተሰቡ ውስጥ ለማስቀረት ብሎ ገዛው። እዚህ ላይ እንደምንረዳው የመቤዥት ወይም ከፍሎ የማስቀረት ተግባር መፈጸም ያለበት በቤተሰብ አባል ነው። በዚህ ምንባብ መሠረት መቤዥት ማለት የቤተሰብ አባል የሆነ ሰው ዋጋ ከፍሉ የቤተሰብ የሆነው ንብረት ከእጅ እንዳይወጣና ለውርስ እንዲበቃ ማዳን ነው። 

ከእነዚህ ክፍለ ምንባቦች እንደምናጤነው፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ መቤዠት ማዳን ወይም መታደግ ይሆናል። ብዙ ጊዜ ግን ነፃ ማውጣት ወይም ማስለቀቅ የሚፈጸመው ዋጋን በመክፈል ነው። አንደኛው ጊዜ ግን ይህ የመቤዥት፥ ነፃ የማውጣትና የመታደግ ነገር በቤተሰብ አባል ይፈጸማል። እነዚህ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የነበሩ አላቦች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለሚገኘው የክርስቶስ ኃጢአተኞችን የመዋጀት ትምህርት መሠረቱን የሚጥሉ ናቸው፡፡ 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 24፡21 አንብቡ ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ይፈጽማል ብለው ተስፋ አደረጉ? ለህ ይህንን ባሉ ጊዜ ምን ማለታቸው ይመስላችኋል? 

ጥያቄ፡- ገላ 3፡13-14 አንብቡ። ደግሞም ገላ. 4፡4-5 ተመልከቱ። ) ክርስቶስ ከምን ተቤዠን? ለ) ክርስቶስ እንዴት ተቤዥን? ሐህ ክርስቶስ ስለ ተቤዥን ምን ጥቅም እናገኛለን? 

ጥያቄ፡– ኤፈሶን 1፡7 አንብቡ። ሀ) በምን በኩል መቤዠትን እናገኛለን? ለህ ይህን መቤዥት በማግኘታችን ምን እናገኛለን? 

ጥያቄ። ቲቶ 2፡13-14 አንብቡ። ሀ) ኢየሱስ እኛን ለመዋጀት ምንን ለጠ? ለ) ኢየሱስ ከምን ዋጀን? ሐ) መዋጀት ለእኛ ምን ጠቀመን? 

ጥያቄ፡- ዕብራውያን 9፡12 አንብቡ። ክርስቶስ መዋጀትን በምን አገኘ? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥሮስ 18-19 አንብቡ። ሀ) በምንድን ነው ያልተዋጀነው? ለ) በምን ተዋጀን? 

ጥያቄ፡- ማርቆስ 10፡45 አንብቡ። የሰው ልጅ ሕይወቱን የሰጠው ለምንድን ነው? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ጢሞ. 2፡6 አንብቡ። ክርስቶስ ለሰው ሁሉ ምን አደረገ? 

ጥያቄ፡- ራእይ 5፡9-10 አንብቡ። ሀ) ክርስቶስ የፍርዱን መጽሐፍ የመክፈት ሥልጣን እንዴት ተሰጠው (ቁጥር 9)? ለ) የክርስቶስ ድርጊት ውጤት ምን ይሆናል (ቁጥር 10)? 

ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት የአይሁድ ሕዝብ ከሮማውያን እጅ ነፃ የሚያወጣቸው ይሹ ነበር። በሉቃስ 24፡21 የምናገኛቸው ሁለት ደቀ መዛሙርት ወደ ኤማኡስ ይጓዙ በነበሩበት ጊዜ፥ ኢየሱስ እስራኤልን ነፃ እንዲያወጣ ተስፋ እንደ ነበራቸው ይወያዩ ነበር። በዚህም የእስራኤልን ሕዝብ ከርማውያን ጭቆና ነፃ እንዲያወጣና እስራኤልን ነነ መንግሥት አድርጎ እንዲያቋቁም አስበው ነበር። ምናልባትም ዘካርያስና ሐና ስለ ሕፃኑ ኢየሱስ የተነበዩት ትንቢት ተመሳሳይ አሳብን ያዘለ ሳይሆን አይቀርም (ሉቃስ 1፡68፤ 2፡38)፡፡ እነዚህ አይሁዶች ነፃ አውጪው የሚያመጣው ነጻነት በሞቱ አማካይነት መሆኑን አልገመቱም ነበር። ዳሩ ግን ኢየሱስ ያመጣው መቤዠት አይሁዶቹ ከገመቱት ነጻነት የላቀ ነበር። አዲስ ኪዳን በኢየሱስ ስለ ተገኘው መዋጀት የሚሰጠው ትምህርት ምንድን ነው? 

