የዘላለማዊ ዋስትና ማረጋገጫ እና የእግዚአብሔር ቅዱሳን ጽናት፥ ክፍል 1 

በክርስቲያኖች መካከል የሚነግ አንደኛው አስቸጋሪና አከራካሪ የሆነ ርእሰ ጉዳይ፥ እውነተኛና ዳግም የተወለዱ አማኞች ደኅንነታቸውን ይዘውት ይቆያሉ ወይስ ያገኙትን የሚያጡበት ሁኔታ ይኖራል? የሚለው ነው። / ማንኛውም ክርስቲያን በአንድ ወቅት ክርስቶስን አምነው የተቀበሉና ኋላ ግን ይህን እምነታቸውን የተዉ ሰዎችን የሚያውቅ ይመስለኛል። አብዛኛዎቹ እማኞች አንድ ጊዜ መልካም የክርስትና አካሄድ የነበራቸውና ኋላ ላይ በኃጢአት ውስጥ ከመውደቃቸው የተነሣ ያንን የመልካም ሕይወት አኗኗርን የማይኖሩ ሰዎች ያውቃሉ። ከዚህ የሕይወት ገጠመኝ የተነሣ፣ ብዙ ሰዎች በአንድ ወቅት ድነው ይዘውት የነበረውን ሕይወት በሌላ ጊዜ ከኃጢአታቸው የተነሣ ወይም በክርስቶስ ማመናቸውን ስለሚያቆሙ፥ የተቀበሉትን ደኅንነት ያጣሉ የሚለውን አሳብ መቀበሉ ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን በትናንትናው ትምህርታችን ላይ እንደተከታተልነው ሁሉ፥ ሌላውን የደኅንነቱን በረከቶች የሚቀበሉትን ሁሉ ክብርን እንደሚቀበሉ እግዚአብሔር ተስፋ ይሰጣል፡ ምንም እንኳን ደኅንነታቸውን ያጡ የሚመስሉ ሰዎችን የምናውቅ ብንሆንም፥ እኛ መደምደሚያ ልናደርገው የሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ትምህርት እንጂ የግል ተሞከሮአችንን ወይም ወንዛቤአችን ሊሆን አይገባም፡ አማኞች ስላላቸው ዋስትና ወይም መተማመኛ+ እንደዚሁም የክርስትና ሕይወታቸውን በማራመድ ረገድ ስላላቸው ጽናትና የመንፈስ ብርታት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? ስለሆነም በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ውስጥ ስለ እነዚህ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጣቸውን መልሶች እንመረምራለን። 

ጥያቄ፦ ሮሜ 4፡22-25፤ 5፡1-2፥ 6፥8-10 አንብቡ። ሀ) ጽድቅ ለማን ተሰጠ? (ሮሜ 4፡22-25) ለ) በእምነት ከጸደቅን ምንን እናገኛለን? (ሮሜ 5፡1) ሐ) በእምነት ከጸደቅን ትርፋችን ምን ይሆናል (ሮሜ 5፡2)? መ) ለዘላለም ሕይወት ያለን ተስፋ በምን ምክንያት አያሳፍረንም? (ሮሜ 5፡5) ሠ) ከቁጥር 8-10 በተጻፈው መሠረት፥ ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዴት እንደምንድንና የዘላለምን ሕይወት እንዴት እንደምናገኝ አብራራ? 

1. አማኞች ለዘላለም ዋስትና አላቸው፥ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር የታረቁ መሆናቸው ስለ ታወቀና ከእርሱም ጋር ሰላም ስላላቸው ነው። 

