የሕይወት እንጀራ

2ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች

ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ ትጉሕ ሠራተኞች ሆነው ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 3:1-18)

ጳውሎስ ይህን አጭር የሁለተኛ ተሰሎንቄ መልእክት የሚያጠቃልለው የተሰሎንቄ አማኞች አንዳንድ ነገሮችን እንዲፈጽሙ በመጠየቅ ነው። እነዚህም ነገሮች ክርስቲያኖች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ ስሙን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ የሚያግዙአቸው ናቸው። 1) አማኞች ጳውሎስ ወንጌልን በስፋት እንዲያሰራጭ በጸሎት ሊደግፉት ይገባ ነበር። ክፉ ሰዎች በተለይም የሐሰት አስተማሪዎች የወንጌሉን ዘር እንዳያጠፉ መጸለይ ይገባቸው ነበር። ጳውሎስ እግዚአብሔር የተሰሎንቄን አማኞች ከእነዚህ ክፉ ሰዎችና ከሐሰተኛ ትምህርታቸው እንደሚጠብቃቸው እርግጠኛ መሆኑን ይናገራል። እኛም በአገራችንና በዓለም ሁሉ ወንጌሉ በስፋት እንዲሰራጭ በዋናነት ልንጸልይ ይገባል። 2) ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሥራ በመፍታታቸው በጽኑ እያስጠነቀቀ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ያሳስባቸዋል። የተሰሎንቄ አማኞች የእርሱን ምሳሌነት በመከተል ተግተው እንዲሠሩ ይመክራቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ሊሠሩ በማይፈቅዱት ሰዎች ላይ ቅጣት እንድትጥልና ማንኛውም አማኝ ከእነርሱ ጋር ኅብረት እንዳያደርግ አዟል። ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ በትክክል ስለማናውቅ ተግተን እየሠራን፥ ስለ ወደፊቱ እያቀድን፥ ልጆቻችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እያሳደግን፥ ወዘተ… ጤናማ ሕይወት መኖራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲሁም እግዚአብሔርን የሚያስከብር የተቀደሰ ሕይወት መኖር ይገባናል። በዚህ ዓይነት የምንመላለስ ከሆነ ክርስቶስ ዛሬ፥ ነገ፥ ከአምስት ዓመታት በኋላ ወይም ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላ ቢመለስ፥ እርሱን በሚያስከብር መንገድ ባለመኖራችን ለኃፍረት አንጋለጥም። ጳውሎስ ከስደትና የሐሰት ትምህርት ጫና ባሻገር ልባቸውን የሚሞላ የእግዚአብሔር ሰላም እንዲኖራቸው በመመኘት ይህንን መልእክት ያጠናቅቃል። ከዚያም በመልእክቱ ላይ የእርሱ መሆኑን የሚያረጋግጥ ስሙን ይጽፋል። የውይይት ጥያቄ፡- ከ2ኛ ተሰሎንቄ መጽሐፍ ጠቃሚ ትምህርቶችን ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ አማኞች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ ትጉሕ ሠራተኞች ሆነው ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 3:1-18) Read More »

ጳውሎስ ክርስቶስ የዐመፁ ሰው ሳይገለጽ እንደማይመለስና አማኞች በታማኝነት ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 2:1-17)

