ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በደኅንነታችን ውስጥ ስለምናገኛቸው በረከተች ስናጠና ነበርን። በዳንንበት ጊዜ ስላገኘናቸው ብዙ የደኅንነት በረከቶች አጥንተናል። ዳግም በዳንንበት ወቅት፣ እግዚአብሔር በዳግም ልደት አዲስ ሕይወትን ሰጥቶናል። በደኅንነታችን ወቅት በውስጣችን ሊኖር ካመጣው ከክርስቶስ ጋር ኅብረት በምናደርግበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር እኛን ከክርስቶስ ጋር አንድ አድርጎ ያየናል። እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር በማለት ደኅንነትን ባገኘንበት ወቅት፣ ወዲያው መጽደቃችንን አስታውቆልናል። እንደ ልጆቹ አድርጎ በመቀበል ደኅንነትን በሰጠን ወቅት፣ አስደናቂ የሆነ ውርስ እንደሚጠብቀን ተስፋ ሰጠን። እንግዲህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምነን እንደ መድኃኒታችን በተቀበልን ጊዜ እግዚአብሔር እነዚህን ሁሉ በረከቶች ሰጠን።
ዛሬ ደግሞ በደኅንነታችን ወቅት ስለሚሰጠን ስለ አንድ ሌላ በረከት እንማራለን። ይህ በረከትም ቅድስና ነው። እግዚአብሔር በሚያድነን ጊዜ፣ ቅዱስ ሕዝቡ አድርጎ ይለየናል። ሆኖም ይህ የቅድስና ሂደት ሦስት የተለያዩ ደረጃ ዎች አሉት። በአንድ መልኩ ሲታይ፥ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ በደኅንነታቸው ወቅት ቅዱሳን ይሆናሉ። በሌላ መልኩ ሲታይ፥ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ አሁንም ቅዱሳን በመሆን ሂደት ላይ ናቸው። በሦስተኛ ደረጃ ሲታሰብ ደግሞ በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ ከመድረሳቸው በፊት ቅዱሳን አይሆኑም፤ በዚያ ስፍራ ግን ፍጹም ቅዱሳን ይሆናሉ። ነገር ገን በዛሬው ክፍለ ጊዜአችን ስለ ሦስቱ የቅድስና በረከት ደረጃ ዎች እናጠናለን።
1. እውነተኛ የሆኑ አማኞች ሁሉ በአቋም ደረጃ መጀመሪያ በዳኑበት ጊዜ ተቀድሰዋል።
ጥያቄ፡- ክርስቲያን ከመሆናችሁ በፊት ስለፈጸማችኋቸው ኃጢአቶች አስቡ። ከእነዚህ ኃጢአቶች የተነሣ አሁንም ርኩሰት ይሰማችኋል? ይህ ከሆነ በማስታወሻ ደብተሮቻችሁ ውስጥ በክርስቶስ ከማመናችሁ በፊት የፈጸማችኋቸውንና አሁንም ድረስ በደለኞች እያደረጉዋችሁ ያሉትን ኃጢአቶች ጻፉዋቸው።
ክርስቶስን አምነን እንደ ግል መድኃኒታችን ከመቀበላችን በፊት የፈጸምናቸውና አሁን ስናስባቸው የሚያሳፍሩን ኃጢአቶች ሁላችንም : ይኖሩናል። አንዳንድ ጊዜ ስለ እነዚህ ኃጢአቶች እናስብና በእግዚአብሔር , ፊት ራሳችንን አጉድለንና አቆሽሸን እናቀርባለን። ከእነዚህ ኃጢአቶች የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ፊት ጨርሶ መቅረብ እንደሌለብንና ለዚህም የተገባን አለመሆናችን ይሰማናል። ግን እግዚአብሔር በዳንበት ጊዜ አስደናቂ የሆነ በረከትን ሰጥቶናል። እግዚአብሔር ከእነዚያ ኃጢአቶች ሁሉ አንጽተ በፊቱ ቅዱሳን አድርጎናል። እግዚአብሔር የተለየን ንጹሐን ሕዝብ አድርጎ ተቀብሎናል። በጌታ ኢየሱስ በምናምንበትና መድኃኒታችን አድርገን በምንቀበለው ጊዜ እግዚአብሔር በአዘጋጀልን ቅዱስ ስፍራ ያስቀምጠናል።
ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡7፤ 1ኛ ቆሮ. 1፡2፤ ቆላ. 1:2፤ ኤፌ. 1፡1 እና ፊልጵ. 1፡1 አንብብ። ጳውሎስ በእነዚህ በእያንዳንዶቹ ጥቅሶች ውስጥ አማኞችን ምን ብሎ ይጠራቸዋል?
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡30 አንብብ። ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ ምን ሆነ?
ጥያቄ፡- ዕብ 10፡10 አንብብ። የኢየሱስ መሥዋዕትነት ምን ጠቀመን?
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 6፡11 አንብብ። በቆሮንቶስ ስለነበሩ አማኞች እውነት የነበረው ነገር ምን ነበር?