አዲስ ኪዳን በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢየሱስ መቤዠት የሚያቀርበው ትምህርት ክኃጢአት፥ ከኃጢአት ቅጣትና ከክፉ ውጤቶቹ እንዳዳነን ነው። ገላ. 45 ኢየሱስ ከሕግ በታች ያሉትን ዋጀ ይላል። እንደዚሁም ገላ. 3፡13 ከሕግ እርግማን ዋጀን ይላል። የእግዚአብሔርን ሕግ ካለመጠበቃችን የተነሣ የሕግ እርግማን ለእያንዳንዳችን የሚገባ ቅጣት ነበር። የእግዚአብሔርን ሕግ ባለሞጠበቃችን ምክንያት ይደርስብን ከነበረው ቅጣት ኢየሱስ ዋጀን። ኤፌ. 1፡7 በደሙ በተደረገ ቤዛነት የበደላችንን ስርየት የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን ይላል። (እንዲሁም ቆላ. 1፡14 ይመልከቱ፡፡) ቲቶ 2፡14 ደግሞ፥ እኛን ከዐመፅ ሁሉ ሊቤዠን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ሰጠ ይላል። ስለዚህ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በሞተ ጊዜ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ከኃጢአት ቅጣትና ከኃጢአት ክፉ መዘዞች ሁሉ ዋጀ፡፡ 

ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት ብቻ ነፃ አላወጣንም። አዲስ ኪዳን እንደሚያስተምረን ከሆነ የክርስቶስ የመቤዠቱ ሥራ በተጨማሪ እኛን ነፃ አውጥቶ ከበለጸገ ውርስ ጋር የእግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ ለመሆን አብቅተናል። 

በገላ. 3፡14 የክርስቶስ የመቤዥት አንዱ ጥቅም፥ አሕዛብ ለአብርሃም የተሰጠውን የበረከት ተስፋ ተካፋዮች መሆናቸውን ነው ይላል። በተለይም የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ተካፋይ መሆናቸው ላይ ነው። እንዲሁም በገላ. 4፡5፣ «ከክርስቶስ መዋጀት ወይም መቤዠት የተነሣ የልጅነትን ሙሉ መብት ሰጠን» ይላል። በኢየሱስ ለሚያምኑት ሁሉ እግዚአብሔር የእርሱ የሆነው ሁሉ ወራሾች የመሆንን መብት ሰጣቸው በማለት ጽፎአል። በቲቶ 2፡14 ክርስቶስ ከዐመፃ አንጽቶ የራሱ ሕዝብ ሊያደርገን የተቤዠንና የዋጀን መሆኑን ያረጋግጣል። በራእይ 5፡19 ከነገድ ሁሉ፥ ከቋንቋም ሁሉ፥ ከወገንም ሁሉ፥ ከአሕዛብ ሁሉ መንግሥትና ካህናት ሆነው በምድር ላይ ይነግሥ ዘንድ በጉ ዋጃቸው ይላል። በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ዛሬም ሆነ ለዘላለም የበለጸገ ውርስ ባለቤቶች ይሆኑ ዘንድ የክርስቶስ ቤዛነት ሁሉንም ዋጀ ይላል። 