እንደዛሬው ዘመን ሁሉ በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን ከፍተኛ ግራ የመጋባት ሁኔታ ነበር። ጳውሎስ የሁለተኛ ተሰሎንቄን መልእክት የጻፈበት ዋናው ምክንያት ይህንኑ ግራ መጋባት ለማስተካከል ነበር። በተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን እርስ በርሳቸው የሚጋጩና በአማኞች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የሚያስከትሉ ሁለት ዓይነት ትምህርቶች የነበሩ ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ በቶሎ ይመጣል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ነበሩ። ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች ሥራ አቁመው ነበር። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጣም እንደ ረፈደባቸው ያስተምሩ ነበር። ክርስቶስ ድሮውኑ ዳግም ተመልሶ እንደመጣና እነርሱ ግን ሊያገኙት እንዳልቻሉ ይናገሩ ነበር። እንዲያውም ከጳውሎስ እንደተጻፈ ተደርጎ የቀረበ ክርስቶስ አስቀድሞ መምጣቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸው ነበር። እነዚህን ሁሉ ውዝግቦች ለማርገብ ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ዘመን ጠቃሚ ትምህርቶችን ይሰጣል። ጳውሎስ ይህንኑ ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ በመጨረሻው ዘመን በሚከሰቱት መልእክቶች ላይ ያተኩራል። በዚህም ክርስቶስ ከዚህ በፊት ዳግም እንዳልተመለሰ ያብራራል። ከእነዚህም ምልክቶች እንዳንዶቹ ምን ምን ነበሩ? ሀ) ጳውሎስ በመጨረሻው ዘመን ዐመፅ እንደሚበዛ ያስረዳል። እንደውም ጳውሎስ ይህንኑ ዘመን ዐመፅ ይለዋል። ይህም በዓለም ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ ከፍተኛ ዐመፅ የሚቀሰቀስበት ዘመን መሆኑን ለማስረዳት ነው። ለ) ይህ የዐመፅ ጊዜ፥ የዐመፅ ሰው ወይም የጥፋት ሰው ተብሎ በሚታወቀው ግለሰብ ይመራል። ይህ ሰው ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት መገለጥ ይኖርበታል። ጳውሎስ የዚህን ሰው ክፉ ባሕርያት በሦስት መንገዶች ያብራራል። በመጀመሪያ፥ በሥርዓት የለሽነት የተሞላ መሆኑን ያስረዳል። ይህ የዐመፅ ሰው የእግዚአብሔርን ሕግጋት ለማፈራረስ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ቀድሞውኑ ፍጻሜውን ወስኗል። ይህ ሰው ለአጭር ጊዜ በዓለም ሁሉ ላይ ሥልጣን ሊኖረው ቢችልም፥ እግዚአብሔር ግን በመጨረሻው ያሸንፈውና ወደ ሲኦል ይሰድደዋል (ራእ. 19፡19-20 አንብብ)። ሦስተኛ፥ ይህ ዐመፀኛ ራሱን እንደ አምላክ በመቁጠር ሰዎች እንዲያመልኩት ያስገድዳቸዋል። እግዚአብሔርንም እንዲቃወሙት ያነሣሣቸዋል። ምሁራን ይህ የዐመፅ ሰው ማን ይሆን በሚለው ጉዳይ ላይ እርስ በርሳቸው ይከራከራሉ። አንዳንዶች ጳውሎስ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት የሚታየውን የመጨረሻው ዘመን አስከፊ ሁኔታ በተምሳሌት እየተናገረ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ጳውሎስ እንደ ኔሮ ወይም ዶሚቲያን ስላሉት ክፉ የሮም መሪዎች እየተናገረ ነው ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በቤተ ክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ያስከትሉ ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ ሐሳዊ መሢሕ የሚናገር ይመስላል። ይህም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ አውሬው የተባለው የመጨረሻ ው የዓለም ገዢ ነው (ራእ. 13)። ጳውሎስ የዐመፀኝነት ምሥጢራዊ ኃይል ሁልጊዜም ይሠራ እንደነበር ይናገራል። ከእግዚአብሔር ጋር በመጣላት ሕዝቡን የሚያሳድዱ መሪዎች ሁልጊዜም ሲታዩ ኖረዋል። በመጨረሻው ዘመን ግን ልዩ የዐመፅ የታላቅ ክፋትና የስደት ጊዜ ይመጣል። ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ ሳናውቀው መጥቶ ተመልሷል ብለው እንዳይሠጉ ያሳስባቸዋል። ምክንያቱም ይህ ታላቅ የክፋት ጊዜ ገና አልደረሰምና። የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ መቼ እንደሚመጣ ወይም ደግሞ ቀድሞውኑ መጥቶ እንደሆነ እንዴት ልናውቅ እንችላለን ሲሉ ጳውሎስን ጠይቀውታል። ጳውሎስ በዓለም ሁሉ ላይ የሚገዛው ክፉ መሪ አለመገለጹ ክርስቶስ ዳግም እንደ ተመለሰ የሚያውቁበት አንደኛው መንገድ እንደሆነ ያስረዳል። ሐ) ዐመፃን የሚከለክለው ገና አልተወሰደም። ነገር ግን ይህ ዐመፅን የሚከለክለው ማን ነው? አንዳንድ ምሁራን ይህ ዐመፅን የሚከለክለው እግዚአብሔር የሚቆጣጠረው የሰዎች መንግሥት እንደሆነ ያስባሉ። የሮም መንግሥት በጳውሎስ ዘመን የክፋትን ስርጭት ይቆጣጠር ነበር። የእኛም መንግሥታት በዘመናችን ውስጥ ያሉትን የክፋት ሥራዎች ይቆጣጠራሉ። በመጨረሻው ዘመን ግን ይህ የዐመፅ ሰው መንግሥታትን ሁሉ ስለሚቆጣጠር ማንም ክፋትን የመፈጸም ዓለም አቀፋዊ ኃይሉን ሊቀንስበት እይችልም። ይሁንና ጳውሎስ የሚናገረው ስለ መንፈስ ቅዱስ ይመስላል። እግዚአብሔር ለመንፈስ ቅዱስ በዓለም ውስጥ የሚሰራጨውን የክፋት ኃይል ለመቀነስ እገልግሎት የሰጠው ይመስላል። ስለሆነም ሐሳዊ መሢሕ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ከዚህ ዓለም ይወሰዳል። ሌሎች ደግሞ ይህንኑ ሁኔታ ከአማኞች መነጠቅ ጋር በማዛመድ ዛሬ በአማኞች ልብ ውስጥ ያለው መንፈስ ቅዱስ ከእነርሱ ጋር እንደሚወሰድ ይናገራሉ። በዚያ የዐመፃ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው ልክ በብሉይ ኪዳን ዘመን ይሠራ እንደነበረው ይሆናል። ሁሉንም የእግዚአብሔር ልጆች ከመሙላት ይልቅ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ብቻ ይመጣል። መ) ክርስቶስ በአፉ እስትንፋስ ሐሳዊ መሢሕን በማሸነፍ ኃይሉን ያስወግዳል። (ክርስቶስ ይህን የሚያደርገው በቃሉ ትእዛዝ ይሆናል)። ክርስቶስ ይህን የመጨረሻውን ክፉ የዓለም መሪ በመገለጡ ኃይል በቀላሉ ያሸንፈዋል። ሠ) ሐሣዊው መሢሕ የሰይጣንን ኃይል በመላበስ ሁሉንም ዓይነት ተአምራት ይፈጽማል። በዚህም አምላክ መሆኑንና ሰዎች ሊያመልኩት እንደሚገባ ያሳምናቸዋል። ረ) በመጨረሻው ዘመን ወንጌሉን ሊሰሙ ያልፈቀዱ ሰዎች የሐሳዊው መሢሕን ውሸት ያምናሉ። በመሆኑም ከሐሳዊው መሢሕ ጋር አብረው ይጠፋሉ። በዚህ የዓመፅ ዘመን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ይኖሩ ይሆን? ክርስቲያኖች ይህንን የክፋት ዘመን እንደሚጋፈጡና ለክርስቶስ በታማኝነት ጸንተው ሊያልፉ እንደሚገባ የሚናገሩ አያሌ ምሁራን አሉ። ነገር ግን መጀመሪያ ቤተ ክርስቲያን እንደምትነጠቅና በአፋቸው ክርስቲያኖች ነን የሚሉት ብቻ ከዐመፅ ሰው ጋር እንደሚጋፈጡ ያስተምራሉ። እነዚህ የአፍ ክርስቲያኖች ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ሳይነጠቁ የቀሩ ናቸው። ትክክለኛው አመለካከት እንግዲህ የትኛው ነው? ይህን ሁኔታ መወሰኑ አስቸጋሪ ነው። ምንም እንኳን በራእይ 6-19 እንደተገለጸው ይህንን በዚህ የዐመፅ ጊዜ ውስጥ ባንገባ ደስ ቢለንም፥ መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳዩን በግልጽ አያብራራም። ስለሆነም አማኞች በዚህ የመከራ ጊዜ ውስጥ ሊያልፉ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ተስፋችንና ትኩረታችን በዚህ የክፋት ዘመን ውስጥ አለመግባት ሳይሆን፥ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ መጽናት ሊሆን ይገባል። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ከመከራ በፊት ቢወስደን ወይም ደግሞ በዚህ የክፋት ዘመን ውስጥ ሲያሳልፈን፥ ክርስቶስን በማስከበር በዘላለሙ መንግሥት በእርሱ እንሸለማለን። ጳውሎስ ይህንን ክፍል የሚያጠናቅቀው የተሰሎንቄ አማኛች የክርስቶስን ምጽአት በሚጠባበቁበት ጊዜ እንዴት ሊመላለሱ እንደሚገባ በመምከር ነው። እግዚአብሔር እንደመረጣቸውና ሊቀድሳቸው በውስጣቸው እየሠራ መሆኑን በመገንዘብ ልበ ሙሉነት ሊሰማቸው ይገባ ነበር። እንዲሁም ከጳውሎስ የሰሙትን የወንጌል እውነት ጠብቀው በታማኝነት ሊኖሩ እንደሚገባ ያስረዳል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ስለ መጨረሻው ዘመን የሚናገረው ትምህርት ክርስቶስ በዚህ ቀን ይመጣል ለሚሉ ሰዎች መልስ እንድንሰጥ የሚረዳን እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ የሚመጣበት ቀን ከመገመት ይልቅ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ እንዳናፍር በሕይወታችን ምን ልናደርግ ይገባል? (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ ክርስቶስ የዐመፁ ሰው ሳይገለጽ እንደማይመለስና አማኞች በታማኝነት ሊመላለሱ እንደሚገባ ያስተምራል (2ኛ ተሰ. 2:1-17) Read More »

ጳውሎስ የኋላ ኋላ አሳዳጆቻቸው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ለፍርድ እንደሚጋለጡ በማሳሰብ በስደት ላይ ያሉትን አማኞች ያበረታታቸዋል (2ኛ ተሰ. 1:1-12 )

እንግዳ ወርቅ ተወልዶ ያደገው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። ቤተሰቦቹ ትምህርት ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘባቸው ብዙ ጥረት አድርገው ትምህርት ቤት አስገቡት። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ መፈለግ ጀመረ። ያገኘው ሥራ ግን አነስተኛና ዝቅተኛ ክፍያ የሚከፈልበት ነበር። እርሱ ግን ይህ ለክብሬ የሚመጥን ሥራ አይደለም ብሎ በማሰቡ ቀኑን ሙሉ ሲንቀዋለል ቆሞ ይውል ጀመር። የግብርና ሥራ ለማከናወንም የትምህርት ደረጃው እንደማይፈቅለት አሰበ። ወላጆቹን ለመጎብኘት ወደ እገር ቤት በተመለሰ ጊዜ በእርሻ ፥ በአረምና በእንጨት ፈለጣ ዘመዶቹን ለመርዳት አልፈለገም። ነገር ግን ወላጆቹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲያሟሉለት ጠበቀ። ቀኑን ሙሉ ከጓደኞቹ ጋር ሲነጋገርና ከቤት ወደ ቤት እየዞረ ቡና ሲጠጣ ይውላል። እንግዳ ወርቅ ምንም ሥራ ስላልነበረው ብዙ ትርፍ ሰዓታት ነበሩት። በዚህም ጊዜ ውስጥ መጥፎ ልማዶችን ያስተናግድ ጀመር። ሥራ ከመፈለግ ይልቅ በሱቆች አካባቢ መዋልን መረጠ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጓደኞቹ ጫት መቃም አስለመዱት። ብዙም ሳይቆይ ወደ መጠጥ ቤቶችና ሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ጎራ ማለት ጀመረ። በመጨረሻም በኤድስ በሽታ ተይዞ ሞተ። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ. እንግዳ ወርቅ ለአነስተኛ ሥራዎች የነበረው አመለካከት ምን ዓይነት ነበር? ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ይመስልሃል? ለ) ሥራ በፈታ ጊዜ ምን ዓይነት አሳቦች ወደ አእምሮው መጡ? ሐ) ሥራ መፍታቱ ምን ዓይነት ውጤት አስከተለ? ሐዋርያው ጳውሎስ ማንኛውም ሥራ ክቡር መሆኑን አስተምሯል። አንዳንድ ሥራ ለተማሩት ሰዎች የማይገባና ትናንሽ ሥራዎችን ከመሥራት ይልቅ ዝም ብሎ መቀመጡ ተገቢ እንደሆነ የሚያስተምረው ዲያብሎስ ነው። አንዳንድ የተሰሎንቄ አማኞች ሥራ አቁመው የክርስቶስን መምጣት በሚጠባበቁበት ጊዜ ጳውሎስ እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲሠራ አዟል። ጳውሎስ ታላቅ ሐዋርያ የሆነው ራሱ ሳይቀር የሌሎች ሸክም እንዳይሆን ቀንና ሌት ይሠራ እንደነበር ገልጾአል (2ኛ ተሰ. 3፡8)። ጳውሎስ ለዚህ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት በመስጠቱ አንድ ሰው ለመሥራት ካልፈለገ መብላት እንደሌለበት አስረድቷል። ጳውሎስ በተጨማሪም እነዚህ ሊሠሩ የማይፈልጉ ክርስቲያኖች እንደ ዓለማውያን የሚቆጠሩ መሆናቸውን ገልጾአል። ሌሎች አማኞች ከእነዚህ ሥራ ከማይወዱ ሰዎች ጋር ኅብረት መፍጠር አያስፈልጋቸውም ነበር (2ኛ ተሰ. 3፡9-15)። ብዙም ለተማሩት ሰዎች የሚስማማ ሥራ በማይበዛበት በዚህ ዘመን ክርስቲያን ወጣቶች መሥራትን አቁመው በወላጆቻቸው ላይ ሊደገፉ ይችላሉ። ይህ ግን ለወንጌሉ እንቅፋት ነው። አነስተኛ ሥራዎችን መፈለግ ወይም ወደ ግብርና ተመልሶ ማረሱ በጣም ጠቃሚ ነው። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሥራቸውን በማክበር በጊዜው ሊያነሣቸውና የተሻለ ሥራ ሊሰጣቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ለክርስቲያኖች ስደትን በደስታ ተቀብሎ ማስተናገዱ ቀላል አይደለም። በመሆኑም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ ከሆነ እነዚህ ክፉ ሰዎች እንዲያሳድዱን የሚፈቅደው ለምንድን ነው ብለን እንጠይቃለን። ወይም እግዚአብሔር አፍቃሪ አምላክ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ስደት እንዲደርስብን ለምን ይፈቅዳል? ለብዙ ክርስቲያኖች በተለይም ብዙ ስደት ላልደረሰባቸው የክርስቲያኖች ልጆች እግዚአብሔር ካአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ይጠብቀናል ብሎ ማመኑ ቀላል ነው። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዲህ ዓይነት የተስፋ ቃል አልተገባልንም። ይልቁንም በሁሉም የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ማለት ይቻላል፥ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ስደትንና መከራን እንደምንቀበል ተገልጾአል። ስለሆነም አስፈላጊው ነገር ከስደት ለመሸሽ መሞከሩ ሳይሆን በስደት ውስጥ ተገቢውን ባሕርይ መጎናጸፋችን ነው። የተሰሎንቄ አማኞች ገና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሳይጠነክሩ ለስደት ተጋልጠው ነበር። በክርስቶስ ካመኑበት ጊዜ ጀምሮ በአይሁዶች ወይም በአሕዛብ ሲሰደዱ ቆይተዋል። ጳውሎስ በስደቱ የደረሰባቸውን ተስፋ መቁረጥ ስለ ሰማ ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ ስደትን የሚመለከት ትምህርት ያቀርብላቸዋል። ጳውሎስ አማኞቹን ለእድገታቸው ያበረታታቸዋል። በእምነት፥ እርስ በርሳቸው ላላቸው ፍቅርና በስደት ውስጥ እምነታቸውን ይዘው ለማቆየት በመቻላቸው ያመሰግናቸዋል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በአመዛኙ ሁሉም ነገር መጥፎ ይሆናል ብለን እናስባለን። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር የመከራ ጊዜያትን በመጠቀም እንዴት መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንዳሳደገው እንድናስታውስ ይፈልጋል። ጳውሎስ በመከራ ውስጥ ያሉት ክርስቲያኖች ወደፊት እንዲመለከቱና የመጨረሻውን ዘመን እንዲያስታውሱ በማድረግ ያበረታታቸዋል። ለአማኞች በስደት መጽናቱ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በሚገቡበት ጊዜ ልማትና ክብርን ያስገኝላቸዋል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ መከራን ለተቀበሉት እማኞች እፎይታን ያጎናጽፋቸዋል። ራእይ 21፡4 እንደሚያስረዳው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ እንባዎች አይኖሩም። መከራም ሆነ ሞት በዚያ ስፍራ የላቸውም። ይህንኑ መጪ የእግዚአብሔር መንግሥት ካስታወስን አሁን የምንጋፈጠውን ጊዜያዊ ፈተና ልንታገሥ እንችላለን (2ኛ ቆሮ. 4፡16–18 አንብብ)። – በአንጻሩ በመጨረሻው ዘመን የሚያምኑ ሰዎችና ስደትን ለማምጣት ሰይጣን በመሣሪያነት የተጠቀመባቸው ሰዎች ለከፍተኛ ቅጣት ይጋለጣሉ። እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ ለሰዎች የሥራቸውን ይከፍላቸዋል። አማኞች የዘላለምን ሕይወት ሲያገኙ የማያምኑ ሰዎች ግን የዘላለም ጥፋት ይጠብቃቸዋል። እግዚአብሔር ካለበት ስፍራና ከግርማው ኃይል ይርቃሉ። ሲኦል የቅጣት ሥቃይ የሚታይባት ብቻ አይደለም። ይህ ሰዎች ለዘላለም ከእግዚአብሔርና ከእግዚአብሔር በረከቶች የሚለይበት ነው። በምድር ላይ የማያምኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር በረከቶች አንዳንዶችን ያገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ጤና፥ ምግብ፥ ዝናብና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል። በሲኦል ግን ከእነዚህ በረከቶች አንዳቸውንም ሊያገኙ አይችሉም። ጳውሎስ አማኞች ለእግዚአብሔር ጥሪ እንደሚገባ ይኖሩ ዘንድ የሚጸልይላቸው መሆኑን ይናገራል። እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ ስደትንም ጨምሮ በኃይል እንዲሠራና ለእነርሱ የወጠናቸውን ዕቅዶች ሁሉ የሚፈጽሙበትን ኃይል እንዲሰጣቸው ይጸልያል። የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሕይወትህ የደረሱብህን አንዳንድ መከራዎች ዘርዝር። በእነዚያ አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ሳይቀር እግዚአብሔር ታማኝነቱን የገለጸልህ እንዴት ነው? በሕይወትህ ውስጥ ምን ለውጦች ተከሰቱ? ችግሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ እነዚህኑ በረከቶችና እድገት ማስታወሱ ለምን ይጠቅማል? ለ) ለክርስቲያኖች ከምድራዊ ሥቃይና ስደት ይልቅ በሰማያዊ የዘላለም በረከቶች ላይ አጽንኦት መስጠቱ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? የወደፊት በረከቶችን በምንዘነጋበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ከአሁኑ ቀላል ሕይወት ይልቅ ዓይኖቻችንን በዘላለማዊ መንግሥት ላይ በምንተክልበት ጊዜ ምን ይከሰታል? ሐ) ጳውሎስ ለጥሪያችን እንደሚገባ እንድንኖር ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ለመጠራታችን እንደሚገባ የምንኖርባቸውን መንገዶች ዘርዝር። (ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

ጳውሎስ የኋላ ኋላ አሳዳጆቻቸው ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ለፍርድ እንደሚጋለጡ በማሳሰብ በስደት ላይ ያሉትን አማኞች ያበረታታቸዋል (2ኛ ተሰ. 1:1-12 ) Read More »