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሚገኙ በርካታ ክፍሎች እንደተገለጸው በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች “ቅዱሳን” ወይም “ቅዱሳን የሆኑ ሰዎች” በመባል ይታወቃሉ። ቅዱሳን የሚባሉት ሰዎች በጾምና በጸሎት ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የለዩ ወይም በተለየ ኃጢአት ላይ አሸናፊዎች የሆኑ ልዩ ሰዎች ብቻም አይደሉም። በክርስቶስ የሚያምኑ አማኞች ሁሉ ቅዱሳን ተብለው ይጠራሉ። ጳውሎስ መልእክቶቹን ወደ ሮሜ ሰዎች (1፡7)፥ ወደ ቆላስይስ ሰዎች (1፡2)። ወደ ኤፌሶን ሰዎች (1፡1)፥ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች (1፡1) እና ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1፡2) በጻፈበት የመጀመሪያ መልእክቱም በእነዚህ ከተሞች በእያንዳንዳቸው ውስጥ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ብሎ ጠርቶአቸዋል። በትክክል በክርስቶስ ያመንና እንደ ግል አዳኙ የተቀበለውና ዳግም የተወለደ ምእመን ሁሉ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል። ቅዱሳን ተብለው ስለ ተጠሩ ዳግም ምንም ዓይነት ኃጢአት አይሠሩም ማለት አይደለም። እንዲህ ማለት፣ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን፥ እግዚአብሔር ወደ እኛ በሚመለከትበት ጊዜ የኢየሱስን ቅድስናና ጽድቅ ስለሚያሳይ ሁላችንም በእግዚአብሔር ፊት ቅዱስ የሆነ ስፍራ ይኖረናል።
«ቅዱስ» የሚለው ቃል «ተለይቶ የተቀመጠ» ማለት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው በምንልበት ጊዜ ካኃጢአትና ተራ ከሆኑ ነገሮች የተለየ ነው ማለታችን ነው። ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛችን በምንቀበለው ጊዜ እግዚአብሔር ለእርሱ የተለየን አድርጎ ያስቀምጠንና፤ ከኃጢአትና ከኃጢአት ጋር ከተያያዙ ነገሮች የተለየን የእርሱ ንብረት አድርጎ ያኖረናል። ይህንን የመሰለውን ስፍራ ነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው በመልካም ሥራችን አይደለም። በ17ኛው ትምህርታችን ውስጥ እንዳየነው፥ ደኅንነታችን ሊመጣ የቻለው ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ነው። እግዚአብሔር ወደ እኛ በሚመለከትበት ጊዜ፣ የኢየሱስን ጽድቅና ቅድስና ያያል። 1ኛ ቆሮ. 1፡30 ኢየሱስ ቅድስናችን ሆነ ይላል። ከኃጢአት ተለይተን የተቀመጥነውና በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳን የሆንነው የኢየሱስ ቅድስና የእኛ ቅድስና ዕለሆነ ነው።
በተጨማሪም፣ ይህ ከኃጢአት ተለይቶ የመቀመጥ ወይም የመገኘት አዲስ ስፍራ ወይም አቋምና ለእግዚአብሔርም የተለዩ የመሆን ሂደት ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘላለም ይቀጥላል። ዕብ 10፡10 ላይ የክርስቶስ መሥዋዕትነት በክርስቶስ እውነተኛ አማኞች የሆኑትን ሁሉ «ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዘ» ቀድሶአቸዋል ይላል። ክርስቶስን እንደ መድኃኒታችን አድርገን በምናምንበት ጊዜ፣ የክርስቶስ የመሥዋዕትነት ደም በእግዚአብሔር ፊት ቀድሶ ለእግዚአብሔር ተለይተን የተቀመጥን ያደርገናል። ይህ ቅዱስ ስፍራ ቋሚ ነው። «ለአንዴና ለመጨረሻ» የሚሆን ነው። ላለፈውም ለወደፊቱ ኃጢአት ይቅርታን አግኝተናል። እግዚአብሔርም በማንኛውም ጊዜ የሚመለከተን ንጹሐንና ቅዱሳን አድርጎ ነው።
አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ የነበራቸውን የቅድስና ስፍራ እንደ ያዙ ይቆያሉ? 1ኛ ቆሮ. 6፡11 እንደ ያዙ እንደሚቆዩ በግልጽ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከመሠረታቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የባለች ኃጢአተኛ ነበረች። በምእመናኑ መካከል ጭቅጭቅና መከፋፈል (1ኛ ቆሮ. 1፡11-12)፣ ዝሙት (1ኛ ቆሮ. 5፡1)፣ እርስ በርስ መካሰስ (1ኛ ቆሮ. 6፡7)። በጌታ እራት ላይ ያላግባብ መብላትና ጠጥቶ መስከርና (1ኛ ቆሮ. 11፡21)፥ በመንፈሳዊ ስጦታ አላግባብ መጠቀም ሁሉ (1ኛ ቆሮ. 14፡26-40) ነበረባቸው። ነገር ግን ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 6፡11 ሲናገር፣ በቆሮንቶስ ያሉ አማኛች ሁሉ ተቀድሰዋል ደግሞም ጸድቀዋል ብሏል። በመጽደቅ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ተብለዋል። በእግዚአብሔር ዘንድ በያዙት ስፍራ አሁንም በመጽደቅ ከኃጢአት ተለይተው ተቀምጠዋል። የኃጢአት ተግባራቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ከነበራቸው ቅዱስ ስፍራ አላስወገዳቸውም። በምትኩ፣ ጳውሎስ ኃጢአትን እንዳይሠሩ ምክንያት የሚሆናቸው በእግዚአብሔር ፊት ያላቸው ቅዱስ ስፍራ መሆኑን ነግሯቸዋል። አማኞች ሁሉ በመጀመሪያ በጌታ ኢየሱስ ባመኑ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሱን ስፍራ እንዲይዙ ተደርገዋል።
አንዳንድ ጊዜ ሰይጣን ወደ እኛ ዘንድ ይመጣና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምነን እንደ መድኃኒታችን አድርገን ከመቀበላችን በፊት ስለሠራነው ኃጢአት ይከስሰናል። በዚህ አጋጣሚ እኛ በዚህ ኃጢአት የረከስንና ንጽሕና የሌለን መሆናችንን እየነገረን፣ ያገኘነውም ደኅንነት ለእኛ የማይገባ መሆኑን በመወትወት ለማዳከም ይጥራል። እንደዚሁም ሰይጣን ባለፉት ጊዜያት ከፈልምናቸው የኃጢአት በደሎች የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ቀርበን በስግደት ልናከብረውና በጸሎት ልንማጠነው እንደማንችል ይነግረናል። ነገር ገን እግዚአብሔር አባታችን በክርስቶስ መሥዋዕትነት ካለፉት ኃጢአቶች የነጻን መሆናችንን ያረጋግጥልናል። ለዚህ ማረጋገጫም በፊቱ ቅዱስ የሆነ ስፍራ ሰጥተናል። ይህ ብቻም አይደለም። ለእርሱ ለይቶ አስቀምጦናል። የመዳናችን አንዱና ታላቁ በረከት እግዚአብሔር በፊቱ የተቀደሰ ስፍራ ስለ ሰጠንና ለራሱ ወስኖ ስላስቀመጠን፣ እኛ በፈለግነው ጊዜ ወደ እርሱ ዘንድ ቀርበን ልናመልከውና ልንጸልይ መቻላችን ነው። በዚህ አኳኋን እግዚአብሔር በፊቱ በሰጠን የቅድስና ስፍራና አክብሮት ወደ እርሱ ዘንድ ቀርበን እንድናመልከው ብርታትን እናገኛለን።
2. እውነተኛ አማኞች ሁሉ በክርስትና ሕይወታቸው ውስጥ በየጊዜው በበለጠ ወደ ተሻለ ቅድስና ደረጃ ይጓዛሉ።
ጥያቄ፡- ዕብ 10፡14 አንብብ። ሀ) የኢየሱስ መሥዋዕትነት ለዘላለም ምን አደረገልን? ለ) አሁንና እዚሁ ምን እየተደረገልን ነው?
ጥያቄ፦ 1ኛ ተሰ. 4፡3 አንብብ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ለእኛ ምንድን ነው?
ጥያቄ- 1ኛ ጴጥ. 1፡14-16 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ምን እንድናደር ጠራን? ለ) እግዚአብሔር ምንን እንዳናደርግ ጠራን? ሐህ ይህንንስ በምን ምክንያት እናደርጋለን?