አዲስ ኪዳን ስለ ክርስቶስ መቤዠት የሚያስተምረን ሦስተኛው ቁም ነገር፥ መዋጀቱ እጅግ ክቡር በሆነ ዋጋ ስለ መገኘቱ ነው። 

ኢየሱስ በክቡር ደሙ ገዝተ ተቤዥን። የኢየሱስ የመሥዋዕትነት ሞት በእርሱ የምናምነውን ሁሉ ከኃጢአት፥ ከኃጢአት ቅጣትና ከሚያስከትለው የክፋት ውጤት ሁሉ ተቤዥ+ ነፃ በማውጣት የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆን እንድንበቃና ወራሾችም እንድንሆን አበቃን። በኤፈ. 1፡7 ቤዛነታችንን በክርስቶስ ደም አገኘን ይላል። ቲቶ 2፡14 ደግሞ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ነፍሱን ስለ እኛ ሰጠ ይላል። እንደዚሁም ዕብራውያን 9፡12 ክርስቶስ በደመ ዘላለማዊ ቤዛነትን አስገኘልን ይላል። 1ኛ ጴጥ. 1፡18-19 በክቡር የክርስቲ ደም የተዋጀን መሆናችንን በግልጽ ያስረዳል። እንዲሁም ሐዋርያል በሚያልፍ ነገር፥ እንደ ብርና ወርቅ ባለ ላይሆን ነውርና እድፍ በሌለዉ በክርስቶስ ደም ተዋጃችሁ ይላል። ብርና ወርቅ ጠቃሚዎች ናቸው፤ ከባድ ሀብቶችም ናቸው፥ ነገር ግን በዚህ ዓለም ላይ አላፊና ጠፊ የሆኑ ነገሮች ከኃጢአት ለመዋጀትና ነፃ ለማውጣት አይችሉም። ፍጹም የሆነ የደም መሥዋዕትነት ብቻ ከኃጢአት የመዋጀት ኃይል አለው። ክርስቶስ ተቤዥቶናል፥ ይሁን እንጂ፣ የዋጀን በገንዘብ ሳይሆን በራሱ ደም ነው። ማር. 10፡45 «መዋጀት» በሚለው ቃል አይጠቀምም። የሚጠቀመው «ቤዛ» በሚለው ቃል ሲሆን፥ ክርስቶስ ነፍሱን በቤዛነት ሰጠ ይላል (በተጨማሪም ማቴ. 20፡28ን ይመልከቱ)። ቤዛነት፥ አንድን ሰው ለማስለቀቅ ለማስፈታት) የሚከፈል ዋጋ ነው። ቤዛ ባሪያን ከባርነቱ ለማስለቀቅ ወይም የጦር ምርኮኛን ከጠላት እጅ ለማስለቀቅ የሚከፈል ዋጋ ነው። ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት፥ ከኃጢአት ቅጣትና ኃጢአት ከሚያመጣቸው የክፉ ውጤቶች ሊያስለቅቀንና ነፃ ሊያወጣን ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። 1ኛ ጢሞ. 2፡6 ደግሞ ራሱንም ለሁሉም ሰው ቤዛ ሰጠ ይላል። እንዲሁም ራእይ 5፡9 ክርስቶስ ከወገን ሁሉ በደሙ ዋጀ ይላል። 

የክርስቶስ ደም እንዴት ሊገዛን ቻለ? በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ ዓመታት አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ ለሰይጣን ቤዛ ከፍሉ የተቤዠን ይመስላቸው ነበር። እንደ መሰላቸው ሰይጣን የኃጢአት ምርኮ አድርጎ ስለ ያዘን ክርስቶስ እኛን ከእጁ ነፃ ለማውጣት ቤዛ መክፈል ነበረበት ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ሞት ቤዛነት መሆኑን ቢያስተምረንም። ይህ ቤዛነት የተከፈለው ለሰይጣን ነው ብሎ አያስተምረንም። ኢየሱስ ለሰይጣን ቤዛ ከፈለ የሚለው አስተሳሰብ ለሰይጣን ከፍ ያለ ኃይልና የቁጥጥር አቅም የሚሰጥ ነው። ሰይጣን ከእግዚአብሔር አንዳችን ነገር ለማግኘት የመጠየቅ መብት የለውም። በአንጻሩም ኃጢአተኞች ለሰይጣን የሚከፍሉት ዕዳ የለባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስም ይህንን አያስተምርም። ገላ. 3፡13 ኢየሱስ ስለ እኛ መርገም ሆኖ እንደ ዋጀን ያስተምራል። እንደ ተገነዘብነው ሁሉ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ካለመታዘዛችን የተነሣ ለእኛ ይገባን የነበረውን ቅጣት እርሱ ተሸከመ። ስለዚህ የኢየሱስ ሞት የኃጢአት ቅጣታችንን ከፈለ ለኃጢአት ቅጣት እንዲከፈል የፈለገው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አይደለም። ለእኛ ኃጢአት ቤዛ የሆነውን ዋጋ ኢየሱስ የከፈለው ለእግዚአብሔር ነው። ስለዚህ ኢየሱስ የቤዛነትን ዋጋ ለሰይጣን ከፈለ የሚለው አስተሳሰብ ሐሰተኛና በጣም አደገኛ ትምህርት ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የእኛን ቅጣት ዋጋ በመክፈል ገዝቶናል። 

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተ ጊዜ የእግዚአብሔር ልዩ ሰዎችና ወራሾች እንድንሆን ከኃጢአት፥ ከኃጢአትም ውጤቶች ዋጀን፥ ነፃ አወጣን። የኃጢአታችንን ቅጣት በመክፈል ገዛን፥ በራሱ ደም ለራሱ እንድንሆን ተቤዥን። ሆኖም የክርስቶስ ፍጹም የመቤዥት ሥራ ፍጻ ማ የሚያገኘው ወደ ፊት ነው። 

ጥያቄ ሉቃስ 25-28 አንብቡ። ሀ) ይህ መዋጀት በምን ጊዜ ፍጻሜ ያገኛል በተለይም ቁማር 27 ይመልከቱ)? ለ) ከምንድን ነው መዋጀት የሚያስፈልገን? 