ባለፈው ትምህርት 18 ላይ አስደናቂ ስለሆነው የጽድቅ ደኅንነት በረከት አጥንተን ነበር። በዚሁ ወቅት ሰዎች ክርስቶስን እንደ መድኃኒታቸው አምነው ሊቀበሉ፥ እግዚአብሔር ከበደላቸው ነፃ መሆናቸውን እንደሚያሳውቅ ተገንዝበናል። እግዚአብሔር እነዚህ ሰዎች ከእርሱ ጋር የታረቁ መሆናቸውን በይፋ ያሳውቃቸዋል። በኢየሱስ ባላቸው እምነት፥ እግዚአብሔር የኢየሱስን ጽድቅ ጽድቃቸው አድርጎ ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ይህ በኢየሱሰ ጽድቅ ላይ የተመሠረተ ጽድቅን የሚሰጣቸው ላለፈው ኃጢአታቸው ብቻ ሳይሆን፥ ለሠሩት ኃጢአት ሁሉ ነው፡፡ ሮሜ 5፡1-2 እግዚአብሔር አማኞች ከእርሱ ጋር ታርቀው ኅብረት መመሥረታቸውን ስለ ገለጠ፥ ከአሁን ወዲያ ከእርሱ ጋር ሰላም አላቸው ይላል። በእምነት ከእርሱ ጋር ለታረቁት፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ መስቀል ላይ የተጠቀመበትን የማስታረቅ ተግባር እዚህም በሥራ ላይ ያውላል። ስለሆነም አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ሰላም፥ ለወደፊቱ ለሚያገኙት ዘላለማዊ ሕይወት ተስፋን ይሰጣቸዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ተስፋ» የሚለው ቃል አሳብ መተማመን ወይም ዋስትናን ያመለክታል። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን እርቅ ቀደም ሲል የታወቀ በመሆኑ፥ ለዘላለም ዓለም እግዚአብሔር ባለበት እኛም እንደምንሆን ለትናው የተረጋገጠልን ነው። 

ጳውሎስ በሮሜ 5፡8-10 ውስጥ፥ ጽድቅ ለዘላለማዊ ደኅንነታችን ማረጋገጥ እንደሚሰጠን ሰፋ አድርጎ በዝርዝር ይጽፋል። እኛ በእግዚአብሔር ላይ ያመጽን ኃጢአተኞች ሆነን ሳለን፥ እግዚአብሔር ጻድቃን አድርጎ እኛን በመቀበል ከእርሱ ጋር ሰላም እንዲኖረን ሲያደርግ፥ ይህን ተግባሩን ከፍጻሜ በማድረስ የዘላለምን ሕይወት እንደሚሰጠን እርግጠኛች ነን። በእነዚህ ሦስት ጥቅሶች ውስጥ፥ ሐዋርያው ጳውሎስ በሁለት ሐረጎች ተጠቅሞ ክርስቶስ ስለሞተላቸው ሰዎች ገልጾአል። በቁጥር 8 ውስጥ ኃጢአተኞች ነበርን ይላል። እንዲህ ሲል እኛ ሕጉን ስላፈረስን ከመንገዱ ወጥተን የትም ስንቅበዘበዝ ነበርን ማለት ነው። ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችን ምክንያት፥ ከእርሱ የምንጠብቀው ምንም መልካም ተግባር እልነበረም። በቁጥር 10፣ ሐዋርያው የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ ነበርን ይናገራል። እንዲህ ማለት በእግዚአብሔር ላይ በግልጽ በማመፃችን፥ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ጦርነት ነበር ማለት ነው። ያም ሆኖ፣ እኛ ደካሞች፥ ሕግ አፍራሾችና ጠላቶቹ ሳለን፥ ክርስቶስ ለእኛ ምን አደረገልን? ለእኛ ሲል ሞተ! ስለዚህ ድርጊት ጳውሎስ ሲጽፍ በመገረም ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ለሌላው ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት የመሞት ድርጊት ያልተለመደና ብርቅ ስለሆነ ነው። ለጠላቱ ሲልሶ የሚሞት ማን ነው? ለበደለውስ ራሱን አሳልፎ ለሞት የሚሰጥ እረ ማን ነው! ነገር ግን እግዚአብሔር በእርሱ ለሚያምኑት ያደረገው ይህን ነው። 

በቁጥር 9 እና 10 ውስጥ ጳውሎስ ነገሩን ሲያጠቃልል፥ «እግዚአብሔር ጠላቶቹ ለነበሩ ለኃጢአተኞች ያደረገውን ተመልከቱ» ይላል። ኢየሱስ ሞቶአል፥ የእርሱም ደም የኃጢአትን ቅጣት ከፍሎአል። እግዚአብሔርም በፊቱ ጻድቃን አድርጎ ተቀብሎአቸዋል። እንደዚሁም ከእነርሱ ጋር ሰላምን መሥርቷል። በዚህም ወዳጆቹ አድርጓቸዋል። ኢየሱስ አሁን ይህን ግንኙነት ጠብቆ ለዘላለም ይኖራል። እንግዲህ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ካደረገ፥ እነዚህ ኃጥአን የነበሩ ሁሉ፥ በፍርድ ቀን የእግዚአብሔር ቁጣ አይወርድባቸውም። ክርስቶስ በመጨረሻው ጊዜ ፍጹም የሆነ ደኅንነትንና የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ነን። አንድ ክርስቲያን ደራሲ እነዚህን ጥቅሶች በሚከተለው ሁኔታ አጠቃሎአቸዋል፡ «እግዚአብሔር አስቸጋሪ የነበረውን ነገር አስቀድሞ ያደረገ ከሆነ፥ ማለትም የመጨረሻ ኃጢአተኞችን የሚያጸድቅ ከሆነ፥ አስቀድሞ በፊቱ ጻድቃን አድርጎ የተቀበላቸውን ከቁጣው እንደሚያድናቸውና እንደሚያጸድቃቸው ያላንዳች ጥርጥር ልናረጋግጥ እንችላለን።» 

አንድ የተከሰሰ ሰው ፍርድ ቤት ውስጥ እንደ ቆመ ገምቱ። ከዚያም ዳኛው ይህን ችሎቱ ፊት ቆሞ ያለውን ሰው ከተከሰሰበት ወንጀል ነፃ መሆኑን በይፋ ያሳውቃል። እዚያው ችሎቱ ውስጥ የነበሩ ዘመድ ወዳጆቹ ይህን ሊሰሙ ብድግ ብለው ያቅፉትና ደስታቸውን ይገልጹለታል። ከዚያም ዛኛው ሰውዬውን አሁን ነፃ ስለሆንክ ልትሄድ ትችላለህ ይለዋል። ሰውዬውና ዘመድ ወዳጆቹ አብረውት ከፍርድ ቤቱ ወጥተው ይሄዳሉ። ነገር ግን በፍርድ ቤቱ በር ላይ ዘብ ቆሞአል። ታዲያ ይህ ነፃ የወጣው ሰው ዘቡን አልፎ መውጣት ይፈራልን? ዘቡ አቁሞ ይዞ ወደ እሥር ቤት እንደሚመልሰው ሰግቶ ይፈራ ይሆን? በፍጹም አይፈራም! ቀደም ሲል ዳኛው በደል እንደሌለበት የገለጸ ስለሆነ ምንም ጥርጥር አያድርበትም። ደግሞም ነፃ ስለሆነ በልበ ሙሉነት በበሩ ወጥቶ ወደፈለገው ሊሄድ ይችላል። 

ለእኛ በክርስቶስ ላመንነው ዳኛው ከማንኛውም በደል ነፃ መሆናችንን አስታውቋል። ይህ መግለግ በመጨረሻ ከተሰጠ በኋላ ከፍርድ ቤቱ ወጥተን ለመሄድ የሚያሠጋን ምንም ምክንያት አይኖርም፡ ሞትንም ሆነ ወይም የመጨረሻውን በእግዚአብሔር የሚሰጥ ፍርድ መፍራት አያስፈልገንም። ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም እንዲኖረን ያደርጋል። እግዚአብሔር በመጨረሻው ጊዜ ለሚሰጠን የዘላለም ሕይወት የማረጋገጥ ዋስትና ይሆናል። ስለዚህ ደኅንነታችን የታመንና የተረጋገጠ ነው።

2. እግዚአብሔር ሁልጊዜ የጀመረውን ሥራ ስለሚፈጽም የአማኞች ሁኔታ ለዘላለም የተረጋገጠ ነው። 

ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡30 አንብብ፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ለመረጣቸው፥ ለጠራቸውና ላጸደቃቸው ምን ተዘጋጅቶላቸዋል?

ጥያቄ፡- ፊልጵ. 1፡6 አንብብ። ጳውሎለ እርጠኛ የሆነው ስለ ምንድን ነው? 

በሮሜ 8 ውስጥ ጳውሎስ በሮሜ 5 ውስጥ የጀመረውን አሳብ ይቀጥላል። እግዚአብሔር ቀደም አድርጎ ከበደል ወይም ከወንጀል ነፃ መሆናችንን አሳውቆልናል፡ እግዚአብሔር የሚጀምረውን ሥራ ሁልጊዜ ከፍጻሜ ያደርሳል። በትምህርት 15 ላይ እንደ ተመለከትነው፥ የእግዚአብሔር የማዳን ተግባር የተጀመረው በራሱ ምርግና ጥሪ ነው። ትናንትናም በርማ 8፡30 ውስጥ እንደ ተከታተልነው፥ ጳውሎስ ሲናገር፥ አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፥ የጠራቸውንም አጸደቃቸው ብሏል። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅን ያገኙ ሁሉ ክብርን አግኝተዋል። በእግዚአብሔር ዓይን፥ ዘላለማዊው የደኅንነታቸው ክብርም አሁኑኑ ተረጋግጧል! በእርግጥ ዳግም የተወለዱ ክርስቲያኖች ወደፊት እንድን ይሆንን ብለው ሊሠጉ አይገባም። እግዚአብሔር እንደሚለው፥ በጽድቅ አማካይነት በደላቸውን ሁሉ ይቅር ካላቸው፥ አስቀድሞ በሰማይ ክብርን አዘጋጅቶላቸዋል። እንደ እግዚአብሔር አደራረግ፥ ሥራውን ለጀመረላቸው ሁሉ የደኅንነት ተግባርን አስቀድሞ ጨርሶላቸዋል። ከእርሱ ጋር የታረቁ መሆናቸውን ካሳወቀ፥ ዘላለማዊው ደኅንነታቸው ልክ አስቀድመው ዘላለማዊ ክብርን እንዳገኙ ያክል የተረጋገጠላቸው እውነታ ነው። 

በእውነት ዳግም በተወለዱ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር የጀመረውን ሥራ እንደሚፈጽም የሚያስተምረን ሌላው ጥቅስ ፊልጵ. 1፡6 

ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ክርስቲያኖች ሲያበረታታቸው በሕይወታቸው ውስጥ የደኅንነት ሥራ የጀመረው አምላክ «እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን» የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጥላቸዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ቀን የሚባለው ክርስቶስ ወደ ምድር የሚመለስበት ቀን ነው። እንደዚሁም ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር እግዚአብሔር አንድ ጊዜ የደኅንነት ተግባሩን በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ መሥራት ሊጀምር፥ እስከ ዘላለም ዓለም መጀመሪያ ድረስ ዘልቆ ይፈጽማል ይላል። ስለዚህ ክርስቶስን እንደ አዳኝ ተቀብለው ወደ እርሱ ዘንድ የሚመጡ ዘላለማዊ ደኅንነታቸው ተረጋግጦላቸዋል። 

3. አማኞች ለዘላለም ደኅንነታቸው ተረጋግጦላቸዋል፥ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉ ስለሆኑና በእርሱም የታተሙ በመሆናቸው ነው። 

ጥያቄ፦ ሮሜ 8፡16-17 አንብብ። ሀ) መንፈስ ቅዱስ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ምንን ይመሰክራል? (ቁጥር 16) ለ) ከማን ጋር ወራሾች እንሆናለን? (ቁጥር 17) ሐ) ወራሾች ሆናችን ምንን ያረጋግጥልናል? (ቁጥር 17) 

ጥያቄ፡– ኤፌ. 1፡13-14 እንብብ። ሀ) በአመንን ጊዜ በምን ታተምን? ለህ እንደ ቁጥር 14 መንፈስ ቅዱስ ምን ያደርግልናል? 

ጥያቄ፡– ኤፌ. 4፡30 አንብብ። መንፈስ ቅዱስ ለምን ሊል አተምን? 

በሮሜ 5፡5 ላይ እንደ ተገነዘብነው፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ስለ ሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የዘላለም ሕይወትን የመውረሱ ተስፋ አያሳፍረንም፡ እግዚአብሔር የዘላለም ሕይወትን እንደሚሰጠን በእውነት ተስፋን ሰጥቶናል። ለዚህም አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስን አፍስሶብናልና ነው። እያንዳንዱ እውነተኛ እማኝ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎአል። የዚህ መንፈስ በልባችን ማደር እግዚአብሔር ሥራውን የሚፈጽም ስለመሆኑ ማረጋገጥ ነው። 

በሮሜ 8 ውስጥ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ መኖር እግዚእብሔር የዘላለም . ሕይወትን እንደሚሰጠን ማረጋገጥ ነው ይላል። ስለዚህ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን ይቀበላሉ (ሮሜ 8፡9)፣ በእኛ ውስጥ ያለው መንፈስ ከእግዚአብሔር መንፈስ ጋር እውነተኞች የእግዚአብሔር ልጅነታችንን ይመሰክራል። ክርስቶስን አምናችሁ እንደ አዳኛችሁ ከተቀበላችሁ፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በውስጣችሁ ያድራል፣ የእርሱ በእናንተ ውስጥ አድሮ በእውነት የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችሁን ያሳስባችኋል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን፥ የሰማዩን የከብር ውርስ ተካፋዮች ነን። በትምህርት 17 ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን፥ የውርሱ ተከፋዮች መሆናችንን አስተውለናል። እንደዚሁም በውስጣችን የሚኖረው መንፈስ ቅዱስ፥ በደኅንነታችን ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን፥ የክርስቶስ ዘላለማዊ ክብር ውርስ ተካፋዮች እንደምንሆን ያረጋግጥልናል። 

መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን በመኖሩ ዘላለማዊውን ደኅንነታችንን ያረጋግጥልናል፥ ደግሞም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንንም ይመሰክርልናል። ይህ በውስጣችን የሚኖር መንፈስ፥ ማኅተማችንና የመጪው ደኅንነታችን ዋስትናም ነው። ኤፌ. 1፡13-14 እና 4፡30 ይህንን የመንፈስ ቅዱስ በረከትን ሁኔታ ይገልጻል። እንዲሁም በኤፌ 1፡13 ውስጥ አውሉላ ሊናገር፥ ማንም ሰው በክርስቶስ እንዳመነ ወዲያውኑ በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ይታተማል ይላል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ እኛ ዛሬ እንደምናደርገው ደብዳቤ በፖስታ ውስጥ ታሽጎ አይላክም ነበር። ደብዳቤ ለመላክ የሚፈልገው ሰው ከጻፈ በኋላ ያንን ይጠቀልልና በትኩስ ሰም ያሽገዋል። በዚህ ትኩስ ሰም ላይ ማኅተሙን በመጫን የላኪው ሰው ማኅተም ይታተምበታል። ማኅተሙ ሁለት ዓላማዎች ነበሩት። አንደኛው፥ ደብዳቤው ለተላከለት ሰው እስኪደርሰው ድረስ እንዳይከፈት ይጠብቀዋል። ሁለተኛው፥ ማኅተሙ ደብዳቤው ከማን እንደ ተላከ ያመለክት ነበር። ጳውሎስም መንፈስ ቅዱስ ይህንን መሰል ተግባር በአማኞች ላይ እንዳለው ነው የገለጸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር በሚሰጠን ደኅንነት ውስጥ እንድንኖር ያደርጋል፥ ቀጥሉም እኛ የእግዚአብሔር መሆናችንን ያመለክታል። ኤፈ. 4፡30ም ይህንኑ የማኅተም ሁኔታ በመድገም፥ የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም «ለቤዛ ቀን» እንደሚሆነን ይነግረናል። የቤዛ ወይም የደኅንነት ቀን እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፊት የምንቆምበትና ወደ መጨረሻው የዘላለም ሕይወት የምንገባበት ቀን ነው። መንፈስ ቅዱስ እውነተኛና ዳግም የተወለደ እማኝን ጠብቆ ለዚያ ቀን ያበቃዋል። በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ ጠብቆና ማንነታችንን ለይቶ ለዚያ ጊዜ የሚያደርሰን ብቻ ሳይሆን፥ ዋስትናችንም ነው። ኤፌ. 1፡14 መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ዘንድ መኖሩ፥ ለውርሳችን የመያዣ ዋስትናችን ነው ይላል። አንድ ሰው ለአንድ ነጋዴ ቀብዱን ከፍሎ ኋላ በመመለስ ቀሪውን ዋጋ እንደሚከፍል እንደሚያረጋግጥለት ሁሉ፥ እግዚአብሔር ደኅንነታችንን እንደሚያሟላ ዋስትናችን መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የዘላለማዊ ደኅንነታችን ቀዳሚ ክፍል ነው። አሁን የተቀበልነው በመሆናችን፥ ቀሪውን የዘላለም ደኅንነታችንን እንደምናገኝ በዚህ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። 