ማንም በእውነት እንደገና የተወለደ ሰው በእግዚአብሔር ፊት የቅድስና ስፍራን በማግኘቱ ብቻ አይረካም። በእውነት ከልባቸው ኢየሱስን እንደ ግል መድኃኒታቸው አድርገው የሚያውቁት በየዕለቱ በሚያደርጉትና በሚያጋጥማቸው ሁሉ የበለጠ ቅዱሳን ለመሆን ፍላጎታቸው ነው። ይህ የቅድስና ስፍራ በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ወደሚገለጥና ወደሚያድግ ቅድስና ይመራናል። ዕብ 10፡14 አንድ መሥዋዕት የሚቀደሱትን ሁሉ ፍጹማን አደረገ ይላል። ይህ ጥቅስ የተሰጠንን የቅድስና ስፍራና እንደዚሁም በሕይወታችን ውስጥ በተሞክር የሚታየውን አዳጊ የሆነ ቅድስና ይገልጻል። የኢየሱስ ብቸኛ መሥዋዕትነት በእግዚአብሔር ፊት ስፍራችንን ፍጹም ያደርገዋል። በዚህ ሁኔታ በስፍራቸው በእግዚአብሔር ፊት ፍጹማን የሆኑ እነዚሁ ሰዎች በየዕለቱ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድስናን እያግኙ ይሄዳሉ። እነዚህ በእውነት ዳግም የተወለዱ በስፍራቸውም ለእግዚአብሔር ተለይተው የተቀመጡ ሰዎች ከኃጢአት ራሳቸውን በመለየት ቀን በቀን በቅድስና ያድጋሉ።
እንደ ክርስቲያንነታችን አንዱና ዋናው ኃላፊነታችን በየቀኑ ከኃጢአት በመራቅ ራሳችንን ለእግዚአብሔር መለየት ነው። 1ኛ ተሰ. 4፡3 የእግዚአብሔር ፈቃድ እኛ እንድንቀደስ ነው ይላል። በቁጥር 4፡5 ውስጥ ጳውሎስ በመቀጠል ሲናገር፡ ቅዱሳን የምንሆንበት አንደኛው መንገድ ከዝሙት በመራቅና ስሜታችንን በመቆጣጠር መሆኑን ያስነዝባል። አንደኛው ቅድስናን ልናገኝ የምንችልበት ሁኔታ የፍትወተ ሥጋን ፈተና በመቋቋም ነው። ሥጋዊ ምኞታችን በፈተናው እንድንወድቅ በሚገፋፋን ጊዜ እንኳን ጸንተን ስናሸንፍ ነው።
1ኛ ጴጥ. 1፡14-16 በልምምጻችንም ቅዱሳን እንድንሆን ያዝዘናል። ክፉ ምኞታቸውን እንደሚከተሉ የሚያምኑ ሰዎች በመሆን ፈንታ፣ በየዕለቱ በሕይወታችን የትኛውም ዘርፍ የቅድስና ቆብ ሊኖረን ይገባል። የግል ! ቅድስናን በምን ምክንያት እንሻለን? የምንሻበት ምክንያት እግዚአብሔር ‘ ራሱ ቅዱስ ስለሆነ ነው። ጴጥሮስም እግዚአብሔር ወደ ራሱ እንደ ጠራን ይናገራል። የደኅንነታችን ዓላማ ለእግዚአብሔር ተለይተን እርሱን በማምለክ ከእርሱ ጋር አንድነት እንዲኖረን ነው። ነገር ግን ኃጢአትን በመቋቋምና ለእግዚአብሔር ታዛዦች በመሆን ቅድስናን ካላገኘን በስተቀር፣ እግዚአብሔርን ለማምለክና ከእርሱም ጋር አንድነት ሊኖረን አይችልም። እግዚአብሔር ለራሱ ለይቶ አስቀምጦናል። ነገር ግን በልምምዳችን ቅድስናን ካልኖርንበት በስተቀር፣ ለእግዚአብሔር የተለየን እንሆንና በየዕለት ልምምዳችንም በእርሱ ልንረካ አንችልም።
ጥያቄ፡- ሮሜ 12፡1 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር መሐሪ ስለሆነ ምን እንድናደር ታዝዘናል? ለ) ሮሜ 12፡2 አንብብ፡፡ ምንን እንድናደርግ እና ምን እንዳናደርግ ታዝዘናል?
ጥያቄ፦ ቆላ. 3፡16 አንብብ። ምንን እንድናደርግ ታዝዘናል?
ጥያቄ፡– ኤፌ 5፡18 አንብብ። ምንን እንድናደርግ ታዝዘናል?
ጥያቄ፡- ገላ. 5፡16፥ 22-23 አንብብ። በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ብንኖር ምን እንሆናለን?
በክርስቶስ አማኞች እንደ መሆናችን በልምምዳችን እንዴት ቅዱሳን ለመሆን እንችላለን? በዚህ ሁኔታ ማንም ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ቅድስናን ሊያገኝ አይችልም። ቅድስናን መለማመድ መላ የሕይወት ዘመንን ይወስዳል። ቅዱስ መሆን ማለት ራስን ለመንፈስ ቅዱስ አስገዝቶ ቀን በቀን በዕድገት ሂደት መጓዝና በበለጠ ክርስቶስን መምሰል ማለት ነው። በትምህርት 12 ውስጥ እንደተመለከትነው፥ ክርስቲያኖች ሁሉ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ እንኳን ኃጢአትን መሥራት አያቋርጡም። በተጨማሪ እንደተመለከትነውም፥ ክርስቶስን በትክክል እንደ ግል መድኃኒታቸው አድርገው የተቀበሉትና ዳግም በመወለድ በእግዚአብሔር ፊት የጸደቁ ሁሉ በሕይወታቸው ሁሉ በቅድስናና በጽድቅ ያድጋሉ። በቅድስና ማደግ ቀላል እርምጃ አይደለም። ሆኖም ለዚህ አንዳንድ ጠቃሚ መመሪያዎች አሉ።
2.1 በቅድስና ለማደግ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር መስጠት አለብን።
በልምምዳችን በቅድስና ለማደግ የመጀመሪያው መርህ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። ሮሜ 12፡1 ሰውነታችንን ሕያው መሥዋዕት አድርገን ለእግዚአብሔር እንድናቀርብ ይነግረናል። በመሆኑም በማወቅና በመረዳት አእምሮአችንን፥ ፈቃዳችንን፥ ውሳኔያችንን፥ ተግባራችንን፡ ማለትም በሕይወታችን ውስጥ ያለንን ሁሉ ለእግዚአብሔር መስጠት አለብን። ክርስቲያኖች ሁሉ ኢየሱስ የሕይወታቸው ጌታ መሆኑን ሊቀበሉና ሕይወታቸውንም ለዚህ ጌታ ሊያስገዙ ይገባል። የብሉይ ኪዳን አማኞች እግዚአብሔርን ለማምለክ በሚመጡበት ጊዜ እንስሳ አምጥተው በመሠዊያው ላይ በመሠዋት ለእግዚአብሔር በሕይወታቸው የተገዙና የእርሱ መሆናቸውን እንደሚያሳዩ ሁሉ፥ እንዲሁም የአዲስ ኪዳን አማኞች በተመሳሳይ መንገድ በተምሳሌታዊ ሁኔታ ራሳቸውን በመሠዊያው ላይ ማድረግ አለባቸው። አንድ ሰው፥ «የሕያው መሥዋዕት ችግር በየጊዜው ከመሠዊያው ላይ ለመውረድ መቻሉ ነው» ብሏል። አሁንም ቢሆን የኃጢአት ተፈጥሮ አለብን፥ ደግሞም ኃጢአትን የመሥራት ዝንባሌም ይታይብናል። ስለዚህ ምንም እንኳ ራሳችንን ሕያው መሥዋዕት አድርገን ለእግዚአብሔር ብንሰጥም፥ እንደገና ተመልሰን ሕይወታችንን በመቆጣጠር የራሳችን ልናደርግ እንችላለን። ስለዚህ ራሳችንን ለእግዚአብሔር መስጠት ሲባል አንድ ጊዜ ብቻ በሕይወታችን ውስጥ ፈጽመን የምንተወው ነገር አይደለም። ሁልጊዜ፥ በየሰዓቱና በየደቂቃው ልናደርገው የሚገባን ተግባራዊ ግዴታ ነው። ባለማቋረጥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነት ራሳችንን አሳልፈን
መስጠትና እንደ መሥዋዕት ማቅረብ አለብን።
ጥያቄ፡- አሁኑኑ ራሳችሁን ለእርሱ ጌትነት በማስገዛትና ሕይወታችሁን ለእርሱ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ በማቅረብ ለተወሰነ ጊዜ በጸሉት ቆዩ።
2.2 በቅድስና ለማደግ አእምሮአችንን በእግዚአብሔር ቃል በመሙላት በእግዚአብሔር እሴቶች የተሞላ እንዲሆን ማድረግ ይገባናል።
በሮሜ 12፡2 ውስጥ ራሳችንን ለእግዚአብሔር በምንሰጥበት ጊዜ የአካባቢአችን ዓለም ወደ ራሱ እንዳይወስደን ያስጠነቅቀናል። ስለዚህ ራሳችን ለእግዚአብሔር እንድንሰጥ ካስፈለገ የማያምኑ ሰዎችን የሕይወት ፈለግ ተከትለን በዚያ መመራት የለብንም። የዓለም እሴቶችና ቀደምት ነገሮች የእኛም እሰቶችና ቀደምት ነገሮች መሆን አይኖርባቸውም። ይህን ትተን በየቀኑ አእምሮአችንን ማደስ ይገባናል። በእግዚአብሔር እሰቶችና ቀደምት ነገርች አእምሮአችንን በመሙላት ልናድሰው እንችላለን። በየቀኑ፥ በየሰዓቱና በየደቂቃው በጸሎት አእምሮአችንን በእግዚአብሔር አሳብ መሙላት አለብን። እንደዚሁም የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብና በቃል በማጥናት፥ ስለ ቃሉም ቀኑን ሙሉ በማሰብ አእምሮአችንን መሙላት አለብን፡ ቀላ 3፡16 የእግዚአብሔር ቃል በሙላት በእኛ እንዲያድርና አንዳችን ሌላውን በጥበብ እንድናስተምር፥ እንድንመስር፥ በመዝሙርና በውዳሰ እንድንሆን ይመክረናል። በእግዚአብሔር ቃል አእምሮአችንን እየሞላን መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብና ቀኑን ሙሉ ስላነበብነው በመነጋገርና በመዘመር በቅድስና እናድጋለን።
ያለጥርጥር መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ማጥናትና እያንዳንዱን ክፍል በቃል ማስታወስ አለብን። ሆኖም፣ በቅድስና እንድናድግ በተለየ ሁኔታ የሚያግዙን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። የመጀመሪያው ክፍል ወንጌል ነው። ወንጌላት የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ያሳዩናል። አእምሮአችንን በክርስቶስ ሕይወት በምንሞላበት ጊዜ ሕይወታችን ይበልጡኑ እንደ እርሱ ሕይወት ይሆናል፣ በቅድስናም እናድጋለን። ሁለተኛው ልዩ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባ ክፍል መልእክቶች ናቸው። መልእክቶች የተጻፉት ክርስቲያኖች እንዴት አድርገው ቅድስና ያለው ሕይወት ሊኖሩ እንደሚችሉ ለማስተማር ነው። ስለዚህ ቅዱሳን ለመሆን አብዛኛውን የመልእክቶች ክፍል ማንበብና ማጥናት ይገባናል። እነዚህም የምናነባቸው ክፍሎች ሮሜ 6-8 እና 12-15፥ ኤፌ 4-6፥ ቆላ 2፥ ገላ. 5-6፥ መላው የ1ኛ ጴጥሮስ መልእክት፥ መላው የያዕቆብ መልእክት፥ መላው የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ናቸው። እነዚህ የመልእክት ክፍሎች በየዕለቱ በልምምጻችሁ በቅድስና እንዴት ማደግ እንደምትችሉ ይነሩዋችኋል።
ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔርን ቃል የምታነቡበት መደበኛ ጊዜ አላችሁ? ስለአለፈው ሳምንት መለስ ብላችሁ አስቡ። የእግዚአብሔርን ቃል ስንት ጊዜ አነበባችሁ? ላ) ቀኑን ሙሉ ለለ እግዚአብሔር ቃል ታላላላላላችሁ? ሙሉውን ቀን ስለ እግዚአብሔር ቃል ይበልጥ አዘውትራችሁ ለማሰላሰል እንድትችሉ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
እያንዳንዱ አማኝ እእምሮውን ስእግዚአብሔር ቃል እንዲሞላ በየቀኑ የጸሎት ሰዓትና የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ጊዘ ያስፈልገዋል። ነገር ቀን አእምሮአችንን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በክርስቶስ ቃል መሙላት አይበቃም። አእምሮአችንን በክርስቶስ ቃል፡ ሰዓት በለዓት፥ ደቂቃ በደቂቃ መሙላት አለብን። ታዲያ አእምሮአችንን እንዴት ይበልጥ አዘውትረን በክርስቶስ ቃል መሙላት እንችላለን? ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅሶችን በመውሰድ በምንሄድበትም ሆነ ሰው በምንጠብቅበት ጊዜ በአእምሮአችን ውስጥ በቃል ልናጠና ወይም መላልሰን በቃል ልንፈታተማቸው እንችላለን። እንዚሁ የተለያዩ ጥቅሶችን በትንንሽ ካርዶች ላይ በመጻፍ በቤታችን ወይ በሥራችን ቦታ በሚታዩን ስፍራዎች ልናስቀምጣቸው እንችላለን። ከክርስቲያን ወገኖች ጋር ተገናኝተን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አብረን ልናጠና እንችላለን። ከዚህም በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በዜማ አቀናብረን ዝቅ ባለ ድምፅ ቀኑን ሙሉ ለራሳችን ልንዘምራቸው እንችላለን። እንግዲህ በዚህ ረገድ አእምሮአችንን በምንሞላበት ጊዜ ቅድስናችን በእግዚአብሔር እለቶችና የእርሱ በሆኑ ቀደምት ነገሮች አእምሮአችን ስለሚታደስ ቀኑን ሙሉ በቃሉ ቅድስና በውስጣችን ለማደግ አመቺ ይሆንለታል።
2.3 በቅድስና ለማደግ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሞላት አለብን።
በቅድስና የማደግ ሦስተኛውና አስፈላጊ መርህ በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መሞላት ነው። ኤፈ. 5፡18 በወይን ጠጅ እንዳንሰክር ወይም በወይን ጠጅ ቁጥጥር ሥር በመሆን ፈንታ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ ያሳስበናል። ለመሆኑ በእዚአብሐር መንፈስ ቅዱስ መሞላት ማለት ምን ማለት ነው? በመጀመሪያ በመንፈስ መሞላት ሊባል በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ሥር መሆን ማለት ነው። አንድ ሰው በሚሰክርበት ጊዜ በወይን ጠጅ ቁጥጥር ሥር መሆንን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ከመሆን ጋር ያነጻጽራል። አማኞች በምንም ነገር ቁጥጥር ሥር በመሆን ፋንታ በመንፈስ ቅዱላ ቁጥጥር ሥር መሆን ይገባቸዋል። ሁለተኛ፥ በመንፈስ የመሞላት ጉዳይ በማንኛውም አማኝ ሕይወት ውስጥ በተደጋጋሚ የሚገባ ልምምድ ነው። ጳውሎስ በዚህ በኤፌ 5፡18 መልእክቱ ላይ «ተሞሉ ሲል የአሁን ጊሸን ይጠቀማል፡ በሌላ አገላለጽ “በተደጋጋሚ ጊዜያት፡ ያለማቋረጥ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ሁኑ” እንደ ማለት ነው። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ስለ ተዋሉ ሰዎች ሁኔታ ብናጠና፥ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ከተለወጡ በኋላ ብዙ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተዋል (የሐዋ. ሥራ 2፡4፤ 4፡31፤ 6፡5፤ 7፡55፤ 9፡17፤ 13፡9)። ስለዚህ በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ሲባል ከዳንን በኋላ አንድ ጊዜ ተከስተ የሚያቀም ድርጊት አይደለም። በመሆኑም በተከታታይ ጊዜያት መፈጸም አለበት፡፡
በመንፈስ ቅዱስ እንዴት እንሞላለን? ሂደቱን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የምንከተላቸውን ደረጃዎች ዝርዝር አይሰጠንም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው በአጭሩ በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር መሆን እንዳለብን ነው። እንደዚህ ማለት የሚያስገነዝበን ፈቃዳችንን በእያንዳንዱ ቀን በሚገኙ ደቂቃዎች ሳይቀር ለእርሱ አሳልፈን እንድንሰጥ ነው። አላባችንን በሙሉ ለእርሱ አሳልፈን መስጠት አለብን፡ አንድ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ውሳኔያችን አሳልፈን ለእርሱ መስጠት ይገባናል። ተባራችንን ሁሉ ለእርሱ አሳልፈን መስጠት አለብን። ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ መጸለይ እንዳለብን ባይነግረንም፥ ራሳችንን አሳልፈን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ጸሎት ድንቅ የሆነ መንገድ ነው። ስለዚህ በቀን ብዙ ጊዜ በዚህ አቅጣጫ መጸለይ ይገባናል። ጸሎታችንንም «ኦ! መንፈስ ቅዱስ እኔን ተቆጣጠር፡ ውሳኔዎቹን ሁሉ ተቆጣጠር፥ ተቀባሪንም ተቀጣጠር አሳቤን ሁሉ ተቀጣጠር፥ ሙላኝ፥ ደግሞም ተቆጣጠረኝ” በማለት ሊቀርብ ይችላል። ሐዋርያት በሐዋ. 4፡23-31 እንዳደረጉት ክርስቶስን ለማገልገል ስንነሣና ለክርስቶስ ባለን አቋም የተነሣ ችግርች ሊከሰቱ ሲሉ፥ በዚህ ሁኔታ ላይም መንፈስ ቅዱስ እንዲሞላን በተለይ መጸለይ እንዳለብን እኔ አምናለሁ።
ገላ. 5፡16፥ 22-23 ያለው ክፍል እንደሚነግረን፣ ሕይወታችን በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር በሚሆንበት ጊዜ የኃጢአት ምኞታችንን አንከተልም፡፡ ይልቁንም መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን የመቆጣጠሩን ውጤት (ፍሬ) ማሳየት እንጀምራለን። በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር በምንሆንበት ጊዜ አፍቃሪዎች፥ ለሌሎች ሰዎች ትሑታንና ራሳችን የምንዝ እንሆናለን፡ በሌላ አነጋገር መንፈስ ቅዱስ ሲሞላንና ሲቆጣጠረን፥ ያኔ የቅድስና ሕይወትን እንኖራለን።
ጥያቄ፡- የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት የሕይወታችሁን የትኛውን ክፍል ለመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር አሳልፋችሁ መስጠት ትሻላችሁ?
3. እውነተኛ አማኞች ሁሉ በሰማይ ፍጹም ቅዱሳን ይሆናሉ።
ጥያቄ፡– ኤፌ 5፡26-27 አንብብ። ቤተ ክርስቲያን ወደ ክርስቶስ ፊት ስትቀርብ ምን ትመስል ይሆን?
ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐ 3፡2 አንብብ። ኢየሱስ በሚገለጥበት ጊዜ ማንን እንመስላለን?
ጥያቄ፡- ዕብ. 12፡14 አንብብ። ሀ) ምንን መከታተል ወይም በምን ላይ ማተኮር አለብን? ለ) ጌታን ለማየት ምን ያስፈልጋል?
በዚህ ዓለም ውስጥ ባለው ሕይወቱ ዘመን ፍጹም ቅዱስ የሚሆን አማኝ አይኖርም። ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠን ተስፋ መሠረት እርሱ ወዳለበት ወደ ሰማይ ስንደርስ ፍጹም የሆነ ቅድስናን እንጎናጸፋለን። ኤፌ. 5፡26-27 ያለው ክፍል፣ በመጨረሻው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሆና ወደ እርሱ ዘንድ እንደምትቀርብ ይገልጽልናል። ስለዚህ በዚያን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን «እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር» አድርጎ በፊቱ ያቀርባታል ይላል። በጋብቻቸው ቀን ሙሽራዋ አምራና ተውባ በሙሽራው ፊት እንደምትቀርብ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያንም ጌታ ወዳለበት የዘላለምን ጅማሬ አሃዱ ለማለት በምትገባበት ጊዜ ከኃጢአት የነጻችና ለክርስቶስ ፍጹም ተለይታ የተጠበቀች ሆና ትቀርባለች። 1ኛ ዮሐ 3፡2 ኢየሱስ ስሚገለጥበት ጊዜ እኛም እንደ እርሱ እንሆናለን ይላል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ በመጨረሻ እኛም እንደ እርሱ ፍጹም ቅዱሳን እንሆናለን። ዮሐንስ እንደሚለው፣ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ቅዱሳን እንደሚሆኑ፣ ይህ እርግጠኛ ዋስትና ያላቸው ሁሉ «ራሳቸውን ላአሁንና ለዘላለም ያነጻሉ»። በዚህ ሕይወትም በቅድስና ያድጋሉ። በሚመለስበት ጊዜ የሚመስሉትን ጌታ ኢየሱስን በበለጠ በልምምዳቸው እየመሰሉ ይሄዳሉ። ወደ ፊት ስለምናገኘው ፍጹም ቅድስና ያለን መተማመን አሁን በልምምጻችን ቅድስና እንድናሳይ ይቀሰቅሰናል።
ዕብ 12፡14 የአሁኑን ቅድስናና የወደፊቱን ቅድስና በማያያዝ ያቀርበዋል። ጸሐፊው የሚያስታውሰን ቅዱሳን የሆኑት ብቻ ጌታን እንደሚያዩት ነው። ሐዋርያው የሚናገረው ወደ መንግሥተ ሰማይ በምንገባበት ጊዜ ስለምናገኘው ፍጹም ቅድስና ነው። ምንም ዓይነት ኃጢአት ፍጹም ወደሆነው የሰማዩ ጌታ ዘንድ ሊደርስ አይችልም። በሞታቸው ጊዜ ወይም ክርስቶስ ሲመለስ እግዚአብሔር ፍጹም ቅድስናን የሚሰጣቸው ብቻ እግዚአብሔር ወዳለበት ይገባሉ። ከዚህ ፍጹም ቅድስና በስተቀር ማንም እግዚአብሔርን ሊያይ አይችልም። ይህንን ቅድስና እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ብቻ ከእርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራሉ። ስምንሞትበት ጊዜ ወይም ኢየሱስ በሚመለስበት ወቅት እግዚአብሔር የሚሰጠን ይህ ፍጹም ቅድስና ዛሬ እዚሁ እያላን ቅድስናን አጥብቀን እንድንከታተል ያበረታታናል። ወደፊት ቅዱሳን ስለምንሆን አሁንም ቅዱሳን መሆን ይገባናል። አሁን በቅድስና እያደጉ ያሉ ጌታ በሚሰጣቸው ፍጹም ቅድስና እርሱን ለማየት የሚችሉት እነርሱ ናቸው። በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ጸሐፊው ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሁሉ አባባላቸው እውነት መሆኑን ለክርስቶስ የታመኑ በመሆን ማስመስከር እንዳለባቸው ይናገራል። እንደዚሁም በዕብ. 12፡14 ባደረገው ማሳሰቢያ በዚህ ሕይወት የቅድስና ሕይወትን በመኖር በኋላ ፍጹምነት ያላቸው ቅዱሳን ሆነው ጌታን ማየት የሚችሉ መሆናቸውን ዛሬውኑ ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይናገራል።
ጥያቄ፡- ክርስቶስን እንደ መድኅናችሁ ተቀብላችሁት ከሆነ አንድ ቀን እግዚአብሔር ፍጹም ቅዱሳን ሆናችሁ እርሱ ባለበት እንድትኖሩ ያደርጋችኋል። አሁን ባላችሁበት ሕይወት በየትኛው የሕይወታችሁ ዘርፍ የቅድስና ልምምዳችሁ አናሳ ሆኖ ይታያችኋል? እግዚአብሔር አንድ ቀን ፍጹም ቅዱሳን እንደሚያደርጋችሁ ለማሳየት አሁን ባላችሁበት ሕይወት ዘቅድስና ለማደግ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?
እምነታችን በክርስቶስ መሆኑን የምንገልጽ ክርስቲያኖች ሁላችንም አሁንም ቢሆን ኃጢአተኞች ነን። ነገር ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር ወዳለበት ስምንገባበት ጊዜ ምን ዓይነት ሰዎች እንደምንሆን ለዓለም ለማስመስከር እንድንችል እግዚአብሔር የግል ቅድስና ሕይወታችንን እንድናሳድግ ይፈልጋል። ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር በመስጠትና አእምሮአችንን በቃሉ በመሙላት፥ እንደዚሁም በመንፈስ ቅዱስ በመሞላት ቀስ በቀለ የአርጌው ኃጢአታዊ ተፈጥሮአችን አካል የሆኑትን ቁጣን፥ ትዕቢትን፥ ምቀኝነትን፥ ሥጋዊ ምኞትን፥ የሀብት ምኞትን ምሬትን፡ ሐሜትን አለመታመንና ራስ ወዳድነትን ማስወገድ እንችላለን። በዚህ ኢየሱስን ይበልጥ እየመሰልን በመሄድ ወደ መንግሥቱ ስንገባ ፍጹም እርሱን ወደ መምሰል እንደርሳለን።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