ጥያቄ፡– ኤፌ 4፡30 አንብቡ። ሀ) መንፈስ ቅዱስ ለምን ጉዳይ አተመን? ለ) ኤፌ 1፡13-14 አንብቡ። መንፈስ ቅዱስ የምን ዋስትና ይሰጠናል? 28ኛ ጥያቄ፡- ሮማ 8፡23 አንብቡ። ወደፊት የሚዋጀው ምንድን ነው? 

ክርስቶስ ለሰዎች የሚያደርገው መቤዥት ፥ እርሱ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ይሟላል። በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ከኃጢአትና ከኃጢአትም ክፉ ውጤቶች ያገኙትን መዳን ፈጽሞ ለዘላለማዊ ሕይወት ክብር እንዲበቁ ያደርጋቸዋል። በሉቃስ 21፡5-28 ውስጥ፣ የሰው ልጅ በኃይልና በብዙ ክብር በደመና ሲመጣ ምድርን ከሚሞላው መከራና ሥቃይ ሕዝቡን እንደሚያድን ተስፋ ተሰጥቷል። በኤፈ. 4:0 ክርስቶስ የሚመለስበትና እኛም በፊቱ የምንቀርብበት ቀን «የቤዛነት ቀን» ተብሏል። መንፈስ ቅዱስ የክርስቶስ መሆናችንን በማተም በዚያን ቀን እግዚአብሔር የሚያወርሰንን ለመቀበል እንድንበቃ ይጠብቀናል፥ ይንከባከበናል (ኤፌ. 1፡13-14)። ሮሜ 8፡23 «ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ሰውነታችን በመጨረሻው ፍጹም ይዋጃል» ይላል። ምንም እንኳን ለዘላለም ከተፈረድብን የኃጢአት ቅጣት ነፃ ብንወጣም፥ አሁንም በዚያው ሟች በሆነው በአሮጌው ሥጋችን ውስጥ ነው የምንኖረው። በዚህ ሕይወት ውስጥ እስካለን ድረስ በሥጋ መሞታችን አይቀሬ ነው። በሰውነታችን አሁንም ቢሆን በሥጋ እየሞትን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ ዳግም የማይሞት አካል እንለብሳለን (1ኛ ቆሮ. 15፡50-57)። ከዚያም ሰውነታችን ከሞት ነፃ ይወጣና የክርስቶስ የመቤዠቱ ተግባር ፍጻሜ ያገኛል። 

ክርስቶስ የራሱ ሊያደርገን በራሱ ደም ገዝቶ ከኃጢአት ነፃ አውጥቶናል። ታዲያ የእኛ ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል? 

ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ 6፡19-20 አንብቡ። ሀ) «በዋጋ የተገዛን» በመሆናችን እንዴት መኖር ይገባናል? ለ) ለዚህ ትእዛዝ ምላሽ የምትሰጡባቸውን ሦስት ግልጽ መንገዶች ጻፉ። 

በ1ኛ ቆሮ. 6፡19-20 ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ሊገዛን ከዚህ በኋላ እኛ ለራሳችን እንዳልሆንን ያሳስበናል። አሁን እንግዲህ የእርሱ ነን፡ የእርሱም ከመሆናችን የተነሣ የምንናገረውም ሆነ የምንሠራው ሁሉ እግዚአብሔርን የሚያስከብር መሆን አለበት። ስለዚህ ትምህርትም ሆነ ሙያ በምንመርጥበት ጊዜ ምርግችን ብዙ ገንዘብ ወይም ከፍ ያለ ክብር ለራሳች የሚያስገኝልንን ሳይሆን ከሁሉም በላይ ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመለ ሊሆን ይገባል። የዕለት ሥራችንንም በምናከናውንበት ወቅት አለቃች በሚመለከተን ጊዜ ብቻ ለመሥራት መሞከር ወይም በሌሎች አንደበ፡ ለመመሥገን መሥራት ከእኛ አይጠበቅም። በዚህ ፈንታ ሥራች እግዚአብሔርን ለማስከበርና ለማስመስገን መሆን አለበት። ከጓደኞቻች ወይም ከወዳጆቻችን ጋር ጊዜ በምናሳልፍበት ወቅት በምንናገረው በምንሠራው ሁሉ ግባችን እግዚአብሔርን ለማክበር ይሁን። ክርስቶስ የዋጀንና የገዛን በመሆናችን፥ ካሁን ወዲያ እኛ የራሳችን አይደለንም። ስለዚህ የእግዚአብሔር ስለሆን በምናደርገው ሁሉ እርሱን ማክበር አለብን።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading