1ኛ ነገሥት 17-22

እጅግ የከፋ ነገር ባለበት ዘመን ሁሉ፥ እግዚአብሔር የራሱ የሆኑ ታማኝ ሰዎች አሉት። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ «ቅሬታዎች» የምንላቸው፥ ለሐሰት ትምህርት አንንበረከክም የሚሉ፥ ወይም ከፍተኛ ስደት ባለበት ጊዜ እምነታቸውን በጽናት ይዘው የሚቆዩ ሰዎች ናቸው።

ብዙውን ጊዜ በእዚህ የጨለማ ወቅቶች፥ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ ሰዎች ተስፋ ሊቆርጡና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን እምነታቸውን ለመተው ሊፈተኑ ይችላሉ። ለብቻ ከመቆም ይልቅ፥ የዓለምን የአኗኗር ስልት በመከተል ከብዙኃኑ ጋር መተባበር እጅግ ቀላል ነው።

ኤልያስ ብቸኛው የእግዚአብሔር ነቢይ ነበር። እጅግ ክፉ በነበረው በአክዓብ ዘመን ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ነቢያት በአክዓብ ሲገደሉ፥ ኤልያስ በእምነቱ ጸንቶ ቆመ። አንድ ጊዜ ኤልያስ እጅግ ተስፋ ቆርጦ ሞቱን ሲለምን እግዚአብሔር እንዲህ በማለት አጽናናው፡- «እኔም ከእስራኤል ጉልበታቸውን ለበአል ያላንበረከኩትን ሁሉ፥ በአፋቸውም ያልሳሙትን ሁሉ፥ ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀራለሁ።» (1ኛ ነገሥት 19፡18)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ሁሉም የተዉት በሚመስልበት ጊዜ ለእግዚአብሔር መቆም አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ተስፋ መቁረጥ ቀላል የሚሆነውስ ለምንድን ነው? ሐ) ጨለማው እጅግ ድቅድቅ በሚሆንበት ጊዜ እንኳ ለእግዚአብሔር ታምነው የሚቆሙ ቅሬታዎች አሁንም ስላሉት በእግዚአብሔር ላይ የምንጽናናው እንዴት ነው? 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 17-22 አንብብ። ሀ) ኤልያስ ያደረጋቸውን የተለያዩ ተአምራት ዘርዝር። ለ) ኤልያስ የጣዖታትን ከንቱነት ያሳየው እንዴት ነው? ሐ) በእዚህ ክፍል የተጠቀሱት ሦስት ነገሥታት እነማን ናቸው? መ) ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሥዕላዊ መግለጫ ስጥ። 

ከ1ኛ ነገ. 17-2ኛ ነገ. 8 ያሉት እነዚህ ምዕራፎች፥ ከነገሥታቱ ይልቅ በኤልያስና ኤልሳዕ ላይ ያተኩራሉ።

የውይይት ጥያቄ፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ኤልያስና ኤልሳዕ የሚለውን ክፍል ተመልከት። ስለ ሕይወታቸው ጠቃሚ የሆኑ እውነቶችን ዘርዝር።

የ1ኛ ነገሥት የመጨረሻ ክፍል (ምዕ. 17-22) የሚያተኩረው ኤልያስ ከእስራኤል ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ነው። ኤልያስና ኤልሳዕ ያገለገሉት በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ነው። የበአል አምልኮ በእስራኤል እንዳይስፋፉ ለመከላከልና ሕዝቡን ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር አምልኮ ለመመለስ የተጠሩ የእግዚአብሔር ነቢያት ነበሩ።

በኤልያስና በኤልሳዕ ታሪክ ውስጥ ልናስታውሳቸው የሚገባን በርካታ እውነቶች አሉ፡-

 1. በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ነቢያት ተግባር የግድ የወደፊቱን ነገር መተንበይ አልነበረም፤ ነገር ግን ነቢዩ እግዚአብሔር በቀጥታ የሚናገረውና በእርሱም በኩል ከሕዝቡ ጋር ግንኙነት የሚያደርግበት ሰው ነበር። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ለነቢያቱ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ይነግራቸው ነበር። ብዙ ጊዜ ግን ነቢዩ የእግዚአብሔርን ቃል የሚያመጣው ለዚያን ጊዜ ነበር። 
 2. በዘመኑ የነበሩት የፖለቲካ መሪዎች (ነገሥታት) እግዚአብሔርን በሚተዉበት ጊዜ፥ የእርሱን መልእክት ለሕዝቡ ያደርሱ ዘንድ የተለዩ ሰዎችን ይመርጥ ነበር። ነቢያቱም ሕዝቡ በጣዖት አምልኮ እንዳይያዙ ያስጠነቅቁ ዘንድ እግዚአብሔር ይጠቀምባቸው ነበር። 
 3. የነቢያት ዘመን ተብሎ በሚጠራው ጊዜ የተነሣ የመጀመሪያው ነቢይ ኤልያስ ነበር። ከኤልያስ ዘመን ጀምሮ፥ በሕዝቡ ላይ ስለሚመጣው የእግዚአብሔር ፍርድ የሚያስጠነቅቅ የነቢያትን ተከታታይ አገልግሎት እናያለን። ኤልያስና ኤልሳዕ «የነቢያት ጉባኤ» በመባል የሚታወቀውን የነቢያትን የቡድን አገልግሎት መርተዋል። ይህ የነቢያት ቡድን ለብዙ ዓመታት በእስራኤል ውስጥ አገልግሏል። 

ለአይሁድ ኤልያስ የእውነተኛ ነቢያት ምሳሌ ለመሆን በቅቷል። አለባበሱና አኗኗሩን በኋላ የተነሡ ነቢያት ሁሉ የተከተሉት ነበር። በተለይ ደግሞ መጥምቁ ዮሐንስ ይህንን አድርጎአል። ብሉይ ኪዳን የሚጠናቀቀው ወደ እስራኤል በመጣ እንደ ኤልያስ ባለ ነቢይ እንደሚሆን ተነግሮ ነበር (ሚል. 4፡5)። ኢየሱስ የዚህ ትንቢት ፍጻሜ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሆነ ተናግሯል (ማቴ. 11፡1)። ኢየሱስ በተራራው ላይ በተለወጠ ጊዜ የሕግ መሪ ከነበረው ከሙሴና የነቢያት መሪ ከነበረው ከኤልያስ ጋር እንደተገናኘ መመልከት የሚያስደንቅ ነው። 

 1. ኤልያስና ኤልሳዕ መልእክታቸውን በጽሑፍ ያላስተላለፉ ነቢያት ናቸው። ይህንን ስንል በእስራኤል የተነበዩ ቢሆንም እንኳ፥ መልእክታቸውን ለሕዝቡ በጽሑፍ አላስቀሩም ማለታችን ነው። ከእነርሱ በኋላ የተነሡት ሆሴዕ ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ ወዘተ. መልእክታቸውን በጽሑፍ ያስተላለፉ ነቢያት ናቸው። 
 2. የኤልያስና የኤልሳዕ አገልግሎት በበአል አምልኮ ላይ የቀረበ ቀጥተኛ ተቃውሞ እንደሆነ መመልከት አስፈላጊ ነው። የሚከተለውን የበአል አምልኮና የኤልያስና የኤልሳዕ አገልግሎት ንጽጽር ልብ በል፡- 

በአልና የእግዚአብሔር ነቢያት የሆኑት- ኤልያስና ኤልሳዕ 

– በአል ዝናምን የሚቆጣጠር አምላክ ተደርጎ ይታመን ነበር 

– ኤልያስ በምድሪቱ ላይ ድርቅ እንዲመጣ አዘዘ

– በአል የተትረፈረፈ ምርትን እንደሚሰጥ ተደርጎ ይታመን ነበር 

– እስራኤል ከፍተኛ ራብና ድርቅ ገጠማት ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር እርዳታ ኤልያስና ኤልሳዕ ግን እህልና ዘይት ሰጡ

– በአል መብረቅንና እሳትን እንደሚቆጣጠር ተደርጎ ይታመን ነበር

– ኤልያስ በእግዚአብሔር ስም በማዘዝ እሳትን ከሰማይ አወረደ

– በአል ሕይወትና ሞትን እንደሚቆጣጠር ተደርጎ ይታመን ነበር 

– ኤልያስና ኤልሳዕ በእግዚአብሔር ስም በሽተኛን ፈወሱ ሙታንን አስነሡ 

ኤልያስና ኤልሳዕ የሠሩአቸው ተአምራት እውነተኛ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነና በአልም ኃይል የሌለው ውሸተኛ አምላክ (ጣዖት) እንደነበረ በግልጥ የሚያሳይ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፥ ክርስቲያኖች የዚህ ዓይነት ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ የማወቃቸው አስፈላጊነት ምንድን ነው? 

በ1ኛ ነገሥት 17:22 ዋናው ነቢይ ኤልያስ ነበር። ስለ ኤልያስ የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

 1. እግዚአብሔር ድርቅና ራብ እንደሚመጣ፥ የድርቁና የራቡ ዘመን እንደሚያበቃም ለመናገር የተጠቀመበት ሰው ነበር። 
 2. እግዚአብሔር በቁራዎች የመገበው ሰው ነበር። 
 3. መበለቲቱን ለመመገብና ልጄን ከሞት በማስነሣት ወደ ሕይወት ለመመለስ እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ነበር። 
 4. ለእስራኤል በሙሉ እውነተኛው አምላክ እግዚአብሔር ብቻ እንደሆና የጣዖት አምልኮ አንዳችም ዋጋ የሌለው ከንቱ ነገር እንደሆነ አሳየ። በቀርሜሎስ ተራራ የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወርዳ መሥዋዕቱን እንድትበላ አደረገ። ከዚያ በኋላ 400 የበአል ነቢያትንም አስገደለ። 
 5. ኤልዛቤል የተባለችውን ሴት ፈርቶ ወደ ምድረ በዳ ሸሽና ሞትን ለመነ። እግዚአብሔርም ተገናኘውና ሠጸው። ለበአል ያልሰገዱ ሌሎች ሰዎች እንዳሉትም ነገረው። 
 6. እግዚአብሔር ኤልሳዕን የሚቀጥለው ታላቁ የእስራኤል ነቢይ አድርጎ ለመጥራት ኤልያስን ተጠቀመበት። 
 7. ኤልያስ የአክዓብን ቤት ፍጻሜና የኤልዛቤልን መሞት ተነበየ። በኤልያስ ዘመን የነበሩ ሌሎች ሁለት ነገሥታትም ተጠቅሰዋል፡-

ሀ. ኢዮሣፍጥ የይሁዳ ንጉሥ (872-848 ዓ.ዓ.)

ከይሁዳ ታላላቅ ነገሥታት አንዱ ኢዮሣፍጥ ነበር። በአሳ የተጀመረውን መንፈሳዊ መነቃቃት ቀጠለ። የጣዖት አምልኮን አጠፋ። በተለይ ደግሞ አሻራ የተባለችውን የከነዓናውያንን የልምላሜ ሴት አምላክ አጠፋ። በይሁዳ ሁሉ እንዲሰማሩና ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ሕግ እንዲያስተምሩ ሌዋውያንና መኳንንትን አደራጀ። በእርሱ የአመራር ዘመን በይሁዳ ምድር ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት አስነሣ። ለእግዚአብሔር ታማኝ ስለሆ፥ እርሱ አከበረው። ፍልስጥኤማውያንና ዓረቦችን በበላይነት ሊቆጣጠርና ምድሪቱንም ጠንካራ ሊያደርጋት ቻለ።

የኢዮሣፍጥ ትልቁ ችግር ከእስራኤል ጋር መስማማቱና ልጁን ለአክዓብ ቤት መዳሩ ነበር። ይህ ድርጊቱ እርሱንና ቤተሰቡን በመንፈሳዊ ነገር ሊጎዳ እንደሚችል አላሰበም ነበር። ከሞተ አሥር ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህ ባለማስተዋል የተፈጸመ ድርጊት ቤተሰቡን ሊያጠፋ ደረሰ። ይህ ያለማስተዋል ተግባር በመላው ይሁዳ የጀመረውን ሃይማኖታዊ ተሐድሶ አደናቀፈው።

ኢዮሣፍጥ ከአክዓብ ጋር የነበረው የጓደኝነት ግንኙነት ሊያስገድለው ምንም ያህል አልቀረውም ነበር። ኢዮሳፍጥ የእስራኤልን ሽንፈት የተናገረውን የእግዚአብሔርን ነቢይ ሚክያስን ስላልሰማ ከአክዓብ ጎን ቆሞ በመዋጋት ላይ ሳለ ሊገደል ነበር። ነቢዩ ሚክያስ እንደተናገረው፥ አክዓብ በጦርነቱ ተገደለ።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔርን የሚፈራ መሪ ከዓለም ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የኢዮሣፍጥ ሕይወት እንዴት ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናል ለ) ከማያምኑ ጋር ስለሚደረግ ጋብቻ አደገኛነትና ይህም በአማኝ ልጆች ላይ ስላለው ተጽዕኖ ምን ያስተምረናል?