4. አማኞች የዘላለም ዋስትና አላቸው፥ ምክንያቱም ኢየሱስ ራሱ ስለሚጠብቃቸውና ስለሚንከባከባቸው ነው። 

ጥያቄ፡- ዮሐ 6፡37-40 አንብብ። ሀ) ኢየሱስ፥ አብ ለሰጠውና ወደ እርሱም ዘንድ ለሚመጡት ምን ያደርጋል? (ቁጥር 37) ለ) እግዚአብሔር ከኢየሱስ የሚፈልገው ወይም የሚጠባበቀው ነገር ምንድን ነው? (ቁጥር 39) ሐ) ኢየሱስ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ምንን ይሰጣል? 

ጥያቄ፡- ዮሐ 10፡28-29 አንብብ። የኢየሱስን በጎች ከእጁ ችሎ የሚነጥቀው ማን ነው? 

በዮሐንስ ወንጌል በሁለት ክፍሎች ውስጥ፥ ኢየሱስ አማኞችን ስለሚጠብቃቸው ለዘላለም ምንም ሊነካቸው እንደማይችል ተስፋ ይሰጣቸዋል። በዮሐ 6፡37 ውስጥ ኢየሱስ አብ የሰጠው ሁሉ ወደ እርሱ እንደሚመጡና እርሱም እንደማያባርራቸው ይናገራል። ስለዚህ ወደ ጌታ ኢየሱስ ዘንድ የሚመጣና በእርሱ የሚያምን ማንም ሰው አይጠፋም። ምክንያቱም በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ከሞት አስነሥተ የዘላለምን ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸዋልና ነው። እንደዚሁም በዮሐንስ ምዕራፍ 10 ውስጥ ኢየሱስ በጎቹን የሚጠብቅና የሚከላከል ቸር እረኛ እርሱ መሆኑን በግልጽ ያስረዳል። ስለዚህ ይህ የእርሱ የጥበቃ ዋስትና ማንም ከእርሱ እጅ ሊነጥቃቸው እንደማይችል የሚረጋገጠው ቃል ነው። በእርግጥም የእርሱ እውነተኛ በጎች የሆኑት ሊጠፉ ከቶ አይችሉም። 

5. አማኛች ለዘላለም የተጠበቁ ናቸው። ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ሞተው ሕያዋን ሆነው የተነሡ ስለሆኑ ነው። 

ጥያቄ፡- ኤፌ 2፡4-6 አንብብ። እግዚአብሔር ምን ስት ነገሮችን አደረገልን? 

ጥያቄ፦ ሮሜ 6፡3-6 አንብብ ከኢየሱስ ጋር እንድ ለመሆን የተጠመቁ ሁሉ ምን ይሆናሉ? 

ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 5፡17 አንብብ። ከክርስቶስ ጋር የተባበሩ ምን ይሆናሉ? 

በ17ኛው ትምህርታችን ውስጥ ዳግም በመወለዳችንና ከክርስቶስ ጋር ስላለን ኅብረት ስለምናገኘው የደኅንነት በረከተች ተምረናል። በትምህርታችንም ወቅት አንድ ሰው በእምነት ክርስቶስን እንደ አዳኙ በሚቀበልበት ጊዜ፥ ሰሞቱና በትንሣኤው ከክርስቶስ ጋር እንደሚተባበር አስተውለናል። ቀድሞ የነበረበት አርጌው ሰውነት ይሞታል። አዲሱ ሰው ሕያው ይሆንና ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ይኖራል (ኤፌ 2፡4-6)። ይህ እግዚአብሔር ለአማኞች የሚሰጣቸው አዲስ ሕይወት መንፈሳዊ ሕይወት ነው። እዚህ አማኞች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ለመሆን ከላይ ተወልደዋል። ክርስቶስን አምነን እንደ አዳኛችን በምንቀበልበት ጊዜ፥ የነበርንበት አርጌው ሰውነት ይሞትና አዲሱ ሰውነት ሕይወት ይወርሳል። በርግ መልእክት ምዕራፍ 6 እንደሚለው፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመሆን የተጠመቅን ሁላችን ከኢየሱስ ጋር ሞተን ተቀብረናል ይላል። በ20ኛ ክፍለ ትምህርታችን ውስጥ እንደምንመለከተው፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች ክርስቶስን አምነው መቀበላቸውን በሕዝቡ ፊት ወዲያው እንዳሳወቁ ይጠመቁ ነበር፡ ይህ የጥምቀታቸው ወቅትቶ የመለወጣቸው ጊዜ ሆኖ ተቀባይነትን አኝቶ ነበር። ስለዚህ አንድ ሰው ወደ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ፥ ከክርስቶስ ጋር ይሞታል፥ ከክርስቶስም ጋር ይቀበራል፥ ከክርስቶስም ጋር ለአዲስ ሕይወት ይነሣል። በእውነተኛው ሁኔታ ዳግም የተወለዱ ሰዎች የአዲስ ሕይወትን ስጦታ ብቻ አያገኙም፥ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው አዲስ ሰዎችም ይሆናሉ እንጂ! 2ኛ ቆሮ. 5፡17 ውስጥ የነበሩበት አሮጌው ሰውነት አልፎአል፥ ስለዚህ አሁን አዲስ ሰዎች ሆነው ዳግም ተወልደዋል ይላል። እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር አስነሥቶን እንደ አዲስ ፍጥረት ካደረገን፥ እንዴት አሳቡ ይለወጣል? እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ ከላይ ዳግም አዲስ ሕይወትን የሰጠን ሥራውን ይለውጣል? አንድ ሰው «ላለመወለድ» ይችላል? ደግሞስ አንድ ፍጥረት «ላይፈጠር» ይችላል? እግዚአብሔር ለእኛ አዲስ ሕይወትን በመስጠት አዲስ ሰዎች የማድረጉ ሁኔታ የሚያረጋግጥልን፥ እግዚአብሔር በሕይወት ዘመናችን ውስጥ የማዳን ተግባሩን የሚፈጽም መሆኑን ነው። 

በዛሬው ትምህርታችን ውስጥ እግዚአብሔር ያዳናቸው ሰዎች የደኅንነታቸው ሁኔታ እግዚአብሔር ወዳለበት እስከሚገቡበት ጊዜ ድረስ ተጠብቆ የሚቆይ የመሆኑን አምስት ምክንያቶች አጥንተናል። በነገው ትምህርታችን ደግሞ አማኞች በምን ምክንያት ለዘላለም የተጠበቁ እንደሚሆኑ፥ እንዲሁም በሮሜ ምዕራፍ 8 ውስጥ አማኞች ስለሚኖራቸው ጥበቃና ዋስትና ጠቅለል ባለ ይዘት መልካም ትምህርት እንቀስማለን።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading