ክርስቲያኖች ለኢየሱስ የሚሰጡትን አምልኮ በርካታ ሙስሊሞች በብርቱ ይቃወማሉ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው፣ አምልኮም ለእርሱ ብቻ ይገባል ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ ለሌሎች ፍጥረታት መስገድ ለሙስሊሞች ሺርክን (ትርጉሙን በሚቀጥለው አንቀስ ይመልከቱ) መፈፀም ማለት ሲሆን፣ ተግባሩም ለማንኛውም ሙስሊም ከባድ ኃጢአት ነው!
ሺርክ የአረብኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‹ማጋራት› ማለት ነው፡፡ በእስልምና ሃይማኖት ሺርክ ማለት የጣኦት አምልኮ ወይም በብዙ አማልክት የማምለክ ኃጢአትን የመለክታል፡፡ በእስልምና ሃይማኖት መሠረት አላህ የሰው ልጅ የሚሰራውን የትኛውንም ኃጢአት ይቅር ሊል ይችል ይሆናል፤ የሺርክ ኃጢአትን መፈጸም ግን ከአላህ ዘንድ ፈጽሞ ይቅርታ የማይቸረው ነው፡፡ ይህንን ኃጢአት የሚፈጽሙ ሰዎችም የእስልምና ጠላቶች ተደርገው ይፈረጃሉ፡፡
ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌሎች ፍጥረታት የሚሰጠው አምልኮ (ስግደት) በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ውግዘት ቢደርስበትም፣ መላዕክት ለአደም/ለአዳም እንዲሰግዱለት እና እንዲያመልኩት አላህ ማዘዙን ግን ቁርአኑ ይናገራል!
- ለመላእክትም ለአደም [ለአዳም] ስገዱ ባልን ጊዜ (አስታውስ)፣ ሁሉም ወዲያውኑ ሰገዱ፣ ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ብቻ ሲቀር እምቢ አለ፣ ኮራም፣ ከከሓዲዎቹም ኾነ፡፡
ሱረቱ አል-በቀራህ (2)፡34
And behold, We (God) said to the angles: “Bow down to Adam.”
- ጌታህም ለመላእክት ባለ ጊዜ (አስታውስ)፡- እኔ ሰውን ከሚቅጨለጨል ሸክላ ከሚገማ ጭቃ እፈጥራለሁ፡፡ (ፍጥረቱን) ባስተካከልኩትና በውስጡ ከመንፈሴ በነፋሁበትም ጊዜ ለርሱ ሰጋጆች ኾናችሁ ውደቁ፡፡
ሱረቱ አል-ሒጅር (15)፡28-29
Behold! Thy Lord said to the angels: “I am about to create man, from sounding clay, from mud molded into shape. When I have fashioned him and breathed into him of My spirit, fall ye down in obeisance unto him.”
እርግጥ ነው ፈጣሪ፣ አደም/አዳም አንድ ቀን የሰይጣንን (የመልአክን) ውሸት በመስማት የሰውን ዘር ሁሉ ወደ ውድቀት ይዞት እንደሚሄድ ያውቃል፡፡ ይሁንና ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የወደፊቱን የሚያውቀው ፈጣሪ በዚህ ጥቅስ መሰረት፣ መላእክት ለመጀመሪያው ሰው አደም/አዳም እንዲሰግዱ አዘዛቸው፡፡
እዚህ ላይ፣ በፊተኛው አዳም ምክንያት የወደቀውን የሰውን ዘር ወደ ስኬት ለመምራት ስለቻለው ‹‹ሌላ አዳም›› መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያወራ ለሙስሊም ወዳጅዎ ማስረዳት በጣም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው (ፊተኛው) አዳም ምድርና ሞላዋን እንዲገዛት እግዚአብሔር ስልጣንና ኃይልን እንደሰጠው ሁሉ፣ ሁለተኛው አዳም ደግሞ በሰማያዊ መንግስት ላይ ሁሉ እንዲገዛ ስልጣንና ኃይልን ሰጥቶታል፡፡ ይህ መንግስት የእግዚአብሔር መንግስት ነው! ሌላኛው ይህ አዳም፣ ‹‹ሁለተኛው አዳም›› ወይም ‹‹ኋለኛው አዳም›› ተብሎ ተጠርቷል፡፡ እርሱም መሲሁ ኢየሱስ ነው! የመጀመሪያው (ፊተኛው) አዳም ምድራዊ ሲሆን ኋለኛው አዳም ደግሞ ሰማያዊ ነው፡፡
- እንዲሁ ደግሞ፡- ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። … የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፣ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። የዚያንም የመሬታዊውን መልክ እንደ ለበስን የሰማያዊውን መልክ ደግሞ እንለብሳለን። ነገር ግን፣ ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እላለሁ። ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም፣ የሚበሰብሰውም የማይበሰብሰውን አይወርስም። ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
1ቆሮንቶስ 15፡45-57
እላይ የቀረቡት ምንባቦች ሁለተኛው አዳም (ኢየሱስ) አዳም በሰይጣን ፈተና ከመዉደቁ በፊት ይኖርበት ወደነበረበቱ ስፍራ፣ ወደ ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መገኘት ሊመልሰን የሚችልበት ኃይልና ስልጣን እንደታጠቀ ያበስሩናል፡፡ ለሚከተሉት ሁሉ ኢየሱስ ይህን መንፈሳዊና ዘላለማዊ ሕይወት ሊሰጥ ስልጣን አለው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን እውነት በግልጽ ያስቀምጠዋል፡-
- ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ፡- አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፣ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፣ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው። እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።
ዮሐንስ 17፡1-3
ኢየሱስ በዚህኛው ዓለምና በሚመጣው ዓለም የከበረ ማንነት እንዳለው ቁርአን ይናገራል፡፡ ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽታን ለመፈወስ፣ ማየት የተሳናቸውን አይን ለማብራት፣ ሙታንን ለማስነሳትና ለመፍጠር [ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡39] የተሰጠውን ኃይልና ስልጣን ከቁርአን በማንበብ ብቻ ከመሲሁ ከኢየሱስ ማንነት ጋር የተያያዘውን ክብር ሙስሊሞች ማስተዋል ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቁርአን ስለ ኢየሱስ የሚከተለውን ይላል፡-
- መላእክት ያሉትን (አስታውስ)፡- መርየም [ማሪያም] ሆይ! አላህ ከርሱ በኾነው ቃል ስሙ አልመሲሕ ዒሳ [መሲህ ኢየሱስ] የመርየም ልጅ በዚህ ዓለምና በመጨረሻውም ዓለም የተከበረ ከባለማሎችም በኾነ (ልጅ) ያበስርሻል፣
ሱረቱ አሊ-ዒምራን (3)፡45
His name will be Christ Jesus (Al-Masih Isa), the son of Mary, held in this world and the hereafter, and of (the company of) those nearest to God.
በሚያሳዝን ሁኔታ በርካታ ሙስሊሞች እግዚአብሔር ኢየሱስን ካስነሳውና ወደራሱ ከወሰደው በኃላ ስለሰጠው ታላቅ ክብር እውቀት እንግዳ ናቸው፡፡ ለሙስሊም ወዳጅህ የሚከተለውን ክፍል ከመጽሐፍ ቅዱስ አካፍለው፡-
- ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።
የሐዋሪያት ሥራ 2፡3233
- በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
ፊሊጱሲዩስ 2፡8-11
- ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።
ማቴዎስ 28፡18
ለዚህ ኃይልና ስልጣን ሁሉ ለተሰጠው፣ ለሰው ልጅ ቤዛነት ለመስቀል ሞት እንኳ ለታዘዘው፣ የ‹‹እግዚአብሔር በግ›› ለተሰኘው፣ ሺህ ጊዜ ሺህና እልፍ ጊዜ እልፍ የሆኑ ማላዕክት ስግደትና አምልኮ ሲያቀርቡለት እንመለከታለን፡-
- አየሁም፣ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፣ በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።
ራዕይ 5፡11፣12
የሚበሰብስ ሥጋን የተሸከምን እኛ፣ እግዚአብሔር የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ ብሎ ለቀባው ስግደት ለማምጣት እንቢ ማለት እንችላለንን (ራዕይ 19፡16)? ሙስሊሞች የፈጣሪ ቃል ነው ብለው ቅዱስ መጽሐፋቸውን እንደሚሳለሙት (እንደሚስሙት) እውነተኛ ክርስቲያኖችም ላልተፈጠረውና ለዘላለም ለሚኖረው የእግዚአብሔር ቃል ክብር ይሰጣሉ፣ በኢየሱስ እግር በታችም ይሳለማሉ (ይሰግዳሉ)! ለእግዚአብሔር ቃል ማለትም ለኢየሱስ መለኮታዊ ማንነት እንጂ ለሌላ አማልክት ወይም ፍጥረት እንደማትሰግድ ሙስሊም ወዳጅህ እንዲገነዘብ ልትረዳው ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ባነበብነው የቁርአኑ ታሪክ መሰረት መላዕክት ከሸክላ አፈር ለተፈጠረው ሰው ሰገዱ፤ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ልምምድ መሠረት ግን፣ አማኞች የእግዚአብሔር ቃል ለሆነው፣ የማይታየው አምላክ አምሳል ለሆነው፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድርስ ከእግዚአብሔር ለማይነጠለውና መለኮታዊ ማንነት ላለው ለኢየሱስ ይሰግዳሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሱስ ስለ ሚያደርሱት ጸሎትም ሙስሊሞች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
ክርስቲያኖች ፀሎትን ወደ ኢየሱስ የሚያደርጉት ከዚህ በላይ በተገለፀው የኢየሱስ መለኮታዊነት ምክንያት እና እርሱ ራሱ ይህንን ትእዛዝ ለተከታዮቹ በመስጠቱ መሆኑን ለሙስሊም ወዳጅህ ለማስረዳት ሞክር፡፡ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በስሙ አንዳች ነገር ቢጠይቁ እንደ ሚሰጣቸው በተናገረው መሠረት ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ በሰማያት በእግዚአብሔር ቀኝ በሕይወት እንዳለ በማመን እና ስሙን ለሚጠሩት ሁሉ ፍፁም የሆነ ነፃነትንና ድኅነትን/መዳንን እንደ ሚሰጣቸው በመቀበል ወደ ኢየሱስ ይጸልያሉ፡፡ እግዚአብሔር በተባረከው ኢየሱስ ላይ ያስቀመጠውን ታላቅ ክብርና ስልጣን ፈፅሞ አያነሳውምና፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ሚነግሩን የሰይጣንን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ኢየሱስ በሥጋ ከእኛ ጋር ተካፈለ፤ እናም ስሙን የሚጠሩትን ሁሉ ፈፅሞ ሊረዳቸውና ሊያድናቸው ይቻለዋል፡፡
- እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና፤ አብም ስለ ወልድ እንዲከበር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
ዩሐንስ 14፡13፣14