እግዚአብሔርን የሚፈሩ መሪዎች ሲሰምርላቸውና እግዚአብሔር በኃይል ሲጠቀምባቸው፥ ሰይጣን ከዓለም ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ሊያጠፋቸው ይሞክራል። የተከበረ ክርስቲያናዊ መሪ አንዳንድ ጊዜ ከሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ጋር ግንባር እንዲፈጥር ወይም የፖለቲካ መሪ እንዲሆን ይመረጣል። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነትና በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ንጹሕ አቋም ከዓለም ጋር በዚህ ዓይነት ኅብረት ውስጥ ሆነው መጠበቅ የሚችሉ ጥቂት ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ናቸው። ይህ ነገር ብዙ ጊዜ የመሪውን ሕይወት ወደ ማጥፋትና በቤተ ክርስቲያን ላይ ጉዳት ወደማምጣት የሚያዘነብል ነው። ክርስቲያኖች በሚመሠርቱት ኅብረትና ከዓለም ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊኖሩ ይገባል። እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ እርሱን የሚፈሩ መሪዎችን በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸው ቢሆንም፥ እርምጃቸውንና እምነታቸውን በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊይዙ ይገባል።

ለ. የእስራኤል ንጉሥ አካዝያስ (853-852 ዓ.ዓ.)

እንደ አባቱ እንደ አክዓብ፥ አካዝያስም ክፉና የበአልን አምልኮ የተከተለ ሰው ነበር። ሁለት ዓመታት ብቻ ከነገሠ በኋላ ወደቀና ሞተ። የቀረው የአካዝያስ ታሪክ በ2ኛ ነገሥት ውስጥ ይገኛል።

የውይይት ጥያቄ፥ በዚህ ክፍል ከተጠቀሱት ነገሥታትና ከኤልያስ ሕይወት ስለ መንፈሳዊ መሪነት የተጠቀሱትን አንዳንድ ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1ኛ ነገሥት 12-16

የአንድ መሪ መንፈሳዊ ሕይወት በአጠቃላይ በሰዎች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ታላቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተመልክተናል። ብዙ ጊዜ መሪው ለእግዚአብሔር ታዛዥ በሚሆንበትና ራሱን ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ፥ ሕዝቡም ለእግዚአብሔር ራሱን አሳልፎ በመስጠት ታዛዥ ይሆናል። መሪው ለእግዚአብሔር በሙላት በማይታዘዝበት ጊዜ፥ ሕዝቡን ከእውነት በቀላሉ ያርቀዋል። 1ኛና 2ኛ ነገሥትን በምናነብበት ጊዜ፥ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት የሕዝቡን መንፈሳዊ ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ እንዴት እንደነኩት እንመለከታለን። 

የምንኖርበት ዘመን በርካታ ስጦታ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም ሰባኪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሠሩበት ዘመን ነው። ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በሰጡት ጥቂቶች፥ እግዚአብሔር በከፍተኛ ሁኔታ ይጠቀምባቸዋል። ለራሳቸው ጥቅም በስግብግብነት የሚሠሩና ብዙዎችን የሚያስኮበልሉም አሉ። ጳውሎስ ለእግዚአብሔር መንጋ የማይራሩ «ጨካኝ ተኩላዎች» እንደሚነሡ አስጠንቅቋል። እንዲያውም እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች የሚነሡት ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሆነ ተናግሯል (የሐዋ. 20፡29-30 ተመልከት)። በዚህ ዘመን በርካታ ሐሰተኛ አስተማሪዎችና መሪዎች ስላሉ፥ የእውነትን መንገድ ለመከተል ራሳችንን የሰጠን ሰዎች፥ የራሳችንና የመንጋችንን ሕይወት ከጥፋትና ከኩብለላ መጠበቅ አለብን። በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መሥራት ከሚገባቸው ዋና ዋና ሥራዎች አንዱ ምዕመናን በስሕተት ትምህርት እንዳይወድቁ መጠበቅ ነው። ይህንን ለማድረግ ግን መንፈሳዊ ሕይወታችን መንጋው ክርስቶስን ለመከተል የሚችልበትን መልካም ምሳሌነት የሚያሳይ እንዲሆን እርግጠኞች መሆን አለብን። የሐሰት አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያኖቻችን ያሉትን ምዕመናን እምነት ለማጥፋት እንዳይችሉ፥ የመሪዎች ሕይወት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) አንድ መሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕይወቱ መልካም ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ለ) ይህ በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደተፈጸመ መግለጫ ስጥ። ሐ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕይወቱ ከፍተኛ የክፋት ተጽዕኖ ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? መ) ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንደተፈጸመ መግለጫ ስጥ። 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ነገሥት 12-16 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ያገለገሉ ነገሥታትን ዘርዝር። ለ) ከየትኛው መንግሥት እንደነበሩ ጥቀስ። ሐ) ምን ዓይነት መንፈሳዊ ባሕርይ እንደነበራቸውም ጥቀስ። መ) በነገሡበት ዘመን የተፈጸሙትን ጠቃሚ ነገሮች ዝርዝር። 

 1. ሮብዓም፡- የይሁዳ ንጉሥ (931-913 ዓ.ዓ.) 

አባቱ ሰሎሞን ከሞተ በኋላ ሮብዓም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ። የእስራኤል ሕዝብ ሊያነግሡት በመጡ ጊዜ አንድ ቅድመ ሁኔታ ጠየቁት። ያለባቸውን የሥራ ጫናና ግብር ቢቀንስላቸው እንደሚያነግሡት ቃል ገቡለት። ይህንን ባያደርግ ግን እንደሚያምፁበት አስታወቁት። ሮብዓምም በዕድሜ የገፉትን ሰዎች ምክር ሳይሆን፥ የወጣቶቹን ምክር ስለሰማ ቀንበራቸውን የባሰ እንደሚያከብድባቸው ነገራቸው። በዚህ ጊዜ አሥሩ ነገዶች ዓመፁበትና ቀዳማዊ ኢዮርብዓምን ንጉሣቸው ይሆን ዘንድ መረጡት። የይሁዳና የብንያም ነገዶች ግን ከሮብዓምና ከዳዊት ሥርወ መንግሥት ከመጡ ነገሥታት ጋር ቆዩ። 

በሮብዓም ዘመነ መንግሥት፥ የእስራኤል ሕዝብ በሁለት ታላላቅ መንግሥታት ተከፈለ። የመጀመሪያው፥ አሥሩን ነገዶች የያዘው የሰሜኑ መንግሥት ሲሆን፥ እስራኤል ተብሎ ተጠራ። አንዳንድ ጊዜ ኤፍሬም ተብሎም ይጠራል። ከሰሜኑ ክፍል የሚበዛው የኤፍሬም ነገድ ነበርና። በነቢያት መጻሕፍት በኋላ ዋና ከተማቸው ባደረጉት በሰማርያ ስምም ይጠራል። የነቢያትን መጽሐፍ በምናነብበት ጊዜ፥ የእስራኤልን ስም ስናገኝ ያ ቃል የሚናገረው በአጠቃላይ ለእስራኤል ይሁን ወይም ለሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት መወሰን በጣም አስፈላጊ ነው። 

ሁለተኛ፥ የደቡብ መንግሥት ደግሞ ይሁዳ ተብሎ ተጠራ፥ አንዳንድ ጊዜ የዚህ መንግሥት ዋና ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌም ስምም ይጠራል። የብንያም ነገዶችም ከይሁዳ ጋር ነበሩ።

እስራኤልና ይሁዳ በተከፋፈሉ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ሌዋውያን እንደዚሁም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሌሎችም ሰዎች ከእስራኤል ወደ ይሁዳ ተሰደዱ።

በሮብዓም ዘመን በእስራኤልና በይሁዳ መካከል ብዙ ጊዜ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በመጀመሪያ ሮብዓም የጌታን መንገድ ተከተለ። መንግሥቱ የበለጠ በጸናች ጊዜ ግን በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀና በመንግሥቱ ውስጥ የጣዖት አምልኮ እንዲንሰራፋ አደረገ። ውጤቱም እግዚአብሔር ግብፃውያን እንዲመጡና እንዲወጉት፥ ከከተሞቻቸውም አብዛኛውን ከይሁዳ መንግሥት እንዲወሰዱ ማድረጉ ነበር። በሮብዓም ዘመነ መንግሥት የደቡብ መንግሥት ኃይል ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሄደ።

 1. ቀዳማዊ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ (931-910 ዓ.ዓ.)

የሰሎሞን አስተዳዳሪዎች ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ኢዮርብዓም የሰሜኑ መንግሥት ንጉሥ ይሆን ዘንድ በአሥሩ ነገዶች ተመረጠ። ለእግዚአብሔር፥ የሚታዘዝ ከሆነ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን እንደሚያደርግ እግዚአብሔር ለኢዮርብዓም ነገረው (1ኛ ነገ. 11፡38)። ኢዮርብዓም ግን ይህንን ሥልጣን እንደጨበጠ ወዲያውኑ በእግዚአብሔር ላይ ዓመፀ። በሰሜኑ የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ እግዚአብሔርን እንዳያመልኩ፥ ኢዮርብዓም ሁለት የማምለኪያ ማዕከሉችን አሠራ፤ ከእነዚህም አንዱ በስተሰሜን የሚገኘው ዳን የሚባለው ስፍራ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ በስተደቡብ ቤቴል ተብሉ የሚጠራው ስፍራ ነው። በሁለቱም ማዕከሎች ሕዝቡ የሚያመልኩትን የጥጃ ምስል ሠራላቸው። በዚህም ኢዮርብዓም ሕዝቡን ወደ ጣዖት አምልኮ መራቸው።

እስራኤላውያን በምድረ በዳ የጥጃ ምስል እንዳመለኩ ታስታውሳለህ። ይህ የጥጃ ምስል አምልኮ ከግብፅ የመጣ ነው። ይህ አፒስ የሚባለው ለእንስሳት፥ ለሰዎችና ለእርሻ ጭምር ሕይወትን፥ ጤንነትን፥ ብርታትንና ፍሬያማነትን ይሰጣል ተብሎ የሚታሰበው አምላክ (ጣዖት) ምስል ነበር። አንዳንድ ምሁራን ኢዮርብዓም የግብፃውያንን አምልኮ ከከነዓናዊያን ጥጃን ከማምለክ ጋር ቀላቅሉአል ይላሉ። የኢዮርብዓም ፍላጎት ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም ከሚሄዱ ይልቅ፥ በዚህ ስፍራ ጣዖትን በመሥራት የእግዚአብሔር ምልክት ብቻ እንዲሆንና ሕዝቡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ቢሆንም፥ እነዚህ የጥጃ ምስሎች ወዲያውኑ ጣዖት ሆነው መመለክ ጀመሩ። በኋላም ከባዓል አምልኮ ጋር ተቀይጦ፥ ሰዎች በመሥዋዕትነት የሚቀርቡበት ቦታ ሆነ (2ኛ ነገ. 17፡15-17)። 

ኢዮርብዓም ይህንን ባደረገ ጊዜ እግዚአብሔር ነቢይ ላከና እንዲገሥጸውና መንግሥቱም ለረጅም ጊዜ እንደማትቆይ እንዲነግረው አደረገ። መሠዊያው እንደሚረክስ የተነገረው ትንቢትም ከ300 ዓመታት በኋላ በኢዮስያስ ተፈጸመ (2ኛ ነገ. 23፡15-20 ተመልከት)። 

የውይይት ጥያቄ፥ ይህ ትንቢትና ፍጻሜው ስለ እግዚአብሔር ቃል ኃይል ምን ያስተምረናል?

ከይሁዳ የሆነው የዚህ ያልታወቀ ነቢይ ታሪክ በጣም አሳዛኝ ነው። እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ ሌላውን ነቢይ ሰማና ስላለመታዘዙ ሞተ፤ ስለዚህ በአልታወቀ ነቢይ ላይ የደረሰው ነገር ኢዮርብዓምንና የእግዚአብሔርን ሕዝብ በሙሉ፥ ለእግዚአብሔር ቃል በጥንቃቄ ስለ መታዘዝ አስፈላጊነት አስተምሯል።

 1. የይሁዳ ንጉሥ አቢያ (913-910 ዓ.ዓ.) 

አቢያ የነገሠው ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር። ልክ እንደ አባቱ እንደ ሮብዓም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ። የጣዖት አምልኮ እንዲስፋፋ ፈቀደ።

በእነዚህ ሦስት ዓመታት በእስራኤል ከነገሠው ከቀዳማዊ ኢዮርብዓም ጋር ከፍተኛ ጦርነት አካሂዷል። አቢያ አንዳንዶቹን የእስራኤል ግዛቶች በጦርነት ለመያዝ ችሉ ነበር።

 1. የይሁዳ ንጉሥ አሳ (910-869 ዓ.ዓ.)

በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት መካከል መልካም ከነበሩት አንዱ ነው። አባቱና አያቱ የሠሩትን ክፉ ነገር ሁሉ ከአገሪቱ ለማስወገድ ሞከረ፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው እንደ መሆኑ መጠን የባዕድ አምልኮ መሠዊያዎችን አፈራረሰ። ጣዖታትን ሁሉ ነቃቅሉ ጣለ። የጣዖት አምልኮ የሚፈጸምባቸውን ከፍተኛ ስፍራዎች ሁሉ አጠፋ። ሕዝቡንም ለሙሴ ሕግ እንዲታዘዙ ነገራቸው። በይሁዳ ምድር መንፈሳዊ መነቃቃት ስለነበረ፥ በእስራኤል ያሉ እግዚአብሔርን በታማኝነት ያመልኩ የነበሩ ሰዎች ወደ ይሁዳ ምድር መጡ።

አሳ ያስተዳድር በነበረባቸው በመጀመሪያዎቹ አሥር ዓመታት ፍጹም ሰላም ነበር። በዚህ ጊዜ የይሁዳ ከተሞችንና ጦሩን አደራጀ፤ ነገር ግን ከእስራኤል ጋር በተደረገው ጦርነት የእስራኤል ንጉሥ አሳን ድል ለማድረግና አንዳንድ ከተሞችን ከይሁዳ መንግሥት ለመውሰድ ቻለ። ከኢየሩሳሌም 8 ኪሎ ሜትር በስተ ሰሜን ርቃ የምትገኘውን የራማ ከተማን ለመውሰድም በቃ። ይህንን ያደረገበት አንዱ ምክንያት የእስራኤል ሰዎች እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደ ይሁዳ እንዳይሄዱ ነበር። አሳ በእስራኤል በተጠቃበት ጊዜ የሶርያን እርዳታ ጠየቀና በአንድነት እስራኤልን አጥቅተው ከይሁዳ እንዲወጡ አደረጉ።

የሚያሳዝነው በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ አሳ ፊቱን ከእግዚአብሔር መለሰ። እንዲያውም በሶርያ ላይ መደገፉን በመቃወም ስለተናገረው የእግዚአብሔር ነቢይ የነበረውን አናኒን አሰረው(1ኛ ዜና 16፡7-10 )።

 1. የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ (910-909 ዓ.ዓ.)

የቀዳማዊው ኢዮርብዓም ልጅ የነበረው ናዳብ በሰሜኑ መንግሥት ላይ ለመንገሥ የቻለው ሁለት ዓመት ብቻ ነበር። ልክ እንደ አባቱ ክፉ መሪ ነበር። ባኦስ ገደለውና ልክ ነብዩ እንደተነበየው መንግሥቱ ከቀዳማዊ ኢዮርብዓም ቤት ተወሰደ (1ኛ ነገ. 14)። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ (909-886 ዓ.ዓ.)

ናዳብን ገድሉ በእስራኤል ላይ የነገሠ ሰው ነበር። በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ በእስራኤል ላይ ባገኘው የንጉሥነት ሥልጣን ችግር ይፈጥሩብኛል ብሎ ያሰባቸውን የኢዮርብዓምን ዝርያዎች ሁሉ መፍጀት ነበር።

ባኦስ ከይሁዳ ጋር የተዋጋ መሪ ሲሆን፥ ሶርያ ከሰሜን መጥታ እስክትዋጋው ድረስ ተሳክቶለት ነበር። ባኦስ ክፉ ነበርና በቀዳማዊ ኢዮርብዓም የተጀመረው የጣዖት አምልኮ እንዲቀጥል ስላደረገ፥ እግዚአብሔር መንግሥቱን እንደሚወስድበት ተናገረው። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ኤላ (886-885 ዓ.ዓ.) 

የባኦስ ልጅ ኤላ በእስራኤል ላይ የነገሠው ለሁለት ዓመታት ብቻ ሲሆን፥ የእኩሌቶቹ ሰረገሎች አለቃ በሆነው በዘምሪ ተገደለ። በኤላ ሞት የባኦስ ቤተሰብ ነቢዩ ኢዩ በተናገረው መሠረት ተደመሰሰ (1ኛ ነገ. 16፡1-4)። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ዘምሪ (885 ዓ.ዓ.)

ዘምሪ የተባለው ሰው በኃላፊነት ለሰባት ቀናት ብቻ ነገሠና የጦሩ አዛዥ በነበረው በዘንበሪ ተገደለ። 

 1. የእስራኤል ንጉሥ ዘንበሪ (885-874 ዓ.ዓ.)

ስለ ዘንበሪ አገዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የተነገረን ነገር ባይኖርም፥ ከእስራኤል ታላላቅ ነገሥታት አንዱ እንደነበር በዓለም ታሪክ ተጽፎ እንመለከታለን። ሥርወ መንግሥቱም የሰሜኑን መንግሥት ጥንካሬ ሊጨምርና ዝነኛ ሊያደርገው ችሎ ነበር። ዘንበሪ የጦሩ አዛዥ ሆኖ በሚነግሥበት ጊዜ የመጀመሪያው ዐቢይ ትኩረቱ የሰሜኑን መንግሥት ማጠናከር ነበር። ያደረገው የመጀመሪያ ነገር ዋና ከተማውን ወደ ሰማርያ ማዞርና ከጥቃት ለመከላከል በዙሪያዋ ምሽግ መሥራቱ ነበር። የሰማርያ ከተማ እስከ 722 ዓ.ዓ. ድረስ የሰሜኑ መንግሥት ዋና ከተማ ሆና ነበር። በበርካታ የነቢያት መጻሕፍት ውስጥ የሰሜኑ መንግሥት በዋና ከተማው ስም ሰማርያ በመባል ይታወቅ ነበር።

ዘንበሪ ሞአባውያንን ለማሸነፍና በጣም ሀብታም ለመሆን የቻለ ሰው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ከይሁዳ ጋር የተደረገ አንዳችም ጦርነት ያለ አይመስልም። 

ዘንበሪ አገዛዙን ለማስፋፋት ይችል ዘንድ ከፎኔሽያ ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር። ፍኔሺያ በሰሜን ምዕራብ የሚገኝ የጢሮስና የሲዶና ግዛት ነበር። ጢሮስና ሲዶና እጅግ ጠንካራ አገር የነበሩና በሜዴትራኒያን ባሕር አካባቢ ከሚገኙ አገሮች ሁሉ በዓለም አቀፍ ንግዳቸው የታወቁ ነበሩ፤ ደግሞም የበአል አምልኮ ማዕከልም ነበሩ።

ስምምነቱን ሕጋዊ ለማድረግ ዘንበሪ ልጁን አክዓብን ከፎኔሺያ (ሲዶና) ንጉሥ ሴት ልጅ ከኤልዛቤል ጋር አጋባው። ይህ ስምምነት ለሕዝቡ መልካም ሊሆን ቢችልም፥ በመንፈሳዊ አንጻር ግን ለሰሜኑ መንግሥት እጅግ የከፋ ነገር አስከትሏል። የአክዓብ ሚስት የነበረችው ኤልዛቤል የበአልን አምልኮ ወደ እስራኤል ስላመጣች፥ አብዛኛዎቹን የእግዚአብሔር ነቢያት አስገደለች። በዚህ ምክንያት ዘንበሪ «ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩት ይልቅ እጅግ ከፋ» ተብሎ ተጽፏል (1ኛ ነገ. 16፡25)።

 1. የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ (874-853 ዓ.ዓ.)

አክዓብ ጥሩ የፖለቲካ መሪ ነበር። የሰሜኑን መንግሥታት የግዛት ክልል ለማስፋፋት፥ ለመከላከል ምቹ የሆኑ ከተሞችን ለመገንባት፥ ወዘተ. ችሉ ነበር።

አክዓብ ከደቡብ የይሁዳ መንግሥት ጋርም ጥሩ ኅብረት ለመፍጠር ችሎ ነበር። ሴት ልጁን አታሊያህን በእርሱ ዘመን የይሁዳ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮሳፍጥ ልጅ ለኢዮራም ድሮለት ነበር። ይህም የግንኙነታቸው ማሰሪያ ነበር። ይህ በይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ላይ ታላቅ ጥፋት የሚያስከትል ክፉ ተግባር እንደነበረ ኢዮሳፍጥ አላስተዋለም ነበር። ከሞላ ጎደል የዳዊትን ቤት በሙሉ ሊያጠፋ ተቃርቦ ነበር። 

አክዓብ የበአል አምልኮን ስላስፋፋና ይህም እጅግ ክፉ ተግባር ስለነበር «ከእርሱ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ» ተብሉ ስለ እርሱ ተጽፏል (1ኛ ነገ. 16፡30)።

በአክዓብ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ ከሶርያ ጋር ጦርነት የተደረገ ቢሆንም፥ በኤልያስ እርዳታ አክዓብ ጦርነቱን በድል ለመወጣት ችሏል። በኋላም ከይሁዳ ጋር በአንድነት በመተባበር በብሉይ ኪዳን ብዙ ጊዜ አራም ተብሎ ከሚጠራውና በአሁኑ ጊዜ በመስጴጦምያ ዋናው ኃይል ከሆነው ከሶርያ ጋር ተዋግቷል። በዚህም ጦርነት አክዓብ ተገደለ።

የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አክዓብ ከእግዚአብሔር ነቢይ ከኤልያስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው።

የውይይት ጥያቄ፥ ከእነዚህ የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ልትማር የምትችላቸውን አንዳንድ መንፈሳዊ ትምህርቶች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የሰሎሞን ውድቀት (1ኛ ነገሥት 11)

ሰሎሞን በዓለም ዘንድ ምንም ያህል ጥበበኛ ይሁን፥ በእግዚአብሔር ዓይን ጥበበኛ አልነበረም። ሰሎሞን በወጣትነቱ ዘመን «የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው» (ምሳ. 1፡7) ሲል ጽፎ ነበር። ይህንን ሲል እውነተኛ ጥበብ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነና የሚገለጠውም ለእግዚአብሔር ወደመታዘዝ በሚያመራው በፈሪሃ እግዚአብሐርነት ነው ማለት ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ይህንን አልተከተለም። ይልቁንም እግዚአብሔርን ረሳ፤ የእስራኤልን አምልኮ አበላሸ፤ ለእስራኤል መንግሥት መከፈል ዋና ምክንያት ሆነ። 1ኛ ነገሥት 11 የሚያተኩረው በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስለነበረው፥ ሰሎሞን ስላደረገውና በኋላም ዘሩ አድጎ የእስራኤልን ሕዝብ ስላጠፋው ኃጢአት ነው። የእስራኤል ሕዝብ ከሕደት እስኪጠፋና ወደ ምርኮ እስኪሄዱ ድረስ የቀጠለው ሥሩን ከሰሎሞን በማቆጥቆጥ ነው።

ሰሎሞንን ወደ ጥፋት የመሩትን የሚከተሉትን ነገሮች ተመልከት፡-

ሀ. ሰሎሞን ብዙ ሴቶችን አገባ። የአብዛኛው ጋብቻ ዓላማ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር የፖለቲካ ስምምነት ለማድረግ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰሎሞን 700 ሚስቶችና 300 ቁባቶች እንደነበሩት ይናገራል። ሰሎሞን ይህንን ያደረገው ምናልባት ታላቅነቱን ለዓለም ለማሳየት ሊሆን ይችላል፤ ዳሩ ግን በምንም መንገድ ቢሆን የእግዚአብሔርን ሕግ በቀጥታ የጣሰ ነበር። (ዘዳ. 17፡17 ተመልከት)። በጥንት ዘመን ነገሥታት በመካከላቸው የሚያደርጉትን ስምምነት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ለጋብቻ በመለዋወጥ ያጸኑ ነበር። ሰሎሞን በርካታ ሚስቶች ያገባበት ምክንያት ይህ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጥር የለም። 

ለ. አብዛኛዎቹ ሚስቶቹ የተሳሰተ አማልክትንና ጣዖቶችን የሚያመልኩ አሕዛብ ስለነበሩ፥ ሰሎሞን ለሚስቶቹ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሐሰት አምልኮ የሚያካሄዱበትን ስፍራ እንዲኖራቸው ፈቀደላቸው (1ኛ ነገ. 11፡7-8)። ቀጥሎም ከእነርሱ ጋር እነዚህን የሐሰት አማልክት ማምለክ ጀመረ። ሰሎሞን ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖች በሚጠመዱበት ወጥመድ ተያዘ። ሚስቶቻቸውን ወይም ቤተሰቦቻቸውን ለማስደሰት፥ ሰዎች እውነተኛውን አምላክና ሐሰተኛ አማልክትን ወይም የቀድሞ ሃይማኖታቸውን በአንድነት ያመልካሉ። ሰሎሞን ከኢየሩሳሌም ውጭ የገነባቸው የሐሰተኛ አማልክት ማምለኪያ ስፍራዎችን ኢዮስያስ እስኪያስወግዳቸው ድረስ ለ350 ዓመታት ቆዩ (2ኛ ነገ. 23፡13 ተመልከት)።

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ይህ ነገር በአንዳንድ ክርስቲያኖች ሲፈጸም ያየኸው ነው? ለ) ስሕተት የሆነውስ ለምንድን ነው? ሐ) ሰሎሞን ሚስቶቹን ለማስደሰት ብሉ ጣዖትን ከማምለኩ ምን ልንማር እንችላለን?

ሐ. ሰሎሞን የአስተዳደር አሠራሩን በከፍተኛ ደረጃ ወደ ውስብስብ ሁኔታ አደረሰው። የመንግሥት ሠራተኞች እጅግ ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ፥ በሰሎሞን መንግሥት ውስጥ ያሉ የአስተዳደር ሰዎችንና የተለያዩ ሥራዎችን ሕዝቡ ሊደግፍ ከማይችልበት ደረጃ ደረሰ።

መ. ሰሎሞን በአንድ ጊዜ ከመጠን በላይ የሆነ ነገሮችን ለመሥራት ሞከረ። አገሪቱ ቀስ በቀስ እንድታድግ ከማድረግ ይልቅ በርካታ ትላልቅ ከተሞችን በአንድ ጊዜ ሠራ። ይህም ነገር ሕዝቡ የመንግሥት ባሪያ እንዲሆን አደረገው። በምድሪቱ በሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ላይ የኑሮ ጫና ፈጠረባቸው። ሕዝቡ እጅግ የጠሉት ነገር ይህ ነበር። ለዚህ ነው ከሰሎሞን ሞት በኋላ ስለ ግብርና ለመንግሥት በመሥራት ረጅም ጊዜ ስለማጥፋት ያጉረመረሙት።

ሠ. ሰሎሞን ዓለም አቀፍ ንግድንና ግንኙነትን ከፍ ለማድረግ ስለሞከረ፥ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ያደርጉ በነበሩ አሕዛብ መንግሥታት ፍልስፍናና የሃይማኖት ተጽዕኖ ሥር ወደቀ። ይህም እስራኤል ዓለም አቀፍ ስምምንት እንዳያደርጉ እግዚአብሔር ከሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ጋር በቀጥታ የሚፃረር ነበር (ዘጸ. 34፡ 12-15፤ ዘዳ. 7፡2)። በሰሎሞን ዘመነ መንግሥት መጨረሻ አካባቢ መንግሥቱ መውደቅ ጀመረ። እግዚአብሔር ግን ለአባቱ ለዳዊት በነበረው ፍቅር ምከንያት፥ በእርሱ የሕይወት ዘመን መንግሥቱ እንደማትከፈል ቃል ገብቶለት ነበር። እግዚአብሔር ግን በሰሎሞን ላይ ፍርድን አመጣ።

 1. እግዚአብሔር መንግሥቱ ለሁለት እንደምትከፈል ተናገረ። ነቢዩ አኪያ የመንግሥቱን መከፈል የሚመለከት መልእክት ተናገረ። አሥሩ ነገዶች እስራኤል ሲባሉ፥ ሁለቱ የደቡብ ነገዶች የይሁዳ መንግሥት እየተባሉ ይጠራሉ። እግዚአብሔር አሥሩን የእስራኤል ነገዶች ከዳዊት ዘር ላልሆነው ለኢዮርብዓም ሰጣቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ለዳዊት ከነበረው ፍቅር የተነሣ የይሁዳን ሁለት ነገዶች (ይሁዳና ብንያምን) በዳዊት ልጆች አመራር ሥር እንዲቆዩ አደረገ። 
 2. የሰሎሞን መንግሥት በተለያዩ ዓመፆች መፈረካከስ ጀመረ።

ሀ. ከሰሎሞን አስተዳዳሪዎች አንዱ የነበረው ኢዮርብዓም በሰሎሞን ላይ ዓምዖ ወደ ግብፅ ኮበለለ። 

ለ. የኤዶም መንግሥት በሰሎሞን ላይ ዓመፀ። ግብፅ ለኢዮርብዓምና በሃዳድ መጠለያ በመስጠት ይህንን ዓመፅ እንዴት እንዳበረታታችና እንደደገፈች መመልከት የሚገርም ነው። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናችን መጠን እንዴት መምራት እንዳለብን፥ ከሰሎሞን ሕይወት የምንማራቸውን ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) ልንከተላቸው የሚገቡን መልካም ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ሐ) ወደ ሕይወታችን እንዳይገቡ ልንከላከላቸው የሚገባን ነገሮች የትኞቹ ናቸው? 

አብዛኛዎቹን የብሉይ ኪዳን የጥበብ መጻሕፍት እንዲጽፍ እግዚአብሔር ሰሎሞንን ተጠቅሞበታል። እነዚህን በሚቀጥለው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ጥናት እንመለከታቸዋለን። ብዙ ምሁራን ሰሎሞን መጽሐፈ ምሳሌን የጻፈው ወጣት በነበረና ከጌታ ጋር በመልካም አካሄድ በነበረው ጊዜ ነው ይላሉ። መጽሐፈ መክብብን ደግሞ የጻፈው በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ከእግዚአብሔር ርቆ የመኖርን መራራነት ከተለማመደ በኋላ ነው። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ደግሞ ምናልባት ሰሎሞን ከሚስቶቹ መካከል አንዷን እንዴት እንዳገባ የሚገልጥ የግጥምና የፍቅር መጽሐፍ ይሆናል ብለው ያስባሉ። 

የውይይት ጥያቄ፥ 1ኛ ቆሮ. 9፡24-27 አንብብ። ጳውሎስ በሕይወቱ ለራሱ ይፈራው የነበረው ነገር በሰሎሞን ሕይወት ውስጥ የተፈጸመው እንዴት ነው? (ቁ. 27)። ጳውሎስ ከነበረው ታላላቅ ፍርሃቶች አንዱ፥ በዕድሜ በገፉ ጊዜ ለብዙዎች ከሰበከና ብዙዎችን ለክርስቶስ ከማረከ በኋላ እርሱ እንዳይወድቅና ለክርስቶስ የማይጠቅም የተጣለ እንዳይሆን ነበር፤ ስለዚህ ሕይወቱን አጥብቆ ሊቆጣጠር ወሰነ። በክርስትና ሕይወትም ሆነ በቤተ ክርስቲያን አመራር ዋናው ነገር መልካም ጅማሬ ሳይሆን ያማረ ፍጻሜ ነው። ሰሎሞን በመልካም ጀመረ፤ ነገር ግን በከፋ ሁኔታ ጨረሰ። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ሰሎሞን ናቸው። አጀማመራቸው መልካም ነው። ዕድሜያቸው በገፋ ጊዜ ግን ከመንገዳቸው ፈቀቅ ይሉና ለቤተ ክርስቲያን የማይጠቅሙ ብቻ ሳይሆን የሚጎዱዋትም ይሆናሉ። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

የ1ኛ ነገሥት አስተዋጽኦ እና ዓላማዎች

 1. የ1ኛ ነገሥት አስተዋጽኦ
 2. ሰሎሞን (1-11) 
 3. ሮብዓም (12) 
 4. የተከፋፈለው የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥት [13-22] (931-853 ዓ.ዓ.) 

ሀ. ቀዳማዊ ኢዮርብዓም (12፡22-14፡20) 

ለ. ሮብዓም (14፡21-33) 

ሐ. አብያ (15፡1-8) 

መ. አሳ (15፡9-24) 

ሠ. ናዳብ (15፡25-32) 

ረ. በአሳ (15፡33-16፡7) 

ሰ. ኤላ (16፡8-14) 

ሸ. ዘምሪ (16፡15-20)

ቀ. ዘንበሪ (16፡21-28) 

በ. አክዓብ (16፡29-34) 

 1. ኤልያስና ነገሥታት

ሀ. ኤልያስና አክዓብ (17፡1-22፡40) 

ለ. ኢዮሣፍጥ (22፡41-50)

ሐ. አካዝያስ (22፡51-53) 

 1. የ1ኛ ነገሥት ዓላማዎች 
 2. በሰሎሞን ጊዜና ከተከፋፈለ በኋላ ማለት ከ931-853 ዓ.ዓ. የነበረውን የእስራኤልን መንግሥት ታሪክ ባጭሩ ለመናገር ጸሐፊው በነገሥታት ጊዜ የነበረውን አጠቃላይና የተሟላ ታሪክ ለመናገር አይፈልግም። በእያንዳንዱ ንጉሥ ዘመን የተፈጸመውን ነገር የሚናገሩ ዝርዝር መዛግብት በቤተ መንግሥቱ ጽሑፎች ውስጥ ይገኙ ነበር፤ ስለዚህ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ፥ እያንዳንዱ ንጉሥ በነገሠበት ዘመን ስለተፈጸመው ነገር እጅግ አጠር ያለ ማጠቃለያ በመስጠት፥ በተለይም ንጉሡ እንደ ዳዊት እንደነበረ ወይም እንዳልነበረ በሚያሳይ መልኩ ብቻ ባሕርዩን ለመዳሰስ ሞክሯል።

የነገሥታቱን ታሪክ በሚናገርበት ጊዜ፥ ጸሐፊው የሚከተለውን መሠረታዊ አወቃቀር ተከትሏል፡-

ሀ. የንጉሡ ማንነት ይነገርና የአባቱ ስም ይጠቀስ ነበር። 

ለ. ንጉሡ ወደዚህ ሥልጣን የመጣበት ዕድሜ ተጠቅሷል። ከይሁዳ ክፍለ መንግሥት ከሆነ ብዙ ጊዜ የንጉሡ እናት ስም ተጠቅሷል። 

ሐ. በንጉሡ ዘመን የተፈጸሙ ዐበይት ክስተቶች ተጠቅሰዋል።

መ. ጸሐፊው የንጉሡን የሥነ-ምግባር ባሕርይና በሕዝቡ ላይ የነበረውን መንፈሳዊ አመራርም ባጭሩ ይገመግማል። ንጉሡ ከይሁዳ ከሆነ ሕይወቱን ከዳዊት ጋር ማወዳደር፥ ከእስራኤል ከሆነ ደግሞ ከቀዳማዊ ኢዮርብዓም ጋር ማወዳደር የተለመደ

ነው።

 1. እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ለምን እንደፈረደ ለማሳየት። ጸሐፊው የ1ኛ ነገሥትን መጽሐፍ በሚጽፍበት ጊዜ፥ ሙሴ በዘዳ. 27-28 የሰጣቸው ተስፋዎች በአእምሮው ነበሩ። ጸሐፊው እስራኤል ለእግዚአብሔር በመታዘዝ በኖረችበት ጊዜ፥ እርሱ የሰጠውን የተስፋ ቃል በሙሉ እንዴት እንደፈጸመ ይናገራል፤ ነገር ግን እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ላይ በሚያምፁበት ጊዜና ግዴታቸውን ሳይወጡ ሲቀሩ፥ በተስፋ ቃሉ የሰጠውን ፍርድ ያመጣባቸው ነበር። 

የውይይት ጥያቄ፥ ዘዳ. 27-28 አንብብ። ሀ) ለቃል ኪዳኑ ባለመታዘዝ ስለሚመጡ ፍርዶች (መርገሞች) የተነገረውን ነገር ዘርዝር። ለ) ለቃል ኪዳኑ በመታዘዝ ስለሚገኙ በረከቶች የተሰጠውንም ነገር ዘርዝር።

 1. እግዚአብሔር ነቢያትን የእርሱ አፈቀላጤ አድርጎ ወደ ነገሥታቱ እንዴት ይልካቸው እንደ ነበር ለማሳየት። እግዚአብሔር ሕዝቡን ተግባራቸው ምን ውጤት እንዳለው ሳይገነዘቡ፣ ኮብልለው እንዲሄዱ አይፈልግም ነበር። በመሆኑም እግዚአብሔር ነቢያትን እያስነሣ ድርጊታቸውን እንዴት እንደሚመለከትና እንደሚፈርድባቸው ሕዝቡን ሁሉ በተለይም ነገሥታትን እንዲያስጠነቅቁአቸው ያደርግ ነበር። እነዚህ ነቢያት እግዚአብሔር በመለኮታዊ መንገዱ የመረጣቸውና ሕዝቡን የሥነ-ምግባር እውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ነበሩ። 

የውይይት ጥያቄ፥ ሀ) ዛሬም ክርስቲያኖች ለኅብረተሰባቸው የሥነ-ምግባር እውቀት (ብርሃን) መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? ለ) ለኅብረተሰባቸው የእግዚአብሔር አፈቀላጤ የሚሆኑትስ እንዴት ነው? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ይህንን ሚና እየተጫወተች ያለችው እንዴት ነው? ግልጥ የሆኑ መግለጫዎችን ስጥ።

 1. ዓመፀኞች፥ የማይታዘዙና ጣዖት አምላኪዎች የሆኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሪዎችና ነገሥታት እንዴት በሕዝቡ ሁሉ ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዳመጡ ለማሳየት ነው። ብዙ ጊዜ በኃጢአት የሚወድቁት ሕዝቡ አይደሉም። የአንድ ሕዝብ መሪ የሆነው ንጉሡ በኃጢአት በሚወድቅበት ጊዜ፥ በራሱ ተጽዕኖ ሕዝቡንም ወደ ኃጢአት ይመራቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ንጉሡ ጻድቅ ከሆነና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ከኖረ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን በሚገባ እንዲያመልኩና ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እንዲኖሩ ሊያደርግ ይችላል። 

የውይይት ጥያቄ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በቤተ ክርስቲያናቸው አባላት መንፈሳዊና ሥነ-ምግባራዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ስለመቻላቸው ከዚህ ምን ለመማር እንችላለን? 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)